by Fasil Yenealem (facebook)
የጃዋር ንግግር ያበሳጫቸው ብዙ የፌስ ቡክ ወዳጆቻችን ቁጣቸውን በቻሉት መንገድ ሁሉ እየገለጹ ነው። ነገሩ ከቁጣ ወይም ከውግዘት ወይም ከይቅርታ መጠየቅ ወይም አቋምን ከመግለጽ ባለፈ በደንብ ተብላልቶ መታየት ያለበት ይመስለኛል። በመጀመሪያ ፣ ጃዋር የዚህ ትውልድ ( የህወሀት ዘመን ልጅ ነው)። እርሱ ቢክደውም ፣ የአብዮታዊ ዲሞክራሲን የብሄር ፖለቲካ ጡጦ እየተጋተ ያደገ ልጅ ነው። የብሄር ፖለቲካን ለመጋት የግድ የህወሀት አባል መሆን አይጠይቅም፤ በማርክስ አስተምህሮ መሰረት የገዢው ፓርቲ ርእዮትዓለም የተገዢዎች ርእዮትዓለም ሆኖ የሚያገለግልበት እድል ሰፊ ነው። በተለይ ነጻ አስተሳሰቦች እንደልባቸው በማይንሸራሸሩበት ወይም ፕሮፓጋንዳው ሁሉ ከአንድ ኩሬ በሚፈልቅበት አገር የገዢው ፓርቲ ርእዮትዓለም በተለይ በወጣቶች አስተሳሰብ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀሬ ነው።
ወጣቶች እያወቁ ወይም ሳያውቁ የገዢው ፓርቲ አይዲዮሎጂ ሰለባዎች ይሆናሉ። እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ በአእምሮ ውስጥ አንዴ ከበቀለ ደግሞ በቀላሉ መንቀል አይቻልም፤ አንዳንድ ምሁራን ሀይማኖት እና ብሄር primordial value ናቸው ይላሉ። እነዚህ አስተሳሰቦች በአእምሮ ውስጥ አንዴ ከበቀሉ በሁዋላ መንቀል አይደለም በቀላሉ አይለወጡም፣ ልለወጥ ቢሉ እንኳ ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል፤ በጣም የሚገርመው ደግሞ እንዲህ አይነት አስተሳሰቦች አብዛኛውን ጊዜ የሚቀረጹት በወጣትነት እድሜ መሆኑ ነው ።
ወጣቶች እያወቁ ወይም ሳያውቁ የገዢው ፓርቲ አይዲዮሎጂ ሰለባዎች ይሆናሉ። እንዲህ አይነቱ አስተሳሰብ በአእምሮ ውስጥ አንዴ ከበቀለ ደግሞ በቀላሉ መንቀል አይቻልም፤ አንዳንድ ምሁራን ሀይማኖት እና ብሄር primordial value ናቸው ይላሉ። እነዚህ አስተሳሰቦች በአእምሮ ውስጥ አንዴ ከበቀሉ በሁዋላ መንቀል አይደለም በቀላሉ አይለወጡም፣ ልለወጥ ቢሉ እንኳ ረጅም ጊዜ ይወስድባቸዋል፤ በጣም የሚገርመው ደግሞ እንዲህ አይነት አስተሳሰቦች አብዛኛውን ጊዜ የሚቀረጹት በወጣትነት እድሜ መሆኑ ነው ።
በኢህአዴግ ዘመን የተማርን ወጣቶች የብሄር ፖለቲካን ስንጋት አድገናል፤ አንዳንዶቻችን ተቀብለነው ጃዋራውያን ሆነናል፣ ሌሎቻችን ሳንቀበለው ቀርተናል። በተለይ ታሪክ በድሎናል በማለት አቤቱታ ከሚያሰሙ አካባቢዎች የመጡ ወገኖች የብሄር ፖለቲካው አስተሳሰብ ተመችቶአቸዋል። እንግዲህ ዋናው ጥያቄ በአገራችን ስንት ጃዋርያውያን አሉ የሚለው ነው። በአገራችን የጃዋርያውያን ቁጥር 50 +1 ከሆነ እንደ አገር አክትሞልናል፤ ህወሀት ያሰበው ሆኖለታል ማለት ነው። ቁጥሩ ከ51 በመቶ የሚያንስ ከሆነ ግን እንደ አገር የመቀጠሉ ተስፋ አለን። አገራችንን ለማዳን መበሳጨት ወይም መፎከር ብቻውን በቂ አይደለም፣ ከእነ ጃዋር የተሻለ አስተሳሰብ ይዞ መገኘት፣ የተሻለው አስተሳሰብም ገዢ አስተሳሰብ እንዲሆን መታገል ይገባል። እነጃዋር አስተሳሰባቸውን እንዲለውጡ ከማስገደድ፣ የእነሱ አስተሳሰብ ወደ ሌሎች ወጣቶች እንዳይሰራጭ ወይም ምርኮኞቻቸውን እንዳያበዙ መታገል ያስፈልጋል። ጃዋራውያንን በሜንጫ ወይም መድረክ በመንፈግ ማሸነፍ አይቻልም፣ በግልጽ መድረክ በመከራከር አስተሳሰባቸውን በአስተሳሰብ ማሸነፍ ሲቻል ብቻ ነው ዘላቂ መፍትሄ ሊመጣ የሚችለው። ጃዋርን በግልጽ በመሞገት እና እጸጾቹን በማሳየት ሌሎች ወጣቶች እንዳይቀበሉት ማድረግ ያስፈልጋል። ሌላው ደግሞ ወጣቶቻችን ታሪክን እንዲያዉቁ፣ የፖለቲካ ግንዛቢያቸው እንዲሰፋ ማድረግ የአንድነትን ሀይል ከሚሰብኩ ወገኖች ይጠበቃል፡፡
ጃዋር ለፕሮፓጋንዳው እንዲጠቅመው አድርጎ ያነበበው ታሪክ ወንዝ የማያሻግር መሆኑን ለማየት ይቻላል። በብዙ ብሄርተኞች ላይ እንደሚታየው ጃዋር በታሪክ ላይ ተሳልቋል፣ ታሪክም በጃዋር ላይ ተሳልቋል። እንዳለመታደል ሆኖ የጥንትኦሮሞዎች የጽሁፍ ባህል አልነበራቸውም፣ ታሪካቸውንም ጽፈው አላስቀመጡም፤ ጃዋር የእነሱን ታሪክ ለማንበብ የግድ በግእዝ ወይም በአማርኛ የተጻፉ መጽሀፍትን ማገላበጥ ሊኖርበት ነው፤ አማርኛን ደግሞ ይጠላል፣ አማርኛ ማንበብ በአማራ ባህል መወረር ነው ብሎ ያምናል፣ ስለዚህ ለጃዋር ያለው ምርጫ በአፈ ታሪክ ላይ ተመስርቶ ተረቱን ታሪክ እያደረገ ጆሮ ለሰጠው ሁሉ ማቅረብ ነው፤ አፈ ታሪክ ደግሞ ረጅም ርቀት አይወስድም፣ ይኸው አሁን እንደምናየው መያዣ መጨበጫ የሌለው ነገር ያናግራል። ስለኦሮሞ ጥንተ-ታሪክ የተጻፉ የፈረንጅ መጽሀፍትም ቢሆኑ ብዙዎቹ በአባ ባህሬን መጽሀፍ ላይ ተንተርሰው ወይም በአፈ ታሪክ ላይ ተመስርተው የተጻፉ ናቸው። አንዳንዶቹ የፈረንጅ መጽሀፍትም ለጃዋርያውያን የሚመቹ አይደሉም፤ ለምሳሌ በጅ የተባለ የታሪክ ጸሀፊ ስለኦሮሞች ማንነት የጻፈው ጽሁፍ ብዙ ኦሮሞችን እንዳበሳጨ ለመመልከት የሚሻ ሰው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መጽሀፍት ቤት ገብቶ መጽሀፉን ተውሶ ማየት ይበቃዋል፤ መጽሀፉ በኦሮሞ ተማሪዎች ተሰርዞ ተደልዞ ታዩታላችሁ። እንደያውም በዩኒቨርስቲው የሚገኙ አብዛኞቹ የታሪክ መጽሀፎች ስርዝ ድልዝ አላቸው በተለይ ኦሮሞን የሚመለከቱ ክፍሎች። በጥንቶቹ የታሪክ መጽሀፍት ውስጥ The Oromo Migration ( ስደት) የሚለው ሀረግ The Oromo Expansion በሚለው እየተሰረዘ እንዲተካ ተድርጓል። ታሪክ አስተማሪዎችም ኦሮሞ ተስፋፋ እንጅ ተሰደደ ብለው እንዳያስተምሩ ታዘው ተግባራዊ እያደረጉት ነው። አንድ ጊዜ ፕ/ር መርእድ ወ/አረጋይን “ለምን?” ብየ ጠይቄአቸው ነበር። “ታሪክ ሰዎችን አብረው