“ኃይሌ ወደ ፖለቲካ መግባቱ መብቱ ቢሆንም እንደስፖርቱ በፖለቲካውም የሚያንጸባርቅ አይመስለኝም” ዶ/ር መረራ
“በአገሪቱ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል የለም። አገሪቱ የጡንቸኞች ሀገር ናት። … ገብቶ ይሞክረው” ፕሮፌሰር በየነ
“እኔ ኃይሌን ብሆን ኖሮ በግል ወደ ፖለቲካ ከምገባ ወደ ፓርቲ መግባቱን ነው የምመርጠው። ከፓርቲው ደግሞ የመጀመሪያ ምርጫዬ የሚሆነው አንድነት ፓርቲ ነው” ዶ/ር ነጋሶ
“ኃይሌ እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ በግሉ ወይም በፓርቲ ወደ ምርጫ መግባቱን እንኳ ግልፅ አላደረገም … ፖለቲካ በግል ፍላጎት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ፖለቲካ እራሱን የቻለ ፖሊሲ መቅረፅ ያስፈልጋል። … ፖሊሲ ማስፈፀም የሚቻለው በፓርላማው አብላጫ ወንበር ሲያዝ ነው፤ … አንድ ሰው ብቻ ከሆነ ግን “አጃቢ” የመሆን አደጋ አለው። አቶ ገብሩ
“አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በክብር እንግድነት እንዲገኝ ጥያቄዎችን ባለመቀበል በአንፃሩ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ በሆኑ ማህበራት ላይ በክብር እንግድነትና በንግግር አድራጊነት መገኘቱ የሚያመለክተው የኃይሌ የፖለቲካ ተሳትፎ በገዢው ፓርቲ ይሁንታ ያገኘ መሆኑ ነው … ወደ ፓርላማ ለመግባት የወሰነውም የግሉን ክብርና ዝና መሻት እንጂ አዳዲስ የፖሊሲ ኀሳቦችን በመያዝ (አይደለም)…” አቶ ሀብታሙ
_______________________________________________________________________________
ዝነኛው አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ከሁለት ዓመት በኋላ በሚካሄደው በ2007ቱ ጠቅላላ ምርጫ አዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በመወዳደር ወደ ፓርላማ ለመግባት ማቀዱን ይፋ አድርጓል።
አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ በግል ወይም በፓርቲ ውስጥ ገብቶ ለመወዳደር ግልፅ ባያደርግም ከሁለት ዓመት በኋላ በምርጫው ተሳታፊ በመሆን የፖለቲካ ጅማሮውን እውን እንደሚያደርግ አስታውቋል። በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን የኢትዮጵያ “ፕሬዝዳንት ይሆናል” የሚለውን ዘገባ በማስተባበል ፕሬዝዳንት መሆን ግን እንደማይጠላ ተናግሯል።
ታዋቂው አትሌት ይሄንን አስተያየቱን በግልፅ ከሰጠ በኋላ በውጪና በሀገር ውስጥ ጉዳዩ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል። የኃይሌን የፖለቲካ ተሳትፎ ከሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል አለመዳበርና አስቸጋሪነት አንጻር እያነሱ የአትሌቱን ተሳትፎ አምርረው የተቹ እንዳሉ ሁሉ መግባቱንም የሚያበረታቱ አልጠፉም።
በሀገሪቱ ያሉ የፓርቲ አመራሮችም የሻለቃ ኃይሌን የፖለቲካ ተሳትፎ የተደበላለቀ ስሜት እንደፈጠረባቸው ከሰጡት አስተያየት መረዳት ተችሏል።
ሰንደቅ ካነጋገራቸው የፓርቲ አመራሮች መካከል የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ኃይሌ ወደ ፖለቲካ መግባቱ መብቱ ቢሆንም እንደስፖርቱ በፖለቲካውም የሚያንጸባርቅ አይመስለኝም ሲሉ ባልተለመደ ሁኔታ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በበኩላቸው ኃይሌ ለሁሉም ክፍት ወደሆነው ፖለቲካ መግባቱ አዲስ ነገር እንደሌለው ገልጸዋል።
“በተለይ እንደሱ ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ወደ ፖለቲካ መድረኩ መምጣታቸው ተገቢ ነው” የሚሉት ፕሮፌሰር ለሀገሩ ብዙ የደከመ፣ ላቡን ያንጠፈጠፈ ሰው በመሆኑ ለሀገሪቱ ቀና ነገር እስካሰበ ድረስ ወደመድረኩ መምጣቱ የሚደገፍ እንደሆነ ገልጸዋል።
ነገር ግን የሀገሪቱ ፖለቲካ የህይወት መስዋዕትትን ጨምሮ ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል፣ ያለስም ስም የሚያሰጥ አስቸጋሪ ውጣውረድ ያለበት በመሆኑ ችግር ሊገጥመው እንደሚችል ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል።
“በአገሪቱ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል የለም። አገሪቱ የጡንቸኞች ሀገር ናት። የሀገሪቱ ፖለቲካ ያልሰከነ፣ ሊገመት የማይችል ነው። የጎበዝ አለቃ ሁሉ ፖለቲከኛ ነኝ የሚልበት ሀገር ነው። ስለዚህ ሻለቃ ኃይሌም ገብቶ ይሞክረው” ያሉት ፕሮፌሰር በየነ የኃይሌ የፖለቲካ ውጤታማነት የሚለካው በሀገሪቱ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
“ኃይሌ ገብረስላሴ ፓርላማ መግባት ያቅተዋል ብዬ አላስብም” የሚሉት ፕሮፌሰሩ “ኃይሌ በቂ ሀብት አለው። እኛ ድሆቹም ሀሳብ ብቻ ይዘን ለምንንቀሳቀሰው ሊያስቸግር ይችላል” ብለዋል። በተጨማሪም ኃይሌ ከተንኮልና ከመሰሪነት ካልተተበተቡ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንዱ በመሆኑ አመጣጡ ጤነኛ ነው ብለዋል።
“ኃይሌ ፓርቲ አቋቁሞ ቢገባ ይሻላል” ስለሚባለው አስተያየት የተጠየቁት ፕሮፌሰር በየነ ፓርቲ ማቋቋም የተሰለቸ ጉዳይ በመሆኑ እንደ አዲስ ፓርቲ ከሚያቋቁም ይልቅ ለኃሳቡ በሚመቸው ፓርቲ ውስጥ ቢቀላቀል የሚመከር ነው ብለዋል። በእርግጥ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎች በውስጥ ችግር እየተነታረኩ መሆኑ ለጊዜው በፓርቲዎቹ ላይ ተስፋ ሊያስቆርጠው ችሎ ይሆናል ብለዋል። ነገር ግን በፖለቲካ ግለሰብ ለብቻው የሚያመጣው ለውጥ እንደሌለም ገልጸዋል።
የአንድንት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ሊቀመንበርና የቀድሞ የፓርላማ የግል ተወዳዳሪ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ወደ ፖለቲካ እንዲገባ የሀገሪቱ ሕገ-መንግስት ይፈቅድለታል ብለዋል።
ኃይሌ ተሳክቶለት ወደ ፓርላማ ከገባም ስፖርቱንና የፓርላማ ተግባሩን በአንድ ጊዜ መወጣት እንደማይችል የጠቀሱት ዶ/ር ነጋሶ በፓርላማውም ቢሆን ከእሳቸው ልምድ በመነሳት ለግል ተወዳዳሪ የሚኖረው መብት እጅግ በጣም የተመጠነ ከመሆኑም በላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም ብለዋል።
“ኃይሌ በግል ተወዳድሮ ወደ ፓርላማ ቢገባ የመናገር ዕድል ሊያገኝ የሚችለው ቢያንስ ሁለት ደቂቃ ቢበዛ ሶስት ደቂቃ ነው። ይሄንንም ዕድል ሊያገኝ የሚችለው በአፈ-ጉባኤዎቹ መልካም ፈቃድ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም በፓርላማው ውስጥ በሚቋቋሙ ቋሚ ኮሚቴዎችም ውስጥ ሊገባ አይችልም። በአጠቃላይ በግል ተወዳድሮ ፓርላማ መግባት ቦታ የሌለው ጉዳይ ነው” ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ለኃይሌ ጥሩ አማራጭ እራሱን በፓርቲ አደረጃጀት ውስጥ ለማስገባት ቢሞክሩ ጥሩ ነው ሲሉ ምክር ለግሰዋል።
“እንደምታውቀው ኃይሌ በአሁኑ ወቅት ባለሀብት ሆኗል። ከዚህ አኳያ የካፒታሊስት ርዕዮተ ዓለም አቀንቃኝ ይመስለኛል። ለዚህ ደግሞ አመቺው የሊብራል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ነው። ስለዚህ ለአትሌቱ ጥሩ ፓርቲ ሊሆን የሚችለው እንደ አንድነት ፓርቲዎች ውስጥ ቢገባ ነው የምመክረው” ብለዋል።
“እኔ ኃይሌን ብሆን ኖሮ በግል ወደ ፖለቲካ ከምገባ ወደ ፓርቲ መግባቱን ነው የምመርጠው። ከፓርቲው ደግሞ የመጀመሪያ ምርጫዬ የሚሆነው አንድነት ፓርቲ ነው” ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ኃይሌን በቅርብ ስለማያውቁት በግሉ ምን አይነት ርዕዮተ ዓለም አራማጅ ስለመሆኑ የማውቀው ነገር የለም ብለዋል።
“ኃይሌ ፕሬዝዳንት ይሆናል ብለው ይገምታሉ” ተብለው ለተጠየቁት ዶ/ር ነጋሶ ሲመልሱ፤ “ፕሬዝዳንት ለመሆን አይችልም። ምክንያቱም ገና ወጣት ነው። ቦታው ለወጣት አይሆንም። ምናልባት የሀገሪቱ መልካም ገፅታ ለማስተዋወቅ ልጁ በዓለም ስለታወቀ በዚያ አቅጣጫ ከማንም በላይ ሊያስተዋውቅ ይችላል። ነገር ግን ቦታው ብዙ መስራት ለሚፈልግ ወጣት አመቺ አይደለም። ከዚህ ጎን ለጎን የመንግስትን አቋም ማንፀባረቅ ይጠበቅበታል። በ2007 ምርጫ ኢህአዴግ መልሶ የሚያሸንፍ ከሆነም የኢህአዴግን አቋም እንዲያንፀባርቅ ሊገደድ ይችላል” ብለዋል።
የአረና ትግራይ ለዴሞክራሲና ለሉአላዊነት ፓርቲ (አረና) ሊቀመንበርና የቀድሞ የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው የኃይሌ ወደ ፖለቲካ መምጣት መብቱ እንደሆነ ገልጸው፤ ዋናው መታየት ያለበት አትሌቱ ወደ ፖለቲካ ገብቶ በምርጫ ሲፎካከር የሚያቀርበው መርሃ ግብር ወሳኝ ነው ብለዋል።
“አትሌቱ ወደ ፖለቲካ መግባቱን፣ በምርጫ መሳተፉን ከመግለፅ ባለፈ ስላነገበው ፕሮግራም የጠቀሰው ነገር አለመኖሩን ያወሱት አቶ ገብሩ፤ ኃይሌ እስካሁኗ ደቂቃ ድረስ በግሉ ወይም በፓርቲ ወደ ምርጫ መግባቱን እንኳ ግልፅ አላደረገም ብለዋል።
አነጋጋሪው ጉዳይ አትሌት ኃይሌ ወደ ፖለቲካ መግባቱ ሳይሆን ምን ይዞ ገባ? የሚለው ነው መታየት ያለበት ያሉት አቶ ገብሩ፤ ኃይሌ ወደ ፖለቲካ ሲገባ ምን አይነት ለውጥ ለማምጣት ነው? የሚለው በግልፅ መታወቅ አለበት። ያለውን ለማስቀጠል ከሆነ ትርጉም የለውም። ለለውጥ ከተዘጋጀ ደግሞ ጥሩ ነገር ነው። ኃይሌ የለውጥ አጀንዳ ከሌለው ግን ቀደም ሲል የነበረውንም ዝና ሊንድበት እንደሚችልም ገልፀዋል።
