Translate

Saturday, April 6, 2013

መንግስቴ ሆይ… በህልምህ ያሰቀየመህን በእውንህ ስለምን ጠመድከው!?


Haile-awra
Abe Tokchaw
ሰላም ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ… ባለፈው ሳምንት ስለ ልዕልና ጋዜጣ ደግ ደጉ ሲወራ አልነበረም፡፡ አንዳንድ ወዳጆችማ በማህበራዊ ድረ ገጾች ላይ ከጋዜጣዋ እየቀነጨቡ ሲያስነብቡን ምን አልባትም የመጨረሻ እትሟ ሳይሆን አይቀርም… እያሉ ሆዳችንን ባር ባር ሲያሰኙት ነበር፡፡
እንግዲህ እንዲህ እየፈራን እየተባን እንድንገናኝ ተፈርዶብናልና ደህናው ቀን እንዲመጣ እየተጋን፤ እስትንፋሳችን እስኪቋረጥ ድረስ ጨዋታችን ይቀጥላል፡፡
በዚህ አጋጣሚ ወዳጄ እና አለቃዬ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ “ኢትዮ ቲዩብ” የተባለው የድረ ገፅ ሚዲያ አምስተኛ አመቱን ሲያከብር ለፕሬስ ነፃነት “እምቢ” ያለ አንበሳ ብሎ ሸልሞታል፡፡ እናም ተሜን እንኳ ደስ ያለህ፤ ደግሞም ይገባሃል! ብዬ አሞካሽቼ፤ ኢትዮ ቲዩቦችንም እንኳን አደረሳችሁ የኛ ጎበዞች! በማለት አበረታትቼ ቀጥታ ወደ ቀደዳችን አሳልጣለሁ፡፡ ማምለጥ እና ማሳለጥ እንደሁ የሚያክለን አልተገኘም…! ብዬም ራሴን አሽሟጥጣለሁ!

