For PDF file please click here: YeZenawi-Misteroch
በየእለቱ አዳዲስ ዜናዎች እንሰማለን። ለአብነት “ስዩም መስፍን በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነ” የሚለው ተራ ዜና ነበር። “ስዩም ተወረወረ” ብለን ያመንንም ነበርን። ስዩም ሌላ ተልእኮ እንደተሰጠው ለመረዳት፣ የቻይናና የወያኔን የንግድ ስምምነቶች ማስላትና አንዳንድ አንጓዎች ብቅ እስኪሉ መጠበቅ ያስፈልግ ነበር። አባይ ፀሃዬ የስኳርና የጨው ሚኒስትር ሆኖ ሲሾም ብዙ ስላቆች አንብቤ ነበር። የአባይ ፀሃዬን አንገት የስኳር ጆንያ ውስጥ በመክተት ያላገጡ ሜዲያዎችም ነበሩ። ሆኖም የስዩምም ሆነ የአባይ ምደባዎች ቀጣዩን የወያኔ ዋና ዋና እቅዶች ጠቋሚ ነበሩ። የስዩምን ሹመት ተከትሎ፣ የወያኔ ባለስልጣናት ልጆች ለትምህርት ወደ ቻይና ተላኩ። እነዚህን ልጆች በኮሚኒስታዊ አስተሳሰብ አደራጅቶ ማዘጋጀት የሽማግሌው የትርፍ ጊዜ ተልእኮ መሆኑ እየተሰማ ነው።
ወያኔ የጦር መሳሪያ በብዛት እየገዛና እያመረተ ነው።
ጦር መሳሪያ የማከማቸቱ እውነተኛ አላማ ምን ይሆን? በአባይ ጉዳይ የግብፅን ጦር ለመመከት? ይሄ የተበላ እቁብ ሆኖአል። ትግራይን ለመገንጠል ቆርጠው ወስነው፣ በሹክሹክታ እንደሚሰማው TDF (Tigray Defense Force) የተባለውን ይፋ ያልሆነ መስሪያ ቤት በምስጢር እያደራጁ ይሆን?
ጦር መሳሪያ የማከማቸቱ እውነተኛ አላማ ምን ይሆን? በአባይ ጉዳይ የግብፅን ጦር ለመመከት? ይሄ የተበላ እቁብ ሆኖአል። ትግራይን ለመገንጠል ቆርጠው ወስነው፣ በሹክሹክታ እንደሚሰማው TDF (Tigray Defense Force) የተባለውን ይፋ ያልሆነ መስሪያ ቤት በምስጢር እያደራጁ ይሆን?
የህወሃት ሰዎች ትግራይ በጠላት ተከባለች ብለው ማመናቸው ወይም እንዲታመን መፈለጋቸው የችግሩ ማእከል ይመስላል። “እንደ እስራኤል በጉልበታችን መኖር እንችላለን” የሚለው ቅዠት ውስጥ የገቡት አምነውበት ነው ወይስ ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ? ይህን በትክክል ማወቅ አይቻልም። ህዋሃት የትግራይን ህዝብ እንደመሸሸጊያ ሊያመቻቸው ካላሰበ በቀር፣ የትግራይ ህዝብ የጎረቤት ጠላት የለውም። ሊኖረውም አይችልም። በፍቅር የመኖር ሰፊ እድል እያለ ግጭት ብቻ ለምን አማራጭ ሆኖ ይቀርባል?
