“የመሬት ባላባቱን” አባይ ማን ይድፈራቸው?
ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተቃውሞና ዓመጽ የተወጠረው ህወሃት/ኢህአዴግ በአስሩም ክፍለከተሞች የሚገኙ እስከ 600 የሚደርሱ የመሬት ባለሙያዎችን ካገደ በኋላ የአዲስ አበባ የመሬት አስተዳደር ሞሳኞች ያላቸውን 85 አመራሮችና ሠራተኞችን በቁጥጥር ሥር አውሏል፡፡ “የመሬት ከበርቴውን” አባይ ጸሃዬንስ ማን ይደፍራቸው ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡
በአባይ ጸሃዬ “ልክ እናስገባለን” ተግባራዊ እንዲሆን የታሰበው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በገጠመው ከፍተኛ ተቃውሞ ከተስተጓጎለ በኋላ ህወሃት/ኢህአዴግ ማስተር ፕላኑን “ትቼዋለሁ” ቢልም የኦሮሞ ሕዝብ ያስነሳው ተቃውሞ ግን እስካሁን አልበረደም፡፡
“መልካም አስተዳደርን አሰፍናለሁ” በሚል ኢህአዴግ የሕዝቡን ቀልብ ለመሳብ ከላይ ታች እየተራወጠ ነው የሚሉ ለጎልጉል አስተያየታቸውን የሰጡ እንደሚሉት ኪራይ ሰብሳቢነት ለመዋጋት በሚል የሚደረገው ድራማ ሙስናን በማንኪያ የመንካት ያህል ነው፡፡ ምክንያቱም ከመሬት ጋር በተያያዘ በሙስናው እና በመሬት ዘረፋው የተጠመዱት ከፍተኛ የህወሃት ሹሞች ናቸው ይላሉ፡፡
“በየትኛውም ደረጃ ያሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት፣ በደህንነት ውስጥ ያሉ ባለስልጣናትና መካከለኛ ደረጃ ሃላፊዎች በግልጽ ሙስና ውስጥ መዘፈቃቸው በመረጃ ቢቀርብም ጸረ ሙስና ኮሚሽን እርምጃ የማይወስደው ሙስና አንዱ የስርዓቱ እድሜ ማራዘሚያ መንገድ በመሆኑ ነው፤ ኢህአዴግን እያገለገሉ ያሉ ባለስልጣኖች ህወሃትን በሚገባ መከራከር የማይችሉትና በታዛዥነት እያጎበደዱ ለመኖር የሚገደዱት የገቡበትን የሙስና ማጥ ስለሚያውቁት ከተቃወምን እንታሰራለን” በሚል ፍርሃቻ መሆኑን የኮሚሽኑ ባልደረባ ለጎልጉል መናገራቸውን ከዚህ በፊት ዘግበን ነበር፡፡
በጥርስ አልባው የጸረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪዎች ዘንድ “የመሬት ባላባት/ከበርቴ” እየተባሉ የሚጠሩት አባይ ጸሃዬ ከሙሰኞቹ በቅድሚያ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ጎልጉል በመስከረም 2005ዓም ባተመው “የመሬት ባላባቱ” ሚኒስትር!! በሚለው ዜና ላይ አባይ ጸሃዬ በዘመዶቻቸው ስም በርካታ መሬቶችን መውሰዳቸውን፤ በተለይ በቦሌ ክፍለከተማ በመሬት አስተደዳር ሥልጣን የነበራቸው የአቶ አባይ የቅርብ ዘመድ መሆናቸውን፤ ከመሬት ጋር በተያያዘ የተፈጸመ ከፍተኛ ሙስና አለ በሚል ጸረ ሙስና በደረሰው ጥቆማ ምርመራ ጀምሮ ጉዳዩ “ወዳልተፈለገ” አቅጣጫ ሊያመራ ሲል ከበላይ በተላለፈ ትዕዛዝ ምርመራው እንዲቆምና በቁጥጥር ሥር ውለው የነበሩት መሃንዲሶች እንዲፈቱ መደረጉን ለጎልጉልከደረሱት መረጃዎች ጋር በማጣቀስ ዘግበን ነበር፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ ባወጣው ዜና 85 የመሬት አመራሮችና ሠራተኞች ሙስና ፈጽመዋል በሚል በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፤ ከዚሁ የመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ ከአዚህ በፊት 600 ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ መወሰዱን ዘግቦ ነበር፡፡
ሰሞኑን የጎልጉል እማኝ ዘጋቢ (ireporter) በላኩልን መረጃ መሠረት እነዚህ 600 ያህል የሚሆኑት “ኪራይ ሰብሳቢነትን” እና “ሙስናን” ለመዋጋት በሚል “ዕርጃ የተወሰደባቸው” በትንሹ ለሰባት ዓመታት በመሬት አስተዳደር በመሃንዲስነትና ተመሳሳይ ሙያ ያገለገሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በተለይ ደመወዛቸው አይነካም በሚል በዝቅተኛ የሥራ መደብ ላይ እንዲመደቡ የተደረጉት በራሳቸው ፈቃድ ሥራቸውን እንዲለቁና በምትኩ አንድን ወገን ያማከለ የታማኞች ቅጥር ለመፈጸም የተሰበ እንደሆነ እማኝ ዘጋቢው ያስረዳሉ፡፡
ከመሬት አስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ ወንጀሎችና የሙስና ተግባራት እንዳሉ የሚናገሩት ዘጋቢው ውሳኔው ወገንተኛና የሥርዓቱን ቁንጮዎች የማይነካ መሆኑ አግባብነት የሌለው ብቻ ሳይሆን ሕዝብን አፍ ማስዘጊያ የማባበያ ጥገናዊ ለውጥ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
ከዚህም ሌላ ሁለት መሠረታዊ ነጥቦችን እማኝ ዘጋቢው ይጠቅሳሉ፤ አንደኛው በሚነሱት ሠራተኞች ምትክ ባለሙያ ለመመደብ በቂ ዝግጅት አለመደረጉና በቅጥር ቦታቸውን ለመተካት የሚደረገው ሙከራ ኅብረተሰቡን ለተጨማሪ እንግልት የሚዳርገው ሲሆን በሁለተኛ ደረጃ ብዙ ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበት “የካይዘን መመሪያ (ፕሪንስፕል)” ለመተግበር በሚል በየክፍለከተማው የተሰጠው ሥልጠና ለነዚሁ ከሥራቸው የተነሱት ባለሙያዎች መሆኑ ሥልጠናውን ዋጋቢስ የሚያደርግ ሲሆን በሠራተኞቹ ላይ ተወሰደ የተባለው እርምጃ ግብታዊና ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ የእማኝ ዘጋቢውም ሆነ የሌሎች አስተያየት ሰጪዎች ዋና ጥያቄ በሙስና የተዘፈቁትን የህወሃት ቁንጮ ባለሥልጣናትን ማነው የሚደፍራቸው የሚል ነው፡፡ “እነሱው ሙሰኛ፤ እነሱው የጸረ ሙስና ሕግ አውጪ፤ እነሱው የሕግ ተርጓሚ፤ እነሱው ፈራጅ፤ እነሱው አሳሪ፤ …”በሆኑበት አገር ዋንኞቹ የመሬት ነጣቂዎችና ከበርቴዎች ምንም ሳይሆኑ ከላይ ከላይ የሚወሰደው እርምጃ ጊዜያዊ ጥገናዊ መሻሻል እንጂ ተሃድሶአዊ ለውጥ እንደማያመጣ ይናገራሉ፡፡
No comments:
Post a Comment