በኤፍሬም ማዴቦ
አባባ . . . አባባ . . . . ስማ አባባ ረሳህ እንዴ አለኝ ያ ባለፈዉ ነኃሴ ወር ስንለያይ ያስለቀሰኝ ልጄ። ምኑን አልኩት። ቅድም ምሳ ላይ የነገርኩህን . . . እንዴ! እሱንማ እንዴት እረሳለሁ። Please don’t አባባ! …… I will not! ሲረጋጋና ደስ ሲለዉ ታየኝና ልቤን ደስ አለው። ልጄ ኮሌጅ የሚገባበት ቀን እኔ ደግሞ ከትግል ጓደኞቼ ጋር የምንገናኝበት ቀን ናፍቆናል። አባባ Good luck አለኝ። እኔም ይቅናህ አልኩት። Good luck እና ይቅናህ የተባባልነው እኔ እሱ የሚመኘዉ ኮሌጅ እንዲገባ እሱ ደግሞ እኔ በድል ኢትዮጵያ እንድገባ ነበር። ሁለታችንም ይቅናን . . . አሜን!!!
አዉሮፕላን ዉስጥ ገብቼ ከተረጋጋሁ በኋላ ኢር ፎኑን ጆሮዬ ውስጥ ሰክቼ አይፎኔ ላይ “Play” የሚለዉን ስጫነዉ ጥላሁን ገሰሰ “አራዊቱ ሁሉ መጥቶ ቢከበኝ” እያለ ጀመረኝ። የምወደው ዘፈን ነበርና ደጋገምኩት። ጥላሁንኮ ድምጻዊ ብቻ አይደለም ነቢይም ነዉ፤ የዛሬ ስንትና ስንት አመት በአራዊቶች እንደምንከበብ ተንብዮ ነበር። የሚቀጥለው ዘፈን ገና ሲጀምር ምን መሆኑ ታወቀኝና. . . . . ኧረ በፍጹም. . . እንዴት ተደርጎ አልኩና አይፎኔን ዘግቼዉ ኪሴ ዉስጥ ከተትኩት። “መለያየት ሞት ነዉ” የሚለዉን የጥላሁን ገሰሰ ሙዚቃ ብወደዉም የጠነከረዉ ሆዴ እንዲባባ በፍጹም አልፈለኩም። አይፓዴን አወጣሁና የአስናቀች ወርቁን ሰዉነት እየሰረሰር ገብቶ አንጀት የሚያርስ ክራር መኮምኮም ጀመርኩ። አስናቀች ኢትዮጵያን ጨምሮ ብዙ ቦታ ወሰደችኝ፤ ደግነቱ ዬትም ትዉሰደኝ ዬት መልሳ መላልሳ እዚያዉ አዉሮፕላኑ ውስጥ ታመጣኝ ነበር . . . አለዚያማ!
አዉሮፕላኑ ወንበር ላይ አንደተኛሁ ከአንድ ጎኔ ወደ ሌላዉ ጎኔ ስገላበጥ ሁለት የተለያዩ ድምጾች ተራ በተራ ጆሮዬ ዉስጥ ገቡ። ከአይፓዴ የሚወጣዉ ድምፅ “እልም አለ ባቡሩ” ይላል፥ የአዉሮፕላኑ ድምጽ ማጉያ ደግሞ “Welcome to Munich” ይላል። እንቅልፋም አይደለሁም፥ እንቅልፌን ሳልጨርስ የሚቀሰቅሰኝ ሰዉም ሆነ ምንም አይነት ድምጽ ግን ጠላቴ ነዉ። ደግሞም የእንቅልፍ ነገር ሆኖብኝ ነዉ እንጂ ሙኒክ መድረሴን ወድጄዋለሁኮ።
እኔንና ሌሎች ከ180 በላይ መንገደኞችን የጫነዉ ዩናይትድ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 106 አዉሮፕላን ጎማዎች ከሙኒክ አዉሮፕላን ማረፊያ ወለል ጋር ሲላተሙ ያ ለካሳ ተሰማ ዘፈን አልበገር ያለዉ እንቅልፌ ዳግም አይመጣ ይመስል እልም ብሎ ጠፋ። እኔም የምን እንቅልፍ አልኩና ሙኒክን ለማየት ቸኮልኩ። ሙኒክ ሲባል ከልጅነቴ ጀምሮ እሰማለሁ እንጂ እቺን ዉብ የባቫሪያ ከተማ ሳያት የመጀመሪያዬ ነበር። አይፎኔን አወጣሁና ከአስመራ አሜሪካ ከገባሁ ጀምሮ ስልክ እየደወለ ሙኒክ ካልመጣህ እያለ ለሚጨቀጭቀኝ የአገሬ ሰዉ ስልክ ደወልኩ. . . . ጋሼ ደረስክ እንዴ አለኝ። አዎ እናንተን እየጠበኩ ነዉ አልኩት። ጋሼ እኛ መግባት አንችልም ስትወጣ ታየናለህ አለኝ። ሁለት ተንጠልጣይ ሻንጣዎቼን ግራና ቀኝ ትከሻዬ ላይ አንጠልጥዬ ሻንጣ የጫንኩበትን ጋሪ እየገፋሁ ወደ መዉጫዉ አመራሁ። የሁለቱ ሻንጣዎች ክብደት ትከሻዬን ሲያጎብጠዉ ግዜ ሁለተኛ ለማንም ሰዉ ዕቃ አላደርስም ብዬ ማልኩ። ሁሌም እየማልኩ የምረሳዉ መኃላ ቢኖር ይህ ብቻ ነዉ። ወደ መዉጫዉ ስጠጋ በሩ ወለል ብሎ ተከፈተ። ታክሲዉና አዉቶቡሱ፤ ሸኚዉ፤ እንግዳ ተቀባዩ፤ እኔን መሰሉ ወደ ሙኒክ የሚመጣዉና ሙኒክን የሚለቀዉ መንገደኛ እዚህም እዛም ይተራመሳል። ከዚህ ሁሉ የሰዉና የመኪና ትርምስ ዉስጥ አይኔ ተሽቀዳድሞ ያረፈዉ በዚያ በዉበቱና በድምቀቱ የባንዲራዎች አዉራ በሆነዉ የአገሬ ባንዲራ ላይ ነበር። ሊቀበሉኝ የመጡ ሁለት ኢትዮጵያዉያን ያንን በትንሽነቴ “ደሙን ያፈሰሰ” ብዬ የሰቀልኩትንና ማታ “ተጣማጅ አርበኛ” ብዬ ያወረድኩትን የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ይዘዉ ሲመጡ አየሁና ተጠጋኋቸዉ። ሰንደቅ አላማዉ “አምባሻ” ስለሌለበት አመንኳቸዉ። አለዚያማ ፊቴን አዙሬ ጉዞዬን ወደ አስመራ እቀጥል ነበር እንጂ አምኜ አልጠጋቸዉም ነበር። ወይ ጉድ …… ዘመን አያመጣዉ ነገር የለም. . . . . . የምንተነፍሰዉንም አየር መጠርጠር ጀመርንኮ!
