Translate

Saturday, March 19, 2016

ግልጽ ደብዳቤ ለጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም




ግልጽ ደብዳቤ ለጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም
Written by አስፋ ጫቦ
ግልጽ ደብዳቤ ለጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም
ይህን ደብዳቤ እንድጽፍልዎ ያስገደደኝ፣ ዛሬ አገራችን የገባችበት ማጥ ነዉ። ከፖለቲካነትን ይልቅ የ“ኧረ ምን ይሻላል! ኧረ ምን ይበጃል !” ደብዳቤ አድርገው ቢያዩልኝ ደስ ይለኛል። እንደ መፍትሔ አፈላላጊ የአገር ሽማግሌ ድምፅ ሆኖ እንዲታይልኝ/ቢታይልኝ እወዳለሁ። ነውም!! ”የጋራ ቤታችን” እንዲህ ማጥ ውስጥ ስትዘፈቅ የሚያይ አገር ወዳድ ሁሉ ድምጹን የመስማት ግዴታ ያለበት ወቅት ላይ ነን ብዬ አምናለሁ። ከፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ይልቅ የአገራችን የኢትዮጵያ መሰንበት፤ ከዚያም “በነጻነትዋ ለዘላለም ትኑር!” ማለት ይቅደም እንደማለት ነው። በደርግ ቋንቋ “ኢትዮጵያ ትቅደም!” እንደማለት!

