በዲ/ን ኒቆዲሞስ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ እያለን ነበር በመጀመሪያ ጊዜ ከበዕውቀቱ ሥራዎች ጋር የተዋዋኩት፡፡ በወቅቱ ካልተሳሳትኩ በዕውቀቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ዋናው ካምፓስ ተማሪ እያለ ‹በራረሪ ቅጠሎች› በሚል ርዕስ ከደርዘን የሚልቁ ጣፋጭና አከራካሪ ወጎችን በአንድ ላይ ጠርዞ ለአንባብያን ያቀረባቸው መጣጥፎቹ በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅነትንና ተደናቂነትን እንዲያተረፍ አድርጎት እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በዚህ መጽሐፉ በዕውቀቱ በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መካከል ያለውን የዘር ሽኩቻ፣ የርዕዮተ ዓለም ቅኝት፣ የዘመኑን የብሔር ፖለቲካዊ ቀውስ፣ ተማሪዎች ዶርም ያለውን አስቂኝ፣ አዝናኝና አሳዛኝ ገጠመኞችን- ራሳችንን በቅጡ እንድናይና ቆም ብለን እንድጠይቅ የሚያደርጉን መረርና ከረር ያሉ እውነቶችን ከቀልድና ከተርብ፣ ከአሽሙርና ከአግቦ ጋር እያዋዛና እያዛነቀ የተረከበት መጣጥፎቹ አሁንም ድረስ በብዙዎች በናፍቆት ተደጋግመው የሚነበቡ ናቸው፡፡
በዕውቀቱ በእነዚህ ጽሑፎቹ የአገራችንን ታሪክ የሞገተባቸው፣ የወቅቱን የአገራችንን ፖለቲካ ንቅዘት፣ የባህል ወረራውን በየፈርጁ የተቸበት፣ የሕይወቱን ፍልስፍና የገለጸበት፣ በሃይማኖትና በሃይማኖተኞች ላይ የተሳለቀባቸው አፈንጋጭና ጎናጭ መጣጥፎቹ ይነሣሉ፡፡ ለዛሬም ለዚህ ጽሑፌ መነሻ የሆነኝ በዕውቀቱ ሥዩም ከዓመታት በፊት በ‹በራሪ ቅጠሎች› እና በቅርቡ ደግሞ ባሳተመው ‹ከአሜን ባሻገር› በሚለው መጽሐፉ ላይ ኢትዮጵያዊቷ ንግሥተ ሳባ/አዜብ/ማክዳ ጥበብን ፈልጋ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገችውን ታሪካዊና መንፈሳዊ ጉዞ መነሻውና መድረሻው የወሲብ ረኻብ/ናፍቆት የወለደው አስመስሎ ያቀረበበት ትርከቱንና እንዲሁም በአለፍ ገደም በኢትዮጵያ ቤ/ን ታሪክና ትውፊት ላይ በስላቅና በትችት ያነሣውን ሐሳቡን ፊትለፊት ለሞግተው ወደድኹ፡፡
በዕውቀቱ በ‹በበራሪ ቅጠሎች› መጽሐፉ ንግሥተ ሳባን በተመለከተ እንዲህ ነበር ያለው፡፡ ‹‹… እንደው የሆነስ ሆነና በሐበሻ ምድር ሰለሞንን የሚያስንቅ ወንድ ጠፍቶ ነው ንግሥተ ሳባ ወንድ ፍለጋ ያን ሁሉ ኪሎ ሜትር አቋርጣ ወደ ኢየሩሳሌም- ንጉሥ ሰለሞን ድረስ የተጓዘችው …?!›› ቃል በቃል እንደጠቀስኩት እርግጠኛ ባልሆንም ፍሬ ሐሳቡ ግን ይኸው ነው፡፡ በዕውቀቱ በተመሳሳይም በቅርቡ ባሳተመው ‹ከአሜን ባሻገር›› በሚለው መጽሐፉ ላይም የንግሥተ ሳባን ጉዞ በተመለከተም የንግሥቲቷን ጉዞ መቋጫው ‹‹የአልጋ ላይ የፍቅር ጨዋታ›› ረኻብ አስመስሎ ሊያቀርበው ሞክሯል፡፡