ሙኒክ የገባሁት ሐሙስ ጧት አስር ሰአት ተኩል ላይ ነበር። እሁድ ጧት ለስራ ጉዳይ ሲዊዘርላንድ እስክሄድ ድረስ ከሁለት ቀን ተኩል በላይ ሙኒክ ዉስጥ ቆይቻለሁ። ግን እንኳን ሁለት ቀን ተኩል ግማሽ ቀንም የቆየሁ አልመሰለኝም። ነገሩ ምንድነዉ ብዬ ተገረምኩ። ሚስጢሩ የገባኝ አስመራ ገብቼ ከእንቅልፌ ስነቃና የቀረብኝን ሳዉቀዉ ነዉ። ሙኒኮች በልቼ የምጠግብ፥ ጠጥቼ የምረካ አይመስላቸዉም። ያገኙኝ ሰዎች ሁሉ ብላ፤ጠጣ፤ እንሂድ፤ እንዉጣ፤ ምን እንግዛ፤ ምን እናምጣ፤ ምን ትፈልጋለህ፤ ምን አነሰ ነዉ ጥያቄያቸው። የሙኒክ ወገኖቼ ከኑሯቸዉ በላይ ሲያስቡልኝና ከራሳቸዉ በላይ ሲሳሱልኝ አይቼ እንደ ዐለት የማይነቃነቅ ደጀን አለኝ ብዬ ተመክቼባቸዋለሁ። በተለይ ሙኒክ ውስጥ ያየኋቸዉ ሴቶች እህቶቼ መጥተን እንቀላቀላችሁ እንጂ ከተማ ዉስጥማ ምን እናደርጋለን ነበር ጥያቄያቸዉ። የሙኒክ ሴቶች ደሜ ዉስጥ የቀረዉን የመጨረሻ የፍርሃት ጠብታ ጠራርገዉ ሲወስዱት ታወቀኝና ድፍረቴ ከአናቴ አልፎ ሲያንሳፍፈኝ ተሰማኝ። እቴጌ ተዋበች ለቋራዉ አንበሳ እቴጌ ጣይቱ ደግሞ ለዳግማዊ ምንሊክ ጉልበት፤ ብርታትና ጽናት እንደሆኗቸው ሁሉ ለኔም የሙኒክ ሴቶች ደሜ ዉስጥ ገብተዉ ብርታት፤ ልቤ ዉስጥ ገብተዉ ጽናት ሆኑኝ። አደራ. . . . ሴት የላካዉ ሞት አይፈራም ብላችሁ ለቆራጥ እህቶቼ የምሰጠዉን ምስክርነት እንዳታሳንሱብኝ። የሙኒክ ሴቶች የልብ ልብ የሰጡኝ ዕቃችንን ጠቅልለን ካልተከተልንህ እያሉ ነዉ እንጂ አይዞህ በርታ አለንልህ እያሉ ብቻ አልነበረም።
ቀኑን እንደ ደዋሪ ከወዲህ ማዶ ወዲያ ማዶ ስሽከረከር ዉዬ ስለደከመኝ አርብ ዬካቲት 26 ቀን (Feb 26) አልጋዬ ዉስጥ የገባሁት በግዜ ነዉ። ከሆቴሉ ሰራተኛ ቁልፍ ተቀብዬ መኝታ ክፍሌ ስደርስ አልጋዋ እንኳን ሙሉዉን ኤፍሬም አንድ እግሩንም ተሸክማ የምታድር አልመሰለችኝም። ትንሽዬ አልጋ ናት። ሽንት ቤቱና መታጠቢያ ቤቱም እንደዚሁ። ብቻ ምን አለፋችሁ አዉሮፓ ዉስጥ ትልቅ ነገር ያለም አይመስል። መንገዱ፤ መኪናዉ፤ ሀንጻዉና መኖሪያ ቤቱ ሁሉም ነገር ትንሽ ነው። አዉሮፓዉያን አንድ ነገራቸዉ ግን ትልቅ ከትልቅም ትልቅ ነዉ። ለሀይል ቁጠባና (Energy Conservation) ለአካባቢ ጥበቃ የሚሰጡት ቦታ እጅግ በጣም ትልቅ ነው። አዉሮፓ ስሄድ ሁለት ጉዳዮች ነበሩኝ። አንደኛዉ የሙኒክ ኢሳት ቤተሰቦች ባዘጋጁት የገንዘብ ማሰባሰብ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ የትግል ጓደኛዬን የአንዳርጋቸዉ ጽጌን 61ኛ አመት የልደት በዐል ሲዊዘርላንድ ዉስጥ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ ጋር ለማክበር ነዉ።
አርብ ማታ በግዜ ቆጤ ላይ ስለተሰቀልኩ ቅዳሜ ዬካቲት 27 ቀን ከእንቅልፌ ስነቃ እንደልማዴ እየደጋገመ አላዛጋኝም ወይም ተኛ ተኛ አላሰኘኝም። ፈጣን ሻወር ወስጄ ልብሴን ለባበስኩና ያደርኩበት ሆቴል በነጻ ብላ ያለኝን ቁርስ መቆርጠም ጀመርኩ። ከቁርሱ ይልቅ የጣመኝ ቡናዉ ነበርና አንዴ ደግሜ ሶስተኛዉን ይዤ ጠረቤዛ ቀየርኩና አይፓዴን ከፍቼ ዜና መቃረም ጀመርኩ። ኦሮሚያ ዉስጥ ከሦስት ወራት በፊት የተቀሰቀሰዉ ሀዘባዊ ቁጣ አለመብረዱ፤ የአዲስ አበባዉ ታክሲ ሾፌሮች አድማና ጎንደር ዉስጥ በየቦታዉ የሚፈነዳዉ ህዝባዊ አመጽ ትኩረቴን ከሳቡ ዜናዎች ዉስጥ ዋና ዋናዎቹ ነበሩ። ዜና ማንበቡን ጨርሼ ቀና ስል ጋዜጠኛ ሀይሉ ማሞና ጓደኛዉ መጡና . . . ጋሼ ምሳ እንብላ እንጂ ብለዉኝ ተያይዘን ወጣን።
