ኤርሚያስ ለገሰ
#1: መግቢያ
በአቶ ለማ መገርሳ ሊቀመንበርነት የሚመራው የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በአዳማ የ10 ቀን ዝግ ስብሰባ ለማድረግ ተቀምጧል። በዚህ ስብሰባ ላይ የተለያዩ ድርጅታዊ፣ ክልላዊ፣ አገራዊ እና አለም አቀፋዊ ሁኔታዎችን በመመርመር ታላላቅ ውሳኔዎችንና የቀጣይ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥ በግምገማው ቃል አቀባይ ተነግሯል። የድርጅቱ ስራ አስፈፃሚ እና የግምገማው ቃል አቀባይ አቶ ሐብታሙ ሐ/ ሚካኤል ለየኦሮሞ ብዙሃን መገናኛ ( OBN) በሰጠው መረጃ መሰረት ግምገማው በአሁን ሰአት ወደ አቢይ አጀንዳዎች ተሸጋግሯል።
ከእነዚህ አቢይ አጀንዳዎች መካከል በአገሪቱ የንግድ ስርአት ላይ ውይይት እየተደረገ መሆኑ ቃል አቀባዩ ተናግሯል። የንግድ እንቅስቃሴው ስልጣንን ተገን በማድረግ በተወሰኑ አካላት ተይዞ የኦሮሚያን ኢኮኖሚ እያቀጨጨው መሆኑ በጥልቀት መታየቱን ገልጿል። ስልጣንን መሰረት በማድረግ በተወሰኑ አካላት የሚለውን በቀይ ብዕር አስምሩልኝና ወደ ቃል አቀባዩ መግለጫ እንመለስ። አቶ ሐብታሙ ለOBN በሰጠው መግለጫ ላይ፣
” የአገሪቱ የንግድ ስርአት ከአድሎነት የፀዳ ነወይ? የንግድ ስርአቱ በፍትሐዊነት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል እኩል ተጠቃሚ እያደረገ ነወይ? ወይንስ የተወሰኑ አካላት ብቻ ከድንብር ድንበር እየተዘዋወሩ እንደፈለጉት ተጠቃሚ የሚሆኑበት ነው? በሚለው ጉዳይ ላይ በጥልቀት ተወያይተናል። በአገሪቱ የንግድ ስርአቱ ውስጥ ትልልቅ ችግሮች አሉ። ስልጣንን ተገን በማድረግ በተወሰኑ አካላት ተይዞ ያለ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ አራማጆች ላይ ታግለን መስመር እንዲይዙ በማድረግ ረገድ ምን እንደምንመስል ፈትሸናል” ብሏል።
#2: የፕሮፐጋንዳው ( ህዝብ ግንኙነቱ) አካሄድ
በንግድ ስርአቱ ላይ የለማ ቡድን ያደረገውን አበረታች ምርመራ ግኝቶቹ ላይ ከማተኮሬ በፊት በስብሰባው አካሄድና መረጃው ለህዝብ እየቀረበበት ባለበት ሁኔታ ላይ ጥቂት ልበል። እዚህ ላይ የህዝብ ግንኙነቱን በቅድሚያ መመልከት የፈለግኩት በደባል አሳብነት ላቀርብ የምፈልገው ነጥብ ስላለኝ ነው።
የመጀመሪያው ለማ መገርሳ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ(ሰአኮ) ያደረገውን ግምገማ አስመልክቶ አራቱ ሊቀመናብርት በቤተመንግስት መግለጫ ሲሰጡ አንድ ነገር ተናግሮ ነበር። በግምገማው ላይ ያደረጉትን ተጋድሎ የኢትዬጲያ ህዝብ እንዲያውቀው በቀጥታ ስርጭት ቢተላለፍ ፍላጐቱ እንደነበር አሳውቋል። በወቅቱ የህውሓት ማእከላዊነት ጥሶ በድፍረት ፍላጐቱን በይፋ መናገሩን አድንቀንለት ነበር። ግን ደግሞ የትግራይ ነፃ አውጪ እና ሁለቱ ጠፍጥፎ የፈጠራቸው ድርጅቶች( ብአዴን እና