“ወያኔ ስልጣን ላይ ለመቆየት የቀረችው አንድ የማጭበርበሪያ ካርድ አሰብን በጦር ሃይል መያዝ ናት። የጦር መሳሪያ ማከማቸቱም ለዚያ ኦፕሬሽን ሊሆን ይችላል” እያሉ የሚተነትኑ፣ በተዘዋዋሪም የሚገፋፉ አሉ።
በርግጥ ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ጦርነት ከገቡ ውጊያው አሰብ ላይ ብቻ ሊሆን እንደማይችል ግልፅ ነው። እና ይሄ ትንተና ውሃ አይቋጥርም። ካልሆነ ታዲያ የወያኔ የተጋነነ የጦር መሳሪያ ክምችት አላማ ምን ሊሆን ይችላል? በርግጥ ከዚሁ ጋር ተያይዞ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጉዳይ በእንጥልጥል የተያዘበት ያልተገለፀ ምክንያት እንደሚኖረውም አስባለሁ።
ያልተመለሱልኝ እና የመጨረሻ አንጓቸውን ያላወቅሁዋቸው ጥያቄዎች ከጥቂት በላይ ናቸው። የመሬት ሽያጩ የመጨረሻ አንጓ ገና ግልፅ አልሆነም። ልማት አለመሆኑ ግልፅ ነው። የኮሚሽን ገንዘብ ለማግኘትና ለመዝረፍ ብቻ ተብሎ ሊታለፍም አይችልም። በርግጥ በዚህ ጉዳይ ላይ የራሴ ጥርጣሬ አለኝ። ጊዜውን አላስታውስም። ሆኖም እኔም በተሳተፍኩበት አንድ የፕሮፓጋንዳ ካድሬዎች ስብሰባ ላይ፣ መሬትን የመሸጥና የመለወጥ አጀንዳ ተነስቶ ነበር። ቃል በቃል የመዘገብኩት ባይሆንም፣ በረከት ስምኦን የተናገረው አይረሳኝም፣
“በዚህ ዘመን መሬት ይሸጥ ይለወጥ ብንል ያልተነካ ሰፊ ድንግል መሬት ያለው በደቡብና በኦሮሚያ ነው። የመሬት ሽያጭ ከፈቀድን መሬት ሊገዛ የሚችለው ገንዘብ ያለው ባለሃብት ነው። በዚህ ዘመን ገንዘብ ያለው ማን እንደሆነ ደግሞ ይታወቃል። በዚህ ወቅት መሬት እንዲሸጥ ከፈቀድን ቀደም ሲል ነፍጠኛው በጠመንጃ ይዞት የነበረውን መሬት አሁን ደግሞ መልሶ በገንዘቡ እንዲቆጣጠረው መፍቀድ ማለት ነው…”
3
ኢህአዴግ ስልጣኑን ከለቀቀ የመሬት ፖሊሲው እንደሚቀየር ያውቀዋል። ስለዚህ ዋጋ ያለውን መሬት ሁሉ ከወዲሁ ሸጦ መጨረስ ይፈልጋል። ዛሬ መሬቱ ለውጭ ዜጎች ተሸጦ ካለቀ ወደፊት መሬት የመግዛት አቅም ያለው ኢትዮጵያዊ ቁራሽ መሬት ሊያገኝ አይችልም። ቢያገኝ እንኳ ውድ ይሆንበታል። ለ50 አመት ውል የተፈረመለትን ህንዳዊ ማባረርም ቀላል አይሆንም። ምክንያቱም ብዙ ችግር ያስከትላል። ሙሴቪኒ ስልጣን ይዞ ምእራባውያንን እርዳታ ሲጠይቅ፣ በቅድሚያ ኤዲአሚን ዳዳ ያባረራቸውን ህንዶች መሬትና ንብረት እንዲመልስ ነበር ያዘዙት። ሳይወድ አፍንጫውን ተይዞ መለሰ። የአማራ ባለሃብቶችን ማዳከም፣ የኦሮሞ ባለሃብት እንዳይፈጠር ማገድ የወያኔ ግንባር ቀደም መርህ መሆኑ ግልፅ ነው። መሬት በችኮላ እንዲህ የሚቸበችቡበት ምክንያት ከዚሁ ጋር የተያያዘ ይመስላል።
በርግጥ “ኢትዮጵያዊው ባለሃብት ቡና ቤት ከመገንባት አያልፍም” እያሉ የሚያላግጡ አሉ።
መቼ ተሞከረና?
እንኳን በዚህ ዘመን፣ በ60ዎቹ መጀመሪያ ላይ ወጣቶች ቦሎቄ እያመረቱ ወደ ውጭ መላክ ጀምረው ነበር። ወያኔ የሃገሪቱን መሬት ለውጭ ሰዎች ሸጦ የማጠናቀቅ ተልእኮ እንደያዘ ብዙ አስረጅ ማቅረብ ይቻላል።
ለአብነት ከአዲሳባ ናዝሬት በግማሽ ሰአት ውስጥ መግባት የሚያስችል ዘመናዊ መንገድ ተሰርቶ በመጠናቀቅ ላይ ነው። የዚህ መንገድ መገንባት አላማ፣ “ወደ ናዝሬት በፍጥነት ለመድረስ ነው” ብሎ የሚያስብ የዋህ የሚኖር አይመስለኝም። ወያኔ ከአዲሳባ ናዝሬት በፍጥነት ስለመግባት ሊያሳስበው አይችልም። የመንገዱ መገንባት ሁለተኛ አንጓ፣ ከአዲሳባ ናዝሬት በሚዘረጋው አዲስ መንገድ ግራና ቀኝ ያለውን መሬት ለቻይናና ለቱርክ ለመሸጥ ያለመ ነው። ምክንያቱም በደብረዘይት በኩል ያለውን መሬት ሸጠው ጨርሰውታል። ይህን ማድረግ ለሃገርና ለህዝብ እንደሚጠቅም የሚያሳምን ማብራሪያ እስካሁን አላነበብኩም። መለስ እራሱ ለውጭ ባለሃብቶች መሬት መሸጥ ጉዳት መሆኑን ሲናገር ተደምጦአል። ዚምቧቡዌ በተመሳሳይ መሬቷ እንዲህ ተበዝብዞ ነበር። ሙጋቤ መሬት ለማስመለስ በተነሳበት ወቅት ሃገሪቱ የገጠማት መከራ ግን መቼ እንደሚያቆም እንኳ አልታወቀም። ኢትዮጵያዊው ዜጋ የገዛ መሬቱን መጠቀም እንዳይችል በአዋጅና በፖሊሲ አግደህ፣ ለውጭ ባለሃብት በርካሽ ዋጋ መቸብቸብ ልማታዊ አላማ ይኖረዋል?
