Translate

Monday, February 19, 2018

የጠቅላይ ተጠቅላይ ጨዋታ

ኤርሚያስ ለገሰ
Image result for ermias legesse
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀጥሎ የኢትዬጲያን የፓለቲካ አየር የሞላው የሚቀጥለው " ጠቅላይ/ ተጠቅላይ" ማን ይሆናል የሚለው ነው። ይህንን ጉዳይ ሰዎች በተለያዩ አቅጣጫዎች ይመለከቱታል። በተለይም በማህበራዊ ድረገጾች ካሉት ፍትጊያዎች አንዱ በዚህ ዙሪያ ያለው እሰጣ ገባ ሆኗል። በአንድ በኩል ስርነቀል የስርአት ለውጥ ለማምጣት እየታገልን ባለንበት ሰአት በዚህ አነስተኛ አጀንዳ ዙሪያ ለምን ጊዜያችንን እናጠፋለን የሚሉ ብዙዎች ናቸው። በሌላ በኩል ከራሳቸው እምነት፣ ጥቅም እና ፍላጐት በመነሳት " እከሌ ጠቅላይ መሆን አለበት!" የሚለውን የሚገፋም አልታጡም።

የትግራይ ነፃ አውጪ የፌስቡክ ካድሬዎች በሁኔታዎች ተደናግጠው ቢጠፉም ከእናት ፓርቲያቸው ጋር እያሴሩ መሆኑ የሚደበቅ አልሆነም። ትኩረት ለሰጣቸው በሕዝብ ፊት የሚደሰኩሩትና ከመጋረጃ ጀርባ የሚሰሩት የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ለየቅል መሆኑን ማየት ይቻላል።
ነገርን ነገር ያነሳዋል እና አንድ ወዳጄ ሰሞኑን ተወዳጅ ሆና ከአብዛኛው አንደበት በተነገረችው አዝናኝ ቃል ተጠቅሞ " ኮካዎች ሸሹ ወይስ አፈገፈጉ?" ብሎ ጠይቆኝ ነበር። እኔም " ኮተታም ካድሬዎችን በዝንብ ከፍ ካለም በጆፌ አሞራ ልትመስላቸው ትችላለህ። ደም እንደ ጐርፍ ሲወርድና የሰው ህይወት በአጋዚ ሲቀጠፍ ጐርፍ ሆነው ይመጣሉ" አልኩት። እውነት ለመናገር ኮካዎች በደም ካልሰከሩ እስትንፋስ ያላቸው አይመስለኝም።
ያም ሆነ ይህ የትግራይ ነፃ አውጪ " የጠቅላይ/ተጠቅላይ" ጨዋታን የሚመለከተው ከራሱ ህልውና አንፃር ብቻ ነው። የዘረጉት ሕግና የአፈና ስርአት የፓለቲካና የኢኮኖሚ የበላይነታቸውን እስካረጋገጠላቸው ድረስ ለተፈፃሚነቱ በትጋት ይንቀሳቀሳሉ። ሕገ መንግስቱን ለማስከበር በሚል ሽፋን የፓርቲያቸውን የበላይነት ለማረጋገጥ የቻሉትን በሙሉ ያደርጋሉ። የተፈጠረባቸውን ቀውስ ለመደበቅ በሚያደርጉት መፍጨርጨር መዳመጥ ያለባቸውን ለመዳመጥ ህገ መንግስት በመጠበቅ ስም አስፈሪ ተኩላ ይሆናሉ። ለዚህ እንዲያግዛቸው የራሳቸው የጫካ ፕሮግራም ግልባጭ የሆነውን ሕገ መንግስት እንደ ጋሻ ይጠቀማሉ። በተጨማሪም በዣንጥላነት እያገለገላቸው ያለውን የኢህአዴግ ህገ-ደንብ ያለምንም ለውጥ እንዲተገበር ያደርጋሉ።
