Translate

Monday, August 19, 2013

ዋስትናችን እርቅ ብቻ ነው!

“እኛ የእሳት አደጋ ብርጌድ የለንምና ዋ!!'' ኦባንግ

recon-e
እሳት ሲነሳ የመጀመሪያው ተግባር እሳቱን በፍጥነት ማጥፋት ለሚችለው የእሳት አደጋ ብርጌድ መደወል ሲሆን፣ ቀጣዩ ተግባር እሳቱ በተነሳበት አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ነፍስ አትርፈው እሳቱን በተገኘው መንገድ ለማጥፋት መረባረብ ነው። ይህ የተለመደው ተግባር ዛሬ በኢትዮጵያ ስለመስራቱ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ ዋና ዳይሬክትር ስጋት አላቸው። እናም “እኛ የእሳት አደጋ ብርጌድ የለንምና ዋ!!” የሚል ማስጠንቀቂያ አዘል ጥሪ ያሰማሉ።
“አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ እሳቱ ፊትና መልክ ይዞ ሲቀጣጠል አላነውም እንጂ በርካታ የማቀጣጠያ ቅመሞች ተዘጋጅተውለት ለመንደድ በዝግጅት ላይ ነው። መንደዱ የማይቀረው ይህ እሳት ቢነሳ የሚያጠፋው የለም” የሚሉት አቶ ኦባንግ ሜቶ፣ ጥላቻው በሰፈር ደረጃ ከርሯል ይላሉ። በየመንደሩ ህዝብ እንዲቧደን ተደርጓል። ሚና ለይቷል። አገር የሚመራው መንግሥትም ችግሩን ከመፍታትና አገሪቱን ከስጋት ከማላቀቅ “ጥሪ አይቀበልም” በሚል የሃይል ርምጃ መምረጡ ነገሮችን ይበልጥ እንዳወሳሰበ ይናገራሉ።
በየአቅጣጫው ያሉ ወገኖች ቆም ብለው ሊደበቁት ከማይችሉት ከህሊናቸው ጋር ሊነጋገሩ እንደሚገባ ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “ግብጾች ግብጾችን ገደሉ፣ ገና ቀውሱ ይቀጥላል። ይህ እጅግ ዘግናኝ የሆነው ቀውስ እኛ ዘንድ ሳይደርስ ወደ እርቅ እናምራ። ለእውነተኛ እርቅ ጊዜው አሁን ነው” በማለት አንገብጋቢ ያሉትን ጥሪ ያስተላልፋሉ።
“ላለፉት 22 ዓመታት ኢትዮጵያ ላይ ከየአቅጣጫው የተረጨው መርዛማ ፖለቲካና፣ ሰብአዊነት የጎደለው አስተዳደራዊ መዋቅር የፈጠረው ውጥረት ወደ መፈረካከስ እየነዳን ነው” በማለት የስጋቱን መጠን የሚጠቁሙት አቶ ኦባንግ ፣ በግብጽ የተፈጠረው ቀውስ በሃይል ሊቆም የማይችልበት ደረጃ ሲደርስ ምዕራባዊያንም ሆኑ አሜሪካ የሃዘን መግለጫ ከማውጣት የዘለለ ስራ አለመስራታቸው ለኢትዮጵያዊያን ታላቅ ትምህርት ሊሆን እንደሚገባ ያሰምሩበታል።
በሩዋንዳ ለቁጥር የሚያዳግቱ ሰዎች አልቀዋል። በኮሶቮ ህዝብ ተጨፍጭፏል። ዳርፉር ንጹሃን የጥይት ራት ሆነዋል። ይህ ሁሉ ከመሆኑ በፊት ሃያላን መንግስታትና “ድርጅቶቻቸው” በእነዚህ አገራት ውስጥ ነበሩ። እያወቁት ነው የሆነው። ግን ጉዳዩ የጥቅም ችግር ስለማይፈጥርባቸው አገራቱ በደም ጎርፍ ሲታጠቡ በዝምታ ተመልክተው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ኦባንግ፣ “ሶሪያ ስትፈርስ፣ ከ100 ሺህ ሰው በላይ ሲያልቅና አሁንም እያለቀ ባለበት ሁኔታ እልቂቱን ማስቆም እየቻሉ ዝምታን መርጠዋል” በማለት አቶ ኦባንግ ከነዚህ አገሮች፣ በተለይም “አሁን ግብጽ ላይ በተፈጠረው ችግር ካልደነገጥንና ለሚቀርበው የእርቅ ጥያቄ መልስ ለመስጠት የማንዘጋጅ ከሆነ አደጋው የከፋ ሊሆን ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ጥያቄው የስልጣን ሳይሆን አገሪቱ ላይ ያንዣበበውን የሞት አደጋ የመግፈፍ አንደሆነ፣ ይህ አሁን ያንዣበበው የቀውስ ደመና ባስቸኳይ ካልተገፈፈ መከራው የሁሉም ወገን እንደሚሆን ጥርጥር እንደማያሻው የጠቆሙት አቶ ኦባንግ “ንጹህ ልብናና ንጹህ ህሊና ያላችሁ ውጡ፣ ለእውነተኛ እርቅ እንስራ፣ አገሪቱንም እናድን፣ የእሳት አደጋ ብርጌድ የለንምና እኛው አገራችንን በማስቀደም እንታደጋት” ሲሉ ከወትሮው በተለየ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በምርጫ ፕሬዚዳንት ሆነው በዓመጽ መፈንቅለ መንግሥት የተደረገባቸው ፕሬዚዳንት ሙርሲን የሚደግፉ የሙስሊም egyptወንድማማች ፓርቲ ደጋፊዎች ላይ የሃይል ርምጃ ከመወሰዱ በፊት በግብጽ ይህ ችግር ሊደርስ እንደሚችል የወተወቱ ነበሩ። ፕሬዚዳንት ሙርሲ ከስልጣን የተወገዱበት አግባብ ቀውስ ሊያስነሳ እንደሚችል ቢነገርም ሰሚ ባለማግኘቱ ቀውሱ ግብጻዊያንን እርስ በርስ አጋደለ። ግብጾች ግብጾችን ጨፈጨፉ። እስከ ሁለት ሺህ የሚደርሱ ሰዎች የተገደሉበት ይህ ቀውስ እንዴት ሊቆም እንደሚችል ፍንጭ የለም። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ የሰዓት እላፊ፣ ግድያና እስር ዓመጹን ሊገታው አልቻለም። ይልቁኑም መሳሪያ የታጠቁ ተቃዋሚዎች ግብጽን በጥይት እያመሷት ነው። እየገደሉም ነው።
በኢትዮጵያም በተለያዩ ወቅት የተነሱ የህዝብ ጥያቄዎችን በጸረ ሽብር ህግ፣ በእስር፣ በድብደባ፣ በግድያ፣ በማስፈራሪያና በጡንቻ የማስተናገዱ አዝማሚያ ከእለት እለት መጠናከሩ የሚከፋቸውን ሰዎችና ቡድኖች እያበራከተ ነው። የተፈናቀሉ ወገኖች ተበራክተዋል። በተፈናቀሉና መሬታቸው እየተቸበቸበ ያሉ ወገኖች ምሬት የከፋ ደረጃ ደርሷል። ሚዛናዊ ያልሆነው የአስተዳደር መዋቅርና የኢኮኖሚ ልዩነት የፈጠረው ቅሬታ በቃላት የሚገለጽ አልሆነም። እንደ አቶ ኦባንግ ሁሉ እርቅ አስፈላጊ እንደሆነ በማመን እየሰሩ እንደሆነ የሚናገሩትና ለጊዜው ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ታዋቂ ምሁር ለጎልጉል እንደተናገሩት “በአሁኑ ወቅት ጥላቻው ከርሮ ህዝብ በገሃድ ስምና ብሔር እየለየ ፊት ለፊት መናገር ጀምሯል፤ የኑሮው ውድነት፣ የመብት ረገጣው፣ ዕንግልቱ፣ … የጥላቻውን መጠን አደባባይ ላይ እንዲታይ እያደረገው መጥቷል። አገራችን ያለችበት መንገድ አደጋ አለው። እርቅ የግድ ነው” ብለዋል፡፡
እኚህ ምሁር “ኢህአዴግ ውስጥ እርቅ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያምኑና አሁን በየአቅጣጫው ያለው ችግር የሚያሳስባቸው ወገኖች ስላሉ እነዚህን ወገኖች በመቅረብ ለእውነተኛ እርቅ ለመስራት ጊዜው አሁን፣ ለዚያውም ሳይረፍድ በቶሎ ሊሆን ይገባል። ይህንን ካላደረግን ሁላችንም እናዝናለን። ይቆጨናል። በቀላሉ ልናልፈው ወደ ማንችልው ጣጣ ውስጥ ሳንገባ እንረባረብ” በማለት ተናግረዋል። አስተያየት ሰጪው በቅርቡ ራሳቸውን ገልጸው አስተያየት እንደሚሰጡ፣ ለጊዜው የተጀመሩ ስራዎችን በነጻነት ለመስራት ሲሉ  ራሳቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡበትን ምክንያት ተናግረዋል።
“አገር እንደ ሰው አካል ነው። አንድ ቦታ ሲታመም ስሜቱ የሙሉው አካሉ እንጂ የተጎዳው አንድ ክፍል ብቻ አይደለም” በማለት የማጠቃለያ አስተያየት የሰጡት አቶ ኦባንግ፣ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ሲቋቋም ዓላማው ሁሉም ነጻ የማውጣት ታላቅ ዓላማ አንግቦ በመሆኑ በዚህ ረገድ በቅርቡ የእርቅ ተግባሩን ሊከውን የሚያስችለውን እቅዱንና የድርጊት መርሃ ግብሩን ይፋ እንደሚያደርግ፣ ለዚሁም ተግባራዊነት ኮንፍራንስ እንደሚያዘጋጅ አመልክተዋል።
በነጻ አውጪ ስም መደራጀትና መታገል ሙሉውን አካል /አገር/ ሊያድን እንደማይችል ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “አሁን ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ጉራጌ፣ ወላይታ፣ ከንባታ፣ ሲዳማ፣ ከፊቾ … እያልን በተበጣጠሰ አመለካከት ከማነከስ የአገራችንን ህልውና በአንድ ትልቅ አጀንዳ ውስጥ በማካተት ለመስራት ድርጅታችን ለሚያቀርበው ጥሪ ህዝብና ጥሪ የሚደረግላቸው ወገኖች ሁሉ ቀና ምላሽ ሊሰጡ ይገባል” ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ሙስሊም፣ ኦርቶዶክስ፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት፣ ወዘተ በማለት ከብሄርና ጎሳው ልዩነት በተጨማሪ መለያየት መፈጠሩ የአገሪቱን እጣ ፈንታ አሳዛኝና አደጋ እንኳ ቢፈጠር ለተግሳጽ የሚፈራ ሰው እንዳይኖር ማድረጉ አሳሳቢ የሆነባቸው በርካታ ዜጎች አሉ። አቶ ኦባንግ እንደሚሉት ግን ሁሉም ቦታ የፖለቲካ ኮተት የሌለባቸው፣ ንጹህ ልብና ያላቸውና ህሊናቸውን የሚያከብሩ አሉ። እነዚህ ወገኖች ብቸኛ አማራጭ በሆነው እርቅ ላይ አበክረው መስራት እንደሚገባቸው አመልክተዋል። እሳቸው የሚመሩት አኢጋንም ለእንደዚህ አይነቶቹ ንጹሃን በሩ ክፍት መሆኑን አረጋግጠዋል።
በመጨረሻም “አሁን ችግር በተባባሰባቸው ቦታዎች ሁሉ ‘እርቅ’ እንደ መፍትሄ የሚቀርበው፣ ዓለም አሁን ከመቻቻል ሌላ አማራጭ ስለሌላት ስለሆነ እኛም እርቅ ላይ ያለአንዳች ማቅማማት መስራት ይገባናል፤ ይህ ዕርቅ ግን በደፈናው ምህረት የሚያሰጥ ሳይሆን በፍትህ ላይ የተመሠረተ ነው” ያሉት አቶ ኦባንግ “ድርጅታችን እርቅ ላይ ያለው ሃሳብ ከሌሎች በተለየ የተቋቋምንበት፣ የሰፋና የተፈጠርንበት መሰረት በመሆኑ ይህንን ሃላፊነት በመውሰድ እስካሁን የሰራናቸውን ስራዎች ውጤት ለህዝብ ይፋ እናደርጋለን፤ ይህም እንደወቅቱ ሁኔታ ተለዋዋጭ ሳይሆን የጋራ ንቅናቄው ገና ከጅምሩ የወጠነውና እስካሁን ለዓመታት ሲሰራበት የቆየ ጉዳይ ነው። ኢህአዴግም ሰላም ስለሚያስፈልገው፣ ባለስልጣኖቹም መኖር ስለሚፈልጉ፣ ደጋፊዎቹም ዋስትና ስለሚያሻቸው የተቃዋሚ ወገኖችም አገራቸውን ስለሚያስቀድሙ፣ ሁሉም ወገኖች ቀና ምላሽ ይሰጣሉ ብለን እናምናለን” የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል።

No comments:

Post a Comment