ተስፋዬ ነጋ (ዋሽንግተን ዲሲ)
በውጭ አገር ማለትም በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ እስያ እና አውስትራሊያ ያሉ ኢትዮጵያውያን በአገራቸውና ህዝባቸው ላይ ሰለሚደርሰው ጭቆና፣ አፈና፣ ግድያና፣ እስራት የሚወያዩበት፣ ሃሳቦቻቸውን የሚካፈሉበት፣ መፍትሄዎችን የሚያንሸራሸሩበት በማህበራዊ ሚዲያና በድረ-ገጾች ላይ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ተቃዋሚም ሆነ ደጋፊዎች የተለያዩ አቋሞች የሚያራምዱ ድረ-ገጾችን መጎብኘታቸው የተለመደ ነገር ነው። ከነዚህ ድረ-ገጾች ውስጥ በሳል ጽሁፎችን በማውጣት የሚታወቀው አቶ አብርሃ በላይ በባለቤትነት የሚያስተዳድሩት ኢትዮጵሚዲያ (www.ethiomedia.com) ነው። በአገር ውስጥም ይሁን በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በወያኔ የጭቆና አስተዳደር የሚደርስባቸውን በደል፣ እስር፣ ጭቆና፣ ግድያና ወከባ በተመለከተ ለማንበብ የሚጎበኙት ድረ-ገጽ ኢትዮሚዲያ ነው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም። ይህን ስል በሌሎች ድህረ-ገጾችንና በማህበራዊ ሚዲያዎችን ሚና ማሳነሴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ።
አቶ አብርሃ ከኢትዮጵያ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና፣ የውጭ ሚዲያ ጋዜጠኞች ኢትዮጵያን የተመለከቱ ወይም በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ የሚኖራቸውን መጣጥፎችንና ቪዲዮችን እየወሰዱ በድረገጻቸው በማተም ለአንባቢያንና ተመልካቾች ሲያደርሱ ቆይተዋል። ኢትዮጵያን የተመለከቱ አስተማሪ ትንተናዎች (የእርሳቸው ባይሆኑም) በድረ-ገጻቸው እያተሙ ሲያስነብቡን መቆየታቸው እሙን ነው። እኔ እስከማውቀው ድረስ ድረ-ገጹ በህወሃው መራሹ መንግስት የተገፉ የኢትዮጵያውያን ድምፅ በማስተናገድ በኩል የተወሰነ አስተዋፅኦ አበርክቷል፥ እያበረከተም ይገኛል እላለሁ።
አቶ አብርሃ በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሰፈነው አስተዳደራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በተመለከተ አልፎ አልፎም ቢሆን ይጽፉ እንደነበረ ድረ-ገጻቸውን የምንጎበኝ ሁሉ እናውቃለን። ሆኖም፣ ህወሃት ማሻሻያ አድርጎ በመንግስትነት እንዲቀጥል እንጂ፣ ከስልጣን እንዲወርድ በምንም መልኩ እንደማይፈልጉ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ የሪፖርተሩ አማረ አረጋዊና የአውራምባ ታይምስ ዳዊት ከበደ በተደጋጋሚ በሚያወጧቸው ጹሁፎችና ዜናዎች አስነብበውናል። አማረ አረጋዊና ዳዊት ከበደ ለይቶላቸው ከወያኔ ጋር ኢትዮጵያ ውስጥ ይሞዳሞዳሉ፥ አብርሃ በላይ በውጭ አገር የወያኔ አርበኛ በመሆን አንባቢዎቻቸውን እንደሚሰልሉ ክስ ቀርቦባቸው እንደነበረ ከዚህ በፊት የምናስታውሰው ነው ። ዋናው ከሳሽም አሁን የህወሃት ባለሟል የሆነው ዳዊት ከበደ ነው። አብርሃ ላይ የቀረበው ክስ ከተሰማ ጥቂት አመታት አልፈዋል። እርሳቸውም እስከዛሬ በድረ-ገጹ ስራ ቀጥለዋል።
የዚህ ፅሑፍ ዋና አላማ በአቶ አብርሃ በላይ ማንነትና ስብዕና ላይ ትንታኔ መስጠት ሳይሆን፣ ሰሞኑን ከአንጋፋው ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ሃያሲና የፖለቲካ ተንታኝ ከሆነው ከሙሉጌታ ሉሌ ድንገተኛ ሞት ጋር ተያይዞ አብርሃ በላይ ያቀረቡት አጭር ጽሁፍ የአርታኢውን ድብቅ ማንነት ገሃድ ማውጣቱን ለአንባቢ ለማሳወቅ ነው።