“አንጓ” ያልኩትን በቀላሉ ለማስረዳት ብዙ ሰው የሚያውቀውን አንድ ምሳሌ ልጥቀስ።
“….በምርጫ 97 ህዝቡ እንደሚያምፅ ታወቀ – አመፀኛውን ለማስቆም የሚቻለው ከሰልፈኞቹ ጥቂት በመግደል መሆኑ ታመነበት – ግድያውን መሸሸግ ስለማይቻል ለአለማቀፍ ትችት መጋለጥ እንደሚኖር ግልፅ ሆነ – ስለዚህ ለሚገደሉ ሰዎች ግድያ በቂ ምክንያት ማቅረብ እንደሚገባ ታመነ – “ሰልፈኛውን የገደልነው፣ ስንከላከል ነው” ብለው ቢከራከሩ እንደሚታመኑ ገመቱ – ለዚህ ደግሞ ጥቂት ፖሊሶች መሞት አለባቸው ተባለ – ስለዚህ ፖሊሶችን የሚገድል ሌላ ሃይል ተዘጋጀና እንደታቀደው ተፈፀመ…”
“የመጨረሻው አንጓ” የፖሊሶቹ መገደል ለፍርድ ቤት ክርክር እንዲመች ተብሎ የተፈፀመ መሆኑ ነበር። ወደፊት ሊሆን የሚችለውን ቁጭ ብለው ወረቀት ላይ እንደ ሂሳብ ይሰሩና በቅደም ተከተል፣ አንጓዎችን በእቅድ ያስኬዷቸዋል። ይህ የተለመደ የወያኔ አሰራር ሲሆን በሙያውም ተራቀውበታል።
4
“አማርኛ ቋንቋን ከስራ ቋንቋነት ማቋረጥ” ከወያኔ ፕሮጀክቶች ሁሉ አስቸጋሪው ነበር። ምክንያቱም በረጅም ጊዜ የተገነባን ባህልና ቋንቋ፣ እንደ ግድብ በአንድ ፈንጂ መደርመስ አይቻልም። ከዚያም ባሻገር ስራው፣ “የራስ ቋንቋን መጠቀም” በሚል ሽፋን የሚሰራ በመሆኑ ፈታኝ ለመሆን በቅቶአል። አዲስ አበባ በሚገኙ አንዳንድ የግል ትምህርት ቤቶች፣ “አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ክልክል ነው” የሚል ማስታወቂያ ሲለጠፍ መንግስት አይቶ እንዳላየ ዝምታን መርጧል። የአፋር ክልል ከአማርኛ ጋር ተጣብቆ አስቸግሮ ነበር። በዚህ አመት ግን አማርኛን ከአፋር ማስወገድ ተቻለ። የዜና ዘገባውን ስሜታዊነት ላስተዋለ የአፋር ክልል ከአማርኛ ሳይሆን፣ ከፖሊዮ ነፃ የሆነ ነበር የሚመስለው። ከጥቂት ጊዜ በሁዋላ አፋር ላይ አማርኛ ከመናገር ዋሽንግተን ዲሲ ላይ አማርኛ መናገር ሊቀል ይችላል። ለደቡብ ህዝብ አባይ ፀሃዬ “ወጋጎዳ” የተባለ ቅይጥ ቋንቋ ፈልስፎላቸው ነበር። የወጋጎዳ ቋንቋ መማሪያ በ7 ሚሊዮን ብር ሜጋ ማተሚያ ቤት ታትሞ ነበር። መፅሃፉ መሰራጨት ሲጀምር ህዝቡ አመፀና ከሸፈ። መፃህፍቱም ከጥቅም ውጭ ሆኑ። የማሳተሚያ ገንዘቡን ግን ደቡብ ክልል ለሜጋ ከፈለ። ከዚያ ወዲህ ግን ደቡቡን ከአማርኛ ለማላቀቅ ሌላ ዘዴ ማግኘት ሳይችሉ ቀርተዋል። ለነገሩ የአማራ ክልል መሪ በረከት ስምኦን፣ አማርኛን እየተጠየፈ ለአማርኛ ቋንቋ እድገት ይሰራል ተብሎ ሊጠበቅ አይችልም።
