- ኤርትራ የጦር መሣሪያ ድጋፏን ቀጥላለች
- የኬንያ፣ የታንዛኒያና የብሩንዲ አክራሪዎችም ከአልሸባብ ጐን ቆመዋል
- ቻይናን ያቋረጡ ፈንጂዎች አልሸባብ እጅ ደርሰዋል
- የኬንያ፣ የታንዛኒያና የብሩንዲ አክራሪዎችም ከአልሸባብ ጐን ቆመዋል
- ቻይናን ያቋረጡ ፈንጂዎች አልሸባብ እጅ ደርሰዋል
ከ16 ዓመታት በላይ መንግሥት አልባ ሆና የቆየችው ሶማሊያ በእርስ በእርስ ግጭትና በጐሣ መሪዎች የበላይነት ሽኩቻ ምክንያት ዜጐቿ በሰላም እጦት ከመሳቀቃቸው ባለፈ፣ የአሸባሪዎች ምቹ መጠለያና መደራጃ በመሆን በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የደኅንነት ሥጋትን ፈጥራለች፡፡
ይህንን ሁኔታ ለመቀየር እ.ኤ.አ. ከ2006 ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግሥት ያደረገው ጥረት አንፃራዊ ሰላምን በሶማሊያ ማስፈን ያስቻለ፣ እንዲሁም ከ16 ዓመታት በኋላ ማዕከላዊ መንግሥት እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ በጐረቤቷ ሶማሊያ ያከናወነችው ጣልቃ ገብነት የራሷን ደኅንነት በዋነኝነት ለማረጋገጥ ያለመ ቢሆንም፣ በርካታ ትችቶችን በወቅቱ አስከትሏል፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ያደረገው ጣልቃ ገብነት በወቅቱ በኢትዮጵያ ላይ ተጋርጦ የነበረውን የደኅንነት አደጋ በማራቅ ረገድ ካስገኘው ውጤት በተጨማሪ፣ የምዕራባዊያኑን ትኩረት የሳበ ሁኔታንም መፍጠሩ ይታወሳል፡፡ ይህም በርካታ የሌሎች አገሮች አክራሪዎች ከሶማሊያ አክራሪ ኃይሎች ጋር ወግነው ከኢትዮጵያ ሠራዊት ጋር መዋጋታቸው ሲሆን፣ በስተመጨረሻም በዓለም አቀፍ አሸባሪነት የተፈረጀው የአልቃይዳ ክንፍ በሶማሊያ መገኘቱ ዋናው የምዕራባዊያኑ ትኩረት ነው፡፡
ይህ የምዕራባዊያኑ ትኩረት በሶማሊያ ሰላምን የመፍጠርና በዚች አገር የሚገኙ አሸባሪ ኃይሎችን በዋነኝነትም አልሸባብን የማክሰም የጋራ አጀንዳ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል፡፡ ከኃያላን አገሮቹ በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአፍሪካ ኅብረት በዚህ የጋራ አጀንዳ ዙሪያ የድርሻቸውን መወጣት ከጀመሩ ጥቂት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በብቸኝነት የተጋፈጠችው የሶማሊያ የደኅንነት ጉዳይ ካጋለጣቸው ጉዳዮች አንዱ፣ የተለያዩ አገሮች አክራሪ ቡድኖች ከሶማሊያ ትርምስ ጀርባ መሰለፋቸው ነው፡፡ እንዲሁም ኤርትራ በመንግሥት ደረጃ በሶማሊያ ጉዳይ የፖለቲካ አቋም በመያዝ ከፍተኛ የጦር መሣሪያ በሶማሊያ ለሚገኙ አክራሪ ቡድኖች ማቅረቧ ነው፡፡
ይህንን የኢትዮጵያ ግኝት ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ያቋቋመው አጣሪ ቡድን በተጨባጭ ማስረጃዎች የኤርትራ መንግሥት የሶማሊያ አክራሪዎችን በጦር መሣሪያ ሲደግፍ እንደነበር አረጋግጧል፡፡ በዚህ የአጣሪ ቡድኑ ሪፖርት መሠረትም ተመድ በኤርትራ መንግሥት ላይ የተለያዩ ማዕቀቦችን ከዓመታት በፊት የጣለ ሲሆን የጦር መሣሪያ ማዕቀብ አንዱ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ማዕቀቡ የኤርትራ መንግሥትን የጦር መሣሪያ ከማግኘት ሊያስተጓጉለው ካለመቻሉም ባሻገር፣ በሶማሊያ ለሚገኙ አሸባሪ ኃይሎች የመሣሪያ አቅርቦትና ድጋፍም ከማድረግም ሊገታው አልቻለም፡፡ በሶማሊያ ጉዳይ የተነደፈውን ሰላም የማስከበርና አሸባሪዎችን የማክሰም ተልዕኮ የደረሰበትን ደረጃ በመገምገም ሰሞኑን ሪፖርቱን ያቀረበው የተመድ አጣሪ ቡድንም ይህንንና ሌሎች አሳሳቢ እውነታዎችን በዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡
ይህ ሪፖርት የኤርትራ መንግሥት የጦር መሣሪያ ድጋፍ አለመቋረጡን በመረጃ ከማረጋገጡም በተጨማሪ፣ የሶማሊያ ቀውስ የሚጐዳቸው የምሥራቅ አፍሪካና የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አገሮች አክራሪ ቡድኖች ከሶማሊያ አልሸባብ ጋር ጥብቅ የሆነ ግንኙነት እንዳላቸውና ድጋፍም እንደሚሰጡ ተንትኖ አቅርቧል፡፡
‹‹አጣሪ ቡድኑ ባገኘው መረጃ መሠረት የኤርትራ መንግሥት ለሶማሊያ ሰላምና ደኅንነት ማጣት ቁልፍ ሚና ካላቸው ግለሰቦች ጋር ጥብቅ ግንኙነትና ሙሉ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን አረጋግጧል፤›› ሲል የአጣሪ ቡድኑ ለተመድ የሰላምና ደኅንነት ምክር ቤት ሪፖርት አድርጓል፡፡
ባለፈው ሳምንት ይፋ የሆነው ይኼው ሪፖርት በሶማሊያ ለሚታየው አለመረጋጋት ቁልፍ ድርሻ ያላቸው ግለሰቦች ከኤርትራ መንግሥት ጋር የፈጠሩት ግንኙነት የጦር መሣሪያና የገንዘብ ድጋፍ በማግኘት ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን፣ የኤርትራ መንግሥት ፍላጐትን በሶማሊያ የሚያስፈጽሙ መሆናቸውንም አረጋግጧል፡፡
‹‹የኤርትራ መንግሥት እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ የሚጠብቀው የመጨረሻ ውጤት የሶማሊያ መንግሥት የፖለቲካ ውሳኔና አስተዳደርን ማምከን፣ በሶማሊያ ሕዝብና መንግሥት መካከል ትስስር እንዳይፈጠር እንዲሁም የሶማሊያ መንግሥት ውስጣዊና ውጫዊ ግንኙነትን ማጨናገፍ ነው፤›› ሲል አብራርቷል፡፡
አል ሂጅራ ወይም በቀድሞ ስሙ የሙስሊም ወጣቶች ማዕከል (ሙስሊም ዩዝ ሴንተር) በመባል የሚታወቀው በኬንያ የሚገኝ አክራሪ ቡድን ጥብቅ የሆነ ግንኙነት ከአልሸባብ ጋር መመሥረቱንም ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
የኬንያ የፀረ ሽብር ተቋም በዚህ አል ሂጅራ ቡድን ላይ ባደረገው ዘመቻ የቡድኑ ጥንካሬ ደክሟል ቢባልም፣ የአጣሪ ቡድኑ ያገኛቸው መረጃዎች አል ሂጅራ አሁንም ጠንካራ እንደሆነና የአልሸባብ የውጭ ግንኙነት ክንፍ መሆኑን በመረጃዎች አረጋግጧል፡፡
ለአብነት ያህል አል ሂጅራ የኬንያ ሶማሌ ያልሆኑ ኬንያውያንን በመመልመል ወደ አልሸባብ በመላክ ላይ እንደሚገኝ፣ አዲስ በቀየሰው የአልሸባብን ውጥን የማሳካት እንቅስቃሴም በታንዛኒያ ከሚገኘው አንሳር የሙስሉም ወጣቶች ማዕከል የተባለ ድርጅት ጋር ጥብቅ ትስስርን መመሥረቱን፣ በተጨማሪም የሎጂስቲክስ መረቡን ለማስፋት ከሩዋንዳና ከብሩንዲ የአልሸባብ ደጋፊዎች ጋር ግንኙነት በመመሥረት ላይ እንደሚገኝ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
‹‹ምናልባትም የኬንያ የደኅንነት አገልግሎት ውጤት አልባ የሆነ የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ምክንያት አል ሂጅራ በሶማሊያ ሰላም የማስፈን የጋራ ጥረት ላይ አደጋ እየሆነ ነው፡፡ አል ሂጅራ ከታንዛኒያው አንሳር የሙስሊም ወጣቶች ማዕከል ጋር በጋራ የጀመረው ዘመቻ ከምሥራቅ አፍሪካ የአልቃይዳ ቁልፍ መሪዎች ከሆኑት አቡበከር ሸሪፍ አህመድ (ማካቡሪ) እና የእንግሊዝ ዜግነት ካለው ጀርሚን ጆን ግራንት ጋር የጠበቀ ግንኙነት መሥርተዋል፤›› ሲል ሪፖርቱ ይገልጻል፡፡ አል ሂጅራ የጀመረው አዲስ እንቅስቃሴ ለአልሸባብ የገንዘብና የጦር መሣሪያ ምንጭ በመሆን ላይ እንደሚገኝ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
ከምሥራቅ አፍሪካ የአልቃይዳ ክንፍ ከሚያገኘው የገንዘብና የጦር መሣሪያ ድጋፍ በተጨማሪ የኬንያ ሙስሊሞችም የሚያደርጉት የገንዘብ መዋጮ ለአልሸባብ እየደረሰ መሆኑን ይገልጻል፡፡
ከዚህ ባለፈም አል ሂጅራ ከአፍሪካ ውጭ ከሚገኙ አሸባሪ ቡድኖች ጋር ግንኙነት እንዳለው በመረጃ ማረጋገጡን አጣሪ ቡድኑ ይገልጻል፡፡
ፑኖ ዋኒ ረያድ ሞስክ ኮሚቴ የተባለ በኬንያ የሚገኝ ሌላ ተቋም በእጅ አዙር የአል ሂጅራ ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ መሆኑን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ የዚህ ተቋም አንድ ሠራተኛ በዲኤችኤል የተላከለትን መልዕክት ሲቀበል እጅ ከፍንጅ መያዙን ያትታል፡፡
በኬንያ የዲኤችኤል ቢሮ በኩል የተላከው ጥቅል ፖስታ ከቻይና የተነሳ መሆኑን በውስጡም የተገጣጠሙ ፈንጂዎች መገኘታቸውን ያስረዳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የአልሸባብ የውጭ መረብ የተዘረጋው በሁለት የሶማሊያ ጐሳዎች በኩል መሆኑን፣ እነዚህ ጐሳዎች በፑንትላንድና በሶማሊላንድ ከሚገኙ ባለሀብቶች ጋር ጥብቅ ግንኙነት እንዳላቸው፣ እነዚህ ባለሀብቶች ደግሞ ከበርካታ የባህረ ሰላጤው ዓረብ አገሮች እንዲሁም ኢራን ድረስ ከሚገኙ ባለሀብቶች ጋር የጠበቀ ግንኙነት እንዳላቸው ያትታል፡፡
በአሁኑ ወቅት አልሸባብ አብዛኛውን የሶማሊያ ደቡብና ማዕከላዊ ግዛቶች በተጨማሪ በአጠቃላይ የጁባ ግዛት በቁጥጥሩ ሥር እንደሚገኝ፣ በተጨማሪም የሒራን፣ ባይና በኮለ የተባሉ ግዛቶች በአብዛኛው በአልሸባብ ይዞታ እንደሚገኙ ሪፖርቱ ያስረዳል፡፡
ከተለያዩ የውጭ የስለላ ተቋማት አገኘሁት በሚለው ሚስጥራዊ መረጃ አልሸባብ አምስት ሺሕ ጠንካራ ወታደሮች እንዳሉት፣ በማንኛውም ጊዜ አደጋ ማድረስ የሚያስችል ዝግጁነት፣ ብቁ ወታደራዊ አመራርና ለመበጣስ ቀላል ባልሆኑ መረቦች የተገናኘ መሆኑን ያስረዳል፡፡ በጦር መሣሪያ ረገድም ከፍተኛ ክምችት እንዳለው የሚያስረዳው ሪፖርቱ፣ አልሸባብ ያጣው ቁልፍ ነገር የወደብ ከተማ የሆነችውን ኪስማዩን እንደሆነ ይገልጻል፡፡
በአጠቃላይ የሪፖርቱ አንድምታ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት ላይ በተመድ የተቀመጠው ውጥን በቁርጠኝነት እየተተገበረ አለመሆኑን፣ የተመድ አባል አገሮችም በዚህ ረገድ የተለሳለሱ መሆናቸውን፣ በአጠቃላይ ዓለም አቀፉ ማኅብረሰብ ለሶማሊያ ጉዳይ የሰጠው ትኩረት ከቁብ የሚቆጠር አለመሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
በመሆኑም የሶማሊያን ጉዳይ በብቸኝነት በጥብቅ የያዘችው ኢትዮጵያ መሆኗን ከሪፖርቱ ለመገመት ይቻላል፡፡ ይህንን ከግምት በማስገባት ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ለመረዳት ባይችልም ኢትዮጵያ በሶማሊያ ያላትን ተልዕኮ በዚህ ሳምንት መቀነስ ጀምራለች፡፡ ባለፈው ሰኞ የኢትዮጵያ ጦር ከባይደዋ የለቀቀ ሲሆን፣ ዓላማው ግን ሙሉ ለሙሉ ከሶማሊያ መውጣት አለመሆኑን መንግሥት ገልጿል፡፡
ሰሞኑን ከወጣው የተመድ አጣሪ ቡድን ሪፖርት መገንዘብ የሚቻለው ቁም ነገር አልሸባብ አሁንም በሶማሊያ አብዛኛው አካባቢ የተንሰራፋ ከመሆኑ ባሻገር፣ ሰፊ አኅጉራዊ ብሎም ከዚያ ያለፈ ኔትወርክ እንዳለው ነው፡፡
እናም ኢትዮጵያ በሶማሊያ እያደረገች ያለችው ፀረ ሽብር ትግልና በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋትን የመፍጠር ጥረት የዓለም ኅብረተሰብን ድጋፍ በሚፈለገው ደረጃ ያላገኘ የተናጠል ዘመቻ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ለማረጋገጫም እስካሁን የተገኘው ውጤትና የሰሞኑ የተመድ አጣሪ ቡድን ሪፖርት ማስረጃ ነው፡፡
ethiopian reporter
No comments:
Post a Comment