“ኃይሌ የአፈፃፀም ችግሮችን መሰረት አድርጎ ወደ ፖለቲካ የሚገባ ከሆነ ዋጋ የለውም። እራሱ ኢህአዴግም የአፈፃፀም ችግር እንዳለበት ነው የሚገልፀው። ከኃይሌ የሚጠበቀው አዲስ የፖሊስ አቅጣጫ ነው። ወሳኙ ነገር ምን ፖሊሲ ለማስፈፀም ነው ወደ ፖለቲካ የሚገባው የሚለው ነው። ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት መሠረታዊ የፖሊስ ለውጥ እየፈለገች ነው። የኢህአዴግን ፖሊሲ የመድገምና የእሱን ፕሮግራም የማስቀጠል ዓላማ ለዚህች ሀገር ፋይዳ የለውም” ብለዋል።
“ፖለቲካ በግል ፍላጎት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ፖለቲካ እራሱን የቻለ ፖሊሲ መቅረፅ ያስፈልጋል። ለፖሊሲው መተግበርም የፀና አቋም ሲኖር ነው” የሚሉት አቶ ገብሩ ኃይሌ ያመነበት ፖሊሲ እስከሌለው በግሉ የሚፈጥረው ነገር የለም ብለዋል። ፖሊሲ ማስፈፀም የሚቻለው በፓርላማው አብላጫ ወንበር ሲያዝ እንደሆነም አቶ ገብሩ ገልጸው አንድ ሰው ብቻ ከሆነ ግን “አጃቢ” የመሆን አደጋ እንዳለውም ገልጸዋል።
የአንድነት ፓርቲ የብሔራዊ ም/ቤት አባልና የባለራዕይ ወጣቶች ማህበር የቀድሞ ሊቀመንበር አቶ ሀብታሙ አያሌው በበኩሉ የሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ወደ ፓርላማ የመግባት ፍላጎት በርካታ መልኮች እንዳሉት ገልጸዋል። ነገር ግን ሻለቃ ኃይሉ ከአዲስ አበባ ወጣት ማህበር ጋር ተደጋግፎ መስራት መጀመሩ ማህበሩን ለምርጫ ተግባር ለማዋል ማቀዱን ያሳያል ብለዋል።
አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በክብር እንግድነት እንዲገኝ ጥያቄዎችን ባለመቀበል በአንፃሩ የገዢው ፓርቲ ደጋፊ በሆኑ ማህበራት ላይ በክብር እንግድነትና በንግግር አድራጊነት መገኘቱ የሚያመለክተው የኃይሌ የፖለቲካ ተሳትፎ በገዢው ፓርቲ ይሁንታ ያገኘ አስመስሎበታል ብለዋል።
ሻለቃ ኃይሌ ወደ ፓርላማ ለመግባት የወሰነውም የግሉን ክብርና ዝና መሻት እንጂ አዳዲስ የፖሊሲ ኀሳቦችን በመያዝ እንዳልሆነ የገመቱት አቶ ሀብታሙ፤ ለሻለቃ ኃይሌ አመቺ መንገድ ሊሆን የሚችለው በፓርቲ በኩል ተደራጅቶ ከፕሬዝዳንትነቱ ይልቅ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ የተረከበ እንደሆነ ብቻ ነው ብለዋል።
የመጀመሪያው የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ እ.ኤ.አ. በ1996 አትላንታ በ10ሺ ሜትር በ2000 ሲዲኒ በ10ሺ ሜትር፣ በአለም ሻምፒዮና በ1993 በስቱትጋርት ፣ በጉተንበርግ አቴንስ፣ በሲቪላ የወርቅ ሜዳሊያ፣ በስቱትጋርት፣ ሲቪላ በ10ሺ የብር ሜዳሊያ እንዲሁም በኤድመንተን በ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ እና ሌሎችም በርካታ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል። (ዘሪሁን ሙሉጌታ፤ ሰንደቅ)
No comments:
Post a Comment