Translate

Monday, October 19, 2015

የኢትዮጵያና የኤርትራ መጻሔ ዕድልና ተስፋ (ኃይለገብርኤል አያሌው)

ከኃይለገብርኤል አያሌው
Ethiopia and Eritrea
የኢትዮጵያና የኤርትራ አንድነት በተካሄደው እልህ አስጨራሽ ጦርነት ከተበጠሰ በሗላ እንደ ሁለት ሃገርና እንደ ሁለት ሕዝብ የመሆን ታሪካዊ ሁኔታ ቢፈጠርም በደም ፤ በባህል ፤ በታሪክና ሃይማኖት በሁልንተናዊ መስተጋብሮች የተቆራኘው የነዚህ ሕዝቦች ሕልውና በጥብቅና በቅርብ ተሳስሮ ያለና ወደፊትም የሚኖር በመሆኑ እንደ ሌሎች ሃገር ሕዝቦች ተለያይቶና ተራርቆ ሊቀር ባለመቻሉ አበው ‘’የሞትንም እኛ የገድልንም እኛ’’ እንዳሉት ከሁለቱም በኩል ባሉ ቀና አሳቢዎች ድልድይነት የሻከረውን ግንኙነት ለማደስ የሚደረገውን ሙከራ በበጎ ጎኑ የማይመለከቱ ሃይሎች ተበራክቶና ተጽኖዐቸው አይሎ በመቆየቱ በአካባቢው ጥቅም ያላቸው ሃይሎች ጣልቃ ገብነት ታክሎበት ፤ ኢትዮጵያን የተቆጣጠርው የሕወሓት ሴራ ተጨምሮበት ፤የአንደነት ሃይሎች ስልት የራቀው ፖለቲካና ግልብ ፕሮፓጋንዳ ተደማምሮ ሁለቱን ህዝቦች ለማቀራረብ በጥቂት ወገኖች የተጀመረው መልካም ጥረት የሚፈለገው ያህል ባይራመድም ይህን ውጥን ጅማሮ በዘላቂነት ማጠናከሩ ለሁለቱም ሃገር ሕዝቦችና ለአካባቢው መረጋጋት ጉልህ ሚና የሚኖረው መሆኑ ሊሰምርበትና የተጀመረውን የማቀራረብና የመወያየት ጅማሮ ሁሉም ድጋፉን ሊቸረው የሚገባ ጉዳይ ነው።

ለረጅም ዘመናት በመከራ የተናጠው የጋራ በረከቱን በህብረት እየተቋደሰ የሰላም የብልጽግናና የፍስሃ ሕይወትን እንዳይኖር የመለያየትን የጦርነትንና የመጠላላትን መርዝ በረጩን ታሪካዊ ጠላቶቻችን ተንኮልና ሴራ ስር ወድቀን ላለፈው ግማሽ ክፍለዘመን እርስ በእርስ ስንባላና ስንጋደል በማያባራ ጦርነት ትውልድ እያለቀ ሃብታችን ለጥፋት እየዋለ ብዙ ዋጋ ስንከፍል ብንቆይም መጨረሻ የደረስንበት ደረጃ የተሻለ ሳይሆን በተቃራኒው ውጤት አልባ በመሆኑ ይህንን አውዳሚ የጥፋት አሚኬላ አስወግዶ የሰላምና የመግባባት አዝመራን ለመዝራት ያለፈውን በቅጡ ገምግሞ የወደፊቱን ለመተለም መዘጋጀትና ሰላማዊ መፍትሄ መሻት አማራጭ የሌለው ምርጫና የወቅቱና የትውልዱ የሕልውና ጥያቄ በመሆኑ ትላንት በተለያየ ጎራ ተሰልፈን የነበርንው ከቅራኔው አዙሪት ወጥተን ችግሮቻችንን ለማረቅ ከቅርብ ግዜ ጀምሮ በኢትዮጵያና በኤርትራ ምሑራን መካከል እየተደረገ ያለው የመቀራረብ በጎ ጅማሮ ይበል የሚያሰኝ በመሆኑ ይህን አይነት ስልጡን እንቅስቃሴ ያቀናጁትና የደከሙት የሰላም ሃዋርያቶች ምስጋና ይገባችዋል፤ በቀጣይም በነካ እጃቸው ፤በጠባብነትና በተስፍንጣሪ የፖለቲካ እይታዎቻቸው በየምሽጋቸው ያደፈጡትን የተለያዩ ሃገራዊ ሃይሎችን ወደ መድረክ አጀንዳቸውን ይዘው ለውይይት ቢጋብዙ መልካም ነው።
ይህ ሰሞኑን በኢትዮጵያና በኤርትራ ምሁራን መካከል እንዲህ ሰፋ ባለ መልኩ የውይይት መድረክ ከመዘጋጀቱ በፊትም ቀደም ሲል ጀምሮ በተናጥልና ተቋማዊም በሆነ
መልኩ በተለያዩ ቦታዎች ጥረት ሲደረግ የቆየ ለመሆኑ አልፎ እልፎ ከመረጃ ምንጮች ሲገለጽ ቆይቷል። ለአብነትም እንደ ፕሮፌሰር ዳንዔል ክንዴ ያሉ ቅን ምሁራን ቀድም ብለው ይንቅሳቀሱ እንደነበር ማስታወሱ ተገቢ ይመስልኛል።
እንዲሁም ከዛሬ ስምንት አመት በፊት የግንቦት 7 አመራር የሆኑት አቶ ነዐምን ዘለቀና አቶ ሙሉነህ እዮዔል እና እኔም የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ በዋሽንግተን ዲሲ ኮንቬንሽን ሴንተር በተዘጋጀው የኤርትራውያን ባህላዊና ብሄራዊ በዐል ላይ ተገኝተን ከብዙ ኤርትራውያን ጋር የመተዋወቅ በግልጽና በጽሞና የመወያየት አጋጣሚ ብዙ ሁኔታዎችን እንድመለከ ስለ ኤርትራውያን ፖለቲካዊና ታሪካዊ ግንዛቤ እንድረዳና የነዚህ ህዝቦች መጻሄ እድልም ታዋቂው ታሪክ ጸሃፊ ክቡር አምባሳደር ዘውዴ እረታ እንዳሉትም አንድ ቀን ወደ አብሮነት እንደሚለውጥ ፍንጭ የሚሰጥና ወንድማማችነታችን በማይበጠስ በጠንካራ ጅማት የተቋጠር መሆኑን የሚያስረዳ አጋጣሚ ሆኖ አግኝቼዋልሁ። ከዚህም በላይ በዚህ አጋጣሚ በእለቱ በአሜሪካ የኤርትራ አምባሳደር የሆኑትን ግለሰብ ጨምሮ ከሌሎች ባለስጣናት ጋር የመተዋወቅና
የመነጋገር እድል ምን ያህል ጠቃሚና አስፈላጊ እንደነበር ለኔ በተለይ የተገለጸልኝ እጅግ ዘግይት ሲሆን ዛሬ ወደ ሗላ ሄጄ ሳስበው ሃገር ወዳድ የሆኑት ወንድሞቼ ታጋይ ነዓምንና ታጋይ ሙሉነህ በቀጣይ ግንቦት 7 ከኤርትራ መንግስት ጋር የተቀዳጀው መልካም ግንኙነትና አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ በእርጋታና በጥንቃቄ የተመራ ከግዜያዊ ስትራቴጂያዊ ጥቅም ባሻገር ዘለቄታዊ አላማ ያለው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን ሲያቀናጁ ለመሆኑ ይህ አጋጣሚ ጥሩ ማሳያ ሆኖ አግኝቼዋልሁ።
አቶ ነዓምን ሙሉነህና የጽሁፉ አቅራቢ ኮንቬንሽን ሴንተር ዲሲ (ፎቶ ረዘነ 2008
expo Eritrea)
የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ጥቅምና ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት ያካሄዱት መጠነ ሰፊና ትውልድ አውዳሚ ጦርነት እንዳይከሰት አስቀድመው የውይይትን በር በመዝጋታቸው ለመሆኑ ያለፈ ታሪካቸውና ያሳለፉት መከራ ምስክር ነው። በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ የሆነው የቀድሞው መንግስት ምክትል ፕሬዜዳንት የነበሩት ኮሎኔል ፍስሃ ደስታ በዘመነ ስልጣናቸው ኤርትራን አስመልክቶ የነበሩትን የሰላምና የውይይት እድሎች በተለይ የሃይል ሚዛኑን በበላይነት ይዞ የነበረው መንግስታቸው ሰላማዊውን መፍትሔ ባለመቀበልና ሃይልን ብቻ እንደ አማራጭ ይዞ መቀጠሉ ለስርዐቱና ለሃገሪቱ ሁለንተናዊ ውድቀት አብይ ምክንያት መሆኑን በግዜ በቦታና በሁኔታ በማስረጃ አስደግፈው እየተነተኑ አጽንዖት በመስጠት በታሪክ ፊት መስክረዋል።
ባለፉት ሁለት አስዕርተ አመታት ኢትዮጵያዊው የአንድነት ሃይል ኤርትራን አስመልክቶ ሲያራምድ የቆየው አስተሳሰብ በአብዛኛው በጀብደኝነትና በአለፈ ታሪክ ላይ የተንጠለጠል ፍጹም ቀኖናዊ በመሆኑ በሁኔታዎች አስገዳጅነት የተፈጠሩትን አጋጣሚዎች ፤ የተለወጠውን የሃይል አሰላለፍና ፤ ነባራዊ ሁኔታ በጥሞና መርምሮ የጠራ አቋም ይዞ እንዳይራመድና በእድሉ ሳይጠቀምበት እንዲቀር ሳንካ ሆኖበት ቆይቷል። በእነዚህ ወርቃማ ግዜያት በአንድነት ሃይሉ ሰፈር ሲስተጋቡ የነበሩት አብዛኞቹ መፈክሮች (የኤርትራን ሕልውና ያለመቀበልና የወድብ ጉዳይ) በተከታታይ በተፈጠረው የአካባቢው ፖለቲካዊ ለውጥ ወቅታዊነታቸው ከሽፎና ተዘንግቶ ዛሬ ጎልቶ የወጣው ሁሉም ሊርቀው ያልቻለው እውነታ ሃገራችንንና ሕዝባችንን የተጋረጠበት የመበታተን አደጋና የጥቂት ዘረኞች አፓርታይዳዊ አገዛዝ ያስከተለው አፈና
የኢትዮጵያንን ሕልውና ዕጅጉን የተፈታተነበት በታሪካችን ታይቶ የማይታወቅ የሕልውና ጠርዝ ላይ በመድረሳችን ፤ ዛሬ ከዚህ ጉድና ጭለማ በማንኛውም መንገድ መላቀቅ የምንችልበትን መንገድ ወደ መመልከትና አማራጮችን መፈተሽ ደረጃ በመድረሳችን ከኤርትራ መንግስትና ሕዝብ ጋር የሚደረገው ግንኙነት ተቀባይነት ያገኘበት ወቅት ላይ ቢደረስም ከኢትዮጵያውያን ሓይሎች ከዚህ በበለጠ መወያየት መተጋገዝ መረዳዳትና አብሮ መስራት ግን ገና ብዙ እንደሚቀር መመልከት ይቻላይ።
