Translate

Saturday, January 26, 2013

በደል እንዴት ይራሳል?



(ክፍል 1)
የኢትዮጵያ ህዝብ መስከረምን ከጥቅምት ወይም ታህሳስን ከጥር ጋር አወዳድሮ ይህ ወር ከዚህ ወር ይበልጣል ወይም ይሻላል ብሎ የሚያምንበት ልዩ ምክንያት ባይኖረዉም እያንዳንዱ ወር በመጣ ቁጥር ግን ይዞት የሚመጣዉ የራሱ የሆኑ ታሪካዊ፤ ባህላዊና ፖለቲካዊ ትዝታዎች አሉት። የቅርቡንም ሆነ ቆየት ያለዉን ታሪካችንን ወደ ኋላ ዞር ብለን ስንመለከት ብሩህ ተስፋ የፈነጠቀልንና የዚያኑ ያክል ተስፋችንን አጨልሞ ጽልመት ዉስጥ የከተተን ወር ቢኖር ወርሃ ግንቦት ነዉ። አዎ ! . . .  ግንቦት የፖለቲካና የባህል ቁመናችንን የዳሰሱ አያሌ ክስተቶችን ያስተናገደ ጉደኛ ወር ነዉ።  . . .  ግንቦት ልደታ፤ ግንቦት 8፤ ግንቦት 20ና ግንቦት ሰባት በየአመቱ የግንቦት ወር በመጣ ቁጥር የምንዘክራቸዉ አገራዊ ትዝታዎቻችን ናቸዉ። ግንቦትንና እነዚህን ትዝታዎች የብዕር ሰዎቻችን በየዘመኑ ያነሷቸዋል፤ የኪነት ሰዎቻችን ቅኔ ይቃኙላቸዋል የየዘመኑ የታሪክ ድርሳኖቻችንም ይዘግቧቸዋል።
ግንቦት 7 1997 በኢትዮጵያ ህዝብ የዲሞክራሲ ትግል ታሪክ ዉስጥ ልዩ ቀን ናት። ግንቦት ሰባት አንድ ትዉልድ ብቻ ሳይሆን ሁለትና ሦስት ትውልድ የደም ላብ አልቦና የህይወት ግብር ከፍሎ በረጂም ዘመን የትግል ታሪከችን መዝገብ ዉስጥ የጫራት አብሪ ኮከብ ናት። አዎ! ግንቦት ሰባት የዲሞክራሲ ትግላችን  የከተባት ግዙፍ ክታብ ናት። ግንቦት ሰባት የ1940ዎቹ ትዉልድ አስቧት፤የ1950ዎቹና 60ዎቹ ትዉልድ አርግዟት የ1970ዎቹና 80ዎቹ ትዉልድ አምጧት የ1990ዎቹ ትዉልድ በጣር የወለዳት የኢትዮጵያ ህዝብ የበኩር ልጅ ናት። የኢትዮጵያ ሀዝብ ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓም በታሪካችን ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ያደረገዉ ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ የዘመናት የነፃነትና የዲሞክራሲ ረሀቡ ዉጤት፤የአርቆ ማስተዋሉ ምልክት፤ወይም ከዉስጥ ሆዱ የመነጨ የፍትህ፤ የነፃነትና የእኩልነት ፍላጎት ዉጤት ነዉ እንጂ የመላምት ታሪክ ቱልቱላዎች ሹክ ሊሉን እንደሚፈልጉት የወያኔ በጎ ፈቃድ ገጸበረከት አይደለም። ግንቦት ሰባት የአዋቂዉ መሳሳብ፤ የሀፃናት መተሳሰብ፤የምሁሩ መናበብና የወጣቱ መተሳሰብ “ቱሉፎርሳ” ብሎ ከዘረኞች ጓዳ በገመድ ጎትቶ እዉን ያደረጋት የዲሞክራሲ ትግላችን ተምሳሌት የሆነች ቀን ናት።