እንዲኖሩ እንጅ እንዲለያዩ አያበረታታም” ብለው መለሱልኝ። ልክ ነበሩ። ኦሮሞ ተስፋፋሁ እንጅ አልተሰደድኩም ቢል ኢትዮጵያዊነቱን ይበልጥ የሚያረጋግጥ በመሆኑ እቀበለዋለሁ። የእኔም ክርክር ኦሮሞ መጤ ሳይሆን ተወላጅ ነው የሚል ነው። እነጀዋር ግን ሳያውቁት አንዴ ራሳቸውን መጤ ያደርጋሉ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ተወላጆች ነን ይላሉ። ታሪክን ማዛባት እንዲህ ያወናብዳል።
ከጃዋር የታሪክ ግድፈት አንዱን እንመልከት። “ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን ከፕሮቱጋሎች እርዳታ በመቀበል ሙስሊም ኢትዮጵያውያንን ወግተዋል” ይለናል። ጃዋር ታሪኩን አዛብቶ ለራሱ በሚመች መልኩ አቅርቦታል። ክርስቲያኖች ፖርቱጋሎችን እርዳታ ከመጠየቃቸው በፊት ፣ ኦቶማን ቱርኮች ለግራኝ ሙሀመድ እርዳታ በመስጠት ልብነድንግልን እንዲወጋ አድርገውታል፣ ለዚህም ነው ግራኝ ያሸነፈው። ፖርቱጋሎች ገላውዲዮስን ለመርዳት ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ ክርስትናን ለማስፋፋት አስበው አልነበረም፤ (ፖርቱጋሎች ካቶሊኮች የኢትዮጵያ ንጉስ ደግሞ ኦርቶዶክስ እንደነበሩ አንርሳ)። ኦቶማን ቱርኮችም ግራኝን ሲደግፉ እስልምናን ያስፋፋልናል ብለው በማሰብ አልነበረም። ሁለቱም የዘመኑ ሀያሎች በኢትዮጵያ ውስጥ ክርስትናን ወይም እስልምናን የማስፋፋት አላማ አልነበራቸውም፤ የሁለቱም አላማ ቀይ ባህርን በመቆጣጠር ንግዳቸውን ማስፋፋት፣ ግዛታቸውን ማስፋፋት ነው። ለሁለቱም አገሮች ሀይማኖት እንደ መሳሪያ እንጅ እንደግብ ሆኖ አላገለገለም።
በአለም የግዛት አመሰራረት ታሪክ ኦቶማን ቱርኮች በአንድ ነገር ይለያሉ። እነሱ አንድን ግዛት ሲቆጣጠሩ በቁጥጥር ስር ያዋሉትን ህዝብ ሀይማኖቱን አስገድደው አያስቀይሩትም። ኦቶማን ቱርኮች ኢየሩሳሌምን በያዙበት ወቅት የዴር ሱልጣን ገዳምን ኢትዮጵያኖች እንደያዙ እንዲቆዩ፣ በእየሩሳሌም የሚገኙ ክርስቲያኖችም ሀይማኖታቸውን እንደያዙ እንዲቀጥሉ ፈቅደውላቸዋል። ቱርኮች በኢትዮጵያ ጉዳይም የተለየ አቋም የሚይዙበት ነገር አልነበራቸውም። ግራኝ እስልምናን በሀይል ለማስፋፋት መሞከሩ እውነት ነው፤ ቱርኮች ለግራኝ ድጋፍ ማድረጋቸውም እንዲሁ እውነት ነው፣ ነገር ግን ቱርኮች ግራኝን የረዱት እስልምናን እንዲያስፋፋላቸው ነው የሚለውን ለመቀበል እቸገራለሁ። ቱርኮች በጊዜው ለእነሱ የሚገብር መንግስት በኢትዮጵያ ይፈልጉ ነበር፣ ያ መንግስት ክርስቲያንም ይሁን ሙስሊም አሜን ብሎ እስከገበረ ድረስ ግድ አልነበራቸውም። ግራኝን የደገፉት ሙስሊም ስለሆነ አይወጋንም፣ ለእኛም ይገዛል ብለው ነው። ልብነድንግል ከቱርክ ጋር ቢስማማ ኖሮ ግራኝ መሳሪያ ባለገኘ ስልጣኑንም ባላጣ ነበር። ማወቅ ያለብን ግን ግራኝም ልብነድንግልም ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ነው። የሁለቱም ታሪክ ታሪካችን ነው። ግራኝ ብዙ ቤተክርስቲያኖችን አውድሟል፤ ክርስቲያኖችም ብዙ መስጊዶችን አጥፍተዋል፤ ታሪኩ ግን ሁለት እምነት የሚከተሉ የአንድ አገር ልጆች ወይም የወንድማማቾች ታሪክ ነው።
