(ጋሻው አለሙ)
በእኔና በአቶ አንዱ አለም ተፈራ መካከል እየተደረገ ያለው ውይይት እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል:: እየተወያየን ያለንው የጋራ ስለሆነችው አገራችን የወደፊት የፖለቲካ ዕድገትና ሁለንተናዊ ለውጥ መምጣት ስለምንችልበትና አሁን ላሉብን ፖለቲካዊ ችግሮች ሊፈቱበት ስለሚገባቸው አግባብ ዙሪያ ነው:: ይህም፣ የተለያዩ ሃሳቦች መንሸራሸርንና ጠንካራ የሃሳብ ፍጭትን የሚጠይቅ ነው:: ለዚህም፣ የሌሎች ተሳትፎ ወሳኝ ነው::
ይሄኛው ምላሼ ትንሽ ዘግየት ብሏል:: አንድም የተወሰኑ ቀናትን ከቤቴ ውጭ ለስራ ጉዳይ በማሳለፌ፤ ሁለተኛም እስኬ ሌሎች እንዲሳተፉ ጊዜ ለመስጥ፤ ሶስተኛም በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ የማቀረበውን ጥናታዊ ጹሁፍ ለማጠናቀርና ለመጨረስ ስሯሯጥ ስለነበር ነው:: መቼም አቶ አንዱ አለም ይረዱኛል ብዬ ተስፋ አረጋለው::
በምናረገው ውይይት ውስጥ “ያልተግባባንበት ጉዳይ ሁለታችንም አንድ ነገር እያልን፤መደማመጡ ላይ ትንሽ የተራራቅን በመሆናችን ነው“:: አዎ፣ በተወሰነ መልኩ መደማመጥ አለመቻል ትልቅ ችግር ነው:: የምናረገውን ውይይት ይበልጥ ፍሬያማ እንዲሆን መደማመጥ እና ሀሳቦቻችንን በግልጽ ማስቀመጥ በጣም ቁልፍ ነገሮች ናቸው:: የተግባባንባቸውን ሃሳቦች ወደ ጎን አድረገን አሁን እየተወያየንባቸው ያሉ መሰረታዊ ሃሳቦች የሚከተሉት ናቸው::
- በመጀመሪያ ጹሁፌ እንዳመለከትኩት፣ የኔ የመከራከሪያ ጭብጥ በተቃማዊ ኃይሎች መካከል ያለው ትልቁ ችግርና ማዕከላዊ ጉዳይ ሊሆን የሚገባው ውስጣዊ ድክመት ነው ስል፤የእርሶዎ ደግሞ አይደለም ዋናው ችግርና ማዕከላዊ ጉዳይ ሊሆን የሚገባው የግብና የዕቅድ ልዩነት ነው፣
- በትጥቅ ትግል ዙሪያ ያሉ ሃሳቦች፣
- በሁለተኛው ጹሁፌ ሰፋ አርጌ ያየሁት እርሶዎ ያቀረቧቸውን 5 ጥያቄዎች ፖለቲካዊ ትርጉማቸው ምን ማለት እንደሆነ በኔ አረዳደድ ነበር ያቀርብኩት:: አሁን ግን የኔ የእርሶዎን 5 ጥያቄዎች አረዳድ ከእርሶዎ ጋር የተለየ መስሎ ይሰማኛል:: ከአምስቱ ጥያቄዎች ከአንድ እስከ ሶስት የተነሱት ሃሳቦች መሰረታዊና ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው:: አራተኛው ጥያቄ የፖለቲካ ባህላችንና የአስተሳሰብ ለውጥን የሚያመለክት ጥያቄ ነው:: በዚህ ጥያቄ ዙሪያ በመርህ ደረጃ ሁሉም ሰው አወንታዊ ሃሳብ ነው ያለው፣ አተገባበሩ ቢለያይም:: የመጨረሻው ጥያቄ እራሱን ችሎ የሚቆም ሣይሆን ከፖለቲካዊ ትንታኔ ተነስቶ አንድ ሰው ድምዳሜ የሚደርሰበትና በምን አይነት መንገድ ጥያቄው መመለስ እንዳለበት የሚደርሰበት ቁም ነገር ነው::
- ስለዚህም በኔ በኩል እርሶዎን የምጠይቆዎት ከአንድ እስከ ሶስት ያስቀመጧቸውን ጥያቄዎች ፖለቲካዊ፣ ንድፈ-ሃሳባዊና ሀገራዊ ትርጉማቸውን ሊገልጹልን ይችላሉ? እነዚህ ጥያቄዎችን በዚህ መልኩ ማብራራትዎ አቶ ዱባለ (የእርሶዎ አስተያየት ሰጪ) ለነሷቸው ሃሳቦች በጠለቀ ሁኔታ የእርሶዎን ምላሽ ማግኘት ስለሚቻል ነው::
- በጸረ-ቀኝ ግዛት ትግል ላይ የሰነዘርኩት ሃሳብ አቶ አንዱ አለምን ቅር እንዳሰኘ ገልጸውልኛል:: በጣም የሚያሳዝነው እውነታውን ግን እኔ ልቀይረው አይቻለኝም:: በምንም አይነት መልኩ ግን ቀኝ ግዛትን እየደገፍኩ አይደለም:: ነጻ-አውጪዎቻችን እራሳቸው ነጻ አውጪ ያስፈልጋቸዋል እያልኩ እንጂ:: በጸረ-ቀኝ ግዛት ትግል ውስጥ የተሳተፉ ሰዎችን በተለይ በአመራር ደረጃ ላይ የነበሩና በኋላም ስልጣን ላይ የተቆናጠጡት እነማን ናቸው? ይህን ጥያቄ ለመመለስ በቀላሉ የስትራተጂ ግሩፕ አናሊሲስ መስራትና ትልቁን ስዕል ማየት ይቻላል:: ይሄ እውነታ ግን ለነጻነት ሲሉ ለተሰዉት ሰዎች ያለኝን ክብርና አድናቆት አይቀንሰውም:: በነጻነትና በሰላም ስም ስንቱ አልቆ የለ እንዴ? ለዚህም እኮ ነው ታዋቂው ጋናዊ ሊቅ አዬቴ አፍሪካ ነጻ አይደለችም እያለ የሚከራከረው::
No comments:
Post a Comment