በመሆኑም የጠቅላይ /ተጠቅላይ ጨዋታን በዋናነት ማየት የሚገባን የትግራይ ነፃ አውጪ ፍላጐት ምንድነው ከሚለው አንፃር ይሆናል። ህውሓት ፓለቲካዊ ሞቱን ለመሞት እያጣጣረ ቢሆንም የፀጥታና የስለላ መዋቅሩ ገና አልተነካም። አሁንም ማሰር፣ መግደል፣ መሰወር ይችላል። አሁንም ህገ መንግስቱን ከአደጋ ለመጠበቅ በሚል ሰበብ እየሞተ ያለውን የፓለቲካ መዋቅር አዛዥና አናዛዡ የፀጥታና ስለላ መዋቅሩ ነው። እያንዳንዱ የፓርላማ አባላት ጋር እየደወለና በአካል እየሔደ " አስቸኳይ ግዜ አዋጁን ባታፀድቅ በሞቀው ህይወትህ ፍረድ። እንደውም ተቃውሞ እያስተባበርክ ያለኸው አንተ መሆንህን ደርሰንበታል" እያለ ያስፈራራል። ለምሳሌ የስለላው መዋቅር አባል የሆነው አስመላሽ ወልደስላሴ ከስብሰባው በፊት በቀጭኑ ሽቦ " አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የፓሊሲ ጉዳይ ነው" ማለት በቂው ሊሆን ይችላል። በኢህአዴግ መንግስታዊ መመሪያም ሆነ የድርጅት ህገ ደንብ አንፃር " የፓሊሲ ጉዳይ ነው!" ከተባለ በተፃራሪው መቆም ፈፅሞ አይቻልም። እናም የፀጥታና ስለላ መዋቅሩ የፓለቲካ አመራሩን እንደ ህዝብ ግንኙነት ተጠቅሞ የፈለገውን በሀይል ሊፈፅም ይችላል።
ወደ ጠቅላይ ተጠቅላይ ጨዋታ ስንመለስ ቀደም ብሎ እንደተጠቀሰው የትግራይ ነፃ አውጪ ሁለት ሰነዶችን መዞ ያወጣል። እነዚህም የኢህአዴግ ሕገ መንግስትንና ህገ ደንቡ ናቸው። እስቲ እያንዳንዱን በተናጠል እና በተዛምዶ እንመልከት።
# የኢህአዴግ ሕገ መንግስት
አስቀድሞ እንደተገለጠው የትግራይ ነፃ አውጪ ሁሉንም መቆጣጠር የሚፈልገው " ሕገ መንግስታዊ ስርአቱን" ለማስጠበቅ በሚል እንደሆነ ይታወቃል። በተለይም የህገ መንግስቱ አንቀፅ ዘጠኝ እየተጠቀሰ የሕግ የበላይነት ለማስከበር ሀላፊነት አለብን የሚባለው በዚህ ምክንያት ነው። አንቀፅ ዘጠኝ የኢህአዴግ ህገ መንግስት የአገሪቱ የበላይ ህግ መሆኑ፣ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ውሳኔ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈፃሚነት እንደማይኖረው ይደነግጋል። በሕገ መንግስቱ ከተደነገገው ውጭ በማንኛውም አኳኃን የመንግስት ስልጣን መያዝ እንደተከለከለ ይገልጣል።
ምንም እንኳን የትግራይ ነፃ አውጪ ቅጥፈት ሞራላዊ እሴት ብቻ ሳይሆን የአገዛዙ ዋልታና ማገር መሆኑ ቢታወቅም እስከጠቀማቸው ደረስ " ሕገ መንግስቱ ይከበር" ማለታቸው አይቀርም። ስለዚህም በደብረፂዬን መሪነት በፀጥታና ስለላ የበላይነት የያዘው ፓርቲ " የጠቅላይ ሚኒስትሩ አሰያየም!" የሚለውን የሕገ መንግስት አንቀፅ 73 ላይ ሙጭጭ ማለቱ አይቀርም። በአዋቂነት ውስጥ ሆነው በኩራት ይገልጡታል። በነገራችን ላይ አንቀፅ 73 ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሕዝብ ተወካዬች ምክርቤት አባላት መካከል ይመረጣል ይላል።
