Translate
Monday, October 19, 2015
የአርበኞች ግንቦት 7 ሪከርድ የሰበረ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በሚኒሶታ * ነአምን ዘለቀ አርበኞች ግንቦት 7 መንፈስ ነው አሉ (ሪፖርታዥ)
የአርበኞች ግንቦት 7 ሪከርድ የሰበረ የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት በሚኒሶታ * ነአምን ዘለቀ አርበኞች ግንቦት 7 መንፈስ ነው አሉ (ሪፖርታዥ)
“የኤርትራ መንግስት ከራሷ ጋር የታረቀች ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትመሰረት ይፈልጋል”
“ሁሉንም ፖለቲካ ሃይሎች ያካተተ የሽግግር ሂደት ይኖራል”
“የወደብ ጥያቄን በተመለከተም ወደፊት በድርድር/በሰጥቶ መቀበል የሚፈታ ይሆናል እንጂ አሁን የትግሉ አጀንዳ መሆን የለበትም”
“የመረጃ ትንሽ የለውም… መረጃ አይናቅም”
(ዘ-ሐበሻ) በሚኒሶታ ትናንት ማምሻውን ለአርበኞች ግንቦት 7 ገቢ ማሰባሰቢያ የተደረገው ዝግጅት በታሪካዊነቱ እንደሚቀመጥ የሚኒሶታ ነዋሪዎች አስታወቁ:: በሚኒሶታ ታሪክ ለአንድ የፖለቲካ ድርጅት በአንድ ቀን 78 ሺህ ዶላር በላይ ሲሰበሰብ የትናንቱ የመጀመሪያው ነበር::
ከ200 በላይ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን በተሰባሰቡበት በዚሁ ታሪካዊ የአርበኞች ግንቦት 7 የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ ነአምን ዘለቀ እና ወጣት ሚካኤል ከላስቬጋስ ነበሩ:: ይህ የገቢ ማሰባሰብ ዝግጅት የተከፈተው የንቅናቄው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና አቶ ኤፍሬም ማዴቦ ከአስመራ በቭዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት ነበር::
ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በመልዕክታቸው እየተደረገ ያለው ትግል አንድን አምባገነን ጥሎ ሌላ አምባገንን ለመተካት ሳይሆን የተሻለች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት እንደሆነ አስምረውበታል:: ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋርም በኢትዮጵያ አንድነት በመተማመን በመነጋገር ላይ መሆናቸውን እና ጥሩ ነገር እንደሚሰማም የገለጹት ፕሮፌሰሩ በቶሎ ትግሉ እንደሚጀመር አስታውቀዋል::
በዕለቱ በአዳራሹ በክብር እንግድነት የተገኙት የንቅናቄው የውጭ ጉዳይ ሃላፊ አቶ ነአምን ዘለቀ ባሰሙት ንግግር “አርበኞች ግንቦት 7 መንፈስ ነው” ብለዋል:: ይህን ሲያብራሩም “የአርበኞች ግንቦት 7 ተዋናዩም ተመልካቹም ሕዝቡ ነው:: ንቅናቄው ዘረኝነትን በተንገሸገሸ – እኩልነት; ፍትህ እና ሰላም በተጠማው የኢትዮጵያ ተማሪ… ወጣት… ገበሬ.. ሴት… ወንድ ውስጥ ያለ ሕዝባዊ ትግል ነው:: ይህም ማለት በሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ንቅናቄው አለ ማለት ነው:: ይህ መንፈስ ሥር እየሰደደ ሄዷል:: አሁን ባለው ዘረኛው ስርዓት ብዙዎች ተገድለዋል… በግፍ ታስረዋል በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተንገላተዋል:: እነዚህ ሁሉ ሚሊዮኖች በውስጣቸው የአርበኞች ግንቦት 7 መንፈስ አላቸው::”
