ለነፃነቱ የቆረጠን ህዝብ የሚያቆመዉ ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል የለም
ከጥንቶቹ ባቢሎናዉያን፤ ሮማዉያንና ግሪኮች አስከ መካከለኛዉ ዘመን እንግሊዞችና ፈረንሳዮች ከዚያም በቅርቡ እንዳየናቸዉ የቱኒዝያ፤ የግብፅና የሊቢያ ህዝብ ወይም ዛሬም ትንቅንቅ ላይ የሚገኘዉ የሦሪያ ህዝብ ታሪክ የሚነግረን አንድ ብቸኛ ሀቅ ቢኖር አምባገነኖች ያሻቸዉን ያክል ሀይል ቢገነቡ ወይም ምድር ላይ አለ የሚባለዉን የጦር መሳሪያ ሁሉ ቢታጠቁ የህዝብን መብት አስካላከበሩና ህዝብ አስካልወደዳቸዉ ድረስ እንደ ዲንጋይ ካብ ተንደዉ መጨፍለቃቸዉ አይቀርም። አምባገነኖች ህዝብን ማስጨነቅ፤ ማሰር፤ መደብደብና መግደል ይችሉ ይሆናል ሆኖም የአምባገነኖችን የበላይነት ተሸክሞ የኖረን ህብረተሰብ ታሪክ መዝግቦት አያዉቅም፤ እናት አገራችን ኢትዮጵያም የዚህ አይነት ቆሻሻ ታሪክ መጀመሪያ አትሆንም።
የኢትዮጵያ ህዝብ ደርግን ለ17 አመት ወያኔን ደግሞ ላለፉት ሃያ አንድ አመታት ተሸክሞ ኖሯልና ስለ ስላምባገነኖች ሊነገረዉ የሚገባ ህዝብ አይደለም። ደርግ በአፍሪካ አህጉር ትልቁን ጦር ገንብቶ ከሚቃወሙህ ጋር በሠላም ተደራደር ሲባል “ እንደ ዉኃ የሚያጥለቀልቅ ኃይል አለኝ” ብሎ ሲኮፈስ ለእግሩ ጫማ በሌላዉና በሚገባ ባልሰለጠነ ኃይል ተጥለቅልቆ እንደ በረሃ ዉስጥ ዉኃ ተንኖ ጠፍቷል።
የአምባገነኖች መምጫቸዉ እንጂ መጥፊያቸዉ አይለያይምና የዛሬዎቹም ባለሳምንቶች እንደ መንግስቱ ሀይለ ማሪያም፤ እንደ ፒኖቼ፤ አንደ ሙባረክና እንደ ጋዳፊ አንድ ቀን የታሪክ አተላ ሆነዉ መደፋታቸዉ አይቀርም፤ ያ “አንድ ቀን” ደግሞ ዛሬ ከምን ግዜም በላይ አጥራቸዉ ዉስጥ ዘልቆ ገብቶ ቤታቸዉን እያንኳኳ ነዉ። የወያኔ አምባገነኖች ያላቸዉ ብቸኛ አማራጭ አንደ ሙባረክ በግዜ እጅ ሰጥተዉ የበደሉትን ህዝብ ማረን ብሎ መለመን አለዚያም እንደ ጋዳፊ ቱቦ ለቱቦ መጎተት ነዉ። ከዚህ ዉጭ ግን ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች ህዝብን ለማስፈራራትና እኛን የሚደፍር ወዮለት የሚል ደካማ መልዕክት ለማስተላለፍ ከሰሞኑ የጀመሩትን የሞኝ ድራማ የሚያይላቸዉ የለምና ካሁኑ ሳይጀምሩት ቢያቆሙ ለእነሱም ቢሆን ይበጃቸዋል።
“እግዚአብሔር ሊያጠፋዉ የፈለገዉን መጀመሪያ የሳብደዋል” ይላሉ አበዉ ሲተርቱ። ዘንድሮ በተለይ ከሰሞኑ ወያኔ የሚያሳየን አዲስ ጸባይ ከላይ ከጠቀስነዉ የአበዉ ተረት ብዙ የራቀ አይደለም። ወያኔ መጥፊያዉ ስለደረሰ እያበደ ነዉ። አዎ! ወያኔ መጥፊያዉ እንደደረሰ በሚገባ ተረድቶ በአጥፍቼ ልጥፋ አባዜ ተለክፎ እያበደ ነዉ። ጨዋዉ፤ አስተዋዩና ይቅር ባዩ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን አሁንም የይቅርታ እጁን እንደዘረጋ ነዉ፤ ወያኔ ማበዱን አምኖ ጤንነት ከተመኘ ያ “ዬኔ ነዉ” የሚለዉ የገጠሩ ህዝብ አብሾ ሊሰጠዉ ከተሜዉ ደግም አማኑኤል ሊወስደዉ ሙሉ ፈቃደኛ ነዉ። አዉቆ አበዱ ወያኔ ይህንን አማራጭ አሻፈረኝ ብሎ ምርጫዉ በእብደት መቀጠል ከሆን ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅር ባይ ነዉ አንጂ አዉቆ አበድ አስተናጋጅ ስላልሆነ በቅርቡ የአረቡ አለም አዉቆ አበዶችን ባስተናገደበት መንገድ ወያኔም ይስተናገዳል ። አዚህ ላይ ካለምንም ጥርጥር ወያኔን አስረግጠን ልንነግረዉ የምንፈለገዉ አንድ ቁም ነገር ቢኖር የኢትዮጵያ ህዝብ ወያኔን እንደ ሙባረክ ወይም እንደ ጋዳፊ ከማስተናገድ የሚያቆመዉ ምንም አይነት ምድራዊ ሀይል እንደሌለ ነዉ።
ከሰሞኑ ወያኔ አንዳንድ ሰብዓዊነት የጎደላቸዉንና የወገን ሰቀቃና ጩኸት የማይሰማቸዉን ግዑዝ የህብረተሰብ ክፍሎች ሰብስቦ ዘረኝነትን መሠረት አድርጊ የተገነባዉን የደህንነት፤የፖሊስ፤የአየር ሀይልና የምድር ጦር ተቋሞቹን በማስጎብኘት ከወያኔ ጋር የሞት የሽረት ትግል ዉስጥ የገባዉን የኢትዮጵያ ህዝብ ለማስፈራራትና ከኔ ዉጭ የሚያዋጣህ ምንም ነገር የለም የሚል የፈሪ መልዕክት ለማስተላለፍ ዉር ዉር እያሉ ይገኛሉ። የእነዚህ ደካማዎች መልዕክት ደግሞ ግልጽ ነዉ። የፈረጠመ ጡንቻ አለኝ፤ በከተማ ዉስጥ ከፈለጋችሁኝ ጠንካራ የፖሊስና የድሀንነት ሀይል አለኝ፤ በሰማይ ካሰባችሁኝ ሰማዩ ዬኔ ብቻ ነዉ፤ በድንበር በኩል ከመጣችሁም ጠንካራ የምድር ጦር አለኝ የሚል ነዉ። እዚህ ላይ አንድ ልብ ልንለዉ የሚገባን ነገር ቢኖር ወያኔ ምንም ነገር ነኝ ወይም አይደለሁም ቢል እንኳን የሚያምነዉ ቀርቶ ጆሮ ሰጥቶት የሚሰማዉ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ ያዉቃል። ለዚህም ነዉ ምድረ ሆዳም ምስለኔዎችን ሰብስቦ “ወያኔ አይቻልምና” አርፋችሁ ተገዙ የሚል መልዕክት ለኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያስተላልፉ ሆዳቸዉን ሞልቶላቸዉ አፋቸዉን እንዲከፍቱ ትዕዛዝ የሰጣቸዉ። እዚህ ላይ አጅግ በጣም የሚገርመዉና የሚያሳዝነዉ ዛሬ የወያኔን ትዕዛዝ ተቀብለዉ ለመብቱና ለነጻነቱ ለሚታገለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔን ጥንካሬና አለመሸነፍ የሚነግሩን ደካማ ፍጥረቶች ደርግን የመሰለ እጅግ በጣም ጠንካራ ሀይል “ነጠላ ጫማና” “ቁምጣ ሱሪ” በለበሰ እንዲሁም በብዛቱና በትጥቁ ከደርግ እጅግ በጣም ባነሰ ሀይል ሲደመሰስ በአይናቸዉ ብሌን ተመልክተዉ “ጉድ” ያሉ ሰዎች ናቸዉ። ችግሩ እነዚህ ደካሞች “ያሉሽን በሰማሽ ገበያም ባልወጣሽ” የሚሉትን ተረት ስለማያዉቁ ነዉ እንጂ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ “ጉድ” የሚለዉ የእነሱን ክህደትና የሞራል ደከማነት እየተመለከተ ነዉ። ወያኔም ሆነ እነዚህ ደካማ ሰዎች የሚገባቸዉ ከሆነ ዛሬ ወያኔ የሚዋጋዉ እንደሱ ከተደራጀና ከታጠቀ ሀይል ጋር ሳይሆን ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ነዉ። ከህብ ጋር ተዋግቶ ያሸነፈ ሀይል ደግሞ አልነበረም፤የለም አይኖርምም።
ለመሆኑ ወያኔ ስልጣን ከያዘ ከሃያ አንድ አመት በኋላ ዛሬ “የመከላከያ ቀን” ተብሎ የሚታሰብ ቀን ፈጥሮ ለማክበርና ይህንኑ በዐል አስታክኮ ከህዝብ የመለመለዉን ሠራዊትና የታጠቀዉን መሳሪያ አይነትና ብዛት ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማሳየት የፈለገዉ ለምንድነዉ? የወያኔ መሪዎች ከዚህ ቀደም ባንዲራችንን ጨርቅ ማለታቸዉ ብቻ ሳይሆን በረሀ ዉስጥ እያሉ ዕቃ ለመጠቅለል ይጠቀሙበት ነበር። ዛሬ ያንን ኃጢያታቸዉን ለመሸፈን የባንዲራ ቀን እያሉ ማክበር ጀምረዋል። የህወሀት መሪዎቸችና የቅርብ ዘመዶቻቸዉ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ፤ ፖለቲካና የጦር ኃይሎች ሙሉ ለሙሉ እየተቆጣጠሩ ኢትዮጵያ ዉስጥ የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ፈጠርን እያሉ ላለፉት ስምንት አመታት የፌዴራሊዚም ቀን እያሉ ህዝብን እያታለሉ ኖረዋል። አሁን ደግሞ ያ ሁሉ አልበቃ ብሏቸዉ የመጀመሪየዉን የመከላከያ ቀን ለማክበር ጉድ ጉዱን ተያይዘዉታል። ለመሆኑ ይህ ሁሉ የበዐል ጋጋታ ለምን አስፈለገ?
አንዳንዴ ፈርንጆች ስለ አንድ ዕቃ ጥሩነት ሲናገሩ “ጥሩ ዕቃ” ማስታወቂያ አያስፈልገዉም ይላሉ። ለመሆኑ ወያኔ “የባንዲራ ቀን”፤ “የፌዴራሊዝም ቀን” አሁን ደግሞ “የመከላከያ ቀን” እያለ የሚያስተዋዉቀን የቀኖቹን መልካምነት ነዉ . . . . . ወይስ ነገሩ “መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ” ነዉ? ባንዲራ “ጨርቅ ነዉ” ተብሎ እንደ ተራ ጨርቅ ዕቃ የሚጠቀለልበት ከሆነ ኢትዮጵያ ዉስጥ የጨርቁ ብዛት ዬትየለሌ ነዉ፤ ታድያ “ጨርቅ ነዉ” ተብሎ የተናቀ ባንዲራ ለምን የባንዲራ ቀን አስፈለገዉ?
ጉዳዩ እንደዚህ ነዉ። ወያኔ ባንዲራ አለ፤ ፌዴራሊዝም አለ፤ ወይም ህገ መንግስት አለ ሁሉም እሱን አስቀጠቀሙት ድረስ ብቻ ነዉ። እነዚህ ለአገርና ለህዝብ እጅግ በጣም ጠቃሚ የሆኑ እሴቶች አገርና ህዝብን ጠቀሙ አልጠቀሙ ወያኔ ጉዳዩ አይደለም። የወያኔ ጉዳይ እነዚህን እሴቶች እየተጠቀመ ህዝብን አታልሎ የስልጣን ዘመኑን ማራዘም ነዉ። ዛሬም “የመከላከያ ቀን” ተብሎ በአል ለማክበር የሚደረገዉ ሽር ጉድ በአሉን ተጠቅሞ ወያኔ ላይ የተነጣጠረዉን የህዝባዊ ቁጣና አመጽ አቅጣጫ ለማስቀየር የሚደርግ ሩጫ ነዉ እንጂ ለወያኔ ጥቅም ብቻ ከቆመዉ ጥቅት የአግአዚ ሠራዊት ዉጭ በዘረኝነት የሚሰቃየዉ ሌላዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት በአል ናፍቆት አይደለም።
ኢትዮጵያ ዉስጥ ዘረኝነት በከፋ መልኩ እራሱን ከገለጸባቸዉ የተለያዩ ተቋሞች ዉስጥ አንዱና ዋነኛዉ የመከላከያ ሠራዊት ነዉ። ዛሬ አብዛኛዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት የሚፈልጉት ወይ ዘረኝነት አለዚያም የዘረኝነቱ አባት ወያኔ ከአትዮጵያ ምድር ተጠራርጎ እንዲጠፋ ነዉ እንጂ ምንም ትርጉም የሌለዉ የመከላከያ ቀን ሲከበር መመልከት አይደለም። ወያኔና ዘረኝነት ደግሞ በስም እንጂ በቅርጽም ሆነ በይዘት ስለማይለያዩ ከኢትዮጵያ ዉስጥ ወያኔ ከተነቀለ ዘረኝነትም በራሱ አይቆምምና አንዱ ሲነቀል ሌላዉም አብሮት መነቀሉ አይቀርም። እንግዲህ ወያኔ ዛሬ “የመከላከያ ቀን” አከብራለሁ እያለ ሽር ጉድ የሚለዉ በአንድ በኩል በዘረኝነት አለንጋ የሚገረፈዉን ሠራዊት ለመደለል በሌላ በሌላ በኩል ደግሞ ሞኙ ደርግ እንዳለዉ “እንደ ዉኃ” የሚያጠለቀልቅ ኃይለ አለኝ እያለ ህዝብን ለማስፈራራትና ለመብቱና ለነፃነቱ እንዳይታገል ለማድረግ ነዉ።
ሰዉ በላዉ ደርግ ከ400 ሺ በላይ ጠንካራና የረጂም ዘመን የዉግያ ልምድ የነበረዉ ጦር ነበረዉ፤ የደርግ ጦር ከማንኛዉም የጥቁር አፍሪካ አገር በላይ የታጠቀ ጦር ነበር፤ በደርግ ዘመን የነበረዉ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በአፍሪካ ዉስጥ ተወዳዳሪ አልነበረዉም፤ ዛሬ ወያኔ የመከላከያ ኢንጂኔሪንግ ገነባሁ ብሎ የሚኩራራበት ትልቁ ወታደራዊ እንጂኔሪንግ ተቋምም ቢሆን የዚሁ የደርግ ዉጤት ነዉ እንጂ ወያኔ ሊነግረን እንደሚፈልገዉ እሱ የሰራዉ ስራ አይደለም። እንግዲህ ይታያችሁ ደርግ ይህንን ሁሉ ወታደር፤ ወታደራዊ ተቋምና የመሳሪያ ብዛት ይዞ ነዉ ከሱ በቁጥር እጅግ ባነሰና በሚገባ ባልሰለጠነ ሚሊሺያ ጦር ተሸንፎ የጠፋዉ። ደርግን ለማጥፋት የ17 አመት የትጥቅ ትግል አስፈልጓል። ህዝብ እክ እንትፍ አድርጎ የተፋዉን ወያኔን ለማጥፋት የዚህ ግዜ ሩብም አያስፈልግም።
ከሰሞኑ አዲስ አበባ ዉስጥ እራሳቸዉን “አርቲስቶች” ብለዉ የሰየሙ የጥፋት ተዋንያንና ዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ በመቀናጀት ሊከይኑት የሚፈልጉት “ የመከላከያ ቀን” ድራማ ልብ ያለዉ ተመልካች አይኖረዉም እንጂ ቢኖረዉ ኖሮ ይህ አርታኢዉም መሪ ተዋንያኑም ጅላጅል የሆኑበት ድራማ የወያኔን ትንሽነትና የአርቲስት ተብዬዎቹን ተላላኪነት በግልጽ የሚያሳይ ድራማ ይሆን ነበር። የሚገርመዉ ይህ “የማይሞከር” ግዙፍ ኃይል ነዉ ተብሎ በድራማ መልክ ለህዝብ እይታ ሊቀርብ የታቀደዉ የመከላከያ ሠራዊት በአሁኑ ሰአት በየግንባሩና በያለበት ቦታ ሁሉ ወያኔን እየከዳ የነፃነት ኀይሎችን እየተቀላቀለ ነው። መቼም ይህ በፈረንጀፐቹ አዲስ አመት የመጀመሪያ ሁለት ወራት ዉስጥ ሊከበር ሽርጉድ የሚባልለት “የመከላከያ ቀን” በአል ይህን በፍጥነት በመናድ ላይ ያለዉን ጦር ገመና ለመደበቅ ካልሆነ በቀር ሌላ ምንም ፋይዳ ያለዉ አይመስለንም።
