Translate

Tuesday, February 27, 2018

“ታሪክ ራሱን ቧልት በሆነ መንገድ ሲደግም!”

ኤርሚያስ ለገሰ
Ermias Legesse, author and ESAT TV and Radio contributor
አንድ safegurding Tegaru lives በሚል ስያሜ የሚጠራ  ካድሬ ” ደኢህዴን ከኃይለማርያም ወደ ሽፈራው ሽጉጤ ያደረገው ለውጥ የጥልቅ ተሃድሶ እድገት ነው፣ ወይንስ ከድጡ ወደ ማጡ ነው?” በሚል ያነሳሁት ጥያቄ ላይ አስተያየት ሊሰጥ ወደ ገፄ መጥቶ ነበር።  ከላይ ከተጠቀሰው ኮካ በተጨማሪ በለውጥ ሀይል ዙሪያ ያሉ ወገኖች ” ሲራጅ ፈርጌሳ የደኢህዴን ሊቀመንበር ሆነ ብለህ ነበር!” የሚል ጥያቄ ስላነሳችሁልኝ ሁኔታውን ትንሽ ልበልበት። በትግራይ ነፃ አውጪ ደጃፍ ታሪክ እራሱን ስለሚደጋግሞ መለስ እያሉ ማስታወሱ ሳይበጅ አይቀርም። ከላይ የተጠቀሰው አይነት ሾርት ሜሞሪ ያላቸውን ኮተታም ካድሬዎች አፍ ማዘጋት የሚቻለው በዚህ መልኩ ነው። በሚያገኙት መረጃ ወደ ሰው ይመለሳሉ ብሎ ተስፋ ማድረግ ታማኝ እንዳለው ” እባብ ለመደ ተብሎ በኪስ አይያዝም!” ቢሆንም እባብነታቸውን እንዳይረሱ ያደርጋቸዋል። እናም እንደሰሞኑ በጅምላ ግድያ በርሜላቸውን እስኪሞሉ አድብተው እንዲቀመጡ ያደርጋቸዋል።

ወደ ገደለው ስመለስ ጠዋት ከእንቅልፌ ነቅቼ መረጃዎች ሳነፈንፍ የኃይለማርያም ድርጅት (ደኢህዴን) ፌስቡክ ድረገፅ ፊትለፊቴ መጣ። የድረ ገፁን ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ ከታች እስከ ላይ ወረድኩበት። ያለምንም ጥርጥር የድርጅቱ መሆኑን አረጋገጥኩ። በፓርቲው ማህበራዊ ድረገፅ ዘገባ መሰረት ሲራጅ ፈጌሳ ሊቀመንበር ሆኖ መመረጡን ያበስራል። አስቀድሞ የተወራ ስለነበር ብዙም አልገረመኝም። ከአራት ቀን በፊት በደቡብ ክልላዊ መንግስት ሬዲዬ የሚሰራ ጋዜጠኛ ” ወዲ ሽጉጤን ተገላገልነው!” በሚል በፌስቡኩ የፃፈውን ተመልክቼ ነበር። ዋሽንግተን ዲሲ ከሚኖሩ የኃይለማርያም እጅግ የቅርብ ዘመዶች በተዘዋዋሪ በደረሰኝ መረጃ መሰረት ሽፈራው ሽጉጤ የሙስና ችግር በሰፊው እንደተነሳበት ጠቁመዋል። ወደ ኃላ ተኪዶ በቡና እርሻ መሬት አሰጣጥ ላይ ከፓስተር ባደግ በቀለ ጋር በሼር የጀመረው ኢንቨስትመንት በአውጫጪኝ እንደቀረበበት መረጃው ደርሶናል። እቤት ውስጥ ተቀምጠው የነበሩ የ70 አመት ሽማግሌ አባቱ ፓስተር ባደግ በወር 50ሺህ ብር እየከፈለ ለቡና እርሻው ስራ አስኪያጅ ማድረጉም በሂስ መቅረቡን ሰምተናል።
ለማስታወስ ያህል ፓስተር ባደግ ለሁሉም ባለስልጣናት እና ጄኔራሎች የማስተርስ ዲግሪ በ30ሺህ ዶላር የሸጠላቸው ሰው ነው። ለምሳሌ አቶ በረከት ስምኦን ከ11ኛ ክፍል በቀጥታ ማስተርሱን እንዲወስድ አድርጐታል። በፓርላማ መለስ ሲያሾመው እየሳቀ ” አቶ በረከት ስምኦን የትምህርት ዝግጅት ማስትሬት ዲግሪ በተቋማዊ አመራር” በማለት አስጨብጭቦለታል። ራሱም አንጨብጭቧል። አንዳንድ የዋሆች ( የዋህነቱ በመርፌ ቀዳዳ የመሹለክ ያህል ከሆነ እኔንም ይጨምራል) እንደዚህ አይነቱን ” ተወዳጅ ፓርላማ!” የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ይሽረዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ወደ ተነሳሁበት ልመለስ እና የኃይለማሪያም ፓርቲ ድረገፅ ላይ የወጣው የሲራጅ ፈጌሳ ሊቀመንበር መመረጥ በአንድ ጊዜ ተሰራጨ። የለማ መገርሳ ድርጅት የሆነው ኦህዴድ በድረገፁ ተቀብሎ አስተጋባው። ከዚህ በላይ መተማመኛ ለማግኘት መሄድ አስፈላጊ አልነበረም። ከበቂ በላይ ነው። በሌላ በኩል እስከ ቀትር ድረስ ደኢህዴን ማስተባበያ ባለመስጠቱ የኢሳት ኢዲቶሪያልም የፓርቲውን ድረገፅ ዋቢ በማድረግ ዜናውን አሰራጨ። ደኢህዴንን የበላው ጅብ አልጮህ አለ። ሁኔታዎች ወደ አልተፈለገ መሄዳቸውን የተገነዘበው የስለላው ቢሮ ( የሽማግሌው ስብሃት ነጋ ቡድን በተለይም ቀጣዩ ስውር ጠቅላይ ሚኒስትር የምትሆነው ፈትለወርቅ ሞንጆሪኖ) ማስተባበያውን በተከፋይ የህውሓት ፌስቡክ የኮካ አለቆች አማካኝነት ማሰራጨት ቻሉ ። የፌስቡክ የኮካ አለቆቹ ከማስተባበያው ባልተናነሰ የለማ ቡድንን መረጃ ተቀብሎ በፍጥነት ማሰራጨቱን ደቂቃና ሰከንድ እየመተሩ ለመሳለቅ ሙከራ አደረጉ። እነዚህ አለቆች አዙረው መመልከት ቢችሉ ኖሮ መጠየቅ የሚኖርባቸው ” የደኢህዴንን የውስጥ ግምገማ እንዴት እኛ የትግራይ ነፃ አውጪ ሰራዊቶች ቀድመን እናወጣለን? ነውር አይደለም ወይ? ደኢህዴን ተላላኪ ነው የሚለውን ምስክርነት እየሰጠን አይደለም ወይ?” ይሉ ነበር።
እናም በሰፊው የተሰራጨውን የሲራጅ ፈጌሳ ወደ ደኢህዴግ ሊቀመንበርነት መምጣት ተመርኩዤ የህውሓት ጨዋታ ( Game theory) ምን ሊሆን እንደሚችል የቢሆን መላምቶች መስራት ጀመርኩ። የጨዋታውን መመዘኛዎች ከሶስቱ እጩዎች( ዶክተር አቢይ፣ ደመቀ መኮንን እና ሲራጅ ፈጌሳ) ጋር በማጐዳኘት ነጥብ መስጠት ጀመርኩ። ሲናሪዬዎቹ በማቲማቲክስ እና ማይክሮ ኢኮኖሚክስ ኮርስ ስወስድ ከተማርኩት እና መልሼ መላልሼ ካነበብኩት የእስረኞች ወለፈንዲ ( prisoner dilemma) ከሚባለው ጨዋታ ጋር ተመሳሰለብኝ። (የዘርፋ ሙያተኞች በሁለት ኮርስ ያገኘሁትን ሚጢጢ እውቀት ወደ ተግባር ለመቀየር ላሳየሁት ተገቢ ድፍረት ይቅርታዬ ከወዲሁ ይድረሳችሁ።) ለማንኛውም በጨዋታው ህግ መሰረት ህውሓት ብአዴንና ደኢህዴንን ባህርዳር እና ሐዋሳ ጨለማ ቤት እንዳይገናኙ አድርጐ አስሮ የለማ ቡድንን ሊጫወትበት ሲሞክር በልበ ህሊናዬ ወከክ ብሎ ታየኝ። ጨዋታውን በእያንዳንዱ መመዘኛ (የስልጣን መወጣጫ መስፈርት) አብጠርጥሬ ተመለከትኩ።
ህውሓት ሌሎችን ከስልጣን ለማግለል የሚጠቀምባቸው ስትራቴጂና ታክቲኮች አሁንም አልተቀየሩም። በመሰረቱ በሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን። ከእነዚህ ስትራቴጂዎች አንዱ ኢህአዴግን መሰረቱ የተባሉት አራቱ ድርጅቶች በስራ አስፈፃሚም (እያንዳንዱ ዘጠኝ) ሆነ በኢህአዴግ ምክርቤት (እያንዳንዱ 45) እኩል ውክልናና ድምፅ እንዲኖራቸው መደረጉ ነው። ይሄ መሆኑ ህውሓትን ቢጠቅመውም በሶስቱ ድርጅት ካድሬዎች እና አባላት ዘንድ የቆየ ቅሬታ እና ቁጭት የፈጠረ ነው። በዘውጌ ድርጅቶቹ ጉባኤ ላይ ዘወትር የሚነሳና ቢያንስ በፓርላማ ወንበር ቀመር መሰረት የፓርቲዎቹ ቀመር ይስተካከል በሚል የሚገለፅ ነው። ዛሬ ሁኔታዎች ወደ ህዝብ ወርደው  ቢያንስ በኦሮሞና አማራ ህዝብ) የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ እና ምክርቤት ቁጥር በሕዝብ ብዛት ይሰራ መባል ተጀምሯል። የለማ ቡድን ደግሞ በህልምም በውንም ሊታሰብ የማይችል ከሶስቱ ድርጅቶች ሊለያየው የሚችል አዲስ የአይዲኦሎጂ ለውጥ ማድረጉ ” ኢህአዴግ ውስጥ ምን ያደርጋል?” የሚል ጥያቄ በሕዝቡ ዘንድ እየተጠየቀ ነው። እርግጥም ” ጨቋኝ ተጨቋኝ” ተረት ተረት እና ” አብዬታዊ ዲሞክራሲ” የሚባል እንቶፈንቶ እንጮቆረር የወረወረው የለማ ቡድን የኢህአዴግ የውሸት ዣንጥላ ውስጥ መቆየቱ ከፍተኛ ኪሳራ ላይ ሊጥለው ይችላል። ህጉ በሚፈቅድለት መሰረት በፍጥነት ፍቺውን ካልፈፀመ የሞት መንገዱን ያፋጥናል። ህውሓት ጊዜ ባገኘ ቁጥር መርዙን አጠራቅሞ በመርጨት ወደ ፍፃሜ ይወስደዋል።
ሕውሓት ባህርዳር እና ሐዋሳ ጨለማ ቤት አስሮ የለማ ቡድንን ከጨዋታ ውጭ የሚያወጣው ” የፓርቲው የስልጣን አተያይ እና መያዣ መንገዶች” የሚለውን ድርጅታዊ መመሪያ ፊት ለፊት በመደንቀር ይሆናል። የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ( ከእያንዳንዳቸው 9 አባላት) ወደ ምክርቤት ከመሄዱ በፊት የድርጅት ሊቀመንበርና ጠቅላይ/ ተጠቅላይ ሚኒስትር በሚኮንበት መስፈርቶች ላይ በመወያየት አስቀድሞ አቋም ይወስዳል።
እነዚህ መስፈርቶች አብዬታዊነት፣ ብቃት፣ ስነ ምግባር ዋናዎቹ ናቸው። ከ40 በመቶ በላይ የሚይዘው አብዬታዊነት ( አብዬታዊ ዲሞክራሲን ማመን እና መጠመቅ፣ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክትንና አንቀፅ 39 በፅናት ማመን፣ ማእከላዊነትን ሳያንገራግሩ መቀበል፣ ድርጅቱ የመደበውን ቦታ መቀበል፣ ከግለሰብ ክብር ይልቅ ለድርጅቱ ክብር መጨነቅ) በመስፈርትነት ያስቀምጣል። የኢህአዴግ ባለስልጣናት ” ድርጅቴ ሊስትሮ ሁን ካለኝ እሆናለሁ” ሲሉ የሚደመጡት በዚህ ምክንያት ነው። በነገራችን ላይ በዚህ መመዘኛ 40/40 የሚያገኙት ከጫካ ድረስ የመጡት የህውሓት ካድሬዎች ብቻ ናቸው።
የብቃት መለኪያ ተደርጐ የሚወሰደውም የአብዬታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰቦችን በሙሉ ተረድቶ በፓሊሲው መሰረት የማስፈፀም አቅም ነው። ” ገበሬም ቢሆን የድርጅቱን ፓሊሲ ማስፈፀም እስከቻለ ድረስ ከበቂ በላይ ነው” ተብሎ በተደጋጋሚ ሲነገር የምንሰማው በዚህ ምክንያት ነው። ትልቅ አገር፣ የታሪክ አቅጣጫ፣ብሔራዊ አላማና ሕልም የሚባል ነገር የለም። ከዚህ ይልቅ ሁሉንም ነገር አጥቦና በጐሳ መነፅር ማየት መቻል የተሻለ ተመራጭነትና ትልቅ ነጥብ የሚያስቆጥር ነው።
