Translate

Tuesday, July 16, 2013

ድል መሰዋትነት ይፈልጋል!

ከተስፋዬ ዘነበ (ኖርዌይ በርገን) Ethiocenter.blogspot.com

Author and writer Tesfaye Zenebe from Norway
ከተስፋዬ ዘነበ (ኖርዌይ በርገን)
ሃብትና ስልጣን አስክሮአቸው፣ በዚህች ደሃ ሃገርና ሕዝብ ላይ ተፈናጠው ሁለት አስርተ አመታት ያስቆጠሩ አምባገነን መሪዎቻችን የሃገርና የሕዝበ ፍቅር አጥተው  በምዝበራ ለመክበር ብቻ፣ ሕዝብንም በሃገሩ በሰላም የመኖር መብቱን ቀምተው ተደላድለው ለመቀመጥ ዘንድሮም እንደ አምናው በሽብር ስም በጫኑብን የአፈና መረብ ሸብበው ሕዝቡን ከዳር እዳር ማስጨነቃቸው ሳያንስ አሁን ደግሞ ለዚህ እኩይ ተልኳቸው ላሰለጠኑዋቸው  የስርዓቱ ሰዎች (ደህንነቶች) በዴሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ችግር ከኑሮው ጋር ደፋ ቀና የሚለውን ሰላማዊ ሕዝብ  የሚያሰቃዩበትንና ባስም ሲል የሚገሉበትን ህጋዊ ፈቃድ ሰጥተዋቸዋል፡፡

ስለዚህ ዘረኛ ቡድን ብዙ ጊዜ ብዙ ቢባልም አሁን ባለንበት ወቅት አለም በዴሞክራሲና በመልካም አሰተዳደር ከደረሰበት ደረጃ አንፃር እንደ ሃገርና ሕዝብ ለሚደርስብን ቤሔራዊ ውርደት፣ ለምንቀበለው መከራና እንግልት የወያኔ ዘረኛ ቡድን ግንባር ቀደም ተጠያቂ ቢሆንም መብታችንንና ስብህናችንን ብሎም ሃገራችንን አሳልፈን ሰጥተን ስለጥቃታችን ስናወራ አመታት ያሳለፍን እኛም የታሪክ ተጠያቂዎች ነን፡፡ በውስጥም በውጪም ያለን ኢትዮጲያዊያን ወያኔ ወገኖቻችንን ጭዳ ሲያደርግ፣ የሃገራችንን ቤሄራዊ ጥቅም ለሌሎች አሳልፎ ሲሰጥ፣ ለሃገርና ለሕዝብ ተቆርቁረው በድፍረት ድምፃቸውን ያሰሙ ጋዜጠኞችም ሆኑ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችን በፈለገው ሰዓት የፈለገውን ስም እየሰጠ ሰላማዊ ህይወታቸውን ቀምቶ ወህኒ ሲወረውራቸው የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ ከማድረግ ውጪ ለምን? እንዴት? ብለን መጠየቅ ተስኖናል፡፡
የሚገርመው በየትኛውም መመዘኛ ፈፅሞ ልክ ሊሆኑ የማይችሉ፣ የሕዝብን በሃገሩ በነፃነት የመኖር መብት የሚፃረሩ አሸማቃቂና አንቀጥቅጠው የሚገዙ የስርዓቱ ሰነዶች ሕግ ሆነው ሲፀድቁ ከዛም ተግባራዊ ሲሆኑ አይተናል፣ ይሁንና ከዚህ ዘረኛ ስርዓት እኩል እድሜ ያላቸው በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ለውጥም እናመጣለን ብለው ከሚንቀሳቀሱት ቱባ ድርጅቶች መግለጫ ከማውጣት ባለፈ ሕዝብን አደራጅተው በመንግስት ላይ ምንም አይነት አስገዳጅ እርምጃ ሲወስዱ አልታየም፡፡ ይልቁንም ልዩነታቸውን አቻችለው የጋራ ወይም የሃገርና የሕዝብ ጠላት የሆነውን ስርዓት ከመታገል ፋንታ እርስ በእርሳቸው ሲናከሱና ሲጠላለፉ ከሃገርና ከሕዝብ በፊት ግለሰብ ወይም ድርጅት እያስቀደሙ የወያኔ መናጆ ሆነው ዘመናቸውን የፈጁ እንዳሉ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡
የራሱ መርህና እቅድ ያለው የፖለቲካ ድርጅት ያለውን የተለየ ሃሳብ ለህዝቡ ማሳወቅ ተቀዳሚ አላማው ሊሆን ይገባል፡፡ ምክኒያቱም ድርጅት እንጂ ወደ ሕዝብ ወርዶ መርሆውንና እቅዱን ማሳወቅ ያለበት ሕዝብማ እንደ ሕዝብ ችግሩንና በደሉን የሚቀርፍለት ታግሎ የሚያታግለው የኔ የሚለው የፖለቲካ ድርጅት መፈለጉ አይቀሬ ነው፡፡
አንድ የፖለቲካ ድርጅት እንደ ድርጅት ምልኡ የሚሆነው የተነሳለትን አላማና እቅድ እንዲሁም የሕዝብን መሰረታዊ የመብት ጥያቄዎች ተግባራዊ ምላሽ እንዲያገኙ በፅናት መታገል ሲችል ነው፡፡ እንደ ወያኔ ያለ አምባገነን ስርዓት አፍኖ ለያዘው የሕዝብ የመብት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጠው በተፅኖ እንጂ በችሮታ አይደለም፡፡ ለሚጠየቀው ህገ መንግስታዊ የሕዝብ ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እንዲሰጥ አይጠበቅም አምባገነን ነውና፡፡ ስለሆነም መብቱን የሚያስከብር  ለምን?! በቃኝ፣! እምቢ! የሚል የሕዝብ አደረጃጀት እንዲኖር የፖለቲካ ድርጅቶች በተገቢው ደረጃ ሕዝብን ማደራጀትና መርሆና፣ እቅዳቸውን ማስረፅ እንዲሁም ለለውጥ የተዘጋጀ ትግሉን ከዳር ሊያደርስ የሚችል ፍርሃቱን የሰበረ የህብረተሰብ ሃይል ሊገነቡ ግድ ይላቸዋል፡፡
የወያኔ ዘረኛ ቡድን ህገ መንግስቱ የሚፈቅድልንን ለቁጥር የሚታክቱ መብቶቻችንን ቢነፍገንም፣ ሚያዚያ 30 1997ዓ.ም የነበረውን የቅንጅት የድጋፍ ሰልፍ ተከትሎ ለስምንት አመታት ቀምቶን የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ህገ መንግስታዊ መብታችንን ለማስመለስ ከአመታት በሗላ  በወጣቶች ለተደራጀው ሰማያዊ ፓርቲ  ምስጋና ይግባውና እጅግ በተጠና ወቅትና ጊዜ የመሰለፍ መብታችንን ከገዢዎቻችን እጅ አውጥቶ አሳየን፡፡የሕዝቡንም የተጫነውን የፍርሃት ድባብ በመግፈፍ እረገድ ሰማያዊ ፓርቲ ሃላፊነቱን ተወቷል፡፡ ነገር ግን ይህንን ማድረግ የቻሉት በሰላማዊ መንገድ እንታገላለን ብለው ሁለት አስርተ አመታት የተጓዙ የተለያዩ ድርጅቶች ሲሄዱበት ከነበረው ሃለፊነት ያለመውሰድና በፍርሃት ከመሸበብ ልክፍት ስለወጡ ነው፡፡ የአገሪቱ ህገ መንግስት ሰላማዊ ሰልፍን ለማካሄድ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚጠይቀው ማሳወቅ እንጅ ማስፈቀድ አይደለም ስለሆነም ሰማያዊ ፓርቲ ማሳወቅን እንደ አንድ ግዴታው በመቁጠር ሂደቱን ካከናወነ በሗላ አላማውን ለማሳካት ቁርጠኛ እርምጃ መውሰዱ አምባገነኑን ቡድን አማራጭ እንዲያጣ ስላደረገው በአንድ ሳምንት ቢራዘምም ይሁንታውን እንዲሰጥ አስገድዶታል፡፡
የሰማያዊ ፓርቲ ስኬት ለሌሎችም እንደ ማንቂያ ደውል በመሆኑ እንሆ አንድነትም በጎንደርና በደሴ በአቋሙ በመፅናቱ ከብዙ ውጣውረድ በሗላ እጅግ የተሳካ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል፡፡ አሁን በተጀመረው የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን በተለይ የድርጅት አመራሮች እራሳቸውን ለተሰለፉለት አላማ በማስገዛትና ድል ያለመስዋትነት እንደማይገኝ በመረዳት ታግለው ማታገል ይጠበቅባቸዋል፡፡
የምንታገለው በሃገራችን በነፃነት የመኖር ሰዋዊ መብታችንን በአፋኝ አምባገነን መሪዎች በመነጠቃችን ነው፡፡መብታችንን ለማስመለስ  አስገዳጅ የትግል ስልት ካልቀየስን በስተቀር ወይም የስርዓቱን አፋኝ ህግጋቶች ላለመቀበል እምቢ እስካላልን ድረስ ከአምባገነን ስርዓት ተፈጥሯዊ ባህሪ አንፃር በነሱ ይሁንታ የምናገኘው ፍታዊ ምላሽ አይኖርምአ፡፡
ድል ለኢትዮጲያ ሕዝብ!!!
ሞት ለወያኔና ከፋፋዮች!!!
ለአስተያየቶ: ftih_lewegen@yahoo.com

No comments:

Post a Comment