በአክሱም ከተማ ከሚገኙ ሆቴሎች ባንዱ ያየኹት የንግሥተ ሳባ ሥዕል አሁንም ይመጣብኛል፡፡ … እንደላላ አምፖል ካፎቱ ለመውደቅ በቋፍ ላይ ያለ ትልልቅ ዓይን ያላቸው አጃቢዎች ተከተሏታል፡፡ ንጉሥ ሰለሞን ፈገግ ብሎ እየጨበጠ ይቀበላታል፡፡ ለነገሩ ማታ የሚያደርገውን ሲያስብ ፈገግ ማለት ሲያንሰው ነው፡፡›› ይለናል፡፡ እንግዲህ ይህ በዕውቀቱ በደረሰበት የታሪክ መረዳትም ሆነ ምርምር፣ አሊያም ደግሞ የሥነ ልቦና ዕውቀት ንግሥተ ሳባ የሰለሞንን ቤተ መንግሥት በረገጠች ቅጽበትና ንጉሥ ሰለሞንም ያችን አፍሪካዊት ዕንቁ፣ ጥቁር፣ ውብ ሳባዊት ንግሥት ማክዳን ባያት በዛች ልዩ አጋጣሚ- በሁለቱም ልብ ውስጥ የነደደው፣ የተንቀለቀለው በውስጣቸው የተዳፈነው የፍትወት ስሜት ወይም በአራዳዎቹ አገላለጽ ‹የወሲብ ሀራራቸው› እንደኾነ ሊያሳምነን ይሞክራል፡፡
በዕውቀቱ በዚሁ ‹‹ከአሜን ባሻገር›› ሥራው አብዮተኛ ወዳጁን ተመስገንን በዘከረበት ጽሑፉ ለወሲብ ያለውን አመለካከት/ፍልስፍና እንዲህ ገሃድ አውጥቶታል፡፡ ከወንድማዊነት ቁጭትና መቆርቆር በሚመስል ስሜት ለተመስገንና ለመጽሐፉን ተደራሲያን ወንድማዊ ምክሩን እንዲህ በማለት አጋርቶናል፡፡ በዕውቀቱ ተመስገን በርግጠኝነት እንደሚታሰር ከውስጠ አዋቂ መረጃ እንደደረሰው ከገለጸለት በኋላ፣
‹‹… ወዳጄ እንግዲህ የፈራኸው የመከራ ቀን ኮተተት እያለ እየመጣ እንደሆነ ሳይገለጽልህ እንዳልቀረ እገምታለኹ፡፡ እናም አብዮተኛው ወንድሜ ከመታሰርህ በፊት ለምትወዳት ልጅ ደውልላትና ተዝናና፣ ዓለምህን ቅጭ …፡፡›› ሲል ወንድማዊ ምክሩን ለግሶታል፡፡ እንግዲህ በነገታው እግረ ሙቅ ለሚጠብቀው ወዳጁ፣ እንደ መልካም ወዳጅ በደጁ ከሚጠብቀው መከራ በፊት ይህን ያንዣበበበትን የመከራ መርግ ለጊዜውም ቢሆን ፈጽሞ እንዳያስበውና፣ ሁሉን አስረስቶ ፍጻሜ የሌለው ወደሚመስል የደስታ ባሕር ሊከተው የሚችለው መፍትሔውና የመጨረሻው ደስታው ‹‹ከሚወዳት ልጅ ጋር አንሶላ ሲጋፈፉ ማደር›› መሆኑን በዕውቀቱ ለሚወደው ወዳጁ አበክሮ ሲነግረው እናነባለን፡፡
በዕውቀቱ በሌላኛው ትረካውም በጠራራ ፀሐይ ወሲብ እንደ ሸቀጥ በሚቸረቸርባት በአሜሪካዋ በላስቬጋስ ከተማ ቆይታው በኋላ ይህችን ከተማ ‹‹አትጠገብም፣ ትጣፍጣለች›› በሚሉ ውብ ቃላት ነው ሊገልጽልን የሞከረው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ከሃይማኖታችን፣ ከኢትዮጵያዊ ባህላችንና ትውፊታችን ያፈነገጠ የበዕውቀቱ ለወሲብ ያለው ይሄ አፈንጋጭ አመለካከቱ እንዴት በልቡ ሊሰርጽ እንደቻለም እንዲህ ሲል ያወጋናል፡፡
