አንድ ጊዜ ፈርዶበት መዋሸት የጀመረ ሰው፤ ውሸቱ ሲደጋገምና ሲለምድበት ዋሾው በየቀኑ፤ጥቂት ቆየት ብሎ ደሞ በየሰአቱ፤ ቆየት ሲል ደሞ በየደቂቃው፤ ውሎአድሮም በየሴኮንዱ ካልዋሸ ሱሱ ቀስፎ ይይዘውና ችግር ይፈጠርበታል፡፡ ራስ ምታት ይነሳበታል፡፡ ጩህ ጩህ ዋሽ ዋሽ ያሰኘዋል፡፡በዚህ ሁኔታ ለጥቂት ጊዜያት ከቆየ በኋላ ደሞ ውሸቱ ከመጠን ሲያልፍና አድማጭ ሲያጣ፤ አድማጫ ለማግኘት ሲል ወጪ በማውጣት አድማጮችን
እየጋበዘ ‹‹መተርተሩን ሊጀምር ነው እየተባለ›› እየታማ ያወርደዋል፡፡የሚዋሽበት ቢያጣ እንኳን ሰማይን ተቀዶ ሲሰፋና፤ ዝናብም የጠፋው የተቀደደውን ስሰፋ የዝናቡን መውረጃ በስህተት ሰፍቼው ነው እስከማለት ይደርሳል፡፡ ከዚያም ያልፍና የምን ላውራ በሽታው ስለሚያስቸግረው ውሸት በመፍጠርም ይባዝናል፡፡መዋሸቱ ከቅሌት ይልቅ እንደመልካም ሙያ ሆኖ ስለሚታየው በመዋሸቱ ሊደነቅና ሊከበር ያምረዋል፡፡ ከአድማጭ ባለፈ በዚህ ውሸቱ ሕሊና ያለው ቤተሰብ ካለው፤ ወዳጆች ካሉት፤ ውሸቱን እንዲተው ከመምከርም አልፈው ‹‹ዳግም ብትዋሽ አብረንህ ላንቆም፤ በተገኘህበት ላንኖር፤ በምትውልበት ላንቀላቀል እርም ብለን ልንምል ነው በማለት ማስጠንቀቂያ ይሰጡታል፡፡
አንዲት ሚስት ባሏ ሲዋሽ ለከት የለውምና፤ ተጋብዘው ሲሄዱ በሄዱበት፤ ለቅሶ ለመድረስ ሲሄዱም፤ ሠርግም ላይ በየተገኙበት ሲዋሽ እሷ ሰውነቷ እያለ ቀና እየተሳቀቀች መጠቋቆሚያና እንዲያውም እንደመታወቂያ ባሏ ውሸት መጠሪያዋ እየሆነ ሄደ፡‹‹፡……. እንትናን አጣሃት እንዴ የዚያ የውሸታሙ ሚስት?›› እየተባለች መጠራቷ ሰለቻትና ለባሏ የመጨረሻውን ማስጠንቀቂያ አቀረበች፡፡ ‹‹እኔ ሳውቅህና ለጋብቻም ስንስማማ፤የማውቅህና የምወድህ
ባሌ፤አሁን አሁን ባመጣኸው ጠባይህ ፍቅሬ እየቀነሰ፤ መግባባትም እየጠፋ ነውና፤ለዚህ አዲስ ጠባይህ አንድ መፍትሔ ካልተገኘለት በስተቀር ከእንግዲህ እንዲች ብዬ በምትሄድበት አልሄድም፡፡›› ትለዋለች ባልየውም ለሱ ውሸት ነውር አይደለምና፤በመዋሸቱ ይህ ችግር ሊፈጠር ይችላል ብሎ ባለማመኑ ‹‹ምን አጠፋሁ?›› አለ፡፡ ሚስትም ግርም ብሏት ‹‹ትዋሻለህ፤ በጣም ትዋሻለህ፡፡ አንተ በዋሸህ ቁጥር ደሞ እኔ ተሳቅቄና ያካባቢው ሰው ሁሉ መሳቂያና መሳለቂያ ሁኜ መሄጃ መንገድ አጣሁ፤ በየደረስኩበት ሁሉ ስለአንተ ውሸት ነው የሚወራው›› ትለዋለች፡፡ ባልየውም ምንም እንደማያውቅና እንደማይዋሽ አይነት በመገረም ‹‹እዋሻለሁ እንዴ?›› ይላታል፡፡ ሚስትዬዋም፤ ንዴትም መገረምም በተላበሰ የብስጭት ስሜት ‹‹አዎን ትዋሻለህ፤ በጣም ትዋሻለህ፡፡›› ስትለው ቃል ገባላት በመሃላ፡፡ ‹‹ይቅርታ ከእንግዲህ አልዋሽም፡፡ ድንገት ግን ሳላውቀው መዋሸት ብጀምር አግሬን ረገጥ አድርጊኝ ቶሎ እንዳቆምና ወደፊትም እንዳልዋሽ አደራሽን›› ይላታል፡፡ በዚህ ስምምነት ላይ ደርሰው እያሉ በዚያው ሰሞን አንድ ግብዣ ይጠሩና፤ ሚስትም ማስጠንቀቂያዋን ትሰጥና፤ ባልም ይቀበልና ተያይዘው ወደ ግብዣው ቦታ ይሄዳሉ፡