ጋሼ ሙሉጌታ ህይወቱ ከማለፉ አንድ ቀን ቀደም ብሎ በአካል አግኝቸው ነበር። የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖ ስለአብርሃ በላይ አንስተን አውርተናል፥ በእርግጥ ከዚህ በፊትም ስለ አቶ አብርሃ አንዳንድ ነገሮችን ነግሮኝ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ከአርበኞች ግንቦት ሰባት መዋሃድ በኋላ አብርሃ በላይ ምክንያቱን ግልጽ ባላደረጉበት ሁኔታ የጋሼ ሙሉጌታን ፁሑፎች በድረገጹ [ኢትዮሚዲያ] ላይ እንዳማያትሙለት ነግሮኛል። ለምን እንደማያትሙለት ደውሎ ሲጠይቃቸውም፣ “ጽሁፎችህ አልደረሱኝም” ወይም “ኢሜይሉን አላየሁትም” ከሚል ሰንካላ ምክንያት ውጭ ሌላ የሚያሳብቡት ነገር እንደሌለ ነግሮኝ ነበር።
በተለይም ደግሞ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ወደ ኤርትራ መሄዱን ተከትሎና አገር አድን እንቅስቃሴ የተባለው አዲሱ የተቃዋሚዎች ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ፣ አብርሃ በላይ ምቾት እንዳልተሰማቸው ከሚለጥፏቸው ጽሁፎችና ከሚዘግቧቸው አፍራሽ ዘገባዎች መረዳት ይቻላል። አቶ አብርሃ በኤርትራ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴም ሆነ አገኘነው የሚሉትን ድል አይዘግቡም ወይም ለመዘገብ ፈቃደኛ አይደሉም። ሞላ አስገዶም ወደ ኢትዮጵያ ሸሽቶ በተመለሰ ጊዜ፣ አቶ አብርሃ ድረ-ገጻቸው ላይ በኤርትራ የሚንቀሳቀስ 700 ተቃዋሚ ሃይል የኤርትራ ወታደሮችን እያጸዳ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ታርቆ እንደገባ አድርገው ነው የዘገቡት። እንዲህም አሉ።
The TPDM forces wiped out Eritrean forces near Omhajer, and later at Seq al-Ketir before heading to Hamdait, all Sudanese towns.
አቶ አብርሃ የተለመደውን የህወሃት ሰዎችን “ጀግንነት” አጉልተው ለማሳየት ከላይ በእንግሊዝኛ እርግጠኛ ሆነው ከጻፉት ጹሁፍ መረዳት ይቻላል። የጻፉትን ሃሳብ ለማጠናከር የፎቶ ማስረጃ ተጠቀመዋል [ፎቶው ከየት እንደተወሰደ ልብ ይሏል]።
የኤርትራን ጦር እያጸዱ ወደሱዳን የገቡ የህወሃት “ጀግኖች” ለምን አፈሙዛቸውን ወደ ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቂ እንዳላዞሩ አቶ አብርሃ ያሉን ምንም ነገር የለም። በተጨማሪም በሴፕቴምበር 13 2015 በጻፉት ዜና መሰል የተጋነነ ሙገሳ፣ ሞላ አስገዶም ጀግና ከመሆኑን በላይ በምስጢር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ሲሰሩ እንደነበረ አቶ አብርሃ በላይ አሁንም እርግጠኝነት ይነግሩናል። እንዲህም ይላሉ፣
“The top leaders of TPDM were working clandestinely with the Ethiopian government security for over a year .”
እንግዲህ አቶ አብርሃ የተጋነነና የተዛባ ዘገባ ማቅረብ የሚያዋጣቸው ከሆነ መብቻቸው ነው፥ የአንባቢያቸውን የእውቀት ልኬት ግን ጠንቅቀው ያወቁ አልመሰለኝም። ከእርሳቸው በላይ በፖለቲካ እውቀት የበሰሉ አንባቢዎችን ሳያገናዝቡ የጻፉት ፅሁፍ ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል። አቶ አብርሃ የህወሃት ተቃዋሚዎች መተባበር እንደሚያስደግጣቸው ለማወቅ በእርሳቸው ስም የሚያወጧቸውን የተወሰኑ ዘገባዎች ብቻ ማንበብ በቂ ነው። ተቃዋሚዎች ላይ የሆነ እንቅፋት ሲፈጠር በብርሃን ፍጥነት አፍራሽ ዘገባ ያዘጋጃሉ። ህወሃትን የሚቃወሙ (ለምሳሌ እንደ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ) ስለአርበኞች ግንቦት ሰባት ትግል የሚያወሱ ጹሁፎችን ለአንባቢ እንዲደርስ ሲጠይቁ ግን ሰውየው ለማስተናገድ ፈቃደኛ አይሆኑም። በኤርትራ በኩል በሚደረግ ትግል ላይ ብዥታ የሚፈጥር ጽሁፍ ካገኙ ግን ቶሎ ለማስተናገድ ወደር አይገኝላቸውም ።
