ፕ/ሮ መስፍን ወ/ማርያም
በሃይማኖታዊ ቋንቋ ንስሐ አለመግባት ማለት ጥፋትንና ስሕተትን አለማመንና በቅብብሎሽ ለሚቀጥሉት ትውልዶች ማስተላለፍ ነው፤ ጥፋቱንና ስሕተቱን የማይቀበል ከነጥፋቱና ከነስሕተቱ ዕድሜውን ይጨርሳል፤ ለልጆቹም የሚያወርሰው ያንኑ ጥፋቱንና ስሕተቱን ነው፤ ዓይን ያለው ያያል፤ ይህንን የጥፋት ውርስና ቅርስ በግለሰብ ደረጃ ብቻ ወስነን ካየነው ጉዳቱ በጣም የሚያንስ ይመስላል፤ በማኅበረሰብና በአገር ደረጃ ካየነው ግን ጉዳቱ ከባድ ነው፤ ከኋላችን የሚመጡት ሁሉ የሚቀድሙን በሌላ ምክንያት አይደለም፤ ከሃምሳና ስድሳ ዓመታት በፊት ከናይጂርያ፣ ከጋና፣ ከማላዊ፣ ከታንዛንያ፣ ከኬንያና ከኡጋንዳ እየመጡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የተማሩ ወጣቶች ሁሉ በከፍተኛ ደረጃ አገሮቻቸውን ሲያገለግሉ ነበሩ፤ በኬንያ እንደሮበርት ኡኮ ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነበረ፤ በታንዛንያ እንደጆርጅ ማጎምቤ ለብዙ ዘመናት በተለያዩ አገሮች አምባሳደር ነበር፤ በዚያን ዘመን ለነዚህ የአፍሪካ አገሮች የተረፈችው ኢትዮጵያ ዛሬ ከእነሱ በታች መሆንዋ ቆሞ ከመቅረት የመጣ ነው፤ ቆሞ መቅረቱ ደግሞ ስሕተትንና ጥፋትን እያዘሉና እሹሩሩ እያሉ ከመንከባከብ የሚመጣ ነው፤ እውነተኛ መልካችንን የምናይበት መስታዋት ሳይኖረን ብዙ ምዕተ-ዓመታት አለፉ፤ አቧራ ሲጠራቀም ከጊዜ ብዛት ተራራ ይሆናል፤ ትንሽ ጉድጓድ ከጊዜ ብዛት ረጅም ገደል ይሆናል፤ ትንሹ ቁስል ከዋለ ካደረ የቆላ ቁስል ይሆንና እንቅልፍ ይነሳል፤ በአንድ ቦታ ላይ አንድ እንቅፋት ደጋግሞ የሚመታው ሰው ረዳት ያስፈልገዋል፤ አለዚያ አንድ ቀን ያው እንቅፋቱ ይገድለዋል።
ኢሳት ለኢትዮጵያ አዲስና ኢትዮጵያዊ አብዮትን የሚያውጅ ይመስላል፤ እስከዛሬ አብዮት የምንለው ሁሉ የተለያዩ አገሮችን የታሪክ ውራጅ በግድ ኢትዮጵያን ለማልበስ የሚሞክር ነው፤ በ1967 ሶሺያሊዝም አዲሱ ሃይማኖት መሆን ሲጀምር በጎንደር በማኅበረ ሥላሴ ኅብረተሰባዊነት (ሶሺያሊዝም) አለ ብዬ ብናገር ውራጅ ሶሺያሊዝምን የሚያመልኩ ብዙ ዘለፋ አወረዱብኝ፤ አሁንም ቢሆን ውራጅ ከመዋስ ገና አልወጣንም፤ የልመና ስልቻችንን ተሸክመን አንዴ በአሜሪካ በር፣ አንዴ በሩስያ በር፣ አንዴ በቻይና በር ላይ እንቅለሰለሳለን፤ ልመና ባህል ነው፤ ለጌታ ማደርም ባህል ነው፤ ሆኖም ሁለቱም ዘዴዎች እድገትንና መሻሻልን አያመጡም፤ መሻሻልን የሚያመጡ ቢሆኑም የሚያስከትሉት ጉዳት ከሚሰጡት ጥቅም የበዛ ነው፤የሚገኘው ግዑዝ ጥቅም የአእምሮና የመንፈስ ውድቀትን በማስከተል ዋጋን ያስከፍላል፤ ይህ ሁሉ ጉዳይ በነጻነትና በሙሉ ልብ ክርክርን የሚጋብዝ ነው፤ ኢሳት ለዚህ ጥሩ መድረክ ሊሆን ይችላል፤ ይሆናል ለማለት ብችል ደስ ይለኝ ነበር።
ይቀጥላል—————–
No comments:
Post a Comment