Translate

Friday, August 2, 2013

ድምፃችን ይሰማ፣ ለጁምአ ሐምሌ 26 የታቀዱ ተቃውሞዎች በመላው አገሪቱ አይኖሩም!

የመንግስት የሽብር መግለጫ የሕዝብን አሸናፊነት ያረጋገጠ ነው!

ጁምአ ሐምሌ 26/2005
ሁለት ዓመቱን ሊደፍን በጣም ጥቂት ወራት የቀሩት የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የመብት ማስከበር ሰላማዊ ንቅናቄ እጅግ አስገራሚ ምእራፎችን ተሻግሮ እዚህ ደርሷል፡፡ ንቅናቄው እንደአጀንዳ ያነሳቸው ተፈጥሯዊ እንዲሁም መሰረታዊ የህገ-መንግስት መብቶችና ደንጋጌዎችን መከበር ነው፡፡ ለተጠቀሱት ጊዜያት ያህል በሰላማዊና ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን በጠበቀ መልኩ ያለምንም እንከን የተደረጉት የተቃውሞ ትእይንቶች ብዙዎችን ግርምት ውስጥ ከመክተት በዘለለ መንግስት እውነት በራቀው አንደበቱ /ዜጎች ግብር በሚከፍሉባቸው መንግስታዊ ብዙሀን መገናኛዎች/ ንቅናቄውን ለማጠልሸት የሰነዘራቸው ስፍር ቀጥር የሌላቸው ውንጀላዎች መክነው እንዲቀሩ ዋነኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
ሕገ መንግስታዊ መብቱን ለመንጠቅ መስጂዱ ድረስ የመጣበትን የመንግስት ድርጊት በመቃወም በአዲስ አበባ አወሊያ መስጂድ የተጀመረው የትግል ንቅናቄ አገር አቀፍ የነበረ ሲሆን ሕዝብ ሙስሊሙን በአጠቃላይ ለማካተትም በጣት የሚቆጠሩ ሳምንታት ብቻ ነበሩ ያስፈለጉት፡፡
የመንግስት ያልተገደቡ ፖለቲካዊ እጆች በእያንዳንዱ የመንደር መስጂድ ውስጥ በመግባት በሙስሊሙ ማኅበረሰብ መካከል ዘለቄታዊ ሰለምና አንድነት እንዳይኖር ሲሰሩ የቆዩ በመሆናቸው ሕዝቡ ቁስሉ ሲነካ ነቅሎ እንዲወጣ ትልቁን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ይህ በብሶትና በእልህ ነቅሎ የወጣ ሕዝብ በሰላማዊና በተናበበ መልኩ ተቃውሞውን እንዲያሰማ ደግሞ የመረጥናቸው ኮሚቴዎች ያደረጉት አስተዋጽኦ ቀላል አልነበረም፡፡ የእነሱ የትግል መርህና ስትራቴጂ፣ እንዲሁም ዲሲፕሊን ዛሬ ለምናወራለት የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ንቅናቄ መነሻና ማገናዘቢያ ነው፡፡
ይህን ሁለተኛ ዓመቱን ለማክበር የተጠጋውን የትግል ጉዞ በማስቀጠል የምንገኝበትን የረመዳን ወር ተንተርሶ ጊዜውና ሁኔታዎች የሚጠይቁትን የትግል ስልቶች በመጠቀም በጉዞ ላይ እንገኛለን፡፡ የረመዳን ወር ከገባ በኋላ የተካሄዱ ብርቱ እና ምልአትን የተላበሱ ተቃውሞዎች አብይ መገለጫ ቢሆኑም ከዚሁ ጎን ለጎን በህብረተሰቡ እየተሰሩ ያሉት ሁሉን አቀፍ ትግሎች ሕዝቡ ጥያቄውን ሳያስመልስና ሕገ መንግስታዊ መብቱን ሳያስከበር ፈጽሞ በዝምታ እንደማይሸበብ ያስመሰከረባቸው ናቸው፡፡ መንግስት ምላሽ ከመስጠት ውጪ አማራጭ እንደሌለው በተጨባጭ ያረጋገጠው የባለፈው ሳምንቱ ዓለም አቀፍ ተቃውሞ ደግሞ ሌላ የሕዝቡን እምቅ አቅም ያሳየ ታሪካዊ ትእይንት ነበር፡፡ ይህ ታሪካዊ እለት በአዲስ አበባ ኑር መስጂድ የፈጠረው ተአምራዊ ትእይንት ከሕዝቡ አልፎ መንግስትን ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ የከተተና ለ‹‹ክፉ ጊዜ›› ያዘጋጀውን የባንዲራ ተረት እንዲያወራ ያስገደደ ነበር – የሕዝባዊ ተቃውሞውን ሐያልነት መካድ ባይችልም!
