Translate

Thursday, October 22, 2015

“ከቤት ኪራይ ባሻገ…” (ተወልደ “ተቦርነ” በየነ)

ተወልደ (ተቦርነ) በየነ
Teborne Beyene Ethiopian journalistሰሞኑን ጋዜጠኛ አርአያ ተ/ማርያም አንዲት አጭር ማስታወሻ በገጹ ላይ ከትቦ ተመለከትኩ። ጋዜጠኛ አርአያ በዲሲና እና አከባቢዋ በሚገኙ ጉራንጉሮች እየቃረመ የሚያስነብበን የተለያዩ ገጠመኞች ናቸው። እርግጥ አብዛኞቹ በግለሰብ ማንነትና ስብእና ያተኮሩ ቢሆንም በሀገረ አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጲያውያን ሌላኛውን ገጽታ ለማሳየት ይጠቅማሉ ። በተለይ ሀገራችንን በወያኔ ተቀምተን ስደትን እንደአማራጭ የወሰድን ኢትዮጲያውያን “ትልቁን – ስዕል” እንዳንረሳ ከእነዚህ ውድቅዳቂ ገጠመኞች ማወቅ እንደሚጠቅመን አስባለሁ። ጋዜጠኛ አርአያም በአደገኛ ቦታዎች እየተሹለከለከ የሚያቀርበውን “ግለሰባዊ” ታሪኮች ቢገፋበት የሚያስከፋ አይደለም። እርግጥ አብዛኛው ሰው “የመንደር ወሬ” እያለ ቢያጣጥለውም እኔ ግን ከምንም ይሻላል የሚል አስተያየት አለኝ። አንዳንዶች ደግሞ “አርአያ አልቆበታል” ሲሉ ይደመጣሉ። ይህም ቢሆን ምላሹ ያለው ራሱ ጋዜጠኛው ጋር ስለሆነ ገፍቼ ልከራከር አልችልም።
በሌላ በኩል ሀገሩን በጥቂት የወያኔ ጉጅሌውች የተቀማው አብዛኛው ኢትዮጲያዊ ጋዜጠኛው ከቃረማቸው አከባቢዎች ውሎ የሚያድር አለመሆኑን መገንዘብ ያሻል። በሀገራቸው የመስራት እድል የተነፈጋቸው ኢትዮጲያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ኑሮን ለማሸነፍ የሚተጉ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል። በሀገር አሜሪካን የኢትዮጲያውያን አንዱ መታወቂያም የስራ ትጋታቸው እና ፍላጎታቸው መሆኑ ምስክር የሚያሻው አይደለም። በመሆኑም የዋሽንግተን ዲሲ ደቡባዊ ምስራቅ የሚገኙ አደገኛ ቦታዎች የሚውሉና የሚያዘወትሩ ጥቂት ኢትዮጲያውያን በመሆናቸው ብዙሃንን እንደማይወክሉ መገንዘብ ያሻል።

