Translate

Thursday, August 29, 2013

ሰማያዊ ፓርቲ በሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ላይ ተቃውሞ አቀረበ

ፓርቲው ከ33ቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ ጋር ተለያየ

yiliqal


በግንቦት ወር 2005 ዓ.ም. የመጀመሪያውን የተቃውሞ ሠልፍ ያካሄደው ሰማያዊ ፓርቲ፣ በመጪው እሑድ በሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በተዘጋጀው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ተቃውሞ አቀረበ፡፡

ሁለተኛውንና በርካታ ሰዎች እንዳሚሳተፉበት ሲገልጽ የከረመውን ሰላማዊ ሠልፍ የሚያካሄደው ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. እንደነበር ፓርቲው አስታውቆ፣ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በተደራቢነት በዕለቱ ሠልፍ እንደሚያደርግ ያስተላለፈው ጥሪ ትክክል አይደለም ብሏል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ነሐሴ 20 ቀን 2005 ዓ.ም. ያስተላለፈውን፣ ‹‹አክራሪነትና ጽንፈኝነትን እናውግዝ›› የሚል የሠልፍ ጥሪ የተቃወመው ሰማያዊ ፓርቲ፣ ከአንድ ወር በላይ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሲያስተዋውቅና ጥሪ ሲያደርግ መክረሙን ገልጿል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚያደርግ ቀድሞ ማሳወቅ ለሚገባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በደብዳቤ ማስገባቱን፣ የፓርቲው ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌታሁን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡
‹‹እኛ በጠራነው ሰላማዊ ሠልፍ ላይ ሌላ ሠልፍ እንዲጠራ መፍቀድ መንግሥት በትንሹ የከፈተውን ቀዳዳ ለመዝጋት ፈልጐ ነው፤›› የሚሉት ሊቀመንበሩ፣ በተመሳሳይ ቦታና ሰዓት ሰላማዊ ሠልፍ መጥራት ለምን እንዳስፈለገ ግልጽ እንዳልሆነላቸውና መንግሥት የጉባዔውን ሠልፍ እንዲሰርዝ ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት የተጠሩ ሁለት የተለያዩ ዓላማና ይዘት ያላቸው ሰላማዊ ሠልፈኞች ሲገናኝ ወደ ግጭት ሊያመሩ ስለሚችል፣ መንግሥት ፓርቲው ቀድሞ መጥራቱንና ለሚመለከተው አካል ማሳወቁን በመገንዘብ ዕርምጃ እንዲወስድ፣ ፓርቲው ነሐሴ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ መግለጫ ማውጣቱን ኢንጂነር ይልቃል ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ሰማያዊ ፓርቲ ለበርካታ ወራት አንድነት ፓርቲን ጨምሮ ከ33 ፓርቲዎች ስብስብ ጋር ኅብረት ፈጥሮ ሲሠራ የቆየ ቢሆንም፣ ሰሞኑን ከስብስቡ እንዲወጣ መደረጉ ተሰምቷል፡፡ ከ33ቱ ፓርቲዎች ስብስብ መገለሉን በሚመለከት አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የሰጡት ኢንጂነር ይልቃል፣ ‹‹የሚያግባባን ነገር ሲገኝ በጋራ ሆነን ለመሥራት ተስማማን እንጂ፣ ማንም ተባራሪና አባራሪ የለም፡፡ መሰብሰባችን በስምምነት እንጂ የሕግ ድጋፍ ኖሮት የተደረገ ስምምነት አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን መግለጫ ሲሰጡ፣ ‹‹ለኢትዮጵያ ሕዝብና ፖለቲካ የሚመጥን የፖለቲካ ፓርቲ አለ ብለን አናምንም፤›› ማለታቸውና ሰማያዊ ፓርቲ እየጣረ ያለው ክፍተቱን ለመሙላት መሆኑን መናገራቸው ሌሎቹን ማስከፋቱ ይነገራል፡፡
የ33 ፓርቲዎች ስብስብ፣ ‹‹እንዴት እንደሌለን እንቆጠራለን?›› የሚል ጥያቄ አንስቶ እንደነበር መስማታቸውን የተናገሩት ሊቀመንበሩ፣ ለምን እንደተናገሩ ጠርተው ሳያናግራቸው ስንቶቹ ተሰብስበውና በስንት ድምፅ ወስነው አብረው መቀጠል እንደማይችሉ ሳይገለጽላቸው ስለመለያየት ማውራት፣ ለእሳቸው የልጆች ጨዋታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹እኛ ከወጣን ከ33 ፓርቲዎች ስብስብ ውስጥ ሰው የሚያውቀውና ስሙ የሚታወቅ ፓርቲ ይኖራል እንዴ?›› ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እውነትን በአደባባይ መናገር ስላልተለመደ እንጂ ሰማያዊ ፓርቲ ‹‹ለምን ተናገረ?›› በሚል አብሮ አለመሥራትን ማወጅ፣ ሕዝቡን ተስፋ ከማስቆረጥ ያለፈ ጥቅም እንደሌለው ኢንጂነር ይልቃል ጠቁመዋል፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር)

