Translate

Tuesday, January 8, 2013

ትዳርን የማሸነፍ ኣቅም ማጣት እድገትን ተከትሎ ኣይመጣም


Click here for PDF

ገለታው ዘለቀ
ኢንፍሌሸንን ሊያመጡ ከሚችሉ መንስኤዎች መካከል ፈጣን የ ኢኮኖሚ እድገት ኣንዱ እንደሆነ የሚስማሙ ምሁራን በርግጥ ኣሉ። ኣንዳንድ ምሁራን ደሞ ኢንፍሌሽንን እድገትEthiopian flag (Alemayehu G. Mariam) ሊያመጣው ኣይችልም ብለው ይናገራሉ። የ ሁለቱ ልዩነት ያረፈበት ነጥብ የሚመስለው ኢንፍሌሽን የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ባዩበት ወሰን ላይ ነው። የ መጀመሪያው ቡድን የሚያምነው ኢኮኖሚ ሲፈነዳ ኣገሮች የ ኢኮኖሚ ጥርመሳ (breakthrough) ሲያደርጉ የ ዋጋ ማሻቀብ ይመጣል። ይህንን የዋጋ ማሻቀብ ተከትሎም የገንዘቡ የመግዛት ኣቅም ይወርዳል ይላሉ። በነዚህ ወገኖች መረዳት የ ኢንፍሌሽንን ጽንሰ ሃሳብ በ ዋጋ ንረትና በ ገንዘብ የ መግዛት ኣቅም ማነስ ኣጥር ውስጥ ነው የሚያዩት። የ ሃገሪቱን ኣጠቃላይ ገቢ እድገት ያዩና ካምናው ዘንድሮ ኣጠቃላይ ኣሃዙ እድገት እያሳየ ግን ደሞ ዋጋ ካሸቀበ  እድገቱ ያመጣው ጣጣ ነው ወደ ማለት ሊሄዱ ይችላሉ። ይህ ማለት እድገት ሲመጣ ዲማንድ ወይም ፍላጎት ይጨምራል ለእድገት በሚደረገው ሩጫ በ ገበያ ላይ ፍክክርን ስለሚያመጣና ገበያውን ስለሚያነቃቃው ግዢ ብዙ ስለሚፈጸም ዋጋ ያሸቅባል ለማለት ነው። ኣድገው የተረጋጋ ኢኮኖሚ እስኪገነቡ ድረስ ለዚሀ የመጋለጥ  እድላቸው ሰፊ ነው ለማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ያለው ግንዛቤ ደሞ ኢንፍሌሽንን ሰፋ ባለ ኣጥር ውስጥ ያያል። በዚህ ትንታኔ መሰረት ኢንፍሌሽን ማለት በ ኣጠቃላይ የ ዋጋ ማሻቀብ ሆኖ በዚህ ሳቢያ የገንዘብ ጉልበት ሊደክም እንደሚችል ያሰምርና በዚህ ኣይቆምም የዚህን ተጽእኖም ያካትታል። በመሆኑም ዋጋ ሲያሻቅብ ገንዘብ ሲደክም የሚመጣው ተጽእኖ የ ሸማቹን ትዳር የ ማሸነፍ ኣቅምም ይመታል ማለት ነው። በመሆኑም ኢንፍሌሽን የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ ከዋጋ ንረት ጀምሮ የገንዘብን ጉልበት ኣድቅቆ የዜጎችን ኑሮ የ ሚያደቅ ነው ማለት ነው። በዚህ ኣገባብ የምናወራው እጅግ ከፍተኛ፣ ከፍተኛ፣ ሲከፋም ሃይፐር ኢንፍሌሽን የሚባለውን ጽንሰ ሃሳብ የተመረኮዘ ኣስተያየት ነው። በ ኖርማል ሬንጅ ውስጥ ስላለው የገበያ መውጣት መውረድ ኣይደለም።