ከዚህም በዘለለ በኢትዮጵያውያንና በኤርትራውያን መካከል የሚደረጉትን ግንኙነቶችና ትብብሮች ያለ በቂ ምክንያትና ባለፉ ታሪኮች ላይ ችክ በማለት የተቃውሞ ስሞታዎችና አልፎም ተርፎም ስም ማጥፋቶችን ከሃገር ወዳዱና ከተቃዋሚው ጎራ አልፎ እልፎ ሲዘነዘር የቆየና አሁንም ያልተዘጋ አጀንዳን መልክ ለማስያዝ የሁለቱን ሃገሮችና ሌሎች ታላላቅ ምሁራን ያቅፈ ውይይት ማካሄዱ ብዙ ጥያቄዎችን የሚመልስና ተቃውሞዎችን የሚያከሽፍ በመሆኑ የተጨበጠና አሳማኝና በቂ ምክንያት ያላቸው ወገኖችም በግልጽ ሊከራከሩበትና ሃሳባቸውን ሊያስጨብጡበት የሚያስችል መድረክ ማመቻቸት ያስፈልጋል።
ውይይት የስልጡንነት መገለጫ ነው። ውይይት ቅራኔን ማስወገጃ መፍትሄን የማግኛ ምንጭ ፤ የክፋትና የሗላቀርነት አምካኝ መድሃኒት ነው። ውይይት የሰላም ቋንቋ የበረከት መንገድ ነው ። ውይይት የተጣላ የሚታረቅብት ፥ የራቀው የሚቀርብበት የጠፋው የሚገኝበት የሰላም አውድማ ነው። ውይይት የሃሳብ ጥራት መለኪያ ሚዛን ፤የሃቅ ማንጠሪያ ወንፊት ነው፤ ይህንን የስልጣኔ መንገድና የሰላም ጎዳና በመተው ባለፉት ዘመናትና ዛሬም በእልህና በጉልበት ቅራኔዎቻችንን ለመፍታት የሄድንበት የቁልቁለት ጉዞ የሚሊዮኖችን ሕይወት ቀጥፎ የሚሊዮኖችን አካል አጉዱሎና ሕሊና አቃውሶ ለአዋራጅ ድህነትና ለእሳፋሪ የስደት ሕይወት አድርሶናል። አዋቂ ሳይጠፋ ፤የምሁራን እጥረት ሳይኖር ፤ሳይንሳዊ ባህላዊና መንፈሳዊ የቅራኔ መፍቻ ጥበባት ሳይጎለን የእልህና የጀብደኝነት አጉል መንፈስ ተጭኖብን በጎውን መፍትሄ ሳንጠቀምበት ኖረናል።
እንደ ሃገርና ሕዝብ መቼ ነው ከዚህ ሗላቀር የቅራኔ ቅርቃር የምንወጣው ፤ እንዴትስ ቢሆን ነው እጅ ለእጅ ተያይዘን ከወደቅንበት የምንነሳው መፍትሄው በእጃችን ነው። መወያየት መነጋገር አንዱ የሌላውን መብትና ፍላጎት አክብሮ መገኘት ፤ ባይስማሙ እንኳ መግባባት ለጋራ ሰላማችን የጋራ ጥረት ማድረግ ዘመኑ የዋጀው ጉዳይ ነው። እርግጥ ነው በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን የገጠመን ጋግርታም የሰላም ቋንቋ የማይገባው ጠመንጃ ነካሽ ሕገእራዊት በሆነው ወያኔ እጅ ውስጥ ሃገራችን ከወደቀችበት ግዜ ጀምሮ ለሰላም ለውይይት የተዘረጉትን እጆች እየነከሰ የስላም ተጓዦችንም እግር እየቆረጠ ከማሰቃየቱም በላይ የብዙዎችን ሕይወት ቀምቶ የቀሩትንም ኑሮዋችው ወህኒ ቤት ከሆነ ስንብቷል። ዛሬም የዘንባባ ዝንጣፊ ይዞ እርቅና ሰላምን የሚጠይቅ በጎ አሳቢ ሃገር ወዳድ ከአደባባዩ አልጠፋም፤ ነገር ግን የስልጣን ጥም ፤ የዘረፋ ሱስና የዘርኝነት ልክፍት የተቆራኛችው ጥቂት ድኩማን የወያኔው መሪዎች ዘንድ የሰላምና የውይይት ጥያቄን በበጎ ጎኑ ከመመልከት ይልቅ የተሸናፊዎች አጀንዳ በማድረግ በንቀትና በትብዒት የሚመለከቱ በመሆናቸው