ሻለቃ ፀአዱና ሟቹ ዶ/ር ልኡል
ከኢየሩሳሌም አርአያ
ሻለቃ ፀአዱ የህወሓት ታጋይ የነበረች ናት። ከኤርትራና ጣሊያን የዘር ግንድ ያላት ሻለቃ ፀአዱ የቀይ ቆንጆ ናት፤ ገፅታዋን በመመልከት ማንነትዋን በቀላሉ መገመት ይቻላል። የሽማግሌው ስብሃት ነጋ ባለቤት ነበረች። ሽማግሌው ስብሃት ከበረሃ ጀምሮ በአብዛኛው የድርጅቱ አባላት የሚታወቁበት ባህርይ ሴሰኝነታቸው ነው። ከፀአዱ ጋር ከበረሃ የጀመሩት ፆታዊ ግንኙነት እስከ 1990ዓ.ም ድረስ የዘለቀ ሲሆን በ <አብሮነት> ጊዜያቸው ልጆች አፍርተዋል። በኮንኮርድ ሆቴል ጀርባ ገባ ብሎ በሚገኘው የተንጣለለ ቪላ የሚኖሩት ሽማግሌው ስብሃትና ሻለቃ ፀአዱ ነጋ-ጠባ ሲያነታርካቸው የነበረው አስገራሚ « አጀንዳ» ፈንድቶ የወጣው ከላይ በተጠቀሰው አመት ነበር። በፓርቲው ሕግ፥ “አንድ የማ/ኰሚቴ አባል በትዳሩ ላይ ችግር ሲከሰት ጉዳዩ የሚታየው በድርጅቱ አመራር ነው”፤ ከዚህ ባለፈ ወደ ፍ/ቤት መሔድ አይቻልም። በዚሁ መሰረት ሻለቃ ፀአዱ ለፓርቲው አመራር አቤቱታ ታቀርባለች። ባጭሩ ያለችው ፥« ..ባለቤቴ ስብሃት ነጋ በትዳራችን ላይ እየማገጠ ነው፤ በተደጋጋሚ ከዚህ ተግባሩ እንዲታቀብ ብመክረውም ጨርሶ ሊሰማና ሊታረም አልቻለም። … ስለዚህም የፍቺ ጥያቄዬን የፓርቲው አመራር ተቀብሎ እንዲያፀድቅልኝ እየጠየኩ..የልጆች ማሳደጊያ ተቆራጭ አብሮ እንዲወሰንልኝ አያይዤ አመለክታለው።»
ጉዳዩን የተመለከተው ከፍተኛው አመራር (የፖሊት ቢሮ) ሁለቱንም አስቀምጦ ለማስታረቅ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም። ጭራሽ ባልና ሚስቱ አስገራሚ የዘለፋ ቃላት ተወራወሩ፤ ሽማግሌው ስብሃት በሰጡት የአፀፋ መልስ « ..እርሷ የምትሰራውን ነው የሰራሁት..» ሲሉ አፈንድተውት አረፉት።..(ሌሎቹ የቃላት ልውውጦች አፀያፊ በመሆናቸው ዘልያቸዋለሁ)… በዚሁ መሰረት ስብሃት የልጆች ማሳዳጊያ ተቆራጭ እንዲያደርጉ በመወሰን የፍቺ ጥያቄው እንዲፀድቅ ተደረገ። መኖሪያ ቤቱ ለሁለት ተከፍሎ እንዲኖሩበት ተወሰነ። ሽማግሌው በአብዛኛው ቀናት ወደ መኖሪያቸው ሲያቀኑ ወጣት ኮረዶችን ሻጥ ማድረጉን በግልፅ ተያያዙት። እንዳውም ሁለት ወጣት ኮረዶችን ይዘው ይገቡ እንደነበር፥ በሕይወት የሌለው የስብሃት የረጅም አመት ሹፌር ተክላይ (ወዳጄ) በየጊዜው ይነግረኝ ነበር። ( በነገራችን ላይ ሹፌር ተክላይ በአንድ የውጭ ድርጅት በተሻለ ደመወዝ ለመቀጠር ፈልጎ ለስብሃት የመልቀቂያ ጥያቄ ሲያቀርብ « ብዙ ሚስጥር ስለምታውቅ ከዚህ መልቀቅ አትችልም» ተባለ። ከዚያም በተመረዘ ምግብ ሕይወቱ አለፈ። መስከረም 2000ዓ.ም ነበር ያለፈው)