ግንቦት ሰባት እዉን እንድትሆን አያሌ ኢትዮጵያዉያን የህይወት፤ የአካልና የንብረት መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ አያሌ ቁጥራቸዉ በዉል የማይታወቅ ዜጎች ታስዋል፤ ተድብድበዋል ወይም ከአገር ተስድደዋል። “ዲሞክራሲ ካለገደብ አሁኑኑ” ብሎ የጮኸዉ የ1970ዎቹ ወጣት በደርግ የቀይ ሽብር ወንጀሎኞች ካለርህራሄ ተጨፍጭፏል፤ ምሁሩ ካለፍርድ ተገድሏል፤ ወታደሩ ተረሽኗል አንዲሁም ብዙ ቤተሰብ ያለ አባትና እናት ተበትኖ ቀርቷል።  ወርሃ ግንቦት በተለይ ግንቦት ሰባት እነዚህን ሁሉ ጀግኖች የምናስታዉስባት ቀን ናት።  ግንቦት ሰባት በየአመቱ ስትመጣ ከምናስታዉሳቸዉ የቅርብ ግዜ ዉድ ሰማእቶቻችን ዉስጥ አንዱ ህጻን ነቢዩ ኃይሌ ነዉ።
ግንቦት ብዙ የሚተረክ ታሪክ፤የሚወሳ ወግና የሚነገር ገድል ያላት ወር ናት። የግንቦትን ጉድና ገድል አዉርተን እንጨርስ ብንል እየመሸ ይነጋብናል እንጂ የግንቦት ወግ ተነግሮ አያልቅም። ስለሆነም ዛሬ የምናወራችሁ ተነግሮ የማያልቀዉን የግንቦትን ታረክ ሳይሆን እቺ ጉደኛ ወር ካፈራቻቸዉ በመቶ ሺዎች ከሚቆጠሩ ጀግኖቻችን ዉስጥ የአንዱን ሰማእት ታሪክ ነዉ። ለወትሮዉ የጀግኖቻችን ገድል ሲነገር ጀግናዉ ደጃዝማች ባልቻ፤ ወጣት ጀግኖቹ ዋለለኝ መኮንንና ማርታ መብርሀቱ፤ የሴት ጀግኖቹ ሸዋረገድ ሐይሌና እቴጌ ጣይቱ እየተባለ ነበር። ዛሬ የምናቀርብላችሁ የግንቦት ሰማእት ግን ደጃዝማችም፤ጎልማሳም፤ ወጣትም አይደለም። ህፃን ነቢዩ ሐይሌ ይባላል። ህፃኑ ጀግና ነቢዩ ሐይሌ እሱ ለራሱ በሚገባ ቀምሶ ያላጣጣመዉን የለጋ ህይወቱን ጣፋጭ መዐዛ እኛ ቋሚዎቹ እየሸተተን እንዲኖር የህፃንነት ለስላሳ ደረቱ በአግዓዚ አዉሬዎች ጥይት ተበጣጥሶ ህይወቱ ያለፈና የታሪካችን ምእራፍ አንዱ አካል የሆነ ህጻን ሰማእት  ሲሆን በዛሬው ትረካችን በዚያን ወቅት ብሩህ ተስፋ ሰንቆ ይጠባበቅ የነበረ የህጻን ነቢዩ የእድሜ አቻ የትናንቱ ለጋ ህጻን የዛሬው የነጻነት አርበኛ ተስፋን የክተት ጥሪ ይዳስሳል።
ግንቦት 6 1997 ዓም ዕለቱ ቅዳሜ ነበር። ቅዳሜ የሳምንቱ የመጨረሻ ቀን ነዉ። ሆኖም የዚያን ጊዜው ህፃን ተስፋ ቅዳሜን እንደ ሳምንቱ መጨረሻ ቀን አይደለም የሚመለከታት፤ ለተስፋ ቅዳሜ የእረፍቱ የመጀመሪያ ቀን ናት። ተስፋ አባትና እናቱ ኑሯቸዉ ሩጫ ነዉ፤ በአንድ በኩል አባቱ የተቀደደ ለመድፈን በሌላ በኩል ደግሞ እናቱ የተደፈነ ለመክፈት ጎንበስ ቀና እንዳሉ ነዉ የሚዉሉት፤ ስለሆነም ማታ ቤት ሲገቡ ሁለቱም