ግብዣው ላይ ምግቡ ተበልቶ መጠጡ እየተቀዳ ጨዋታው ሲሟሟቅ፤ አቶ ባልም ወደ ጨዋታው ዘው ብሎ ይቀላቀላል፡፡ የሚወራው ደሞ ስለ እባብ አደገኛነትና ከነደፈም ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ ነበርና አጅሬ ዋሾ ጣልቃ ገብቶ ‹‹እኔ ገጠር እያለሁ አንድ እባብ ርዝመቱ በትንሹ 12 ሜትር ይሆናል›› ሲል ሚስትየዋ እግሩን ረገጥ ስታደርገው የገባው ቃል ትዝ አለውና ‹‹ማለቴ 19 ሜትር ይሆናል›› ሲል ሚስት እንደገና ረገጥ ስታደርገው ‹‹ይገርማችኋል ከጭራው ጫፍ ላይ ሆነን ጭንቅላቱን ማየት አልቻልንም ነበር በጣም ረጂም ነው ማለት በትንሹ 21 ሜትር…..›› ሲል ሚስት ብድግ ብላ ጥላው እብስ አለች፡፡ ባልየውም ደላውና ገላማጭ በሌለበት መተርተሩን ቀጠለ ሰዉም ትዝብቱንና ሳቁን ግን እያዳመጡት ጨዋታው ቀጠለ፡፡
አቶ ታምራት ላይኔ የዛሬን አያርገውና ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ፤ ሕዝባዊ ስብሰባ በአማራው ክልል አድርገው እያሉ አንዱ ታዳሚ እጁን ያወጣና ‹‹ክቡር ሆይ ትውልድዎ ከዚሁ አካባቢ ነው ይባላልና እስቲ ግድሙን ይንገሩን ማን ያውቃል ዘመዳሞችስ ብንሆን?
አዎን እዚሁ ግድም ነው ብለው አንድ ወረዳ ይጠራሉ የዚያ ወረዳ ተወላጆች ነበሩና
ያማ የኛው ነው ከነማን ተዋልደው
አይ ትክክል እዚያ ሳይሆን ወደ ጠርዝ ዳር ላይ ነው ወጣ ይላል
ቢሆንስ አንድ ቤተክርስቲያን አይደል የምንስመው? ውሏችንስ አንድ ገበያ አይደል ከነማን
አይ ከወረዳው ወጣ ብሎ ካለው ግድም ነው
ጌታው እንዲያው እቅጩን ካልነገሩን አለያም ከኛ ቀዬ ወጥተው ወደ ሌላ ይሄዳሉ እንጂ ከዚህማ ማረፊያም አያገኙ፡፡ብለዋቸዋል ይባላል፡፡
ውሸት የማያስዋሽ አንዳንድ አለ፡፡ የማያላውስ፡፡ አሁን አሁን ግን አሳፋሪው ቀርቶ ተቀብሎ ዋሺው እየበዛና እየበረከተ፤ እየተቀባበለ የውሸት ፋብሪካ ሼር ተካፋይ መሆን የሚያስመሰግን እየሆነ ነው፡፡ በተለይ አለቃ ከዋሸ የሱን ውሸት እውነት ለማድረግ አፋሽ አጎንባሽ ሁሉ የተቀጠረበትን ሥራ ትቶ የአለቃውን ውሸት በድርጅቱ ውስጥ ባሉት ሁሉ እውነት እንዲባልና ያንን ውሸትም በየንግግራቸው፤ በየውይይታቸው፤ በየጨዋታቸው ሁሉ ጣልቃ በማስገባት ውሸቱን እንዲደጋግሙት ማድረግ ሆኗል ተግባራቸው፡፡ ይሄ ደሞ ያሾማል፤ ያሳድጋል ግን ሹመቱም ሆነ እድገቱ የውሸት መሆኑን ልብ ሊሉት የግድ ነው፡፡
አሜሪካ የሚኖር አንድ ሰው ለጉብኝት ለዘመድ ጥየቃ ይመጣና እድሜ ለተጫናቸው እናቱ መጠኑ ከፍ ያለ ያለ ችግር ሊመለከቱበት የሚችሉት ቴሌቪዥን ገዝቶላቸው ይሄዳል፡፡ በዓመቱ ይሄው ሰው ወደ ሃገር ውስጥ ሲመጣ ለእናቱ የገዛላቸው ያ ትልቅ ቴሌቪዥን መጠኑ እጅግ ቀንሶ፤ የባለ 29 ኢንች የነበረው ወደ 17 ኢንች አሽቆልቁሎ ያገኘዋል፡፡ ገርሞት እናቱን እንደዋዛ አድርጎ፤ ‹‹እማዬ ቴሌቪዥንሽን አይጥ በላው እንዴ? ምነው አነሰብኝ?›› ይላቸዋል፡፡ እናትየዋም ፈገግ ብለው ነገሩ ወዲህ ነው ልጄ›› ይሉታል፡፡‹‹ ለወጥሽው እንዴ እማዬ››ሲላቸው ‹‹እንዴ ምነው ቢቸግረኝ አንተ አለህልኝ በየጊዜው እንደላክህ ነው ታዲያ ለምን ብዬ ነው የምለውጠው›› ይሉታል ውለታ አለመርሳታቸውንም ለማሳወቅ ሲሉ፡፡ ‹‹ታዲያ ምን ነካው?›› ሲሉት ‹‹ውሸት በዛበታ! እነሱ ሲዋሹ እሱ ሲሸማቀቅ፤ ደሞ ሲዋሹ ደሞ ሲሸማቀቅ ይሄው እንዲህ ወርዶ ወርዶ እዚህ ደረሰ፤አሁንማ ጭራሽ አልከፍተውም እንዲሁ ለጌጥ ያህል አለ እንጂ›› አሉት ተብሎ ሲቀለድ ሰምቻለሁ፡፡ ይህን የሰማ ሌላ ቀልደኛም ‹‹የኛ ሃገር ውሸት እንኳን ሰው ቴሌቪዥን ያሸማቅቃል›› ብሏል አሉ፡፡