በእኔ እምነት የደብረፂዬን ፓርቲ ይሄን የህገ መንግስት አንቀፅ የሚቀየረው በመቃብሬ ላይ ነው ማለቱ አይቀርም። በተደጋጋሚም " ህገ መንግስቱ ይከበር!" የሚል ከበሮ መደለቅ ይጀምራል። እናም ይሄ ከሆነ ዘንዳ ከውሳኔው የማያሻማ ቁምነገሮችን ማውጣት ይቻላል።
የመጀመሪያው ቁምነገር " ጠቅላይ/ ተጠቅላይ" የሚሆነው ግለሰብ የግዴታ የፓርላማ አባል መሆን ይገባዋል። ይሄ መመዘኛ ለማ መገርሳ፣ ዶክተር አቢይ አህመድ እና ወርቅነህ ገበየሁን በመጀመሪያው ዙር ከጨዋታ ውጭ ያወጣል። ስለዚህ የለማም ሆነ የዶክተር አቢይ ጠቅላይ መሆን እንደማይችሉ የተረጋገጠ ነው።
በሌላ በኩል ደመቀ መኮንን፣ አባዱላ ገመዳ፣ ደብረፂዬንና አዲሱን የደኢህዴን ሊቀመንበር( ምንአልባት ሽፈራው ሽጉጤ) ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፋ ይሆናል። በመሆኑም የትግራይ ነፃ አውጪ ክንፍ የሆነው የፀጥታና ስለላ መዋቅር ሕገ መንግስቱ ሳይሸራረፍ ይተግበር ካለ ጠቅላዩ ደብረፂዬን ሊሆን ይችላል። ተጠቅላዬቹ ደመቀ፣ አባዱላ እና ሽፈራው ሽጉጤ ሊሆኑ ይችላሉ።
የራሴን ግምት አስቀምጬ ለመሄድ ያህል የስለላ እና የፀጥታ መዋቅሩ ለደመቀ መኮንን 60 በመቶ፣ ለአባዱላ 40 በመቶ በመስጠት የደሜክስን ተጠቅላይነት የሚያፀና ይመስለኛል። እናም ከሐይለማርያም ተስተካካይ ሰው በዙፋኑ ላይ እናገኛለን።
እዚህ ላይ የትግራይ ነፃ አውጪ ክንፍ የሆነው የፀጥታና ስለላ መዋቅር በሚፈልገው የህገ መንግስት ማእቀፍ የሚዘልቅ ከሆነ ስለ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርም ጥቂት ማውራት ያስፈልጋል። በህገ መንግስቱ መሰረት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን የፓርላማ አባል መሆን አይጠይቅም። በሌላ አነጋገር ም/ ጠ/ ሚኒስትሩ የፓርላማ አባል መሆን አይጠበቅበትም። እናም ለም/ጠ/ ሚኒስትርነት ህውሓት ወይዘሪት ፈትለወርቅ ( ሞንጆሪኖ)፣ ኦህዴድ ዶክተር አቢይ ሊያቀርቡ ይችላሉ። በእኔ ግምት ወቅቱ ከምንግዜውም በላይ ለትግራይ ነፃ አውጪ ወሳኝ በመሆኑ ወይዘሪት ፈትለወርቅ የመመደብ እድሏ ሰፊ ነው። በሌላ በኩል ዶክተር አቢይን ከስሩ ነቅለው በውሃ ላይ የሚንሳፈፍ ደረቅ ኩበት ማድረጉ የበለጠ የሚጠቅማቸው ከሆነ ምክትል ተጠቅላይ ሚኒስትር በማድረግ ይመድቡታል። በመሆኑም የምክትልነት ጨዋታው ( game theory) የሚሆነው ደመቀ መኮንንን በምትጠቀልለው ሞንጆሪኖ እና ተጠቅላዪ ዶክተር አቢይ መካከል ይሆናል።