አልጋቸዉ ላይ የሚወጡት በግዜ ነዉ። ተስፋ ግን ወላጆቹ ቴሌቭዢኑን ዝጋ ብለዉት እሱን ሳያስተኙ እነሱ እንደማይተኙ ያዉቃልና እቺን በግዜ መተኛት የሚሏት ነገር አይወዳትም፤ በተለይ አርብ ማታ። በ1997 ዓም በተለይም ከገናዉ ወር ከታህሳስ ጀምሮ ነቢዩ ቤታቸዉ ዉስጥ አንዳንድ ለዉጦችን መመልከት ጀምሯል። ለወትሮዉ በግዜ አልጋቸዉ ላይ የሚወጡት ወላጆቹ ትተዉት የነበረዉ ቴሌቭዢን ፊት መደርደር ጀምረዋል። ተስፋ የወላጆቹን መለወጥ ቢወድደዉም ምክንያቱን አያዉቀዉምና ግራ ግብት ብሎታል። አንዴ ከወላጆቹ ጋር ቁጭ ብሎ ቴሌቪዥን ሲመለከት ከተቀመጠበት ብድግ ብሎ እናቱን ያቅፋቻዉና ምነዉ አንቺና አባዬ አለወትሯችሁ ቴሌቪዥን ማዘዉተር ጀመራችሁ ብሎ ይጠይቃቸዋል። ትምሀርት ቤት አይነግሯችሁም እንዴ! ዘንድሮኮ ትልቅ ምርጫ አለ ይሉታል እናቱ እጁን ይዘዉ ወደ ጉያቸዉ እየሳቡት። ት/ቤት ስልምርጫዉ በየቀኑ ነዉ የሚነግሩን ግን ምርጫዉንና ቴሌቪዥኑን ምን አገናኛቸዉ ይላቸዋል ፊቱን ወዳእናቱ አዙሮ አይን አይናቸዉን እየተመለከተ። አይ ልጄ! ቴሌቪዥን ላይ የምናየዉ ፉክክር፤እሰጥ አገባ፤ ሽሙጥ፤ ጉንተላና እንተ ትብስ አንተ ትብስ ክርክር ዘንድሮ የድፍን አበሻን ልብ ሰቅዞ ይዞታል። ይህ ምርጫ ደግሞ የዋዛ እንዳይመስልህ፤ የወያኔን የመጨረሻና የኢትዮጵያን ትንሳኤ መጀመሪያ የሚያበሰር ምርጫ ነዉ።ደግሞም ከእኔና ከአባትህ በላይ ይህ ምርጫ የሚጠቅመዉ አንተን ነዉ ብለዉ እናቱ ንግግራቸዉን ሳይጨርሱ አባትየዉ ቀበል ያደርጉና . . . . አየህ ተስፋ ተቃዋሚዎች አሸንፈዉ ስልጣን ከያዙ ከአሁን በኋላ አገራችንን የሚመራት ጠመንጃ የተሸከመ ሀይለኛ ሳይሆን ህዝብ በችሎታዉና በባህሪዩ የመረጠዉ ዜጋ ብቻ ስለሚሆን እንተም እድገትህ አገር ከመምራት ጋር የተያያዘ ነዉ ብለዉ ወደ መኝታ ክፍላቸዉ ገቡ።
ተስፋ አልጋዉ ላይ ወጥቶ አይኑን እየጨፈነ ለመተኛት ቢሞክርም ቡና ሲጠጡ እንደዋሉ ባልቴት እንቅልፍ በአይኑ አልዞር አለ።  ብንን ባለ ቁጥር አሁንም አሁንም ፊቱ ላይ እየመጣ የሚደቀንበት አባቱ “እንተም እድገትህ አገር ከመምራት ጋር የተያያዘ ነዉ” ብለዉ የተናገሩት ንግግር ነዉ።  እኔም ኢትዮጵያን መምራት እችላለሁ እንዴ . . . . ብሎ ተስፋ እራሱን ጠየቀ። በአባቱ ንግግር ግራ ተጋብቶ ወይም የልጅ ነገር ሆኖበት አልነበረም ተስፋ ይህንን ጥያቄ የጠየቀዉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ስልጣን የባለጠመንጃ ነዉና ተስፋ እንደማንኛዉም ኢትዮጵያዊ ህጻን የአገር መሪ የመሆን ህልም ከምኞት ዝርዝሩ ዉስጥ የለም። ተቃዋሚ ፓርቲዎች ምርጫዉን ካሸነፉ ግን ከዚህ በፊት ያልተመኘዉንና እሆናለሁ ብሎ ያላሰበዉን ማሰብና መመኘት ይችላል። አዎ! ተቃዋሚዎች ካሸነፉ ህፃን ተስፋ አድጎ አገር መምራት ይችላል።  