ኤፍሬም ማዴቦ ከአርበኞች መንደር
መብራቱን አጥፍቼዉ አልጋዬ ላይ የወጣሁት በግዜ ነዉ። አለወትሮዬ እንቅልፍ የሚባል ነገር በአይኔ አልዞር ብሎኝ ከጨለማዉ ጋር ፊት ለፊት ተፋጥጠናል። የነፋስ ሸዉታ እንኳን የማይሰማበት ደረቅ ሌሊት ነዉ። ጨላማዉ አይን ይበሳል። እቤቱ ዉስጥ ያለዉ ሰዉ ሁሉ ተኝቷል። ቀኑን በሠላም ላዋለኝ አምላክ ምስጋና ሰጥቼ ሌሊቱንም አደራ ብዬዉ ፀሎቴን ጨረስኩ። ያ ምቀኛ እንቅልፍ ግን አሁንም እንደከዳኝ ነዉ። ትንሿ አልጋዬ ላይ ግራ ቀኝ እያልኩ ተገለባበጥኩ። እንቅልፍ ተጎትቶ የሚመጣ ይመስል አሁንም አሁንም ላይ ታች እያልኩ አልጋዉ ላይ እራሴን ጎተትኩት . . . እንኳን እንቅልፍ ሊወስደኝ ጭራሽ አይኖቼ መርገብገባቸዉን ያቆሙ ይመስል ቀጥ ብለዉ ቀሩ። ከተጋደምኩበት ብድግ ብዬ መብራቱን አበራሁና ለመንገድ ከያዝኳቸዉ ሁለት መጻህፍት አንዱን አዉጥቼ ማንበብ ጀመርኩ። እኔ ላንብበዉ ወይ መጽሀፉ ያንብበኝ አላዉቅም። ጧት ስነሳ ግን “The Architecture of Democracy” የሚል መጽሐፍ ደረቴ ላይ ተለጥፎ ነበር።
ሰዐቴን ሳየዉ ከሌሊቱ ስምንት ሰዐት ተኩል ይላል። ከአልጋዬ ላይ ዘልዬ ወረድኩና ሰዉነቴን ታጥቤ ልብሴን ከለበስኩ በኋላ መኪናዉ ዉስጥ ገብቼ “I’m ready” አልኩ። የመኪናችን መብራት ጨለማዉን እየገላለጠዉ የአስመራ ከረንን መንገድ ተያያዝነዉ። መኪናዉ ዉስጥ ከገባሁ በኋላ እንደገና አፌን የከፈትኩት ባሬንቱ ደርሰን ቁርስ ሳዝ ነዉ። ባሬንቱ በግዜ መድረሳችን ደስ ቢለኝም የቀረን መንገድ ርዝመት ታየኝና ቁርስ መብላቴን ትቼ . . . በሰዐት ይህን ያክል ብንጓዝ እያልኩ ዋናዉ ጉዳያችን ቦታ የምንደርስበትን ሰዐት ማስላት ጀመርኩ። የስሌቱ ዉጤት ከሦስት ሰዐት ሲበልጥብኝ ተናደድኩ። ቀሪዉ መንገድ ገና ሳልጀምረዉ ሰለቸኝ። በተፈጥሮዬ መንገድና መኃላ ሲረዝም አልወድም።
ተሰነይ ስንደርስ መኪናዉ ዉስጥ የነበረዉ ሰዉ ሁሉ ቡና ካልጠጣሁ አለ። መኪናችንን አቁመን በቁማችን ቡናችንን ፉት አድርገን መንገዳችንን ተያያዝነዉ። እሁድ ጥቅምት 7 ቀን 2008 ዓም አርበኞች ግንቦት ሰባትን የፈጠሩት ሁለት ድርጅቶች ከተዋሃዱ በኋላ ለሁለተኛ ግዜ የሰለጠኑ ታጋይ አርበኞች የሚመረቁበት ቀን ነበር። ከዚህ ቀደም እንደዚህ አይነቱን የምርቃት ዜና የምሰማዉ በኢሳት ሬዲዮና ቴሌቭዥን ብቻ ስለነበር እቦታዉ ደርሼ የምረቃዉን ስነስርዐት ለማየት የነበረኝ ጉጉት እጅግ በጣም ከፍተኛ ነበር። የምሳ ሰዐት ከመድረሱ በፊት በቀኝ በኩል ዋናዉን መንገድ ለቅቀን ዉስጥ ዉስጡን ወደ ምርቃቱ ቦታ የሚወስደዉን ኮረኮንች መንገድ ተያያዝነዉ።