ታዲያ በዚህ ሰፋ ባለ መረዳት ጊዜ ኢንፍሌሽን ሲታይ እድገት ካለ የ ዋጋ መናር ሊኖር ቢችልም ገንዘብ ቢደክምም ግን የ ዜጎች የ መግዛት ኣቅም ያን ያህል ኣይደክምም። ምክንያቱም እድገት ስላለ የዜጎች የ ገቢ መጠንም ኣብሮ ከ ኢንፍሌሽኑ ጋር እየተፎካከረ ያድጋልና ነው። የነዚህ ቡድኖች እይታ የመጀመሪያዎቹን ምሁራንን ትንታኔ ግልጽነትና ተለጣጣቂ ተጠይቃዊ(logical) ጥያቄዎችን የ ማይመልስ የ ሚያደርግ ሊሆን ይችላል።ምክንያቱም ዋጋ ማሻቀቡና የገንዘብ ዋጋ መድከሙ ብቻውን ወይም በራሱ ምንም ኣይደለም። ዋናው ጉዳይ በሸማቹ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ነው መሆን ያለበትና።
በነዚህ ወገኖች እሳቤ ኢንፍሌሽን ማለት በቀላል ኣገላለጽ ለምሳሌ የ ዛሬ ኣመት ኣንድ ቅርጫት ይዞ ገበያ ሄዶ በ 500 ብር ግጥም ኣርጎ ቅርጫቱን ሞልቶ በ ወዛደር ኣሸክሞ ወደ ቤቱ የ ሄደ ሰውዬ ዛሬ ያንንው እቃ በዚያው ቅርጫት በዚያው ገንዘብ መጠን ገዝቶ ግን የገዛው እቃ ትንሽ ሆና በ ኣንድ እጁ ጠልጠል ኣርጎ ወይም ሸከም ብሎ ወደ ቤቱ እያዘነ ሲሄድ ማለት ነው። የ እቃው መጠን  በርግጥ እንደ ደረጃው ይለያያል፡፡ ጥያቄው ታዲያ ግን ይሄ ነገር በማደግ ላይ ባለ ኣገር ይሆናል ወይ? እድገት ሲባል እኮ የምርት መጠን ወይም ኣቅርቦት መጨመርንና በዚህ ለውጥ ሳቢያ የ ህብረተሰብ የኑሮ ዘየ ላይ ተጽእኖ ሲያርፍ ነው።
ልክ ሁሉም እንደሚያምነው እድገት ሲመጣና ኢኮኖሚ ሲፈነዳ የዜጎች ፍላጎት ይጨምራል። ለምሳሌ በኛ ሃገር ደረጃ ስናየው ከዚህ በፊት ልሙጥ ሽሮ ይበላ የነበረው ዛሬ ኣዱኛ ወደ ቤቱ ብቅ እያለ ነውና ተነቃቅቶ በዘይት መብላት፣ ከዚያም ምሳና ራት የተለያዩ ምግቦችን መብላት ይፈልጋል። ትንሽ የተሻለ ኑሮ ሊያኖረው የሚችል ገንዘብ ስላገኘ በገበያ ላይም ለጋስ ይሆናል። ይከፍላል፤ ይገዛል። ሻጩም ገበያው ሲሞቅ እያየ የገዢውን ብዛትና ኣቅም እያየ ዋጋ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በእንደዚህ ኣይነት ሂደት ጊዜ የዋጋ ንረት የሚከሰት ሲሆን እንዲህ ኣይነቱ ንረት ከ ፍላጎት መጨመር ከ ህዝብ ምቾት ፍለጋ ጋር የተፎካከረ የዋጋ ሽቀባ ስለሚሆን ይህ ጉዳይ የኢኮኖሚ እድገት ያመጣው ጣጣ ነው ሊባል ይችላል።