በዕውቀቱ ይህ ለወሲብ ያለውን አፈንጋጭ ሐሳቡን ባስነበበት ‹‹ከአሜን ባሻገር›› መጽሐፉ የሦስተኛ ዓመት የሳይኮሎጂ ተማሪ እያለ ‹‹The Future of an Illusion›› የተባለውን የሲግመንድ ፍሮይድን መጽሐፍ ካነበበ በኋላ ከሃይማኖት ጋር ፍቺ እንደፈጸመ በዚሁ መጽሐፉ ውስጥ ይነግረናል፡፡ እናም ባጭር ቃል በዕውቀቱ ኢ-አማኒ ነው ማለት ነው፡፡ በዕውቀቱ ሥራዎቹን አብዝቶ የሚያደንቅለትና ከነገረ ሃይማኖት ሰላማዊ ፍቺ እንዲፈጽም የረዳው ሲግመን ፍሮይድ ወሲብን በተመለከተ ያራምድ የነበረው እሳቤው ደግሞ በዕውቀቱ የተለያዩ ጽሑፎቹ ውስጥ በጉልህ ሲንጸባረቅ እናያለን፡፡
በዕውቀቱ አብዝቶ የሚያደንቃቸው እንደ ሲግመን ፍሮይድና የወሲብ አብዮት የሚለውን ዝነኛ ስያሜ እ.ኤ.አ. በ1945 ላስተዋወቀው ቪልኽም ሪች ላሉ ምሁራን ከሞላ ጎደል ወሲብ የሕይወት ሁነኛ አስጨናቂ ጥያቄ አድርጎ የሚበይንና ወሲብ የብዙ ነገር መንሥኤ በመሆኑ ከሕሊና ጓዳችን አርቀን መደበቅ የለበትም የሚል እሳቤን ሲያቀነቅኑ የኖሩ ምሁራን ናቸው፡፡ ፍሮይድ ለሥነ-ልቡና ዐውድ ያሻገረው ጠቃሚ ዕውቀት የለም ብሎ መከራከር ፈፅሞ የማይቻል ነው፡፡ ምንም እንኳን ፍሮይድ ለአያሌ የሥነ-ልቡና መርማሪዎች አመቺ መንገድ መጥረግ የቻለ ቢሆንም ቅሉ እጅግ በርካታ ‹ወፈፌ› ሳይንቲስቶችን በማፍራት፣ ማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ የሞራል ቀውስንና የመንፈስ መራቆትን በጥልቀት መትከል የቻለ የነገረ ወሲብ መርማሪ ነው፡፡
ፍሮዳይኒዝም በበርካታ ሥራዎቹ ሙሉ በሙሉ የሚያስተምረው ራስን ያለልክ መውደድን ነው፡፡ ሃይማኖትን አለመከተል፣ እግዚአብሔርን አለመቀበል፣ ባህልን አለመጠበቅ፣ ወሲብን ለእርካታ ብቻ መጠቀም፣ የገዛ እናትን ለወሲብ መመኘት፣ የገዛ ወላጅ አባት እንዲሞት በጥልቅ መሻት የመሳሰሉት እሳቤዎች የፍሮይድ አስተምህሮ የማዕዘን ድንጋይ ናቸው፡፡ ለፍሮዳዊያን ወሲብ እንቅልፍ ማምጫ እንጂ ከአብሮ መቆየት፣ ከቅዱስነት፣ ዘርን ከማስቀጠል፣ ሓላፊነት ከመውሰድ ጋር ፈፅሞ አይገናኝም፡፡
በሃይማኖትም ኾነ በሞራል አስተምህሮ መሠረት ወሲብ/የግብረ ሥጋ ግንኙነት በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መኻል ያለ፣ የነበረ እንዲሁም በቀጣይነት ሊኖር የሚገባው መተሳሰብ፣ መቻቻል፣ መፈቃቀር … ወዘተ በጠንካራ ትዳር እንዲታሰርና የሰው ልጅ ዘሩን ጠብቆ እንዲኖር ያስቻለ ቅዱስ ግንኙነት እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በዕብራውያን መልእክቱ፣ ‹‹መጋባት በኹሉ ዘንድ ክቡር መኝታውም ንጹሕ ይሁን፤ ሴሰኞችንና አመንዝሮችን ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል፡፡›› ይላል፡፡
በርግጥም ወሲብ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ የተጫወተው ሚና ላቅ ያለ ለመሆኑ እማኝ አያሻውም፡፡ ይሁንና ዛሬ ላይ ፍተወተ ሥጋን ለመቀስቀስ ሲባል በመንፈስ ልዕልና የተቀመረው የወንድና የሴት ግንኙነት ‹‹ቀስቃሽ (sexy/hot) ነች ወይስ አይደለችም?›› ወደሚለው የላሸቀ የዳሌና ጭን አስተሳሰብ ዝቅ እንዲል መደረጉ በሂደት ፍፁም የመከነ ትውልድ እንድንጥለቀለቅ እያደረገን እንደሆነ እየታዘብን ነው፡፡ በርካታ የዓለማችን የመገኛኛ ብዙኃን፣ ኢንተርኔቱ፣ ሶሻል ሚዲያውና የፊልም ኢንዱስትሪውም በደረሱበት ኹሉ ይሄንኑ የሞራል ቀውስና የመንፈስ መራቆት በመትከል ላይ ይገኛሉ፡፡
ወደፍሮይድ የነገረ ወሲብ አስተምህሮ/ፍልስፍና ስንመለስም ለፍሮይድና ለተከታዮቹ ወሲብ ሁሉም ነገር ነው፡፡ ለወቅት፣ ለዕድሜና ለአእምሮ ኹናቴ የማይገዛ የህልውና ምሰሶ፡፡ በእርሱ እምነት ደመነፍሳዊ የወሲብ መሻት ይጨቆናል እንጂ ለአመል ያህል እንኳን አይለዝብም፣ አይደበዝዝም፡፡ ይህ የተቸከለ አስተሳሰብ ሲግመን ፍሮይድን ሲያጠቃ የኖረ ‹‹በሽታ›› ነው፡፡ እናም እነዚህ የ20ኛው መቶ ክ/ዘ ቀንደኛ የወሲብ አብዮት እንቅስቃሴ/Sexual Revolution አራማጅ ለሆኑት የእነ ሲግመን ፍሮይድና ቪልኽም ሪች አድናቂ ለሆነው ለበዕውቀቱ ይህ ከምንምና ከሁሉም በፊት ወሲብ የሚለውን የተጋነነና አፈንጋጭ የሆነ አመለካከት ቢያራምድ እብዛም የሚያስደንቅ አይመስለኝም፡፡
እናም በዕውቀቱ ይህ ለወሲብ ያለው መስመር የለቀቀ የሚመስል አመለካከት በጥበብ ፍቅር ወድቃ፣ ሕዝቧን፣ አገርዋን፣ ዙፋኗን ጥላ ወደ ኢየሩሳሌም የተሰደደችውን የንግሥተ ሳባን ታሪካዊና መንፈሳዊ ጉዞዋን ወሲብን ለመሸመት ያደረገችው ተራና መናኛ ጉዞ እንደሆነ አድርጎ ሊያሣየን የደፈረው፡፡ እኛ ግን የንግሥተ ሳባ/አዜብ/ማክዳ ጉዞ- ከታሪክ አጣቅሰን፣ ከቅዱሳት መጽሐፍት አመሳክረን ዓላማው በፍጹም፣ በጭራሽ የወሲብ ረኻብ የወለደው እንዳልነበረ እንዲህ እንሞግተዋለን፡፡
ጥበብን ሽታ፣ ጥበብን ተጠምታ፣ የልቧን ምስጢር ሁሉ ልታጫውተውና እንቆቅልሽዋንና የነፍሷን ጥያቄም ሁሉ ይፈታላት ዘንድ ከምድር ዳርቻ በብዙ ስጦታዎችና አጀብ ወደ ኢየሩሳሌም የተጓዘችው ንግሥተ አዜብ/ሳባ የኢትዮጵያ ንግሥት እንደነበረች የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ሊቃውንቶች ያስረዳሉ፡፡ ይህችን የጥበብ ርሃብተኛ የአክሱምን ንግሥት ሌትና ቀን እረፍት ነስቷትና ነፍሷን አስጨንቋት፣ ባሕር ተሻግራ፣ ድንበር አቋርጣ በጆሮ የሰማችውን በዓይኗ አይታ ለማረጋገጥ በመፈለግ ወደ ኢየሩሳሌም እንድትገሠግሥ ያደረጋት ምስጢር አንድና አንድ ነገር ብቻ ነበር፡፡ እርሱም ዓለም ሁሉ ጉድ የተሰኘበትና የተደነቀበት- ከእርሱም በፊት ከእርሱም በኋላ ያልሆነ የእስራኤል አምላክ ‹ያሕዌ› ለሰለሞን የሰጠው ታላቅ ‹ጥበብና ማስተዋል› ነበር፡፡