እንግዲህ ባለፈው ሳምንት ከሙሉጌታ ሉሌ ጋር በዚህ ጉዳይ ላይ ትንሽ አውግተን ነበር። ያኔ ድሮ ሙሉጌታ ሉሌ የኢትዮጵያ ፕሬስ መምሪያ ሃላፊ በነበረበት ጊዜ፣ ለአቶ አብረሃ በላይ ከፍተኛ ውለታ ውሎላቸዋል። የዘር ካርድ በማይመዘዝበት በዚያን በደርጉ ዘመን፣ አቶ አብርሃ ስራ አጥተው አዲስ አበባ ሲንከራተቱ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዲቀጠሩ ያደረጋቸው ሙሉጌታ ሉሌ ነበር። አቶ ሙሉጌታ ለአብርሃ በላይ የሚከፈላቸው ደሞዝ ትንሽ ስለነበር፣ በባዶ እግራቸው እንዳይሄዱ በማሰብ ለጫማ መግጃ የሚሆን ገንዘብ ሰጥቷቸዋል። ለሻይ ቡና የሚሆን የኪስ ገንዘብም ደጉሟቸዋል። ሁለቱም እዚህ አሜሪካ ከመጡ በኋላም አብርሃ በላይ ሙሉጌታ የዋሉላቸውን ውለታ እያነሱ ያመሰግኗቸው እንደነበረ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ሌሎች እማኞች ባሉበት ጋሼ ሙሉጌታ ነግሮናል።
ይህ ከተነጋገርን ከ 1 ቀን በኋላ ነው እንግዲህ አቶ ሙሉጌታ ህይወቱ ያለፈው። እንደተለመደው በተቃዋሚዎች ጉዳት ጮቤ የሚረግጡት አብርሃ በላይ፣ የአንጋፋው ጋዜጠኛ ህይወት የማለፉን መርዶ በሰአታት ውስጥ በድረ-ገጻቸው ላይ አስነበቡን። መርዶው ግን የሙሉጌታ ሉሌን አንጋፋነት በመመስከር “ነፍስ ይማር” የሚል ሳይሆን፣ ሟቹ በበአሉ ግርማ ግድያ ወንጀል የሚጠየቅ፣ አድርባይነት የሚያጠቃውና “ጭፍን ተቃዋሚ” መሆኑን በመተንተን ሙሉጌታ ሉሌ ስብዕና ላይ ጥላሸት መቀባት ነበር። አብርሃ ከጻፉት ጽሁፍ እንዲህ የሚል አስገራሚ አረፍተነገር ሰፍሮ ይገኛል።
“Mulugeta never addressed the accusation that he and friends like literary critic Asfaw Damte had a hand in the disappearance of Ba’alu”
ይህ አረፍተነገር ሙሉጌታ ሉሌ ከአስፋው ዳምጤ በመሆን በአሉ ግርማን በማስገደሉ ሂደት እጃቸው አለበት የሚል ሲሆን፣ አቶ ሙሉጌታም ሳያስተባሉ መሞታቸው በድርጊቱ ተሳታፊ ሳይሆኑ አይቀሩም የሚል እንድምታ ያለው ሃሳብ የያዘ ነው።
በኢትዮጵያውያን ባህል እንኳን እንደ ሙሉጌታ ሉሌ አይነት ሰላማዊ የተባ ብዕረኛ ይቅርና፣ በአደባባይ ንጹሃንን ያስግደሉ አምባገነን መሪዎች ከሞቱ በኋላ አልተወቀሱም [መለስ ዜናዊን እዚህ ላይ ይጠቅሷል]። ሙት አይወቀስም። እዚህ ላይ አብርሃ በላይ ነውረኛ ሙት ወቃሽ የበሉበትን ወጪት ሰባሪ ራስ ወዳድ ግለሰብ መሆናቸውን ነው ያስመሰከሩት። በአሉ ግርማ በደርግ ባለስልጣናት ታግቶ ከተወሰደ ከ31 አመት በኋላ በግድያው ምንልባትም የአቶ ሙሉጌታ እጅ ሊኖርበት ይችላል የሚል ከንቱ ክስ ማንሳታቸው ለምን ይጠቅማቸው ይሆን? “ጋዜጠኛ” ነኝ የሚሉት አብርሃ በላይ በምርመራ ጋዜጠኝነት (investigative journalism) የበአሉን አሟሟት ሁኔታ እስካሁን ድረስ ለምን አልዘገቡም? የወንጀል ክስ መርዛቸውን ለመርጨት ሙሉጌታ ሉሌ እስኪሞቱስ ድረስ ለምን ጠበቁ? ለብዙ አመታት የሙሉጌታ ሉሌን ጽሁፎች ሲያስተናግዱ የቆዩና በስልክም ጭምር ሲያገኟቸው የኖሩትን ሰው ስለ በአሉ ግርማ ምስጢራዊ አሟሟት በግልም ቢሆን ለምን እስካሁን አልጠየቁትም? እ.ኤ.አ በ1984 ዓም አፈናውን ማን እንደፈፅመ ባልታወቀበት ሁኔታ [በደርግ ዘመን እንኳን ኦሮማይን የመሰለ የደርግን መንግስትን ከንቱነትን የሚያሳይ መጽሃፍ ተጽፎ ይቅርና በትንሽ የሃሳብ ልዩነት ሰው በሚረሸንበት ዘመን] መረጃ ሳይዙ እንዲህ አይነት ጥላሸት የመቀባት ሱስ ምን የሚሉት ነው? ዛሬ የሙሉጌታ ሉሌ ትኩስ ሬሳው ሳይቀበር እንዲህ አይነት የስም ማጥፋት ዘመቻ መክፈታቸው የግል ቂም ለመወጣት ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ደርግ በአሉ ግርማን ለመግደል የሙሉጌታ ሉሌን ወይም የአቶ አስፋው ዳምጤን ሃሳብ (recommendation) የሚፈልግ አይመስለኝም። ለደርግ ባለስልጣናት ኦሮማይ መጽሃፍ ደራሲውን ለመግደል በቂ መረጃ ነበር።