በዚህ ሳምንት የእንቅስቃሴውን ተጽእኖ አሳዳሪነትና ሕገ መንግስታዊ ጥያቄ የማስመለስ አቅም ለማሳደግ የአዲስ አበባው ተቃውሞ ትእይንት ወደ ፍልውሃ ተውፊቅ መስጂድ ሲቀየር የሚጠበቀው የተጽእኖ ፈጣነት አቅም መታየት የጀመረው ገና ከመጀመሪያው የቦታ መቀየር መረጃ መውጣት ጀምሮ ነው፡፡ መንግስት ነውረኛ በሆኑትና የሕዝብን አደራ በበሉት ሚዲያዎቹ ከሰሞኑ ሲያሰራጫቸው የነበሩ መረጃዎች የመንግስት የልብ ትርታ ምን ያህል መጨመሩን ለመናገር ምስክር የሚሹ አይደሉም፡፡ ለህዝቦች ሰላምና ብልጽግና፣ እንዲሁም የአብሮነት ህይወት ብዙ መድከም ያለበት መንግስት በተቃራኒው ህዝቦች በጋራ ተሳስበው እንዳይኖሩ የሚፈነቅለውን ድንጋይ ብዛትና አይነት በሚዲያዎች የተመለከተ የመንግስትን መሰረታዊ ፍላጎት ለመጠየቅ በእርግጥም ይገደዳል፡፡
‹‹ድምጻችን ይሰማ›› ያስተላለፈውን የጁምአውን የፍልውሃ መስጂድ የዝምታና የምልክት ተቃውሞ ጥሪ በእጅ አዙር ሲነካካ የከረመው መንግስት ዛሬ ባወጣው መግለጫ ለህገ መንግስቱ መከበር አንዳችም ደንታ እንደሌለው ሊያሳየን ሞክሯል፡፡ መንግስት በዛሬው መግለጫው በግልጽ ህገ መንግስቱን በመቃረን ዜጎችን ሊያስፈራራ መሻቱ በእርግጥም ዜጎች እጅግ ስለ አገራቸው ህልውና እንዲያስቡ የሚያስገድድ ነው፡፡ መንግስት ያወጣው መግለጫ ፈጽሞ ሃላፊነት የጎደለውና ዜጎችን ለማሸበር የታለመ ነው፡፡ መንግስት በዚህ መግለጫው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እያደረግን ያለነውን ሰላማዊ ትግል በሽብር በመፈረጅና በሙስሊሙ መካከል ክፍፍል በመፍጠር አለመግባባት እንዲነግስ ለማድረግ ጥረት አደርጓል፡፡ ይህ ግን የሚሳካ አለመሆኑን ካለፉት ሁለት አመታት ሂደቶች መንግስት ሊገነዘብ አለመቻሉ አስገራሚ ነው፡፡ ሙስሊሙ ባለፉት ወቅቶች ታስሮና ተደብድቦ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ወንድሞቹን ህይወት በመስዋእትነት ገብሮም ትግሉን መቀጠሉ የቆምንበት የትግል መንገድ የህልውና በመሆኑና ዓላማችን በዛቻና በድብደባ የምንሸሽለት ሳይሆን ጥይትን በደረታችን የምንቀበልበት ጭምር መሆኑን መንግስት መገንዘብ ያሻዋል፡፡
ይህ በፌዴራል ፖሊስ ስም የወጣው መግለጫ ከላይ እንደገለጽነው የንቅናቄያችንን ተጽእኖ ፈጣሪነት ያሳየ ሲሆን መንግስት ተገዶም ቢሆን የንቅናቄውን ዳና እየተከተለ ምላሽ በመስጠት እንዲጠመድና ዋነኛ የቤት ስራው እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በዛሬው መግለጫ የተገነዘብነው ሀቅም ይኸው ነው፡፡ ይህ ንቅናቄ ህዝባዊ መሰረት ያለውና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በምልአት እየመሩትና እየተሳተፉበት ያለ እንቅስቃሴ መሆኑ ለመንግስት ደጋግሞ አልዋጥ ቢለውም በመሬት ላይ ህዝቡም ሆነ ሚዲያው የሚመለከተው እውነታ ግን ያንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት እውነታውን ለመካድ ሕዝባዊ ንቅናቄውን ከሚፈልጋቸው ስያሜዎች ጋር በማያያዝ የተለየ ትኩረት ለማግኘት ያደረገው ጥረት በፍጹም ሊሳካ አይችልም፡፡ ሊካሄድ የተቀጠረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ለማስቆም የተሰጠው መግለጫ ከዚህ አንጻር ፍሬ ቢስና ዋጋ አልባ ነው፡፡ በመሰረቱ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በአገሪቱ ባሉት መስጂዶች ሁሉ ሀይማኖታዊ ስርአቱንም ሆነ ድምጹን የማሰማት የማይገረሰስ መብት አለው፡፡ ይህ መብቱም በምንም አይነት መልኩ እንዲቀማ እድል የሚሰጥበት መንገድ የለም፡፡ ሆኖም በተለያዩ ጊዜያት የሰላማዊ ትግሉን ህልውና ለመጠበቅና የተሻለ ፍሬያማ ውጤት ለማስመዝገብ የተለያዩ የስትራቴጂ ለውጦችን ስናደርግ መቆየታችን አይካድም፡፡