ይህን ዓለም ሁሉ ዕፁብ ድንቅ በማለት ዝናውን በአጥናፈ ዓለም ሁሉ የናኘለትን የሰለሞንን ጥበብ ከጆሮ ባለፈ በዓይኗ ልታየውና ልትደነቅበት አክሱማይቷ፣ የእኛይቷ የጥቁር ምድር እንቁ በልቧ ወሰነች፡፡ እናም ንግሥት በልቧ እንዲህ ያለች ይመስለኛል፡- ‹‹ይህ በዝና፣ ‹በስማ ብለው› ብቻ በሩቅ የሚሳለሙት ሣይሆን በአካል ተገኝቶ ጆሮ ሊሰማው፣ ዓይን ሊያየው የሚገባ ድንቅ ጥበብ ነው…፡፡›› እናም የነፍሷን ናፍቆት፣ የጥበብ ረሃቧን መፍትሔ ለመስጠት ንግሥት ቆርጣ ተነሳች፡፡
ንግሥትን ከዚህ ውሳኔዋ ሊያስቆማት የሚችል አንዳች ምድራዊ ኃይል አልነበረምና፡፡ እናም የተመኘችውንም አደረገችው፡፡ ውሳኔዋ ተግባራዊ ሊሆን ያን ቅዱስ ቀን መጣ፤ በጥበብ ፍቅር ልቧ የነደደ፣ ነፍሷ የተመኘችውን እስክታገኝ እረፍት እምቢ ያላት ያቺ ገናና ልዕልት የከበረ ቤተ-መንግሥቷን ጥላ፣ ከሠራዊቷና ከሕዝቧ ተነጥላ ትመንን ዘንድ የጥበብ ፍቅር ግድ አላት፣ እናም ጉዞ ጥበብን ፍለጋ … ጉዞ ጥበብን ሐሰሳ … ‹መንገዶች ሁሉ ወደ ኢሩሳሌም ያቀናሉ!› ስትል ለነፍሷ ጮኻ ተናገረች፡፡
ይህ ታላቅና ታሪካዊ የሆነ ጥበብን ፍለጋ፣ ጥበብን ሐሰሳ የንግሥት ሳባ ጉዞ፡- ተራ ጉዞ፣ አልባሌ መንገድ አልነበረም፡፡ የነፍስ ጩኸት፣ ጥልቅ የሆነ ከልብ የመነጨ፣ የዘመናት ናፍቆት የታከለበት የጥበብን ፍለጋ ጉዞ- የከበረና ከጉዞዎች ሁሉ የላቀ ልዩ ጉዞ እንጂ፡፡ እናም በኋለኛው ዘመን የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነ፣ የአብ ክንዱና ኃይሉ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የአክሱማይቷን የጥበብ ርሃብተኛ ተጓዥ እንዲህ ሲል አወደሳት፣ ዘከራትም፡፡ ‹‹ንግሥተ አዜብ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነስታ ትፈርደበታለች፣ የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳርቻ ድረስ መጥታለችና፡፡››
‹‹ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል፤ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም፡፡ … ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ፡፡ … ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች፤ የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፣ እነሆም ከሰለሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ፡፡›› ማቴ ፲፪ ፣ ፴፰-፵፪፡፡
