(ECADF) – ሰሞኑን የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት በጎንደርና ደሴ የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ሲያስተላልፉና ቅስቀሳ ሲያደርጉ ነው የከረሙት። ሂደቱ በራሱ ከፍተኛ ትግል የተካሄደበት ነበር፣ አባላቱ ሲታሰሩ ሲፈቱ ከርመዋል፣ በደሴ ቅስቀሳ ላይ የነበሩ የአንድነት አመራር አባላት በቀን ውስጥ ሁለት ጊዜ ታስረው ተፈተዋል። ኢህአዴግ/ወያኔ ሰልፉን በቀጥታ ለማገድ ከሞሞከር አንስቶ መላ ካድሬዎቹን አሰማርቶ ህዝቡ አንድነት በጠራው ሰልፍ ላይ እንዳይገኝ ሲያግባባና ሲያስፈራራ ሰንብቶ ነው ሰልፉ የተጠራበት ቀን ሀምሌ 7 እንዳይደርስ የለም የደረሰው።
ፖሊሱና የፖለቲካ ካደሬው አንድ አካል ሆነው በሚኖሩበት ኢትዮጵያ ህዝብን ከአደጋ እንዲከላከል ከህዝብ በሚሰበሰብ ገንዘብ ደሞዝ ተቆርጦለት የተሰማራው የፖሊስ ሀይል ያለምንም እፍረት የካድሬ ስራ ያከናውናል።
በጎንደር ሰላማዊ ሰልፈኛው የሚጓዝባቸው ጎዳናዎች መጋቢ መንገዶች በፌደራል ፖሊሶች ተዘግተው ውለዋል፣ አላማቸው በተቻለ መጠን የሰላማዊ ሰልፈኛውን ቁጥር መቀነስ ነበር። ይሁንና የጎንደር ህዝብ መንገዶችን እያሳበረ፣ የሚጥለው ዝናብና መንገድ የዘጋው የፌደራል ፖሊስ ሳይበግረው ሰልፉን ተቀላቅሏል።
ብቸኛው ተቃዋሚ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሴይፉ የተገኙበትና ንግግርም ያደረጉበት ስልፍ ደግሞ በደሴ ሞቅ ባለ ሁኔታ ተካሂዷል።
በደሴ የአንድነት ፓርቲ አመራሮች ኢህአዴግ ተቃዋሚዎች አባይ እንዳይገደብ ይፈልጋሉ… በሚል የሚረጨውን ፕሮፓጋንዳ ያመከነ ንግግሮች አድርገዋል።
አቶ ግርማ ሴይፉ “ኢህአዴግ በካድሬዎቹ አማካኝነት ነጻነታችንን ቀምቷል ነጻነታችንን ማስመለስና ወደፊትም እንዳይወሰድብን መከላከል ይኖርብናል” ብለዋል… አቶ ግርማ አያይዘውም “…የሚያሳዝነው ነገር ነጻነታችንን የሚቀሙን ካድሬዎች ለራሳቸውም ነጻነት የላቸውም…” ብለዋል።
በጎንደር እና ደሴ የተደረጉትን የሰላማዊ ሰልፎች የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታዎች መወያያ መድረክ (ECADF Paltalk room) በቀጥታ በዓለም ዙሪያ ላሉ ኢትዮጵያውያን ሲያስተላልፍ ውሏል።
No comments:
Post a Comment