(የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎች)
ሼኽ መሐመድ “ለቀቅ አድርጉን” አሉ
ከኢትዮጵያ “አንድም ሳንቲም” እንዳልወሰዱ ተናገሩ
ባለፈው ሳምንት ከፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲ የገዟቸውን የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ፣ የጐጀብ እርሻ ልማትና የቡና ማደራጃና ማከማቻ ድርጅት የርክክብ ፊርማ በሆቴላቸው ሸራተን አዲስ መጋቢት 26 ቀን 2005 ዓ.ም. ውለታ በፈጸሙበት ወቀት “አንዳንድ የመገናኛ ብዙኅን እባካችሁ ለቀቅ አድርጉን እንሥራበት፡፡ አሁን ጊዜው የሥራ ነው እንጂ የአሉባልታ አይደለም፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናትንም አትጨቅጭቋቸው፡፡ ውጤቱን የሚያውቁት እነሱ ናቸው፡፡ ለእናንተ በሬ እንኳ ዝግ ነው፡፡ እባካችሁ በአገር ልማት ላይ እወቁበት፡፡ ነገር ፍለጋ፣ ቁስቆሳና አሉባልታ አያዋጣም፤ አገራችንን እንገንባ፤” በማለት ማሳሰቢያ አዘል መልዕክት ማስተላለፋቸውን ሪፖርተር ዘገበ።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት በስነ ስርዓቱ ላይ የተለያዩ ሚዲያዎች እንዲገኙ በጋበዘው መሰረት ሪፖርተር ጋዜጣ ሸራተን ሆቴል የላካቸው ጋዜጠኞች “ሪፖርተር ከሚድሮክ ጋር ተስማምቶ እስከሚሠራ ድረስ ከእኛ ጋር እንዲሠራ አንፈቅድለትም፤” በማለት በሆቴሉ ጥበቃዎች አማካይነት እንዳስወጣቸው ሪፖርተር ዘግቧል። ባለሃብቱ በፊርማው ስነስርዓት ላይ “አንድም ሳንቲም አልወሰድንም። የምናለማው ከውጪ በምናስገባው ገንዘብ ነው” ማለታቸውንና፣ የኤጀንሲው ዳይሬክተርም አብዝተው እንዳመሰገኑዋቸው ሪፖርተር አስታውቋል። ሪፖርተር ሼኽ መሐመድን በተመለከተ እየተከታተለ ዜና የሚያቀርብ ብቸኛ ጋዜጣ መሆኑ ይታወቃል። ከዚሁ ጋር ተያያዥነት እንዳለው በሚነገርለት ኦፕሬሽን የጋዜጣው ባለንብረት አቶ አማረ አረጋዊ የግድያ ሙከራም እንደተደረገባቸው ይታወሳል። (ፎቶ: ሪፖርተር)
ቴዲ አፍሮ አይኑን በአይኑ አየ
ከሳምንት በፊት አፕሪል ዘፉል እየተባለ በሚቀለድበት ቀን፣ ቴዲ አፍሮ ከባለቤቱ አምለሰት ሙጬ ጋር ፍቺ ፈጸመ በሚል ወዳጆቹን ያስደነገጠ ዜና መዘገቡ ይታወሳል። ይህ ኢትዮጵያዊ ወግ የሌለው “ከርዳዳ” ቀልድ ላስደነገጣቸው ሁሉ ቴዲ አዲስ ዜና ይዞ ብቅ ብሏል።
ኢኤምኤፍ እንደዘገበው ቴዲ አፍሮ የወንድ ልጅ አባት ሆኗል። ቴዎድሮስ ካሳሁን ወንድ ልጅ ካገኘ ስሙን “ሚካኤል” ብሎ እንደሚጠራው አስቀድሞ በተናገረው መሰረት የባለቤቱ ውድ ስጦታ የሆነውን ወንድ ልጅ ሚካኤክ ቴዎድሮስ ካሳሁን ብሎ እንደጠራው ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል። ቴድሮስም ሆነ ባለቤቱ ለወደፊት ስንት ልጅ የመውለድ እቅድ እንዳላቸው እስካሁን በይፋ አልተናገሩም። ዝግጅት ክፍላችን ለቴዲ አፍሮና ለባለቤቱ እንዲሁም ለአድናቂዎቻቸው በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ ይላል። (ፎቶ: teddyafro.info/)
ከ106 በላይ ክስ ያለበት ተመስገን “እንታገል” አለ