በእርግጥም የዚህች ኢትዮጵያዊት ንግሥት የጉዞዋ የመጨረሻ አድራሻ ለጊዜው ሰለሞን ቢሆንም ፍጻሜው ግን የሰለሞን የጥበብና የማስተዋል ምንጭ የእግዚአብሔር ጥበብ፣ የአብ ክንዱና ኃይሉ የሆነው እርሱ በነቢያት ትንቢት እንደተነገረለት፣ ሱባኤ እንደተቆጠረለት በዘመኑ መጨረሻ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሊሆን የፈቀደው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር፡፡ ኢየሱስም በመዋዕለ ስበከቱ ለተከታዮቹ፣ ለደቀ መዛሙርቱ ለብቻቸው እንዲህ ብሎአቸው ነበር፡-
‹‹የምታዩትን የሚያዩ ዓይኖች ብፁዓን ናቸው፡፡ እላችኋለሁና፣ እናንተ ዛሬ የምታዩትን ብዙዎች ነቢያትና ነገሥታት ሊያዩ ወደዱ አላዩም፣ የምትሰሙትን ሊሰሙ ወደዱ አልሰሙም አለ፡፡›› (ሉቃ. ፲፣፳፫-፳፬፡፡) የእኛዋ ንግሥተ ሳባ ያን ታላቅ ጥበብ፣ ያን ዕፁብ ጥበብ፣ ያን ሕያው ጥበብ፣ ያን ዘላለማዊ ጥበብ… እንደቀደሙ የአይሁድ አባቶች- እንደእነ አብርሃምና ሙሴ በናፍቆት በዓይነ ኅሊናዋ አሻግራ እያየችው በሩቅ የተሳለመችው ይመስለኛል ይህች የጥበብ ርሃብተኛ፣ ይህች የጥበብ ስደተኛ፣ የጥበብ ረሃብና ናፍቆት ልቧን ያጀገናት ኢትዮጵያዊ ንግሥት፡፡
እናም የዚህች ታላቅ ንግሥት ይህ የከበረ ጉዞዋ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እንዲጻፍላት ሆነ፡፡ ልጅነትና ክብር፣ ኪዳንም የሕግም መሰጠት፣ የመቅደስም ሥርዓት፣ የተስፋውም ቃል ለእነርሱ የሆኑ አይሁዳውያኑ ግን ለዘመናት አባቶቻቸው ሊያዩ የተመኙትን፣ በሩቅ ሆነው የተሳለሙትን፣ ሱባኤ የቆጠሩለትን፣ በናፍቆትና በስስት የጠበቁትን- በሥጋ የተገለጠውን ያን ዕጹብና ታላቅ ጥበብ፣ የእግዚአብሔርን ሕያው ልጅ ክርስቶስን ሊቀበሉት አልወደዱም፡፡
አባቶቻቸው በብዙ ናፍቆት የጠበቁትንና የጓጉለትን ይህ ጥበብ፣ ይህ ዘላለማዊ ፍቅር በዓይናቸው ፊት ክብርና ሞገስን አላገኘም… እናም ሊያስወግዱት ወደዱ፡፡ ‹‹ወደገዛ ወገኖቹ መጣ ግን የገዛ ወገኖቹ አልተቀበሉትም፡፡›› እንዲል ቅዱስ መጽሐፍ፡፡
እነዚህ የጻድቁን መምጣት አስቀድመው ትንቢት የተናገሩትን አባቶቻቸውን ነቢያትን ያሳደዱና የገደሉ አንገተ ደንዳና ሕዝቦች በኋለኛው ዘመንም ሊቀበሉት ያልወደዱትንና የገፉትን አስቀድማ ግን በንጉሥ ሰለሞን ልዩ ጥብበና ማስተዋል ውስጥ ያየችውንና የተሳለመችውን የእስራኤልን ቅዱስ፣ የፍቅርን አምላክ የጥበብን ጌታ- ኢየሱስ ክርስቶስን የአብራኳ ክፋይ፣ የጥቁር ምድሯ ትሩፋት- የንግሥት ህንደኬ ባለሟል የሆነው ኢትዮጵያዊው ጃንደረባው ያን ጥበብ፣ ያን ዘላለማዊ ፍቅር፣ በሥጋ የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ልጅ፣ ‹ጥበብ› ኢየሱስ ክርስቶስን በሐዋርያው ፊሊጶስ አማካኝነት በታላቅ ሐሴትና ደስታ በጥምቀት፣ በፍጹም እምነት ተቀብሎ የእናት ምድሩን ጥበብን ፍለጋ የዘመናት ጉዞ የታሪክ ምዕራፍ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ዘጋው፡፡
