~አንድ እርምጃ ወደኋላ ሁለት እርምጃ ወደፊት!
(ጌታቸው ሺፈራው)
ቴዲ አፍሮ ባህርዳር ላይ "ጃ ያስተሰረያል!"ን ዝፈንልን ተብሎ ሳይዘፍን ከመድረክ ወረደ፣ ሕዝብም ቅር ተሰኘ አሉ። ይህን ስሰማ በሁለቱም ጫማ ውስጥ ገብቼ አየሁት። የኮንሰርት ተሳታፊ እና ዘፋኙን ሆኜ!
ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁስሉ እየጠዘጠዘው ነው። ቴዲ የብሶቱን እንዲዘፍንለት ይፈልጋል። ባህር ዳር ደም ያልደረቀባት ከተማ ነች፣ ቁስሉ ያልጠገገ፣ በየጊዜው እየደማ ያለ ሕዝብ ነው። ትናንት እንኳ ሕዝን የወልዲያን ሰቆቃ ሰምቶ ነው ወደ ኮንሰርቱ የገባው። ሕዝብ የፍቅር ሳይሆን የትግል ዜማ፣ የብሶት ዜማ ነበር መስማት የሚፈልገው።
በሌላ በኩል ደግሞ ቴዲ አፍሮ "ይህን ከዘፈንክ አይቻልም" እየተባለ ፍዳውን አይቷል። ገንዘብ ከስሯል። ዋናው ገንዘቡ አይደለም። አድናቂዎቹን ማግኘት አልቻለም። ሌላው ቀርቶ ስለ መተባበር፣ ስለ ሕዝብ ፍቅር በአካል ተገኝቶ መስበክ አልቻለም! ከ "ጃ" አንፃር ካላየነው በስተቀር አብዛኛው የቴዲ ዘፈን ፖለቲካ ነው። ሀገር የመሰረቱትን እንደሰይጣን የሚጠሉ ገዥዎች ባሉበት ሀገር "ጥቁር ሰው"ን ያህል ፖለቲካ ያለ አይመስለኝም። ቴዲ በቅርቡ ያወጣው አልበም የተወደደው "ጃ ያስተሰራልን"ስላካተተበት አይደለም። ዝም ብሎ ዘፈን ስለሆነም አይደለም። ፖለቲካም ስለሆነ ነው። ተወዳጁ ቴዎድሮስ ካሳሁን ስለዘፈነውም ጭምር ነው!
በመከራ ያለ ሕዝብ ስሜት ለማንም ሊያስቸግር ይችላል። የባሰው ሕዝብ በስልት፣ ቀስ እያልክ ከምትነግረው አፍርጠህለት ግንባርክን ብትባል "ወንድ" ይልሃል። እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማደር የሚለውም ይህንኑ ነው። ይህ የሕዝብ ስሜት ከበደል ብዛት የመጣ ነው። የብሶት ነው!