ግቢዉ ዉስጥ ያለዉ ጥድፊያና ግርግር አንድ ትልቅ ዝግጅት መኖሩን በግልጽ ይናገራል። የተለያየ ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱና መሳሪያ የተሸከሙ አርበኞች ግቢዉን ሞልተዉታል። ያነገቱትን ጠመንጃ ስመለከት ቆራጥነታቸዉ ታየኝ። በቀጭኑ ተጎንጉኖ ማጅራታቸዉ ላይ የወደቀዉን ፀጉራቸዉን ሳይ ቴዎድሮስና ዮሐንስ ትዝ አሉኝ። ፈገግታ በፈገግታ የሆነዉን ፊታቸዉን ስመለከት ደግሞ የእናት አገሬ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ደጃፍ ላይ መሆኑ ታየኝና የኔም ፊት እንደነሱ በፈገግታ ተሞላ። ተራ በተራ እየመጡ “ጋሼ አፍሬም” እንደኳን ደህና መጣህ ብለዉ ሲጠመጠሙብኝ በአንዱ ትከሻዬ ፍቅራቸዉ በሌላዉ ጀግንነታቸዉ ዘልቆ ሰዉነቴ ዉስጥ ገባ። ጥንካሬያቸዉ በጅማቴ ፍቅራቸዉ በደም ስሬ ዘለቀ። እኔነቴ ሲታደስና በአገሬ ላይ ያለኝ ተስፋ ሲለመልም ተሰማኝና ደስ አለኝ። አዎ ደስ አለኝ . . . እየመጣ የሚሄድ ግዜያዊ ደስታ ሳይሆን የዉስጥ አካላቴን የዳሰሰ ዘላቂ የመንፈስ ደስታ ተሰማኝ። በጣም ደስ የሚልና በአሁኖቹ ቋንቋ “የሚመች” ቀን ነበር። የዕለቱን ዝግጅት ለማየት መቸኮሌን ያወቁት እግሮቼ የምረቃዉ በዐል ወደሚከበርበት ዳስ- ፍትህ፤ ነጻነትና እኩልነት የናፈቀዉ ልቤ ደግሞ ወደ ወደፊቷ ኢትዮጵያ ይዘዉኝ ጭልጥ አሉ፡ . . . ለካስ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ሩቅ አይደለችም።
“ማነዉ ሚለየዉ . . .ሚለየዉ፤ ይህም ትዉልድ ፍም እሳት ነዉ” የሚለዉን የጃሉድ ዘፈን በርቀት ሲሰማ በቀኑና በዘፈኑ መግጠም ተገረምኩ። “እዉነትም ይህ ትዉልድ ፍም እሳት ነዉ” እያልኩ በለሆሳስ ለራሴ እየነገርኩት ዳሱ ዉስጥ ገብቼ ቁጭ አልኩ። እርግጠኛ ነኝ ይህንን ጽሁፍ የሚያነብ ሰዉ ዳሱ ዉስጥ የነበረዉን ፍጹም ኢትዮጵያዊ የሆነ የጀግንነት፤ የቆራጥነት፤ የእልህና የመተማመን ልዩ ስሜት መረዳት የሚችለዉ እኔ በዚህ ባልተባ ብዕሬ ስገልጸዉ ሳይሆን እንዳዉ በደፈናዉ ዳሱ እራሱ ኢትዮጵያዊ ነበር ብዬ ባልፈዉ ነዉ።