ፉጨቱ፤ ሆታዉ፤ መዝሙሩና አዳራሹ ዉስጥ በየማዕዘኑ የሚዉለበለበዉ ሰንደቅ አላማችን ገና ስብሰባው አዳራሽ ዉስጥ ሳልገባ በሩቁ የአዳራሹን ስሜት ነገረኝ። አዳራሹ ዉስጥ ያሉት ኢትዮጵያዉያን አላማቸዉ አላማዬ ምኞታቸዉ ምኞቴ እንደሆነ ካውቅኩ ቆይቷል። አዳራሹ ዉስጥ ገብቼ ስሜታቸዉን ሳይ ግን ልባቸዉ ከልቤ ተገናኘና ደሜ ደማቸዉ፤ ሞቴ ሞታቸዉ መሆኑ ዉስጤ ድረስ ዘልቆ ተሰማኝ። ከሰዉነቴና ከሰዉነታቸዉ የአካል ፍላጭ ወጥቶ አዲስ አካል ሲፈጠር ታወቀኝ። አዎ. . . ዜግነት መሰረቱ፤ እኩልነት ማዕዘኑ፤ ነጻነት ጣራዉ፤ ፍትህ ወለሉ፤ አንድነትና ዲሞከራሲ ድርና ማጉ የሆነ ፍጹም አዲስ አካል ሲፈጠር ተሰማኝ። ፍጹም ልዩ ስሜት ነበርና ወደድኩት። አዳራሹ ዉስጥ ገብቼ ብዙም ሳልቀመጥ እኛ በህይወት እንድንኖር የሞት መስዋዕትነት ለከፈሉልን ጀግኖች የሂሊና ጸሎት እናድርስ ሲባል አዳራሹ ዉስጥ ያለዉ ሰዉ በሙሉ ከመቀመጫዉ ተነሳ። አዳራሹ ላንዳፍታ ሰዉ የሌለበት ኦና ቤት መሰለ። ያንን ሰው የሞላበት የስብሰባ አዳራሽ የዝምታ ጽላሎት ዋጠዉ። ሁላችንም በአንድ አፍንጫ እንተነፍስ ይመስል ትንፋሻችን እራሱ አንድ ሆነ።
ሁለቱ የኢሳት ጋዜጠኞች አፈወርቅ አግደዉና ሀይሉ ማሞ ማይክሮፎናቸዉን ጨብጠዉ መድረኩ ላይ ቦታ ቦታቸዉን ይዘዋል። አዳራሹን የሞላዉ ህዝብ እነሱን እነሱ ደግሞ ህዝቡን ያዩታል። ጋዜጠኛ ሀይሉ ማሞ ለእለቱ ጨረታ የቀረበዉን ዉብ የኢሳት አርማ ለተሰበሰበዉ ህዝብ ሲያሳይ ያ የሂሊና ፀሎት ሲደረግ ዝምታ የዋጠዉ አዳራሽ በጭብጨባ ጩኸት የፈረሰ መሰለ። ጨረታዉ በአንድ ሺ ዩሮ ተጀመረ። አፈወርቅ አግደዉ መድረክ ላይ ወጣና በዚያ ጀት ድምጹ ንግግሩን ሲጀምር አዳራሹ ዉስጥ ኢሳት ቴሌቭዥን የተከፈተ መሰለኝ። ከጋዜጠኛ አፈወርቅ አግደዉ አፍ እንደ አብሪ ጥይት እየተወረወሩ የሚወጡት ቃላት አድራሻቸዉ ጆሮ ሳይሆን የተሰበሰበዉ ሰዉ ኪስ ዉስጥ ይመስል ሁሉም እየተነሳ ያለዉን ይለግስ ጀመር። በአንድ ሺ ዩሮ የተጀመረው ጨረታ ብዙም ሳይቆይ አምስት ሺ ዩሮ ደረሰ። አዳራሹ ዉስጥ የነበርኩት ብቸኛ የበረሃ ሰዉ ጨረታዉ አምስት ሺ ዩሮ ላይ የሚቆም መስሎኝ ነበር። ምን ላድርግ እዉነቴን ነዉ። በረሃ ዉስጥ ብቸኛዉ የገንዘብ ቋንቋ ናቅፋ ብቻ ነው። አምስት ሺ ዩሮ ደግሞ እጅግ በጣም ብዙ ናቅፋ ነዉ። ለሁሉም ጨረታዉ እኔ እንዳሰብኩት አልቆመም፤ እንዲያዉም የማሸነፍ እልህ ዉስጥ በገቡ ከተሞችና ግለሰቦች መካከል ፉክክር ፈጠረና 6 ሺ፤ 7 ሺ፤ እና 8 ሺ እያለ ቀጠለ።
የሙኒክ ጨረታ ትዉስታቸዉ በበጋው ፀሐይና በክረምቱ ዝናብ የማይደበዝዝ ሶስት ትዝታዎች ጥሎብኝ አልፏል። ለወትሮዉ እኔ ጨረታ የማዉቀዉ ግለሰቦች በቡድን ወይም በግል ሲጫረቱ ነዉ። የሙኒኩን ጨረታ ለየት ያደረገብኝ አንዱ ነገር የጀርመን ኢትዮጵያዉያን ሙኒክ፥ በርሊን፥ ፍራንክፈርትና ኑረምበርግ. . . ወዘተ እያሉ በከተማ ጭምር ያደረጉት ጨረታ ነዉ። እንግዲህ ይታያችሁ አዉሮፓ ዉስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ጨረታ በተካሄድ ቁጥር የሚጫረቱት በግል፥ በቡድንና በከተማ ጭምር ከሆነ እነዚህ ኢትዮጵያዉያን ለፍትህና ለነጻነት ለሚደረገዉ ትግል የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ከሌሎቻችን ይበልጣል ማለት ነው። ሌላዉ የሙኒክ ትዝታዬ የጀርመን ኢትዮጵያዉያን ወያኔን ለማጥፋት በሚደረገዉ ትግል ዉስጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ባደረጉ ጀግኖች ኢትዮጵያዉያን በነ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ ርእዮት አለሙ፤ እስክንድር ነጋ፤ ኡስታዝ አቡበከር፤ በቀለ ገርባና አንዱአለም አራጌ . . . ወዘተ ስም መጫረታቸዉ ነዉ። በእነዚህ ጀግኖች ስም የተደረገዉ ጨረታ የጀግኖቹ ስምና ህያዉ ስራቸዉ ከልባችን እንዳይጠፋ ማድረጉ ብቻ ሳይሆን የእነሱን ፈለግ እንድንከተል የሚገፋፋ ነበርና ለሙኒኮች ያለኝ አድናቆት ከፍተኛ ነው። Dank u München!
