Translate

Monday, January 8, 2018

የኤርሚያስ ለገሠ ማስታወሻ ለዶ/ር አቢይ አህመድ

ሰላም ላንተ ይሁን።
ይህን ማስታወሻ የምፅፍልህ የምከትበው ነገር ላታስበው ትችላለህ ከሚል እምነት ተነስቼ አይደለም። በዙሪያህ ያሉ የድርጅቱ ሃላፊዎች እና አማካሪዎችም ያጡታል ከሚል ጥራዝ ነጠቅነት የመነጨ አይደለም። ነገር ግን በፓርቲው የፕሮፐጋንዳ እና ድርጅት እቅድ የማውጣት እና አፈፃፀሙን የመከታተል ስራዎች ላይ ቆይታ አድርጐ እንደነበረ ሰው ቀለል ያሉ ምክረ ሐሳቦችን ለመሰንዘር ነው። እነዚህ አስተያየቶች ቀላልና ህውሃት ቀርጾ ለሩብ ክፍለ ዘመን እየተገበረ ካለው ” ህጋዊ ማእቀፍ” ሳትወጡ ልትፈፅሙት የምትችሉት ናቸው።
ካልተቀየረ በስተቀር የድርጅትና ፕሮፐጋንዳ እቅድ ስታወጡ የሁኔታዎች ትንተና ( SWOT analysis) እንደምታደርጉ አውቃለሁ። ከእነዚህ የሁኔታዎች ትንተና ተነስታችሁ በአመቱ የምትፈፅሟቸው ቁልፍ እና አበይት ተግባራት እንደምትዘረዝሩም እገምታለው። በሌላ በኩል ይህ ከባድ ሃላፊነት በአንተ ጫንቃ ላይ እንደወደቀ ደግሞ ከያዝከው ስልጣን በመነሳት መገመት ይቻላል። መቼም እንደ ሰገሌው ዘመን ህውሓት በትግርኛ እቅድ አውጥቶ በአማርኛ እና ኦሮምኛ ተርጉማችሁ ወደ ስራ አውሉት የሚለው ዘመን ታሪክ የሆነ ይመስለኛል። እርግጥ እነ አባይ ፀሀዬና በረከት ስምኦን ይሄን ሊያደርጉት አይችሉም ብሎ መገመት ግን የዋህነት ነው። ይሁን እንጂ የበላይ አለቃህ የሆነው ለማ መገርሳ ” ቀዳድጄ ቅርጫት ውስጥ ከተትኩት!” እንዳለው አንተም የአለቃህን አርአያነት እንደምትከተል አልጠራጠርም። የፈጠነ አስተያየት ቢሆንም በአጭር ጊዜ ያሳየኸው የአመራር ጥበብ ለዚህ አገላለጤ መነሻ ነው።

በቅርብ እርቀት እንደተመለከትኩት አንተም ሆነ አለቃህ ለማ መገርሳ ” የጥሩ መሪ ባህሪያት” እንደተላበሳችሁ ብዙ ኢትዬጲያውያን ምስክርነት እየተሰጡ ነው። አንዳንድ የቅርብ ወዳጆቼ ከዚህ በኃላ ብትሳሳቱ እንኳን ኢትዬጲያዊነትን የሰቀላችሁበት ማማ ታሪክ የሚያስታውሰው ነው በማለት በግላጭ እየመሰከሩ ነው። በእኔ አመለካከት የሰው ልብ የሚሰርቅ ተወዳጅነት በእርግጥም የአመራር ጥበብና ቅመም በውስጣቸው የሌላቸው ሰዎች ሊኖራቸው አይችልም። በፍፁም። በተለይ ደግሞ ተቀባይነቱ ወደ ኔጌቲቭ ወርዶ የአመራር ትርምስ ውስጥ የገባው ህውሓት ጣዖት መሆኑ ባልተለወጠበት ሁኔታ የእናንተ ጐልቶ መውጣት የጥሩ መሪ ባህሪ ለመላበሳችሁ ምስክር ሊሆን ይችላል።