በመሰረቱ ክልሎች በእናት ቋንቋቸው መጠቀማቸውን ከመርህ አንፃር አጥብቄ የምደግፈው ነው። በረጅም ጊዜ የተገነባውን የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ጨርሶ ለማውደም የሚደረገው ጥረት ግን ከጥላቻ የመነጨ፣ ሃገራዊ ፍቅር የጎደለው ዘረኝነት ነው ብዬ አምናለሁ። በግድም ሆነ በውድ አማርኛ ቋንቋ ያደገና በአካባቢያችን ብዙ ተጠቃሚ ያለው ቋንቋ ሆኖአል። በመሆኑም አማርኛ የአማሮች ቋንቋ መሆኑ አብቅቶለታል። ቢሆንም ወያኔ አማርኛ ቋንቋን በአማራ ክልል ብቻ ገድቦ ለማስቀረት የሚያደርገው ሙከራ እየተሳካ በመሄድ ላይ መሆኑን አለማመን የዋህነት ነው። ይህን እየፃፍኩ እያለ ፋና ከተባለች ልጅ የሚከተለው ደብዳቤ ደረሰኝ። ልጅቱን አላውቃትም። ከአንባቢዎቼ አንዷ ናት። ጭንቀቷን እንደወረደ አንብቡት፣
(….Hello Mr. gazetegnaw! i just have finished Yederasiw Mastawesha before an hour and now i dont know even what i feel (crazy, nonsense, stupid, useless or something like this) may be just like u felt after u talk with Mehbuba. I cant wait to read ye Sidetegnaw Mastawesha. b/c i know it will include part of my life….When i think politics of this poor country u know what makes me really worried…after 20 years if things continued like this…. እዚህ ምን እንዳጋጠመኝ ብነግርህ ትገረማለህ። እኔ አማርኛ ተናጋሪ ነኝ። ልጁ ደግሞ ኦሮምኛ። ሁለታችንም የመጣነው ከኢትዮጵያ ነው ብለናል። ግን ርስበርሳችን የምንግባበት ቋንቋ አጥተን በእንግሊዝኛ ነው ስናወራ የነበረው። ጉድ አያሰኝም? ከኤርትራኖች ጋር በእንግሊዝኛ ያወራሁት ሳያንሰኝ ደግሞ ከራሴ ሰው ጋርም በሰው ቋንቋ ሳወራ፣ እስቲ ምን ይባላል? …)
ከዜናዎች ጀርባ የተሸሸጉ ምስጢሮችን ወዲያውኑ ለማወቅ ይቸግር ይሆናል። ለመተንተን መሞከር ግን በጣም ተገቢ ነው። ሶስተኛው ወይም አራተኛውን አንጓ ማወቅ መቻል ያስፈልጋል። በርግጥ ከዜናዎች ጀርባ ሁሉ አንድ ምስጢር መፈለግ ይገባል ማለቴ አይደለም። ለአብነት የቴዲ አፍሮ መታሰር ጉዳይ አጠራጣሪ ነበር። ከጥላሁን ገሰሰ እግር መቆረጥ ጀርባ ግን ምንም ምስጢር አልነበረም። የጥላሁን ገሰሰ እግር መቆረጥ እና የሃየሎም አሟሟት ተመሳሳይ ናቸው። የእያሱ በርሄ አሟሟት በአንፃሩ እንደ ቴዲ አፍሮ መታሰር ብዥ ያለ ነው።
5
ሰሞኑን ቴዲ አፍሮን የተመለከተ ቀልድ አንብቤ ነበር። ቴዲ እስር ቤት እያለ ለእስር ቤቱ ሃላፊ አንድ ጥያቄ አቀረበ፣
“ጊዜዬን ቁጭ ብዬ ከማሳልፍ እዚሁ አዳዲስ ዘፈኖችን እንድሰራ ይፈቀድልኝ?”
የእስር ቤቱ ሃላፊ የሚመለከተውን ካነጋገረ በሁዋላ ምላሽ አመጣለት፣
“የጠየቅከው ተፈቅዷል። ዘፈን ሰርተህ ማሳተም ትችላለህ። ሆኖም ግጥም ከኛ! ዜማ ካንተ!”
ሌላ ጊዜ ደግሞ ቴዲ ወባ ታመመ አሉ። ቴዲ እንደገና አመለከተ፣
“ወባ ታምሜያለሁና ወደ ህክምና እንድሄድ ይፈቀድልኝ?”