ሶስተኛዉ ትዝታዬ ሙኒክን ለቅቄ አስመራ ከገባሁ ከሶስት ሳምንታት በኋላ አሁንም ፊቴ ላይ አለ። ካሁን በኋላም ቢሆን እየረሳሁ ብዉልና ባድር ሶስተኛዉን ትዝታዬን የምረሳ አይመስለኝም። ይህ እንደ አፍላ ፍቅር ልቤ ዉስጥ ተተክሎ የቀረዉ ትዝታ የሶስት ሰዎች ትዝታ ነዉ። በአንድ በኩል ፊት ለፊት የመጀመሪያዉ ረድፍ ላይ ተቀምጦ ከተሸነፍኩ ሞቼ እገኛለሁ የሚል ዶክተር አለ። በሌላ በኩል ደግሞ አዳራሹ ኋላ ሆነዉ አንሸነፍም ብለዉ የመሸጉ ባልና ሚስት አሉ። እነዚህ ሶስት ሰዎች ኋላና ፊት ተቀምጠዉ ያካሄዱት ለሰአታት የዘለቀ ፉክክር ተሰብሳቢዉን እንደ ልብ ሰቃይ ድራማ ከፍና ዝቅ ያደረገ ልዩ ትርዕት ነበር።
ዶክተሩ የህክምና ዶክተር ነዉ። ታላቄ ነዉ ሆኖም በቁመት እንጂ በዕድሜ ብዙ አንበላለጥም። የምፈልገዉን ነገር አድርግልኝ ስለዉ ያደርጋል፤ ና ስለዉ ይመጣል። ከሙኒክ ሲዊዘርላንድ እንሂድ ስለዉ ሳያቅማማ ስራዉን ጥሎ ነዉ የተከተለኝ። ቀልዱ፥ጨዋታዉና ቁምነገሩ አይጠገብም፥ በተለይ ከአፈወርቅ አግደዉ ጋር ሲተራረቡ የአራት ሰአቱ የሙኒከ ሲዊዘርላንድ መንገድ እንኳን ያለቀ የተጀመረም አይመስልም ነበር። ብቻ ምን ልበላችሁ ዶ/ሩ ለኔ የነበረዉ አክብሮትና ለእናት አገሩ ለኢትዮጵያ ያለው ፍቅር በኔ ደካማ ብዕር የሚገለጽ አይደለም።
ባልና ሚስት ናቸዉ፥ የተቀመጡት አዳራሹ የመጨረሻ ረድፍ ላይ ነዉ። አይቸኩሉም ደግሞም አይዘገዩም። ፈጣሪ ያደላቸዉ ስጦታ ነዉ መሰለኝ ትክክለኛዉን ግዜ ያዉቁታል። ሲማከሩ ጆሮና አፍ ገጥመው ያንሾካሽካሉ። ሲስማሙ ስምምነታቸዉን የሚናገረዉ ባልየዉ ነዉ። የእነዚህ ባልና ሚስት ፍላጎት ጨረታዉን ማሸነፍ ሳይሆን ኢሳትን መርዳት መሆኑን የሁለቱም ፊት በግልጽ ይናገራል። ከላይ ባስተዋወቅኳችሁ ዶክተርና በእነዚህ ባልና ሚስት መካከል የተደረገዉ የጨረታ ፉክክር አዳራሹ ዉስጥ የተሰበሰበዉን ኢትዮጵያዊ ልብ ሰቅዞ የያዘ ፍጹም ልዩ ድራማ ነበር። ፉክክሩ ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን የአገር ፍቅርና እኛነት የታየበት እንዲሁም የማይቀረዉን ብሩህ የአገራችንን ተስፋ ከወዲሁ በናሙና መልክ ፈንጥቆ ያሳየ ዉብ መድረክ ነበር። በገንዘብ አስተዋጽኦ መልኩም ቢታይ ባልና ሚስትና ዶክተሩ ያደረጉት ፉክክር የጨረታዉን ጣሪያ ከሃያ ሺ ዩሮ በላይ አድርሶታል። በነገራችን ላይ እዚህ መጣጥፍ ዉስጥ ስማቸዉን ጠቅሼ ብጽፍ ደስ የሚለኝ ብዙ ኢትዮጵያዉያን አሉ። የማላደርገዉ ክፉ ብቻ ሳይሆን ጭራሽ ደንቆሮ የሆነ ጠላት ስላለን ነዉ። ይህ ጠላት የደደብነቱ ብዛት የሥልጣን ክልል ያለዉም አይመስለዉም፤ አዉሮፓና አሜሪካ ዉስጥ የጻፈ፥ የተናገረና ሀሳቡን የገለፀ ኢትዮጰያዊ ላይ እድሜ ልክ እስራት ይፈርዳል። ደሞስ ጭንቅላታቸዉ በንፍጥ ብቻ የተሞላና ሰዉነታቸዉ በተዘረፈ ሀብት የደለበ ሰዎች ከዚህ የተለየ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
ከሙኒክ የሲዊዟ መናገሻ ቤርን ድረስ የአራት ሰአት መንገድ ነዉ። በረጂም በረራና በቅዳሜዉ የአዳራሽ ዉስጥ ቆይታ የተዝለፈለፈዉ ሰዉነቴ እየከዳኝ ቢሆንም የግድ ሲዊዘርላንድ መሄድ ነበረብኝና ተንገዳግጄ መኪናዉ ዉስጥ ገብቼ የአራት ሰአቱን መንገድ ተያያዝኩት። የሙኒከ ሲዊዘርላንድ መንገድ የሚያልፈዉ በኦስትሪያ በኩል ነዉ። ከጀርመን ወጥቼ ኦስትሪያ መግባቴን ያውቅኩት ሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ የቆሙትን ፖሊሶች ስመለከት ነዉ፤ ለዚያዉም ባይነገረኝ ኖሮ አላዉቅም ነበር። መኪናዉ ዉስጥ እንቅልፍ ብጤ ሞካክሮኝ ነበር ግን የጋዜጠኛ አፈወርቅ አግደዉና የዚያ ደግ ዶክተር ጨዋታ እንኳን እንቅልፍ ሌላም ነገር የሚያስረሳ ነበርና ጨዋታቸዉ እንቅልፌን አባረረዉ። የመኪናዉ ዉስጥ ቀልድ፥ ተረብና ጆክ ከአካባቢዉ የተፈጥሮ ዉበት ጋር ሆነዉ መንፈሴን እያደሱት ድካሜን አስረሱኝ። አፈወርቅን የምትወዱት በቴሌቭዥን መስኮት ዉስጥ ብቻ አይታችሁት ከሆነ ብዙ ገና ብዙ ይቀራችኋል . . . ምኑን አያችሁና። አፈወርቅ ሲቀርቡት ጨዋታዉ፤ ቀልዱና ቁም ነገሩ አይጠገበም። ስለምንም ነገር ሲናገር የራሱ የሆነ ልዩ ዜማና ቃና አለዉ። ታሪክ ሲናገር በታሪኩ ዉስጥ ይዟችሁ ያልፋል። የታሪኩን መቸትና የተዋንያኑን ስም ከአባት ስም ጋር ሲናገር መጽሐፍ የሚያነብ እንጂ በቃሉ የሚናገር አይመስልም። የአማርኛ ቋንቋ በተለይ የቅኔ ችሎታዉ ይኸ ሰዉ ዋልድባ ነዉ ጋሙጎፋ ተወልዶ ያደገዉ ያሰኛል።