ደኢህዴግ) ሳይስማሙ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስቸግር አስተያየት ተሰጥቷል። ሆኖም ግን ቲም ለማ በራሱ የስልጣን እርከን ውስጥ የሚካሄደውን የኦህዴድ ሰአኮ ግምገማ በቀጥታ እንዲሰራጭ ማድረግ እንደሚገባው ምክረ ሃሳብ ሰጥተን ነበር። ይሄን ማድረግ ግልፀኝነትን ከማሳየቱም በላይ በኦህዴድ ውስጥ ማን ከኢትዬጲያ ህዝብ ጐን እንደቆመ፣ ማን የትግራይ ነፃ አውጪን ተልእኮ ለማሳካት እንደሚንቀሳቀስ በቀጥታ መገንዘብ እንደሚያስችል ተገልጦ ነበር። ከዚህ አንፃር Team ለማ ከባድ ነጥብ ጥሏል። እናም ለምን የቀድሞ ፍላጒቱን በራሱ የስልጣን ማእቀፍ ውስጥ ማድረግ እንዳልቻለ በይፋ መናገር ይኖርበታል። አለበለዚያ አንቺው ታመጭው፣ አንቺው ታሮጭው ይመስልበታል። በባላንጣዎቹም መዘባበቻ ይሆናል።
በሌላ በኩል የግምገማውን ሂደትና የተደረሰበትን ድምዳሜ እየተገለፀበት ያለው አግባብ ከላይ የተነሳውን ጥፋት ባይጋርደውም ከፍተኛ ለውጥ የታየበት ነው። የተመረጠው የህዝብ ግንኙነት ስልት የለማ ቡድን ሀላፊነት እና ሚናውን በተሻለ ሁኔታ አሳይቶበታል። አንደኛ: መግለጫው እየተሰጠ ያለው በፓሊት ቢሮ ደረጃ ባለ ከፍተኛ ካድሬ ነው። ስጠረጥር ወጣት ሐብታሙ ሐ/ሚካኤል የቲም ለማ አካል ይመስላል። ርግጥ ወጣቱ የስብሰባውን ውጤቶች በሚፈለገው መልኩ ገለጥለጥ አድርጐ ማሳየት ባይችልም ለፍተሻ በቂ ተደርጐ ሊወሰድ የሚችል ነው። ሁለተኛ: መረጃዎቹ ለህዝብ እየተሰራጩ ያሉት በኦሮሞ ብዙሃን መገናኛ ( OBN) አማካኝነት ነው። ይሄ አካሄድ ከዚህ በፊት በሞኖፓሊ ያለ ከልካይ መረጃ ሲቀበሉና ሲያሰራጩ የነበሩትን የትግራይ ነፃ አውጪ የሚዲያ ተቋማትንና የፌስቡክ ስኳዶች ( የኮካ አለቆች) ያስደነገጠ ነው።
የትግራይ ነፃ አውጪ የፌስቡክ አለቆች ድንጋጤያቸው እንዳይታወቅና አጀንዳ ለማስቀየር አርበኞች ግንቦት ሰባት እና ኢሳት ላይ ባለ በሌለ ሐይላቸው ርብርብ አደረጉ። አርበኞች ግንቦት ሰባትና ኢሳት ካልተዳከሙ በስተቀር የሚፈልጉት የዘር ( DNA) አደረጃጀት እና “የጐሳ ሚዲያ” መመስረት የማይችሉ የሚመስላቸው ( ጭንቅላት፣ ልብ፣ አንጀት፣ምላስ፣ እጅና እግራቸውን ያሰርናቸው ይመስል!) ከትግራይ ነፃ አውጪ የፌስ ቡክ ሰራዊት አለቆች ጋር ተጃምለው ገቡ።ለኮካ አለቆች በጊዜያዊነት አጀንዳ ለማስቀየስ ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረላቸው። ጊዜያዊ የሆነበት ምክንያት ቲም ለማ በአዳማ የደገሰላቸው ድግስ አይደለም እነሱን እናት ድርጅታቸውን የሚያስደነግጥ ስለሆነ ነው።