የእስር ቤቱ ሃላፊ የሚመለከተውን ጠይቆ ምላሽ አመጣለት፣
“ከ17ቱ መርፌ አንዱን ተወጋ!”
በትክክል ወያኔን የሚገልፅ ቀልድ ሆኖ አጊንቼዋለሁ። ሰለሞን ተካልኝ ስለ መለስ ቅንድብ ማማር የዘፈነውን ግጥም ማነው የፃፈለት? በረከት ስምኦን ነው ሊሆን የሚችለው። በረከት እንደምታውቁት አሿፊ ገጣሚ ነው። ሰለሞንን ለዘልአለሙ ለማዋረድ፣ ስለ መለስ ቅንድብ ማማር ግጥም ፅፈው ሰጡት። ስለ አዜብ ጆሮዎች ማማር ቢገጥሙለት በተሻለ ነበር። ምክንያቱም ወንድ ስለ ሴት ሲዘፍን ነው ደስ የሚለው። በባህላችን ወንድ ስለ ወንድ መዝፈን ነውር ነው። እንዲያውም እኔ ሰምቼ አላውቅም። ለነገሩ ሰለሞን ራሱ የሆነ ጅል! ነገር ነው። ሌላው ቢቀር “ግጥሙን ለሴት አድርጉልኝ” ብሎ እንኳ አይከራከርም? በኢትዮጵያ የመሪዎች ታሪክ ውስጥ ስለ መልኩ ቁንጅና የተዘፈነለት የመጀመሪያው መሪ – ወዲ ዜናዊ!
በመግቢያዬ እንደገለፅኩት የህወሃት አንጋፋ ሰዎች አሟሟት ጉዳይ መክረሚያውን የድረፆች ርእሰ ጉዳይ ሆኖአል። ጉዳዩ ወደ ግንባር የመጣበት አላማ ግን አጠራጥሮኛል። ጉዳዩ ትኩረት ያገኘው መለስ ዜናዊ ማጅራት መቺ መሆኑን ለማሳመን ከሆነ፣ ከመነሻው መለስ መቸ ካደ? አስረጅስ መቸ ጠፋ? በእጅ የተጨበጠ ብዙ መረጃ እያለ የሃሰት ታሪክ መፈብረክ ለምን አስፈለገ? ምናልባት ሌላ ልዩ አላማ እና ሌላ አንጓ ይኖረው ይሆን?
ከእያሱ በርሄ ባሻገር ያሉት የህወሃት ሰዎች አሟሟት አከራካሪ ነው ብዬ አላምንም። አሟሟታቸውን ልብ ሰቃይ ተውኔታዊ ለማድረግ የሚያስፈልግበት አላማም አይገባኝም። የአትላንታው ዳዊት ከበደ የፃፈው ትንታኔ እውነት ስለመሆኑ ምንም ጥርጣሬ የለኝም። ምክንያቱም እስር ቤት ገብቼ ጀሚልን ባነጋገርኩት ጊዜ፣ አሁን ዳዊት የሚገልፀውን ነበር ለኔም የነገረኝ። በወቅቱም እፎይታ መፅሄት ላይ አትሜዋለሁ። ጀሚልን ሳነጋግረው ስመኝ ግዛው የተባለች ጋዜጠኛ አብራኝ ነበረች። ስመኝ አሁንም አዲስአበባ በጋዜጠኛነት ሙያ እየሰራች ነው።
(…በእያሱ በርሄ አሟሟት የመለስ ዜናዊ እጅ ሊኖርበት እንደሚችል መጠርጠር የሚቻል ነው። ethsat.com እና ethiomedia.com የተባሉትን ድረገፆች በመጎብኘት መረጃውን ማየት ይቻላል። በተለይ እያሱ በርሄ ሸገር FM ሬድዮ ላይ ከመአዛ ብሩ ጋር ያደረገው ቃለምልልስ ከመለስ ጋር በቀጥታ ሊያላትመው የሚችል ከመሆኑ አንፃር ጉዳዩን እንድንከታተል የሚያደርግ ነው። ከእያሱ ጋር እስከ እለተ
6
ሞቱ ድረስ ቀጣይነት የነበረው ግንኙነት ነበረኝ። የእያሱ አሟሟት ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት የመሄድ እድል ካገኘ፣ ይፋ የማደርጋቸው የኢሜይል ደብዳቤዎቹ ይኖሩኛል። )
