መሳይ መኮንን
በእርግጥ ቄሮዎች ዛሬ ላይ ላቀጣጠሉት እምቢተኝነት እርሾው ቀደም ተብሎ የተዘጋጀ መሆኑን እዚህ ላይ መጥቀስ ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የትግራይ አገዛዝ ቤተመንግስት ከገባ ጀምሮ ትግል ነበር። በተለያዩ አካላት ሲደረግ የነበረው እልህ አስጨራሽ የነጻነት ተጋድሎ በቅብብሎሽ እዚህ ዘመን ላይ ደርሷል።
በተናጠልና በጋር የተደረጉ ንቅናቄዎች ያበሰሉት የኢትዮጵያውያን ትግል ለቄሮዎች መንገዱን በመጥረግ ረገድ አስተዋጽኦው በታሪክ በደማቁ የሚመዘገብ ነው። በተለይም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል ምንጊዜም የሚታወስ፡ በሰላማዊ እምቢተኝነት የኢትዮጵያውያንን የነጻነት ትግል አንድ ምዕራፍ ወደ ፊት የወሰደ ታላቅ ተጋድሎ መሆኑን መጠቀስ ግድ ይላል። እናም ቄሮዎች እንደዱላ ቅብብል የተጀመረውን የነጻነት ተጋድሎ አድምቀው ተያይዘውታል።የቄሮዎች ትግል በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መስመሩን በትክክል ይዞ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ከሚጋብዝበት መድረክ ላይ ወጥቷል። ክልላዊ ስሜት ያጠላበት፡ ለሌላው የሚጎረብጥ የሚመስለው፡ በመልዕክቱና በእንቅስቃሴው ሁሉን አሳታፊ ያልነበረው የቄሮዎች ትግል ወሳኝ ለውጥ አድርጓል። አዳማ፡ ጂማ፡ አምቦ በቄሮዎች የተላለፉት የቅርብ ጊዜ መልዕክቶች የሌላውን ኢትዮጵያዊ ልብ የሚከፍቱ፡ ለአብሮነት ትግል መደላድል የሚፈጥሩ በመሆናቸው በቄሮዎች ትግል ብዥታ ውስጥ ለነበረ፡ በጥርጣሬ የዳር ተመልካች ሆኖ ለሰነበተ ምላሽ የሰጠ የትግል አቅጣጫን ይዟል። እንግዲህ ሜዳውም ፈረሱም አለ። አብሮ ከመታገል ውጪ ምርጫ የለም። ለጋራ ድል በእኩል መስዋዕትነት መክፈሉ ለቀጣዩ አብሮነታችንም ዋስትናው እንደብረት የጠነከረ ይሆናል።
ለነገ የተጠራው ዘመቻ በቄሮውች እስከዛሬ ከተደረጉት አድማዎች የበለጠ ውጤታማና አገዛዙን ሽባ በማድረግ ረገድ ክፍተኛ ተጽዕኖ የሚፈጥር እንደሆነ ይሰማኛል። የቄሮዎች ትግል እያደገ፡ እየተመነደገ፡ በዕውቀትና ብልሃት እየተመራ ለመሆኑ የነገው ዘመቻ ትልቅ ማሳያ ነው። ነዳጅ ላይ የሚጠራ አድማ ውጤቱ የአገዛዙን የስልጣን ወንበር እስከመፈንቀል የሚደርስ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። ነዳጅ ያልገባበት የህይወታችን እንቅስቃሴ የለም። ነዳጅ ደምስር ነው። የአንድ ሀገር የጀርባ አጥንት፡ የሁለንተናዊ መዘውር አንቀሳቃሽ ሞተር ነው። እናም የነገው ዘመቻ ሀገሪቱን ቀጥ አድርጎ፡ ከየትኛውም እንቅስቃሴ ገድቦ፡ የሚያስቀር እንደሚሆን ይታመናል። በተለይ ለአገዛዙ ብርቱ ፈተና ከመሆን ባለፈ ሀገሪቱን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን አቅም የሚያሳጣው፡ ከቆየና ከጠነከረ ደግሞ እስከወዲያኛው የሚያሰናብተው ስለመሆኑ ከቶም አልጠራጠርም።
