Translate

Wednesday, February 3, 2016

ሰውየው ---ብርሃኑ ነጋ ( ሄኖክ የሺጥላ )


አጭር ፍቅር
ሰውየው ሕልም አለው ። የአንደበቱ ርትዖነት ካለው የቃላት አጠቃቀም እና ልቀት ሳይሆን የሚመነጨው ከሃሳቡ ጠጣርነት እና ከቆመለት ትልቅ እውነት እንጂ !
ሰውየው ሕልም አለው ፣ ለዚያውም በሞቀ ቤት እና በቀዘቀዘ ቢራ ውስጥ በሚደረግ የሳይበር ጦርነት የሚጸና ሳይሆን ፣ የማሽላ እንጀራ እየበላ አፈር ላይ እየተኛ ፣ ከእባብ እና ገጊንጥ ጋ እየተታገለ ፣ በሞርታር እና በፈንጂ ወረዳ ውስጥ ውድ ነብሱን አቁሞ የሚሞትለት እጹብ ሕልም ።

ሰወየው ትሁት ነው ፣ የትልቅነት ሚስጥሩ ምን እንደሆነ የገባው ትሁት ። ሕልሙ ባለ ወፍራም ቆዳ ያደረገው እንደራሴ ፣ አላማው ለትንንሽ ነገሮች እና በትንንሽ ነገሮች ከማኩረፍ እና ከመኮፈስ ነጻ ያወጣው የኔ ዘመን በትረ አሮን ። በግልምጫ እና በእርግጫ ፖለቲካ ውስጥ ሊባክን የሚችል ታል-ኢት ( የሰኮንድ ግማሽ ) የሌለው ሰው ። ሰውየው አፋር ነው ሃገሩ ፣ ጎጃሜም ነው ፣ በኦሮሞነቱ አይታማም ፣ ጥርት ያለ ጉራጌ ነው ፣ ዘሩን የቆጠሩ ሱማሌ ስለመሆኑ ይናገራሉ ፣ አብረውት ያደጉት እና በቅርብ የሚያውቁት ስለመንዜነቱ የሚያውቁትን ሁሉ ሳይደብቁ ያወራሉ ፣ እርግጥ ሰውየው ኢትዮጵያዊ ነው ። ማነስ አይችልም ፣ በጎጥ እና በጎሳ ፣ በአውራጃ እና ወረዳ ፣ ተቆርሶ እና ተሰባብሮ የሚነገር ማንነትም ሆነ ፣ የሚቆጠር ደም የለውም ። ሕሉሙ ከደሙ ጋ አንድ አይነት ነው ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊ እና ዘረ ኢትዮጵያዊ ፣ ሰወየው !
ስለ ሰውየው ሳስብ ኩራት ይሰማኛል ፣ ምክንያቱም ኢትዮጵያዊነት እንደማይሞት ምሳሌ ሆኗልና ፣ ቃሉን አላጠፈምና ፣ የሚኖርለት ሰው ባይኖር እንኳ የሚሞትለት ክብር እና ነጻነት ያለው ስለሆነ ። በቅርቡ ዋሽንግተን ዲስ ባደረገው ንግግር " እዚህ ውስጥ ብዙ የማውቃችሁ ጓደኞቼን ወዳጆቼን አይቻለሁ ፣ ሁሌ አስባችሗለሁ ፣ ላናንተ ብዬ ግን ከምሄድበት አልቀርም " የምትለዋን ሐረግ ድግሜ ደጋግሜ አደመጥኩ ፣ በእድሜ የሱ እኩዮች የሆኑ ፣ እንደሱ ወይም ከሱ በላይ የተማሩ ፣ ሀገር ሀገር የሚሉ ግን አንዳች ቁም ነገር ያለው ሥራ መስራት ያልቻሉት ወዳጆቹ ምን ይሰማቸው ይሆን ? እነዚህ በጥላቻ እና በማጥላላት የፖለቲካ ቁማር የሰከሩ << የፖለቲካ ቁሞ ቀሮች >> ወይም ዊዶዎች ይህንን ሲሰሙ ምን ይሉ ይሆን ?
እርግጥ ይህንን ጽሑፍ ከምታነቡት ሰዎች ውስጥ ኣንዳንዶቻችሁ እያሽቃበጥኩ ሊመስላችሁ ይችላል ። አልተሳሳታችሁም ፥ ኣዎ እያሽቃበጥኩ ነው!! ሰው እንኳን ለብርሃኑ ነጋ ለወያኔ ያሽቃብጥ የለ ?! ታዲያ ምን ሽግር ኣለው ?
ሺዎች ከጎንህ ነን ። ከጎንህ ያቆመን ደሞ የቆምክለት አላማ ነው !
ሄኖክ የሺጥላ

No comments:

Post a Comment