Bewketu Seyoum
ሃይማኖቶች ምእመናንን ብቻ ሳይሆን መናፍቃንንም ያፈራሉ፡፡ብሄርተኞች በስሜት የሚነድደውን ምእመንብቻ ሳይሆን የኔ ቢጤውን መነፍቅም እንደሚያፈሩ አንርሳ፡፡በነገራችን ላይ ሃይማኖትን መካድ ማለትሃይማኖት የሚያነሳቸውን አብይ ጥያቄዎች መካድ ማለት አይደለም፡፡እንዲሁም፣ ብሄርተኝነትን መካድማለት የኢትዮጵያን ብሄር ብሄረሰቦች ህልውና መካድ ማለት አይደለም፡፡በዚህ ጉዳይ ፣መናፍቅ መሆንማለት፣ የብሄርተኛ ነቢያት ሰለ ጭቆና ስለ ነጻነት ብሎም ስለ ኢትዮጵያዊነት የሚያቀርቡትን አጉል እምነትመጠራጠር ማለት ነው፡፡
ከዘመናችን የብሔርተኝነት ነቢያት አንዱ ጃዋር መሐመድ በቅርቡ ከእንቁ መጽሔት ጋር ባደረገውቃለመጠይቅ ላይ ስለኢትዮጵያዊነት የሚከተለውን ይላል፡፡
‹‹…ኢትዮጵያን የመሠረታት የሶሰትዮሽ ጦርነት ግብግብ ነው፡፡በአማራው፣በኦሮሞው፣በትግሬው ግብግብውስጥ ወደ መጨረሻ ላይ በአመራር ስር የበላይነቱን የያዘው አማራው ነበር፡፡በዚህ የተነሳ አሁን የምናያትኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባህላዊ ሥርጭት እና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች፡፡…የኢትዮጵያ አገራዊማንነት የምንለው የአማራ ባህላዊ ማንነት ነው››
ጃዋር የኢትዮጵያን መሠረት የሦስት ብሄረሰቦች የስልጣን ግብግብ አድርጎ ወስኖታል፡፡ በመጀመርያ፣ ሌሎችብሄረሰቦች በግብግቡ ተሳትፎ እንዳልነበራቸው አድርጎ ማቅረቡ አንድ ጉድለት ነው፡፡ ግን ዋናው ቁምነገርይሄ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የግጭት ውጤት ብቻ እንደሆነች አድርጎ ማቅረቡ ነው ትልቁ ስሕተት፡፡ ሲጀምር፣የግብግብ ታሪክ መሠረት ይንዳል እንጂ መሠረት አይገነባም፡፡ እንደኔ ግምት፣የኢትዮጵያ መሠረት የሆነውብሄረሰቦች ለጋራ ሕልውና ሲሉ የሚያደርጉት የመደጋገፍ ታሪክ ነው፡፡
ዛሬ ዛሬ፣ ታሪክ ከላሾች፣የብሄሮችን የ‹‹ግብግብ››ታሪክ ሞቅ አድርገው፣አኳሽተው ሲጽፉ፣የብሄሮች መደጋገፍታሪክን ግን ቸል ይሉታል፡፡ አለያም እጅግ በቀዘቀዘ ስሜት፣ በጥቂት መስመሮች ብቻ ጨረፍ አድርገውያልፉታል፡፡ለነገሩ፣ከፋፋይነትን ብቸኛ ያስተዳደር ፈሊጥ አድርጎ የሚቆጥር ሰው በታሪክ ገጾች ውስጥመመልከት የሚፈልገው ክፍፍልን ብቻ ነው፡፡ታሪክ ግን ብዙ በጎ የትብብር ገጠመኞችን መዝግቧል፡፡ለምሳሌጀግናው አጼ ዮሐንስ አራተኛ በበዛሬይቱ ኤርትራ የግብጽን ወራሪ ጦር ድል የነሡት የትግራይ ጀግኖችን ብቻአሠልፈው አልነበረም፡፡ በዚህ ጦርነት ከግብጽ ጎን ሆኖ፣የተዋጋው አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ዊልያም ዴይእንደመሠከረው ወልቃይቶች፣ጥልጣል የተባሉ የአፋር ንኡስ ክፍሎች፣የወረኢሉ ኦሮሞዎች ለንጉሰነገስቱድጋፍ ለማድረግ ተሸቀዳድመዋል፡፡በራስ ወሌ የሚመሩ የአማራ ወታደሮች ተሳትፈዋል፡፡የጎንደር ቀሳውስትለጦርነቱ ድጋፍ ለማድረግ አድዋ ገብተዋል፡፡ የጎጃሙ ራስ አዳል የደርሼልሀለሁ አለኝታቸውን አሳይተዋል፡፡የሸዋው ንጉስ ምኒልክ ሳይቀር በመቶ የሚቆጠሩ በቅሎዎችንና ማበረታቻ ልከዋል፡፡ ዝርዝሩን ማንበብለሚፈልግ Muslim Egypt Christian Abyssinia የተባለውን የዚህ ደራሲ ማስታወሻ ገጽ 291-292ያንብብ፡፡ መጽሐፉን በኢንተርኔት ቤተ-መጻህፍት ውስጥ በብላሽ ማግኘት ይቻላል፡፡ከተለያየ መአዘን የመጡእኒህ ኢትዮጵያውን ከዘመቻው የሚያገኙት ድልን ብቻ አልነበረም፡፡ በዘመቻ ወቅት ባህል ይዋዋሳሉ፣ቃላትይወራረሳሉ፣ ስንቅ ያዋጣሉ፣ ልምድ ይለዋወጣሉ፡፡ በሂደት ተቃራኒ ከሚመስሉ ልማዶች የነጠረ ኢትዮጵያዊባህል እንደ አረቄ ይወጣል፡፡ ይህን በመዋጮ የተገኘ ባህል ‹‹የአማራ ባህል ››ብሎ ማጥበብ የጸና ድጋፍ ያለውአይመስለኝም፡፡
ጃዋር‹‹አሁን የምናያት ኢትዮጵያ ማንነቷ በአማራ ባህላዊ ሥርጭትና በአማራ ፖለቲካ የተገነባች ነች››በማለት ሳይወሰን ‹‹የኢትዮጵያ አገራዊ መለያ ማንነት የምንለው አማራ ብሄራዊ ማንነት ነው›› ሲልይጨምራል፡፡ ጎበዝ ኧረ በህግ አምላክ!!! የኢትዮጵያ ባህልኮ ካንድ አለት የተጠረበ ሕንጻ አይደለም፡፡ ከብዙየመዋጮ ጡቦች የተገነባ ነው፡፡ ጃዋር እያንዳንዱን ጡብ ቀርቦ ቢመረምረው እዚህ የደረሰበት እርግጠኝነትውስጥ የሚደርስ አይመስለኝም፡፡
እስቲ ከደቃቅ ምሳሌ እንጀምር፡፡ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራ ሲሠራ አስቀድሞ የሚመጣው የቡናስነ-ስራታችን ነው፡፡ አንዲት ጠይም ፣ባለሹርባ ሴት፣ያበሻ ቀሚስ ለብሳ ቡና ስትቀዳ የሚያሳይ ምስልበየቦታው ማየት የተለመደ ነው፡፡ይህ ችክ ያለ ምስል በስነ-ስእል ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ ቢዮንሴና ጆን ኬሪአገራችንን በጎበኙበት ሰአት የቡና ስነስርአት ተሳታፊ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡ ይህ ማለት የውጭ እንግዳ የቡናስርአታችንን እንደ ኢትዮጵየዊ መለዮ እንዲመዘግብልን ፈልገናል ማለት ነው፡፡ ለዋለልኝ መኮንን እና ለጃዋርመሀመድ ይህ የአማራ ባህል መሆን አለበት፡፡ በመጀመሪያ እይታ ይመስላል፡፡ ጉዱ ዝርዝሩ ላይ ነው፡፡የሴትዮዋ ሹርባ ከሐማሴን ወይም ከተንቤን ሴቶች ልማድ ጋር ስምም ነው፡፡ ያበሻ ቀሚሱን የሽሮሜዳ ጋሞየሸመነው ሊሆን ይችላል፡፡ ጀበናው የጂማ ሙስሊም ኦሮሞዎች ያስተዋወቁት ነው፡፡ አቦል ቶና በረካ አረብኛወይም የተወላገደ አረብኛ የተገኙ ቃላት ናቸው፡፡ ዛሬ በክርስቶስ ትንሳኤ በአል በሉባንጃ የሚታጀብ ቡናየማያፈላ ክርስትያን ኢትዮጵያዊ ማግኘት ይከብዳል፡፡ ከጥቂት መቶ አመታት በፊት ግን ቡና የእስላም ልማድተደርጎ ይቆጠር ነበር፡፡የቡና ትርኢት የሙስሊም አበው በኢትዮጵያ ባህል ላይ የጨመሩት በጎ መዋጮእድርገን ልንቆጥረው እንችላለን፡፡ ኢትዮጵያ ጊዜ በተባለው አናጢ ከብዙ ጡቦች የተገነባች ናት የምንለውለዚህ ነው፡፡
ጃዋር አማራው የራሱን ባህል በኦሮሞው ላይ እንደጫነ ሲያምን ተገላቢጦሹ ያለው አይታየውም፡፡ ኦሮሞበረጅም ዘመን፣በሠፊ ምድር፣ ሰፍሮ የመኖሩን ያክል በጎረቤቶቹና በወደረኞቹ ላይ የባህል ተጽእኖ አላሳደረምማለት ብርቱ ባህል የለውም ከማለት አይለይም፡፡ ባገራችን ዋና ዋናዎቹ የባህል ቀራጺዎች ጦርነትና ሐይማኖትናቸው፡፡ ለምሳሌ ፣ጀግኖችን እና ነገስታትን አባ በዝብዝ አባ ታጠቅ፣ አባ ዳኘው አባ ነጋ ወዘተ እያሉ መሰየምገናና ኢትዮጵያዊ ባህል መሆኑን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ ብዙዎቻችን የማናውቀው ይህንን ባህልያስተዋወቁት ለግማሽ ምእተአመት ያክል ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት የየጁ ኦሮሞዎች መሆናቸውን ነው፡፡ብላቴን ጌታ ማህተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ቼ በለው በተሰኘው መጽሐፋቸው ይህንን እንዲህ በማለትያረጋግጣሉ-
‹‹ነገስታቱ በ‹‹አባ›› ወይም የእገሌ ባለቤት በሚል ቅጽል ስም መጥራት የጀመሩት የኦሮሞዎችን ወይምየወረሸሆችን ልምድ በመከተል ነው ከ1838 ዓም ወዲህ እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል፡፡ ወትሮ ግን በተለይም1474-1713 ዓም ባለው ጊዜ ውስጥ ቅብዓ መንግሥቱ በሚደረግላቸው ሰአት ይወጣላችው የነበረውየግርማ ስም ወይም ስመ መንግስት ‹‹ሰገድ›› የሚል ኃይለቃል በመጨመር እንደነበር ቀጥሎ ያለውያረጋግጣል፡፡ ወናገድ ሰገድ፣ አጽናፍ ሰገድ፣ አድማስ ሰገድ፣ መለክ ሰገድ፣አድያም ሰገድ ሉል ሰገድ››በማለትይዘረዝራሉ፡፡
ከጥቅሱ ሦስት ፍሬ ነገሮችን መረዳት ይቻላል፡፡
1- ይህ ባህል ባንድ የዘመን ምዕራፍ ላይ ከኦሮሞ ብሄረሰብ የመነጨ የኢትዮጵያ ባህል ነው፡፡