በዚህ ጊዜ መንግስት የኢኦኖሚክ ስሌቱን እያሰላ የንረቱን መጠን ማደጉን ቢገልጽም በዜጎች ዘንድ ማጉረምረም እብዛም ኣይታይም። በዚህ ጊዜ ባለፈው ጊዜ በ 500 ብር በግ ገዝቶ የገባ ሰው ዛሬ ዋጋው በ 50 በመቶ ኣድጎ ያንኑ የሚያህል በግ 750 ብርም ቢሆን ገዘቶ ይገባል እንጂ ይህ ሰው ባዶ እጁን ኣይገባም። እድገት ካለ በጨመረው ዋጋ ያንኑ በግ እንደውም የተሻለ ገዝቶ ሊገባ የሚያስችል ኣቅም ይኖረዋል።በፈጣን እድገት ላይ ያለ ኣገር ማለት እኮ እያደገ መሄዱን በዜጎች ህይወት ላይ እያሳየ ነው የሚሄደው። እድገት ኣንዴ የኣምስቱ ኣመት የእድገት ፕላን ሲያበቃ በመጨረሻዋ ቀን ሰርፕራይዝ ተብሎ ፓርቲ የምናደርግበት ሂደት ኣይደለም። በየ ኣንጓው ዜጎች ለውጥን እያዩ የሚሄዱበት ሂደት ነው እድገት።
የዋጋ ንረት ሲመጣ ዜጎች በውነት መንግስትን ኣጥብቀው መጠየቅ የሚፈልጉት ለምን እቃ ተወደደ ኣይደለም። ለምን የኔ ትዳር የማሸነፍ ኣቅሜ ደከመ ነው የ ውስጠኛውና ዋናው ጥያቄ። ለዚህ ነው ሰራተኛው የደመወዝ ጭማሪ የሚያነሳው።ለምን ዋጋ ጨመረ ሳይሆን ዋጋ ጨምሮ የኔ ገቢ ለምን ኣይጨምርም ነው። እንግዲህ በኛ ሃገር ሁኔታ ኢንፍሌሽኑ የመጣው በ ፈጣን እድገት ምክንያት ነው ከተባለ ዜጎች የሚጠይቁት የነፍስ ወከፍ ገቢያቸው ከ ኢንፍሌሽኑ ጋር ታገሎ ተሸነፈኩ ትዳሬን ማሸነፍ ኣቃተኝ ያ እድገት ኣለ ያላችሁት ለምን ኣይደርስልኝም?  ነው እንጂ ፍልስፍናው ምንም ኣይጠቅማቸውም። ኢንፍሌሽን ከ እድገት ጋር ተያይዞ ይመጣል ኣይመጣም እያሉ ሊከራከሩና ኣዳዲስ ኣሳቦችን እያነሱ በፍልስፍናው ሊዝናኑ(entertain ሊያደርጉ) ይችላሉ። ለተራው ዜጋ ግን እውነተኛው ምስክሩ የሱንና የቤተሰቡን የጏጓደኞቹን የ ኣካባቢውን ለውጥ ማየት ነው። እውነተኛ ምስክሮቹ እነዚህ ናቸው። ይሄውልህ በፈጣን ሁኔታ እድገት ስለጀመርን ነው ኣንተ ትናንት ትኖረው የነበረውን ኑሮ መኖር ያቃተህ ወይም ትዳርህ ያንገዳገደህ የሚል  ኣንድምታ ያለው ፕሮፓጋንዳ ሲነዛ ኣፉን እያጣመመ ይታዘባል።
እንግዲህ ቅድም እንዳልነው ኢንፍለሽን የ ዋጋ ማሻቀብ እሱን ተከትሎ የገንዘቡ መሽመድመድ ከሚለው ጀርባ የ ዜጎች ትዳር የማሸነፍ ኣቅምን ያዘለ ጽንሰ ሃሳብ ነው። ለዚህ ነው እድገት ካለ ኢንፍሌሽን የለም የሚያሰኘን።