ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የጋራ እንቅስቃሴ አስተባባሪ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
ኢትዮጵያ የብዙ ብሔረሰቦችና ሀይማኖት ተከታዮች ሀገር ናት። እነዚህ ብሔረሰቦች ለብዙ ዘመናት በአንድነትና በሕብረት ተደጋግፈው፤ ተጋብተውና ተስማምተው ኖረዋል። ከውጭ የመጣባቸውን ጠላትም በተባበረ ክንዳቸው መክተው በመመለስ በዓለም ታዋቂ ታረክ አስመዝግበዋል። በአሁኑ ወቅት ከመሀከላቸው የበቀሉ ተንኮለኞች ለፓለቲካ ሥልጣንና ለግል ጥቅም ማራመጃ ሲሉ የሚያካሂዱትን የመከፋፈል እርምጃ የኢትዮጵያ ሕዝብ በተከታታይ እያከሸፈው ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት በጦር ኃይል እያስገደዱ በአንድ ብሔረስብ ላይ ያተኮረ አስከፊና አደገኛ የዘር ማጥፋት ተግባር እያከናወኑ ይገኛሉ።
ይህንን ሰላም ወዳድና በሰላም የኖረ ሕዝብ እርስ በራሱ በማጋጨትና አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሳሳ የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር/ሕወሓት መሪዎች ከፅንሳቸው ጀምረው በፖሊሲ ደረጃ ነድፈው እስካሁን በማስፈጸም ላይ ይገኛሉ። ወደፊትም በሥልጣናቸው ለመቆየትና ከሕዝብ የሚዘርፉትን ንብረት ካለምንም ተቃውሞ ለማካሄድ ወገኖቻችንን በዘርና በቋንቋ በመለያየት ለዘመናት ከኖሩበት አካባቢ ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ ሆን ተብሎ በተቀየስ የዘር ማጥራት ፖሊሲ አማካኝነት ለጊዜው ከተወሰኑ ክልሎች በማፈናቀል ላይ ናቸው።
የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጭ ግንባር ከአመስራረቱ ጀምሮ በተለይም በአማራው ኅብረተሰብ ላይ ያነጣጠረ የዘር ጥላቻ ፓሊሲ በተለያየ መልኩ ሲያስፈጽምና ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። ይህም ድርጊቱ በአጭሩ ካልተቀጨ በቀር በደቡብ አፍሪካና በሩዋንዳ ሀገሮች ከተካሄዱት የዘር ማጥፋት ዘመቻዎች የማይተናነስ ዕልቂት በአገራችን ሊደርስ እንደሚችል መገመተ አያዳግትም። በቅርቡ ከቤንሻንጉል-ጉሙዝ ክልል ወደ 8000 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የአማራ ተወላጆች በመሆናቸው ብቻ ከሚኖሩበት አካባቢ ለቀው እንዲወጡ መደረጋቸው የዚህ አንዱ ማስረጃ ነው። ከእነዚህ ውስጥም በርካታ ሕፃናት፣ እርጉዞችና አዛውንቶች እንደሚገኙበት ታውቆአል። ተፈናቃይ ወገኖቻችን ያፈሩትን ንብረት እንኳን ሳይሸጡና ሳያሰባስቡ በመሣሪያ ኃይል ተገደው እንዲባረሩ በመደረጉ ብዙዎች ለከፋ አደጋና እስከ ሞት የሚያደርስ ጉዳት ተዳርገዋል።
ባለፈው ዓመትም እንደዚሁ በተመሳሳይ ሁኔታ ብዛታቸው 20,000 በላይ የሆኑ የአማራ ተወላጆች ከደቡብ ክልል ጉራ ፈርዳ ወረዳ ተፈናቅለው በከፍተኛ ችግር ውስጥ ወድቀው በያሉበት ከተበታተኑ በኋላ፤ በአሁኑ ወቅት የት እንዳሉና በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ በትክክል አይታወቅም።የተፈናቃዮቹን ስቆቃ ለኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ለዓለም ኅብረተሰብ ለማሳወቅ ጋዜጠኞችም ሆኑ የተቃዋሚ ድርጅት ተወካዮች ተከታትለው እንዳይዘግቡ በአካባቢው በሚገኙ ካድሬዎቹና ታጣቂዎች አማካኝነት ከተፈናቀሉት ተጎጅዎች ጋር ግኑኝነት እንዳይኖር ዘረኛው መንግሥት ከልክሏል። በአንድ ሕብረተሰብ ላይ ይህንን የመሰለ አረመኔያዊ ግፍ ሲፈጸም ዝም ብሎ መመልከት በታሪክ ተወቃሽ ከማድረጉም በላይ፤ በተለይ ግን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የድርጊቱ ተባባሪ የሆነ ሁሉ ወደፊት በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን ሊታወቅ ይገባል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ተብዬውም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት በአንድ ሕዝብ ላይ በዘር ቆጠራና በቋንቋ ምክንያት ነጥሎ ጥቃት ማድረስ በሕግ የሚያስጠይቅ መሆኑን የሚደነግግ ጠንካራ ሕግና የማስፈጸሚያ ደንቦች አሉት። በተለይም ኢትዮጵያ ይህንን የተባበሩት መንግሥታት ሕግ ተቀብላ በፊርማዋ ያጸደቀች በመሆኑ፤ የሕወሓት/ኢሕአዴግ መሪዎች በቀጥታ በዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠያቂዎች ናቸው። ለጊዜው በጉራ ፈርዳና በቤንሻንጉል-ጉሙዝ አካባቢዎች የተፈጸሙት አረመኔያዊ ተግባራት በአጋጣሚ ይፋ ሆነው ወጡ እንጂ፤ በሌሎች አካባቢዎች በስውር የተፈናቀሉ ከነቤታቸው በእሳት የተቃጠሉ፤ ገደል የተጣሉ፤ በየጫካው ለዱር አራዊት ቀለብ የተደረጉ እንዳሉ የታወቀ ነው። በአንድ ወቅት የሕወሓት መንግሥት የሕዝብ ስታቲስቲክስ መ/ቤት ዲሬክተር በ2000 ዓ.ም. በተደረገው የሕዝብ ቆጠራ ከ2 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ አማራዎች መረጃው ከሚያሳየን ውጭ የት እንደገቡ አናውቅም በማለት ለፓርላማ ተብዬው ቀርበው አስረድተዋል። በዚህ መረጃ ላይ መንግሥት እስካሁን ይህን ያህል ብዛት ያለው ወገኖቻችን የት እንደገቡ የሰጠው መግለጫም ሆነ ማብራሪያ የለም።
ሕወሓት/ኢሕአዴግ ይህንን በአማራው ላይ የሚያካሂደውን የዘር ማጥፋት ተግባሩን በዚህ ብቻ ያቆማል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው።የኢትዮጵያ ሕዝብ እነኝህን የሕዝብ ጠላቶች በቃኝ ብሎ ከሥልጣን እስካላስወገደ ድረስ፤ ዘመቻው በተጠናከረና የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም እንደሚቀጥል የተረጋገጠ ነው። ከአማራው ቀጥሎ የኦሮሞው፤ ከኦሮሞው ቀጥሎ የወላይታው እያለ ይቀጥላል። ምክንያቱም የዘረኛው መንግሥት ዕድሜ የሚራዘመው ወይንም የመኖሩ ምሰሶ የተመሠረተው ወገንን ከወገን በማናቆርና በማጋጨት ላይ በመሆኑ ነው። ይህን አስከፊና አረመኔያዊ ተግባሩን ለማስቆምም ሆነ ለመግታት የሚቻለው የኢትዮጵያ ሕዝብ የተነሱበትን የጥፋት ሴራ በሚገባ ተገንዝቦ ይህንን አደገኛና ጠባብ የዘረኛ ቡድን ከሥልጣን አስወግዶ በምትኩ በሕዝባችን ፈቃድና ሙሉ ፍላጎት ላይ ብቻ የተመሠረተ እውነተኛ መንግሥት ሲያቆም ብቻ ነው።
ይህ ጉዳይ የሚመለከተውም ሁሉንም የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ክፍል በመሆኑ ሁላችንም በቋንቋ፣በጎሳና በሃይማኖት ሳንለያይ በአንድነት ተነስተን በመቆም በተባበረ ኃይል የሕወሓት/ኢሕአዴግን አምባገነናዊ ሥርዓት በማስወገድ በፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመተካት በጋራ መሥራትና መታገል አለብን።
ለዚህም የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የጋራ እንቅስቃሴ አስተባባሪ ኮሚቴ በሚቻለው ኃይሉ ሁሉ የዘረኛውን ቡድን እኩይ ተግባራት ለማጋለጥና የኢትዮጵያ ሕዝብ መሠረታዊ ዲሞክራሲያዊ መብቶቹን ተጎናጽፎ በአሸናፊነት እንዲወጣ የበኩሉን አስተዋፅዖ ማድረጉን ይቀጥላል።
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች የጋራ እንቅስቃሴ አባላት፥
ጥምረት ለነፃነት ለእኩልነትና ለፍትህ በኢትዮጵያ
ብሩህ ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ንቅናቄ (ብሩህ)
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ
የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት
የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ (ሸንጎ)
ኢትዮጵያዊነት፤ የዜጎች መብት ማስከበሪያ ጉባዔ
ዓለም አቀፍ ሕዝባዊ ንቅናቄ ለለውጥ በኢትዮጵያ (በቃ)
የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር (በጀ/ል ከማል ገልቹ የሚመራው)
No comments:
Post a Comment