ከዚህ ባሻገር የኢትዮሚዲያ የኢንተሊጀንስ ዩኒት፣ ከስዬ አብርሃ ጋር የተያያዘ ከሆነ ትንሽ ፍንጭ ቢሰጠን መልካም ነው። በርግጥ በሃየሎምና በክንፈ አሟሟት ላይ መለስ ዜናዊ እጁ አለበት ከተባለ፣ ቢያንስ በህወሃት ክፍፍል ጊዜ ከተባረሩት አንዱ ስለዚህ ጉዳይ ሊገልፅልን ይገባል።
ስዬ አብርሃ፣ አለምሰገድ ገብረአምላክ፣ ገብሩ አስራት፣ ተወልደ ወልደማርያም፣ ስለ ክንፈ አሟሟት አንዲት ቃል ሲተነፍሱ ተሰምቶ አይታወቅም። “ፈርተው ነው” ብላችሁ እንዳታስቡ አደራ እላችሁዋለሁ። በግልባጩ መለስ ነው የሚፈራቸው። እንደሰማነው የተባረሩት የህወሃት ሰዎች የክንፈ ቀብር ላይ እንዳይገኙ ታግደዋል። የክንፈ ገዳይ ከስዬ ጋር የቀረበ ግንኙነት ስለነበረው ለደህንንታቸው ታስቦ ነው ተብሎአል። ሆኖም እነ ተወልደ ወደ ቀብሩ የአበባ ጉንጉን ልከዋል። ዞሮ ዞሮ ሁለቱም የህወሃት ተቀናቃኝ ወገኖች ክንፈን አልቅሰው ቀብረውታል። ለነገሩ መለስም ጅል አይደለም። ፀሃዬ ሲገደል በግድያው እለት፣ የክንፈ ጎረምሳ ልጅ የሞት አፈፃፃሙን ቆሞ እንዲመለከት አድርጎታል። ከዚያ ወዲህ ስለ ክንፈ አሟሟት በህወሃት ሰዎች ዘንድ ተነስቶ አያውቅም። እስከ ሳልስት ሃዘን ካደረጉ በሁዋላ ወደ ስራቸው ገብተዋል። አጀንዳውም ተዘግቶአል። የሃየሎምም እንዲሁ ነው። ሌላው ቀርቶ የሃየሎም ሚስት ከመለስ ጋር አብራ እየሰራች ነው። እንግዲህ ባለጉዳዮቹና ጓደኞቹ ያልተቸገሩበት እና የማያውቁት ታሪክ ከየት መጣ? ዋናው ነጥብ፣ “እንዲህ ያሉ ወሬዎች ወደ ሚዲያ የሚመጡት ለምንድነው?” የሚል ነው።
አንድ ሰው፣ “እንዲህ ርስበራስ ቢጨራረሱልን ጥሩ ነበር” ያለኝ ትዝ ይለኛል።
ይሄ እንግዲህ የአየር ባየር ፖለቲካ ይባላል። ዝሆኑ ሲጓዝ፣ ስጋ ይወድቅልኝ ይሆናል በሚል አንድ ቀበሮ በተስፋ ትከተለዋለች። ወያኔ ይህን የተረዳ ይመስላል። ይህን ለመሰሉ ወሬዎች ማስተባበያ አይሰጡም። “ተዋቸው! ይዝናኑበት” ብሎ ችላ ይላል። ሜዲያዎች በወያኔ አጀንዳ እንዳይጠለፉ ማስተዋል አለባቸው። ተቃዋሚዎችም በራሳቸው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ ብቻ ቢበረቱ ይመረጣል። በተስፋ የተጠቀለሉ ተረቶችን በማስተናገድ ጊዜያቸውን ማባከን አይጠበቅባቸውም።
ታማኝ በየነ ይህን ተገንዝቦ በኢሳት ገንዘብ የማሰባሰቢያ ዝግጅት ላይ ጉዳዩን አንስቶት ነበር። ወያኔ ብርቱካን ሚደቅሳን ከእስር ፈትቶ፣ እስክንድርና ደበበ እሸቱን አሰረ። እዚህ ላይ ወያኔ ምንም አልከሰረም። የከሰረው ተቃዋሚ ሃይሉ ነው። “የታሰሩት ይፈቱ” ከሚለው ድምፅ ፈቀቅ ሊል አልቻለም። እንደሰማሁት ከአስር አመት በፊት ለፕሮፌሰር ታዬ ተብሎ የተፃፈ፣ “የህሊና እስረኞች ይፈቱ” የሚል መፈክር ለብርቱካን ጭምር አገልግሎአል። ሰሌዳ ላይ የተፃፉ መፈክሮችን እንደ ባንዴራ በቋሚነት ያስቀመጡ አሉ። ገና ለአንዷለም አራጌ ያገለግላሉ።
መለስ ተቃዋሚዎች ላይ ማሾፉን ቀጥሏል፣
“የኛዎቹ እንደ አልሻባብ ፕሮፌሽናል አይደሉም” አለ።
እንግዲህ መለስ ከዚህ በላይ ምን ይናገር?
“እባካችሁ በማውቀው ቋንቋ አናግሩኝ” እያለ እየለመነ የሚሰማው አጣ!
7
በርግጥም ህወሃት የታገለው በመዋጮ ብቻ አይደለም። ባንክ እየዘረፈ፣ ምእራባውያንን እያታለለ፣ ፈላሾችን ለእስራኤል ነግዶ፣ አሸዋውን ስንዴ ነው ብሎ እየሸጠ፣ እየሞተና እየገደለ ነው የታገለው ወይም አዲሳባን የተቆጣጠረው። የቀበሌ ሊቀመንበሮችን መንገድ ላይ አጋድሞ እየረሸነ ነው የታገለው። አንዳርጋቸው ፅጌ በቅርቡ ኢሳት ላይ ሲናገር ይህን አንስቶታል። ህወሃት የሚመካው፣ “ለመስዋእትነት ባለን ቁርጠኛነት እንበልጣችሁዋለን” እያለ ነው። እዚህ ላይ “መገደል” እና “ለመሞት መወሰን” የተለያዩ መሆናቸው ይጤን። መለስ “አልሻባብ ፕሮፌሽናል ነው፣ የኛዎቹ አማተር ናቸው” የሚለው ከዚህ አንፃር ነው። በርግጥ ህወሃትም በትግሉ ወቅት እንደ አልሻባብ ፕሮፌሽናል ነበር። ለዚህም በወቅቱ አሜሪካ ህወሃትን በአሸባሪነት መመዝገቧ ማስረጃ ነው።
አንድ እውነት አለ።
መግደል ቀላል ሊሆን ይችላል። መሞት ግን በጣም ከባድ ነው። ጊዜውን እና ገንዘቡን እንኳ ለመስጠት የሚስቆነቆን “ታጋይ” ህይወቱን ሊከፍል አይችልም። እናም ይህን መሰል “ታጋይ” ነፃነትን ለዘልአለሙ አያገኛትም። እድሜ ልኩን የሜዲያ አርበኛ ሆኖ ይቀራል። ወይም በመለስ አባባል፣ “የወረቀት አንበሳ” ሆኖ ዘመኑን ያጠናቅቃል። ለዚህ መራር አባባል አስረጅ የሚሆነኝን አንድ ታሪክ ላጫውታችሁ፣
ገብረእግዚአብሄር ጋይም የሚባል የኢህአፓ ታጋይ የህወሃትን ጥቂት መሪዎች ለመግደል አዲሳባ ገብቶ ነበር። ስናይፐር ጠመንጃዎቹን አዘጋጅቶ ጥናት እያደረገና ምቹ ቀን እየጠበቀ ሰነበተ። በመካከሉ እነ ክንፈ ደረሱበትና ሊይዙት ከመሸገበት ቤት ሄዱ። የጋይም ልጅ “እጄን አልሰጥም” ብሎ ተታኩሶ ሞተ። በነጋታው ክንፈ ቢሮው ጠራኝና፣ ከገብረእግዚአብሄር ዘንድ የተገኙትን ሰነዶች ፎቶኮፒ እያደረገ ሰጠኝ። ታሪኩንም ከሀሁ እስከ ፐፑ አጫወተኝ። ከተገኙት ሰነዶች መካከል የአባይ ፀሃዬና የስብሃት ነጋ የመኖሪያ ቤት አድራሻዎች ነበሩበት። እንደ ክንፈ ግምታዊ ትንተና የገብረእግዚአብሄር ጋይም እቅድ መለስ፣ ስብሃትና አባይን ለመግደል ነበር። ከዚያም የጋይምን ልጅ ፎቶግራፍ የሽፋን ዘገባ አድርጌ፣ ታሪኩን እፎይታ መፅሄት ላይ አተምኩት። ከኔ ሌላ ስለ ጋይም ልጅ መረጃውን ያገኘ ጋዜጠኛ አልነበረም። እኔም በወቅቱ ክንፈ የፈቀደልኝን ቁንፅል ታሪክ ብቻ ነው ያተምኩት። እድሜና ጊዜ ከፈቀደ ወደፊት አንድ ኖቬላ እሰራበት ይሆናል። ስለ ጋይም ልጅ ከክንፈ ጋር ስናወራ አንድ በጣም የገረመኝን ነገር ነገረኝ። በወሬ መሃል ክንፈን፣
“ለመሆኑ እንዴት ደረሳችሁበት?” ብዬ ጠይቄው ነበር።
ክንፈ እየሳቀ፣ “ጓደኞቹ መረጃውን ሸጡልን” አለኝ።