ነገ ተጀምሮ ለሳምንት የሚዘልቀውን የነዳጅ ዝውውርን የማስተጓጎል ዘመቻ እንዲሳካ የቄሮዎች ጥረትና መስዋዕትነት ብቻውን በቂ አይደለም። ውጤታማም አይሆንም። ከመቀሌ እስከ ሞያሌ፡ ከከቤንሻንጉል ጉምዝ እስከ ሀረር የተዘረጋ፡ ሁሉን ያሳተፈ፡ በሁሉም ክልል ተግባራዊ እንዲሆን ማድረግ ያስፈልጋል። የነዳጅ አቅርቦቱ በአብዛኛው በሱዳን በኩል የሚገባ በመሆኑ ከመተማ ጀምሮ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ የነገውን ዘመቻ በባለቤትነት ሊመራው ይገባል። በመተማ መስመር ከዚህ በፊት ከ5በላይ የነዳጅ ቦቴ ተሽከርካሪዎች እንደጧፍ የነደዱበትን አደጋ የጣሉት የሰሜኖቹ ፋኖዎች የነገውን ዘመቻ ተፈጻሚ ለማድረግ የሚገድባቸው ነገር ይኖራል ብዬ አላምንም። ከመተማ ጎንደር፡ ከመተማ ሁመራ የሚወስዱትን መንገዶች ለነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪዎች ዝግ ማድረግ፡ ለባለንብረቶችም መልዕክት በማስተላለፍ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ ከማስጠንቀቂያ ጋር ማሳወቅ ይገባል። ተደርጓልም ብዬ አምናለሁ።
የነገው ዘመቻ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር በወደቀችው፡ ደም በጠማቸው የአጋዚ ወታደሮች በታፈነችው፡ የትግራይ አገዛዝን የዕልቂት አዋጅ ለማስፈጸም በተሰማራው የመከላከያ ሰራዊት ማንቁርቷን በተያዘችው ኢትዮጵያችን የሚከናወን በመሆኑ መስዋዕትነቱ ከባድ ሊሆን ይችላል። ቄሮዎች ዘመቻውን በትንሽ መስዋዕትነት፡ በግዙፍ ስኬት ለማጠናቀቅ የሚያስችል ዕቅድ እንዳላቸው ስለማምን በዚህ በኩል ብዙም ስጋት አይኖረኝም። በዚህ ላይ የነዳጅ አመላላሽ ተሽከርካሪ ባለቤቶች ቢያንስ ንብረቶቻቸውን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲሉ፡ ገፋ ካለም ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ለመደግፍ ብለው ተሽከርካሪዎቻቸውን ከስምሪት ውጭ ያደርጋሉ የሚል ተስፋም ውስጤ አለ።
ጥንቃቄም ያስፈልጋል። የትግራይ አገዛዝ ከቄሮዎች ጥሪ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር ግን የእርስ በእርስ ግጭትንና ጥፋትን የሚጋብዝ መልዕክት አሰራጭቷል። በቄሮ ስም የተበተነው መልዕክት የነዳጅ ማደያዎችን በእሳት ማጋየት፡ በትግራይ ተወላጆች ንብረቶች ላይ ጥቃት መፈጸምና ሌሎች እርምጃዎች እንዲወሰዱ የሚጠይቅ ነው። ቄሮዎች እንዲህ ዓይነት ጥሪ አላደረጉም። እውነተኛው ጥሪ ግልጽና ጥርት ያለ ነው። የነዳጅ ተሽከርካሪዎች እንዳይዘዋወሩ ማድረግ ብቻ ነው። ወደ ሀገር ቤት የሚገቡና በውስጥም ነዳጅ የሚያመላልሱ ተሽከርካሪዎች ለአንድ ሳምንት ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆነው እንዲቆሙ የተጠራ ዘመቻ ነው። ከዚህ የሚጨምርም የሚቀንስም ዓላማ የለውም።
ከደህንነት አከባቢ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተውም በአዲስ አበባና በአንዳንድ የሀገሪቱ አከባቢዎች በተለይ በነዳጅ ማደያ አከባቢዎች ፍንዳታ ለመፈጸም አገዛዙ በስውር ተዘጋጅቷል። ይህን ሴራ ማክሸፍ የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው። አጥፍቶ ለመጥፋት ቆርጦ የተነሳው የትግራዩ አገዛዝ የቄሮውችን ትግል ጥላሸት ለመቀባትና የነገውን ዘመቻ በኢትዮጵያውያን ዕልቂት እንዲጠናቀቅ ሃላፊነት የጎደለው እርምጃ ሊወስድ መሆኑ ሾልኮ የወጣ መረጃ ላይ ተመልክቷል። በመሆኑም ህዝባችን ይህን አውቆ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል።
ነገ ሁላችንም ቄሮዎች ነን!!!!!!
No comments:
Post a Comment