Translate

Monday, January 14, 2013

በደሴ የዳቦ ግራም የቀነሱ ሶስት ዓመት ተፈረደባቸው


“በተደጋጋሚ ከመቀሌ ኮንትሮባንድ ጭነው የሚያዙ ነጻ ይወጣሉ” የደሴ አመራር

corruption vs reform
በደሴ ከተማ ግብር ከፋዩ ነጋዴና ግብር ሰብሳቢው ክፍል አልተስማሙም። የከተማዋ ሹመኞች፣ ነጋዴዎች፣ በአነስተኛና ጥቃቅን ንግድ የታቀፉና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከንቲባውን ሲወቅሱ ተሰማ። በፓርላማ የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ርምጃ እንደሚወሰድ ጠቁሟል። በግምገማው ማብቂያ ከንቲባው ለፓርላማ አባላቱ ቢሯቸው ክፍት አድርገው እሳቸው ግን አልነበሩም። የጎልጉል ምንጮች እንደሚሉት ግምገማውን ተከትሎ የሚወሰድ ርምጃ ይኖራል። የዳቦ ግራም ቀንሰው የተገኙ ሶስት ዓመት ተፈርዶባቸዋል።
የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት አየር ላይ ያዋለው ዜና በደሴ ከተማ ግምገማና የመስክ ምልከታ የተደረገበትን ዋና ምክንያት አልጠቆመም። በዘገባው እንደተጠቆመው የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባካሄደው የመስክ ምልከታ የከተማዋን ከንቲባ የሚያጋልጥ አቤቱታ ቀርቦላቸዋል።
ከደሴ ምክር ቤት አባል አንዱ የሆኑት ሲናገሩ “ከመቀሌ ስኳር በኮንትሮባንድ ጭነው የተያዙ አሉ፤ በነጻ ተለቀቁ” በማለት የፍርድ ሂደቱ ሚዛን የተለያየ መሆኑን አመልክተዋል። ሲያብራሩም “የዳቦ ግራም ቀንሰው በተያዙ ላይ ብቻ ሶስት ዓመት ተፈርዷል” ማለታቸውን ኢቲቪ ባልተለመደ ሁኔታ ይፋ አድርጓል።
ከኮንትሮባንድ ጋር በተያያዘ የህወሃት የቀድሞ ታጋዮችና ለመከላከያ ቅርበት ያላቸው የትግራይ ሰዎች በስፋት የሚሳተፉበት የህገወጥ የንግድ ስራ መሆኑ በስፋት አቤቱታ የሚቀርብበት ችግር ነው። ግብር እና ቀረጥ የሚከፍሉ ነጋዴዎች በኮንትሮባንድ ከሚያስገቡ ህገወጦች ጋር መወዳደር ያልቻሉበት ደረጃ ላይ መድረሳቸውን ጠቅሰው ለሟቹ ጠ/ሚኒስትር በገሃድ መናገራቸው አይዘነጋም።
እስከመተማ እህል በትራክተር በማጓጓዝ በሱዳን በኩል ወደ ኤርትራ ጤፍና የቅባት አህል በኮንትሮባንድ የሚያስተላልፉት “ሻዕቢያ ጠላታችን ነው፤ ሻዕቢያ ህገወጥ ንግድ እያካሄደብን ነው” በማለት ጥይት እስከመተኮስ የደረሱት የህወሃት ሰዎች እንደነበሩም በተደጋጋሚ የተገለጸ ጉዳይ ነው።
ኢቲቪ ቀንጭቦ ያሰማን የደሴ አስተዳደሮች  ያቀረቡት የፍርድ ሂደት  መዛባት ጥያቄ ተከትሎ አስተያየት የሰጡ እንዳሉት “ህግና የህግ የበላይነት ለአንድ አገር ህዝብ መሰረታዊ ዋስትና ነው። ሁሉም ብሔሮች እኩል ናቸው በማለት የሚወተውተው ኢህአዴግ በተቀመጠበት የፍትህ ወንበር ላይ በብሄር እየተለየ እንደሚፈረድ በተደጋጋሚ ይሰማል።እንዲህ ያለው አካሄድ በየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል መፈጸሙ ከህጋዊው አሰራር ይልቅ ህገወጡ አካሄድ እየጠነከረ መሄዱን የሚያሳይ መስታዋት ነው”፡፡
ከንግድ ጋር በተያያዘ አለመተማመን መፈጠሩን አስመልክቶ በተደረገ ውይይት የደሴ ንግድ ዘርፍ ፕሬዚዳንት አቶ አረፋይኔ በላይ “በደሴ ከተማ  የነጋዴውን ህብረተሰብ የሚያስተዳደር ስራ አስፈጻሚ የለም። ስለ አዲስ ሪፎርም በተባራሪ ከምንሰማው በስተቀር የተማርነው ነገር የለም ” ሲሉ ተደምጠዋል።
በደሴ ለግብር ክፍያ ተመን መነሻ ከሚሆነው የነጋዴዎች የዕለት ገቢ መዝገብ ዘጠና አምስት ከመቶ ተቀባይነት ሳያገኝ ውድቅ ተደርጓል። ነጋዴዎች የተጭበረበረ የሂሳብ መዝገብ ስለማቅረባቸው ዜናው በዝርዝር ባያስረዳም የቋሚ ኮሚቴው መሪ “ዘጠና አምስት ከመቶ የዕለት ገቢ መዝገብ ውድቅ ሆነ ማለት ምን ማለት ነው? መተማመን አልተቻለም” በማለት የችግሩን ግዝፈት ሲናገሩ በምስል አስደግፎ ኢቲቪ አቅርቧል።
ሶስት ዓይነት የሂሳብ መዝገብ እንዳለ የጠቆሙት የኮሚቴው መሪ፣ ትክክለኛ መዝገብ፣ ኪሳራንና ትርፍን የሚያመዛዝኑበት መዝገብ፣ ግብር ለመክፈል ከጥገኛ የሂሳብ ባለሙያ ጋር በመመሳጠር ባላንሱን ዜሮ አድርጎ የሚያቀርቡት መኖራቸውን አመልክተዋል። በስተመጨረሻም የማስተካከያ ስራ እንደሚሰራ አመልክተዋል።
በደሴ ከተማ የተካሄደው የመስክ ምልከታ ላይ ተደራጅተው በንግድ ስራ የተሰማሩ “የመዋቅር” ሰዎች ከንቲባውን ኮንነዋል። በቀረቡት አቤቱታዎችና ችግሮች ዙሪያ ለመነጋገር የከንቲባው ቢሮ የሄዱት የፓርላማ የንግድ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ያገኙት ባዶ ቢሮ ነበር። ከንቲባው ለምን ቢሯቸው መገኘትና መወያየት እንዳልፈለጉ የተገለጸ ነገር ባይኖርም፣ ከንቲባ ጀማል ካሳውና እሳቸው የሚመሩት ካቢኔ ከመኮርኮም እንደማያመልጡ ተገምቷል። የኢህአዴግ ባህልና አሰራር እንደሚያመለክተው መኮርኮም ሲፈልግ አስቀድሞ የሚዲያ ሥራ ይሰራል።

No comments:

Post a Comment