ሆኖም “ከህዝብ በተገኘ ጥቆማ” እንደተደረሰበት እንድፅፍ ነገረኝ። አሳልፈው የሸጡት የገብረእግዚአብሄር ጋይም ጓደኞች እነማን እንደሆኑ አላውቅም። አዲሳባ ያሉ ይሁኑ ውጭ ሃገር አላጣራሁም። ብጠይቀውም ኖሮ ክንፈ ስማቸውን አይነግረኝም ነበር። እኔም ልጠይቀው አልደፈርኩም። ከክንፈ ጋር በነበረኝ ግንኙነት የግንኙነታችንን ገደብ በትክክል አውቀው ነበር። የገብረእግዚአብሄር ጋይም ጓደኞች ቀላሉን መግደል መፈፀም ችለዋል። በአንፃሩ የጋይም ልጅ ከባዱን መሞት ማስተናገድ ቻለ። የተቃዋሚዎች ሰላማዊም ሆነ የትጥቅ ትግል ባለበት ሲረግጥ የኖረው፣ “በማያቋርጥ ክህደት ምክንያት ይሆን?” ብዬ ማሰቤ አልቀረም። በርግጥ ይህ ጉዳይ ከክህደት ባሻገር ፖለቲካዊ ምክንያትም ሊኖረው ይችል ይሆናል። ያንን ግን አላውቅም።
ይህን ለማስረዳት ብዙ ደከምኩ መሰለኝ?
8
በእውቀቱ ስዩም በጥቂት ቃላት ገና ድሮ ገልፆት ኖሮአል፣
እልፍ ከሲታዎች – ቀጥነው የሞገጉ፣
“ስጋችን የት ሄደ?” ብለው ሲፈልጉ፣
በየሸንተረሩ በየጥጋጥጉ፣
አስሰው፣ አስሰው – በምድር በሰማይ፣
አገኙት ቦርጭ ሆኖ – ባ’ንድ ሰው ገላ ላይ፣
ህወሃት ከትግሉ ጊዜ ጀምሮ እያሳደገው የመጣው፣ እንደ ሸረሪት ድር ያለ የመረጃ እና የአደረጃጀት መዋቅር አለው። ያ መዋቅር ከህወሃት ኮር ይነሳል። ከላይ ወደ ታች እየሰፋ እስከ ገበሬውና ለማኙ፣ እስከ ነጋዴ እና ጠንቋዩ ይደርሳል። ህወሃት በሚዲያ የማይገልፀው መልእክት፣ ሸረሪቷ ካለችበት ማእከል በቀጭጭኖቹ ክሮች በኩል ይወርዳል። እያንዳንዱ ቀጭን ክር ርስበርሱ በጥብቅ የተቆራኘ ነው። በቤተሰባዊ እና በጎሳዊ ሽቦዎች የታሰረው ክር ለአንጓዎቹ ግብአት ይመግባል። በሚዲያ የማይነገር መልእክት ሁሉ በዚህ ክር አማካይነት ይፈሳል። በትግራይ፣ በአዲስ አበባ፣ በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ፣ ሁሉ ተዘርግቶ ከታች ወደላይ፣ እንደገና ከላይ ወደታች መረጃዎች ያለማቋረጥ ይመላለሳሉ። ክሮቹ አልፎ አልፎ ቢበጠሱም ተመልሰው እየተጠገኑ ይተካሉ። አራት ኪሎ ቀለበቱ ላይ ያለችው ሸረሪት እስትንፋሷ እስካለ ድሩ ከአደጋ የተጠበቀ ነው።
እዚህ ላይ የገጣሚ ታገል ሰይፉ አንድ ቀልድ ታወሰችኝ።
አንድ ሰው ሰንበት ማለዳ ወደ ቤተክርስትያን ብቅ ብሎ ድምፁን ከፍ አድርጎ ፀለየ፣
“አምላኬ ሆይ! ልቤ ላይ ያደራውን የሃጢአት ድር ጥረግልኝ!”
በሚቀጥለው ሰንበት ማለዳም እንዲሁ ድምፁን ከፍ አድርጎ ተመሳሳዩን ፀለየ። በሶስተኛው ሰንበትም እንዲሁ። የሰውየውን ፀሎት በተደጋጋሚ የሰሙ አንድ ቄስ ጠጋ ብለው መከሩት፣
“ልጄ! በየሰንበቱ የሃጢአት ድር ከምታስጠርግ፣ አንደኛውን ሸረሪቷን ብታስወግድ አይሻልም?”
• ፀሃፊውን ለማግኘት፡ tgebreab@gmail.com –
No comments:
Post a Comment