እየተሰማ እንዳለው ከሆነ አዳማ የከተመው የለማ ቡድን ጠንካራ ውሳኔዎችን እየወሰነ ነው። የትግራይ ነፃ አውጪ ተላላኪ ከሆኑት ውስጥ እንደ አስቴር ማሞ፣ ሶፊያን አህመድ አይነቶቹን አባረዋል። ሶፊያን ከተዘፈቀበት ሌብነት እና ዝርፊያ አንፃር እግረ ሙቅ እንዲጠልቅለት አስተያየት እንደቀረበም ተሰምቷል። በሌላ በኩል የበረከት ስምኦን እና የትግራይ ነፃ አውጪ ጠላት የሆነው ሱሊማን ደደፎ ወደ ስራ አስፈፃሚ መጥቷል።( ሱሊማን የኢትዬጲያን መርከቦች አስመልክቶ ለውጭ ጉዳይ የፃፈው እና ሾልኮ የወጣው ደብዳቤ የትግራይ ነፃ አውጭን የአለም አቀፍ ፍርድ ቤት የሚያስከስሰው እንደሆነ ልብ ይሏል።) የለማ ቡድን OBN በተመለከተም ከማንም ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆኖ እንዲሰራ ከሚዲያው ጐን እንደሚቆም ቃል ገብቷል። ይሄ ዘርአይ አስግዶምን ለመሰሉ የትነግ የሚዲያ ጠርናፊዎች፣ የትነግ የሚዲያ ተቋማትና የፌስቡክ የኮካ አለቆች ሌላ ራስ ምታት ነው።
እርግጥም የለማ ቡድን የገባውን ቃል ኪዳን የሚጠብቅ ከሆነ የኦሮሞ ህዝብ የኢትዬጲያን አንድነት ለማስጠበቅ የከፈለውን ጀግንነት ሳይበረዝ በሚዲያው እንሰማለን። የኦሮሞ ህዝብ በአገር ፍቅር ስሜት የውጭ ጠላቶቹን ለመመከት ያደረገውን ተጋድሎ በዘጋቢ ፊልም ቀርቦልን እንማርበታለን። OBN ነፃነቱን ከተጐናፀፈ የጐብልስን “ኩሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል” ስራ የያዙትን የትነግ የሚዲያ ተቋማትና የፌስቡክ የኮካ አለቆች እርቃናቸውን ያስቀራል። በምትኩም እውነትን በመግለጥ ብሔራዊ ስሜትን ለመቅረፅና ኢትዬጲያዊ ወኔን ለማነሳሳት እድል ያገኛል።
#3:የንግድ ስርአቱና “የTeam ለማ” ግኝት
የለማ ቡድን ስብሰባውን ሲጨርስ በሚያወጣው መግለጫ አብነቶች እያስቀመጠ የትግራይ ነፃ አውጪ ለ26 አመት የተገበረውን ወንጀለኛ የንግድ ስርአት እንደሚነግረን ይጠበቃል። ለጊዜው በቃል አቀባዩ ሐብታሙ ሐ/ሚካኤል አማካኝነት የአገሪቱ የንግድ ስርአት አድሎአዊ እንደሆነ አስረግጦ ነግሮናል። ሐብታሙ የንግድ ስርአቱ ፍትሐዊ እንዳልሆነ አረጋግጧል።በተለይም ስልጣንን ተገን በማድረግ የንግድ ተቋማት በተወሰኑ አካላት ቁጥጥር ስር እንደዋሉ ማረጋገጫ ሰጥቷል። እነዚህ ለጊዜው ስማቸው ያልተጠቀሰ የተወሰኑ አካላት ስልጣናቸውን ተጠቅመው ከድንበር ድንበር እየተዘዋወሩ እንደሚፈልጉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታ እንደፈጠሩ ግኝቱን አቅርቧል።
እውነቱን ለመናገር አዳማ የመሸገው የለማ ቡድን የአገሪቱን የንግድ ስርአት አስመልክቶ አስተውሎት ያነገበ ድምዳሜ አስቀምጧል። ይህ ነገ ከነገ ወዲያ በዳኝነት መንበር ላይ የሚመዘን አስተውሎት የተፈፀሙ ወንጀሎችን ለማመን ያለውን ፍላጐት የሚፈነጥቅ ነው። ከቃል አቀባዩ አንደበት እንደተረዳሁት የለማ ቡድን የግምገማ ውጤት የንግዱ ስርአት ብሎም የኢኮኖሚ ግንባታው “ወዴት እየሔደ ነው?” ከሚለው ባሻገር ” ወዴት መሄድ አለበት?” ወደሚለው በቁጭት የመምራት ፍላጐት የታየበት ነው። በአጠቃላይ መልኩ የአገሪቱን የንግድ ስርአት አስመልክቶ የተገለጠው የትግራይ ነፃ አውጪ የገነባው የንግድ ስርአት ምን ያህል አደገኛና ለራሱ የንግድ ድርጅቶች ብቻ ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑን ነው።