ይህ እውነት እንደተጠበቀ ሆኖ አንዳንዶች በአቋራጭ መንገድ ኑሮአቸውን ለመግፋት የሚፈልጉ ኢትዮጲያውያን አልታጡም። አቋራጭ መንገድ በራሱ መጥፎ አይደለም። ቢሆንም የምቆምበትን “ኢትዮጲያዊ ምሶሶ” በሚንዱ ተግባራት ላይ የሚመሰረት ከሆነ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም።
እንደሚታወቀው አገዛዙ ኢትዮጲያዊነትን ለማጥፋት “ህወሀታዊ ፓሊሲ” ነድፎ ቀን ከሌት እየተጋ ነው። በምንወዳት ሀገራችን ውስጥ ኢትዮጲያዊ ምልክት የሆኑ እሴቶች እየተሸረሸሩ የግለሰቦች መጫወቻና መወደሻ እየሆኑ መሄዳቸው በግልጽ እየታየ ነው። ትላንትና አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ኢትዮጲያዊ በዓል በዓል እንዲሸት የሚያደርጉት እነ ብሔራዊ እና ሀገር ፍቅር ቲአትር ቤቶች እንዲደበዝዙ ተደርገው የበአሉ ድምቀት ወሳኞቹ ግለሰቦችና ሆቴላቸው ሆኗል። ኢትዮጲያዊ አንጋፋ አርቲስቶች ወደጎን ተገፍተው (አሊያም ለባለጊዜው እንዲያድሩ ተደርገው) በደጋፊነት የሚታዩበት በዋናነት ደግሞ ከምዕራቡ አለም በዶላር ተገዝተው የሚመጡ ባህላችንን በቅጡ የማያውቁ የሚጨፍሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጲያዊ ኩራታችን እና ክብራችን ማሳያ የሆኑት ገድሎች እየቀሩ በሌላ ማንነታችን በማይገልጹ ታሪኮች እየተተካ ነው። ዛሬ በኢትዮጲያ ምድር ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ እየተደረገ የሚከበረው የካቲት 11 እንጂ የካቲት 23 አይደለም። ደደቢት አድዋን ተክቶታል። ዛሬ በኢትዮጲያ ምድር ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ እየወጣ እንዲከበር የሚደረገው ሚያዚያ 27 ሳይሆን ህዳር 11 ሆኗል። ድላችንን የወያኔ የበኩር ልጅ የሆነው ብአዴን ተክቶታል። እውነተኛ ታሪክ እየተፋቀ አዲስ ታሪክ እየተዳፈነ ነው። ኢትዮጲያዊነት የሚታይባቸው ተቋማት እየተሸረሸሩ የቡድኖችና የዘመናችን ባለ ገንዘቦች መጨፈሪያ ሆነዋል።
ሆኖም ግን ከአገዛዙ ቁጥጥር ውጪ ባሉ ቦታዎች እንዲህ አይነት ሁኔታ እንዳይፈጠር ኢትዮጲያውያን በእልህና ቁጣ እየተንቀሳቀሱ ነው። ከዚህ አንጻር ኢትዮጲያውያን “በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጲያውያን የባህልና ስፖርት ፌስቲቫል” የሚባለው ቅርስ በጠላቶች እጅ እንዳይወድቅ የሚያደርጉት የሞት ሽረት ትግል በምሳሌ የሚታይ ነው። ይህ የአንድነታችን እና ነጻነታችን አርማ የሆነ ፌስቲቫል በባለገንዘቦች እንዳይከፋፈል ኢትዮጲያውያን ጥረት በሚያደርጉበት ሰዓት ከከፋፋዮች ጋር መሠለፍ ወይም መሳተፍ ከዘመናዊ ባንዳነት የማይተናነስ ሀቅ ነው። “የቤት ክራይ እና የኑሮ ወጪዎች” እንደ አመክንዮ በማቅረብ አሊያም በእነሱ ድግስ ብገኝም “ባለገንዘቡን እና ባለራዕዩን አላወደስኩም” የሚል ወንዝ የማይሻገሩ ምክንያቶች የሚያስኬድ አይደለም። በእንደዚህ አይነት ፀረ- ኢትዮጲያዊ ተግባራት ከጊዜያዊ ድለላዎችና ጥቅማ ጥቅሞች በመነሳት የሚሳተፉ ኢትዮጲያውያን ሊያፍሩ ይገባል። ሊፀፀቱ ይገባል። እውነትም ሊሸማቀቁ ይገባል። እነዚህ ግለሰቦች ማህበረሠቡ ያገለላቸው የነፃነት አርማውን፣ ከትውልድ ትውልድ ሊያስተላልፍ የሚፈልገውን ቅርስ እና የኢትዮጲያዊነት ህልውናውን ሊነጥቁ ቀን ከሌት ከሚተጉ ቡድኖችና ባለ-ገንዘቦች ጋር በመተባበራቸው ምክንያት ብቻና ብቻ ነው።
ጋዜጠኛ አርአያም ትልቁን ስዕል ትቶ ማሞና መታወቂያውን ለማዛመድ የሄደበት አካሄድ ትክክል የማይሆነው በዚህ ምክንያት ነው። እንደ ግለሰብ በሸራተን መዝፈንም ሆነ በባለ ገንዘቦች ክርን ስር መውደቅ የምደግፈው አይደለም። ነገር ግን “ኢ. ኤስ. ኤፍ. ኤን. ኤ.“ እና ሸራተን አንድ አይደሉም።  ለምክንያት እና መንስኤ ማነጻጸሪያ ሊሆኑ አይችሉም። ሸራተን የዘፈነ ሁሉ አልተወገዘም። ይወገዝም አልተባለም።
በተረፈ ጋዜጠኛ አርአያ “ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ነው” እንዲሉ በእኔና በሰይፉ ፋንታሁን መካከል ያለውን ግኑኝነት በድፍረት መግለጽ መሞከሩ ሳያስገርመኝ አልቀረም። ያቀረባቸው መረጃዎች የጋዜጠኛውን የዛሬ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን ትላንትና እና ነገን እንድጠራጠር አድርጎኛል። ፈጣሪ ለአሉባልታ እሩቅ፣ ለመረጃ ቅርብ ያድርገን እንዲሉ!

1 comment:

  1. Goodd day! Do you use Twitter? I'd like to follow you if that would be ok. I'm absolutely enjoying your blog and look forward to new updates. rental mobil bogor

    ReplyDelete