አገራችን ኢትዮጵያ ከራሱ ምቾትና የተደላደለ ኑሮ ይልቅ የወገኖቹ መብትና ነጻነት የሚያንገበግበዉና እራሱን ለፍትህ፤ ለአንድነትና ለነጻነት ለመሰዋት ዝግጁ የሆነ የየዘመኑ ምርጥ ትዉልድ አላት። ይህንን የኛን ዘመን ምርጥ ትዉልድ ነዉ አርቲስት ጃሉድ “ይህም ትዉልድ ፍም እሳት ነዉ” ብሎ በጣፋጭ ዜማዉ ያወደሰዉ። እኔ ጥርጥርም የለኝ ይህ ትዉልድ አንድና ሁለት ብቻ ሳይሆን ለቁጥር የሚታክቱ ብዙ ፍም እሳቶች አሉት። ችግሩ የእሳት ነገር አዚህ ቤት ነደዳ እዚያም ቤት ነደደ ስራዉ ማቃጠል ነዉና አንዱን እሳት ከሌላዉ እሳት መለየት አስቸጋሪ ነዉ። እኔም ችግሬ እዚህ ላይ ነዉ። ፊት ለፊቴ ላይ ቁጭ ብለዉ ስለማያቸዉ ፍም እሳቶች (ጀግኖች) ላወራችሁ እየፈለኩ ምርጫዉ አዋጅ ሆነብኝ. . . የራሱ ጉዳይ ብዬ አንዱን ጀግና መረጥኩ። ይህንን ዛሬ የምተርክላችሁን ጀግና ስመርጥ ግን እንዳዉ በደፈና አልነበረም። ጉዳይ አለኝ . . . . ጉዳዩ አንዲህ ነዉ።
በዕለቱ በተመራቂ አርበኞች ተዘጋጅተዉ ከቀሩቡት የተለያዩ የኪነት ስራዎች ዉስጥ አንዱ የድራማ ዝግጅት ነበር። ሦስት የተለያዩ ድራማዎች መታየታቸዉ ትዝ ይለኛል። ዳሱ ዉስጥ የተሰበሰበዉን በብዙ መቶዎች የሚቆጠር ሰዉ ስሜት የኮረኮረዉና የእያንዳንዱን ሰዉ የልብ ትርታ ሰቅዞ የያዘዉ ግን በእዉነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተከወነዉ የመጨረሻዉ ድራማ ነበር። ድራማዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ በተለይ ሰሜን ኢትዮጵያ ዉስጥ የአርበኞች ግንቦት 7 አባላት ናችሁ እየተባለ በየቀኑ በህወሃት የደህንነት ሠራተኞች እጃቸዉ እየታሰረ በየወንዙና በየፈፋዉ በግፍ እየተገደሉ ስለሚጣሉ ኢትዮጵያዉያን የሚተርክ ድራማ ነበር።
ድራማዉ “ኮሜዲ” የሚባል ክፍል የለዉም። ተጀምሮ እስኪያልቅ “ትራጄዲ” ብቻ ነዉ። ያሳዝናል፤ ያስቆጣል፤ ያስቆጫል፤ያንገበግባል፤ አንጀት ያቆስላል፤ ልብ ያነድዳል . . . ወይ ነዶ ያሰኛል ። እኔማ እንኳን ትራጄዲ አይቼ በተፈጥሮዬ ሆደ ቡቡ ነኝና በደል ስመለከት ማዘን ልማዴ ሆኖ አምባዬ መፍሰስ የጀመረዉ ገና ድራማዉ ሲጀምር ነበር። በተለይ አናታቸዉ እየተደበደበ የሚቀበሩበትን ጉድጓድ በግድ እንዲቆፍሩ የተደረጉትን ሁለት ወጣት ወገኖቼን ሳይ ሆዴ ባባ፤ አንጀቴም ቆሰለ። ልቤ ዉሰጥ የነደደዉ እሳት ትንታጉ እየተንቦገቦገ ወጥቶ የዉጭ ሰዉነቴን ጭምር ለበለበዉ። ለወትሮዉ ነገር ማመዛዘን የሚቀድመዉ አዕምሮዬ በቀል በቀል አሰኘዉ። የነደደዉ ልቤም ለበቀል አደባ። ጉድጓዱ ተቆፍሮ ካለቀ በኋላ የደህንነት ሠራተኛዉ AK ጠመንጃዉን አንደኛዉ ወጣት አገጭ ላይ ቀስሮ በአፈሙዙ አንገቱን ቀና እንዲያደርግ እያስገደደዉ . . . “አየኸዉ የምትገባበትን ጉድጓድ” እያለ ወጣቱ ወገኔ ላይ ሲሳልቅበት ሰማሁና በሀይወቴ ለመጀመሪያ ግዜ ኢትዮጵያዊነቴን ጠላሁት። አጠገቡ የቆመዉና በቁሙ ሞቱን የሚጠባበቀዉ ሌላዉ ወጣት ወገኔ ደግሞ . . . ግደለኝ . . . ግደለኝ. . . ግደለኝ እንጂ! . . . ምን ትጠብቃለህ እያለ የጓደኛዉን ሞት በአይኑ ከሚያይ የራሱን ሞት የሚለምነዉን ቆራጥ ኢትዮጵያዊ ድምጽ ስሰማ ደግሞ 360 ዲግሪ ተገለበጥኩና ከደቂቃዎች በፊት የጠላሁትን ኢትዮጵያዊነት መልሼ ወድድ አደረኩት። የወያኔዉ ጨካኝ ነብሰ ገዳይ ፉከራና ቆራጡ ኢትዮጵያዊ ያደረጉት የቃላት ምልልስ እምባዬን ጎትቶ አመጣዉና ፊቴ እምባ በእምባ ሆነ። ያ ከግማሽ ሰዐት በፊት ሲጨፈርበትና ሲደነስበት የነበረዉ ዳስ ሰዉ የሌለበት ባዶ ቤት ይመስል ጭጭ አለ። እኔ ኤፍሬም ሰዉ አልገድልም፤ በእኔ እጅ የሰዉ ህይወት ይጠፋል ብዬ አስቤም አልሜም አላዉቅም። ያንን የህወሃት ቅጥረኛ በዚያች ሰዐት ባገኘዉ ኖሮ ግን ለመበቀል ሳይሆን ለሰዉ ልጅ ህይወት ክብር ስል እገድለዉ ነበር።
ድራማዉ እንዳለቀ ወደ ዉጭ ወጣሁና ድቅድቅ ጨለማ ዉስጥ ብቻዬን ቁጭ አልኩ። ሀሳብ. . . የትናንት ሀሳብ፤ የዛሬ ሃሳብ፤ የነገ ሀሳብ፤ የከረመ ሀሳብና ሁሉም ሀሳብ አንድ ላይ ተሰባስበዉ ወረሩኝ። ግራ ሲገባኝና መላቅጡ ሲጠፋኝ ግዜ ትንፋሼን ዋጥ አደረኩና አንቺ እማማ ብዬ አገሬን ተጣራሁ . . . አሁንም አሁንም ደግሜ ተጣራሁ። ህመሟ ብርቱ ነበርና አልሰማችኝም። አይዞሽ ይህ ቀን ያልፍና አንቺም ከህመምሽ እኔም ከማያባራዉ የሀሳብ በሽታ ድነን አዲስ ታሪክ እንጽፋለን ብዬ ከአገሬ ጋር ቃል ኪዳን ገባሁና ከተቀመጥኩበት ተነስቼ ዳሱ ዉስጥ ከነበሩት አርበኞች ጋር ተቀላቀልኩ። እለቱን ሲያስጨፍረን የዋለዉ አደራ ባንድ “ነይ ደኑን ጥሰሺ” የሚለዉን ቆየት ያለ የመሀሙድ አህመድ ዘፈን ሲጫወት ልጅነቴ ትዝ አለኝና ከፍም እሳቶች ጋር መደነስ ጀመርኩ።
ጭልጋን ይዞ፤ጋይንትን ይዞ፤ የጎበዞቹን ጎራ ጃናሞራን ይዞ፤ ደምቢያን ይዞ፤ ወልቃይት ጠገዴን ይዞ፤ ላይ አርማጭሆንና ታች አርማጭሆን ይዞ ወዘተ . . .ድፍን ጎንደር የጀግኖች አገር ነዉ። አዎ! ወልቃይት ጠገዴ ከጀግናም የጀግና አገር ነዉ።ወልቃይት ጠገዴ ጎንደሬ አይደለህም ተብሎ ከተነገረዉ ከሃያ አራት አመታት በኋላ ዛሬም ህልዉናዉን ለወያኔ ፋሺስቶች አላስረክብም ብሎ ጎንደሬነቱን ለማረጋገጥ ሽንጡን ገትሮ የሚዋጋ የጀግኖች አገር ነዉ። ጎንደር የአፄ ቴዎድሮስ፤ የእቴጌ ምንትዋብ፤ የፊትአዉራሪ ገብርዬ፤ የአየለ አባ ጓዴና የጄኔራል ነጋ ተገኝ አገር ናት። ጎንደር ኢትዮጵያ ከሌለች እኛ የለንም ብለዉ ሙሉ ህይወታቸዉን ለትግል የሰጡ እነ ታማኝ በየነንና እነ አርቲስት ሻምበል በላይነህን ያበቀለች አገር ናት። ወላድ በድባብ ትሂድ. . . የጎንደር ማህፀን ዛሬም አልነጠፈም።