የህዝባችን ተጨባጭ ሂደቶች እና ነባራዊ ሁኔታዎች ሳይፈቅዱ ሲቀሩ ያወጣናቸውን መንገዶች በመተው አዲስ መስመር እያሰመርን ስንሄድ እንደነበር ለማወቅ የባለፉትን ሁለት ዓመታት ጉዞዎች መታዘብ በቂ ነው፡፡ የሰላማዊ ትግል ሁነኛ መርህም እንደሁኔታዎች ባህሪ ተለዋዋጭነት ስልቶችን እየቀያየሩ የተጽእኖ ደረጃን ከፍ ማድረግ ነው፡፡ በቀደመው ወቅት በአንዋር መስጂድ ሊካሄዱ የነበሩት ሁለት የተቃውሞ መርሐ ግብሮች መሰረዝም መነሻቸው ይኸው ነበር፡፡ በእለተ ጁምአ በአገር አቀፍ ደረጃ፣ በተለይም በአዲስ አበባ ፍልውሃ ተውፊቅ መስጂድ ልናካሂድ ያሰብነውን የዝምታ እና የምልክት ተቃውሞ በሌላ የሁከት ትርኢት ለመቀየር በመፎከር ላይ የሚገኘው መንግስት የቀድሞዎቹን ዘመናት እንድናስታውስ የሚያስገድዱ መግለጫዎችን በመደርደር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ የተቃውሞ ትእይንታችንን ወደ ሌላ ትርኢት የመለወጥ እኩይ ፍላጎት ያዘለ የመንግስት ጥረት እንዳይሳካና ቀጣይ የትግሉን ሜዳ ለማመቻቸት በማሰብ በነገው እለት ሊካሄዱ የታሰቡት አገር አቀፍ ተቃውሞዎች በሙሉ መሰረዛቸው እጅግ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
በነገው እለት ሊካሄዱ ታስበው የነበሩ ተቃውሞዎች እንደተለመደው ፍጹም ሰላማዊና የተለመዱትን ዲሲፕሊኖች የጠበቁ ሆነው የሚካሄዱ መሆኑ ምንም ጥርጥር የሌለው ቢሆንም፣ እንዲሁም ኅብረተሰቡ ለሃይማኖቱ መስዋእትነት ለመክፈል እጅግ ራሱን አዘጋጅቶ የሚጠባበቅ ቢሆንም የመንግስትን ጸብ አጫሪነት በመረዳትና የትግሉን የወደፊት የስኬት እድሜ በመገንዘብ የነገውን ተቃውሞ በአገር አቀፍ ደረጃ መሰረዙ አስፈላጊ ሆኗል፡፡ ከመግለጫው መውጣት በኋላ በመስጂዶች አካባቢ የተደረጉ ውይይቶችና በውስጥ መልእክት የደረሱን አስተያየቶች ፕሮግራሙ ባለበት እንዲቀጥልና የመጣውን ለመቀበል አጥብቀው የሚያሳስቡ ቢሆንም የመንግስትን ደርሶ ጠብ አጫሪነት በሰላማዊነት ማሸነፍ በራሱ ትልቅ ድል በመሆኑ መርሀ ግብሩን የመሰረዝ ውሳኔ ላይ ደርሰናል፡፡ በመሆኑም የነገውን የጁምአ ሰላት በአገር አቀፍ ደረጃ በአቅራቢያችን በሚገኙ መስጊዶች ብቻ ያለምንም የተቃውሞ መርሀግብር እንድናሳልፋቸው ተወስኗል፡፡ የፍልውሀ ተውፊቅ መስጂድን ትእይንት ዛሬ ባናደርገውም በቅርቡ በተሻለ ቅድመ ዝግጅት የምናደርገው መሆኑና የአገሪቱ መስጂዶች በሙሉም የሙስሊሙ ህብረተሰብ ንብረቶች መሆናቸው ፈጽሞ መረሳት አይኖርበትም፡፡ ሆኖም በዚህ ተቃውሞ ልናገኝ የምንችለውን ድል አሁንም በመንግስት መግለጫ ሙሉ በሙሉ ያየነውና የተረዳነው ሐቅ መሆኑ ከግምት ውስጥ ይገባል፡፡ ሕዝቡ በትግሉ ያየው ውጤትም የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ንቅናቄ የአገሪቱ ቁጥር አንድ አጀንዳ እንደሆነና ይህ መለወጥ የሚችለውም የሙስሊሙ ጥያቄ ያለምንም መሸራረፍ ሲመለስ ብቻ መሆኑን ማስገንዘቡን ነው፡፡ ለገዢዎቻችን የምናስተላልፍላቸው መልእክትም ይኸው ነው፡፡ ጥያቄያችን በፍፁም ዛቻና ማስፈራሪያም ሆነ የሀይል እርምጃ ሊገታ አይችልም፡፡ የህዝቡ ማእበል ወደቤቱ ሊመለስ የሚችለው ሕጋዊ ጥያቄዎቻችን ተገቢውን ምላሽ ሲያገኙ ብቻ ነውና፡፡
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment