ኢሳት ዜና:-በዳውሮ ዞን በማረቃ ወረዳ ከወረዳ እና ከሌሎች ማህበራዊና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን ግጭት መርተዋል ከተባሉት መካከል አቶ ዱባለ ገበየሁ፣ አቶ ጎሳሁን ዶሳ ዶሻና አቶ ግዛቸው ታደሰ ከበደ በትናትናው እለት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል።
በዞኑ የሚታየው አለመረጋጋት ያሳሰበው መንግስት ግለሰቦቹ በአካባቢው የሚደረገውን ተቃዎሞ በማደራጀት በኩል እጃቸው አለበት በሚል እንዳሰራቸው፣ ቤቱ ለፍተሻ በሄደበት ወቅት ያነጋገርነው በአሁኑ ጊዜ በእስር ላይ የሚገኘው፣ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሀይሎች ድርጅት የደቡብ ክልል ዋና አደራጅ አቶ ዱባለ ገበየሁ ገልጸዋል።
አቶ ዱባለ በክልሉ ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር እርሳቸው የኢህአዴግ አባል በነበሩበት ጊዜ በተለይም የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት የደኢህዴግ የፖለቲካ ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት አቶ አለማየሁ አሰፋ ቤተሰቦቹን እያሾመ ነው በማለት ገምግመዋቸው እንደነበርና አሁን የሚደርስባቸው ነገርም የዚያ በቀል መሆኑን ገልጸዋል
በአሁኑ ጊዜ ከአቶ ዱባለ ጋር በእስር ላይ የሚገኙት የማረቃ ወረዳ አቃቢ ህጎች መሆናቸውን አቶ ዱባለ ገልጸዋል
በማረቃ ወረዳ በማሪ አካባቢ ሰሞኑን በተነሳው የሕዝብ አመጽ ሕዝቡ በፖሊስ ላይ እርምጃ መውሰዱ ይታወሳል። ሻለቃ በዛብህ ገዝሙ የተባሉ የዞኑ ፖሊስ ከፍተኛ አመራርና አንድ ወታደር በድንጋይ ተደብድበዋል። አንድ የመንግሥት መኪና ተሰባብሮ ከጥቅም ውጪ መሆኑና የመኪና መንገድ በመቆፈር ግንኙነት እንዲቋረጥ መደረጉ ይታወሳል።
የፌዴራል ፖሊስ ከትናንትና ጥዋት ጀምሮ አካባቢውን መቆጣጠሩ ታውቋል።
ለአሁኑ ግጭት መነሻ የሆነው የአካባቢው ካድሬዎች መንግስት ነው የማሪና የዋካ ከተማ ህዝብ እንዲጋጭ እያደረገ ያለው በማለት በመናገራቸው መሆኑ ታውቋል። ካድሬዎቹ ከዚህ ቀደም ለማሪ ነዋሪዎች ዋካ ወረዳ አይገባውም ብላችሁ ተቃወሙ በማለት ሲቀሰቅሱ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል። መንግስት የወረዳ ማእከልነቱ ለዋካ እንዲሰጥ መወሰኑን ተከትሎ፣ ካድሬዎች ዳግም ወደ ሕዝቡ በመንቀሳቀስ እኛ አይደለንም መንግሥት ነው እናንተን ከዋካ ሕዝብ ጋራ ያጣላው፤ እኛ በሉ የተባልነውን ነው ያልነው በሚል በመናገራቸው ተቃውሞው ሊነሳ መቻሉ ታውቋል። በአሁኑ ጊዜ የፌደራል ፖሊሶች በኣካባቢው በብዛት እንደሚገኙ ታውቋል። የወረዳውን ባለስልጣናት አስተያየት ለማወቅ ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።
No comments:
Post a Comment