# የሕውሓት/ ኢህአዴግ ድርጅታዊ ህገ ደንብ
በህውሓት/ ኢህአዴግ ህገ ደንብ መሰረት 180 አባላት ያሉት ( ከእያንዳንዱ 45) የኢህአዴግ ምክርቤት የድርጅቱን ሊቀመንበር በሚስጥር በሚሰጥ ድምፅ ይመርጣል። በድምፅ አሰጣጡ ላይ 180 የምክር ቤት አባላት እኩል ድምፅ አላቸው። ምንም እንኳን ከ3ሚሊዬን አባል እና ከ40 ሚሊዬን በላይ ህዝብ ወክያለሁ የሚለው ኦህዴድ ከግማሽ ሚሊዬን በታች እና ከ5 ሚሊዬን በታች ወክያለሁ የሚለው ህውሃት እኩል ድምፅ መያዛቸው ሊያነጋግር ቢችልም።
በህገ ደንቡ መሰረት አራቱም የዘውጌ ድርጅቶች የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና ምክትል አጩ የማቅረብ መብት አላቸው። ለሊቀመንበርነት የሚወዳደሩት የብሔር ድርጅቶቹ ሊቀ መናብርት ይሆናሉ። እዚህ ላይ በህገ ደንቡ ሊቀመንበሩ የድርጅቱ የበላይ አስፈፃሚ መሆኑን ቢገልፅም በመንግስት ስልጣን ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል የሚል በግልፅ የተቀመጠ ነገር የለም። ለነገሩ ፓርቲው እንደ አቶ መለስ የመንግስት ዘላለማዊነትን ካልተላበሰ በስተቀር ሊያስቀምጥ አይችልም። ነገር ግን ድርጅት መንግስትን የሚመራ እንደመሆኑ መጠን ፓርቲው በውድም ይሁን በግድ ስልጣኑን የተቆናጠጠ በመሆኑ የፓርቲው ሊቀመንበር የመንግስት የበላይ ሆኖ መቀመጡ ተመራጭ ይሆናል።
እናም በዚህ ስሌት መሰረት ከወዲሁ ግምቴን ለማስቀመጥ ህውሓት "ለሊቀመንበርነት እንዲወዳደር የማቀርበው እጩ የለኝም" ይላል። ደብረጲዬንን ከትግራይ አምጥቶ ማወዳደር ከባድ ስለሚሆንበት። ፌዴራሉን በስውር ለመምራት ደብሪፅን ማምጣት አደጋ ይኖረዋል። ብአዴን በሊቀመንበርነት ደመቀ መኮንን እጩ እንዲሆን ያቀርባል። ኦህዴድ ለድርጅት ሊቀመንበርነት በእጩነት የሚያቀርበው የሚኖር አይመስለኝም። ለማ መገርሳ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ ቢመረጥ እንኳን ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ስለማይችል የፓርቲው ቁንጮ መሆን የሚፈይድለት ነገር የለም። የደቡብ ድርጅቱ ደኢህዴግ አዲሱ ሊቀመንበሩን ለኢህአዴግ ሊቀመንበርነት እጩ አድርጐ ሊያቀርብ ይችላል። የደኢህዴኑ ሊቀመንበር የፓርላማ አባል ከሆነ ከደመቀ መኮንን ጋር የሚገጥመው ለድርጅት ሊቀመንበርነት ብቻ ሳይሆን ለተጠቅላይነትም ጭምር ይሆናል። እናም የትግራይ ነፃ አውጪ ሙሉ ድጋፍ ያለው ደመቀ መኮንን በተጠቅላይነት አራት ኪሎ ይሰጠዋል።