በመስቀል አደባባይ የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ እያወዛገበ ነው

‘‘ቀድመን ሰልፍ የጠራነው እኛ ነን’’ ሰማያዊ ፓርቲ
‘‘የቀደምነው እኛ ነን’’ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ
‘‘ሰማያዊ ፓርቲ በዕለቱ የሚያካሂደው ሰልፍ ህገ-ወጥ ነው’’ የአ.አ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍ፣ የስብሰባና የማኀበራት ፈቃድ ጽ/ቤት
በመጪው እሁድ ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ በማወዛገብ ላይ ነው። ቀደም ሲል ሰማያዊ ፓርቲ በዕለቱ ሰልፍ እንደሚያካሂድ ቢያስታውቅም፤ የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽ/ቤት በበኩሉ ነሐሴ 20 ቀን 2005 ዓ.ም በጽ/ቤቱ በሰጠው መግለጫ በተመሳሳይ ቀን ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱን ይፋ አድርጓል።
ይህንን ተከትሎ በፓርቲው እና በአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ መካከል የቀደምኩት እኔ ነኝ በማለት በመወዛገብ ላይ ሲሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍና የስብሰባ ማሳወቂያ ጽ/ቤት በበኩሉ፤ ሰልፍ እንደሚካሄድ ቀድመው ያሳወቁት የሃይማኖት ተቋማቱ በመሆኑ በዕለቱ የሰማያዊ ፓርቲ ሰልፍ የሚካሄድ ከሆነ ህገወጥ ነው ብሏል።
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂነር ይልቃል ጌትነት ጉዳዩን በማስመልከት ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገሩት ፓርቲው ከወር በፊት ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚያካሂድ በጽ/ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ማድረጉን በማስታወስ ፓርቲያቸው ሰላማዊ ሰልፉን ለማካሄድ በቅድሚያ ጥያቄ ማቅረቡን ተናግረዋል።semayawiparty
እንደ ፓርቲው ሊቀመንበር ገለፃ ፓርቲው አስቀድሞ ቀን መቁረጡንና በተባለውም ቀን ሰልፉን ለማካሄድ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላማዊ ሰልፍ፣ ስብሰባና የማኀበራት ፈቃድ ጽ/ቤት በአካል በመቅረብ ጭምር የማሳወቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን ተናግረዋል። በወቅቱ ጽ/ቤቱ ደብዳቤውን ለመቀበል ፍላጎት ባያሳይም በህጉ መሠረት ማሳወቅ ብቻ በቂ በመሆኑ ደብዳቤውን በጽ/ቤቱ አስቀምጠው መመለሳቸውንና በኋላም ጽ/ቤቱ በፖስታ ቤት በኩል በሬኮማንዴ ለፓርቲው ሰልፍ የት እንደሚያካሂድ፣ ምን ያህል ሰው እንደሚሳተፍ ማብራሪያ በመጠየቁ ፓርቲው በበኩሉ ለጽ/ቤቱ ወዲያውኑ ምላሽ መስጠቱን ተናግረዋል። ሆኖም ጽ/ቤቱ በህጉ መሠረት በ48 ሰዓታት ውስጥ ምላሽ መስጠት ሲገባው ዝምታን በመምረጡ፣ ዝምታው ደግሞ ሰልፉ እንደተፈቀደ የሚጠቁም በመሆኑ በሰልፉ ዙሪያ ፓርቲው ዝግጅት ማድረግ መቀጠሉን አስታውቀዋል።