ጓድ አቢይ! እንደምታውቀው ጥሩ መሪ መሆን በተከታዬች እና በውጤት የሚሰጥ እውቅና ነው። አዴይር ጆን የሚባል የአመራር ሳይንስ ፀሀፊ ” ውጤታማ መሪ” በሚለው መፅሐፋ ጥሩ መሪነት የሚለካባቸው ሁለት ቁልፍ ጉዳዬችን ያነሳል።
የመጀመሪያው ተከታዬቹ ” እከሌ/ እከሊት መሪዬ ነው!” በማለት እውቅና ሲሰጡት የሚመጣ ነው። ይህም በተከታዬች ዘንድ ጥልቅ ስሜት፣ ሁለንተናዊ እይታ፣ የማሳመን እና የመወሰን ችሎታ እንዳላቸው ማረጋገጫ ሲሰጥበት እንደሆነ ይመሰክራሉ። ጥሩ መሪ አንደበተ ርቱዕ መሆን ይጠበቅበታል። የመሪነት ጨው ያላቸው መሪዎች አብሮ መቆምን፣ ከራስ ስልጣን በላይ ለሚመሩት ህዝብ ከፍተኛ ፍቅር እና አክብሮት አላቸው። ህይወታቸውን ይሰጣሉ። ከአገር እና ህዝብ በላይ የሚበልጥባቸው ነገር የለም።
አዴይር ጆን በሁለተኛ ደረጃ የሚያስቀምጠው መመዘኛ በመሪው የአመራር ጥበብ ድርጅቱ አላማውን በማሳካት መጠን የሚለካ ይሆናል ይላል። የድርጅቱን አላማ የማያውቅ መሪ ጥሩ መሪ ሊሆን አይችልም። የፓለቲካ ፓርቲ ደግሞ የሰዎች ስብስብ እንደመሆኑ መጠን ቀዳሚ አላማው ሰብአዊነት ነው። ሰብአዊነት የሚሰማው አመራር ያሻል። የፓለቲካ አመራር አላማ ከሰብአዊነት እና ከህዝብ እምነት ጋር መግጠም ይኖርበታል። በበቀልና በጥላቻ የተበከለ ልብ ይዞ የሚጓዝ መሪ የዜጐች መብት እና ክብር፣ አልፎም ሄዶ የአገር ፍቅር ሊኖረው አይችልም። (የአቶ መለስ ዜናዊ የሞቱ መንስኤ በበቀልና በጥላቻ የተበከለ ልብ ይዞ መጓዙ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል።)
ጓድ አቢይ!ቀደም ሲል ወዳነሳሁት ልመልስህና በያዝነው አመት እተገብረዋለው ብለህ የምታወጣው የድርጅትና ፕሮፐጋንዳ እቅድ ላይ ሊካተት ይገባል ወደምላቸው ቁምነገሮች ልመለስ። መላልሼ እንደገለጥኩት መክረ ሃሳቤ የእኔን ፍፁማዊ ፍላጐት የሚያሟላ አይደለም። እኔ ህውሓት ከኢትዬጲያ ፓለቲካ ምህዳር ተጠራርጐ እንዲወጣ የምፈልግ ሰው ነኝ። በሌላ በኩል አንተ በህውሓት የበላይነት ውስጥ እየኖርክ የእኔን ምኞት መቶ በመቶ ክተብልኝ የምል ማሞ ቂሎ አይደለሁም። በመሆኑም አንተ (የድርጅቱን የበላይ ሀላፊ!) የምጠይቀው በህውሓት የህግ ማእቀፍ ውስጥ ሆነህ እስከሚቀጥለው የድርጅቱ ጉባኤ ልትፈፅመው ይገባል የምለውን “ህጋዊ” ተግባራት ይሆናል። የማቀርባቸው አስተያየቶች በድርጅት እና ፕሮፐጋንዳ ዙሪያ የታጠሩትን ብቻ ይሆናል።
ተግባር አንድ:- በኦህዴድ ውስጥ ያሉ ምንደኛ አመራሮች መመንጠር ህውሓት በውስጠ ድርጅት ትግል ውስጥ ቢሸነፍ ሕልውናቸው አጠያያቂ ከሚሆነው ክፍል ውስጥ በኦህዴድ ውስጥ ያሉ ተላላኪዎች ይሆናሉ። እነዚህ ዘወትር ” ከጳጳሱ ቄሱ” ለመሆን ሲፍገመገሙ የነበሩ የኦህዴድ አመራሮች በቀጣዩ ግምገማና ድርጅታዊ ጉባኤ መመታት ከቻሉ ማረፊያ ያጣች ወፍ መሆናቸው አይቀርም። ለማ መገርሳ( የኦህዴድ ሊቀመንበር) እና አንተ ( የፅህፈት ቤት ሀላፊ) በያዛችሁት ቁመና መቀጠል ከቻላችሁ የምንደኞቹ እጣ ፋንታ ከፓለቲካው መድረክ መወርወር ይሆናል። ህውሓትም ቁመናው ስለተዳከመ እና ስለሚፈራ ከአሸናፊዎቹ ጋር በማበር አብሮ ወርዋሪ ይሆናል። በመሆኑም የድርጅት እና ፕሮፐጋንዳ እቅድ የመጀመሪያ ተግባሩ እነዚህን ተላላኪዎች ከድርጅት ስልጣን ማባረር ሊሆን ይገባል። ወርቅነህ ገበየሁን፣ ድሪባ ኩማን፣ አብድላዚዝን፣ ፍቃዱን ፣ እሸቱ ደሴን…ወዘተ ከድርጅት ስልጣን ማእከሉ ማባረር የእናንተ ስልጣን በመሆኑ የህጋዊነት ጥያቄ የሚነሳበት አይደለም። ኩማ ደመቅሳን፣ ግርማ ብሩን፣…ወዘተ ከጡት አባትነት ገሸሽ ማድረግ በተመሳሳይ ቀላል ነው። ይህም ሆኖ የአልሞት ባይነት ተጋድሎ ሊያደርጉ ቢችሉም የሚያመጡት ለውጥ አይኖርም።
ተግባር ሁለት:- የኢህአዴግ ሊቀመንበርነት እና የፅህፈት ቤት ሀላፊነቱን መረከብ ጓድ አቢይ! ለኢህአዴግ ቁመናም ሆነ የአባላት ብዛት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደረጋችሁት እናንተ ናችሁ። የህውሓት እና ደኢህዴን አባላት ተደምረው የእናንተ በእጥፍ ይበልጣል። የኦሮሞን ህዝብ ወክላችኃል የሚል እምነት ባይኖረኝም እናንተ ” ወክለናል” ያላችሁትን ተቀብዬ በህዝብ ብዛትም ማንም አይደርስባችሁም። ከዚህ በተጨማሪም ኢህአዴግ በአብዛኛው የሚያገኘው ገቢ አባል ድርጅቶቹ ድጐማ የሚሰጡት እንደሆነ ይታወቃል። ከፍተኛ ድጐማ የሚመጣው ከኦህዴድ በመሆኑ ሊቀመንበሩነቱንም ሆነ የፅህፈት ቤት ሀላፊነቱን መረከቡ ፍትሐዊ ነው። ተገቢም ነው። ከሁሉም በላይ በብቃትና ኢትዬጲያዊነት በኢህአዴግ ውስጥ የሚስተካከላችሁ ባለመኖሩ ወንበሩን በውድም ይሁን በግድ መንጠቅ ይኖርባችኃል።
ተግባር ሶስት:- የ18 ቀኑን የኢህአዴግ ሰአኮ ግምገማ እና በቀጣይ የኦህዴድ ሰአኮ እና ማእከላዊ ኮሚቴ የሚያደርገውን ግምገማ እንደ ወረደ ይፋ ማድረግ።
ጓድ አቢይ! በቤተመንግስት የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ(ሰአኮ) ግምገማ ያደረጋችሁት ትግል ህዝቡ ሳይቆራረጥ እንዲያዳምጠው እና የህሊና ፍርዱን እንዲሰጥ በይፋ መጠየቃችሁን ሰምቻለሁ። ይሄ ውሳኔያችሁ ለድርድር የሚቀርብ መሆን የለበትም።
እስከማውቀው ድረስ የቀረፃውን ስራ የሚሰራው የኢህአዴግ ፅህፈት ቤት ዶክመንቴሽን ክፍል ነው። ዶክመንቴሽን ክፍሉ ደግሞ የብሔር ድርጅቶቹ ኮፒ አድርገው ለመውሰድ ጥያቄ ካቀረቡ የመስጠት ግዴታ አለበት። አይደለም ድርጅቶቹ የሁሉም ፓርቲ አመራሮች ለጥናት አሊያም ዶክመንት ለማዘጋጀት ከጠየቁ ዶክመንቴሽን ክፍል ሄደው መጠቀም ይችላሉ። ዛሬም ቢሆን የተለወጠ ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም።
በሌላ በኩል የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚውን ግምገማ ህውሓት ከድርጅቱ ህግ በላይ ሆኖ መስጠት ካልቻለ ሌላ አማራጭ መከተል ይቻላል። የኦህዴድ ስራ አስፈፃሚ ፣ ማእላዊ ኮሚቴ እና የጉባኤ ስብሰባውን በቀጥታ ስርጭት ማስተላለፍ። በእነዚህ ስብሰባዎች በቤተመንግስት ያነሳችሁትን መከራከሪያዎች በግልፅ ማቅረብ ያስፈልጋል። ይሄን አለማድረግ የፈጠራችሁትን አመኔታ ከመሸርሸሩም በላይ አሁንም ተላላኪዎች ናቸው የሚለውን ስማችሁን ትንሳኤ የሚያረጋግጥ ይሆናል። ይሄን አለማድረግ በሸፍጥ ላይ ለተመሰረተው የህውሓት ፓለቲካ ተጠልፎ በመጣል ታሪካዊ ስህተት መፈፀም ነው። ኢትዬጲያዊነት የሚባለው ስሜት በሚተናነቃቸው እግር ስር በመውደቅ ማንሰራራት የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
ተግባር አራት: – ሶህዴፓ ወደ ኢህአዴግ የሚቀላቀል ከሆነ ግንባሩን ጥሎ መውጣት በአብዲ ኢሌ የሚመራው ሶህዴፓ ወደ ኢህአዴግ ለመቀላቀል ከህውሓት አረንጓዴ መብራት እንደበራለት የህውሓት የደም አባላት ነግረውናል። ጓድ አቢይ! አንተም ሳታዳምጠው የቀረህ አይመስለኝም።እነዚህ በሚሊዬን የሚቆጠር ገንዘብ ከአብዲ ኢሌ የሚከፈላቸውና የሰውየውን የፕሮፐጋንዳ ማሽን በኮንትራት የወሰዱ የአድዋ ልጆች ከጀርባ ግፊት እንዳደረጉ የሚያጠያይቅ አይደለም። አላማውም ለህውሓት ተጨማሪ አቅም መፍጠር እና ኦህዴድን ከጥቅም ውጭ ማድረግ ነው። ይሄ ሸፍጥ አይገባችሁም ከሚል አይደለም። ነገር ግን ግንባሩን ለቃችሁ እንደምትወጡ በአደባባይ መናገሩ ገንዘብ እየተከፈላቸው ህዝብ ከህዝብ የሚያጨፋጭፋትን የአድዋ አወናባጆች ኩምሽሽ ያደርጋል። በሂደትም በመካከለኛ ጊዜ ውስጥ የራሳችሁን ጥቅም በተሻለ ደረጃ ለማስጠበቅ ኢህአዴግን ለቆ ለመውጣት የምታደርጉትን ሩጫ መደላድል ያመቻቻል። መቼም የኦህዴድ በኢህአዴግ ዣንጥላ ውስጥ መገኘት በኢትዬጲያውያን ዘንድ ከመሰደብና ከመናቅ ውጭ ያተረፈላችሁ ነገር እንደሌለ ጠንቅቃችሁ ታውቁታላችሁ።
ተግባር አምስት:- ኦፌኮን ይቅርታ መጠየቅና በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስ የፓለቲካ ምህዳሩን ማመቻቸት ጥሩ መሪ የለውጥ ሐዋርያ ነው። ለመሰረታዊ ለውጥ ያልተነሳሳ ሰው መሪ መሆን አይችልም። መሰረታዊ ለውጥን መምራት ደግሞ የእሳት ወላፈኑንም ሆነ የጥይት አረርን ቀድሞ ለመቀበል ዝግጁነት ይጠይቃል። በሌላ በኩል ጥሩ መሪ ራሱን በተሻሉ መሪዎች ለመተካት ማመቻቸት ይኖርበታል።
ለሁሉም ግልፅ ሆኖ እንደሚታየው ፕሮፌሰር መረራን ጨምሮ የኦፌኮ አመራሮች እና አባላት ብሔራዊ ውርደትን ላለመቀበል፣ ንቅዘት እና የሞራል ድቀትን ለመታገል፣ ዘረኝነት እና ኢ-እኩልነትን ለማስቀረት መስዋእትነት ከፍለዋል። መረጃና ማስረጃ ላይ ተደግፈው የህውሓት አገዛዝን ገበና እርቃኑን የሚያስቀረውን፣ ቅጥፈቱንና ውስልትናውን የሚያጋልጥ ስራ ሰርተዋል።
የለማ እና አቢይ አመራር ለዚህ የኦፌኮ የነፃነት ትግል ለተከፈለ መስዋእትነት እውቅና መስጠት ይኖርበታል። እግራቸው ስር ወድቆ ይቅርታ መጠየቅ አለበት። ይሄን ማድረግ ጀግንነት ነው። ሰዋዊም ነው።መሪዎች ጥፋት ተሰርቶ ሲመለከቱ ” ስህተት ሰርቻለሁ፣ አጥፍቻለሁ፣ ይቅርታ ይደረግልኝ!” የሚሉ ከሆነ በአርአያነት እንዲታዩ ያደርጋቸዋል። በኢትዬጲያ ህዝብ ዘንድ አክብሮት እና ግርማ ሞገስ ይላበሳሉ። እውነቴን ነው የምልህ ይቅርታ መጠየቅ የትልቅነት ምልክት ነው። የኢትዬጲያ ህዝብ ለማ መገርሳ እና ፕሮፌሰር መረራ ከአንድ መሶብ እንጀራ እየቆረሱ ሲበሉ ማየት ይፈልጋል። እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ ከሌሎች የዲሞክራሲ ሀይሎች ጋር መሪውን ጨብጣችሁ ” ኢትዬጲያዊነት ሱስ ነው!” እንድትሉ ይፈልጋል።
መውረድ ይሆንብኛል እንጂ ለኦህዴድ ከህውሓት ይልቅ ኦፌኮ ቅርቡ ነው። ለዚህ ምስክር ጥራ ብባል እሩቅ መሄድ ሳያስፈልገኝ አንተ እና አለቃህን እማኝ ማቅረብ እችላለሁ። እስከገባኝ ድረስ ኦፌኮ ከጅምሩ ጀምሮ በኢትዬጲያዊነት ላይ ጥያቄ ያለው ድርጅት አይደለም።የድርጅቱ ፕሮግራም ላይም ” አንድ ሰው አንድ ድምፅ” መሆኑን አውቃለሁ። ይህ ከሆነ ዘንዳ በሂደት ኦህዴድ ኢህአዴግን ህጋዊ በሆነ መንገድ ፍቺውን ፈፅሞ ከኦፌኮ ጋር ግንባር መፍጠር ይችላል። በሂደትም ወደ ውህደት በመሄድ ከሌሎች ዲሞክራሲያዊ ሀይሎች ጋር ጥምረት መፍጠር ይችላል። አልፋ እና ኦሜጋው የኢትዬጲያ አንድነት እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በሚካሄድ ምርጫ ስልጣን ለመያዝ እስከሆነ ድረስ። አበቃው!!

No comments:

Post a Comment