ከሙኒክ ተወጥቶ ኦስትሪያ እስኪገባ ድረስ ከመንገዱ ግራና ቀኝ የሚታየዉ ዘመናዊ እርሻ ከሳንሆዜ ሳንታክላራ ሲኬድ የሚታየዉን ሜካናይዝድ እርሻ አስታወሰኝ። የአዉሮፓና የአሜሪካ መመሳሰል ገረመኝ። በሃሳቤ ረጂም ርቀት ወደኋላ ተጓዝኩና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስማር ከአዋሳ አዲስ አበባ በአዉቶቡስ ስጓዝ አዉቶቡሱ ቆቃን እንዳለፈ አርሲ ነጌሌ እስኪደርስ ድረስ አልፎ አልፎ የማያቸዉ ትናንሽ እርሻዎች ፊቴ ላይ መጡ። አስናቀች ወርቁ “እንደ መቀነቴ ዞሬ ዞሬ እዚያዉ” ብላ የተጫወተችዉ ዘፈን ትዝ አለኝና ሆዴ በቁጭት ተሞላ። አዎ የኛ ነገር ዞሮ ዞሮ እዚያዉ ነዉ። እርሻው እዚያዉ፤ ገበሬዉ እዚያዉ፤ ፋብሪካዉ እዚያዉ ባጠቃላይ የኑሮ ደረጃዉ እዚያዉ ነዉ። እዚያዉ ድሮ የነበረበት ቦታ። ወደፊት እናያለን እንጂ ወደፊት አንሄድም። ይህንን ሳስብ ተቆጨሁ . . . ተናደድኩ። ለምን አልናደድ ለምንስ አልቆጭ . . . እኛና ድህነት፤ እኛና ኋላቀርነት፤ እኛና እየረገጡ ከሚገዙን ጋር መሞዳሞድ ሞት ካልለየን በቀር ላንለያይ የቆረብን ይመስላልኮ!
እኛ ኢትዮጵያውያን ከአዉሮፓና ከአሜሪካ ለምንድነዉ ይህን ያህል የምናንሰው ብዬ እራሴን ጠየኩና መልሳ ሳጣ የአዉሮፓን ዉበት ማድነቄን ቀጠልኩ። እዉነቱን ለመናገር የኋላ ቀርነታችን ምክንያት ጠፍቶኝ አይደለም። ለምን መናጢ ደሃዎች እንደሆንም ጠፍቶኝ አይደለም። ችግሩ. . . የኋላ ቀርነታቸንን ምክንያት ባሰብኩ ቁጥር ከዚህ አሳፋሪ ኋላ ቀርነት ለመላቀቅ የምናደርገዉ ጥረት እምብዛም መሆኑን ስለማዉቅ ማሰቤን አቆምና ንዴትና ቁጭት ዉስጥ እገባለሁ። የኔ ነገር ደግሞ ጉድ ከጉድም ጉድ ነው፤ አራሴን ስጠይቅ የማገኘዉ መልስ ቁጭትና ንዴት ነዉ። ቁጭትና ንዴት ደግሞ እንደገና ጥያቄ ያጭሩብኛል። ይገርማል .… አገሬ ከድህነት ኡደት እኔ ከጥያቄ ኡደት ላንላቀቅ የተማማልን ይመስላል። የራሱ ፊደል፥ ስነጽሁፍና የራሱ የሆነ የዘመን መቁጠሪያ ቀመር ያለዉ ሀዝብ እንዴት ያልሰለጠነ ህዝብ ተበሎ ይጠራል? አባይን፤ አዋሽን፤ ሸበሌን፤ዴዴሳን . . . ወዘተ ይዞ አገር እንዴት ይራባል? አክሱምን፤ ላሊበላንና ፈሲለደስን የገነባ ህዝብ ለምን ከኋላ ቀሮች ተርታ ስሙ ይጻፋል? ለምን? ለምን? ለምን?
ኦስትሪያ ስደርስ እርሻዉ፤ መኪናዉ፤ ከተማዉ፤ የሰዉ መልክና ቋንቋዉ ምንም አልተለየብኝም። ልዩነት አለ ቢባል ጀርመንን ለቅቄ ኦስትሪያ የሚባል አገር መድረሴ ብቻ ነዉ። ኦስትሪያን ለቅቄ ሲዊዘርላንድ ስገባም ፊት ለፊቴ ላይ ጉብ ጉብ ብለዉ ከሩቁ ከሚታዩኝ ተራራዎች ዉጭ ከተማዉ የጀርመንን ከተሞች ይመስላል፤ ብዙዎቹ መኪናዎች ጀርመን ዉስጥ የተሰሩ መኪናዎች ናቸው፤ ቋንቋዉም ጀርመንኛ ነዉ። ከአሜሪካ ተነስቼ ሲዊዘርላንድ እስክደርስ ድረስ በአራት አገሮች ዉስጥ አልፍያለሁ (አሜሪካ፥ ጀርመን፥ ኦስትሪያና ሲዊዘርላንድ) – ማነህ ተብዬ ፓስፖርት የተጠየኩት አሜሪካንን ስለቅና ሙኒክ ስገባ ብቻ ነው።
ሽፍታዉ ልቤ መሸፈት አይታክተዉ ነገር አሁንም ሸፈተ። ደግሞስ ይሸፍት አንጂ. . . . ለምን አይሸፍት? የተወለድኩት ኢትዮጵያ ዉስጥ ነዉኮ! እኛ ሰዎች እግዚአብሄር በአምሳያዉ እኩል አድርጎ ፈጥሮን አንዱ መሪዉን መርጦ ሲሾም ሌላዉ በገዛ መሪዉ ሲጎሸም፤ አንዱ በልቶ ጠግቦ ሲያምርበት ሌላዉ የሚበላዉ አጥቶ ህይወት ሲከዳዉ፤ አንዱ ሁሌም አሳሪ ሌላዉ ሁሌ ታሳሪ፤ አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ሲሆን እንኳን የሰዉ ልብ ከሳር ዉጭ ሌላ የማያዉቀዉ በሬም ይሸፍታል። ጀርመንን፤ ኦስትሪያንና ሲዊዘርላንድን ሳይ በገዛ አገራቸዉ ማናችሁ እየተባሉ በየኬላዉ የሚጉላሉት ምስኪን ወገኖቼ ትዝ አሉኝ። ቤንች ማጂ ዉስጥ ወደ ክልልህ ተመለስ ተብሎ የተገፋዉ ወገኔ በርቀት ታየኝ። ቤኒሻንጉል ዉስጥ አለክልልህ ምን ታደርጋለህ ተብሎ ንብረቱን ተቀምቶ እየተረገጠ የተባረረዉ ኢትዮጵያዊ ወገኔ ትዝ አለኝና ሆዴን አመመኝ። ጋምቤላ ዉስጥ የአያት ቅድም አያቶቹ መሬት ጠመንጃ ባነገቱ ጉልበተኞች ተቀምቶ ሲታርስ እሱ ተመልካች የሆነው አኝዋክ ወገኔ ትዝ አለኝ።