እኔ የምለው እንዴት ነው ነገሩ የኢህአዴግ ጉባኤ ወሬ አሁንም ድረስ ጋብ አላለም እኮ! በተለይ የወይዘሮ አዜብ ነገር በጣም አነጋጋሪ ሆኖ ሰነበተ አይደል እንዴ…!
አረ ወዳጄ… አቶ መለስ ዜናዊ ለካስ መንጃ ፈቃድ አልነበራቸውም! እንዴ… እኔ ወይዘሮዋ ተናገሩ ሲባል አይደል እንዴ የሰማሁት…! እኛማ ኢቲቪ ያስተላለፈልንን  አይተን “በአለም ላይ ምስኪኖቹ እኛ ነን በፔሮል የሚከፈለው የሀገር መሪ መለስ ብቻ ነው” የሚለውን ብቻ አድምጠን እንደው ለእኒህ ሴትዮ መዋጮ ነገር እናሰባስብላቸው ይሆን እንዴ… ብለን ስንጨነቅ ነበር፡፡
(እዝችው ላይ በቅንፍ ወይዘሮ አዜብን እንጠይቃቸው፤ እኔ የምልዎ ክብርትነትዎ (በሌላ ቅንፍ ደግሞ ክብርት ነው ያልኩት “ሪ” አላልኩም… ) እኔ የምልዎ በፔሮል እየፈረመ ደሞዝ የሚወስድ የሀገር መሪ መለስ ብቻ ነው… ያሉን ነገር ትንሽ ግር ብላናለች… ሌሎቹ መሪዎች እንዴት ነው ደሞዛቸውን የሚወስዱት “ባንክ ቤት ሄደው ዝም ብለው ዘገን አድርገው ነዋ” ይበሉና እስቲ ያስቁኝ)
እናልዎ ወዳጄ ለካስ ኢቲቪ ቆርጦብን ነው አንጂ የቀድሞዋ ቀዳማዊታችን ስለ አቶ መለስ መረሳት የሌለበት ብለው ከተናገሩት ውስጥ “መለስ መንጃ ፈቃድ እንኳ የሌለው መሪ ነበር” የሚል ይገኝበታል አሉ፡፡ ኢቲቪ አሁን ገና ልብ ገዛ ይቺን ነገር ቆርጦ ባያወጣት ኖሮ ሰውየው መሪውን የጨበጡት ለካስ ያለ መንጃ ፈቃድ ነበር…!? ብሎ የሀገሬ ሰው ማጉረምረሙ አይቀርም ነበር፡፡ ለመሆኑ የአሁኑስ መሪ መንጃ ፈቃድ ይዘው ይሆን… ኋላ ይሄንን ሁሉ ሰው ጭነው ጉድ እንዳያደርጉን!
ከዘንድሮ የኢህአዴግ ጉባኤ አንድ ግር ያለን ነገር የአቶ አዲሱ ለገሰ ወደ ስልጣን ብቅ ማለት ነው፡፡ ባለፈው ጊዜ አቶ መለስ “ጓድ አዲሱ ከዚህ በኋላ ይበቃዋል” ብለዋቸው ከኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባረዋቸው፤ እርሳቸውም አንተ ካልክ ይሁን ብለዋል፤ ሲባል የሰማሁ መስሎኝ ነበር፡፡
ታድያ አሁን ደግሞ ከየት መጥተው ነው የብአዴን ስራ አስፈጻሚ አባል ሆነው ተመረጡ የሚባለው…? እንዴት ነው ነገሩ ብአዴን ጡረተኛ ይወድለታል ያለው ማነው…?
የምር ግን ህውሃት አቶ አርከበ እቁባይን የመሰለ ገና ብዙ የሚተጋ ሰው በመተካካት ሲያባረር ብአዴን ግን አቶ በረከትንም ሆነ አቶ አዲሱን ሳይተካ በነበረው አዘግማለሁ ማለቱ የምርም ድርጅቷን የመጦሪያ አደረጓት እንዴ… ለሚል ትችት ይዳርጋልና ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡
ኦህዴድ እንኳ እንደ አቶ ጁነዲን ባለስልጣኖቹ በራሳቸው ግዜ ሊኮበልሉ ይችላሉ ተብሎ ስለሚታሰብ መተካካት አያስፈልገውም፡፡ እኔ የምለው ኦቦ ጁነዲን ግን የምር በዛው “ላጥ” እንዳሉ ቀሩ እንዴ…!? ጥገኝነት የጠየቁት እዝችው ኬኒያ ነው አሉ፡፡ ከዛ በኋላ የት እንደደረሱ ምንም ፍንጭ አልሰማንም፡፡ ምናልባት የፓርቲ ስም ቀይረው በሞያሌ በኩል ሊመጡ አስበው ይሆንን ብለን እንጠርጠርጥር ወይስ አንጠርጥር…?
የምር ግን አብዮት ልጆቿን ትበላለች የሚባለው ነገር በአቶ ጁነዲን እና በህውሃት ሰዎች በግልጽ እያየነው ነው፡፡ እንዴ ቀላል ቀረጠፈቻቸው እንዴ! አበላሏን ልብ ብሎ ለተመከተውኮ “አብዮታዊ ዲሞክራሲዬ እንዴት ቢርባት ነው…” ያሰኛል!
ከሁሉ ከሁሉ በአቶ ሃይሌ የምትመራው ደህዴን ናት በላችም ተበላችም ሲባል ድምጧ የማይሰማው፡፡ እንደሚባለው ከሆነ ይቺን የጠቅላይነት ቦታ አስከብሮ ለመያዝ ደህዴን የጥንቃቄ ጉዞ እየተጓዘች ነው አሉ፡፡ ለዛ ነው ኮቴዋ የማሰማው፡፡
አረ ወዳጄ ወደ ዋናው ጨዋታ ሳንገባ የባጥ የቆጡን ስቀባጥር ገፄን ፈጀሁት፡፡ እንደሚከተለው ልግባ…
የአራት ፓርቲዎች ጥምረት የሆነችው ኢህአዴግ የኢትዮጵያ መንግስት ለመሆን ከበቃች ዛሬ ሃያ ሁለት አመት ሊሆናት ነው፡፡
በሃያ ሁለት አመት ውስጥ እንዲህ አድርጋ እንዲህ ሆና ብዬ ለማውራት አልከጅልም፡፡ እንኳንስ እኛ ወዳጆቿ ዋናዎቹ ሰዎችም ሁሉን ነገር ለሟቹ ሰጥተዋቸው ኢህአዴግ የምትባል ፓርቲ እንዳልነበረች ደጋግመው ነግረውናል፡፡ ኢህአዴግዬ ሁሉ ነገሯ መለስ ነበር፡፡ እርሱ አሁን የለም፡፡ ኢህአዴግስ ካለሱ እንደምን ትኖራለች… ብለን በሀዘን ከንፈራችንን እንመጣለን!
የኔ ነገር አሁንም ሌላ አቅጣጫ ልይዝ ነው አረ ተመለስ ይበሉኝ ወዳጄ…
“መንግስቴ ሆይ በህልምህ ያስቀየመህን በእውንህ ስለምን ጠመድከው?” የሚል ርዕስ ይዤ የተነሳሁት እንደው የመንግስቴ ሁኔታ ከእለት እለት በጣም እያሳሰበኝ ቢመጣ ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር መንግስታችን በርካታ ዜጎቹን እንደ ወገብ ቅማል ጠምዶ ይዟል፡፡ ቁጠር ካሉኝ እስር ቤቱ ይቁጠረው ብዬ እመለስለሁ፡፡ ምን እስር ቤቱ ብቻ መስሪያ ቤቱም ይቁጠረው ብዬም እጨምራለሁ፡፡
በትንሹ እንኳ በአደባባይ ሁሌ የምንሰማው እስክንድር ነጋ፣ ርዮት አለሙ፣ ናትናኤል መኮንን፣ አንዷለም አራጌ፣ አቡበከር እና ሌሎችም የታሰሩት አንሷቸው ከታሰሩበት ቀን አንስቶ በየጊዜው እየደረሰባቸው ያለውን አበሳ ልብ ስንል መንግስታችን በህልሙ ያስቀየምነውን በእውኑ ስለምን ጠመደን…? ያሰኛል፡፡
የእውነት እንነጋገር ከተባለ ግን እኛ የተሰደድነውም ሆንን በሀገር ውስጥ ያለው ዜጋ መንግስቱን ያን ያህል የሚያስቀይም ምን ነገር ሰርቷል…? አንድ ጦማሪ እንዳለው “ሀገርን መውደድ እኮ ጦርነት ማወጅ አይደለም” በእውኑ የታሰሩት ሆነ የተሰደዱት ብዙዎች ኢትዮጵያውን አድርባነትን ሽሽት አይደለምን…!?  በትክክል ነው፡፡
ኢህአዴግ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ያለብኝ ችግር በአድር ባዮች መከበቤ ነው፡፡ ስትል ከድምዳሜ ላይ ደርሳለች፡፡ እንግዲያስ አድር ባይ አልሆንም ብሎ ከሀገር የተሰደደው እና በእስር ቤት የታጎረውን ዜጋ ይቅርታ ልትጠይቅ ከዚህ የተሻለ ጊዜ ከየት ታመጣለች!?
የምሬን ነው፡፡ ባስበው ባስበው በእስር ቤት ተከርችሞባቸው ስቃያቸውን የሚያዩ ምስኪኖች መንግስት ላይ ያደረሱት ጥቂት እንኳ በደል ምንም ሊከሰትልኝ አልቻለም፡፡ አቶ ሃይለማርያምም ሆኑ ሌሎቹ የኢህአዴግ “ባሉካዎች” ፀልየው ሁሉ ቢያስቡት ከነዚህ ሰዎች አንድም ጥፋት አላገኘንም እንደሚሉ በጣም እርግጠና ነኝ፡፡
በከተማው በገጠሩ መንግስቴ ጥምድ አድርጎ የያዛቸው ሰዎች ምናልባት በህልሙ አስቀይመውት እንደሆን እንጂ በእውን ያደረጉት ነገር አንድስ እንኳ ሊመጣልኝ አልቻለም፡፡ ታድያ መንግስቴ በህልሙ ያስቀየሙትን በእውኑ ስለምን ጠመዳቸው!?
በአሁኑ ሰዓት የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅቶች እንደሚያወጡት ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት የገዛ ዜጎቹን በማጎሳቆል የሚደርስበት አልተገኘም፡፡ ምን አልባት ከተገኘ እንኳ የኤርትራ መንግሰት ነው፡፡
እመክራለሁ፤
የመዳን ቀን ዛሬ ነው! መንግስቴ ሆይ በህልምህ የበደሉህን ይቅርታ ጠይቀህ ንስሃ ግባ!
ወዳጄ ለማንኛውም የዛሬው ወጋችን እዚህ ላይ ይቋጫል፡፡ እንመራረቅ እና እንሰነባበት!
ለአንባቢ እግዜር ይስጥልን፤ ለከልካይ ልብ ስጥልን!
አማን ሰንብተን!

No comments:

Post a Comment