ወደ ሻለቃ ፀአዱ እንመለስ፤ ከመከላከያ ጤና ኰሌጅ በጥርስ ህክምና < ነርስ> ተብላ የተመረቀችው ፀአዱ ማ/ዕዝ ተብሎ በሚጠራው ወታደራዊ ሆስፒታል የተመደበችው በ1989ዓ.ም ገደማ ነበር። የሙስና ውጤቶች የሆኑ ሰባት ዘመናዊ አውቶሞቢሎች አሉዋት፤ ከነዚህም ቀይ ቮልቮ፡ ቡናማ ዘመናዊ ኮብራ፡ ነጭ ሊፍት ባግ፡ ነጭ ሃዮንዳይ፡ ቡናማ አቶዝ…በከፊል ይጠቀሳሉ። በሚሊዮን ረብጣ የተሸመቱ ሲሆኑ የሚገርመው ለመጀመሪያ ልጃቸው የልደት ስጦታ በሚል በአንድ ሚሊዮን ብር የተሸመተ ዘመናዊ ኮብራ እንዳበረከቱ በዚህ አጋጣሚ መጠቆም ያሻል። ይህ ሁሉ ደግሞ ስብሃት በሙስናው መንደር ከተከሉዋቸው «ሉሲ አካዳሚ፡ የጎንደር-ሁመራ መጠነ ሰፊ የሰሊጥ እርሻን» ጨምሮ ከሌሎች የግል ተቁማቸው የተገኙ የሕዝብ ጥሪቶች ናቸው።
ሻለቃ ፀአዱ በጣም አምባገነን ባህርይ የተጠናወታት ናት ሲሉ ብዙዎች ይገልፁዋታል። <ነርስ> የሚል ካባ ብትደርብም በሙያው ምንም እውቀት እንደሌላት የማ/ዕዝ ሆስፒታል ዶክተሮች ጭምር ይመሰክራሉ። ሆስፒታሉን ከላይ እስከታች እንዳሻት ታሽከረክራለች። እያንዳንዱ ሰራተኛ ወደ ግቢው ሲገባና ሲወጣ ጥብቅ ፍተሻና ብርበራ ይደረግበታል፤ በአንፃሩ ሻለቃዋን ማንም አይፈትሽም፡ አይታሰብም። በየጊዜው የሆስፒታሉን አስተዳደር ጨምሮ ዶክተሮችንና ረዳቶቻቸውን ስብሰባ በመጥራት « ግምገማ» ታካሂዳለች። ዘለፋና ስድብ ታዥጎደጉዳለች። ከዛም ባለፈ የካቲት 12 ሆስፒታል በማምራት ተመሳሳይ ተግባር ታከናውናለች። በተለይ በማ/ዕዝ ሆስፒታል በርካታ የህክምና ባለሙያዎችና ሌሎች ሰራተኞች እጅግ ተማረው ለመልቀቅ ተገደዋል። መልቀቂያ ለማግኘት ፀአዱን ደጅ የጠኑ፡የተሰደቡ፡ በተቃዋሚ ፓርቲ አባልነት ተፈርጀው እስርና እንግልት የተፈፀመባቸው በርካቶች ናቸው። የሆስፒታሉ ሃኪሞችና ሰራተኞች በ1998ዓ.ም ለዋናው አስተዳደር መ/አለቃ ገ/መድህን አቤቱታ ቢያቀርቡም የተሰጣቸው መልስ « ሻለቃ ፀአዱን ከዚህ ተግባሩዋ እንድትታቀብ ለቀድሞ ባለቤትዋ ስብሃት ጭምር ነግረናል። የፈለገችውን ማድረግ መብትዋ ነው፤ የሚል ምላሽ ነው የተሰጠን፤ ከአቅማችን በላይ ነው።» የሚል ነበር።
በ1993ዓ.ም በማ/ዕዝ ሆስፒታል የተፈጠረው አሳዛኝ ሁኔታ በዋንኛነት ይጠቀሳል። የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ተከትሎ በሆስፒታሉ በርካታ የጦር ቁስለኞች ነበሩ። ጉዳተኞቹን ለማከም ሌት ተቀን ይተጉ ከነበሩት አንዱ ዶ/ር ልኡል ይገኝበታል። መልከ-መልካም የሆነው ዶ/ር ልኡል ተወልዶ ያደገው ጎንደር ሲሆን ሲበዛ ትሁትና ተወዳጅ ባህሪይ ያለው ነበር። ሻለቃ ፀአዱ በተለያየ መንገድ ለመቅረብ ጥረት ብታደርግም ..ዶ/ር ልኡል ግን ፊት ሊሰጣት አልቻለም። « ባልና ሚስት ከአንድ ባህር ይቀዳሉ፥ የሚባለው …»> እያሉ በፀአዱ ሴሰኝነት ተግባር የሚያሽሟጥጡ አልታጡም ነበር። ..