ሙሉጌታ ሉሌ ስለ በአሉ ግርማ አሟሟት የሚያውቀው ምንም ፍንጭ እንደሌለው በተደጋጋሚ ተናግሯል። ይህንን አቶ አብርሃ በላይም በደንብ አብጠርጥረው ያውቃሉ። ሆኖም አብርሃ ዛሬ አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ለቀረበበት ክስ መመለስ በማይችልበት ደረጃ አንደበቱ ሲዘጋ በሰአታት ልዩነት ውስጥ የወንጀለኝነት ክስ አዥጎደጎዱትበት። አብርሃ በላይ ክሱን ለድረ-ገፅ ጎብኚዎቻቸው በዜና እረፍት ዘገባ ማጣፈጫነት ለውሰው ሲያቀርቡት ለአፍታም አልዘገዩም፥ ሬሳው እስኪቀበር እንኳን አልቆዩም። አብርሃ በላይ የጻፉት ዜና ዋናው ሃሳብ የአቶ ሙሉጌታ ዜና እረፍት ሳይሆን፣ ሙሉጌታ ሉሌ ከግድያ ወንጀል ተጠርጣሪነት ነጻ ለመሆኑ ማረጋገጫ አለመስጠቱ ለማመላከት ነው! አርታኢው አብርሃ ይህንን ዜና እረፍት በሚጽፉበት ወቅት ከፊታቸው ድቅን ያለባቸው፣ በፊት የተደረገላቸው ውለታ ሳይሆን በቅርቡ ሙሉጌታ ሉሌ ወያኔን የሞገቱበት የሰላ ብዕር ነው። አብርሃ በላይ የሚያስተዳድሩትን ድረ-ገጽ በመጠቀም የትሁቱን ጋዜጠኛ ዝና ጥላሸት ለመቀባት ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም (የተፈነቀለው ድንጋይ ወደ እርሳቸው ተወርውሮባቸው ግን ይሆናል)። የሙሉጌታ ሉሌን ዜና ዕረፍት አስመልክተው በጻፉት ጽሁፍ ሆዳቸው ያባውን በደስታ ስካር ዘረገፉት። የህወሃት ሰዎች መሞገት የማይችሉትን ሰው አጋጣሚ በመጠበቅ የፈጠራ ወሬ ፈብርኮ ማሸማቀቅ የመጨረሻ ግባቸው ነው።
የአቶ አብርሃ ሃተታ በዚህ አላበቃም። አብርሃ በላይ አንደበቱ በሞት በተዘጋው ሙሉጌታ ሉሌ ላይ ጥላሸት መቀባታቸውን ቀጠሉ። በዚያው የመርዶ ሳይሆን የመልካም ሰው ስም ለማጉደፍ በሞከሩበት ከንቱ ጹሁፋቸው፣ ሙሉጌታ ሉሌ አጥፍቶ መጥፋት የሚል መጽሃፍ የጻፈው የደርግን ስራ በማንቋሸሽ እራሱን ነጻ ለማድረግ እንደሆነ አድርገው የፈጠራ ወሬ ፈበረኩ። እንዲያውም፣ እጥፍቶ መጥፋት የተባለው መጽሐፍ የተጻፈው ለህወሃት እጅ መንሻ ነበር አሉ። በመቀጠልም ህወሃት መጽሃፉን ወደ ቆሻሻ መጣያ በመጣል፣ ሙሉጌታንም ስራ አጥ አድርጓቸዋል በማለት ሃሳባቸውን ይደመድማሉ። የአብርሃ በላይ ጹሁፍ እንደሚከተለው ይነበባል።
የአቶ አብርሃ ሃተታ በዚህ አላበቃም። አብርሃ በላይ አንደበቱ በሞት በተዘጋው ሙሉጌታ ሉሌ ላይ ጥላሸት መቀባታቸውን ቀጠሉ። በዚያው የመርዶ ሳይሆን የመልካም ሰው ስም ለማጉደፍ በሞከሩበት ከንቱ ጹሁፋቸው፣ ሙሉጌታ ሉሌ አጥፍቶ መጥፋት የሚል መጽሃፍ የጻፈው የደርግን ስራ በማንቋሸሽ እራሱን ነጻ ለማድረግ እንደሆነ አድርገው የፈጠራ ወሬ ፈበረኩ። እንዲያውም፣ እጥፍቶ መጥፋት የተባለው መጽሐፍ የተጻፈው ለህወሃት እጅ መንሻ ነበር አሉ። በመቀጠልም ህወሃት መጽሃፉን ወደ ቆሻሻ መጣያ በመጣል፣ ሙሉጌታንም ስራ አጥ አድርጓቸዋል በማለት ሃሳባቸውን ይደመድማሉ። የአብርሃ በላይ ጹሁፍ እንደሚከተለው ይነበባል።
“Even though he had stayed close to the top men of the Derg, Mulugeta had also tried to break clean with the fallen regime, by rolling out a red carpet for EPRDF in the form of writing a book, Atifto Metfat. The book discredits the mengistu regime for beginning to end, but EPRDF rewarded Mulugeta by tossing his book into a trash can and himself into the mass of the unemployed.”