መቼም እንደውሸታሞቹ አሉባልተኛውም እየበዛ ነው፡፡ አንድ ነገሩ ያልገባው ሰው ተቃዋሚዎችን ከምክር ቤታችን ምን በላቸው? ቢሉት ‹‹ውሸቱ አሸማቆ አሸማቆ ጨረሳቸው›› ብሏል፡፡ አሁን ደሞ ውሸቱ በሃገርና በሕዝብ ላይ እየሆነ ነው፡፡ ሟቹ ጠ/ሚኒስትር፤ ኤኮኖሚያችን አደገ ተመነደገ፤ ይህን አሌ የሚል ደሞ ሽብርተኛ ነው፡፡በየገጠሩ ያለው ገበሬ ሚሊዮኔር ሆኗል ይህን ሃሰት የሚል ከሽብርተኛ ተለይቶ አይታይም፡፡‹‹መንግሥት መሬትን ሁሉ የኖረም ይሁን አዲስ ስሪት ሊዝ ውስጥ አስገብቷል፤ በውርስም በስጦታም የተገኘ ይሁን ያው ሊዝ ነው፡፡ ይህንን መቃወም ሽብርተኝነት ነው አሉን፡፡ ስለዚህ ባናምንበትም አምነንበታል ብለን በመዋሸት ማስመሰል ጀመርን ካላደረግን ግን ሽብርተኝነት ነዋ!፡፡
ልብ በሉ እስቲ አሁን ፓርላማ ከተቋቋመ ስንት ጊዜው ሆነ? ሕወሃት ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ የሥልጣን ፍርፋሪ ለአጃቢ ተለጣፊ ፓርቲዎች መመጽወት ከጀመረ ስንት ዓመታት ሆነ? ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትርስ ሞት ገላገላቸው እንጂ በገደብ አልባ ምርጫ ቦታውን ከያዙ ስንት ዓመታት አለፉ? ዳኝነት የዓምላክ ሆነና የሥላጣን ጊዜ ያሳለፈ እራሱም ይለፍ ያለ ይመስል ማለፋቸው ገላገለን እንጂ መች ፍንክች ሊሉ! ያስ ስንት ዓመት ሆነው? እዚህ ላይ ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ በነዚህ ‹‹ስንት›› በተባሉት ጥያቄዎችስ መጠን ምን ያህል ውሸት ተዋሽቷል? ያስ ሱስ አላስያዘም ሊባል ይችላል? በጭራሽ! ሱስማ ባይሆን ‹‹ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ›› በትእዛዛቸው በጥይት ያስረፈረፉትን ሁሉ ሃሰት ነው ብለው እውነትን አይቀብሯትም ነበር፡፡ ሱስማ ባይሆንባቸው፤አምልጧቸው የዋሹትን አገልጋዮቻቸው ሁሉ እንዲዋሹላቸው መመርያ አያወጡም ነበር፡፡ ሱስማ ባይሆንና የውሸት ቋት ባይሆኑ ኖሮ የማይታይ እድገትን በቅዠት አይተው፤ ቁጥሩን በማይታወቅ ስሌት አዋቅረው ከፍተኛውን የእድገት መለኪያ ደረስንበት ባላሉ ነበር፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውሸትና ዱሮ በትምህርት ቤት ያነበብነው ‹‹የንጉሱ አዳዲስ ልብሶች አንድ ነው፡፡ ንጉሱ ያልተሰፋለትን ልዩና ማራኪ የሆነ ልብስ ተሰፍቶልሃል ተብሎ፤ አልባሾች ባዶ እጃቸውን ልብስ አመጣን ብለው አለበስንህ ብለውት በአደባባይ መሃል እርቃኑን ይሄድ ነበር፡፡ ከአዲሱ ልብስ ስፌት ጋርም ያንን የንጉሱን አዲስ ልብስ ማየት የሚችሉት እውቀት የዘለቃቸውና ያወቁ የተመራመሩ፤ ለንጉሱ ታማኝና አገልጋይነታቸውን ያረጋገጡ ብቻ ናቸው በመባሉ፤ ንጉሡ በአደባባይ መሃል እርቃነ ስጋቸውን ሲረገረጉ ሕዝቡ በመላ የንጉሡ አዲስ ልብስ የሚያምርና ታይቶ የማይታወቅ ነው በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡ ንጉሡ ግን ራቁቱን ሆኖ ገበናው ሁሉ ተጋልጦ ነበር:ቢሆንስ ማን ደፍሮ ይናገር? የኛም ጉዳይ ባልመረጥናቸው የምክር ቤት አባላት እንዲሁ ነው፡፡የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር የሌለውን አለ፤ የወደቀውን ሞተ፤ እንቅፋት የመታውን እግሩ ተቆረጠ በማለት ክቡር እምክቡራን ተብለው በዚያ የሕዝብ ተወካዮች ሊቀመጡበት በማይገባ አዳራሽ በድፍረት ተኮፍሰው ውሸትን መልሰው በመዋሸት ጌቶችን እውነተኛ ለማድረግ በመጣር ላይ ናቸው፡፡ ሕዝቡ ግን ውሸቱ ገብቶታል፡፡ ውሸት መሆኑን ከተረዳ ሰነበተና አሁን አሁን ሊገርመው የሚችለው ባይዋሽ ነው እንጂ ውሸትማ ተዋህዷቸው፤ ሱስ ሆኖባቸው፤ በየእሩብ ደቂቃው ካልዋሹ ሥራም አልተሰራ እነሱም ቀሪ ይባላሉ፡፡
ኤኮኖሚያችን በ……..መቶ አድጓል ከተባለ ከዚያ ዕድገት ላይ ትንሽ ትንሽ የሕዝቡ ኑሮም ባያድግ እንኳን ቁጥቋጦ ማብቀል ነበረበት፡፡ የገንዘባችንም አቅም ባይጠናከርም ከመውደቅ ለመዳን መንገዳገድ ነበረበት፡፡ የግዢ ጉዳይም ቢሆን አንድ ጊዜ የተሰቀለው ተመን ዝቅ ማለት መቻል ነበረበት፡፡ግን ይህ ሁሉ የለም፤ አልሆነም፤ ሃሰት ነው፤ ኤኮኖሚው መሪ እንዳጣ ጦር ወይ አይሄድ ወይ አይቆም እንዲያው ባለህበት ሂድ ሆኗል፡፡ችግሩ ደሞ ይህን በይፋ አንስቶ በዚህ ነጥብ ላይ መወያየትና እውነትና ውሸቱን ማውጣት አለመቻሉ ነው፡፡ማንሳት ቀርቶ መሞከር እንኳን ከሽብርተኝነት ጋር ያስፈርጃል፡፡እርግጥ ነው የሰራተኛው ደምወዝ ቢከርምም ተጨምሯል፤ የመቀጠርያ ደምወዝም ድሮ ከነበረው በቁጥር ጨምሯል፤ ችግሩ ግን የቁጥሩ መጨመር የብሩን የመግዛት አቅም አጠናክሮ ሳይሆን አልፈስፍሶና ዝቅዝቅ ወጥሮት ነው የሚገኘው፡፡ ቀደም ሲል በ100 ብር ይገዛ የነበረው ሁሉ አሁን‹‹ኤኮኖሚያችን ባደገበት ዘመን››(በሳቅ ሞትኩ) ከ1000 ብር በላይ ይጠይቃል፤ ምሳሌ መስጠት ካስፈለገ መዘርዘር ቀላል ነው፡፡
ለምሳሌ
ዶሮ ከ2.ብር እስከ 4 ብር (ሲወደድ) የነበረው፤ አሁን ከ180 ብር እስከ 200 ብር
በግ ደህና ጠቦት በ 60ና በ70 በዛ ሲባልም በ200 እና 300 ብር ይገዛ የነበረው፤ አሁን ከ800 ብር እስከ 1000 ብር
ነጭ ሽንኩርት በኪሎ 2 ብር የነበረው አሁን፤ በኪሎ 30 ብር……አይበቃም ብላችሁ
ነው፡፡ያልጨመረ ነገር ቢኖር የሰው ዋጋ ብቻ ነው፡፡ሰው ቀድሞ ለመተመን ያስቸግር የነበረው ክቡር የሰው ልጅ፤ አሁን በዜሮ ብር ይተመናል፡፡
ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ከአናት ቁንጮው ከነበሩት የቀድሞው ባለስልጣን እስከ ተዋረድ ምንዝር ሹመኞች ድረስ አድገናል፤ አልፎልናል፤ ኑሮ ተስተካክሏል ሲሉን በሃፍረት ተሸማቀን ልናልቅ ነው፡፡ እነሱ ተደላድለው በልዩ የኑሮ ወጪ ድጎማ ሁሉም ስለሚሟላላቸው የሕዝብን ችግር ማወቅ አይጠበቅባቸውም ይሆን?
እያንዳንዱ ሹመኛ ትራንስፖርት አያስብ፤ ከህዝብ መገልገያ ትራንስፖርት ጋር ግፍያ የለበት፤መኪና ተመድቦለታል፤ ለነዳጅ አያስብ፤ ከነቤተሰቡ የሚሆነው መኪና ከነነዳጁ አለው፤በየገበያው ቤተሰቡ ለሸመታ አይንከራተት፤በተመደበለት መኪና፤ነዳጅና ሾፌር ሁሉም ነገር ይጠናቀቅለታል ስለዚህ እንዴት ብሎ የሕዝብን ችግር ይወቅ?፡፡
ይህን ሁሉ በማግኘቱና ኑሮው በመደላደሉ፤ ኤኮኖሚያችን አድጓል የሚለውን ውሸት ከበላይ ተቀብሎ እንደበቀቀን መደጋገሙ ሲያንሰው ነው፡፡ የራሱ ማሰቢያ የሌለው ነውና! ስለዚህም ውሸት ቁርስ፤ምሳ፤ራቱ ለሆነ ሁሉ፤ የውሸት ሱስ ለያዘው ሁሉ፤ ከውሸት ውጪ መተንፈስ ስለማይችል፤የሃገራችን ሕልውና፤የሕዝቡም ራዕይ የተዘረጋለት በውሸት ላይ ለመሆኑ አያጠራጥርም፡፡ፈጣሪ በተአምሩ ከውሸት ቅዠት እንዲያወጣን፤ እኛም ውሸትን አንሰማም ውሸት ነው ለማለት ጥንካሬውንና ብርታቱን ይስጠን፡፡ እነሱንም በሰሩት ሃጢያት ፈጣሪም ሕዝብም መሃሪ ነውና ምህረቱን እንዲያወርድላቸው ከውሸት ልክፍታቸው ለመገላገል ንስሃ ይገቡ ቢሰማቸው!፡፡
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርን ራዕይ እንከተላለን የሚሉት ሁሉ ያልገባቸው አንድ ጉዳይ ቢኖር የሳቸው የመጨረሻ ራዕይ ሞታቸው ነበርና ሁሉም ባዷችንን ጥለውን በሞት ራዕይ እንዳይሄዱ ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አንዱ ራዕያቸው የሾሟቸውን አገልጋዮች ሁሉ ሃጢአት ማጠራቀሚያ ልዩ ካዝና ነበራቸው አሉ፡፡ አገልጋዮች ደሞ በየዕለቱ ይጠሩና ጠዋት ጠዋት በየተራ እየገቡ ከዚያ ካዝና ሃጢያታቸውን የያዘው ፋይል እየተሰጣቸው ከቡና ጋር እንዲመለከቱት ይደረግ ነበርና ሁሉም ባለስላጣን ነኝ ባይ ሕይወቱ በጣር ያለች ነበረች፡፡ አሁን እሳቸው ቢያልፉም ያቺ ካዝና አለች፡፡ የዚያች ካዝና ቁልፍም በቅርቡ ስለተገኘ ሙስና ፈጸሙ የተባሉ ባለስልጣናት እንደፋይል አቀማመጣቸው ቅድም ተከተል ወደ ቂሊጦና ቃሊቲ እያዘገሙ ነው፡፡
አንዲት ፋይል ደግሞ ባማረ ክፈፍ ተለብዳ መጨረሻው ደርዝ ላይ ተቀምጣ ‹‹ልዩ›› የሚል ጽሁፍ አርፎባት አለች፡፡ ያቺን መቼና ማን እንደሚገልጣት የታወቀ ሁኔታ የለም ግን ሁሉም በጉጉት የሚጠብቃት እሷን ነው፡፡
የማያርፈው አቦይ ስብሃት አንድ ቀን የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ከቢሮ አስወጥቶ ካዝናዋን ለመክፈት ቢጥርም ስለአልሆነለታ፤ ምናልባት ተመሳሳይ ቁልፍ ያለያም የሚስጥር ቁልፉን ባገኝ ብሎ ሲቧግት አንድ ፋይል ያገኝና ቢያነባት የቀድሞው ጠ/ሚነስትር ባለቤት በሱ ላይ ያቀረበችው የውንጀላ ክስና ሃጢአት የሚያወራ ሆኖ ያገኘዋል፡፡ በመገረም እስከመጨረሻው አነበባትና መዝጊያው ላይ ሲደርሱ የባሰውን የሚያስደነግጥ አረፍተ ነገር ያነባል፡፡ እንዲህ የሚል፡
‹‹ስብሃት ይህ ብቸኛ ፋይል መስሎህ ለማጥፋት አትሞክር፡፡ የዚህም ፋይል፤ ይዘት ይሄ ብቻ አይደለም፡፡ በፎቶግራፍ የተደገፈ ያንተን ተገባር የሚያስረዳ ሰፋ ያለ ሲሆን፤ይህ ግን ለዓይነት የተቀነጨበ ነው፡፡ ሙሉው ፋይል የኔ ለምላቸውና በምንም መልኩ ልትደርስባቸውና ልታታልላቸው ልታግባባቸው ከማትችላቸው ሰዎቼ እጅ አለ፡፡ አትልፋ›› የሚል፡፡ ስብሃትም ይህን ሲያይ ነው ‹‹ይሄ ሰው እኮ ብቻውን አልሞተም እኛንም ሕወሃትንም ገድሎ ነው የሞተው›› ያለው፡፡
ውሸት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አብሮ ሞቶ አልተቀበረም፡፡ ገና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕይወታቸው ሳያልፍ ከማጣጣር ባለፈ በነበሩበት ወቅት እነ አቶ በረከት ‹‹ጤና ናቸው ለአዲስ ዓመት እንኳን አደረሳችሁ ይሉናል›› በማለት ቀዛብረው ነበር፡፡