# እና ምን ይጠበስ?
አንዳንድ ሰዎች የቅርብ ወዳጆቼን ጨምሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜ ማጥፋት እንደማያስፈልግ ሲገልጡ እሰማለሁ። የትግራይ ነፃ አውጪ በሰጠን አጀንዳ ላይ የተጠመድን አድርገው ይወስዱታል። በመሰረቱ በዚህ አስተያየት አልስማማም።
በመጀመሪያ ደረጃ የትግራይ ነፃ አውጪ የገባበት ሁኔታ ቀውስ እንጂ ስኬት አይደለም። የቀውሱ መሰረታዊ ምንጭም የኢትዬጲያ ህዝብ እምቢተኝነት የወለደው እንጂ አገዛዙ የመለወጥ ፍላጐት ስላለው አይደለም። በሕዝብ አመፅ ምክንያት የትግራይ ነፃ አውጪ እየተፍረከረከ፣ የአመራር ሽኩቻው በግልፅ እየታየ ትኩረት አንስጠው ማለት አያስኬድም።አይደለም የአገሬው ሰው ምእራባውያን፣ አለም አቀፍ ተቋማት እና ሚዲያው በትግራይ ነፃ አውጪ ውስጥ የተፈጠረውን የስልጣን ፍጥጫ በአንክሮት እየተከታተሉ ስጋታቸውን በሚገልፁበት ሁኔታ የስርአት ለውጥ ፈላጊዎች ትኩረት ካልሰጠነው የለውጥ ግንዛቤያችንን መፈተሽ ይኖርብናል። ይሄን ማስታወሻ እየፃፍኩ በኢትዬጲያ የአሜሪካን ኤምባሲና አምባሳደር የአቶ ኃይለማርያም ከስልጣን መውረድ ጋር ተያይዞ ይፋ ያደረጉት ማስጠንቀቂያና በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ያወጡት መግለጫ በትዝታዬ መጥቶ ነበር። የስርአት ለውጥ ፈላጊውም ሆነ የሚዲያ ተቋማት እንዴት ተሯሩጠው እንደተቀባበሉት ጭው አለብኝ። በብዙ ሰዎች ትንተና ውስጥም ይህ በተደጋጋሚ የሚጠቀስና በእያንዳንዳችን አእምሮ ውስጥ የሚንገዋለል ነው።
በሁለተኛ ደረጃ ደጋግሜ እንደገለፅኩት ትናንሽ ለውጦች ትላልቅ ለውጦችን ይጋብዛሉ። ለነገሩ በትግራይ ነፃ አውጪ ውስጥ የሚኖርን የስልጣን ሽኩቻ እንደ ትንሽ ለውጥ ሊወሰድ ይገባል ወይ የሚለውም መጠየቅ ይኖርበታል። የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት የፋሺስት እና አፓርታይድ ድቃይ በመሆኑ በጣም አደገኛ ነው። ይሄ አደገኛ ስርአት በተነሳበት የሕዝብ ጥያቄ ውስጣዊ ህይወቱ ውስጥ ያጋጠመው የአመራር መፍረክረክ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። እነሱ ሲወድቁ እኛንም ይዘው እንዳይወድቁ ፣ ሽብርና የእርስ በርስ እልቂት እንዳይፈጠር በቅርበት መከታተል ያስፈልጋል። ለማንም ግልጥ እንደሆነው ይሄ ፋሽስታዊ አገዛዝ እስከአሁን ለግፍና ለጭፍጨፋ አዲስ ባይሆንም ከኢትዬጲያ ህዝብ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ የተቆራረጠበት እና እርስ በራስ መበላላት የጀመረበት ነው። ይሄ በአግባቡ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። ይሄን ማድረግ ዋናውን ትግል ያግዘዋል እንጂ የሚያዘናጋው አይሆንም። ይልቁንስ በትግራይ ነፃ አውጪ እና ተላላኪዎቹ ውስጥ የተፈጠረው ክፍፍል ለመሰረታዊ ለውጡ በአቀጣጣይነት ሊታይ የሚችል ነው። " የጉልቻ ለውጥ" ብቻ ተደርጐ መወሰድ የለበትም። እንደዚህ ማሰብ ተራራ የሚያክል ስህተት ለመስራት እንደመዘጋጀት ተደርጐ ሊወሰድ የሚችል ነው።
