Translate

Saturday, August 24, 2013

የዕርቁ ካርድ እንዳይባክን!! የተደበቃችሁ ተገለጡ!!

(ርዕሰ አንቀጽ)

final move
ወደ ሥልጣን የተጠጉና ለመጠጋት የሚያስቡ ፓርቲዎችና ግለሰቦች እንዲሁም ሥልጣንን የተቆጣጠሩ ወዘተ በአገራችን ዕርቅ እንዲመጣ ሲመኙ፣ ሲያቅዱ፣ ፕሮግራም ሲያወጡ፣ ዲስኩር ሲሰጡ፣ … ቢያንስ አራት አሥርተ ዓመታትን አስቆጥረናል፡፡ “ብሔራዊ ዕርቅ፣ አገር አቀፋዊ ዕርቅ፣ … ” እየተባለ ሲነገር የሰማነው አሁን አይደለም፡፡ እስኪሰለቸን ሰምተናል። እርቅን ያህል ታላቅ ጉዳይ “የፖለቲካ ሃይሎጋ ሆ” አስመስለው ሲጫወቱበት የቆዩ፣ አሁንም ድረስ “ባገር ሽማግሌነት” ስም የሚቆምሩ የትውልድና ያገር “ችግር ቁልፍ ተወናዮች” እንዳሉ ህዝብ ያውቃል። ለይቶ በስም ይጠራቸዋል።
በአገራችን ከትዳርና መሰል ማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ግጭቶች ሲከሰቱ ተጣዪ ወገኖችን ለማስታረቅ ሽማግሌዎች ይመረጣሉ፡፡ እነዚህ ሽማግሌዎች ተናግረው የሚያሳምኑ፣ ነገራቸው ተቀባይነት ያለው፣ ኅብረተሰቡ የሚያከብራቸው፣ ቃላቸው መሬት ጠብ የማይል፣ ከፍ ያለ የመንፈስ ልዕልና የተጎናጸፉ፣ የተከበሩ፣ እውነተኛና ዋንኛ ዓላማቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ ሰላምና ዕርቅ የማስፈን ብቻ የሆኑ ናቸው፡፡
ይህንን ዓይነቱን አገራዊ ቅርስ ወደ ፖለቲካው በማምጣት ሙሉውን ሃሳብ ሳይሆን ቁንጽል የሆነውን “ሽምግልና እና ዕርቅ” የሚለውን ሃሳብ ብቻ በመውሰድ በርካታ የፖለቲካ ሰዎች የዕርቅን ሃሳብ ሲያራምዱ ቆይተዋል፡፡ እኛም እንጠይቃለን – ለምን አልተሳካላቸውም? መልሱ ቀላል ነው – የዕርቅንና የሽምግልና መስፈርትን ስለማያሟሉ ወይም ማሟላት ስላልቻሉ ነው!!
ሥልጣንና ወንበር በቀን ቅዠትና በሌት ሕልማቸው ዕረፍት የነሳቸው፣ ኅብረተሰቡ ሙሉ እምነት ሊሰጣቸው የማይችሉ፣ የማይታመኑ፣ ከዚያም አልፎ በተደጋጋሚ ቀይ ካርድ የተሰጣቸው፣ እውነትና ሐቅን ይዘው ሳይሆን ቂምንና በቀልን ቋጥረው የተነሱ፣ ሲናገሩ ሕዝብን ሊያሳምንና ሊያቀራርብ የሚችል ሃሳብ ሳይሆን የበለጠ የሚያራርቅና የሚያጨካክን መርዝ የሚረጩ፣ ላመኑበት ዕውነት እስከመጨረሻ የመቆም ወኔ ያላቸው ሳይሆኑ ከየቦታው ለሚወረወርላቸው ቁራሽ የተገዙና ኅሊናቸውን የሸጡ፣ ዕድሜያቸው ዓመታትን ከመቁጠር በስተቀር “ሽማግሌ” ተብሎ ለመጠራት ማዕረግ ያልበቁ፣ ተምረናል፣ አውቀናል፣ ተፈላስፈንበታል ቢሉም ሲናገሩ ግን አፋቸው ደም የሚሞላ፣ … ዝንተዓለም ዕርቅ፣ ብሔራዊ ዕርቅ፣ … እያሉ ቢሰብኩ እንዴት ለሽምግልናና ዕርቅ ሹመት ይበቃሉ? እንዴትስ ሕዝብ አመኔታውን ይሰጣቸዋል?
ስለዚህ የዕርቅ ሃሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ አልሆነም ብቻ ሳይሆን የምንለው መልዕክቱም በትክክለኛ ሰዎች አልተሰበከም፡፡ ወደ ሕዝብ ጆሮ አልደረሰም፡፡ ህዝብ እንዲሰማ አልተደረገም። ሕዝብ እንዲሰማ የተደረገውና የሚደነቁርበት “እንግዴ” የሆነ እርቅ በመሆኑ ችግርን ከማክረር የዘለለ መፍትሄ አላስገኘም። በጉቦ፣ አንጃ በመፍጠርና ድርጅትን በመሰንጠቅ የሚደረጉ መስማማቶች መካን ሆነው ቀርተዋል። ሽምግልናውን ጭምር ያቆሸሸው ኢህአዴግ ቀና ከሆነ አሁንም ተስፋ አለ። ሕዝብ አልተጣላምና!!
ከቀድሞው አለቃቸው በተለየ መልኩ መንፈሣዊ እንደሆኑ የተነገረላቸው ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያምም ሃሳቡን የገለጸን ሁሉ “አሸባሪ፣ አክራሪ፣ …” በማለት ሳይሆን ያነበቡት ቅዱስ መጽሐፍ ባስተማራቸውና አምነዋለሁ በሚሉት መልኩ ታሪክ በመሥራት የኢትዮጵያ ታዳጊ ለመሆን ጊዜው አላለፈባቸውም፡፡ ከአለቃቸው ሞት ብዙ የሚማሩት እንደሚኖር እናምናለን፡፡ ሕዝብ ተመርሮና፣ ስቃይ የዕለት ተዕለት ኑሮው በሆነበት በአሁኑ ወቅት ለማርገብ ያልሞከሩት ውስብስብ ችግር ማሰሮው ተሰብሮ ጂኒው ከወጣ በኋላ የገነቡት “ታላቅ የመከላከያ ሠራዊትም ሆነ የፌዴራል ኃይል” መልሶ ወደ ማሰሮው መመለስ አይችልም፡፡ እናም አቶ ሃይለማርያም ራሳቸውን ለመስዋዕት እስከማቅረብ ድረስ በመሔድ ኢትዮጵያ ላይ የረመጠውን ረመጥ ለማስወገድ የእርቅ ዋጋ እንዲከፍሉ ለማሳሰብ እንወዳለን። እሳቸውና የሚመሩት ኢህአዴግን ጨምሮ ሰላም የሚሹ በርካቶች አሉና እርቅን እንደሚቀበሉ ለማወጅ ይዘጋጁ። አሁን የቀረው አንድ መፍትሔ እርቅ ብቻ ነውና!!
ከላይ ከጠቀስናቸው ሌላ የኅብረተሰብ ክፍሎች ደግሞ አሉ፡፡ የመንፈስ ልዕልናቸው እጅግ ከፍ ያለ፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ መታመን የሚችሉ፣ የአገራቸውን ሰላምና ጸጥታ እንጂ ሌላ ዓይነት የሥልጣንም ሆነ የግልጥቅም የሌላቸው፣ የዕርቅን ሃሳብ ከልባቸው የሚያምኑና ተበድለውም እንኳን ለመጪው ትውልድና ለአገር ጥቅም ሲሉ በደላቸውን ውጠው ልባቸውን ለዕርቅ ክፍት ያደረጉ፣ በእርግጥ ሽማግሌ የሚለው ሥልጣንና ሹመት የሚገባቸው – በዕድሜ ስለበለጸጉ ሳይሆን ሃሳባቸው ጽዱ፣ አመለካከታቸው ቅን፣ ምኞታቸው ግልጽ የሆኑ የአገር ልጆች አሉ፡፡