ዛሬ ይዤላችሁ የመጣሁት ጀግና ተወልዶ ያደገዉ አማራ ክልል ጭልጋ ወረዳ ልዩ ስሟ ጫኮ በምትባል ቦታ ነዉ። የገበሬ ልጅ ነዉ፤ እሱም ምኞቱ ገበሬ መሆን ነዉ። የሚኖረዉ መተማ ከተማ ዉስጥ ነዉ። ስሙ መሠረት ሙሌ ይባላል። ፈገግታ የማይለየዉ ፊቱ የዋህነቱንና ገራገርነቱን አፍ አዉጥቶ ይናገራል። ሲናገር ረጋ ብሎ ነዉ። አተኩሮ ላየዉ ሰዉ አይነ አፋር ይመስላል፤ የቁርጥ ቀን ሲመጣ ግን እንደ መሠረት ሙሌ ደፋር ሰዉ የለም። አይኑ እፊቱ ላይ ቆሞ ከሚያናግረዉ ሰዉ አይን ጋር ሲጋጭ አንገቱን ይሰብራል። እቺ የሰዉ አይን የመሸሽ በሽታ ደግሞ አበሾች ስንባል የሁላችንም በሽታ ናት። ጠይም ፊቱ ላይ እንደ ችቦ የተተከሉት የመሠረት ሙሌ አይኖች የሰዉን ዉስጥ ዘልቀዉ የሚያዩ ይመስላሉ። ሰዉነቱ ደንዳና ቁመቱ መካከለኛ ነዉ። ልቡ ግን ትልቅ ነዉ። አዎ መሠረት ሙሌ ልቡ ትልቅ ነዉ።
ዕለቱ ሰኞ ነዉ – ሰኞ ሚያዝያ 26 ቀን 2007 ዓም። የህወሃት የደህንነት ሰዎች አንድ ኮሎኔልና ሌሎች አራት ሰዎች ተገድለዋል በሚል ድፍን መተማን እያመሷት ነዉ። እያንዳንዱ የመተማ ነዋሪ በግድያዉ የተሳተፈ ይመስል በአጠገባቸዉ ያለፈዉን ሁሉ ወንድ፤ ሴት፤ ወጣትና ሽማግሌ ሳይለዩ ሁሉንም እያስቆሙ አጥንት ዉስጥ ዘልቆ የሚገባ ስድብ ይሰድባሉ፤ ይደበድባሉ ያስራሉ። በሠላም አዉለኝ ብሎ በጧት የተነሳዉ መሠረት ሙሌ የእህል ወፍጮዉን አስነስቶ የዕለት ስራዉን ለመጀመር ጉድ ጉድ ማለት ጀምሯል። ሴቶች እህላቸዉን ያስመዝናሉ። ሸክም የተራገፈለት አህያ ያናፋል። ነጋዴዉ፤ ደላላዉ፤ ገበሬዉና ሸማቹ ዋጋ ቀንስ ዋጋ ጨምር እያሉ ይንጫጫሉ። መተማ መደበኛ ስራዋ ላይ ናት።
“ቁም . . . እጅ ወደ ላይ . . . እንዳትነቃነቅ” የሚል ድምጽ የደራዉን የመተማ ገበያ በአንድ ግዜ ጭጭ አሰኘዉ። መሳሪያ ያነገቡ ፖሊሶችና ሲቪል የለበሱ የደህንነት ሰራተኞች ከመኪና እየዘለሉ ወርደዉ መሠረትን የፊጥኝ አስረዉ መኪናዉ ላይ ወረወሩት። ምነዉ? ምን አጠፋሁ . . . ዬት ነዉ የምትወስዱኝ? አለ መሠረት በሁኔታዉ እጅግ በጣም ተደናግጦ። አንድ አጠገቡ የነበረዉ የህወሃት ነብሰ ገዳይ . . . ዝም በል ብሎ በጥፊ አጮለዉና ለአርበኞች ግንቦት 7 የመለመልካቸዉን ሰዎች አድራሻና ስም ዝርዝር ካላመጣህ ዕድሜህ ከአንድ ጀምበር አያልፍም አለዉ።
መኪናዉ ዉስጥ ከተቀመጡት ሁለት ሰዎች አንደኛዉ አንሂድ ብሎ በእጁ ምልክት ሲያሳይ መሬት ላይ የነበሩት ፖሊሶች እየዘለሉ መኪናዉ ላይ ወጡና መሠረትንና ሌሎች ሦስት እስረኞችን የያዘችዉ ቶዮታ ሂሉክስ መኪና ፍጥነት እየጨመረች የመተማ ሁመራን መንገድ ተያያዘቸዉ። በሚቀጥለዉ ቀን ጧት ሲነጋጋ ሁመራ ደረሱና አራቱ እስረኞች እጃቸዉ እንደታሰረ ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ ተደረገ። ከምሽቱ ሦስት ሰዐት ሲሆን መሠረትና ጓደኞቹ እጅ ለእጅ እንደተሳሰሩ ጉዞ ወደ ተከዜ ወንዝ ሆነ። የዚህች ከንቱ አለም የመጨረሻ ጉዟቸዉ ነበር።
ዶማና አካፋ ያዙ እንጂ . . . ደግሞም ፈጠን በሉ ግዜ የለንም. . . አለ የነብሰ ገዳዮቹ አለቃ። ከሁመራ ፖሊስ ጣቢያ ወደ ተከዜ ወንዝ የሚያደርገዉ ጉዞ በህይወቱ የመጨረሻዉ ጉዞ እንደሆነ የተረዳዉ መሠረት . . . አንተዬ ልትገድሉን ነዉ እንዴ ብሎ ጠየቀ። ፊት ለፊቱ የነበረዉ ፖሊስ ከተቀመጠበት ዘልሎ ተነሳና . . .ዝም በል . . . አንተ የሴት ልጅ . . . ምን አስቸኮለህ ይልቅ የተጠየከዉን ጥያቄ መልስ አለዉና የያዘዉን የእጅ መከርቸሚያ ካቴና ፊቱ ላይ ወረወረበት። ካቴናዉ ሳይሆን ከዚያ ባለጌ አፍ የወጡት ቃላት ጅማቶቹ ድረስ ዘልቀዉ ገብተዉ መንፈሱን ጎዱትና መሠረት ለመጀመሪያ ግዜ ተስፋ ቆረጦ . . . ምንም የምሰጥህ መልስ የለኝም አለና አንገቱን ደፋ። . . . አንቺ ወላዲት አምላክ ምነዉ . . . ምን አደረኩሽ ብሎ ቀና ሲል እሱንና ሦስት ጓደኞቹን ለመዋጥ አፋቸዉን ከፍተዉ የሚጠባበቁትን አራት ጉድጓዶች ተመለከተ። አይኔ እያየ እዚህ ወስጥ አልገባም ብሎ ንግግሩን ሳይጨርስ ተከታታይ የጥይት ድምጽ ሰማ። ዞር ሲል ፖሊሶች አብረዉት ከታሰሩት ሦስት እስረኞች ዉስጥ አንዱን በእግራቸዉ እየገፉ የተቆፈረዉ ጉድጓድ ዉስጥ ሲጨምሩት አየ። ደቂቃዎች የቀሩት የሱ የራሱ ህይወት ሳይሆን በህወሃት ነብሰ ገዳዮች በግፍ የተገደለዉ የጓደኛዉ ህይወት አንገበገበዉ። አዘነ – በአይኑም በሆደም አነባ። “አይኔ እያየ እዚህ ወስጥ አልገባም” ብሎ የተናገረዉ የራሱ ድምጽ ጆሮዉ ላይ አቃጨለበት። መሠረት ሞት ፈርቶ አያዉቅም፤ ግን ህይወቱ የህይወትን ክቡርነት በማይረዱ ባለጌዎች እጅ እንድታልፍ አልፈለገም። ያ የንጹሃን ኢትዮጵያዉያንን ሰዉነት ማፍረስ የለመደዉ የህወሃት ጠመንጃ ወደሱ ከመዞሩ በፊት አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ ብሎ ወሰነ። እጁ ከጓደኛዉ ጋር የታሰረበትን ገመድ በጥርሱ በጣጠሰዉና ከቀለሁ እንደተላቀቀ ጥይት ተወርዉሮ እግሬ አዉጭኝ ብሎ ጫካ ዉስጥ ዘልሎ ገባ። የህወሃት ነብሰ ገዳዮች የጥይት ናዳ ለቀቁበት፤ እሱ ግን ጫካ ጫካዉን ይዞ ወደማያዉቀዉ ቦታ ሩጫዉን ተያያዘዉ።
መሠረት- ቆራጥነቱና የልቡ ትልቅነት ጉልበት እየሆኑት ነዉ እንጂ ያ የሚጠላዉ የህወሃት ጥይት አካሉን በሳስቶ ወንፊት አድርጎታል። ሰዉነቱ ቁስል በቁስል ሆኗል። ከራሱ ሰዉነት እንደ ጎርፍ የሚፈስሰዉ ደም ጠልፎ የሚጥለዉ እስኪመስለዉ ድረስ አካሉ ደምቷል። ሩጫዉን ግን አላቆመም። ደም እንዳይፈሰዉ ጥይት የበሳዉን ቦታ ሁሉ በሁለት እጆቹ ሸፈነ። እንደኛዉ ቁስል ጋብ ሲልለት እጁን ከሱ ላይ እያነሳ ሌላዉን ቁስል ሸፈነ። ደሙ መፍሰሱን ግን አላቆመም። መሠረትም ሩጫዉን አላቆመም። መሠረት ሙሌ ህይወቱን ለማዳን ወደ ፊት የህወሃት ነብሰ ገዳዮች ደግሞ ወንጀላቸዉን ለመደበቅ ወደኋላ በተለያየ አቅጣጫ ሩጫቸዉን ተያያዙት። ሁለቱም አግሬ አዉጭኝ አሉ።
መሠረት ሞትን እየሸሸ መሆኑን ነዉ እንጂ ከሞት ለመራቁ ምንም ዋስትና አልነበረዉም። ደግሞም መሮጡን ብቻ ነዉ እንጂ ወዴት እንደሚሮጥ አያዉቅም ነበር። ከኋላዉ የሚከተለዉ ማንም ሰዉ እንደሌለ ቢረዳም ከፊት ለፊቱ ህይወቱን የሚታደግለት ሰዉ እስኪያገኝ ድረስ ሩጫዉን ቀጠለ። ጧት ጎህ ከመቅደዱ በፊት “ጠጠዉ በል” የሚል ድምጽ ሲሰማ ያ ሁሉ ሩጫዉ መልሶ ሞት ዉስጥ የከተተዉ መሰለዉና ደነገጠ። ሩጫዉን እንዳይቀጥል ቁም ያሉት ሰዎች ከበዉታል። እሺ ብሎ እንዳይቆም ሞትን አልቀበልም ያለዉ ልቡ አሁንም እንደደነደነ ነዉ። ትንፋሹን ሰበሰበና. . . ማናችሁ እናንተ ብሎ ያቆሙትን ሰዎች ጥያቄ ጠይቆ መልሱን ሳይሰማ ተዝልፍለፎ መሬቱ ላይ በግንባሩ ተደፋ።
የኤርትራ ድንበር ጠባቂ ወታደሮች መሠረትን አንድ ወር ሙሉ በህክምና ሲንከባከቡት ቆዩና እሱ እራሱ በጠየቃቸዉ መሠረት ሃሬና ወስደዉ ለአርበኞች ግንቦት 7 አስረከቡት። መሠረት ሙሌ ጥቅምት 7 ቀን ከተመረቁት አርበኞች ዉስጥ አንዱ ነዉ። ለዚህ ጀግና ያቀረብኩለት የመጨረሻ ጥያቄ . . . ሊገድሉህ የነበሩትን የህወሃት ሰዎች አሁን ብታገኛቸዉ ምን ታደርጋቸዋለህ የሚል ጥያቄ ነበር። ነጻ አወጣቸዋለኋ! አለኝና ጭፈራዉ ዉስጥ ዘልሎ ገባ። አርግጠኛ ነኝ መሠረት ሙሌ አንድ ቀን ሁላችንንም ሸገር ላይ ያስጨፍረናል። ቸር ይግጠመን።
ኤፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር
ebini23@yahoo.com
ebini23@yahoo.com
No comments:
Post a Comment