ከጀርመን ሲዊዘርላንድ ስንጓዝ መኪናዉ ዉስጥ የነበርነዉ አምስት ሰዎች ሁላችንም ኢትዮጵያዉያን ነን። አዉሮፓ ዉስጥ አገሮችን በሚያሳስብ ደረጃ ከፍተኛ የስደተኛ ቀዉስ አለ። ሆኖም ከጀርመን ወጥተን በኦስትሪያ በኩል ሲዊዘርላንድ እስክንደርስ ድረስ አንድም ግዜ ማናችሁ የሚል ጥያቄ አልቀረበልንም። ተመልሰን ጀርመን ስንገባም እንደዚሁ። እትብቴ በተቀበረባትና የዚህ አለም ጉዞዬን ስጨርስ የመጨረሻ ማረፊያዬ እንድትሆን በምፈልግባት ምድር እንደ ቆሻሻ ነገር የሚረገጠዉ መብቴ በባዕድ አገር ሲከበር አየሁና “ኢትዮጵያዊነት” ምን ያደርጋል ብዬ አማረርኩ። ችግሩ ኢትዮጵያዊነት ላይ ሳይሆን ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ቆርጠዉ በተነሱ ከሃዲዎች ላይ መሆኑ ገባኝኛ እነዚህን ከሃዲዎች ማጥፋት አለብኝ አለኩ። አዎ! እነዚህን ከሃዲዎች ማጥፋት አለብኝ ። “ማጥፋት” አለብኝ ሲባል አባባሉ በተግባር ካልተተረጎመ የባዶ ቃላት ጫጫታ ወይም የሞተ ሰዉ ዛቻ ነዉ። አንተ/አንቺ አንባቢ አስተዉል/አስተዉይ። ነፃነትና ፍትህ የሌሉበት አገር ሁሉ የአጥፊዎችና የጠፊዎች መድረክ ነዉ። ጠፊና አጥፊ ባሉበት ቦታ ደግሞ ሁለቱም ያጠፋሉ። አጥፊ ስራዉ ማጥፋት ነዉና ያጠፋል። ጠፊ ደግሞ ላለመጥፋት የሚያደርገዉ ምንም ነገር ስለሌለ እራሱን በማጥፋት ከአጥፊዉ ጋር ይተባበራል። የኛ የኢትዮጵያዉያን ችግርም ይኼዉ ነዉ. . . ጠፊዉም አጥፊዉም እኛዉ እራሳችን ነን። ከዛሬ በኋላ ግን እኛ አጥፊዎች ጠላታችን ጠፊ መሆን አለበት። ተፈላሲፌባችሁ ከሆነ ይቅርታ . . . እንደዚህ የሚያንበለብለኝ ዉስጤ ያለዉ ላለመጥፋት የማጥፋት ፍላጎት ነዉ። ሲዊዘርላንድ መናገሻ ቤርን መድረሴን ያወቅኩት መኪናዋ ቆማ . . . ጋሼ እንዉረድ ስባል ነው።
የኢትዮጵያን የቁርጥ ቀን ልጅ የአንዳርጋቸዉ ጽጌን 61ኛ አመት የልደት በዐል ለማክበር ሲዊዘርላንድ ዉስጥ የሚኖረዉ ኢትዮጰያዊ ከያለበት ተሰባስቧል። አዳራሹ ከመሙላቱ የተነሳ መቀመጫ ያጣዉ ሰዉ ያዳራሹን ዳር ዳር አጨናንቆታል። በየማዕዘኑ የሚወዛወዘዉ የኢትዮጰያ ሰንደቅ አላማ ለአዳራሹ ልዩ ዉበት ሰጥቶታል። የእንኳን ደህና መጣህ ጩኸቱ፥ ጭብጨባዉና ፉጨቱ አዳራሹ የእግር ኳስ ስታድዩም እስኪመስል ድረስ ቀለጠ። አጠገቤ የቆመው ጋዜጠኛ አፈወርቅ አግደዉ ጭብጨባዉ ለኔ ነዉ ላንተ ብሎ ጠየቀኝ . . . ለኛ ነዉ አልኩት። ሳቅ አለና ሁለት እጆቹን ዘርግቶ ተሰብሳቢዉ እንዲቀመጥ ተማፀነ። እኔም እጆቼን ዘርግቼ አብሬዉ ተማፀንኩ። ከእግራቸዉ ጣት እስከ ጸጉራቸዉ ጫፍ ድረስ ፍቅር በፍቅር የሆኑት የሲዊዝ ኢትዮጵያዉያን የምን መቀመጥ አሉና ሆታዉና ጭብጨባዉ ቀጠለ። ጧት ሙኒከን ስለቅ ድካም በድካም የነበረዉ ሰዉነቴ ዉስጥ አዲስ ሀይል እየገባ ሲያጠነክረኝ ተሰማኝ። ለካስ እኛ ሰዎች ምናብ ለምናብ ስንናበብ ዉጤቱ ፍቅር፥ ሀይልና ብርታት ነዉ። ብቻ ምን አለፋችሁ የሲዊዘርላንድ ኢትዮጵያዉያን እንደ ሲዊዝ ቸኮለት የሚጣፍጥ የአገር ልጅነት ፍቅር አቀመሱኝና በወገን ፍቅር ሰከርኩ። ሲዊዞች፥ ቸኮለታቸዉና ፍቅራቸዉ በጣም ተመቸኝ…….. ግን ብዙ ስራ ስላለብኝ የአንዲን ልደት ሻማ አብርተንና ኬኩን ቆርሰን “መልካንም ልደት” አንዲ ብለን ከዘመርን በኋላ ተለያየን። ጉዞ እነሱ ወደ ቤታቸዉ እኔ ወደ ሙኒክ ሆነ።
ረቡዕ መጋቢት 2 (March 2) ቀን በጧት ተነስቼ ቁርስ ከበላሁ በኋላ ከአዲሶቹ የሙኒክ ጓደኞቼ ጋር ተያይዘን ጉዞ ወደ ኦሎምፒክ መንደር ሆነ። ሙኒክ ኦሎምፒክ ልጅነቴን ይዞ የሚመጣ ብዙ ትዝታ አለዉ። የሜክሲኮዉ ኦሎምፒክ ጀግና ሻምበል ማሞ ወልዴ የመጨረሻዉን የኦሎምፒክ ማራቶን፤ ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ደግሞ የመጀመሪያዉን የኦሎምፒክ ሩጫ የሮጡት ሙኒክ ኦሎምፒክ ላይ ነዉ። ምሩዕ ይፍጠር ሙኒክ የሄደዉ ለ10ሺና ለ5ሺ ሜትር ዉድድሮች ሲሆን በ10ሺ ሜትር ሦስተኛ ከወጣ በኋላ የ5ሺ ሜትር የመጨረሻዉ ዉድድር ከተጀመረ በኋላ በመድረሱ ያሸንፋል ተብሎ በጉጉት ይጠበቅ በነበረዉ ዉድድር ላይ ሳይሳተፍ ቀርቷል። ሙኒክ ኦሎምፒክ አሳዛኝ ታሪክም አለዉ። ጨለማዉ መስከረም (Black September) በመባል የሚታወቀዉ የፍልስጥኤማዉያን አክራሪ ቡድን ኦሎምፒክ መንደር ዉስጥ አሸምቆ ገብቶ በእስራኤል አትሌቶች ላይ አደጋ ያደረሰዉ በዚሁ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1964 ዓም በተካሄደዉ ሙኒክ ኦሎምፒክ ላይ ነበር። በነገራችን ላይ ሙኒክ ኦሎምፒክ የተካሄደዉ ጥቁር አሜሪካዊዉ ጆዜ ኦዉንስ በርሊን ኦሎምፒክ ላይ የወርቅ ሜዳሊያዎች አሸንፎ የናዚ ሂትለር መሪዎች ጥቁር ስለሆንክ ከኛ እጅ ሜዳሊያ አትቀበልም ካሉት ከ36 አመታት በኋላ ነበር።
ሙኒክ ዉስጥ በመጨረሻ የጎበኘሁት ከከተማዋ 19 ኪሎ ሜትር ወጣ ብሎ የሚገኘዉንና በ1944 ዓም የተሰራዉን የዳሁ ናዚ ማጎሪያ (Concentration Camp) ነበር። ዳሁን ጎብኝቶ ለመጨረስ ወደ ሦስት ሰአት አካባቢ ፈጅቶብኛል። እነዚህ ሦስት ሰአቶች ወደፊትም ወደኋላም እየወሰዱኝ ዳሁ የጭካኔና የእልቂት ቦታ የመሆኗን ያክል የይቅርታና የመማማሪያ ቦታም እንደሆነ አሳይተዉኛል። ዳሁ ለሰዉ ልጅ ቁስሉም መድኃኒቱም ሰዉ መሆኑ የታየበትና የሰዉ ልጆች ጭካኔ መድረስ የሚችልበት የመጨረሻዉ ከፍታ ላይ የደረሰበት ቦታ ነዉ። ዳሁ አሁንም ድረስ ሲያዩት ጣረ ሞትን የሚጣራ የጨለማና የብርህን፤ የሞትና የህይወት፤ የጭካኔና የምህረት ቦታ ነዉ። ዳሁ የናዚ ግፍና ጭካኔ እማኝ ነዉ። ዳሁ የዘግናኝ ታሪክ ቅርፊት፡ የብሩህ ዘመን ትዉፊት፥ ቂምና ጥላቻን አብናኝ ይቅር ብሎ ይቅርታ ለማኝ ቦታ ነዉ። ዳሁ አይዋሽም . . . እንኳን ሊዋሽ ጭራሽ ዉሸት የሚባል አያዉቅም። ዳሁ ከአንዱ ክፍል ወጥተን ወደ ሌላዉ ክፍል በገባን ቁጥር የሚነግረን እዉነት ግን እግዚኦ መሀረነ ክርስቶስ ያሰኛል። ያቆስላል፤ ያደማል፤ ልብ ይሰብራል፤ ሆድ ይቆርጣል። እስረኞች ከመኝታ ቤታቸዉ እየተነዱ ገላችሁን ስለምትታጠቡ ልብሳችሁን አዉልቁ ተብለዉ ወደ ሌላ ክፍል ይወሰዳሉ። የሚቀጥለዉ ክፍል ዉስጥ የሚጠብቃቸዉ የመታጠቢያ ገንዳ ሳይሆን የመርዝ ጋዝ ገንዳ ነዉ። እስረኞቹ በመርዝ ጋዝ ከተገደሉ በኋላ እሬሳቸዉ ወደሚቀጥለዉ ክፍል ይወሰድና አገር የሚያክል ምድጃ ዉስጥ እየተጣለ ይቃጠላል። ይህ ግፍና ጭካኔ የተፈፀመዉ በሰዉ ልጆች ላይ ነዉ፤ ይህንን ግፍና ጭካኔ የፈፀሙትም የሰዉ ልጆች ናቸዉ። ጀርመንና ፖላንድ ዉስጥ ስላሉ የናዚ ጀርመን ማጎሪያ ካምፖች ከሰማሁ ቆይቷል። ይህንን በተለያዩ መጽሐፍት ላይ ያነበብኩትን ታሪክ ታሪኩ የተፈጸመበት ቦታ ላይ ቆሜ ስመለከት ግን አእምሮዬ ማሰብ አቆመና በድን ሆኜ ቀረሁ። ሁለት እጆቼን ዘርግቼ አማተብኩና . . . . . እንዲህ አይነት ክፉ ጭካኔ ዬትም ቦታ መደገም የለበትም ብዬ የዳሁ ጉብኝቴን ጨረስኩ።
ጀርመን፥ ኦስትሪያ፥ ሲዊዘርላንድና ዳሁ ስለ አሁኗና ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ በየራሳቸዉ መንገድ የሚነግሩን ብዙ ነገር አለ። ዳሁ በሚባለዉ የናዚ ሂትለር ማጎሪያ ካምፕ ዉስጥ የተፈጸመዉን ግፍና ጭካኔ የፈጸሙት እኛን የመሰሉ የሰዉ ልጆች ናቸዉ እንጂ ከጥልቅ ባህር ዉስጥ የወጣ ዲያብሎስ አይደለም። ጀርመን፥ ኦስትሪያና አራት የተለያዩ ቋንቋዎች የሚነገሩባት ሲዊዘርላንድ ድንበር፤ ቋንቋ፤ባህልና ሐይማኖት ሳያግዳቸዉ ከአንዱ አገር ወደ ሌላዉ እንዳሰኛቸዉ እየተዘዋወሩ በኤኮኖሚ ተሳስረዉ በሰላም የሚኖሩት አርቆ አስተዋይ መሪዎቻቸዉ በወሰዱት መልካም እርምጃ ነዉ እንጂ እግዚአብሄር ከሰማይ ወርዶ የልዩነት ግድግዳቸዉን አፍርሶላቸዉ አይደለም። ክፉዉም ስራ የሰዉ ልጆች ስራ ነዉ፥ መልካሙም ስራ የሰዉ ልጆች ስራ ነዉ።እኛ ኢትዮጵያዉያን ምርጫችን ምንድነው? አዉሮፓ ዉስጥ ሰዉ ከአባቱ ገዳይ ጋር ተስማምቶ ሲኖር እያየን እኛ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር በሠላም ጎን ለጎን መኖር ለምን አቃተን? አዉሮፓዉያን በየአገሮቻቸዉ መካክል ያለዉን ድንበር አፍርሰዉ በአንድ ገንዘብ ሲገበያዩ እኛ በአንድ አገር ዉስጥ ለዘመናት አብሮ በኖረ ህዝብ መካከል አጥር የምንሰራዉ ለምንድነዉ?
ሙኒክ ከመሄዴ በፊት አሜሪካ ሜሪላንድ ዉስጥ አንድ ትልቅ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ነበር። እዚህ ስብሰባ ላይ የእምነት አባቶች፤ የሲቪክና የፖለቲካ ድርጅቶች መሪዎች፤ አባቶች፤ እናቶችና ወጣቶች ተገኝተዉ ነበር። የሁሉም ፍላጎት አንድ፤ አንድና አንድ ብቻ ነበር። እሱም ፍትህ፤ እኩልነትና ነጻነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ እዉን ሆና ማየት ነዉ። አዉሮፓ መጥቼ ጀርመንና ሲዊዘርላንድ ዉስጥ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ወገኖቼ ጋር ስገናኝ የተሰማኝ ስሜት አሜሪካ ዉስጥ ከተሰማኝ ስሜት ጋር ፍጹም ተመሳሳይ ነበር። እርግጠኛ ነኝ ኢትዮጵያዉያን በሚኖሩበት የአለም አካባቢ ሁሉ ፍላጎታቸዉ ፍትህ፥ ነጻነትና ዲሞክራሲ ነዉ። ግን ፍትህና ነጻነትን ስለፈለግናቸዉ ብቻ አናገኛቸዉም። የተናጠል ትግል ደግሞ ተራ በተራ የወያኔ ምሳና ቁርስ ያደርገናል እንጂ ነጻነታችንን አያስገኝልንም። በእርግጥ ነጻነት ስንደሰትበት ደስታዉ በግለሰብ ደረጃ ነዉ፤ ሆኖም ነጻነታችንን ጠላት እንዳይቀማን የምንጠብቀዉና ከተቀማንም ታግለን የምናስመልሰዉ በጋራ ነዉ። ስለዚህ ጽኑ የሆነዉ የፍትህና የነጻነት ፍላጎታችን ጽናት ባለዉ የጋራ ትግል ካልተደገፈ ያለን አማራጭ እየተረገጥን መኖር ብቻ ነዉ።
ወያኔ የበላይ በሆነባት በዛሬዋ ኢትዮጵያ ዉስጥ እንደዳሁ አይነት በሰዉ ዘር ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊፈጸም አይችልም የምንል ሰዎች ካለን ወደ ኋላ ዞር ብለን አኝዋክንና ኦጋዴንን ልንመለከት ይገባል። ዛሬ ወያኔ ኦሮሚያ ዉስጥ መብቴ ይከበር ብሎ በጮኸ ኢትዮጵያዊ ላይ የሚወስደዉ ፍጹም አረመኔያዊ የሆነ እርምጃም የሚያሳየን ወያኔ የስልጣን ገመዱ ባጠረ ቁጥር የማያደርገዉ ምንም ነገር እንደሌለ ነዉ። የወደፊቷ መልካም ኢትዮጵያ የምትናፍቀን ኢትዮጵያዉያን ከጀርመን፥ ከኦስትሪያ፥ ከሲዊዘርላንድና ከዳሁ የምንማረዉ ጠቃሚ ትምህርት አለ። ዛሬ በማድረግ ወይም ባለማድረግ የምንፈጽማቸዉ ብዙ ስህተቶች አሉ። እነዚህ ስህተቶች የጠላታችንን የወያኔን የሥልጣን ዘመን ማራዘማቸዉ ብቻ ሳይሆን ወያኔ ከተወገደ በኋላም ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት በምናደርገዉ ጥረት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርጋል። ለምሳሌ ኦሮሚያ ዉስጥ ለወራት የዘለቀዉ ህዝባዊ ቁጣና እምቢተኝነት በሌላ አገር የሚካሄድ ይመስል ብዙዎቻችን ከጎን ቆመን ተመልክተናል። ይህ አጉልና የማያዋጣ ቸልተኝነት ነገ በአማራ፤ በሲዳማ፤ በሃዲያና በኮንሶ … ወዘተ አካባቢዎች የሚነሱ ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን ኦሮሞዉ በቸልተኝነት እንዲመለከት ያደርገዋል። ኢትዮጵያ ዉስጥ አማራዉ ለኦሮሞ ካልጮኸና ኦሮሞዉ ከአማራዉ ጋር አብሮ ካልታገለ አማራዉ፤ ኦሮሞዉ ባጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብ ከወያኔ ባርነት ነፃ አይወጣም። ወደድንም ጠላን ታሪክ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሲዳማን በወላይታ፤ ጉጂን በጌዲኦ፤ ትግሬን በአማራ፤ አማራን በኦሮሞ . . ወዘተ አዉድ ዉስጥ ጠቅልሎ አስቀምጦናል። ከዚህ ጥቅልል ዉስጥ በተናጠል አንዱ ብቻዉን ነፃ መሆን አይችልም። ወያኔ ጨፍልቆ የሚረግጠን አንድ ላይ ነዉ፤ ነፃ የምንወጣዉም አንድ ላይ ነዉ። ኢትዮጵያና አንድነቷ አደጋ ላይ ወድቀዋል። ኢትዮጵያዊነት የምንለዉ ክቡር ማንነትም ከፍተኛ አደጋ ላይ ነዉ። እነዚህን ጣምራ አደጋዎች ማቆም የዚህ ትዉልድ ሃላፊነት ብቻ ሳይሆን ግዴታም ነዉ። የወደፊቷ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዳሁን የመሰለ የመታሰቢያ ቦታ እንዲኖራት በፍጹም መፍቀድ የለብንም። ይህ እዉን የሚሆነዉ ግን እኛ ኢትዮጵያዉያን እጅ ለእጅ ተያይዘንና ትከሻ ለትከሻ ተደጋግፈን የዛሬዋን ኢትዮጵያ ከእልቂት አድነን የነገዋን ኢትዮጵያ በፍትህ፤ በነጻትና በዲሞክራሲ መሰረት ላይ መገንባት ከቻልን ብቻ ነዉ። ሌላ ምንም መንገድ የለመልኩም። ቸር ይግጠመን።
አፍሬም ነኝ ከአርበኞች መንደር – ebini23@yahoo.com
No comments:
Post a Comment