ጉዳዩ፦ አለም አቀፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግበረሀይል እያደረገ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ተአቅቦ ዘመቻ ስለመደገፍ
የተከበራችሁ ኢትዮጵያዊያን፣
ከዲሴምበር 29 ቀን 2017 ጀምሮ በአለም አቀፍ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ግበረሀይል አስተባባሪነት የውጭ ምንዛሬ ተአቅቦ ዘመቻ እየተደረገ ይገኛል። የዘመቻው አላማ የገዳዩ እና ዘራፊው የህወሓት መንግስት በውጭ አገራት ከሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን የሚያገኘው የውጭ ምንዛሬ እንዲቀንስ ማድረግ እና የአገዛዙን ኢኮኖሚያዊ አቅም ማዳከም መሆኑን ትብብራችን መረዳት ችሏል። በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የወገናቸውን የነጻነት ትግል የማገዝ ሀላፊነት እና አቅም እንዳላቸውም ትብብራችን ያምናል። ግብረሀይሉ ያወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው እና ትብብራችንም እንደሚያምንበት፣ ኢትዮጵያዊያን ከታች የተዘረዘሩትን ጥሪዎች ተግባራዊ ለማድረግ ከተንቀሳቀሱ፣ በአገዛዙ ላይ ትርጉም ያለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ማድረግ ይቻላል።
1. ዌስተርን ዩኔዮን እና መኒ ግራምን ከመሳሰሉ ከአገዛዙ የባንክ ስርአት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ባላቸው መደበኛ የገንዘብ መላኪያ መንገዶች ገንዘብ ወደ አገር ቤት ከመላክ ይልቅ ሌሎች አማራጮችን ማፈላለግ እና ገንዘቡን መላክ።
2. ሌሎች የመላኪያ አማራጮች ካልተገኙ እና የግድ በባንክ በኩል ገንዘብ መላክ ካለበት፤ የቤተሰብን የኢኮኖሚ ሁኔታ ባገናዘበ መልኩ የሚላከውን ገንዘብ መጠን መቀነስ፤ ከተቻለም ለተወሰነ ጊዜ ማቆም።
3. ንግድም፣ ግንባታም ጥቅም የሚኖረው አገር ስትረጋጋ እና ሰላም ስትሆን ነው። በዚህ ወቅት ወገናችን ነጻነቱን እና ሰብአዊ ክብሩን ለማስከበር በርካታ መስዋእትነት እየከፈለ ይገኛል። የህዝቡ እምቢተኝነትን ተከትሎ አገዛዙ ከፍተኛ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ የገባ ሲሆን አገሪቱም የተረጋጋ ሰላም አጥታለች። የአገዛዙ ባለሟሎች ሳይቀሩ ንዘብ ማሸሽ በጀመሩበት በዚህ ጊዜ ለንግድ፣ ለግንባታ እና ገንዘብ ለማስቀመጥ ሲባል ዶላር፣ ይሮ፣ ፓውንድ እና ሌሎች የውጭ ገንዘቦች ወደ አገር ቤት መላክ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። በተጨማሪም፣ የህዝቡን የነጻነት ትግል ለማገዝ ሲባል፣ ንግድ እና ግንባታ ያሰባችሁ ወገኖች አገር እስክትረጋጋ እና የህዝቡ መብት እስኪከበር ድረስ እቅዳችሁ እንዲዘገይ ማድረግ።
አጠቃላይ የዘመቻው አላማ እና የቀረቡት ጥሪዎች ትብብራችን በሙሉ ልብ የሚደግፋቸው እና ለተግባራዊነታቸውም የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ተግቶ እንደሚሰራ በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እንወዳለን። በመሆኑም፣ ትብብራችን ለዘመቻው ያለውን ሙሉ ድጋፍ እየገለጸ፤ ባጠቃላይ በውጭ አገራት የሚኖረው ማህበረሰብ እና እንዲሁም የትብብራችን አባል ድርጅቶች እና ደጋፊዎች የዘመቻው አላማ እንዲሳካ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ ያቀርባል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ያሸንፋል!!
የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ድርጅቶች ትብብር
ግልባጭ፦ ለሁሉም የሚዲያ ተቋማት፣ የየአካባቢው ሬዲዮኖች እና ለማህበራዊ ሚዲያ ተሳታፊዎች
No comments:
Post a Comment