~አንድ እርምጃ ወደኋላ ሁለት እርምጃ ወደፊት!
(ጌታቸው ሺፈራው)
ቴዲ አፍሮ ባህርዳር ላይ "ጃ ያስተሰረያል!"ን ዝፈንልን ተብሎ ሳይዘፍን ከመድረክ ወረደ፣ ሕዝብም ቅር ተሰኘ አሉ። ይህን ስሰማ በሁለቱም ጫማ ውስጥ ገብቼ አየሁት። የኮንሰርት ተሳታፊ እና ዘፋኙን ሆኜ!
ሕዝብ ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁስሉ እየጠዘጠዘው ነው። ቴዲ የብሶቱን እንዲዘፍንለት ይፈልጋል። ባህር ዳር ደም ያልደረቀባት ከተማ ነች፣ ቁስሉ ያልጠገገ፣ በየጊዜው እየደማ ያለ ሕዝብ ነው። ትናንት እንኳ ሕዝን የወልዲያን ሰቆቃ ሰምቶ ነው ወደ ኮንሰርቱ የገባው። ሕዝብ የፍቅር ሳይሆን የትግል ዜማ፣ የብሶት ዜማ ነበር መስማት የሚፈልገው።
በሌላ በኩል ደግሞ ቴዲ አፍሮ "ይህን ከዘፈንክ አይቻልም" እየተባለ ፍዳውን አይቷል። ገንዘብ ከስሯል። ዋናው ገንዘቡ አይደለም። አድናቂዎቹን ማግኘት አልቻለም። ሌላው ቀርቶ ስለ መተባበር፣ ስለ ሕዝብ ፍቅር በአካል ተገኝቶ መስበክ አልቻለም! ከ "ጃ" አንፃር ካላየነው በስተቀር አብዛኛው የቴዲ ዘፈን ፖለቲካ ነው። ሀገር የመሰረቱትን እንደሰይጣን የሚጠሉ ገዥዎች ባሉበት ሀገር "ጥቁር ሰው"ን ያህል ፖለቲካ ያለ አይመስለኝም። ቴዲ በቅርቡ ያወጣው አልበም የተወደደው "ጃ ያስተሰራልን"ስላካተተበት አይደለም። ዝም ብሎ ዘፈን ስለሆነም አይደለም። ፖለቲካም ስለሆነ ነው። ተወዳጁ ቴዎድሮስ ካሳሁን ስለዘፈነውም ጭምር ነው!
በመከራ ያለ ሕዝብ ስሜት ለማንም ሊያስቸግር ይችላል። የባሰው ሕዝብ በስልት፣ ቀስ እያልክ ከምትነግረው አፍርጠህለት ግንባርክን ብትባል "ወንድ" ይልሃል። እውነቱን ተናግሮ ከመሸበት ማደር የሚለውም ይህንኑ ነው። ይህ የሕዝብ ስሜት ከበደል ብዛት የመጣ ነው። የብሶት ነው!
ግን በእየ ግላችን እንኳ የምንቀንሳት፣ እንሰንብት፣ ውጭ እንቆይ "ኧረ እነዚህ ሰዎችኮ" የምንልበት አጋጣሚ በርካታ ነው። ገብስ ገብሱን የምናወራበት ብዙ ነው። የምንወደውንም "አታክረው፣ ምን ነክቶህ ነው?፣ ተው እነዚህ ሰዎች!፣ ተው ሞኝ አትሁን፣ አንዳንዴ ብልጠት ያስገልጋል……" እያልን ይደርሳል ከሚባለው ችግር ማይል ርቀን የምንፈራ ብዙ ነን። አንድን ትልቅ ጉዳይ ለማስፈፀም ከዋናው ያነሱ ነገሮችን የምንቀንስበት ጊዜ ብዙ ነው።"ልጆቼን ላሳድግ ብየ እንጅ፣ ትምህርቴን ብጨርስ ኖሮ፣ ውጭ ሀገር ብሆን……" የምንል ሞልተናል። ይህ ሁሉ የሰው ባዶ ፍራት አይደለም። የገዥዎቹ አረመኔነት ነው። እንዲያውም አዲስ የሚሆነው አለመፍራት ነው!
ሰለሞን ተካ ነገ የቴዲን "ጃ ያስተሰረያልን" ቢዘፍን "ይቅር" የሚለው ሰው ያለ አይመስለኝም። ቴዲ ሌላ ሙዚቀኛ ቢዘፍነው ላይሰማ የማይችል ዘፈን ሲዘፍን እንኳ የሚሰማው ሕዝብ "የእኔ ነው!" ስላለው ነው። የ"እኔ ነው" የምትለውን ደግሞ የፈለከውን ሁሉ ስላላደረገልህ አይንህን ለአፈር ልትለው አይገባም። እንዲያውም የሚወደው አካል የጠየቀውን ያልፈፀመው ምን የከበደ ነገር ገጥሞት ይሆን ብለን መጠየቅ የጥሩ ወዳጅ ባህሪ ነው።
ቴዲ ቋሚ ስራው ዘፈን ነው። ሁሌም ስለዘፈን፣ ስለ ደጋፊዎቹ ነው የሚያስበው። ትናንት ባህርዳር ስቴዲዬም የተገኘው ሕዝብ ደግሞ በአብዛኛው ዘፈንን በተወሰነ የመዝናኛ ጊዜ ብቻ የሚያስታውሰው ነው። ቴዲን ለስንት አንዴ ቢሰማው ነው። ከዘፋኞች ሁሉ ሊያስቀድመው ቢችልም ቴዲ አድማጮን የሚያስበውን ያህል ቴዲን አያስበውም። ቴዲ ለታዳሚው ከዘፋኞች መካከል አንዱ ነው። ዋነኛው ቢሆንም። ለቴዲ ግን ብቸኛው አድማጩ ሕዝብ ነው። ትናንት "ዝፈንልን" ብሎ ለምኖ ሳይሆን ሲቀር ቅር ካለው ሕዝብ በላይ፣ እየተለመነ መዝፈን ያልቻለው ቴዲ ቅሬታ የባሰ እንደሚሆን መገመት ይቻላል።
ቴዲን የሚወደደው የሕዝብ ስሜትን ስለተረዳ ነው። ግን ጃ ያስተሰረያልን ዘፍኖ ቁጭ ቢል አሁን ያገኘውን የሕዝብ ፍቅር ማግኘት ባልቻለ ነበር። በተደጋጋሚ የሕዝብን ስሜት የሚገልፁ ዜማዎች በማውጣቱ ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ የከፈለው ዋጋም ይበልጥ ተወዳጅና ታማኝ አድርጎታል። በዚህ ሁሉ ጊዜ ቴዲ ብቻ የሚያውቃቸው ለሕዝብ ያልተገለፁ በደሎች ደርሰውበት ይሆናል። እሱ የበገነበትን፣ የተቆጨበትን፣ ምን አልባት ያለቀሰበትን ሁሉ አልተጋራነውም ይሆናል። እሱ ግን የሕዝብን ስሜት በአደባባይ ገልፆአል። ዛሬ አንድ ዘፈኑን ለመዝፈን ሲከበድ ጭንቀቱን ልንጋራው ይገባል። የምር ስንወደው ቢጨንቀው እንጅ በእኛ አይጨክንም ነበር ማለት ነበረብን። የምንወደው ሰው ለእኛ ስሜት ግዴታ እንዳለበት ሁሉ እኛው ለውሳኔው ቦታ ልንተውለት፣ ለእሱ ስሜትም ግዴታ ሊኖርብን ይገባል።
እንደኔ ቴዲ አድናቂዎችን ማግኘት ይፈልጋል። ይህን ሲያደርግ የተደራደረው ነገር “ጃ ያስተሰረያልን” አለመዝፈን ነው። ይህ ለእሱ ልብ የሚሰብር ሊሆን ይችላል። ግን ደግሞ ያለው አንድ ዘፈን ብቻ አይደለም። በሌሎቹ ዜማዎች አድናቂዎቹን እያገኘ፣ አሳካለሁ የሚለውን ለመተግበር ያቀደ ይመስለኛል። ቀስ በቀስ……እንዲሉ። ከአማራ ቲቪ ጋር ከነበረው ቆይታ መረዳት እንዳሚቻለው ስለ ሕዝብ ፍቅር፣ ታሪክ……መስበክ ይፈልጋል። የተወሰነውን አጥቶ ካጣው የተሻለ ነገር ማድረግ ይፈልጋል። ፖለቲከኞቹ ሁለት እርምጃ ወደፊት አንድ እርምጃ ወደኋላ እንደሚሉት ማለት ነው። አንድ እርምጃ ያተርፋል ማለት ነው! ትርፍና ኪሳራ አስልቶ ማለት ነው። ጃ ያስተሰረያልን ብቻ ከስሮ የምኒልክን ታሪክ፣ የቴዎድሮስን ታሪክ፣ የሙስሊም ክርስትያኑን ታሪክ………መስበክ ፈልጓል።
እኔ በበኩሌ ይህ መንገድ አዋጭ ይመስለኛል። እኛ የለመድነው ወደፊት ገፍተን ቁም ስንባል “ቁም ተብያለሁ፣ አይታችኋል” ብለን እማኝ ቆጥረን መቆም ነው። አሊያም ይህ ካልሆነ ፈቀቅ አልልም ብለን ባለበት መርገጥ ወይጭራሽ ቀኝ ኋላ ዙር ነው።
ከምንም በላይ ግን ቴዲ ዘፈነ፣ ንዋይ አዜመ፣ እኛ የራሳችን ጥቅምና ጉዳት ምን ሊሆን ይችላል፣ ምን ሊሆንስ ይገባል ብለን አንቆጥርም። ከፍ ለማድረግ አንጥርም። ያ በሆነበትም ግን ሕዝብ ስሜቱን ገልፆአል። ከፍ ለማድረግ ብንጥር ደግሞ ከዚህ የተሻለ ሊሆን በቻለ ነበር። ቴዲን ከመጠበቅ ከራሳችን የሚጠበቀውንም ማድረግ እንችል ነበር።
ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ከኮንሰርቱ ባህርዳር ምን ልታገኝ እንደምትችል እያወራን ነበር። ብዙዎቻችን በረባ ባረባው ስብሰባ፣ ኮንፈረንስ፣… እየተባለ የት የት እንደሚደረግ እንኳ መረጃው ላይኖረን ይችላል። በምሽት ዜና ዘገባዎች የሚታዩ ስብሰባዎች የት ከተማ፣ የት ሆቴል እንደሚደረጉ እንኳ አስበነው አናውቅም። በቴዲ ኮንሰርት የባህርዳር ባጃጆች፣ ሆቴሎች፣ ታክሲዎች፣ ማተሚያ ቤቶች፣ ጌጣጌጥ የሚሸጡ ወጣቶች የሚያገኙትን መንግስት በአንድ ቀን ቀርቶ በወር በጀት አይመድብላቸውም።
ከቴዲና ከጃ ያስተሰረያልስ ማን ይበልጣል? የወደድነው በዚህ ዘፈን ብቻ ነው? ከወደድነው ሊዘፍን ያልቻለበት ምክንያትስ ለምን አላስጨነቀንም? ጃ ከእኛ እና ከቴዲ ከማን ይቀርባል? ከፈጣሪው ቴዲ እና ከአድማጮቹ የጃ ያስተሰረያል መከልከል ማንን ያመዋል?
Casinos Near Trump International Casino, Atlantic City, NJ
ReplyDeleteA 진주 출장샵 map showing casinos and other 당진 출장안마 gaming facilities located near 계룡 출장샵 Trump International Casino, Atlantic City, NJ, 안양 출장마사지 including 김해 출장마사지 casinos, cheques,