Translate

Tuesday, October 27, 2015

የተቦርነ የፈራረሱ ቅኝቶች (ከአርአያ ተስፋማርያም)

ከአርአያ ተስፋማርያም
ወዳጄ ተቦርነ በተመለከተ ግልፅ ያልሆኑልኝ ነገሮችን አንስቼ በጥያቄ መልክ አቅርቤ ነበር። አንተም ለኔ ጥያቄ የሚሆን የመልስ ፅሑፍ ለጥፈህ አነበብኩት። የመለስክልኝ መልስ በጣም አስገርሞኛል፣ ግራም አጋብቶኛል። ያንተኑ ተረት በመዋስ “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” ብየዋለሁ። ምክንያቱም ጥያቄዬን መመለስ ስላልቻልክ ወይም ስላልፈለክ እኔን በመሳደብ ጥያቄውን ለማድበስበስ ስትሞክር ነበር። ሃሳብን በሃሳብ መርታት ሲቃትህ ሃሳቡን ያቀረበውን ግለሰብ የማጥቃት የተባለ የክርክር ግድፈት ወይም ሎጂካል ፋለሲ ነው። ምን አልባት ጥያቄዬን ካልተረዳኸው ደጋሜ ላንሳው።
ዘረኛ፣ ኣምባገነንና ሙሰኛ የሆነው የኢህአዴግ መንግስት ህዝባችንን ከፍላጐቱ ውጭ በሀይል፣ በማስፈራራትና በዘር በመከፋፈል እየገዛ 24 አመታት አለፈ። ይህ መንግስት የስልጣን ዘመኑ እንዲቀጥል ህዝቡን በዘር መከፋፈል፣ በሀይል ማፈንና አዲሱ ትውልድ በተለያዩ የማይረቡ ጉዳዮች ማደንዘዝ ዋና አላማዬ ነው ብሎ እየሰራ ይገኛል። ለብዙ ኢትዮጵያዊያን ሞት፣ እስራት፣ ግርፋት፣ ድህነትና ስደት ተጠያቂ ከሆነው ከዚህ መንግስት ጋር የጥቅም ተካፋይ ሆነው ስልጣኑ እንዲረዝም በገንዘባቸውና በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከሚረዱት ሰዎች አንዱ ሼኽ አልሙዲ ናቸው። ሼኹ በኢትዮጵያ ፖለቲካ በፈፀሙት ደባ፣ የሀገሪቱን ሃብት በመበዝበዝ የሃገራችንን ባህልና ወግ የሚያናጋ የማህበራዊ ቀውስ በህብርተሰቡ ውስጥ በማምጣት የሚጠየቁ ሰው ናቸው።
ከላይ እንደጠቀስኩት የዚህ መንግስት ዋና አላማው ህዝቡን ከፋፍለህ መግዛት ብቻ ሳይሆን ትውልዱን ስለሃገሩ ታሪክ፣ ስለማንነቱ፣ ስለሰብዓዊና ዴሞክራሲ መብቶቹ እንዳያውቃና እንዳይጠይቅ ማደንዘዝ ነው። ለዚህ አላማ መሳካት የፖለቲካ፣ የታሪክ፣ የፍትህ፣ ፍልስፍናና የማንነት ጥያቄ የማያነሱትን እንዲሁም ህዝብ እንዲነቃ የሚያደርጉትን የመገናኛ ብዙሃን እየዘጋ፣ ሽብርተኛ እያለ ጋዜጠኞችንም እያሰረ፣ እያሸማቀቀ፣ ከሀገር ያሰድዳል። በተቃራኒው ደግሞ ህዝቡ ከሀገሩ ጉዳይ ጋር እንዲፋታ የፖለቲካም ሆነ የመብት ጥያቄ ሲያነሳ የተባለውን አድራጊ፣ የተጠየቀውን ፈፃሚ ይሆን ዘንድ እንደ ሰይፉ ፋንታሁን አይነት ትውልዱን የሚያደነዝዙ ዝግጅቶችንና መገናኛ ብዙሃንን “የመዝናኛ ፕሮግራም” በሚል ስም ይለፈልፋል።
አነተ ገለልተኛ እያልክ የምታወድሰው ጓደኛህ ሰይፉ ፋንታሁን ይህንን የኢህአዴግን አላማ ግንባር ቀደም አስፈፃሚ ከመሆኑ በተጨማሪ አሁን በስልጣን ላይ ያለውን አምባገነን መንግስት የሚደግፍ ካድሬ መሆኑን አገር ያውቃል። ከዚህ በተጨማሪ ሰይፉ የኢሃዴግ መንግስትን እድሜ ለማርዘም ሌት ተቀን የሚለፉትና የአገርን ሃብት ያለአግባብ የሚዘርፉት የሼኹ ሎሌ ነው። በቅርቡ በሸራተን ሆቴል ሲያገባ የሰርጉን ወጪ ሙሉ በሙሉ በሼኹ የተሸፈነለትም በዚሁ የኢህአዴግ ካድሬነቱና ታማኝነቱ የውለታ ምላሽ ነው። ከሼኹና ከገዢው ፓርቲ ጋር አልተባበርም ያሉና ከተፅዕኖ ውጭ የሆኑ አርቲስቶች ፈተና ሲገጥማቸው አይተናል። ህዝብ የጀግንነት ክብር ከሰጣቸው ታማኝ በየነና ቴዲ አፍሮ ይጠቀሳሉ።
ኢ.ሴ.ኤፍ.ኤን ከኢህአዴግና ከሼኽ አልሙዲ ተፅዕኖ ራሱን አላቆ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመስራቱ ምን ያክል የህዝብ ድጋፍ እንደነበረውና ውጤታማ እንደነበረ አይተናል። እኔ ለአንተ የማቀርበው ጥያቄ የሚነሳው እዚህ ላይ ነው። እዚህ አሜሪካ አላሙዲ ከፈጠሩት የስፖርት ፌዴሬሽን ጋር የተባበሩትን አርቲስቶች እያወገዝክና ሌላ ስራ እንዳይሰሩ እያሳደምክ፣ በአንፃሩ ቀንደኛ የገዥው ፓርቲ ካድሬና የሼኹ ወዳጅ በመሆን ከኢትዮጵያ ህዝብ ከተዘርፈው ገንዘብ ተካፋይ የሆነው ሰይፉ ፋንታሁንን የአንተ ጋዷኛ በመሆኑ ብቻ አላሙዲ በሸራተን ደግሰው ሲድሩት ለምን ለማውገዝ ተሳነህ?..ማውገዝ እንኳ ቢቀር የሼኹ ሎሌ የሆነው ሰይፉን በምን መለኪያ ገለልተኛና በእመነቱ የሚፀና ለማለት ደፈርክ?.. ወይም ገለልተኛነትና በእምነት መፅናት ምን እንደሆኑ አታውቅም! አለበለዚያ ለአንተ ገለልተኛነትና በእምነት መፅናት ማለት ከአንተ ጋር የሚመሰረት ጓደኝነት ነው ማለት ነው። ሌላው ጥያቄ እዚህ አሜሪካ አገር ከአልሙዲ ጋር የተባበሩትን አርቲስቶች ከተቃወምክ አዲስ አበባ ላይ ከዚያው ግለሰብ (ሼኹ) ጋር የሚተባበሩትንና የቅርብ ወዳጅ የሆኑትን ሰዎች ማንቆለጳጰስ እንዴት ትችላለህ?..በተጨማሪ በአላሙዲ የሚረዳውን ፌዴሬሽንና ሸራተን ለየብቻ እንደሆኑ አድርገህ ለመግለፅ ሞክረሃል። እጅግ አስቂኝ ነው።ሁለቱም በሼኹ የሚዘወሩ ናቸው!
ከአምባገነኑ መንግስት ኢህአዴግና መንግስትን ከሚደግፉት እነሼኽ አላሙዲ ጋር መተባበር አይገባም ካልክ አቋምህ ወጥ ሊሆን ይገባል። አዲስ አበባም ሆነ አሜሪካ፣ ሰርግም ሆነ ስፖርት ጓደኝነት ኖረም አልኖረ፣ የግል ጥቅም ተገኘም አልተገኘ፣ አቋምህ ወጥ መሆን ይገባዋል። ስትቃወም፣ ስትደግፍ፣ ወጥ የሆነ አቋም ይኑርህ!
በእነኚህ ጉዳዮች ላይ የምታንፅባርቀው ወጥ ያለሆነ አቋም ሳስብ አንድ ጥንታዊ የቻይና ተረትን አስታወሰኝ። ሰውዬው በመንደሩ ውስጥ ሱቅ ከፍቶ ጦርና ጋሻ አንድ ላይ ይሸጣል። የሚገርመው ግን ጦሩን ሲያሻሽጥ “ሁሉንም ነገር ይበሳል” እያለ ሲሆን ጋሻውንም ሲያሻሽጥ “ምንም ነገር አይበሳውም” እያለ ነበር። አንተም፣ ያንተም ጓደኛም ሰይፉ ፋንታሁን ከአልሙዲ ተሻርኰ እየሰራና ሸራተን ሰርግ ሲደገስለት እያየህ ገለልተኛና በእመነቱ የሚፀና ብለህ ታወድሰዋለህ! አሜሪካ አገር ያሉ አርቲስቶች ከአልሙዲንና አላሙዲ ከፈጠሩት ፌዴሬሽን ዝግጅት ላይ ሲዘፍኑ ደግሞ “ባንዳና ከሃዲ” ብለህ ታወግዛለህ፤ እንዴት ነው ነገሩ?..የባንዳነትና የኢትዮጵያዊነት መለኪያው የአንተ ፍቃድና ጓደኝነት ሆነ እንዴ?..ለነገሩ የአንተን የአቋም መዘባረቅ በተመለከተ ግራ የሚያጋቡኝን አንድ ሁለት ነገሮች ልጠቃቅስልህና ወደ ዋናው ሃሳቤ ልመለስ። ድምፃዊ ቴዴ አፍሮ ከአልሙዲ ጋር ላለመስራት ወስኖ የኢትዮጵያ ህዝብ ጀግና እያለ ሲወድሰው ኢህአዴግ ደግሞ እንደጠላት ሲያዋክበው በነበረት ጊዜ አንተም ከሰይፉ ጋር ሆነህ ቴዲ አፍሮን በማዋከቡና የድምፃዊውን መልካም ስም በማጠልሸት ዘመቻ ላይ ከሰይፉ ጋር ተሳታፊ ነበርክ። ሁለተኛ የሰይፉን በመዝናኛ ስም ህዝብ የማደንዘዝ ተግባር ላይ አካልና አጋር ነበርክ። አንተ የእኔን የትላንት፣ የዛሬና የነገ አቋም ለመጠየቅ አንዳችም ማስረጃ ባይኖርህም እኔ ግን እነዚህንና ሌሎች ለጊዜው የማልገልፃቸውን ስህተቶችህን እያወቅኩ ኢትዮጵያዊነትህን አልተጠራጠርኩም።
ስለጋዜጠኝነቴ ደረጃ ለመስጠት መሞከርህ አስቆኛል። ስለፖለቲካ፣ ማህበራዊና ሌሎች ጉዳዮች ለመፃፍ ስፈልግ – የምፅፈውን ነገር አንተ ልትመርጥልኝና ልትወስንልኝ አትችልም! ለነገሩ በሁሉም ነገር ደረጃ የመስጠትና ታፔላ የመለጠፍ ችግር ስለራስህ ካለህ የተዛባና የተጋነነ ግምት የመጣ ነው። በምን የጋዜጠኝነት እውቀትህ፤ ልምድህና ብቃትህ ለእኔ የጋዜጠኝነት ደረጃ ልትሰጥ እንደፈለግክ አልገባኝም። ለመሆኑ ኢትዮጵያ በነበርንበት ጊዜ ለእውነት ቆመን መንግስትን ስናጋልጥና ፊት ለፊት ስንጋፈጥ፣ የአገዛዙን ደባ ስናጋልጥ አንተ የት ነበርክ? ..አንተ የት እንደነበርክ ትዝ ካላለህ እኔ ላስታውስህ፤ በወቅቱ አንተ የመንግስትን ትውልድ የማደንዘዝ አላማ ከሚያስፈፅመው ከሰይፉ ጋር ተሰልፈህ ህዝብን ግራ በማጋባት ትሰራ ነበር። በወቅቱ ድምፃዊ ቴዴ አፍሮ ከመንግስትና ከነአላሙዲ ጋር አልተባበርም፣ ሃገሬ ትበልጣለች ብሎ ራሱን ሲያገል፣ አንተ ከሰይፉ ጐን ቆመህ የድምፃዊውን መልካም ስም በራዲዬ ታጠፋ ነበር። ለመሆኑ አንተ ጋዜጠኛ ሆነህ በፍትህና በዲሞክራሲ ድምፅህን አሰምተህ ወይም ፅሁፍ ፅፈህ የምታወቅው መቼ ነው?..እኛ በጋዜጠኝነት ስንታሰር፣ ስንደበደብና ዋጋ ስንክፈል አንተ ግን በዛኛው ወገን ቆመህ ትውልዱን ታደነዝዝ ነበር። ሆኖም ሰው ሊለወጥ ይችላል። እዚህ መጥተህ «አርበኛ ነኝ» ስትለን በበጐ ስሜት ተቀበልነሃል። በመጨረሻ ሁሌ በአዕምሮህ ልታኖረው የሚገባውን አንድ እውነት ልነገርህ። አገራችን የብዙ ሚሊየኖች አገር ናት። ትግሉም ህዝባዊና ሁሉን አሳታፊ ነው! በመሆኑም አንተ በማንኛውም መለኪያ የጋዜጠኝነት ደረጃ አውጪ፣ የፖለቲካ አቋሞች አጣሪና የኢትዮጵያዊነት ፈቃድ ሰጪ ልትሆን አትችልም!

No comments:

Post a Comment