አቶ ነአምን ንግግራቸውን ቀጥለው “የወያኔ ፋሽስታዊ አገዛዝ በግፍ ብዙዎችን ከመሬታቸው ፎቅ ካልሰራችሁ እየተባሉ እንዲገፉ አድርጓል:: ቦታቸው ተቸብችቧል:: እነዚህ ዜጎች መሥእረታዊ የዜግነት መብታቸውን ተነጥቀዋል:: በጋምቤላ በደቡብ እየተደረገ ያለው ይኸው ነው:: የዘር ማጥፋት እየደረሰባቸው ነው:: እነዚህ የወያኔ ሰለባ የሆኑ ወገኖቻቸን ዴሞክራሲን የሚናፍቁ ናቸው:: ብዙ ኢትዮጵያውያን ካለፍርድ በ እስር ይማቅቃሉ:: ፍርደ ገምድሉ ሥር ዓት በፍትህ ላይ ቀልደዋል:: በነዚህ ሚሊዮኖች ውስጥ ሁሉ የአርበኞች ግንቦት 7 መንፈስ አለ” ብለዋል::
“በኮንትሮባንድና በዘረፋ የተሰማሮ 90% የሕወሓት ጀነራሎች እና መኮንኖች ሃብታም በሆኑበት መከላከያ ሠራዊት ውስጥ… አርበኞች ግንቦት 7 አለ:: ሠራዊቱ በከንቱ የወያኔ ጣልቃ ገብነትና ወረራ ደማቸው ደመከልብ ለመሆን ችሏል:: ይህ ሠራዊት እኩልነትን የተጠማ ሠራዊት ነው::” በማለት አሁን ስላለው የሕወሓት/ኢሕ አዴግ ሠራዊት ስለሚደርስበት የዘር መድልዎ የጠቀሱት አቶ ነአምን የትግሉ መዳረሻ የት ነው? በሚለው ንግግራቸው አርበኞች ግንቦት 7 መዳረሻ ዴሞክራሲያዊ ሥር ዓት መገንባት እንደሆነ ገልጸዋል:: አሁን ያለው ሥርዓትም በኃይል የወጣ የመጨረሻው አምባገነን ሥርዓአት ይሆናል ብለዋል::
“ሁሉንም ፖለቲካ ሃይሎች ያካተተ የሽግግር ሂደት ይኖራል:: ከሁሉም ባለድርሻዎች ጋር ቁጭ ብለን የምንነጋገርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም” ያሉት አቶ ነአምን በ3ኛ ደረጃ ስለ ኤርትራ መንግስት አብራርተዋል::
“የኤርትራ መንግስት ከራሷ ጋር የታረቀች ጠንካራ ኢትዮጵያ እንድትመሰረት ይፈልጋል:: እንድትበታተን ይሰራል ብለን አናምንም:: ኢትዮጵያን የማዳከም ስልት ወይም ፖሊሲ ኤርትራ አላት ብለን አናምንም:: በጣም ጤናማ ስኬታማ ኢትዮጵያ እንድትኖር የኤርትራ መንግስት እንደሚፈልግ ነው የምናውቀው” በማለት የተናገሩት አቶ ነአምን አርበኞች ግንቦት 7 ከኤርትራ መንግስት ጋር ኢትዮጵያን በሚመለከት ስትራቴጂካዊ በሆኑ ጉዳዮች; በወደብ ጥያቄ ለመደራደር ምንም ዓይነት ስልጣን እንደሌለው እንዲሰመርበት እፈልጋለሁ ብለዋል::
“የወደብ ጥያቄን በተመለከተም ወደፊት በድርድር/በሰጥቶ መቀበል የሚፈታ ይሆናል እንጂ አሁን የትግሉ አጀንዳ መሆን የለበትም” ያሉት አቶ ነአምን በ4ኛ ደረጃ በውጭ ከሚገኘው ኢትዮጵያዊ ይህ የነፃነት ትግል ምን እንደሚጠብቅ አብራርተዋል:: በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ይህን ትግል በዲፕሎማሲው; በቁሳቁስ እና በገንዘብ ሊደግፍ እንደሚገባ ያስታወቁት የንቅናቄው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ “በውጭ ያለው ኃይል በየከተማው ያሉትን ሴናተሮችን እና ኮንገረሶችን ስለኢትዮጵያ መንግስት ጥፋቶች ሊነግሩ ይገባል:: በየከተማው ባሉ ሚዲያዎች እየወጡ በመጻፍና በመናገር የዲፖሎማሲው አካል በመሆን ትግሉን ማገዝ ይገባቸዋል:: የህክምና