ከዚያም በኋላ የበረከት ተከታዮች የማይሰለቻቸው እነ ሽመልስ ኩምአለ (በአባቱ ስም እንዳልጠራው አባቱ ክደውት ነበር ማለትን ስለሰማሁ ነው) የፍርድ ጉዳይ ቁንጮ የነበሩትም አቶ ብርሃነ ፍትሕ በኢትዮጵያ እንከን በሌለው መንገድ እየተተገበረ ነው ባሉ በሳምንቱ፤ እስክንድር ነጋ ሳያጠፋና ባልሰራው አልተወነጀለም ባሉ ማግስት ለርዕዮት የትምህርት እድልና የማይገባ ውሳኔ ባሰጡ በነገታው፤ እሳቸውም እንዳልሆነ ሆነው ‹‹ወጣ ወጣና ……….›› እንዲሉ ተንከባለሉ፡፡ ታዲያ አሁንስ አቶ ብርሃነ ምን ይሉ ይሆን?
ቅን ሰዎችና ቅንነት የጎደላቸው አንድ ላይ ጨርሶ መቆም አይችሉም፡፡ አንዱ ሌላውን አጥፊ ነውና፡፡ የገዢው ፓርቲ ሹመኞችና አገልጋዮችም ከኢትዮጵያውያን መልካም አሳቢዎች ጋር እንዲሁ ናቸው፡፡ አጥፊና ጠፊ፡፡ እርስ በርሳቸውም ቢሆን አንዱ ከሌላው የበለጠ ዲያቢሎስ ለመሆን በሚያደርገው ጥረት ግጭት ይፈጥራሉ ያን ጊዜ ነው አደጋው፡፡ ለሃጥአን የወረደ ለጻድቃን ይደርሳል እንዲሉ ነውና ይሰውረን፡፡
በሌላ በኩልም ጥፋታቸው ታይቷቸው፤ የሚያስፈራው ሃይል ሲለቃቸው ወደ ሰብአዊነት ለመመለስ ሲጥሩ ገና ከልክፍቱ ያልተላቀቁት ጋር ግጭት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ሰይጣን ለወዳጁ ድርብ ስለሆነም ወደመልካም የሚመለከቱትን ለማጥፋት ለእኩዮች ሃይል ይሆንና መንገዱን ዘግቶ በማገድ እጃቸውን ያስያዘቸውና ለቃሊቲ ይዳርጋቸዋል፡፡ሰሞኑን እያየን ያለውም ያንን ነው፡፡
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ተብሎ ተጠብቆ ነበር፡፡ የነበረውን አለመግባባት አጥፍቶ በይቅር ለእግዚአብሔር የተለየ ሁኔታ ሊያስገኝ ይችላል ተብሎ ታስቦ ነበር፡፡ አሁንም ገና ተስፋ ያልቆረጡ አሉ፡፡ ክፋቱ ግን ስብሃት ነጋ፤ በክት ስምኦን፤ ሳሞራ፤ አባይ (ግድቡን አይደለም) ጸሃዬ፤ አዜቧ፤ እና ሌሎችም በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየሙት ከግራ ቀኝ የውጥር ይዘውት እንዴት ብሎ ለውጥ ለማምጣት ይችላል፡፡
ሌላው ቢቀር አማኝ በመሆኑ ሳቢያ ክፉ ነገር ላያስብ ቀና መንገድ ሊመርጥ ይችላል፤ የፈጣሪን ህግጋት የሚያከብር ከሆነ ፈጣሪ ለሰው ልጆች የሰጠውን ችሮታና የመኖር መብት ለማስከበር ይቆም ይሆናል በሚል እምነት ለለውጥ ይቆማል የሚሉ አሁንም ገና ተስፋ አልቆረጡም፡፡ እንደአፋቸው እንደምኞታቸው ያድርገው፡፡
ይህን ጽሁፍ በመጻፍ ላይ እንዳለሁ በሲ ኤን ኤን ላይ የደቡብ አፍሪካ የነጻነት አባት ኔልሰን ማንዴላ ከዕድሜያቸው መግፋትና በወህኒ በነበሩበት ወቅት በተጠናወታቸው የሳንባ በሽታ ሳቢያ ሆስፒታል ገብተው ሳለ የደቡብ አፍሪካ ሕዝብና ዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ ምን ያህል እንደተጨነቀላቸው፤ ለደህንነታቸው በጸሎት ላይ እንደሆነ ሳይ በቅናት ልቤ ተቃጠለ፡፡ማንዴላ እኮ 96 ዓመታቸው ነው፡፡ ማንዴላ እኮ ዓለምን በክፉም በደጉም እስኪበቃቸው ኖረውባታል፡፡ ማንዴላ እኮ ትልቅነትን ክብርን፤ መወደድን፤ አንቱታን እስከበቃቸው ተንበሽብሸውበታል፡፡
አሁንም ለማንዴላ አክብሮታችን የበዛ ነው ፈጣሪም ምህረት ከዚያ የከፋ ነገር ከመጣም መንግስተ ሰማያትን እንደሚያወርሳቸው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ማዴባን ሳነሳ ምን ትዝ አለኝ እባካችሁ የኳሱ ነገርና የሥራ አስፈጻሚው እንደፈጠራቸው ምድራዊ የስልጣን አባታቸው አይነት ቅጥፈት በቅጥፈት፤ ውሸት በውሸት፤ የሆኑበት መግለጫቸው ትዝ አለኝ፡፡
