Translate

Wednesday, July 3, 2013

የአንድነት ፓርቲ ሕዝባዊ ንቅናቄ ከጅምሩ በመንግስት መጠነ-ሰፊ ዘመቻ ተከፍቶበታል።

576820_643438789017118_1777115518_n
ኢሳት ዜና :-አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ‹‹የሚልዮኖች ድምጽ ለነጻነት››በሚል መሪ ቃል በጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ በመንግስት ሀይሎች እንቅፋት እየተፈጠረበት መሆኑን አስታውቋል።
ፓርቲው የመጀመሪያውን የአደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ በጎንደር ከተማ ሰኔ 30 ቀን 2005 ዓ.ም ለማድረግ በህገ መንግስቱ መሰረት ለሚመለከተው አካል የማሳወቂያ ደብዳቤ በማስገባት የቅስቀሳ ስራውን በጎንደርና አካባቢው መስራት ቢጀምርም፤ መንግስት በ አባላቱ ላይ ህገወጥ እስር እያካሄደ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
እንደ ፓርቲው መግለጫ፤ለቅስቀሳ ስራ ወደ ምዕራብ አርማጭሆ ተንቀሳቅሰው የነበሩ አራት የፓርቲው አባላት “ህገ ወጥ ወረቀት በትናችኋል” ተብለው ባሳለፍነው ቅዳሜ ሰኔ 22 ቀን 2005 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለውና ማክሰኞ ሰኔ 24 ቀን 2005 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው የአራት ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆባቸዋል፡፡

እስሩ፤ ህገ መንግስታዊ መብትን ለመጠቀም በተወሰደ እንቅስቃሴ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎች የተደረገ አፈና መሆኑን የገለጸው አንድነት፤ ታሳሪዎቹ እንዲለቀቁና ይህንን ባደረጉ የጸጥታ ሃላፊዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ የዞኑን አመራሮች ቢጠይቁም የ አካባቢው ባለስልጣናት በአፈናቸው በመቀጠል ትናንት ማክሰኞ ረፋዱ ላይ በጎንደር ከተማ ቅስቀሳ ላይ የነበረን ሌላ የፓርቲውን አባል ማሰራቸውን ገልጿል።
በተያያዘ ዜና ከትናንት በስቲያ ሰኞ በጎንደር ከተማ ለሰላማዊ ሰልፉ የተዘጋጀውን በራሪ ወረቀት ሲያሰራጩ የነበሩት አቶ አምደ ማርያም እዝራ እና አቶ ስማቸው ግንቤ የተባሉ የፓርቲው አባላት በህገወጥ መንገድ መታሰራቸውን አንድነት ጨምሮ ገልጿል።
እንዲሁም ትናንት ማክሰኞ አቶ ማሩ አሻግር የተባሉ የዞኑ የአንድነት አመራር ማክሰኞ ዕለት የታሰሩ አባላትን ለመጠየቅ ወደ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ በሚሄዱበት ወቅት በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው መታሰራቸው ተገልጻል፡፡
በተጨማሪም በላይ አርማጨሆ ትክል ድንጋይ ከተማ አቶ እርሻው አደራጀው የተባለ የአንድነት አባል የሰላማዊ ሰልፍ ቅስቀሳውን የሚመለከት በራሪ ወረቀት በማሰራጨቱ መታሰሩን የገለጸው የፓርቲው ልሳን ፍኖተ-ነፃነት፤ በሰሜን ጎንደር ወገራ ወረዳ ተመሳሳይ በራሪ ወረቀት ሲበትኑ ከነበሩ አባላት መካከል አቶ ጄጃው ቡላዴ የተባሉ የአንድነት አባል በህገወጥ መንገድ ሲታሰሩ- አቶ ጋሻው ዘውዱ የተባሉ አባል ላይ በጥይት የግድያ ሙከራ ተደገርጎባቸው ማምለጣቸውን የሰሜን ጎንደር ዞን የአንድነት ፓርቲ አመራሮችን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል፡፡
የአንድነት ፓርቲ የህዝባዊ ንቅናቄ ግብረሀይል በፓርቲው አባላት ላይ እየተወሰደ ያለውን ህገወጥ እስርና የግያ ሙከራ አውግዞ፤የትኛውም የመንግስት ህገወጥ እርምጃ ከንቅናቄው እንደማይገታው አስታውቋል፡፡

No comments:

Post a Comment