እነዚህ ሁለት አረፍተነገሮች የተመለከተ ሰው የአብርሃ በላይ ማንነትና እሳቤ (motive) በደምብ ይረዳል። አቶ አብርሃ የፈለጉት፣ ሙሉጌታ ሉሌ የደርግ ከፍተኛ ባለሟሎች ጋር ቁርኝት እንደነበራቸው በማሳየት የበአሉ ግርማን አሟሟት ምስጢርም ከዚህ ሰው ጋር በማያያዝ ወንጀለኛ ነው ብሎ አንባቢው እንዲያምን ማድረግ ነበር። ከዚያ በሁላም ሙሉጌታ ከጊዜው ጋር ለመመሳሰልና ራሱን ከደርግ ለመለየት ከህወሃት ቡራኬ ለማግኘት ምን ኣንዳደረገ ሊነግሩን ሞክረዋል። እኔ እስከገባኝ ሙሉጌታ ሉሌ ወያኔንና ግብረአበሮቹን በብዕር ፍላፃ ሲወጋ የኖረ ታላቅ ሰው ነው። ወያኔ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ይወጡ የነበሩት የሙሉጌታ ሉሌ መጣጥፎችና መጽሄቶች መመልክቱ ሰውየው ህይወቱን እስከመክፈል የሚደርስ የማይነቃነቅ አቋም እንደነበረው ያስረዳሉ። ሙሉጌታ ሉሌ እንኳን ለወያኔ አሽከር ሆኖ መጽሃፍ ሊጽፍ ቀርቶ ከራሱ ህሊና ውጭ ምንም የማይበገረው ጀግና መሆኑን በሚጽፋቸው ጽሁፎች አስመስክሯል።
ሙሉጌታ ሉሌ ለማንም ዘረኛ አላጎበድድም ብሎ መሰለኝ የሚወደውን አገር ጥሎ፣ ቤተሰቡን በትኖ፣ በስደት አለም ኖሮ፣ በስደት አለም የሞተው! ለህሊናው እንጂ ለሆድ አልኖርም ብሎ መሰለኝ የወያኔን አምባገነንነት፣ ዘረኝነት፣ ሸር፣ ቂመኝነት፣ ጠላትነት በተባ ብዕሩ ሲዋጋ የኖረው! በአገሩ ኢትዮጵያ ሰላም ዲሞክራሲ ነጻነት ሰፍኖ የማየት ህልም ኖሮት መስሎኝ እፎይ ብሎ ማረፍ በነበረበት በጡረታ ጊዜው ራሱም መስዋዕት አድርጎ ሌት ተቀን የታገለው።
አብርሃ በላይ ሙሉጌታ ሉሌን ከከፍተኛ የደርግ ባለስልጣናት ጋር ቁርኝት ነበረው ብለው ሲከሱ፣ በየትኛው መረጃ ላይ ተመስርተው ይሆን? ጋሼ ሙሉጌታ አጥፍቶ መጥፋት የተባለውን መጽሃፍ የጻፈው ወያኔን ለማስደሰት ብሎ ኣንደሆነ አብርሃ በላይ እንዴት አወቁ? ወያኔስ መጽሃፉን አልፈልግም በማለት የቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ እንደጣለ የጽሁፍ ወይም የሰነድ ማስረጃ አላቸውን? ወይንስ ግምታቸውንና (personal opinion) መረጃን (hard facts) ለጋዜጠኝነት ግብዓት አንድ ላይ ቀላቅለው እየወቀጡት ነው? እኔ እስከገባኝ ድረስ ዜና ዕረፍት ነው ብለው የጻፉት የፈለጉትን ወይም የገመቱትን ሃሳብ እንጂ በመረጃ ተመርኩዘው አይደለም። መረጃ አለኝ የሚሉ ከሆነ ግን ያቅርቡትና እንወያይበት።
አብርሃ በላይ በሙሉጌታ ሉሌ ላይ የጀመሩት የስም ማጥፋት ዘመቻ ከላይ ባነሳኋቸው በሁለት ሃሳቦች ብቻ አያበቃም። አቶ አብርሃ ሙሉጌታ ሉሌ ምን አይነት መጣጥፎችን ይጽፍ እንደነበረ ዜና-እረፍት-መሰል ጽሁፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል።
“….Mulugeta had the time to write engaging articles under the pen names of Tsegaye Gebremedhin Araya and Sineshaw Tegegn. Almost all commentaries were shots fired at the TPLF/EPRDF regime.