የትምህርት ዝግጅትን በተመለከተ በኢህአዴግ ” የአመራር ምደባ ፓሊሲ” ውስጥ የተቀመጠው እጅግ በጣም የሚያስደነግጥ ነው። ብዙ ሰዎች ህውሓት/ ኢህዴግ የመሐይማን ጥርቅም መሆኑ በጣም እየገረማቸው ሲናገሩ ይሰማል። ይሄ ግን ሆን ተብሎ በታቀደ መልኩ የሚፈፀም ነው። በህውሓት ውስጥ ትምህርት እና ከፍተኛ ስልጣን ተቃራኒ ተዛምዶ (Inversely related) ናቸው። ጥቂት አብዬታዉያን ብቻ ናቸው የአካዳሚያዊ ትምህርት የመጨረሻው እርከን ( ዶክተር ልበለው) እንዲደርሱ የሚፈቀድላቸው።
ይሄን በማስመልከት ” የመለስ ትሩፋት: ባለቤት አልባ ከተማ” በሚለው መፅሐፍ ላይ በገፅ 309 ላይ፣
የኢህአዴግ የውስጠ ድርጅት መመሪያ ከፍተኛ ምሁራንን በሁለት ጐኑ የተሳሉ ቢላዋ በማለት በንዑስ ከበርቴነት ጐራ ይመድባቸዋል። በጀማሪ ካፒታሊዝም ውስጥ የምሁራን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ለጥገኛ ዝቅጠት የተመቸ እንደሆነና ከፍተኛ መደላድል እንደሚፈጥር ያሳስባል። በመሆኑም የምሁራን አሰላለፍ በንዑስ ከበርቴ ደረጃ በመሆኑ በህዝቡ ውስጥ የሚካሄድ ትግል ሲፋፋም በመጀመሪያው የንቅናቄው መስመር በመሰለፍ ግንባራቸውን ለጥይት እንደሚሰጡ፣ ትግሉ ሲቀዛቀዝ ደግሞ ከሌላው የበለጠ ተስፋ የሚቆርጡና የሚያስቆርጡ፣ ይባስ ብሎም ለግል ጥቅማቸው የሚሯሯጡ ሆዳሞች ይሆናሉ ይላሉ። በመሆኑም ድርጅቱን የሚቀላቀሉ ምሁራን አብዬቱን የመምራት ሃላፊነት ስለሚሸከሙ በመርፌ ቀዳዳ ማለፍ የሚችሉ ሆነው ከአጠቃላይ ተመልማዬች ከ1 በመቶ መብለጥ የለባቸውም በማለት ይገልፃል” ይላል።
እንግዲህ ህውሓት ስልጣንን እንደ ርስት ለመያዝ የሚጠቀምባቸውን መስፈርቶች በመመልከት የለማ ቡድን ወደ ድርድር መምጣት ካልቻለ ቢያንስ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መቀበል) ሲራጅ ፈጌሳ ሊቀመንበር እና ተጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆን እንደሚችል የትንበያ ለውጥ አደረኩ። ከእኩለ ቀን በኃላ የደኢህዴን እና የለማ ቡድን ደረገፆች ባይቀየሩም የህውሓት ኮተታም ካድሬ አለቆች ከሚከፍላቸው ስለላው መስሪያቤት ( የስብሃት ነጋ ገዥ መደብ በበላይነት ሞንጆሪኖ) ከሲራጅ ፈጌሳ ወደ ” ወዲ ሽጉጤ!” መቀየሩን ይፋ አደረጉ። መጀመሪያ ስሰማ በጣም ተገርሜ ነበር። የጥልቅ ተሐድሶው ለውጥ ከድጡ ወደ ማጡ መሆኑን በቀጥታ ማረጋገጣቸው እጅጉን አስደነቀኝ። በውስጤ ኃይሌንና ሽጉጤን ሚዛን ላይ እያስቀመጥኩ ኃይለማርያም በምን ጣዕሙ አልኩኝ። የጀርመኗ የአገልግል ዶሮ ወጥ በአይኔ ላይ ሄደች። ለመወሰን መረጃ የለኝም የሚለው ንግግሩ ትውስ አለኝ። ዲሊቨሮሎጂ በእጄ ላይ ተንከባለለ። ጄኔራል ሳሞራ በህዝቡ በጥፊ ስለተመታው ወታደር የተረከለትን አስታወስኩ። የግመል ቁመት የማያውቀው የቻይና መሐንዲስ ቤጂንግ ድረስ በትውስታ ወሰደኝ። ለኃይሌ እናንተ ኢትዬጲያውያን መኪና ትበላላችሁ እንዴ? በማለት የጠየቀው ፈረንጅ የየት አገር ዜጋ ሊሆን እንደሚችል ግምቴን አስቀመጥኩ። የመብራት ፓል እየገጨ አዲሳአባን በጨለማ የሚያውላት ሰካራም ስሙ ማን ሊሆን እንደሚችል ጠረጠርኩ። ኸረ ወዲያ! ኸረ ወዲያ! አሁን እውነት ከህውሓቶች ውጭ ከኃይለማርያም የሚብስ ሰው ይመጣል ብሎ የሚጠብቅ አለ?