በሶስተኛ ደረጃ በስርአት ለውጥ ፈላጊው ዘንድ የሚታዩ የተሳሳቱ ዝንባሌዎችን ነቅሶ በማውጣት ለመታገል ያግዛል። ይሄ ወቅት ዘረኝነት እና ፋሺዝም አብረው የቆሙበት የሞትና የሽረት ዘመን ነው። የዘረኝነት ፓለቲካ በአገዛዙ ውስጥ ብቻ አይደለም። ተቃዋሚ ሀይሉም ጋር የDNA ፓለቲካ ስር እየሰደደ ሄዷል። እንደዚህ ባለ አደገኛና ደካማ አቋም ምክንያት አመዳዩን አለላ ለማስመሰል ጥረት እየተደረገ ነው። እከሌ በሕዝብ ተወዳጅ ስለሆነ በጠቅላይ/ ተጠቅላይነት ካላየሁት ሞቼ እገኛለሁ የሚሉ አደገኛ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው። ሌሎች ድብቅ ፍላጐት ያላቸው ደግሞ የሕዝቡን ልቦና በማዳመጥ እነሱ ወደሚፈልጉት ለማሽከርከር ያለ የሌለ ጉልበታቸውን በመጠቀም ላይ ናቸው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ለማ መገርሳ እና ዶክተር አቢይን ወደ ፌዴራል ተጠቅላይነት እንዲሄዱ የሚደረገው ግፊት ነው።
በእኔ እምነት በለማ እና አቢይ ላይ እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ከስራቸው በመንቀል አስብቶ የማረድ ነው። እርግጥም ከአፈራቸው ላይ ስራቸውን መንቀል እንዳያብቡ ያደርጋል።ለማና አቢይ ለመካከለኛ ጊዜ የኦሮሚያን የፓለቲካና የድርጅት ስራ በበላይነት መምራት ይኖርባቸዋል። እስከ ሶስት ሚሊዬን ይጠጋል የተባለውን የኦህዴድ አባልና ቄሮን በአዲሱ አስተሳሰባቸው ኢንዶክትሬት ማድረግ ይኖርባቸዋል። በመንግስት የስራ አመራርና የካድሬ ስልጠና ማእከላት " ኢትዬጲያዊነት ሱስ መሆኑን፣ የብሔር ጭቆና የሚባል ተረት ተረት መሆኑን፣ የኦሮሞ ጀግኖች ኢትዬጲያ አገራቸውን ለማቆየት ያደረጉትን ተጋድሎ፣ ኢትዬጲያዊነት እንደ ጉልት ማንም ሲፈልገው የሚያቋቁመው እና የሚበትነው እንዳልሆነ፣ መታወቂያ ላይ ብሔር መፃፍ ያስቆሙበትን ምክንያት፣ የኦሮሞ ህዝብ ወርቃማ እሴቶችን…ወዘተ" የሚያስተምሩበት ካሪኩለም በመቅረፅ ማስተማር ይኖርባቸዋል። ሚሊዬን ለማዎችና አቢዬች መፈጠር ይኖርባቸዋል። የትምህርት ቤት ካሪኩለሞችን በእነሱ አዲስ ተራማጅ አስተሳሰብ መቃኘት የቅድሚያ ስራቸው ሊሆን ይገባል።
የለማ ቡድን አባላት ከላይ የተጠቀሰውን እያደረጉ የአገሪቱን ሕገ መንግስት ወደ ፕሬዝዳንታዊ ስርአት ( የአንድ ሰው አንድ ድምፅ) የሚቀየርበት ሁኔታ ማመቻቸት ይኖርባቸዋል። በዚህ ዙሪያ የፕሮፌሰር መረራ ፓርቲ እና የሌሎች ድርጅቶች ድጋፍ ስለሚያገኙ ትግሉ አስቸጋሪ ላይሆን ይችላል።የለማ ቡድን ይሄን ማድረግ ከቻለ በኢትዬጲያ ታሪክ ውስጥ ዘወትር የሚታወስ ደማቅ ታሪክ ይሰራል። የኢትዬጲያ አምላክ ይርዳቸው።

No comments:

Post a Comment