ንግሥተ ሳባ በሩቅ ሆነና በሰሎሞን ውስጥ በናፍቆት ያየችውና የተሳለመችው፣ ወደ ሀገሯና ሕዝቧ ስለመጣው መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ- ታላቅ ማዳን፣ ሕያው ጥበብ ከሰማይ ሠራዊት ከቅዱሳን ከመላእክቱ ጋር በሰማይ በአንድነት ታላቅ ሐሴትንና ደስታን ያደረገች ይመስለኛል፡፡ ለምን ቢሉ የእርስዋ የዘመናት ናፍቆት የሕዝቧም ናፍቆት ነበርና፡፡ በሩቅ የተሳለመችውን ያን የእግዚአብሔርን ቅዱስ ልጅ፣ የዳዊትን ልጅ፣ የቅድስት ድንግል ማርያምን ልጅ፣ ‹የሰው ልጅ› ተብሎ የተጠራው ኢየሱስ ክርስቶስ በኢትዮያጵያዊው ጃንደረባ በእምነት መታዘዝ ምክንያት ምድራችንን ቀድሷታል፣ ባርኳታልና!! አስቀድሞም በእስራኤላዊው በንጉሥ ዳዊት የተተነበየው ‹‹ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር፡፡›› የሚለው የመዝሙረኛው ትንቢትና የንግሥተ ሳባ የዘመናት የሩቅ ሕልምም በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ፍፃሜውን አገኘ፡፡
በእውነትም ጥበብን የመሻትና የመጠማት የኢትዮጵውያን ብርቱ የነፍስ ጩኽትና ፍላጎት ዘመናትን የሚሻገር ታሪክ ያለው እንደሆነ ቅዱሳት መጻሕፍትም ሆነ ሌሎች በዓለማችን የሚገኙ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ የታሪክና የፍልስፍና መጻሕፍቶች እማኝነታቸውን የሰጡበት እውነታ ነው፡፡ በተለምዶ ‹‹የታሪክ አባት›› ተብሎ የሚጠቀሰው ግሪካዊው ሄሮዱተስ የዓለምን ታላላቅ ሕዝቦችን የስልጣኔ ታሪክ በጻፈበት መጽሐፉ፡- ‹‹ኢትዮጵያውያን ጥበብን የሚያፈቅሩ፣የጥበብና የእውቀት ሰዎች፣ ምድራቸውም በተፈጥሮ ሀብት የበለጸገ፣ ለጤና ፈውስ በሆኑ የተፈጥሮ ምንጮችንና ወንዞችን የታደሉ ታላቅ ሕዝቦች ናቸው… ፡፡›› ሲል በአድናቆት ጽፏል፣ መስክሯል፡፡
በመጨረሻም … ግን …ግን … ጥበብን አፍቃሪው በዕውቀቱ ሥዩም ጥበብን ፈልጋ፣ ጥበብን ሽታ ዙፋኗን ጥላ የተሰደደችውን የጥበብ ምርኮኛ- የኢትዮጵያዊቷን ንግሥት የሳባን ጉዞ ለምን እንዲህ አብዝቶ ከአልጋ ላይ የፍቅር ጨዋታ/ከወሲብ ጋር ብቻ አያይዞ ሊተርከው ፈለገ ወይም ወደደ …?! እኛ ግን ከታሪክ አጣቅሰን፣ ከቅዱሳት መጽሐፍት አመሳክረን የንግሥተ ሳባ/አዜብ/ማክዳ ጉዞዋን በተመለከተ በዕውቀቱ እንደመሰለው ዓላማው በፍጹም፣ በጭራሽ የወሲብ ረኻብ ወለደው እንዳልነበረ እንዲህ እንሞግተዋለን፡፡ አበቃሁ!
ሰላም!
No comments:
Post a Comment