#4:የለማ ቡድን ቀጣይ ሐላፊነት እና ሚና
አዳማ የተቀመጠው የለማ ቡድን የሕዝብ ቁጣና የመደፈር እልህ ያቃጠለው ሁሉ በአንድነት መነሳቱን አይቶ ጠንካራ ውሳኔ አሳርፏል። በዚህም የተነሳ የትግራይ ነፃ አውጪ ከመጀመሪያው የአገዛዝ ቀን አንስቶ በሌላው ህዝብ ኪሳራ ና ማቆርቆዝ ላይ ተመስርቶ የሃብት ማማ ላይ መውጣቱን በእንድምታ (Deductive logic) ነግረውናል። መቼም ባለፋት 26 አመታት ስልጣኑን ተጠቅሞ ከጫፍ እስከ ጫፍ ንግዱን ያጧጧፈው ማን እንደሆነ መናገሩ ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል።
ተደጋግሞ እንደታየው የኢትዬጲያ ህዝብ ወደ አደባባይ በመውጣት በጥይት የተጨፈጨፈው ኢፍትሐዊነት የፈጠረበትን የሕሊና ህመም መቋቋም ባለመቻሉ ነው። ለለማ ቡድንም ቢሆን ቅፅበታዊ አቀጣጣይ ሆኖ ለሕዝቡ ተቆርቋሪ እንዲሆንና በሕዝቡ ህሊና ውስጥ ስሙ እንዲገዝፍ የሆነው ህዝባዊ ማዕበሉ የማይቆም በመሆኑ ነው። እርግጡን እንነጋገር ከተባለ ይህ የለማ ቡድን ውሳኔ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተቃራኒው የግል ሀብትንና ስልጣንን የማደላደል ቢሆን ኖሮ ወደ ፍፅም አፓርታይድነት እየተቀየረ ላለው ዘረኛ አገዛዝ መስሎ መደር ይቻል ነበር። በኢትዬጲያውያን ሕይወትና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ብዝበዛ አይቶ እንዳላየ አሊያም የድርሻን መዝረፍ ይቻል ነበር። በመሆኑም Team ለማ የትግራይ ነፃ አውጪ የበላይነት፣ የትግራይ ዋነኛ ተጠቃሚነት፣ አግአዚነት ላይ የጋረጠውን አደጋ ወደ ተግባር እንዲመነዝረው መጐትጐት ( “መደገፍ”) ያስፈልጋል።
ለለማ ቡድን ከሚሰጠው ድጋፍ ውስጥ የቅድሚ ቅድሚያ የሚሆነው እና ለድርድር የማይቀርበው ጉዳይ ሕዝባዊ እምቢተኝነትን አጠናክሮ መቀጠል ይሆናል። የቡድኑ አባላት አፍ አውጥተው አይናገሩት እንጂ ህዝባዊ እምቢተኝነት ነዳጃቸው ነው። ነዳጅ የሌለው መኪና ሹፌሩ ምንም ያህል ጐበዝ ቢሆን መሄድ እንደማይችለው ሁሉ ህዝባዊ እምቢተኝነት ከሌለ የለማ ቡድን ይሸነፋል። ከጨዋታ ውጭ ይሆናል።በምትኩም በኦህዴድ ውስጥ የተገዥነት ስነ ልቦና ያላቸው ሰዎች በትግራይ ነፃ አውጪ ጉልበት ወደ ፊት ይመጣሉ። በሂደትም የስርአት ለውጥ ፈላጊዎቹ በሚደርስባቸው አካላዊና መንፈሳዊ ዛቻ ሰማይ እንደ አክንባሎ የተደፋባቸው ሊመስላቸው ይችላል። እናም በአጭር ጊዜ ውስጥ ባልተጠበቀ ሁኔታ የትግራይ ነፃ አውጪን ይቅርታ ጠይቀው ከኢትዬጲያ ሕዝብ ጋር ለመጨረሻ ጊዜ ሊቆራረጡ ይችላሉ። በመሆኑም ቲም ለማ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሄድ ዋስትናው አንድ እና አንድ ብቻ ነው። ያልተቋረጠ ህዝባዊ እምቢተኝነት! ያልተቋረጠ ህዝባዊ ማእበል!
ለለማ ቡድን ከሚሰጠው ድጋፍ ውስጥ ቀጣይ የሚሆነው ውሳኔያቸውን ሊያጠናክር የሚችል ሀሳቦችን መስጠት ይሆናል። ለምሳሌ ያህል ከኢፍትሐዊ የንግድ ስርአቱ ጋር በተያያዘ ቡድኑ በአጭር ቀናት ውስጥ መስራት ያለበት ነገር አለ። ከእነዚህ መካከል፣
* የትግራይ ነፃ አውጪ ንብረት የሆነው ጉና ትሬዲንግ በኦሮሚያ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ማገድ። ሁሉም እንደሚያውቀው የኤፈርት ንብረት የሆነው ጉና የኢትዬጲያን የቡና ኤክስፓርት 33 በመቶ ይዟል። ይሄንን ቡና የሚወስደው ከኦሮሚያ እና ደቡብ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ጉና በኦሮሚያ ከተሞች በራሱ እና በአብዛኛው በግለሰብ ስም የያዛቸው የጅምላ እና የችርቻሮ ሱቆች አሉት። እነዚህን በአጭር ጊዜ አጣርቶ መዝጋት።
* በኦሮሚያ ቅርንጫፍ የከፈቱትን የኤፈርት ንብረት የሆኑትን የፋይናንስ እና የኢንሹራንስ ተቋማት በአስቸኳይ መዝጋት። ከእነዚህ ውስጥ ወጋገን ባንክ፣ አንበሳ ባንክ፣ አፍሪካ ኢንሹራንስ…ወዘተ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል።
* በኦሮሚያ የተገነቡና ንብረትነታቸው የኤፈርት የሆኑትን ፋብሪካዎች የግንባታ፣ የማሽን ግዢና ተመሳሳይ ክፍያዎችን በመክፈል በጊዜያዊነት መውረስ። በሂደት በግልፅ ጨረታ ወደ ግል ማዞር።
*በኦሮሚያ ዋና ዋና ከተሞች የሚገኙ የትግራይ ልማት ማህበር ፅህፈት ቤቶች እና ንብረቶችን መውረስ። የማህበሩ ንብረት የሆነው ሰላም ባስ በኦሮሚያ እንዳይንቀሳቀስ ማገድ።የትግራይ ልማት ማህበር አባላትን ስም ዝርዝር በመያዝ የትግራይ ነፃ አውጪ አባል መሆን እና አለመሆናቸውን ማጣራት። የነፃ አውጪ አባልነታቸውን በፍቃደኝነት መሰረዝ ፍቃደኛ ካልሆኑ ነፃ ወዳወጡበት አካባቢ እንዲሄዱ በሰላም መሸኘት።
* የህውሓት አባላት ሆነው በኦሮሚያ ንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ግለሰቦች ቢዝነስ እና ኢንቨስትመንታቸውን እንዲያቋርጡ ማድረግ። የትግራይ ተወላጅ ሳይሆኑ ከህውሓት/ ኢህአዴግ የንግድ ተቋማት እና ባለስልጣኖች ጋር በመሻረክ ቢዝነስ የከፈቱትን በሙሉ ማገድ።
No comments:
Post a Comment