አብዛኞቻችን ጸጋዬ ገብረመድህን አርአያና ስንሻው ተገኝ የአቶ ሙሉጌታ ሉሌ የብዕር ስም መሆኑን እናውቃለን። እዚህ ላይ የአብርሃ በላይ አንኳር ሃሳብ፣ ሙሉጌታ ሉሌ በቋሚነት ህወሃትን የሚቃወም ጸሃፊ ነበር ነው የሚለው። አዎ! ሙሉጌታ ሉሌ ህወሃት የሚሰራውን እኩይ ስራ ሲቃወም ነበር። መቼም አቶ አብርሃ ለምን እንደእርሳቸው አንዳንዴ ህወሃትን አልደገፍክም ካላሉት በስተቀር። ታዲያ ሙሉጌታ ሉሌ ሞላ አስክዶም ወደ ኢትዮጵያ ሲከዳ ጅግናው የወያነ ሰራዊት የሻቢያን ጦር እየደመሰሰ ወደኢትዮጵያ ኮበለለ ማለት ነበረበት ይሆን? ወ/ሮ ዊንዲ ሸርማን የኢትዮጵያ መንግስት ዴሞክራሲያዊ ነው ሲሉ ወይም አርበኞች ግንቦት ሰባት አሸባሪ ነው ሲሉ አቶ ሙሉጌታ “አዎን” ማለት ነበረበት ይሆን? ከዚህ ጋር ተያይዞ “ እርዱን ፍረዱልን አንልም፤ በነፃነት ተጋድሎአችን አይግቡብን!” በሚል ርዕስ የተሰየመችው የጸጋዬ ገብረመድህን አርአያን ጽሁፍ በሰኔ ወር ለአቶ አብርሃ ተልኮላቸው ለምን እንዳላተሟት እርሳቸውም እኛም እናውቃለን። አቶ አብርሃ ከላይ በእንግሊዝኛ በጻፉት አረፍተ ነገር ለማስተላለፍ የፈለጉት አቶ ሙሉጌታ የገዢው ፓርቲ መልካም ስራ የማይታየው “ጭፍን ተቃዋሚ” ነው የሚለውን ሃሳብ ነው። አቶ አብርሃ፣ ሙሉጌታ ሉሌ አዲስ አበባ እያለ በመኪና የግድያ ሙከራ እንደተደረገበት ሳያነሱ፣ ህወሃት በፍርድ ቤት ይሞግታቸው እንደነበረ በዜና ዕረፍት ጹሁፋቸው ላይ ያሰፈሩው ሃሳብ የወያኔ መንግስት በህግ የበላይነት የሚያምን ድርጅት እንደሆነ ለማሳየት የተደረገ የተሸፋፈነ የማስመሰያ ስልት ነው።
እኔ ሙሉጌታ ሉሌን ሳውቀው፣ የህወሃትን እኩይ ድርጊት ከማጋለጥና ከመቃወም በተጨማሪ ስለሰው ልጆች መብት፣ ስለፍትሃዊነት፣ ስለነፃነት፣ ስለፍቅር፣ ስለእኩልነትና ስለዲሞክራሲያዊነት ከንጉሱ ጊዜ ጀምሮ በቆራጥነት ሲጽፍና ሲያስተምር እንደኖረ ነው። ሙሉጌታ ሉሌ ስለአገር አንድነት፣ ሉአላዊነት፣ ስለመልካም አስተዳደር ያለመታከት ዜጋውን በእውቀት ለማነጽ የቻለውን ሁሉ አድርጓል። ለዚህ የማይነቃነቅ ጽኑ አላማ ዋጋ ከፍሏል። የሚወዳትን አገሩን ትቶ፣ ቤተሰብ በትኖ በስደት አለም በብቸኝነት ተንከራቷል፣ በስደት እያለም ህይወቱ በድንገት አልፏል። እንደአንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ሃያሲና፣ ደራሲ ለአገሩና ለወገኑ አቅሙ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል።
ሙሉጌታ ሉሌ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነጻነት ናፋቂ ኢትዮጵያውን ዘንድ በስራው ገንኖ የሚኖር፣ ከሞት በስተቀር ማንም ያልበገረው ጀግና ታጋይ ነው።ጋሼ ሙሉጌታ ለሁላችንም የትግል አርአያ ሊሆን የሚችል ጠንካራ ዜጋ ነው። ሁላችንም ልንኮራበት የሚገባ ታላቅ የነጻነት አባት ነው። ባለጊዜዎችና አድርባዮች ጊዜና ወቅት እየጠበቁ ክህደት ቢፈጽሙም፣ የሙሉጌታ ሉሌ መስዋዕትነት ግን መቼም ቢሆን ሲታወስ የሚኖር ድንቅ ስራ ነው። ሙሉጌታ ሉሌ በኢትዮጵያ ውስጥ በህወሃት መራሹ መንግስት የሚደርሰውን በደል ተቋቁሞ፣ ጸጋዬ ገብረመድህን አርአያና ስንሻው ተገኝ በሚሉ የብዕር ስሞቹ ለህይወቱ ሳይፈራ፣ ለቤተሰቡ ደህንነት ሳይሳሳ ወያኔ/ህወሃትን ያርበደበደ የጀግኖች ጀግና ነው።