ብዙ ተንቆራጠጠ፤ አሰበ፤ አለመ. . . . ይበልጥ ባሰበና ባለመ ቁጥር “መሪ መሆን እችላለሁ” የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ መጣበትና የልጅነት አንጎሉ ይህንን ትልቅ ሃሳብ ማስተናገድ አቃተዉ፤ እሱም ቢሆን እዉነትም አንድ ፍሬ ልጅ ነዉና እንቅልፍ ይዞት ጭልጥ አለ። ሲነቃ ወላጆቹ እቤት ዉስጥ የሉም፤ ዬት እንደሄዱ ስለሚያዉቅ ተመልሶ ተኛ። ቀኑ ግንቦት ሰባት 1997 ዓም ነበር።
ተስፋ ከእንቅልፉ ተነስቶ የግድግዳዉን ሰዐት ሲመለከት የምሳ ሰዐት አልፏል . . . . .  .አይመጡም እንዴ አለ ተስፋ መዘግየታቸዉ አስጨንቆት። ተስፋ ተቃዋሚዎች አሸነፉ ሲባል ለመስማት ቸኩሏል፤ ደግሞም የልጅ ነገር ሁሉንም በአንዴ ነዉና  እናቱና አባቱ ሲመጡ ማን እንዳሸነፈ የሚነግሩት መስሎታል። አሁንም ቀና ብሎ ሰዐቱን ሲመለከት ከቀኑ ስምንት ሰዐት አልፏል። ወላጆቹ በቆዩ ቁጥር ተቃዋሚዎች የተሸነፉ እየመሰለዉ  መቁነጥነጥ ጀመረ። የወያኔ ማሸነፍ የወደፊት እድሉን እንደሚያጨልም በዉል የተረዳዉ ተስፋ ሰዐቱ በጨመረ ቁጥር የእሱም ስጋትና ጭንቀት ጨመረ።
የቤታቸው ሰዐት ዘጠኝ ሰዐት ሆኖ ሲደዉል፤ ተስፋ ከእንቅልፉ ሲነቃና የቤቱ በር ሲከፈት እኩል ሆነ።  ተስፋ ከተጋደመበት ፎቴ ተነስቶ “ማን አሸነፈ” እያለ ወደ በሩ ሲሮጥ ለግማሽ ቀን ቤቱን ሞልቶት የነበረዉ ዝምታ ተገፈፈ። አይ ልጄ! የኛ ስራኮ መምረጥ ብቻ ነዉ፤ ህዝብ የሰጠዉን ድምጽ ቆጥሮ ዉጤቱን የሚነግረን መንግስት ነዉ አሉት እናቱ እግራቸዉ ወደ ኩሺናዉ እየቀደመ። እንዴ!  መንግስት ድምጽ ቆጥሮማ እንዴት ተቃዋሚዎች ያሸንፋሉ አለ እናቱን ተከትሎ ወደ ኩሺናዉ እየገባ። እናቱና አባቱ አይናቸዉ ሳያስቡት ገጠመና መልሱን በማያዉቁት የልጃቸዉ ጥያቄ ተገረሙ። የተስፋ እናት ባለሙያ ናቸዉ፤ ይሀንን ደግሞ መንደሩ ሁሉ ያዉቀዋል። ኩሽና ዉስጥ እንደገቡ የጀመሩት ጥብስ ቤቱን አዉዶታል በእርግጥም የጥብሱ ሽታ እንኳን የተራበ ሆድ በልቶ የጠገበን አንጀትም ያስጎመጃል፤ ልጃቸዉ ተስፋ ግን የራበዉ ምግብ ሳይሆን የምርጫዉን ዉጤት ማወቅ ነበረና ሁሉንም ነገር ትቶ ከቴሌቪዥኑ ጋር ተፋጥጦ ቁጭ አለ።
(ክፍል 2 በሚቀጥለው ሳምንት ይቀርባል)

No comments:

Post a Comment