ፊፋ ጉዳዩን ይፋ ባደረገበት ጊዜ የመጀመርያው የፌዴሬሽኑ ኑዛዜ
‹‹ጥቂቶቻችን እናውቅ ነበር፡፡ ተጫዋቹ 2 ቢጫ እንዳየ በሚገባ እናውቅ ነበር፡፡ ያንን ግን ለአሰልጣኙም ለተጫዋቾችም ለተቀጣውም ተጫዋች አልነገርናቸውም ምክንያቱም ሴንተራል አፍሪካን እንደምናሸነፍ እርግጠኞች ስለነበርን ተጫዋቾቹንም አሰልጣኙንም ላለመረበሽ አልነገርናቸውም›› የሚል ሆኖ ሳለ ከምንጊዜው ቃላቸውን አጥፈው፤ የቀላመደ አባባላቸውን ሰርዘው፤ ውሸት መናገራቸውን እያወቁ አናውቅም ብለው፤ ዳጋም መግለጫ፤ ደግሞም መግለጫ፤ ደሞ ስብሰባ ፤ ሌላም ሌላም ተደርጎ ያወቃሉ የተባሉት እንደማያወቁ፤ አያውቁም የተባሉት እንደሚያውቁ እንዴት ሆነ ጎበዝ፡፡
ሆይ አቶ በረከት እንዴት ያለ ትምህርት ቤትና የትምህርት ስርአት ቢቀይሱ ነው ሰዉን ሁሉ የውሸት ቋት ሊያደርጉ የቻሉት?
በረከትን ሳነሳ ሰሞኑን በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ በተካሄደ በዓል ላይ ያየሁት ነገር ታወሰኝ፡፡ በበዓሉ ላይ የስልጣን ውርስ ይገባናል ባዮችና ከሁሉም ቅድሚያ ለኛ ሊሰጠን ይገባል የሚሉ፤ እንዲሁም አናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው በማለት ያለፈውን ትተው መጪውን የሆድ ጌታ የሚጠብቁም፤ በሞተ ከዳ የተሾሙትም፤ ጊዜው ሲያልቅ በመጪው ምርጫ ተረካቢ ነን የሚሉትም ሁሉም አይነት ተደርድረው ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝን በመጠበቅ ላይ ናቸው፡፡
ሰአቱ ደረሰና ጠቅላይ ሚኒስትሩ መጡ፡፡ገቡ፡፡ በአቶ ደመቀ ተነስቶ በማክበር አቀባበል ብቻ ተቀመጡ፡፡ ይህን ሳይ በዚያ የነበሩት የሕወሃት አባላትና ሌሎችም አጨፍጫፊዎች የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር በእንዲህ አይነት ስብሰባ ላይ ሲመጡ ጠቅላላው ታዳሚ ተሸቀዳድሞ አየተጎነበሰ ነበር በአክብሮት የሚቀበላቸው፡፡ ላሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ግን ከአቶ ደመቀ ሌላ የተነሳና ለሳቸው ሳይሆን ለያዙት ቦታ ተገቢውን አክብሮት ያደረገላቸው አልነበረም፡፡ በረከትና ከፊት ወንበር የነበሩት በመላ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ማለፊያ እግራቸውን ሰበሰቡ እንጂ ብድግ? አልሞከራቸውም፡፡ ይህ እጅጉን ያስገረመኝና ከበሬታው ለግለሰቡ ሳይሆን ለተቀመጡበት የስልጣን መንበር መሆኑንና ያ ደግሞ የኢትዮጵያ ውክልና ያለው መሆኑን መናቃቸውን ነው፡፡
ይህ በዚህ አለፈና የዕለቱ ቀደምት ተናጋሪ የሆኑት በረከት ወደመናገሪያው ቦታ ሄደው ንግግር በማድረግ ላይ ሳሉ የቀረበላቸውን ውሃ ጠጥተው በመጨረሳቸው ከፊት ለፊት የተቀመጠውን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀን ውሃ እንዲያቀብላቸው ሲጠቅሱት ደመቀም ከመቅጽበት ተፈናጥሮ በመነሳት የተጠየቀውን ውሃ አቀረበ፡፡ ለነገሩ አስተናባሪዎች ሞልተው ሳለ በረከት ይህን ያደረገው ሆን ብሎ ለማዋረድና ‹‹ለስሙ የተሰጠ ስልጣን›› ለማለት ፈልጎ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ምናለበት ደመቀስ ተነስቶ ከማሳለፍና ከማጋፈር ቦይ ጠርቶ ቢያዝለት ኖሮ፡፡ አይ የዛፍ ላይ እንቅልፍ!