የሆነው ሆኖ ከሲራጅ ፈጌሳ ወደ ” ወዲ ሽጉጤ!” ከመቅፅበት የተቀየረው ድራማ አንዲት ነገር አስታወሰኝ። ታሪክ ራሱን በቧልት መልኩ ይደግማል ያልኩት በዚህ ምክንያት ነው። ታሪኩ ፎርቹን በሚባለው ጋዜጣ ላይ ወጥቶ ስለነበር እንዲሁም ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና በተደጋጋሚ የሚያነሳው በመሆኑ በብዙዎች ጭንቅላት ውስጥ እንደሚኖር እገምታለሁ። የመጀመሪያው ታሪክ ባለቤት ሟቹ መለስ ዜናዊ ሲሆን ተጨዋቾቹ አባዱላ ገመዳና ሟቹ አለማየሁ አቶምሳ ናቸው። የዛሬዎቹ ቧልተኛች ጄኔራል ሳሞራ ( ሲራጅ) እና ጌታቸው አሰፋ ( ሽፈራው ሽጉጤ) ናቸው። ታሪኮቹ ተመሳሳይ ስለሆኑ የሟቹ መለስ ዜናዊን ላጫውታችሁ እና መጣጥፌን ልቋጭ።
እንዲህ ነበር የሆነው፣
የኦህዴድ ማእከላዊ ኮሚቴ በአዳማ ይሰበሰባል። አጀንዳው የድርጅት ሊቀመንበር ምርጫ በመሆኑ አባዱላ ኔትወርኩን ተጠቅሞ በሙሉ ድምፅ ራሱን ሊቀመንበር ያስመርጣል። አባዱላ ራሱን ማስመረጡ ያበሳጨው መለስ ዜናዊ አባዱላ ስብሰባውን አቋርጦ ወደ አዲሳባ እንዲመጣ ያደርገዋል።በማስፈራራት አለማየሁ አቶምሳን በአስቸኳይ እንዲተካ ይነግረዋል። ውሃ የገባ ፀጉራም ውሻ የሆነው አባዱላ በውስጡ ቂም ቋጥሮወደ አዳማ በመመለስ ” ራሴን አግልያለሁ አለማየሁ አቶምሳ ሊቀመንበር እንዲሆን አቅርቤያለሁ!” ይላል።ለጥቂት ሰአታት የማእከላዊ ኮሚቴው የብርጭቆ ማዕበል አስነስተው ድምፅ እንስጥ ይባባላሉ። ከአንድ ሰው በስተቀር አባዱላ ተሽሮ አለማየሁ አቶምሳ ይተካ በሚለው ላይ ይስማማሉ። በነገራችን ላይ አባዱላ በውጭ ተፅእኖ መቀየር የለበትም ብሎ ድምፅ የሰጠው የዛሬው የኦሮሚያ ሊቀመንበር ለማ መገርሳ ነበር። የዛሬው የቲም ለማ ቡድን መሪ።እነሆ! አለማየሁ አቶምሳ ብዙም ሳይቆይ የተመረዘ ውሃ እንዲጠጣ በማድረግ የቂም ቋጠሮው ፍቺ አገኘ። ፀረ ሌባው አለማየሁ አቶምሳ ለዘላለም አሸለበ።ለማ መገርሳ የአለማየሁ እጣ እንዳይደርሰው የእግዜር መላእክት ክንፋቸውን ይዘርጉለት።

No comments:

Post a Comment