እንገዲህ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ ይህንን ምስጥ እንደበላዉ አጥር በየቀኑ የሚፈርሰዉን ሰራዊት ነዉ ወያኔና ለዚህ ሰሞን የተከራያቸዉ ጌኛ ፈረሶች አንደ ትልቅና አንደማይበገር ሀይል አድርገዉ አንተን ለማስፈራራት የጅል ድራማ መስራት የጀመሩት። የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ ከዚህ ህዝብ አብራክ የወጣዉ የመከላከያ ሠራዊት ግን “ማን ሀይለኛ” “ማን ደካማ” እንደሆነ ጠንቅቀዉ ያዉቃሉ። በተለይ ከኢትዮጵያ ህዝብ አብራክ የወጡ የፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወያኔ እነሱኑ ተጠቅሞ እነሱንና እነሱ ለመብቱና ለነፃነቱ መከበር የቆሙለትን ህዝብ እንደሚያስር፤ አንደሚደበድብና አንደሚገድል ከተገነዘቡ ቆይቷል።
በአለም ላይ ጥፋት እንዳጠፉ ኖረዉ የእነሱ ቢጤ ከሠራዉ ስህተት ሳይማሩ የሚሞቱ ደነዝ ፍጥረቶች ቢኖሩ አምባገነኖች ብቻ ናቸዉ። አምባገነኖች ከራሳቸዉም ሆነ ሌሎች አምባገነኖች ከሰሯቸዉ ስህተቶች በፍጹም አይማሩም፤ ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ ያሳዘነዉም የገረመዉም ነገር ቢኖር የአምባገነኖች ደነዝ መሆን አይደለም . . . . . በሚገባ ያዉቃቸዋልና! የኢትዮጵያን ህዝብ ከልብ ያሳዘነዉ ባህሌን፤ ወጌንና ታሪኬን ያለመልሙልኛል ከትዉልድ ወደ ትዉልድም ያስተላልፉልኛል ብሎ እምነቱን የጣለባቸዉ አንዳንድ “አርቲስት” ተብዬዎች የኢትዮጵያን ህዝብ ባህልና ታሪክ ከሚጸየፉ ሰዎች ጋር እጅና ጓንት መሆናቸዉ ነዉ። ከኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነትና የእኩልነት ጥማት ጋር ሲወዳደር ወያኔ ከትንሽም ትንሽ ነዉና እንኳን ትልቅነቱን ዛሬ ትንሽነቱንም የሚናገርበት አፍ የለዉም። ኢዚህ ላይ በጣም የሚያሳዝነን ነገር ቢኖር እነዚያ እራሳቸዉን “አርቲስቶች” ብለዉ ወያኔ እንዲጋልብባቸዉ የፈቀዱ ሀይሎች አልገባቸዉም እንጂ ወያኔ ስለራሱ የሚናገርበት አፍ ሰለሌለዉ ወይም እየተንተባተበ ቢናገርመ የሚሰማዉ ስለሌለ ነዉ እነሱን የተከራያቸዉ እንጂ እነሱንም ቢሆን ወድዷቸዉ አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይ ወጣቱ፤ ሠራተኛዉና በወያኔ የዘረኝነት ወጥመድ ተተብትቦ የሚሰቃየዉ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ወያኔ የህዝብን የአምጽ፤የእምቢተኝነትና ለነፃነት የመነሳሳት ስሜት ለመስበር የሚወስዳቸዉን አርምጃዎች ሁሉ በመበጣጠስ ለአገር አንድነት፤ ለመብት፤ ለነጻነት፤ ለዲሞክራሲና ለአኩልነት የሚደረገዉን ትግል የመቀላቀል ታሪካዊ፤ ወገናዊና አገራዊ አደራ አለባቸዉ። ወያኔ የቱንም ያክል ትልቅ ነኝ ቢል ወይም የማይደፈር መስሎ ለመቅረብ ቢሞክር ለነጻነቱ የቆረጠ ህዝብ ፊት ሲቆም ፀሐይ እንደገላመጠዉ በረዶ ሟምቶ የሚጠፋ ሀይል ነዉ።
No comments:
Post a Comment