Translate

Saturday, October 10, 2015

ቅጥ ላጣው ሙስና “ተጠያቂ ነኝ” – ህወሃት

"ህወሃት/ኢህአዴግ ያመጣውን ሙስና ራሱ ይፍታው" - ሕዝብ

corrupt


ኢትዮጵያን በነጻ አውጪ ስም እየገዛ ያለው የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር – ህወሃት በተለይ በአዲስ አበባ ቅጥ ያጣውን ሙስናና ዘረፋ በተመለከተ በጠራው ስብሰባ አስቀድሞ በመቀሌው “ተጠያቂ ነኝ” በማለት እንዳመነው አሁን ደግሞ ነዋሪው ችግሩን ራሱ እንዳመጣው ራሱ ይፍታው ማለቱ ተነግሮዋል:: የሪፖርተር ዘገባ እነሆ:-

* ሙስና በአዲስ አበባ በኔትወርክ ተይዞዋል
ሙስና፣ ኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር እጦት ከወረዳ እስከ ከተማ አስተዳደሩ ድረስ በኔትወርክ የተያያዙ በመሆናቸው ሊፈታቸውም ሆነ ሊያስቆማቸው የሚችለው ድርጅቱ ኢሕአዴግ ብቻ መሆኑ ተጠቆመ፡፡
የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን መስከረም 20 ቀን 2008 ዓ.ም. በግዮን ሆቴል ለግማሽ ቀን አዘጋጅቶት በነበረው የውይይት መድረክ ላይ ከተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት፣ የሁሉም ክፍላተ ከተሞች፣ ወረዳዎች ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተው ነበር፡፡ ተሳታፊዎቹ እንደተናገሩት የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡
በመጠናቀቅ ላይ ካለው መስከረም ወር አጋማሽ ጀምሮ በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ሊባል በሚችል ሁኔታ ከግንባታ፣ ከመሬትና ቤቶች ጋር በተገናኘ ነዋሪዎች እያለቀሱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የመድረኩ ተሳታፊዎች በተለይ በአዲሱ የሥራ ዘመን ከኃላፊነታቸው እንደሚነሱ ያወቁ፣ የጠረጠሩና ሹክሹክታ የሰሙ የክፍላተ ከተሞችና የወረዳዎች ተሿሚዎች “የሚፈርስ የማይፈርስ፣ መንገድ የሚወጣበት የማይወጣበት፣ ክርክር ያለበት የሌለበት፣ ግንባታ የተፈቀደለት ያልተፈቀደለት…” በማለት በሥራ ሰዓትና ከሥራ ውጪ የነዋሪዎችን ግድግዳና የውጭ በር ቀለም ሲቀቡ እንደሚውሉ ጠቁመዋል፡፡ ያለምንም ማስጠንቀቂያ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ኅብረተሰቡን ሰላም እየነሳው በመሆኑ፣ የአስተዳደሩና የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች ትኩረት ሰጥተው ሊያስቆሟቸው ወይም ዕርምጃ ሊወስዱባቸው እንደሚገባ ተሳታፊዎቹ አሳስበዋል፡፡
በመቀሌ ከተማ በተደረገው የገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ አሥረኛ ጉባዔ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ጥሩ ሥራ መሠራቱ የተገለጸ ቢሆንም፣ በመልካም አስተዳደር በኩል ግን ከፍተኛ ችግር እንደነበር መታመኑንና ፓርቲው “ተጠያቂ ነኝ ማለቱን”፣ የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን ለተሳታፊዎች አስታውሰዋል፡፡ በመቀጠልም ይህንን ምቹ ሁኔታ ሕዝቡ መጠቀም ስላለበት ከመንግሥት ጎን በመቆም ብልሹ አሠራርን፣ ሙስናንና ሌሎች ለሕዝቡም ሆነ ለአገር የማይጠቅሙ አሠራሮችንና ድርጊቶችን ማጋለጥ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በየስብሰባው በመወዳደስና በጭብጨባ በመደጋገፍ መንቀሳቀስ መቆም እንዳለበትና ሕዝብ ያስቀመጠው ኃላፊ ለሕዝብ ማገልገል እንዳለበት መንገር ያለበት ኅብረተሰቡ መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፣ በየስብሰባው የጉንጭ ጅምናስቲክ ሠርቶ መለያየትን ቆም አድርጎ ባለሥልጣኑ የሚጓዝበት ተሽከርካሪ፣ የሚኖርበትና የሚከፈለው ደመወዝ ሕዝቡ በሚከፍለው ታክስ መሆኑን በመግለጽ፣ በአግባቡ እንዲያገለግለው መናገር እንዳለበት አስታውቀዋል፡፡
የኮሚሽነሩን ማብራሪያ ተከትሎ የመድረኩ ተሳታፊዎች እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ የመንግሥት ተሿሚዎች የሕዝብ ሀብት በሙስናና በኪራይ ሰብሳቢነት እንዳይበዘብዙና መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን በማለት የሕዝብ ተሿሚዎች ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ ማድረጉ ትልቅ ነገር ነበር፡፡ ነገር ግን በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የመንግሥት ተሿሚዎች መመዝገባቸው ከመገለጹ ውጪ ለሕዝቡ ይፋ አልተደረገም፡፡ ተመዝግቦ በድብቅ መያዙ ትርጉም ስለሌለው የትኛው ባለሥልጣን ምን ያህል ሀብት እንዳስመዘገበ ለሕዝብ ይፋ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ለሕዝብ ይፋ መደረጉ ሕዝቡ የሚያውቀውን ያህል ማስመዝገቡንና ያላስመዘገበም ከሆነ ተጨማሪ መረጃ በመስጠት እውነቱ ላይ እንዲደርስ እንደሚረዳ ተሳታፊዎች አውስተዋል፡፡