ከጽ/ቤቱ እስካሁን (ነሐሴ 21 ቀን 2005 ዓ.ም) ምላሽ ባለመገኘቱም ፓርቲው በዕለቱ የጠራውን ሰለማዊ ሰልፍ ከማካሄድ ወደኋላ የሚመልሰው የህግ መሠረት ባለመኖሩ ሰልፉን እንደሚያካሂድ አስታውቀዋል። ፓርቲው ከነገ ሐሙስ ጀምሮ በአምስት ተሽከርካሪዎች በአስሩም ክፍለ ከተማ መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ ለማካሄድ መዘጋጀቱን ተናግረዋል። በመላ ከተማዋና በአካባቢዋም በመቶ ሺህ የሚቆጠር ወረቀት እንደሚበተንና ሰልፉም ካለፈው ሰልፍ ልምድ በማግኘት ከፍተኛ ስራ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ባለፈው ሰኞ (ነሐሴ 20 ቀን 2005) በዋና ጽ/ቤቱ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱን ያስታወቀው የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የቦርድ ሰብሳቢ ርዕሰ ደብር በሪሁን አርአያ በተለይ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት በዕለቱ ሰማያዊ ፓርቲ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራቱን እንደማያውቁና ጽ/ቤታቸውም ቀደም ብሎ ሰልፉን ሲያዘጋጅ መቆየቱን ተናግረዋል።
ምንም እንኳ ርዕሰ ደብር በሪሁን አርአያ የሃይማኖት ጽ/ቤቱ በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ያሳወቀበትን ቀን ለመናገር ባይፈልጉም በዕለቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በሰጡበት ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ በ10ሩም ክፍለ ከተሞች እና በ116 ወረዳዎች በተካሄደ ሕዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፍትህ ቢሮ ጋር በመተባበር በከተማ ደረጃ ነሐሴ 15 እና 16 ቀን 2005 ዓ.ም በተዘጋጀው ማጠቃለያ የሰላም ኮንፈረንስ የተለያዩ ሃይማኖት መሪዎችና ተከታዮቻቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከተማችን እየታየ ያለው የአክራሪነትና የፅንፈኝነት እንቅስቃሴ የሀገራችንን ልማት የሚያውክ፣ በሰላም አብሮ የመኖር እሴቶቻችንን የሚያናጋ እና የሃይማኖት መልክ የሌለው የጥፋት እንቅስቃሴ ከመሆኑም በላይ በሕገ-መንግስታችን የተደነገገውን የኃይማኖት እኩልነትና የእምነት ነፃነት የሚፃረር ስለሆነ በሰላማዊ ሰልፍ ተቃውሞአችንን እንግለፅ በማለት የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች መንግስት ሁኔታዎችን እንዲያመቻች፣ የኃይማኖት ተቋማት የጋራ ጉባኤም እንዲያስተባብር መወሰኑን ተናግረዋል።
ከዚህ መግለጫ መረዳት የሚቻለው የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽ/ቤት ሰልፉን ለማካሄድ ጥያቄ ያቀረበው ነሐሴ 15 እና 16 በኋላ መሆኑን መረዳት ይቻላል። በአንፃሩ ሰማያዊ ፓርቲ ነሐሴ 16 ቀን 2005 ዓ.ም የማሳወቂያ ደብዳቤ ማስገባቱን አመልክቷል።
የአዲስ አበባ ሰላማዊ ሰልፍና ስብሰባ ማሳወቂያ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማርቆስ ብዙነህ ጉዳዩን በተመለከተ የእውቅና ጥያቄ በማቅረብ ቀዳሚ የነበሩት የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጽ/ቤት በመሆናቸው ሰማያዊ ፓርቲ በዕለቱ ሰልፍ እንዲያካሂድ አልተፈቀደለትም ብለዋል። ሰልፉ የሚካሄድ ከሆነም ህገወጥ ነው ከማለት ውጪ ሁለቱም ወገኖች የሰላማዊ ሰልፍ ያሳወቁበትን ቀን እና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ከመናገር ተቆጥበዋል። (ምንጭ: ሰንደቅ)

No comments:

Post a Comment