ደፋሩ ጃዋር ” ኦሮሞች በሀረር የሚገኙ ሙስሊሞችን ከክርስቲያኖች ጥቃት አድነዋቸዋል” ይለናል ። በየትኛው መጽሀፍ ተጽፎ እንዳገኘው አላውቅም። እኔ እስከማውቀው ድረስ በምስራቅ ዝቅተኛ ቦታዎች የሚገኙ የሶማሊ ተወላጆች ( አብዛኞቹ ሙስሊሞች) ፣ ከጥንት እስከዛሬ ከኦሮሞች ጋር በግጦሽ መሬት እንደሚዋጉ ነው ( በቦረናና በባሌ አካባቢዎች ያለውን ይመለከቷል) ። ለመሆኑ ኦሮሞ ጥንት ግዛቱን ሲያስፋፋ የዋቄ ፈታን እምነት ለምን አብሮ ሳያስፋፋ ቀረ? የኦሮሞ ባላባቶች “ንጉስ ሿሚ እና ሻሪ” በነበሩበት የእነራስ አሊ አንደኛ እና ሁለተኛ ዘመን ለምን የዋቄ ፈታን እምነት ትተው ክርስትናና እስልምናን ተቀበሉ? የትኛው የሙስሊም ንጉስ ነው ኦሮሞችን በሀይል አስገድዶ እስልምናን እንዲቀበሉ ያደረጋቸው? ጃዋር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ የሚያገኝ አይመስለኝም።
በኢትዮጵያ ውስጥ ከግራኝ በፊትና በሁዋላ እስልምና በአብዛኛው የተስፋፋው ከንግድ ጋር በተያያዘ እንጅ በሀይል አይደለም፣ ኦሮሞችም ሁለቱን ሀይማኖቶች የተቀበሉት ተገደው ሳይሆን የግዛት ማስፋፋት ፖሊሲያቸው አንዱ አካል ስለነበር ነው። ኦሮሞዎች ወደ መሀል ፣ ሰሜን እና ደቡብ ኢትዮጵያ ሲስፋፉ በሄዱበት አካባቢ ያለውን ባህል እና እምነት ያከብራሉ ወይም የራሳቸውን በማዳቀል አዲስ እምነት ይፈጥራሉ። ጎጃም፣ ጎንደር ፣ ወሎና ከፊል ሸዋ ብትሄዱ የክርስትና እምነት ተከታይ የሆነ ሰው ለአባይ ወንዝ ስለት ሲያስገባ ወይም ወርካውን ቅቤ ሲቀባ ታዩታላችሁ። ሙስሊሞችም ዶሮአቸውን አርደው አካባቢውን ይረጩታል፣ ቆሎም ይበትናሉ። በእነዚህ አካባቢዎች የዋቄ ፈታ እምነት ከክርስትና ወይም እስልምና ሀይማኖት አስተምሮዎች ጋር ተደባልቋል። ይሄ ስህተት አይደለም፣ እምነትም ባህልም በዚህ መንገድ ነው የሚስፋፋው፤ የኦሮሞ የመስፋፋት ፖሊሲ እንደ ኦቶማን ቱርኮች በባህል ላይ ጫና አያደርግም፣ የእኔን እምነት ካልተቀበልክ ብሎ ሰው አይገድልም። እንዲህ ባያደርግ ኖሮ ኦሮሞ ዛሬ የያዘውን የመሬት ስፋት ባልያዘ ነበር። ኢትዮጵያም ተረጋግታ እንዳገር ባልቀጠለች ነበር። ለጥንት የኦሮሞ ፖለቲከኞች ያለኝ አድናቆት የሚመነጨውን ከዚህ አንጻር ነው። በነገራችን ላይ እኔ ባደኩበት አካባቢ (ጎጃም) ኦሮሞ መባል፣ እነጃዋር እንደሚሉት የሚያሳፍር ሳይሆን፣ የሚያኮራ ነው። አንድ ጊዜ እናቴን እንች እኮ የኦሮሞ ደም አለሽ፣ ይህ አካባቢ እኮ በኦሮሞዎች የተያዘ ነበር አልኳት። ” እንዴ ልጄ ምን ማለትህ ነው፣ እኔ እናትህ እኮ የባላባት ዘር ነኝ፤ ኦሮሞ እኮ ባላባት ነው፣ የእነ እከሌ ዘር ነኝ፣ ከዚህ በመለስ እኮ ያለው የዘመዶቼ …ግዛት ነበር” አለችኝ። ኦሮሞ ማለት በጎጃሞች ዘንድ የባላባትነት መገለጫ መሆኑን የአሁኑ ዘመን የኦሮሞ ተወላጆች ሊሰሙትም አይፈልጉም።
በአንድ ወቅት መለስ ዜናዊ ትግራይ ላሉ ወጣቶች ሲናገር ” የእኛ ስጋት ምን ያክል የትግራይ ወጣቶች ርእዮተአለማችንን እስከመጨረሻው ይዘው ይዘልቃሉ፣ እኛ ብናልፍ ለምን ያክል ጊዜ አላማውን ይዘው ይጓዛሉ? ” የሚለው ነው በማለት ተናግሮ ነበር። መለስ ዛሬ ከመቃብር ወጥቶ ጃዋር የሚለውን ቢሰማ በደስታ በተፍነከነከ ነበር።
በአለም ላይ የተከሰቱ የብሄር ግጭቶች ታሪክን ከማጣመም ወይም ታሪክን ከመጠምዘዝ ጋር የተሳሰሩ ናቸው፡፤ ፖለቲከኞች ስልጣን ሲያምራቸው ታሪክን አጣመው ደጋፊዎችን ለማሰባሰብ ይሻሉ፤ ለስልጣን በሚያደርጉት እሩጫ የዘላለም ጠባሳ ጥለው ያልፋሉ። ለምሳሌ በዩጎዝላቪያ የእርስ በርስ ግጭት ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ( እኤአ 1989) ሚሎሶቪች ከ600 አመት በፊት ሰርቦች በቱርኮች መሬታቸውን መቀማታቸውን የተመለከተ ንግግር በማድረግ ህዝቡን ለጦርነት አነሳስቶ ነበር። የእነጃዋር አካሄድም ግቡ ከዚህ የተለየ አይደለም። የብሄር ፖለቲካ የዜሮ ድምር ፖለቲካ ነው። ሁሉንም በእኩል አያስተናግድም።
አንድነትን የሚሰብኩት ወገኖች ጃዋርያውያንን በመሳደብ ፣ በማውገዝ ፣ በማግለል ወይም ፎቶአቸውን በማበላሸት ማሸነፍ እንደማይቻል ልብ ሊሉት ይገባል። እንዲህ አይነቱን አስተሳሰብ ማሸነፍ የሚቻለው የተሻለ አስተሳሰብ በማምጣትና በመሞገት ነው። ለምሳሌ ጃዋር ኦሮሞ ቁጥሩ ብዙ ስለሆነ ስልጣን መያዝ ይገባዋል ይላል። በጉልበት ማለቱ ከሆነ ተሳስቷል፤ ቁጥር ብቻውን ጉልበት እንደማይሆን እናውቃለን፤ እንዲያ ቢሆን ህወሀት 22 አመታት ባልገዛን ነበር። በምርጫ ማለቱ ከሆነም እንደ ሁኔታው ይወሰናል። ኦሮሞ ከእያንዳንዱ ብሄረሰብ ጋር ሲወዳደር በእርግጥም ቁጥሩ ብዙ ነው። ነገር ግን ኦሮሞ ከሌሎች ብሄሮች ድምር ጋር ሲወዳደር ቁጥሩ 50+1 አይሞላም። ለምሳሌ በኦሮሞ ፓርቲና በአንድ ህብረ-ብሄራዊ ፓርቲ መካከል የምርጫ ፉክክል ይደረግ እንበል። ሁሉም ኦሮሞዎች የኦሮሞውን ፓርቲ ቢመርጡና ከኦሮሞ ውጭ ያለው ህዝብ ደግሞ ህብረ-ብሄራዊ የሆነውን ፓርቲ ቢመርጥ የኦሮሞው ፓርቲ 51 በመቶ ድምጽ ስለማያገኝ መሸነፉ አይቀርም። ኦሮሞ ብዙ ቁጥር አለኝ ቢልም በምርጫ ለያሸንፍ የሚችለው፣ ሌሎች ህዝቦችን በመያዝ ብቻ ይሆናል ማለት ነው።
የእነ ጃዋር የቁጥርም ሆነ የታሪክ ጨዋታ እሩቅ እንደማይሰድ ለማሳየት ብዙ ማለት በተቻለ። ለአሁን በዚህ ለብቃ፣ ሙግቱን የምናሰፋው ከሆነ ከተጨናነቀው ጊዜየ እየቆጠብቁ አንዳንድ መስመር ለመወርወር ዝግጁ ነኝ።
No comments:
Post a Comment