ሀብታቸውን ያስመዘገቡ ባለሀብቶች ይፋ እንዲደረጉ በተነሳው ጥያቄ ላይ ምላሽ የሰጡት ኮሚሽነር ዓሊ፣ መሥሪያ ቤታቸው ለማንም ክፍት መሆኑንና ማንም መጥቶ የሚፈልገውን ማስረጃ ማግኘት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ መረጃ የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ ደብዳቤ ጽፎ፣ “የእከሌን ባለሥልጣን ሀብት ማወቅ እፈልጋለሁ?” ካለ ወዲያውኑ እንደሚገለጽለት ተናግረው፣ በመገናኛ ብዙኃን ግን “የእከሌ ባለሥልጣን ሀብት ይህንን ያህል ነው፤” ብሎ ይፋ ማድረግ ከሕግ አንፃርም እንደሚያስኬድና ነውር መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ በዓለም ደረጃም ከሲንጋፖር በስተቀር የሁሉንም ዜጎች ሀብት መዝግቦ ይፋ ያደረገ አገር አለመኖሩን አክለዋል፡፡ በቅርቡ በኮሚሽኑ ድረ ገጽ በኢሜይል መጠየቅና መረጃ ማግኘት እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊዎች በርካታ አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ በተለይ በሙስና ተጠርጥረው ስለሚታሰሩና ስለሚፈረድባቸው ተከሳሾች ተናግረዋል፡፡ አንድ በሙስና የተጠረጠረ ሰው በርካታ ገንዘብ በሙስና ካገኘ በኋላ ዘመዶቹ ዘንድ በታትኖ በማስቀመጥ፣ ሲፈተሽ የሚገኝበት ጥፋት በጣም ትንሽ ስለሚሆን የተወሰነ ዓመት ታስሮ እንደሚፈታ ገልጸዋል፡፡
ከእስር እንደተፈታ ለተወሰኑ ወራት ቀድሞ ከሚኖርበት አካባቢ በመልቀቅ ከቆየ በኋላ አስመጪና ላኪ ሆኖ እንደሚታይ የገለጹት ተሳታፊዎቹ፣ ይህንን የሚያዩ ተሿሚዎች የተወሰኑ ዓመታት ታስረው ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው እንደሚተርፉ ራሳቸውን በማሳመን ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ ሀብትን እየበዘበዙ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይህንን ተግባር የሚመለከተው አካል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ዕርምጃ ሊወስድበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር ትምህርቱ ከአምስት ዓመት ሕፃን እንዲጀምር በኮሚሽኑ የቀረበውን ሐሳብ የውይይቱ ተሳታፊዎች ድጋፍ ሰጥተውታል፡፡
በመቀሌው ጉባዔ የተደረገው ስምምነት እንዳለ ሳይቀነስ ወደ ታች መውረድ እንዳለበት ያሳሰቡት የውይይቱ ተካፋዮች፣ በተለይ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ዕጦት በሚታይባቸው ግብር አስከፋይና ንግድ ፈቃድ አዳሽ መሥሪያ ቤቶች የማይተገበር መመርያ እያወጡ የንግዱን ኅብረተሰብ ሳይወድ በግድ ወደ ሙስና እንዲገባ የሚያደርጉበት አሠራር ትኩረት እንዲሰጥበት ጠይቀዋል፡፡ የመልካም አስተዳደርና የፍትሕ ዕጦት ቢስተካከል ለውጥ ሊመጣ እንደሚችልም አክለዋል፡፡
“ድርጅቱ ይታማል” ያሉ አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ተሿሚው እንክት አድርጎ ከበላ በኋላ እሮሮ ሲበዛበት ከነበረበት ቦታ ወይም ክፍለ ከተማ ተነስቶ ወደ ሌላ ክፍለ ከተማ ወይም ማዘጋጃ ቤት እንደሚሾም ገልጸው፣ “እርስዎ (አቶ ዓሊን) ለድርጅቱ ቅርብ ስለሆኑ ቢወያዩበትና መፍትሔ እንዲመጣ ቢያደርጉ የተሻለ ነው፤” ማለታቸው የስብሰባውን ተሳታፊዎች አስፈግጓል፡፡ ከድርጅቱ ውጪ ማንም ሊፈታው እንደማይችልም አክለዋል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችን ችግር የሚፈታ መንግሥት እንዴት የሙስናን ችግር መፍታት እንዳቃተው እንዳልገባቸውም ተናግረዋል፡፡
ገዢው ፓርቲ ብቻውን የሚያደርገው ነገር እንደሌለ የገለጹት አቶ ዓሊ፣ የኅብረተሰቡ ተሳትፎ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ድርጊቶችን ማስፈጸም እንዳልተቻለ የገለጹት አቶ ዓሊ፣ የማይገባ ድርጊት መፈጸሙ እየታወቀ ዞር ተደርጎ በከፍተኛ ደረጃ የሚሾም ተሿሚ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡ (ሪፖርተር)

No comments:

Post a Comment