እንዲህ ዓይነት ሰዎች በተቃዋሚው ጎራ ወይም በሃይማኖት ድርጅት ብቻ ሳይሆን በገዢው ኃይልም ውስጥ አሉ፡፡ “ከአነሳሳችን ኢትዮጵያን እንደዚህ ለማድረግ አይደለም” የሚሉና እስካሁን ከቁጭት ባላለፈ ምንም ሳያደርጉ የተቀመጡ ግን አጋጣሚ የሚጠብቁ አሉ፡፡ የሚደረገው ነገር ሁሉ ያቅለሸለሻቸውና መውጫውን የሚፈልጉ ወይም አስተማማኝ መውጫ ከሚያሳያቸው ጋር ለመሰለፍ ፍላጎት ያላቸው አሉ፡፡
በሁሉም ወገን ያለው ሚዲያ ሰክሮና ሕዝቡንም እያሰከረ ባለበት ባሁኑ ወቅት ዕድል ፈንታ ያልተሰጣቸው ቅን ሰዎች መኖራቸው ሊያስደንቀን አይገባም፡፡ የሃይማኖት መሪዎች ካድሬ በሆኑበትና ወንጌላውያን ለብጣሽ ዳቦ አዳሪ በሆኑበት ዘመን ኢትዮጵያ አሁንም ሃቀኛና ትሁት ሰዎች አሏት፡፡ ለእነዚህ ኢትዮጵያውያን የእኛም ጥሪ ከተደበቃችሁበት ውጡ! ለኅሊናችሁ ተገዙ! ለአገራችሁ የዕርቅን መፍትሔ በመተግበር ከዚህ በፊት ተሰርቶ ያልታወቀ ታሪክ ሥሩ! የሚል ነው፡፡ ለአገራችን የወደፊት ዕጣ የቀረን አንድ የመጫወቻ ካርድ ዕርቅ ነው፤ እንዳይባክን ማድረግ በዓላማው የሚያምኑና ሕዝብ የሚቀበላቸው ሽማግሌዎች ኃላፊነት ነው፡፡ ሕዝብ እንደማይቀበላችሁ እያወቃችሁ እንደማንኛውም የፖለቲካ ፕሮግራምም ሆነ ተሞክሮ ዕርቅን በመሞከር ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ለመልከፍ የምትፈልጉ ሁሉ እስካሁን ያልተሳካላችሁ ለምን እንደሆነ በመመርመር ራሳችሁን ጠይቁ፡፡ከማትደበቁት ህሊናችሁ ጋር በመስማማት ቀናውን ውሳኔ እንድትወስኑ ለመመወከር እንወዳለን።
እናንተ በተለያየ ምክንያት ራሳችሁን ደብቃችሁ ያላችሁ ለዚህ ክቡር ዓላማ በመነሳት አገራችሁን አድኑ፤ ኢትዮጵያን የዕርቅ ተምሳሌት አድርጓትና ደም መፋሰስን በየቀኑ የሚመኙላትን የውስጥና የውጭ ኃይሎች አሳፍሩ! በሽፍንፍን፤ በአዝሃለሁ – ተቀበል አካሄድ፤ ለሥልጣን ባተኮረ ድብቅ ዓላማ፣ … ሳይሆን በእውነትና በፍትሕ ላይ የተመሠረተ ዕርቅ ለአገራችሁ አምጡ፡፡ እንደ አንድ የሚዲያ አካል ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣም ከጎናችሁ ይቆማል፡

No comments:

Post a Comment