በሚወዱት የብረት ቋንቋ ሊያናግሯችው የሚችለው ሃይል ዝግጅቱን አጠናቆ እስኪጋብዛቸው ድረስ ሌሎች ህዝባዊ ሃይሎች ያነገቡትን አላማ እንደያዙ በመለስተኛ ደረጃ እንኳ ቢሆን የተጀምረውን የውውይት ባህል በማዳበር ሃገርን ከብተና ሕዝቡን ከሰቆቃ ለመታደግ የሚያስች አቅም ለማዳበር መነሳት ይኖርባቸዋል። ይህ በኢሳት አሰባሳቢነት የሚካሄደው የውይይት ፕሮግራም ከተንሳ ዘንድ ፤ የዚህ በምሳሌነት የሚጠቀስ የኤርትራና የኢትዮጵያውያን የመነጋገርና የመቀራረብ አጀንዳ በይዘቱም ሆነ በአቀራረቡ እንከን የማይወጣለት ቢሆንም ይህን መሰል መድረክ በማዘጋጀት በኢትዮጵያውያን የፖለቲካ ሃይሎችና በምሁራን መካከል ያለውን ብሄር ተኮር መሻከርና የተደፋፈነ ሁኔታ በመቅረፍ በሕዝባችን መካከል አብሮነቱ እንዲጎለብትና አንድነቱ እንዲጠናከር እጅግ አስፈላጊ ከመሆኑም በላይ የህወሓት አገዛዝ የዘራውን የመጠፋፋት እንክርዳድ ከስሩ ለመንቀልና ሕዝባችንን እውነታውን ለማስገንዘብ ያገባናል የሚሉ የዘውግ ፖለቲካ አቀንቃኞችንና ሌሎች በመስኩ የሰለጠኑና ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ የሚያቀርቡ የውጭና የሃገር ውስጥ ምሁራንን በመጋበዝ ለዘለቄታዊ የሕዝብ ጥቅም ለዜጎች ደህንነትና ለሃገር አንድነት የሚበጀውንን ለማመላከት እንዲቻል ይህ የውይይት አቅራቢ ተቋም ቢያስብበት መልካም ይመስለኛል።
እዚህ ላይ እንደምሳሌ የሚሆን አንድ ሁኔታን ተሞክሮውና ጠቃሚነቱና አስፈላጊነቱ ሳልጠቅሰው አላልፍም። ክ1997 ዓ/ም ምርጫ ማግስት ሕወሓት በገጠመው የፖለቲካ ሽንፈትና ኪሳራ በመደንበር በራሱ አቀናባሪነትና ሴራ ጠንሳሽነት በተቃዋሚዎች ላይ በነዛው የጸረ ትግራይ ቅስቀሳ በውጭም በሃገር ውስጥ ያሉ የብሄሩን ተወላጆች በተወሰነ መልኩ ከጎኑ ለማሰልፍ ከመቻሉም በላይ የህዝባችንን ድል ቀልብሶ ለአያሌዎች ሞት ፤ እስር ፤ ስደትና መፈናቀል ሲዳርግ ፤ የዚህ ሃገር አፍራሽና እርስ በርስ የሚያጫርስ የተንኮል ሁኔታ የተረዱ በስማችን አይነገድ ያሉ የትግራይ ተወላጅ ምሁራን ከተለያዩ ስቴቶች በክቡር ፕሮፌሰር ተኮላ ሃጎስ (የቀድሞው የመለስ ዜናዊ አማካሪ) አስተባባሪነት በመሰባሰብ ከኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ሕብረት አመራር ጋር ተከታታይ ውይይት በማድረግ በብዙ ጉዳዮች ላይ የመከርና እንዴት የትግራይን ሕዝብ ከሕወሃት መነጠል እንደሚቻል ያመላከት ጠቃሚ እቅድና በቀጣይነት መካሄድ ያለብትን ሁኔታ ያመላከት በጎ የውይይት ጅማሮ ብዙ ሳይጓዝ በአቅም ውስኑነትና በሁኔታዎች ፈጥኖ መለዋወጥ የታቀዱት የድርጊት መርሃ ግብሮች ለግዜው ባይሳኩም ፤ ለኔ በግሌ የተረዳሁት ከስሜት ባሻግር መመልከት እንዳለብን ሁሉንም በአንድ ቅርጫት ከቶ ከመፈርጅ መቆጠብ እንደሚገባና በተቃዋሚው በኩል የሚዘጋጁ መድረኮች ምህዳራችውን በማስፋትና ጸጥ ብሎ ሂደቱን የሚከታተልውን የምሁር ሃይል አሳታፊ የሚያድርግ መሆን ቢችል ፈቃድኛና ሰላም ፈላጊ ኢትዮጵያውያንን ወድ ትግሉ ጎራ እንዲቀላቀሉ መንገዱን የሚጠርግ አሰራር ይመስልኛል።
በመጨረሻም በኤርትራና በኢትዮጵያውያንን መካከል እየጎለበተ የመጣው የአብሮነትና የትብብር ሁኔታ ለሕልውናው የሚያሰጋው የሕወሃት ዘረኛ አገዛዝ ይህን የተቀደሰ የሕዝቦች ግንኙነት ለማሰናከል የማይፈነቅልው የተንኮል ድንጋይ አይኖረውም። ይህ ቡድን ለማንም ለምንም የማይጠቅም የውጭ ሃይሎች ተላላኪና ከጸሃይ በታች ከስልጣንና ከጠባብ ቡድናዊ የዘረፋ ፍላጎቱ ውጭ ሃገራዊም ሆነ አህጉራዊ ራዕይ የሌለው ሰይጣናዊ ድርጅት ከአካባቢው አስወግዶ የተሻለ ስርዐት ለማስፈን የሚደርገውን ሁለገብ ትግል በከፍተኛ ደረጃ እየረዳ የሚገኘው ወገናችን የኤርትራ ሕዝብና መንግስት ሊመሰገን ይገባል። ከዚህም ባሻገር የሕወሓት ቡድን መወገድ ለኢትዮጵያውያን የመጥቀሙን ያህል ለኤርትራውያንም ሃገራዊ ሕልውና እና ለሕዝቡ ነጻነት ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። ሕወሓት የኢትዮጵያን ሕዝብ በዘርና በጎሳ ከፋፍሎና የራሱን ፍላጎት ሊያስፈጽሙ ለሆዳቸው ያደሩ ትንንሽ ሰዎችን የየብሄሩ ተወካይ አስመስሎ ሕዝባችንን እንዳወናበደው ሁሉ ይህ ቡድን ጉልበቱ በፈረጠመና ግዜ ካገኘ የኤርትራን መንግስት አስወግዶ የራሱን ቅጥረኞች ከማሰማራት የማይመለስና ይህንንም እኩይ አላማውን ለማሳካት የውጭ ሃይሎች ድጋፍና በተለይ የምዕራብውያንን ይሁንታ እንደማይለየው የዚህንም ጥርጊያ በማመቻቸት የኤርትራን መንግስት ከዓለም እንዲገለልና በማዕቀብ ኢኮኖሚያዊ አቅሙ እንዲዳከም በማድረግ በአዝጋሚ ሁኔታ ስርዓቱን እየገዘገዘ በመሆኑ ይህን አገዛዝ በተባብረ ክንድ ማስወገዱ ለአፍሪካ ቀንድ አጠቃላይ መፍቴሄን የሚያስገኝ በመሆኑ በተለይ የኤርትራ ሕዝብና መንግስት ቀኑ ሳይጨልም ከኢትዮጵያውያን ጋር የተጀመረውን መተጋገዝ በማጠናከር ፈጣንና ጠንካራ ምላሽ መስጠት ይኖርበታ ።
ፍቅር ሰላምና ወንድማማችነት ለኢትዮጵያና ለኤርትራ እንዲሁም
በተራዘመ መከራ ውስጥ ላለው የምስራቅ አፍሪካ ሕዝብ አምላክ ያድለን!!!

No comments:

Post a Comment