የፍትህ ጋዜጣ ሲታገድ አዲስ ታይም የሚል መጽሔት ማሳተም ጀምሮ ነበር። ፍትህን የከረቸሟት አምባገነኖች አዲስ ታይምንም ጠረቀሟት። ለሶስተኛ ጊዜ ልዕልና ጋዜጣ ማሳተም የጀመረው ተመስገን ደሳለኝ አሁንም ለሶስተኛ ጊዜ የማሳተምህጋዊ መብቱ ተገፏል። አጋጣሚውን የኮነነው ተመስገን “ያለኝ አማራጭ ከሲቪክ ተቋማት ጋር በመተባበር፣ ከጫካ ትግል በመለስ ያሉትን የሰላማዊ ትግል አማራጮች በመጠቀም፣ አስገዳጅ ሁኔታ በመፍጠር መብታችንን እናስከብራለን” ማለቱን ኢሳት አስታውቋል።
“ዜና በጫወታ” በሚል ገጽ የሚጽፈው አቤ ቶኪቻ “እንኳን ልዕልና መለስም ተሰውተዋል” በማለት ልዕልና መሰዋትዋን በኢህአዴግ ቋንቋ በመግለጽ አምባገነኖቹን ተሳልቆባቸዋል።
“ልዕልናጋዜጣ ታግዳለች፤ እንደ “ፍትህ” እና አዲስ ታይምስ ሁሉ የስርዓቱ የአፈና ሰለባ ሆናለች፤ የሚገርመው ግን መታገዷ አይደለም፣ የታገደችበት መንገድ እንጂ፡፡ ከዚህ ቀደም ደጋግሜ እንደገለፅኩት አቶ መለስን የተኩት ሰዎች ከእርሱም የባሱ ጭፍን አምባገነኖች ናቸው፡፡ ማንንም አይፈሩም፡፡ እግዚአብሄርንም ቢሆን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ካልተጠመቅህ አምላክ ሆነ እንድትቀጥል አንፈቅድልህም” እንደሚሉ ተመስገን ግርምቱን የጋዜጣዋን መታገድ አስመልክቶ ሰሞኑን በተለያዩ ድረገጸች ባሰራጨው ጽሁፍ አመልክቷል። (ፎቶ: አውራምባ ታይምስ)
አንደበት
“እኛ ከክልል ሶስት ውጪ ስለሚኖሩ አማሮች አያገባንም፡፡ ምክንያቱም በነፍጠኝነት ለወረራ የሄዱ ናቸው” አቶ ታምራት ላይኔስልጣን ዘመናቸው በርካታ የአማርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ተወላጆች በየአካባቢው ሞትና መፈናቀል እየደረሰባቸው ስለመሆኑ በተጠየቁበት ወቅት ከመለሱት፤
“ከኢትዮጵያ አስመራ፣ ኤርትራ የሄዱት ለአፈና ነው። ስለነሱ ጉዳይ አይመለከተንም” የአንድነት ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ አቶ ስዬ አብርሃ የመከላከያ ሚኒስትር እያሉ ኤርትራ ስለተማረኩና በኤርትራ ስቃይ እየደረሰባቸው ስላሉ ወገኖች ተጠይቀው ከመለሱት፤
የቤኒሻንጉል ጉምዝ መሪ የተምታታ መግለጫ ሰጡ
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ፕሬዚዳንት አቶ አህመድ ናስር በህገወጥ መንገድ መፈናቀላቸውን የሚገልጹትን አማርኛ ተናጋሪዎች አስመልክቶ አስተባበሉ። ባለስልጣኑ Ethiopian forum for political civility on current issues ከሚባለው የፓልቶክ ክፍል ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ተፈናቃዮቹ መኪና ተከራይተውና ንብረታቸውን ይዘው በፍላጎታቸው ወደ ክልላቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል። በግፍ ተፈናቅለናል የሚሉት አማርኛ ተናጋሪዎች እስካሁን መፍትሄ አላገኙም። ንብረታቸው ተዘርፏል። ለዓመታት ያፈሩት ሃብት መና ቀርቷል።