በግልፅ ለዶ/ር ያቀረበችለት ጥያቄም ከዚህ ውጭ አልነበረም። ከረጅም ወራት ማግባባትና ጥያቄ በኋላ የሻለቃ ፀአዱ የጥፋት < ሰይፍ> በዶክተር ላይ ተመዘዘ። በግምገማ ሰበብ ቁም-ስቅል ታሳየው ገባች። ጭራሽ ዶክተሮችን ሰብስባ እንዲህ አለች፥ « በማሃከላችን ለሻዕቢያ የሚሰልሉ፡ መረጃ አሳልፈው የሚሰጡ አሉ። ከነዚህ አንዱ ዶ/ር ልኡል እንደሆነ ደርሰንበታል። » ስትል ንዴቱን መቆጣጠር ያልቻለው ዶ/ር፥ « እኔ ሙያተኛ እንጂ ፖለቲከኛ አይደለሁም። ጥርት ያልኩ ኢትዮጲያዊ ነኝ። ደግሞስ ለሻዕብያ ማን ይቀርባል?..» በማለት ጉንተላ ጭምር ሰነዘረ። ህክምና በሚያካሂድበት ሰዓት ሳይቀር እያስጠራች ይህንኑ ውንጀላና ዛቻ ማውረዱዋን ገፋችበት። ከአቅም በላይ ሲሆንበት የመልቀቂያ ጥያቄ አቀረበ። በሆስፒታሉ ስድስት አመት ያገለገለው ዶ/ር ልኡል የተሰጠው ምላሽ « ሰባት አመት ለማገልገል ፈርመሃል። ስለዚህ መልቀቅ አትችልም» የሚል ነበር። ውሳኔው ደግሞ የፀአዱ እንደነበር ከራሱ አንደበት አረጋግጫለሁ።
ከዛ የተከተለው አሳዛኝ ሁኔታ ነበር፤ በሻለቃ ፀአዱ አቀነባባሪነት የጥፋት ሴራ ተዘጋጀ። « ዶ/ር ልኡል ወደ ብርሸለቆ ወታደራዊ ማሰለጠኛ ካምፕ በመሄድ በዛ የሚገኙ የጦር ጉዳተኞችን በመመልከት በቦርድ መሰናበት የሚገባቸውንና የማይገባቸውን እየለየህ ውሳኔ እንድትሰጥ ተመድበሃል» የሚል የቃል ትዕዛዝ ደረሰው። ነሃሴ 1983ዓ.ም ወደ ተጠቀሰው ካምፕ ሲያቀና መኪና ተመድቦለት ነበር። ነገር ግን የተባሉት የጦር ጉዳተኞች በስፍራው አልነበሩም። ቀደም ሲል ከፀአዱ ቀጭን ትዕዛዝ የተቀበሉ ወታደሮች ዶ/ር ልኡልን ለሶስት ቀናት አስረው ካሰቃዩት በኋላ በክንዱ መርፌ ወጉት። በጣም ታሞ መስራት እንዳልቻለና ወደ አዲስ አበባ ይዘውት እየተመለሱ እንደሆነ ወታደሮቹ ባስተላለፉት መልክት ተናገሩ። ይህ ሆን ተብሎ የተደረገው በሆስፒታሉ ያሉ ሃክሞችና ባልደረቦቹ ሌላ ነገር እንዳይጠረጥሩ በሚል ነበር።ወሬውም በግቢው እንዲሰራጭ ከተደረገ በኋላ በሌሊት ይዘውት መጡ። ከዛም የካቲት 12 ሆ/ል አስገቡትና ጥለውት ሄዱ። በጣም የተዳከመው ዶ/ር ልኡል የሆስፒታሉን ባለሞያ ስልክ እንዲተባበረው ጠየቀ። ለቅርብ ጉዋደኛው ዶ/ር ሰሎሞን (ለደህንነቱ ሲባል ስሙ ተቀይሮዋል) እንዲሁም ለዚህ ፅሁፍ አቅራቢ በተዳከመ አንደበት በውስን ቃላት ይህን አለ፥ « መርፌ ወግተውኛል…መሞቴ ነው..ሻለቃ ፀአዱ..» ለእኔ የጀመረውን አልጨረሰውም።… በዛው ሌሊት ዶ/ር ልኡል በ35 አመት እድሜው በሞት እንዲቀጠፍ ሆነ።..በጣም የሚያሳዝነው በነጋታው በማ/ዕዝ ሆስፒታል ሆን ተብሎ የተሰራጨው ወሬ « ልኡል የገዛ ራሱን መርፌ ወግቶ ነው ለሞት የበቃው» መባሉ ብዙዎቹን ያሳረረ ነበር። ነሃሴ 26 1993 ዓ.ም በወታደራዊ ተሸከርካሪ አስክሬኑ ተጭኖ ወደ ትውልድ አገሩ ጎንደር ተሸኘ። ተከራይቶ ይኖርበት ከነበረውና ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ጀርባ ይገኝ ከነበረው ቤት የግል ድክሜንቶቹ እንዲወሰዱ ተደረገ። እውነቱ ግን ተደብቆ አልቀረም፤ በማ/ዕዝ ሆስፒታል ሁሉም ጆሮ ተዳረሰ።
No comments:
Post a Comment