እንግዲህ ከህወሃት ጋር ንክኪ ያላቸው ግለሰቦች በምን ወቅት ጉዞአቸውን አቋርጠው ወደቀድሞ ጎሬያቸው እንደሚመለሱ ለማወቅ እጅግ አዳጋች ነው። ከህወሃት ጋር ትስስር የነበራቸው ጋዜጠኞችና ሌሎች ዜጎች [አቶ አብርሃ ያሞገሷቸው] የአካባቢውን ሁኔታና አየር ንብረቱ በማየት አሰላለፍ መቀየር እና ነጥብ ማስቆጠር ያደጉበት ጥበብ ነው። አቶ አብርሃ በላይም ከዚህ የተለየ ስራ አልሰሩም። ዛሬ ሙሉጌታ ሉሌ አንደበቱ በተዘጋበት ሁኔታ እንደአብርሃ በላይ ያሉ የህወሃት አጨብጫቢዎች የሟቹን ሬሳ በጩቤ ሊወጉት ቢሞክሩም፣ የሙሉጌታ ሉሌ ስራዎቹ በገሃድ የሚታዩ ህያው ምስክር ናቸውና ከማንኛቸውም አደጋ እስከወዲያኛው ይከላከሉታል።
“ጋዜጠኛ” አብርሃ በላይ ከዚህ በፊት በተለያዩ ሰዎች እና ጉዳዮች ላይ የጻፉዋቸውን እንዲህ አይነት እሳቤዎችን (latent motives and personal attacks) እያነሳሁ ብዙ ልሞግታቸው አስቤ ነበር። የአቶ አብርሃ በላይን ድረ-ገጽ የሚያነብ ሰው የአርታኢውን ማንነት ጠንቅቆ ስለሚረዳ ለጊዜው ትቸዋለሁ። አስፈላጊ ሆኖ ካገኘሁት ግን መመለሴ አይቀርም። ይህንን ጽሁፍ ያዘጋጀሁትም አቶ አብርሃ በላይ ሆን ብለው የሟቹን መልካም ስም ለማጉደፍና በሆድ የቋጠሩትን ቂም ለመወጣት ብለው የጻፉት እንደሆነና ለወደፊቱም ትምህርት እንዲሆናቸው አንባቢን ላለማሰልቸት በትንሹም ቢሆን [ብዙ ማቅረብ የምችለው መረጃ ቢኖረኝም] ለማሳየት ነው።
ለአቶ አብርሃና ሌሎች ድብቅ አጀንዳ ላላቸው ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች መናገር የምፈልገው ነገር አለ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ጋዜጠኝነት ምን እንደሆነ በትክክል መረዳት ያለባቸው ይመስለኛል። አንድ ጋዜጠኛ የአከባቢው አውድና (social context) በዙሪያው ያሉትን አንባቢዎች ወይም አድማጮች (diverse audience) ፍላጎትና ግንዛቤ ማወቅ ይኖርበታል። ጋዜጠኝነት እንደፈለጉ የሚጋልቡበት ፈረስ አይደለም። የፈለጉትን እያሞገሱ፣ ያልጣማቸውን እያኮሰሱ መጋለብ እንደማይችሉ አንባቢው ለአቶ አብርሃ በላይ በደምብ የነገራቸው ይመስለኛል። ዱላ ስለበዛባቸውም ነው በዜና ዕረፍት መልክ የጻፉትን መርዘኛ ጽሁፍ ከተወሰነ ሰዓት በኋላ ያነሱት። በእኛ ማህበረሰብ አውድ ሙት አይወቀስም፥ ባሃላችንም አይደለም። ጋዜጠኞቹ ሆነ ሌላ ሰው ለክሳቸው ማስረጃ እንኳን ቢኖራቸው፣ ሟች አፈር እስኪለብስ መረጃውን ማቆየት ለዘመናት አብሮን የኖረው ባህላችን ነው። ከተቻለም፣ ጋዜጠኞቹ መረጃ ካላቸው በዚያ መረጃ ተመርኩዘው አንድ ሰው የሰራውን