(ዘ-ሐበሻ) የኦሮሞ ሕዝብ እንቅስቃሴ 4ኛ ወራት እያስቆጠረ ነው:: ቀደም ሲል የኦሮሞ ሕዝብ ቁጣ እየተቀጣጠለ ሲሄድ ክልሎ ከኦህዴድ አስተዳደር እጅ ወጥቶ በቀጥታ በሕወሓት መሪዎች; የደህነነት ኃይሎች እና ወታደሮች እንዲመራ መደረጉን ዘ-ሐበሻ በተደጋጋሚ ስትዘግብ ነበር::
ሕወሓት ክልሉን በደህንነት እና በወታደሮች እንዲመራ ቢያደርግም ምንም ዓይነት መፍትሄ ሳይመጣ ይበልጡኑ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ከማስተር ፕላኑ አልፎ ወደ ሰብ አዊ መብቶች እና እስከ ነፃነት ጥያቄ ተሸጋግሯል:: በአንዳንድ ከተሞች እንደውም የኦህዴድ ባንዲራዎች በኦነግ ተተክተው መታየታቸው የሚታወስ ነው::
እስካሁን 4ኛ ወሩን ባስቆጠረው የኦሮሞ ሕዝብ አመጽ ከ200 ሰዎች በላይ መገደላቸውን የሰብ አዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይናገራሉ:: የሕዝቡ ቁጣ አሁንም ያስፈራው ሕወሓት የሚመራው መንግስት ዛሬ በኦሮሚያ በግልጽ የወታደራዊ አስተዳደር አውጇል:: በዚህም መሠረት ክልሉን በ8 ቀጠናዎች በመከፋፈል በሕወሃት ጦር እንዲመራ ወስኗል::
ይህ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ተደረገ በተባለው የሕወሓቶች እና የድህነነቶች ስብሰባ እንደተገለጸው 8ቱን ቀጠናዎች የሚመሩት የሕወሓት አባል የሆኑ የጦር መኮንኖች ናቸው::
ይህን የሕወሓትንና የድህነንቱን ውሳኔ አንዳንድ የኦሮሞ ብሄረሰብ ተወላጅ የሆኑ የመከላከያ አባላት ቢያወግዙትም “ኦነጎች ናችሁ” እየተባሉ እንደተሽሟጠጡና ሃሳባቸውም በሕወሃት ሰዎች ተቀባይነት እንዳላገኘ ተገልጿል:: እንደዘ-ሐበሻ ምንጮች ገለጻ በሠራዊቱ ውስጥ ያሉት የኦሮሞ ተወላጆች እየተሰለሉ እንደሆነ በሌላ ሰው እንዲነገራቸው እየተደረገ ይገኛል::
No comments:
Post a Comment