ኢንፍሌሽንን በዚህ መረዳት ካየነው እድገትና ኢንፍሌሽን ሳይሆኑ ኣብረው የሚሄዱት የ ድህነት መጨመርና ኢንፍሌሽን ናቸው ኣብረው የሚሄዱት የሚል ድምዳሜ ላይ ኣረጋግቶ ያስቀምጠናል። ምን ማለት ነው እድገትን ተከትሎ የዋጋ ማሻቀብ ቢኖርም የዜጎች ገቢም በኣጭር ርቀት ከ ኢንፍሌሽኑ ጋር ስለሚሮጥ በዜጎች ህይወት ላይ የሚያመጣው ተጽእኖ ቀላል ነው።  ዜጎች በዋጋ ጭማሪ ጉዳይ ርሃብ ላይ ከወደቁ ወይም ሰፊው ህብረተሰብ ኑሮው ከደከመ በርግጥ ኢንፍሌሽኑ ከእድገት ጋር የተያያዘ እዳልሆነ ያሳያል። ዋናው ቀላሉ ሎጂክ ያለው እዚህ ጋር ነው። እድገት የሚባለው ነገር ልማታዊ ከሆነና ጤነኛ ከሆነ ኢንፍሌሽን የዜጎችን ቤት ኣያፈርስም። በዚህ ደረጃም ኣያስመርርም።ይህ ማለት ገበያው በ ኣስር ሳንቲም ሲጨምር እድገት ባለባቸው ኣገሮች የዜጎች ገቢም ኣስር ሳንቲም እየጨመረ መሄድ ኣለበት ማለት ኣይደለም። እንዲህ ኣይነት ነገር በተገባር ኣይሆንም ግን ታዲያ በተከታታይ ለኣመታት ኢንፍሌሽን ሲከሰት የዜጎች ገቢ ተፎካክሮ ካልቆመ ድህነት እየጨመረ መሄዱን ያሳያል እንጂ እድገት ኣለ ማለት ኣይቻልም።ኢንፍሌሽን እየጨመረ የዜጎች ትዳር የማሸነፍ ኣቅም እየወረደ ከመጣ በዚያች ሃገር ድህነት እየጨመረ እየጨመረ መምጣቱን ነው የሚያሳየው። የ ምርት እጥረት የ ኣቅርቦት እጥረት መኖሩን ነው የሚያሳብቀው።
ኢንፍሌሽን ሁለት ኣይነት ሊሆን ይችላል። ኣንዱ በተፈጥሮ ወይም ሰው ሰራሽ ኣደጋ ሳቢያ ድንገት የሚፈጠር የዋጋ ማሻቀብ  ሲሆን ይህ ኣይነቱ ግሽበት ዜጎችን ለጊዜው ቢያስደነግጥም ኣገር ሲረጋጋ ወደ ነበረበት ሊመለስ ይችላል። ኢትዮጵያን የገጠማት ግን በተከታታይ ለረጅም ኣመታት የሚዋዥቅ ኢንፍሌሽን ነው። በ ዚህ ጊዜ ደሞ ዜጎች በ ከፍተኛ ሁኔታ ሲያማርሩ ይታያል፡፡ ይህ ኣይነቱ ችግር የሚመጣው እድገትን ተከትሎ ሳይሆን የ ኣቅርቦት እጥረት ሲከሰት ነው። በቂ ኣቅርቦት ከሌለ በዚያ ምክንያት በሚፈጠር ፉክክር ገበያ ያብዳል። በዚሀ ጊዜ ሰፊው ህዝብ መከራው ይበዛል፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ኣሁን ያለው ኢንፍሌሽን በምን ተከሰተ ለሚለው ጥያቄ ብዙ ጥናት ላይጠይቅ ይችላል። ፋክቶች ስላሉ እነሱን ኣይቶ ኣንጻራዊ ድምዳሜ መስጠት ይቻላል። እንግዲህ ተመልከቱ የዛሬ ሃያ ሁለት ኣመት ገደማ ኣንድ እንቁላላል በኣስር ሳንቲም በሚሸጥበት ሰኣት ኣንድ  የ 500 ብር ደመወዝተኛ ኣሁን ኣገሪቱ ኣድጋ 2000 ብር የሚከፈለው ሆኖ የኣንድ እንቁላል ዋጋ 1 ብር ከ 50 ከሆነ ኣሁን ይህ ሰራተኛ የ እድገቱ ተካፋይ ኣልሆነም ማለት ነው።እንዴውም ማደጉ ቀርቶበት በ ብዙ በ ብዙ ትዳር የማሸነፍ ኣቅሙ ወርዷል ማለት ነው።  የ ሰራተኛውን ገቢ ስናይ እድገት የለም ብቻ ሳይሆን ወደ ሗላ ሄዶ ደክሞ ነው የሚታየው። የግብርናውን ጉዳይም ስናይ በርግጥ የ ከፋ ነው።
መንግስት እድገት ኣለ የህዝብ ብዛት ውጦት ነው እንጂ ኣይነት ይናገራል።በመሰረቱ ኣባባሉ ራሱ ት ህትና የጎደለው ይመስላል።  እዚህ ጋር የምርት እድገትን በሁለት መንገድ ለ መግለጽ እንሞክር።በመጀመሪያ ደረጃ ኣሳባችንን ለማፋፋት ምርት ኣላደገም የሚባለው መቼ መቼ እንደሆነ እንግለጽ:: ምርት ኣላደገም ሲባል በሁለት መንገድ የሚገለጽ እሳቤ ነው። ኣንደኛ በ ሰው ሰራሽ ወይም በ ተፈጥሮ ችግሮች ሳቢያ ካምናው የ ዘንድሮው ምርት በመጠን ቀንሶ ሲገኝ ምርት ቀነሰ ወይም ኣላደገም የምንል ሲሆን ሁለተኛው ደሞ ምርቱ ሳይጨምር ቀርቶ ወይም ጨምሮ ግን የጨመረው ምርት ከህዝቡ ብዛት ጋር የማይጣጣም ከሆነ ምርት ኣላደገም ወይም ቀንሷል ነው መባል ያለበት። ለ ምሳሌ የ ዛሬ ስንት ኣመት ሃያ ሚሊዮን በነበርንበት ጊዜ 50 ሚሊዩን ኩንታል ነበር የምናመርተው ኣሁን ዘጠና ሚሊዩን ሆነን 100 ሚሊዮን ኩንታል ነው የምናመርተው ዛሬም ቁጥራችን ሃያ ሚሊዮን ሆኖልን ቢሆን ኖሮ ኣድገን ነበር ኣይባልም። ኣሁን ላለው ምርት ኣስተዋጽኦ ያደረገው ይሄው ዘጠና ሚሊዮኑ ህዘብ ነውና ይህንን ህዝብ የሚያረካ እድገት ካልተገኘ የድሮውን ኩንታል ቆጥሮ ካሁኑ ጋር እያወዳደሩ ኣድገን ነበር የህዝብ ብዛት ጉዳይ ጉድ ኣረገን እንጂ ኣይባልም።የዘጠና ሚሊዩን ህዝብ ቀረጥ ሰብስቦ በዚሁ ጉልበት ኣምርቶ ምርቱን ወደ ኣነስተኛ የህዝብ ቁጥር ዘርዝሮ ችግር ነው ማለት ኣግባብ ኣይደለም። በመሆኑም በኢትዮጵያ ውስጥ ከ ህዝቡ ብዛት ጋር ግብርናውም ስላላደገ እድገት በ ኢትዮጵያ ውስጥ ኣለ ማለት ኣይቻልም። በርግጥ የህዝብ ብዛትን በተመለከተ ለ ኢኮኖሚ እድገት ለሃገሪቱም ተስፋ (future) ጥላ የሚፈጥር በመሆኑ መንግስት የ ስነ ህዝብ ፖሊሲ መንደፍ ተግቶ ማስተማር ኣለበት።
በኣጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሰዎች ያልፈጠረ የጥቂት ሰዎች እድገት ይኖር ይሆናል።  እነዚህ ሰዎች ያበዱ ቤቶች ሊሰሩ ይችላሉ። ያ ማለት ግን ኣገር ኣደገ ማለት ኣይደለም። በ መጀመሪያ ደረጃ ኣገር የሚባለው ጽንሰ ሃሳብ ራሱ የ ቆመው በ ማጆሪቲ ነው። ሰፊው ህዝብ ነው የ ሃገር መገለጫው፡፡ ኣጠቃላይ በ ማክሮ ደረጃ ኣድገናል ከተባለ እድገቱ ሃገራዊ ነው ማለት ነው። ሃገራዊ ከሆነ ደሞ ሰፊውን ህዝብ ያቅፋል ማለት ነው። በ ዴሞክራት ሃገሮች የኢኮኖሚ እድገቱ ብዙና ሰፋ ያለ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች የሚፈጥሩት ኣንዱ ልባቸው የዴሞክራሲ ጽንሰ ሃሳብ መገለጫው የዚሁ የማጆሪቲው ህይወት በመሆኑ ነው።
በ ኣጠቃላይ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚታየው ኢንፍሌሽን በተከታታይ ኣመታት እጅግ በጣም ከፍተኛ ና ከፍተኛ በሚባል የኢንፍሌሽን ሬንጅ ውስጥ በመሰንበቱ ዜጎች ሲሰቃዩ ይታያል። ባለፈው ጊዜ ጠቅላይ ሚኒስትር ኣቶ ሃይለ ማርያም ደሳለኝን ኣንድ የፓርላማ አባል የጠየቁ ሲሆን ጥያቄያቸው ትክክል ነው። ህዝቡ ይህ እድገት የሚባለው ነገር የዜጎችን ኑሮ የሚያሻሽል ኣይደለም ወይ? እያለ ካማረረ ኢንፍሌሽኑ የድህነት መገለጫ መሆኑን ያሳያል። ኣቶ ሃይለማርያምም ጥያቄውን ሊያዩት የሚገባው ኢንፍሌሽኑ የመጣው በ እድገታችን ነው ወይስ በ ህዝብ ብዛት የተነሳ የ ኣቅርቦት ችግር በሚል ሰሌት ኣይደለም። ኣማካሪዎቻቸው በ ያዝነው እድገት ምክንያት ነው የመጣው ቢሏቸው እድገቱን ሊያቆሙት ነው?  በህዝብ ብዛት ምክንያት ምርቱ ኣላደገም ሊሉም ኣይጠበቅም።
ምን ማለትስ ነው? የተጠየቁት ጥያቄ ኢንፍሌሽኑን ባለበት ከማስቆም ኣልፎ ሄዶ ትዳር የማሸነፍ ኣቅም መዳከምን የሚያሳይ ነው። ኣሁን ያለውን ኢንፍሌሽን ቢያስቆሙም ለረጅም ጊዜ ሰፊው ህዝብ በሩጫው መስመር ላይ ወደ ሗላ ስለቀረ ከባድ ማስተካከያ ይጠይቃል።
እንግዲህ ኢንፍሌሽንን በሁለተኛው ትርጓሜ ካየነው እድገት የሚያመጣው ኣለመሆኑን እንረዳለን። ይህ ማለት ግን እድገትን ተከትሎ የገበያ ማሻቀብ ኣይታይም ማለት ኣይደለም ብለናል። ይህ ነገር ሊከሰት ቢችል ኣይገርምም። ይሁን እንጂ እድገት መጥቶ ግን በኢንፍሌሽን ምክንያት የዜጎች ኑሮ ወደ ሗላ ከሄደ እድገትን ሳይሆን ድህነትን የሚጠቁም፣ የ አቅርቦት እጦትን የሚያጋልጥ ክስተት ነው የሚሆነው። ኢትዮጵያም የገጠማት ነገር ይህን ይመስላል።
እግዚኣብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!
ኣስተያየት ካለዎ እነሆ ኢሜየል ኣድራሻዬ
geletawzeleke@gmail.com

No comments:

Post a Comment