2- ባህሉ ብርቱ ተጽእኖ ከመፍጠሩ የተነሳ አማራና ትግራይ ነገስታት ለረጅም ዘመን ይጠቀሙበት የነበረውንየስያሜ ዘይቤ ሽሯል፡፡
3- አማራው ታሪክ ጸሀፊ ለባህሉ አስተዋዋቂዎች የባለቤትነት እውቅና ሰጥተዋል፡፡
በሃይማኖት ረገድም ተመሳሳይ ነገር ነው የሚገጥመን፡፡ ለምሳሌ አቴቴ የሚለውን ቃል ደስታ ተክለወልድሲተረጉሙ ‹‹ዛር፣በሴት ስም የምትጠራ፣ ውቃቤ ፣ አማሮች ከኦሮሞዎች የወረሷት ጨሌ የሚያጠልቁላትአቴቴ ጊንቢ ሐራ አቴቴ ዱላ እያሉ እንቀት የሚቀቅሉላት አምልኮ ባእድ፣ትርጓሜ ጠባቂ ማለት ነው››ይላሉ፡፡
‹‹አምልኮ ባእድ ››የሚለውን አሉታዊ ሐረግ፣የክርስትያን አድልኦ ያለበት ፍርድ አድርገን እንለፈው፡፡ ዋናውፍሬ ነገር፣ የአሮሞው ባህል በአማራው ባህል ላይ ተጽእኖ ማሳደሩን ማወቃችን ነው፡፡ ይህም አንዱ ብሄረሰብሁልጊዜ ጫኝ ፣ ሌላው ብሄረሰብ ሁልጊዜ ተሸካሚ እንደነበረ አድርገው ሊነግሩን የሚፈልጉትን ሰዎችያስተባብላል፡፡ በሁለቱ ግዙፍ ብሄረሰቦች መካከል የነበረው ግኑኝነት የእኩዮች ልውውጥ ነው፡፡ የባህሎችውርርስ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋልና፣ የማንኩሳ ዘመዶቼ የሚያስደነግጥ ነገር ሲገጥማቸው‹‹አቲቲን ወሰድከው›› ይላሉ፡፡ ቀልቤን ገፈፍከው ለማለት ነው፡፡ የኦሮሞ ባህላዊ ተጽእኖ በወለጋ ድንበር ላይቆሟል ያለው ማነው?
ስለጉዲፈቻ ባህል ብዙ ሰዉ የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ በጦርነት ወቅት ምርኮኞችን ባርያ ማድረግ ወይምመግደል በብዙ ማህበረሰቦች የተለመደ ነው፡፡ በኦሮሞ አበዋዊ ባህል ውስጥ ግን ምርኮኞች በልጅነትይታቀፋሉ፡፡ ከሌላ ብሄረሰብ ቢመጡም የኦሮሞ ብሄረሰብ የሚያገኘውን መብት ሳይነፈጋቸው ያድጋሉ፡፡ይህንን ልማድ በአማራው ማህበረሰብ ውስጥም እናገኘዋለን፡፡ ለምሳሌ በጎጃሙ ንጎስ ተክለይማኖትና በወለጋመሳፍንት መሀል በተደረገው ጦርነት የተማረከው ብላቴና ነገሮ ዋቅጅራን እንደልጅ አሳድገውታል፡፡ ክርስትናአስነስተው ተክለኢየሱስ አሰኝተውታል፡፡ ራሱ በጻፈው ማስታወሻ ‹‹በጠጅና በስጋ አደግሁ›› በማለትየመሳፍንት ልጆች ያገኙት የነበረውን ምቾት ሳይነፈገው ማደጉን ይመሰክራል፡፡ ነገሮ ፣ ከማእረግ ወደ ማእረግእየወጣ የንጉሱ ጸሐፌ ትዝዛዝ እስከመሆን ደርሷል፡፡ ተመሳሳይ መልኩ በሸዋ ምርኮኛው ቆሴ ዲነግዴበቤተመንግስት እየተቀማጠለ አድጎ ሐብተጊዎርጊስ በሚል ስመ ክርስትና የኢትዮጵያ የጦር ምኒስትርእስከመሆን ደርሷል፡፡ ሰዎችን በልዩ ቋንቋቸው ምክንያት ባይተዋር ማድረግ ኢትዮጵያዊ ባህል አልነበረም፡፡
እኩዋን ባህላችን አማርኛችን እንኳ የጉራማይሌነታችን ምስክር ነው፡፡ አሁን ኦሮምኛ ያልተነካካ አማርኛማግኘት ይቻላል?፡፡ እሰቲ ለናሙና ያክል ‹‹ተወርዋሪ ኮከብ›› ከተባለው የዮሐንስ አድማሱ ምርጥ የአማርኛግጥም ውስጥ ጥቂት መስመሮች ልቆንጥር፡፡
1) ተወርዋሪ ኮከብ በራሱ ነበልባል በራሱ ነዲድ ተቃጥሎ የጠፋ
ተወርዋሪ ኮከብ በምናውቀው ሰማይ ነበረ በይፋ
ተወርዋሪ ኮከብ በምናውቀው ሰማይ ነበረ በይፋ
2) ሜዳና ተራራ በመሐል ሸለቆ
ጨፌውና መስኩ በኒህ ተደብቆ
ጨፌውና መስኩ በኒህ ተደብቆ
3) ሐቀኛ ጠፍቶበት በዋለበት መልቲ
ጌጥ ነው ድንቁርና የገዳዮች ሎቲ
ጌጥ ነው ድንቁርና የገዳዮች ሎቲ
4) ብልጭ ብሎ ጠፋ
ተወርዋሪ ኮከብ የሐሳብ አንጋፋ
ተወርዋሪ ኮከብ የሐሳብ አንጋፋ
በመረጥኳቸው መስመሮች ውስጥ የሚገኙት ‹‹ይፋ፣ ጨፌ፣ መልቲ፣ ሎቲ፣ አንጋፋ፣›› የተባሉት ቃላትኦሮሚኛ ናቸው፡፡ ካንድ የአማርኛ ግጥም ይህን ያህል ኦሮሚኛ ከተገኘ በሙሉ መዝገበ ቃላት ውስጥ ምንያህል ሊገኝ እንደሚችል አስቡት፡፡ ይህን ያክል ነው የተዋሀድነው፡፡
የኢትዮጵያ ባህል የተውጣጣ ባህል እንጂ ጃዋር እንደሚለው የአማራ ባህል ብቻ አለመሆኑን በመጠኑምቢሆን ያሳየሁ ይመስለኛል፡፡ ጃዋርን እዚህ ላይ ላሰናብትና ለማጠናቀቂያ የምትሆን አንዲት አንቀጽልጨምር፡፡
ባህልን ማክበር ጥሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በስሜት ሚነድደው የብሄርብሄረሰብ ፖለቲካችን፣ ዜጎች ለባህልያላቸውን ፍቅር ወደ ጭፍን አምልኮአዊ ፍቅር እያዘቀጠው ነው፡፡
ባባቶቻችንና በእኛ መካከል የባህል ፋይዳ ልዩነት ያለ ይመስለኛል፡፡ አባቶች ባህላቸውን ያገኙት በኑሮ ጣጣአስገዳጅነት ነው፡፡ ለምሳሌ የኔ አያት ቁምጣ ሱሪ የሚታጠቀው ከሌሎች ብሄረሰቦች ለየት ብሎ ለመታየትአይመሰለኝም፡፡ በቂ አቡጀዲ ስላላገኘ ነው፡፡ ወይም ለስራ እንዲያመቸው ባጭር መታጠቁ ይሆናል፡፡ እኔ ግንየብሄረሰቦች ቀን ሲከበር ቁምጣ ለብሼ ራሴን በማስጎብኘት እንድኮራ ይጠበቅብኛል፡፡ ጉድ እኮ ነው!!! ጋቢበጥንት ጊዜ የሙቀት ምንጭ ነበር፡፡ ዘንድሮ የኩራት ምንጭ ሊሆን ይቃጣዋል፡፡
የዛሬዎቹ ባህል አምላኪዎች ባህል ሲያስቡ ለውጥን ይረሳሉ፡፡ ባንድ ወቅት የሚያኮራው ያንድ ብሄረሰብ ባህልበሌላው ወቅት ይናቃል፡፡ ባንድ ወቅት የሚያስሸልመው በሌላ ጊዜ ያስቀጣል፡፡ ከጥቂት መቶ አመት በፊትዝሆን መግደል በማህበረሰቡ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ የሚያጎናጽፍ ተግባር ነበር፡፡ ዝሆን የገደለ ልዩ አምባርክንዱ ላይ ያጠልቃል፡፡ እስኪ ዛሬ ያባቶቼን ባህል ለማክበር ነው ብለህ ፓርክ ውስጥ አርፎ የተኛውን ዝሆንግደል፡፡ በአምባር ምትክ ካቴና ይጠልቅልሀል፡፡
የብሄር ብሄረሰቦች አልባሳት የተባለውን የተደጋገመ ግን ያልታሰበበት ቃል ከዚህ አንጻር ቃኙት፡፡ ሲጀምር፣ዛፍ እንኳ ቅርፊቱን በሚቀያይርበት ዓለም፣ብሄር ብሄረሰቦች በየጊዜው አልባሳታቸውን አይቀያይሩምወይ?፡፡ የብሄረሰቡ አልባስ ሲባል በየትኛው ዘመን የሚለበሰው ነው? የእንዳለጌታ ከበደ እናት ሲነግሩን፣ ዛሬበጉራጌ ዘፈን ላይ በቲቪ የምናየው የሴቶች ሻማ ቀሚስ በደርግ ዘመን የተጀመረ ነው፡፡ ከዚያ በፊት የነበረውሸማ ነው፡፡ ከሸማው በፊት ደግሞ የቆዳ ቀሚስ ይለበስ ነበር፡፡
ሌላው፣ አንድ ማህበረሰብ አልባሳት በየማእረጉ ልዩ ልዩ ልብሶች ይኖሩታል፡፡ ወታደሩ ያባ ገዳውን ልብስየሚለብስ አይመስለኝም፡፡ ባሮች ከጌቶች ልብስ ጋር የሚመሳሰል ልብስ እንዲለብሱ አይፈቀድላቸውም ነበር፡፡በፊውዳል ማህበረሰብ ከላይ አስከታች መልበስ መከናነብ የጨዋነት ምልክት ነው፡፡ ይህንን በሸዋና በትግራይብቻ ሳይሆን በቅድመ ምኒልክ ከፋ ውስጥ እናገኘዋለን፡፡ ባንጻሩ፣ባሮች በከፊል ተራቁተው መታየትአለባቸው፡፡ ባጠቃላይ በኢትዮጵያ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ አለባበስ በበሄረሰብ ላይ ሳይሆን በመደብ ላይየተመሰረተ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ስለዚህ የብሄር አልባሳት የሚባለው እንደ ማንኛውም ሾላ በድፍን ሐሳብበጥርጣሬ መታየት አለበት፡፡
ትውልዱ የባህል ፈጣሪ መሆን ሲገባው፣የባህል ሙዚየም ሆኖ ተተክሏል፡፡አፈወርቅ ገብረኢየሱስ ባንድ ወቅትእንዳለው ‹‹ካባቶቹ የማይበልጥ ትውልድ፣ እንዳልተፈጠረ ይቆጠራል››
ማሳረጊያ
ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ያቆያት የነገስታቱ ጉልበት ብቻ ነው ብለው የሚያስቡ ሰዎች ኢትዮጵያየተሸመነችበትን ውስብስብ ክር ማየት ያልታደሉ ናቸው፡፡ዛሬ ኢትዮጵያን በታትነን ክልላችንን እናድናለንብለው ባደባባይ ሳያፍሩ የሚናገሩ ሰዎችን የምናይበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡በርግጥ ኢትዮጵያ ማእበልከበረታባት እንደ ታይታኒክ ትሰጥም ይሆናል፡፡ግን መርከቢቱ ስትሰጥም የመርከቢቱ ሳሎን ብቻውንአይንሳፈፍም፡፡የመርከቢቱ ጓዳ ብቻውን አይተርፍም፡፡ኢትዮጵያ ስትከስም ብሄሮች ተነጥለው ይለመልማሉማለት ተፈጥሮ አመሏን እንደ ግትቻ የትም ጥላለች ማለት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment