መሳይ መኮንን
ያለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ትልልቅ ክስተቶች የተሰተናገዱበት ነው። ተስፋና ስጋት፡ ብርሃንና ጽልመት፡ አንድነትና መነጣጠል፡ ከፊታችን ተደቅነው ጉዟቸንን እንድናሳምር፡ መንገዳችንን እንድንመርጥ፡ አካሄዳችንን እንድናስተካክል፡ እድል እጣፈንታችንን እንድንወስን ከሚያስችለን ዋናው ምዕራፍ የተጠጋን ይመስላል። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ህወሀት ክፉኛ ቆስሏል። ከእንግዲህ በመንግስትነት የመቆም እድል የለውም። ኳሷ በኢትዮጵያውያን እግር ስር ገብታለች። የጊዜ ጉዳይ ነው። በጣም ጥንቃቄ የሚያስፈግበት ወቅት ላይ ነን። ጥሞና ያስፈልገናል።
አዎን! እስረኞች ተፈተዋል- የሚቀሩ ቢኖሩም። አቶ ሃይለማርያም ስልጣን ለቋል- ስልጣን ባይኖረውም። አስቸኳይ አዋጅ ተደንግጓል- ለውጥ ባያመጣም። ህዝባዊ ትግሉ ተጠናክሯል- በፈረቃ መሆኑ ባይቀርም። ይህ ሁሉ የሆነው በዚህ ሳምንት ውስጥ ነው። በኢትዮጵያ የ27 አመታት የትግራይ ነጻ አውጪ የአገዛዝ ዘመን እንደዚህ ሳምንት ክስተቶች በፍጥነት ተደራርበው የመጡበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም። እነኚህ ክስተቶች ወዴት ይመሩናል? በእርግጥ ቁልፍ ጥያቄ ነው።
የእስረኞች መፈታት
ጀግኖቻችን ነጻ ሆነዋል። ዶ/ር መረራ ተፈተዋል። እነበቀለ ገርባ ከቤተሰቦቻቸውና ከህዝባቸው ጋር ተቀላቅለዋል። እክንድር ነጋ፡ አንዱዓለም አራጌ፡ እማዋይሽ ዓለሙ፡ አህመዲን ጀበል፡ ሌሎችም ከትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር የግዞት ማዕከላት ወጥተዋል። ብ/ጄ ተፈራ ማሞ፡ ብ/ጄ አሳምነው ጽጌ ኮ/ል ደመቀ ዘውዴ፡ ወጣት ንግስት ይርጋና ሌሎች እንዲፈቱ ተወስኗል። እሰየው ነው። የሚቀሩ ጀግኖቻችን አሉና እንጠብቃለን።
የዋልድባ አባቶች ከአረመኔዎቹ እጅ አልወጡም።ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ከድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ናቸው። ዮናታን ተስፋዬ አሁንም በዚያ አስቀያሚ እስር ቤት ውስጥ እንደተቆለፈበት ነው። ፍቅረማረማርያም አስማማው ከወጣትነት እድሜው ተቀንሶ ከገባበት የማጎሪያ እስር ቤት አልወጣም። አንዳርጋቸው ጽጌ ምን ላይ እንዳለ አናውቅም። በሺዎች የሚቆጠሩ፡ በስም የማናውቃቸው፡ ጀግንነታቸው በወርቃማ መዝገብ ላይ የሚቀመጥላቸው ወንድምና እህቶቻችን አሁንም በትግራይ ደህንነቶች ስቃይና መከራውን እየተጋቱ ነው። ሁሉም ነጻ መሆን አለባቸው። የታሰሩበት ምክንያት አንድ ነው። የሚፈቱበት ምክንያት መለያየት የለበትም።
የትግራዩ ነጻ አውጪ ግንባር እጁ ተጠምዝዞ መፍታቱ እርግጥ ነው። የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት፡ ብሄራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚል እንዲፈቱ ተወስኗል የሚለው ጨዋታ ካድሬዎቹን ካረጋጋለት፡ ካጠገበለት ይበቃል። ለእኛ አይመጥንም። የተፈቱት በሙሉ በአንድ ቃል የሚመሰክሩት ''ያስፈታን ህዝባችን ነው። የህዝብ ጉልበት ነጻ አውጥቶናል'' በሚል ነው። የኢትዮጵያውያን ወጣቶች ክርን አለኝታ መከታችን ነው። ወጣት የነብር ጣት። የእነ ደብረጺዮንን እብሪት ያስተነፈሰለን፡ የጌታቸው አሰፋን ድንፋታ ያስታገሰልን፡ የሳሞራ የኑስን ጥጋብ ያበረደልን፡ የአባይ ጸሀዬን እብጠት ኩምሽሽ ያደረገልን የኢትዮጵያ ወጣቶች ተጋድሎ ክብር ምስጋና ይግባው። በደማቅ ቀለም በታሪክ መዘገብ ላይ የሚሰፍር ታላቅ ተጋድሎ። ኢትዮጵያ እስክትፈታ የማይቆም የነጻነት ጉዞ።
የተፈቱት ጀግኖቻችን በእስር ዘመናቸው ከመረጃ ጋር ተቆራርጠዋል። የውጭ ሚዲያ አያገኙም ነበር። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነውን ሲሰሙ የነበረው ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ብቻ ነው። አያነቡም። አይጽፉም። ፍጹም ጨለማ ውስጥ እንደነበሩ ከማንም የተሰወረ አይደለም። እናም ከወጡ በኋላ በሚናገሩት አንዳንዶች ሲከፋቸው አስተውዬአለሁ። የመረጃ ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ ልንፈርድባቸው አይገባም። የነበሩበትን፡ የከረሙበትን የሚያውቁት እነሱ ብቻ ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ እነሱ እስር ቤት በነበሩ ጊዜ የደረሰበትን ውሳኔ አያውቁትም ይሆናል። ህዝባችን የመረረ ትግል ውስጥ መግባቱን እንዲረዱ ትንሽ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። አሁን ማለት ያለባቸውን እያሉ ነው። ሲረዱትና ሲገባቸው የሚሉት ሌላ ሊሆን ይችላል።
ዓንዱአለም አራጌ ከእስር ከተፈታ በኋላ እንዲህ ብሏል "ስለወደፊቱ ለመናገር ገና ነኝ። ታስሬ የነበረው ምንም መረጃ በሌለበት ቦታ ነው። መጀመሪያ ጆሮና ዓይኔን ከፍቼ አካባቢውን መረዳት አለብኝ። እኔ ባልነበርኩበት ጊዜ የተፈጠረው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ምን ይመስል እንደነበርና የአገሪቱን ሁኔታ በጥሞና ለመረዳት ጥረት አደርጋለሁ"
የሃይለማርያም ከስልጣን መልቀቅ
በ17 ቀናቱ የኢህአዴግ ጉባዔ ወቅት አቶ ሃይለማርያም ከስልጣን እንደሚለቅ ፍቃዱ እንደሆነ መግለጹ ሾልኮ ወጥቶ ነበር። በወቅቱም ''ወንድ ልጅ ቆረጠ'' ከሚል ስላቅ ጋር ''የትኛውን ስልጣን ነው የሚለቀው?'' የሚል ጥያቄ በብዙዎች ዘንድ ተነስቶም ነበር። እርግጥ ነው ሃይለማርያም ስልጣን አልነበረውም። መከላከያውንና ደህንነቱን የማያዝ፡ የማይቆጣጠር ጠቅላይ ሚኒስትር እንደምን ስልጣን ነበረው ይባላል? ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ለውጭ መንግስታት ግራ እስኪገባቸው በሀገሪቱ አባወራውን መለየት አቅቷቸው ነበር የሰነበቱት። ለማንኛውም የአቶ ሃይለማርያም ወደ ስልጣን ወደ ቤተመንግስት መግባት ወንበሩን ኦሮሞና አማራው እንዳይዘው በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር በኩል ጠንከር ያለ አቋም ስለነበር መሆኑ ሁላችንንም የሚያስማማ ነው።
አቶ ሃይለማርያም እንዲሁ እንደባከነ ሳያምርበት ወንበሩ ላይ ቆየ። እያሳቀቀንና እያሳቀን ለ5ዓመታት ተጎልቶ ከኢትዮጵያውያንም፡ ከአምላኩም ተጣልቶ፡ ጥቁር ሌጋሲ ትቶ ተሰናበተ። ሃይለማርያም ፈጣሪን በመለስ ለውጧል። ዘላለማዊ ክብርናሞገስ ለታላቁ መሪያችን ካለበት ጊዜ አንስቶ መንፈሳዊ ካባው ተገፎ፡ በመለስ አስተምህሮት ተተክቷል። መጽሀፍ ቅዱስን ትቶ፡ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተጠምቋል፡፡ በመጨረሻም ከሁለቱም ሳይሆን ቀርቷል። ፈጣሪ ምህረት አይነፍግምና
ከአምላኩ ሊታረቅ ይችላል። ሊስትሮ ቢሆን ጠርጌ አገለግለዋለሁ ያለው የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ግን እንደሸንኮራ አገዳ መጦ ተፍቶታል።ምስኪን ሃይለማርያም!
ከአምላኩ ሊታረቅ ይችላል። ሊስትሮ ቢሆን ጠርጌ አገለግለዋለሁ ያለው የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ግን እንደሸንኮራ አገዳ መጦ ተፍቶታል።ምስኪን ሃይለማርያም!
ሃይለማርያም ሄዷል። የትግራይ ነጻአውጪ ግንባር ደህነቱንና መከላከያውን የሙጥኝ እንደያዘ ስልጣን አልባው ወንበር ላይ አሻንጉሊት ጠቅላይ ሚኒስትር ለማስቀመጥ ፈልጓል። በእርግጥ ነገሮች እንደትላንቱ አይደሉም። እንዳሻው መፈንጨት የሚችልበት ዘመን አልፏል። ኦህዴድ ቀና ብሏል። ብአዴን እየተንደፋደፈም ተግደርዳሪ ሃይል ሆኖ መጥቷል። እናም ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ላይ የሚቀመጠው ሰው ከእነዚህ ከሁለቱ ድርጅቶች ውጭ ሊወጣ አይችልም። የእኛ ጭንቀት ባይሆንም ሰሞኑን በአንዳንድ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ዘንድ እየተራገበ ያለ ጉዳይን በዝምታ ማለፍ ተገቢ ሆኖ አልታየኝም።
ኢህዴግን መምራት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ የመያዝ ተራው የእኛ ነው የሚል በዘመቻ የተከፈተ አጀንዳ በማህበራዊ መድረክና በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሳይቀር እየተቀነቀነ ነው። ኦህዴድ ውስጥ ያሉ የድርጅቱን ገጽታ በማህበራዊ መድረኮች ላይ ወጥተው የሚያስተጋቡና በባህር ማዶ የሚገኙ አንዳንድ የኦሮሞ አክቲቪስቶች አቶ ለማ መገርሳ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን አለባቸው ብለው አንድ ላይ ተሰልፈዋል። አልጀዚራ ላይ የማከብረው የኦፕራይድ ሚዲያ አዘጋጅ መሀመድ አዴሞ ስልጣኑ ለኦሮሞ መሰጠት አለበት ሲል ሰማሁት። ሀሳቡ እንዲሁ እንደወረደ ችግር የለበትም። የአቶ ለማ መገርሳ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን የሚያስከፋ አይደለም። ሲያንሳቸው ነው። ጉዳዩ ግን ያ አይደለም። ደህንነቱና መከላከያው በትግራዩ ነጻ አውጪ መዳፍ ውስጥ በተቀረቀረበት ሁኔታ ስልጣን በሌለው ወንበር ላይ መቀመጡ ነው ችግር የሚሆነው።
የቄሮዎች ትግል መስዋዕትነት የስርዓት ለውጥ እንጂ ሌላ ሃይለማርያም ከኦህዴድ ለማስቀመጥ አይደለም። ደግሞም የኢትዮጵያውያን የዘመናት ጥያቄ በብሄር ኮታ ስልጣን እንዲከፋፈል አይደለም። ህዝብ በነጻነትና ፍትሀዊ በሆነ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የፈለገውን መንግስት የመሰየምና ሲያሻው የማንሳት መብቱ እንዲረጋገጥ ነው። በዕወቀት፡ በብስለት፡ በጥበብና በእኩልነት የሀገሪቱን ልጆች የሚመራ መንግስት እንጂ የተራብነው ዘርና አጥንቱ ተቆጥሮ አራት ኪሎ ቤተመንግስት የሚገባ ሰው ለመሰየም አይደለም።
እነለማ ለዕወቀቱና ጥበቡ የሚያንሱ አይደሉም። ስለሀገራቸው ኢትዮጵያ ያላቸው ስሜት፡ ስለኢትዮጵያውያን ውስጣቸው የሚንቀለቀለው ፍቅር ሀገር እንዲመሩ ከበቂም በላይ ተመራጭ ያደርጋቸዋል። በዘር ማንነታቸው ለክተው ቦታው ይገባቸዋል ለሚሉት ግን የኢትዮጵያ ህዝብ እየተዋደቀ ያለው ህወሀትን በኦህዴድ ለመተካት አለመሆኑን በሚገባቸው ቋንቋ ሊነገራቸው ይገባል። አቶ ለማን በህወሀቷ ኢትዮጵያ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ አጀንዳ ከፍተው የሚያራግቡ ወገኖች ሰውዬው በኢትዮጵያውያን ዘንድ ያገኙትን ተወዳጅነት ለማጥፋትና በአቋራጭ የኦሮሞ መሪ ሆኖ ብቅ ለማለት እንደሆነ መገመት ይቻላል። የአቶ ለማ መምጣት ስምና ዝናቸውን ያደበዘዘባቸው አንዳንዶች የሚያጮሁት አጀንዳ መሆኑ አይጠፋንም። አቶ ለማ ኢትዮጵያውያን የመረጡት፡ ፈቅደውና ይሁንታ ሰጥተው የሰየሙት መንግስት መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆኑ ድምጼን የማልነፍጋቸው ሰው ናቸው። ከመጀመሪያዎቹ ምርጫዎቼ ፊት የሚቀመጡ ምርጥ ኢትዮጵያዊ መሪ ናቸው።
የአስቸኳይ አዋጁ ነገር
የቃላት ጨዋታ እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ በይፋ መፈንቅለ መንግስት ተካሂዷል። ደም ያልፈሰሰበት መፈንቅለ መንግስት። አሜሪካ አውግዛዋለች። በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ''ያሳስበኛል'' ከሚል አዙሪት ወጥታ ጠንከር፡ ከረር ባለ አቋም አስቸኳይ አዋጁን ማውገዟ ብዙ ነገሮችን ያሳየናል። አሜሪካ በትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ላይ ተስፋ መቁረጧን ምልክት ካሳየች ቆይታለች። ማን ይተካ የሚለው ጨንቋት እንጂ የትግራዩ ቡድን በቶሎ ቢሰናበት ትመርጣለች። ለዚህም ነው ተከታታይ ጫናዎችን እየፈጠረች ያለችው። በHR 128 የሰነዘረችው ዱላ ቀላል አይደለም። አምባሳደሩ በቅርቡ ያስተላለፉትም መልዕክት 'አለ ነገር' የሚያሰኝ ነው። አስቸኳይ አዋጁን በተመለከተም የአሜሪካ አቋም ለትግራዩ ቡድን ዱብእዳ ነው። ወዳጅ ሲንሸራተት አይጣል ነው። እርጥባን የሚያቀርብ ጌታ ሲከዳ ሰማይ ምድሩ ይዞራል።
የትግራዩን ቡድን ለአራት ኪሎ ቤተመንግስት ያበቁት አንጋፋው ዲፕሎማት ኸርማን ኮሀን በቲውተር ላይ እንደጻፉት አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ወታደራዊ ፍንቀላ ነው። ሁሉንም አካላት ያሳተፈ የእርቅ ጉባዔ ስንጠብቅ ወታደራዊ አገዛዝ ተተከለ ሲሉ ነው አስቸኳይ አዋጁን የወረፉት። ለመንግስታቸውም ጥሪ አድርገዋል- ''የአሜሪካን መንግስት ሆይ! ይህ በፍጹም እንዳይሆን አድርግ''
አስቸኳይ አዋጁ የተደነገገው እየፈራረሰ ያለውን የትግራዩን ነጻ አጪ ግንባር ለማረጋጋት እንደሆነ ብዙዎች ይገልጻሉ። የመንግስት ኮሚኒኬሽ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ዶ/ር ነገሬ ሌንጮ ሀሙስ ዕለት እዚህ አሜሪካ ሆነው ሲናገሩ ''አስቸኳይ አዋጅ ሊያስወጣ የሚያስችል ምንም ሁኔታ የለም'' ብለው ነበር። በማግስቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት አዋጁን ደነገገ። በሚቀጥለው ቀን ሲራጅ ፈርጌሳ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብሎ ሀገሪቱ በወታደራዊ ዕዝ ስር ለስድስት ወር እንደምትቆይ ገለጹ። ጥያቄው የዶ/ር ነገሬ ሌንጮ አቋም የማን ነው የሚል ነው።
በተደጋጋሚ በሚሰጧቸው የተዛቡና፡ በውሸት የተለበጡ መግለጫዎች ትዝብት ላይ የወደቁት ዶ/ር ነገሬ የአትላንቲክን ውቅያኖስ ተሻግረው ሲመጡ ሰዎቹ መረጃ ደበቀዋቸው ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ተሰጥቶ ነበር። ነገር ግን የሳቸው ምላሽ የፌደራሉ መንግስት(የትግራዩ ቡድን) ሳይሆን የኦህዴድን አቋም ያንጸባረቁበት ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰቡ ሊያስኬድ ይችላል። ምክንያቱም አስቸኳይ አዋጁ ላይ በኢህ አዴግ አባል ድርጅቶች መሀል ጫፍና ጫፍ የቆመ ልዩነት መፈጠሩ በስፋት እየተነገረ መሆነ ነው። ኦህዴድ በአስቸኳይ አዋጁ ላይ አቋም መያዙን መረጃዎች ያመለክታሉ። ብ አዴንም እየተንገዳገደም ቢሆን የተለየ አቋም እንዳለው ጭምጭምታዎች ያሳያሉ። በአዋጁ ላይ ከትግራይ ነጻ አውጪ ቡድን ጋር የተሰለፈው የደቡቡ የህወሀት ክንፍ ደኢህዴን ብቻ ነው።
በዚህኛው የአስቸኳይ አዋጅ የኮማንድ ፖስት ከፍተኛ አመራሮች ዝርዝር የሚያሳየን የጭምጭምታውን እውነትነት ነው። ከስድስቱ የኮማንድ ፖስቱ ከፍተኛ አመራሮች ውስጥ ኦህዴድ የለበትም። ብአዴንም ቢሆን በወላዋይ አቋሙ በሚታወቀው፡ በአደርባይነቱና አገልጋይነቱ በማያፍረው ደመቀ መኮንን ነው የተወከለው። በተረፈ 3ቱ አመራሮች ከደቡብ፡ ሁለቱ ከትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ናቸው። አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ፡ አቶ ሲራጅ ፈረጌሳና አቶ አሰፋ አቢዬ ከደኢህዴን፡ አቶ ጌታቸው አሰፋና ጄነራል ሳሞራ የኑስ ከትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር አባል የሆኑበት ኮማንድ ፖስት ነው የተቋቋመው። ይህም ኦህዴድ በአስቸኳይ አዋጁ አልተስማማም የሚለውን መረጃ ያጠናክረዋል።
አዋጁ ከ15 ቀናት በኋላ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መጽደቅ አለበት። እስከዚያው በአሰራር ተግባራዊ ሆኖ ይቆያል። እንግዲህ ጦርነቱ የሚጠበቀው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። የኦህዴድ አቋም የሚታወቀውም ያን ጊዜ ነው። እንደሚባለው ኦህዴድና ብአዴን አዋጁን ውድቅ ሊያደርጉት ይችላል። ያ ከሆነ የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ይበልጥ ቀውስ ይገጥመዋል። ኢህአዴግ የሚባል የኩሸት ስብስብም የመፍረስ አደጋ ይደቀንበታል።
ህዝባዊ ተቃውሞ የት ደርሷል?
አንዱዓለም ''ፍርሃትን የሰበረ ህዝብ ማየት ምኞቴ ነበር። ከ6ዓመታት የእስር ቆይታ በኋላ ከቃሊቲ እግሬ ሲወጣ ያየሁት ህዝብ ያ የምመኘው ህዝብ ነው። ፍርሃትን የሰበረ ህዝብ።'' ብሎ ነበር ከእስር ቤት እንደወጣ። እውነት ነው። ፍርሃት ተሰብሯል። ዳመናው ተገፏል።
በ1997ቱ ምርጫ ወቅት ለቅስቀሳ ወደ ቦንጋ ያመሩት የኢህአዴግ እጩዎች ከሀገር ሽማግሌዎች የገጠማቸው ምላሽን አስታወስኩት። ''ቡሉኮ(ጋቢ) ከስድስት ወራት በላይ ከቆየ ተባይ ያፈራል። መቀየር አለበት። ኢህዲግም ይበቃዋል። መቀየር አለበት''። የቦንጋ የሀገር ሽማግሌዎች ያን ከተናገሩ 13 ዓመታት አለፈ። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር አሁንም እዚያው ነው። ከተባይም በላይ ደም መጣች አውሬ ወጥቶታል። ለመጪውም ልቀጥል ብሎ ወታደራዊ አገዛዝ አውጇል። ሰሞኑን ጉራጌዎች ተነስተዋል። ወልቂጤን በአመጽ ቀጥ አድርገዋታል። ወደ ሌሎችም ወረዳዎች ተዛምቷል። ጉራጌዎች ''መንግስት አርጅቷል። ደክሞታል። ይረፍ'' የሚል መልዕክት አሰምተዋል።
ይህን ማስታወሻ በማዘጋጅበት ሰዓት ከተለያዩ የአማራ ክልል አከባቢዎች መልዕክት እየተቀበልኩ ነበር። ለነገ ለተጠራው ተቃውሞ ሰዉ መዘጋጀቱን የሚገልጹ መልዕክቶች ናቸው። አስቸኳይ አዋጁ በታወጀ ማግስት የሚደርግ ከሆነ ለአገዛዙ አደገኛ ነው። የትኛውም የሃይል እርምጃ የቆረጠን ህዝብ ሊመልሰው እንደማይችል ግልጽ መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው።
የህዝብ ጉልበት የማያንበረክከው ሃይል የለም። አሜሪካም ቅኝቷን እንድትቀይር የተገደደችው የህዝብ ጉልበት እያየለ መምጣቱን ስትረዳ ነው ማለት ይቻላል። ሁሌም ከጉልበተኛ ጋር መሰለፍ የምትመርጠው አሜሪካ ከወዲሁ ምልክት አሳይታለች። የሙባረክ ወዳጅ ሆና ለ30 ዓመታት የዘለቀችው አሜሪካ የሙባረክ ጠላት ለመሆን ብዙ ጊዜ አልፈጀባትም። የጃስሚን አብዮት ግብጽን በጥፍሯ ሲያቆማት አሜሪካም ለሙባረክ ጀርባ ሰጠች። አሁንም ይሄ እየሆነ ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ስርዓት ሳይለወጥ የሚቆም ትግል እንዳልጀመረ አሜሪካ ተረድታለች። የህዝብ ጉልበት ለHR 128ም ዋስትና ሆኗል። ረቂቁ ወደ ህግነት እንዲቀየር የህዝብ ጉልበት ይበልጥ መጠናከርን ይፈልጋል። ቀሪዎቹ በየማጎሪያ እስር ቤት የሚገኙ ጀግኖቻችን እንዲፈቱ ህዝባዊ ተቃውሞ አድማሱን አስፍቶ መቀጠል ግድ ይለዋል። የሁሉም ነገሮች ዋስትና የህዝብ ንቅናቄ ነው። አሜሪካ አይደለችም። HR 128ም አይደለም። ለማና ገዱም አይደሉም። ወይም ውጭ ያሉ ሃይሎችም አይደሉም። እነዚህ ሁሉ ዋስትናቸው የህዝብ ሃይል ነው። የተጀመረው ተቃውሞ ነው። ኦሮሚያ ክልልን ያዳረሰው፡ የአማራን ክልል ያጥለቀለቀው፡ ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ የጀመረው፡ በሌሎችም የሚጠበቀው የህዝብ እምቢተኝነት ነው።
27 ዓመት ኪሳራ ነው:: የደርግ ሲጨመርበት ግማሽ ክፍለዘመን ከእድሜአችን ተቀንሷል:: ሀገሪቱም በዚያው መጠን ደቃለች። ይበቃታል። ከዚህ በኋላ አምባገንነና ዘረኛ ስርዓትን የምትሸከምበት ጫንቃ አይኖራትም።
No comments:
Post a Comment