እርስ በርሱ የሚጋጭ ምላሽ ሲሰጡ የነበሩት አቶ አህመድ “ችግር ካለ ለመገምገም ከአማራ ክልላዊ መንግስት ጋር በጋራ ተቀምጠናል” በማለት የማጣራት ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል። “አንድ ክልል የመሬት እጥረት ካጋጠመው በሁለቱ ክልሎች በጋራ በሚደረግ ስምምነት ይከናወናል” በማለት የክልሎችን መብት አጉልተው አሳይተዋል። ለዓመታት በክልሉ የኖሩና ህጋዊ ሰነድ ያላቸውን ዜጎች አማርኛ ስለተናገሩ ብቻ ማፈናቀላቸው መዘዝ እንደሚያስከትል የተረዱት አቶ አህመድ፤ ብሄር ባይጠቅሱም በኢንቨስትመንት ስም ሰፋፊ መሬት ይዘው እየሰሩ ያሉ እንዳሉ ጠቁመዋል። ከብአዴን አባላት ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ እየተሰማ በመሆኑ ሁኔታውን ለማርገብ በፌደራል ደረጃ ሩጫ መጀመሩንና የተወሰኑ የወረዳ ባለስልጣናትን ለመቅጣት እንደታሰበ ለማወቅ ተችሏል።
“የመለስ ፋውንዴሽን” ተመሠረተ
ወ/ሮ አዜብ የቦርዱ ፕሬዚዳንት ሆነዋል
በሟቹ ጠ/ሚ/ር ስም የተቋቋመና “አቶ መለስ በማህበረ ኢኮኖሚ ዘርፍ ያበረከቷቸውን አስተዋፅኦዎችን ከመዘከር ባለፈ የእሳቸውን ራእይ አስቀጥሎ ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ብልፅግና የሚሰራ ፋውንዴሽን” መመሥረቱን ኢሬቴድ አስታወቀ፡፡
የፋውንዴሽኑን ምስረታ አስከትሎም በተደረገ ምርጫ ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ የቦርዱ ፕሬዚዳንት፤ አቶ ካሳ ተክለብርሃን ምክትል ሆነው የተመረጡ ሲሆን ጄ/ል ሳሞራ ዩኑስ፣ ዶ/ር ቴድሮስ አድሓኖም፣ አቶ ሱፊያን አህመድ፣ ወ/ሮ አስቴር ማሞ፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ እና ሌሎች በድምሩ 13 አባላትን ያካተተ ቦርድ መመሥረቱን አብሮ ተዘግቧል፡፡ ከ13ቱ አባላት መካከል አራቱ የአቶ መለስ ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን የዘገበው ዜና፤ ወ/ሮ አዜብ የቦርዱ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት ሆነዉ ከተመረጡት በኋላ ባደረጉት ንግግር “የተሰጠኝ ሃላፊነት ከባድ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በመሆን እወጣዋለሁ” ማለታቸውን ጨምሮ ገልጾዋል፡፡
የፋውንዴሽኑን መመሥረት አስመልክቶ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝ እንዲሁም የካናዳው አምባሳደር ዴቪድ አሸር ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይም የካናዳው አምባሳደር “በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስም የተቋቋመው ፋውንዴሽን ለምርምርና ለጥናት መሰረት የሚጥል ነው” ማለታቸውን በመለስ ስም የተከፈተ የፌስቡክ ገጽ ዘግቧል፡፡
ዜናውን አስመልክቶ አስተያየት የሰጡ አንባቢ “በርግጥ የአቶ መለስ ጉዳይ ከስማቸው ጀምሮ ከበረሃ እስከ መሪነት ድረስ የፈጸሙት ተግባራት እንዲሁም የ4ሺህ ብር ደመወዝተኛ በመሆን አገር የማስተዳደራቸው ጉዳይ በርካታ ምርምርና ጥናት የሚያሻው ነው” በማለት ስላቅ አዘል ምልከታቸውን ሰጥተዋል፡፡ (ፎቶ: የአቶ መለስ ሐውልት ጅጅጋ)
No comments:
Post a Comment