ጥፋት በቁም (በህይወት) እያለ መጠየቅና ማጋለጥ እንጂ፣ የመልካም ሰውን ስምና ዝና ሆን ብሎ ለማጉድፍና የግል ቂምን ለመወጣት ሲባል ሰው ከሞተ በኋላ ዝባዝንኬ አይዘገብም። እንደ አቶ አብርሃ በላይ፣ የሙት ልሳን ስለተዘጋና መልስ ስለማይሰጠኝ ያሻኝን አወራለሁ ማለት የመልስ ምቱ እጅግ የከፋ ነው የሚሆነው። መረጃ የሌለው አሉባልታ መፈብረክ የትም አያደርስም፥ ተዓማኒነትም ያሳጣል እንጂ። መልካም ስም ሁሌም ከመቃብር በላይ በመሆኑ ሰው የሚዳኘው አንድ ስም ለማጥፋት ሆን ብሎ የተንቀሳቀሰ ግለሰብ በተናገረው ሳይሆን መላው ማህበረሰብ በመሰከረው ነው።
ሁላችንም ከሞት አንቀርም። እኔ [ቀድሜ ካልሞትኩ] አቶ አብርሃ ሲሞቱ [መሞታቸው አይቀርምና] የወያኔ ሰላይ ነበሩ ብዬ ዜና ልሰራባቸው አስቤ ነበር። ለዚህም ጥሩ ጥሩ ማስረጃዎች አሉኝ። ሆኖም ለአቶ አብርሃ ትምህርት መስጠት ፈለግኩ። የሞተ ሰው አይከሰስምና አቶ አብርሃን በህይወት እያሉ ልጠይቃቸውም ወሰንኩ። ኤዲያ! እኔ እንደእርሳቸው የሰው ልሳኑ ተዘግቷልና ገና ለገና መልስ አይሰጠኝም ብዬ አስከሬን መክሰስ አልፈለግም!
የምጠራጠረው ሰው በህወይቱ እያለ ጥርጣሬዬን ሊያጠራልኝ ይገባል። አቶ አብርሃ በላይ ከሙሉጌታ ሉሌ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት፣ በበአሉ ግርማ ግድያ የሙሉጌታ ሉሌ እና የአስፋው ዳምጤ እጅች እንዳሉበት የሚያሳይ ማስረጃ፣ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ ለወያኔ እጅ መንሻ መጽሃፍ ጻፉ ብለው ለከሰሷቸው፣ ህወሃት አልቀበልም አለ ለሚለው ክስ ማመሳከሪያ የሰነድ ወይም የሰው ማስረጃ፣ ስለሞላ አስገዶም [የሻቢያን ጦር እየደመሰሰ ሱዳን ስለመግባቱ] ስለጻፉት የጀግንነት ገድል የሚያወሳ ማስረጃ [ስንት ሰው እንደገደሉ፣ ለስንት ሰአት ጦርነት እንዳደረጉ፣ በየትኛው መሳሪያ እንደተዋጉ፣ የኤርትራም፣ የሞላ አስገዶም የጦር አሰላለፍ የሚያሳዩ ማስረጃዎች]፣ አቶ አብርሃ ህወሃት ወደውጭ ለስለላ የላካቸው ናቸው የሚለውን ክስ ውድቅ የሚያደርግ የመከላከያ ማስረጃ [በሚጽፉትና በሚሰሩት ስራ ከህወሃት ያልተሻሉ በመሆናቸው]፣ በትጥቅ ትግል የሚታገሉ ተቃዋሚዎችን የሚያወሳ ጹሁፍ አያስተናግዱም ለሚለው ምክንያታዊ መልስ እና ለሌሎች አያሌ ጥያቄዎች አሉኝ እና ምላሽ ይስጡኝ! ሰውን በሚገባው ቋንቋ ማናገር በህይወት እያለ ነው። እኔም አቶ አብርሃን የጠየቋቸው በህይወት እያሉ እንዲመልሱኝ ነው። ከሞቱማ ሞቱ ነው፣ መክሰስም አያስፈልገኝም። ሙትን የሚከስ ሰው ራሱ በህይወት መኖሩን የማያውቅ ነው።
ለክሱ መልስ መስጠት የማይችለውን የጋሼ ሙሉጌታ ሉሌን ስም እዚህ በተደጋጋሚ ማንሳቴ እጅግ እያሳዘነኝና እየቆጨኝ ነው። ይህን ያደረኩግ ግን ወድጄ አይደለም። ጋሼ የሙሉጌታ ነፍስ በገነት ያኑርልን! አሜን!
ጸሃፊውን በኢሜይል fentaye@gmail.com ማግኘት ይችላሉ።
No comments:
Post a Comment