ይሀ እንዲያው ለማለት ተብሎ የተጻፈ ሳይሆን ከምር የተፈጸመና በአደባባይ የተከናወነ ድፍረት የተመላበት ብልገና ነው፡፡
አዘንኩ፡፡ በጣም አዘንኩ፡፡ ምን ዓይነት ጉዶች ጋር ነው የምንኖረው ብዬ ከምር አዘንኩ፡፡ ለካ የጫካ ባሕሪና ብልግና በቀላሉ አይለቅምና!
ይሄ የውሸት ቅልመዳ በሽታ ተጋቦትነት አለው ማለት ያስቻለኝ ሰሞኑን በሽታው ከሌላ አቅጣጫ መምጣቱን በመስማቴ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የሙስሊሙ ሕብረተሰብ ላለፉት 18 ወራት የሃይሞነት ነጻነታችን በሕገ መንግስቱ ላይ በተደነገገው መሰረት ሊከበርልን ይገባል፤ ይህም የዜግነት መብታችን ነውና አንታፈን በማለት በሰላማዊ መንገድ ባዶ እጃቸውን በሕገ መንግስቱ መከታነት በማመን ተሰለፉ፡፡ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ጮሁ፤ ተደበደቡ፤ ቆሰሉ፤ ተገደሉ፤ ታሰሩ፤ ሴቶቹ ተደፈሩ፤ ይህን ሁሉ ከማንም በተሻለ ለመመስከር ችሎታውና አቅሙ ያላቸው ወጪው አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ ህወሃት/ኢሕአዴግ የወሰደውን እርማጅ ትክክለኛነት በተዘዋዋሪ መንገድ መግለጻቸው የቅጥፈት ተጋቦት በሽታ ተጠናውቷቸው መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ከዚህም አለፍ ባለ አምባሳደሮች ጊዜያቸውን ጨርሰው ሲሰናበቱ መሪዎች መታሰቢያ ስለሚቸሯቸው ምናልባት ያንን መጡንን ለማሳደግ ይሆን ቅልመዳው? ያሳዝናሉ ሰውዬው!
በሌላ በኩል ደግሞ የአሜሪካን መንግስት የሽብር ተጠቂዎች ሊሆኑ ይችላሉ ያላቸውን ሃገራት ሲዘረዝር ኢትዮጵያን ከዝርዝሩ ባለማስገባቱ ኢህአዴግ/ህወሃት እና አለቅላቂዎቹ፤ እዬዬ ማለት ይዘዋል፡፡ እንዴት ተንቀን ነው ሽብር ያሰጋቸዋል ከሚባሉት ሃገራት ያልተካተትነው በሚል ለቅሶ ላይ ከረሙ፤ በለቅሷቸው ሰልስትም ዶሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ቴዎድሮስ አድሃኖም ሀጋራችንን ሽብር ያሰጋታልና ጥንቃቄ አድርጉ በማለት ለውጪው ኮሚኒቲ አባላትና ድርጅቶች ኤምባሲዎች ጋዜጣዊ መግለጫ አውጥተዋል፡፡ የዶሩ ጋዜጣዊ መግለጫ ሽብርተኝነት ያሰጋናል ያሉት በትክክለኛው አተረጓጎም በሙስሊሙ ወገኖቻችን ኢድ በዓል ወቅት ያ አመልካች ጣቱን የሚያሳክከው አግአዚ የተባለ ሽብርተኛ ቡድን በፈጸመው ሽብር ንጹሃን ዜጎችን በመጨፍጨፉ አሸባሪው ራሱ አግአዚ የወያን ኢህአዴግ ስሪት መሆኑን አረጋግጧል፡፡ አግአዚ/ሽብርተኛነቱን ያረጋገጠው ዘንድሮ ብቻ ሳይሆን በ97ም ይህንኑ ተግባር በፈጸመበት ወቅትም ነው፡፡ ይሄንን ነው አምባሳደሩም ትክክል ነው ለማለት የበቁት፡፡
ወያኔ ኢህአዴግና ሹሞቹ፤ ባለስልጣኖቹ፤ ካድሬዎች፤ በዓሉ በሰላም ተጠናቀቀ ያሉት፡፡ ማ ፈ ሪ ያ ምስክርነት!
ደግሞ እኮ እንኳን አደረሳችሁ ይባልልኛል!!!
No comments:
Post a Comment