ሙያ ላይ የተሰማሩ ሰዎችም እንዲሁ በመድሃኒት አቅርቦት ላይ ብዙ ይጠበቅባቸዋል” ያሉት አቶ ነአምን አርበኞች ግንቦት 7 ጠላትን በተመለከተ ትልቅ የመረጃ ማሰባሰቢያ ኔትወርክ እንዳለው ጠቁመው ሁሉም ኢትዮጵያዊ መረጃዎችን ለድርጅቱ በተዘራጋው መዋቅር በኩል እንዲያስተላለፍ ጠይቀዋል:: “የመረጃ ትንሽ የለውም… መረጃ አይናቅም” ያሉት አቶ ነአምን በውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ በስር ዓቱ ላይ እስካሁን እያሳየ ያለውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት እንዲቀጥል አበክረው ጠይቀዋል::
ከነመሪዎቹ አስመራ ለሚገኘው አርበኞች ግንቦት 7 መርጃ የተደረገው ጨረታ ላይ የግንባሩ ሴት ታጋዮች ምስል ቀርቦ 20 ዶላር ከተሸጠ በኋላ ወደ ጥያቄና መልስ ተገብቷል::
ፖስትሮድ የሚገኙ የኤርፖርት ታክሲ ሾፌሮች 10 ሺህ ዶላር አዋጥተው ሰጥተዋል::
በስፍራው “የፈራ ይመለስ” የሚል ቲሸርትና ህፃናትን ሳይቀር ያሳተፈ የገንዘብ ልገዛ ለግንባሩ ተደርጓል::
ከተሰብሳቢውም በአሁኑ ወቅት የሕወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በሃይማኖቶች ውስጥ ጣልቃ በመግባት በተለይ ተሃድሶ የሚባል ነገር በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ በመፍጠር ሕዝቡን ለማለያየት አውቆ እየሠራ መሆኑን አርበኞች ግንቦት 7 እንዴት እንደሚመለከተው; ሞላ አስገዶም የትህዴን ሠራዊቱን ይዞ ወደ ወያኔ ሲገባ ከግንባሩ በቂ ምላሽ አልተሰጠም የሚል; አቶ ነአምን በቭኦኤ ላይ ቀርበው ስለአሜሪካዊ ዜግነት እንዳላቸው ሲጠየቁ ለምን መመለስ እንዳልፈለጉና ተመሳሳይ ጥያቄዎች ቀርበውላቸዋል::
አቶ ነአምን አሁንም የአሜሪካዊ ዜጋ ስለመሆናቸውና ስላለመሆናቸው መናገር እንደማይፈልጉ ገልጸዋል:: ይልቁንም በቅርብ ጊዜ የሕወሓት አስተዳደር “የአርበኞች ግንቦት 7 አመራሮች የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ስለሆኑ እንከሳቸዋለን” ማለቱን ጠቅሰው “ይምጣና ይሞክረን:: እንደውም ክስ ቢመሰርቱብን ጥሩ ነው:: በክሱ ሂደት ምን ዓይነት ወንጀሎችን እንደሰሩ እናሳያቸዋለን” ብለዋል:: አቶ ነአምን አክለውም የሰሞኑ የወያኔ ድንፋታ የአሜሪካንን ሕግ ካለማወቅ የመጣ መሆኑን አስምረውበታል::
በሞላ አስገዶም ዙሪያ ለሕወሓት መንግስት በቂ የሆነ ምላሽ አልተሰጠበትም ለሚለው ጥያቄም “በቂ ምላሽ ስለሰጠንበት እኮ ነው ዛሬ ይህን ሁሉ አዳራሽ ሙሉ ሰው ያያችሁት” ሲሉ መልሰዋል::
የአርበኞች ግንቦት 7 የገቢ ማሰባሰብ በተለይም የአቶ ነአምን ዘለቀ ንግግርን ማንኛውም ጋዜጠኛ እንዳይቀርጽ መከልከሉ ተሰብሳቢውን አሳዝኗል:: በተለይ አርበኞች ግንቦት 7 ለመናገር ነፃነት እታገላለሁ የሚል ድርጅት በመሆኑ እንዲህ ያለው የጋዜጠኛ ክልከላ ገና ከጅምሩ እንዲህ ከሆነ የወደፊቱ ያሳስበናል የሚሉ አስተያየቶችም ተደምጠዋል:: በአጠቃላይ ግን አርበኞች ግንቦት 7 በሚኒሶታ የተሳካ ገቢ ማሰባሰብ ማድረጉን በሙሉ አፍ መመስከር ይቻላል:
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment