ኢሳት ዜና:-ምርጫ ቦርድ እስካለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀርበው የምርጫ ምልክቶቻቸውን ያልወሰዱ ፓርቲዎች በሚያዝያው ምርጫ መሳተፍ እንደማይችሉ በይፋ አስታወቀ፡፡
ከ33ቱ ፓርቲዎች መካከል የአንዱ የአመራር አባል የምርጫ ቦርድ እርምጃ 33ቱ ፓርቲዎች ከምርጫው ወጥተናል ከማለታቸው በፊት “አባረናቸዋል” ለማለት የተወሰደ ስልታዊ እርምጃ ነው በሚል አጣጥለውታል፡፡
ቦርዱ ባወጣው ፕሮግራም መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎች በማዕከል በቦርዱ ጽ/ቤት ተገኝተው የመወዳደሪያ ምልክቶቻቸውን የሚወስዱበት ጊዜ ህዳር 14 ቀን 2005 ዓ.ም የነበረ ቢሆንም ፣ የፓርቲዎችን ተሳትፎ ለማበረታታት ሲባል ይኸው ጊዜ በተደጋጋሚ እንዲራዘም መደረጉን ጠቅሶ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ጊዜው መጠናቀቁን ይፋ አድርጓል፡፡
ከቦርዱ ጽ/ቤት በተገኘው መረጃ መሰረት በጊዜ ገደባቸው ቀርበው የመወዳደሪያ ምልክቶቻቸውን የወሰዱ ፓርቲዎች ካሉት 75 ፓርቲዎች መካከል 28 ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡
የ33ቱ ፓርቲዎችን ከሚወክሉ ፓርቲዎች የአንዱ የአመራር አባል የሆኑ ስለጉዳዩ ተጠይቀው ነገሩ ቦርዱ ጩኸታችንን ለመቀማት እሽቅድድም ውስጥ የገባ ያስመስለዋል ብለዋል፡፡
“33ቱ ፓርቲዎች ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከምርጫው በፊት ከምርጫ ጋር በተያያዘ ባሉ ችግሮች ላይ ተወያይተን እንድንፈታ ዕድል ስጠን በሚል ጥያቄዎቻችንን በዝርዝር አቅርበናል፡፡ ቦርዱ ለጥያቄዎቻችን መልስ ሳይሰጥ ከአንድ ወር በላይ ከቆየ በኋላ ልክ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በየመድረኩ የሚሉትን በመድገም “ችግሮች አሉ ለተባለው የቀረበ ማስረጃ የለም፣ያሉትም ተፈትተዋል” በሚል በወጉ እንኳን ሳያነጋግረን ጥያቄያችን ውድቅ አድርጓል፡፡ይህ ሁኔታ ፓርቲዎቹን ብቻ ሳይሆን የሚወክሉትን ህዝብ መናቅ መሆኑን በመገንዘብ በምርጫው አጃቢ ሆኖ ላለመቅረብ የጋራ ስምምነት እንደነበረ እና ይህንንም አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን በመዘገባቸው በይፋ “ከምርጫው ወጥተናል” ብለን መግለጫ ከመስጠታችን በፊት ቦርዱ ተሸቀዳድሞ “ምልክት ባለመውሰዳቸው ተባረዋል” ለማለት የዘየደው የሕጻን ጨዋታ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡
ያለፓርቲዎች ስምምነት እየተጓዘ ያለው የዘንድሮ ምርጫ ሚያዝያ 6 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስአበባ፣በድሬዳዋ ፣በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ለከተማ አስተዳደር፣ለወረዳና የቀበሌ ም/ቤቶች ምርጫ እንደሚካሄድ ቦርዱ ያወጣው መርሃግብር ያሳያል፡፡
No comments:
Post a Comment