ታዋቂዉና ዝነኛዉ የጥንቱ የቻይና ሊቅ ሱን ዡ (Sun Tzu) በ “የጦርነት ጥበብ “ (The Art of War) መጽሐፉ ከጻፈው ጠቅሼ ብጀምር የሚሻል መስለኝ፡-
“..ጠላትህን (ይቃወመኛል የምትለውን) የምታውቅ ከሆነ ፤ደግሞም ራስክን የምታውቅ ከሆነ የግጥሚያ ወጤት ከቶም አያጠራጥርም:: ሆኖም፤ ራስክን ብቻ አውቀህ ጠላት ነው (ተቃዋሚ ነው) የምትለውን የማታውቅ ከሆነ አሸነፍኩ ባልክ ቁጥር ሽንፈት ያጋጥመሀል። ከዚህ ውጭ ግን ራስክንም ጠላቴ (ተቃዋሚዬ የምትለውን) የማታዉቃቸው ከሆነ በገጠምክ ቁጥር ሽንፈት እጣህ ይሆናል” ይላል፡፡
ከነጉዳንጉዱ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን መንግስት ለማድረግ ሙከራ ያደረገ መንግስት ቢኖር ደርግ ብቻ ነበር ለማለት የምንችል ይመስለለኛል። የስልጣን መሠረቱ ብሔረሰብ አልነበረም። ያም ሆኖ የብሔረሰብ ጭቆና መኖሩን ተቀብሏል። ተቀብሎም በመላ- ምት ሳይሆን ጥናት ላይ በተመሠረት መፍትሔ ለመሻት ተንቀሳቅሷል። “የብሔረሰብ ጥናት ተቋም” (Institute)፤ በምርጥ የኢዮጵያ ምሁራን የሚመራ፣ አቋቁሟል። የዚያ ጥናት ውጤት ሰባት የመፍትሔ አማራጮች ያቀፈ ነበር። በጊዜያዊነትም ቢሆን ከነዚህ አማራጮች አንዱን “የራስ ገዝ” የሚለውን በስራ አውሎ ኢትዮጵያን በዚያ ለማስተዳደር ሞክሯል።
ኢሕአዴግ ከዚህ የደርግ ጥናት ውስጥ ሰባተኛ የነበረውን አማራጭ ወስዶ አገሪቱን “ክልል” በሚል መጠሪያ ክልል አዋቀረ። ክልል ማለት በዚህኛው አገባቡ፣ለኔ፣ “አጥር ታጠረ!” እንደማለት ነው” “ድርሽ ትልና! ድርሽ ትይና!” እንደማለት። ደርግ ለኃይለሥላሴ ሲል እንደነበረው፤ “ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረው” ይኸዉ ላለፉት አራት ወራት ቁርጡ ለይቶለት መፈረካከስ ጀመረ። መንግስትዎን ይህ ነገር “ወትሮ ነበር እንጅ መጥኖ መደቆስ፤ አሁን ምን ይባላል ድስትን ጥዶ ማልቀሰ!”ን አስታወሰኝ። በዚህ ላይ መንግስትዎ አሁንም ሐሳብ- ወለድ ጠላቶች ላይ ጣቱን መጠንቆሉን ቀጠለ። ያ የተለምደ ስለሆነ አይገርመኝም። ሆኖም አዲስ ኪዳን ውስጥ ያለ አንድ ነገር ያስታውስኛል።” ሌላው አይን ውስጥ ያለ ትቢያ ከመጠቆምህ በፊት አንተ አይን ውስጥ የተጋረጠውን ግንድ መጀመሪያ አስውግድ!” የሚለው ነው።
በምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር- “ተከለለ” ማለት “ታጠረ” ማለት ነው። ጋሞ “ካሎ” ይለዋል። ማስቃላ ከመድረሱ ወራት በፊት የከብቶች ማስማሪያ መሐሉ ላይ አንድ እንጨት ይተከላል። ያንን በምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር። ያ ቦታ/መስክ “ካሎ” ሆነ ማለት ነው። ያንን እንጨት መጀመሪያ የተከለው ባለስልጣን እስኪነቅለው ከብት ድርሽ አይልበትም። ጎሜ/ ኃጢአት ነው የሚሆነው። ወንጀል/ሽብርተኝነት እንድምትሉት! ጋሞ ውስጥ ካሎ አይጣስም። ምክንያቱም ቀላል ነው። ሕዝቡ የተቀበለው፣ ለዘመናትም ተቀብሎት የኖረው፤ እምነቱ ፤ንብረቱ ስለሆነ ነው።
ዛሬ በአገሬ፤ በኢትዮጵያ፣ ያለው በግሪክ ተረታ-ተረት (Mythology) ያለውን የፓንዶራን ሙዳይ (Pandora Box) ያስታውሰኛል። አማልክት እንደ ምርቃት/ እርግማን ሙዳይዋን በአለም ላይ በሚገኙ ክፋቶችና ተስፋ ሞልቶ ይሀጣታል። ፓንዶራ ቸኩላ ስከፍተው ክፋቶቹ ሁሉ በረው ወጡና እቡይ ስራቸውን ተያያዙት። ወያኔ በዚህ አዲስ የመንግስት አዋቃቀሩንና ሕግ መንግስቱ ያደረገው የፓንዶርን ሙዳይ እንደመክፈት መስሎ ይታየኛል። አንድ የሚያጽናናኝ ነጥብ ቢኖር ሙዳዩ ውስጥ አሁንም ተስፋ አለ። ኢሕአዴግ ብርታትን፣ ቅንነትን፤ “ለጋራ ቤታችን” ዘላቂነትን የሚፈልግ ቢሆን፤ይህችን ሙዳይዋ ውስጥ የተረፈቸውን ተስፋ አውጥቶ ተግባር ላይ ማዋል ብቻ ነው። የዚያን እለት፤ በዚያ ወቅት ፤የኢትዮጵያ ሕዝብ በተቃውሞ ሳይሆን በድጋፍ ከአጽናፍ እስከ አጽናፍ ይውጣል ብዬ አምናለሁ። እኔ ደግሞ በመሠረቱ ተስፋ መቁረጥ አላውቅበትም። ተስፋ የምቆርጥ ብሆን ይህንን ደብዳቤ ባልጻፍኩም!!
ጠቅላይ ሚኒስቴር ለነበሩት ለአቶ መለስ ዜናዊ፤የዛሬ ስንትና ስንት አመት በጻፍኩት ግልጽ ደብዳቤ አገሪቱን “አያድሩበት ቤት አያመሻሹበት አያፈርጉት!” ብዬ ነበር። እርስዎን ደግሞ “ላለፈ ክረምት ቤት አይሰራም!” ለማለት እፈልጋለሁ። ያለፈው ክረምት ቤቱን ነካካው እንጅ አላፈራረሰውም፤ ወይም ወደማፈራረስ አላቃረበውም ብዬ አምኜ ነው ይህንን ተረት የጠቀስኩት። እዚህ ተረት ውስጥ በውስጠ ታዋቂነት ያለው፤ ወይም አንድምታው “ያለፈው ክረምት ያናጋውን አይነት ቤት ደግመህ አትስራ!” የሚል ይመስለኛል። ማለትም እዚያ፤ ያለፈው ክረምት ቤት አወቃቀር ላይ/ውስጥ የነበረውን ደካማ ጎን አትድግመው ነው። ማለትም “ካለፈው የግንባታ ስህተት ተማር!” ነው።
ከሆነ ደግሞ የግንባታው ስህተት ምን ነበር? ዙሪያውን ላለመዞር ስህተቱ ሕገ መንግስቱ ነው ! ስህተቱ ኢትዮጵያን በክልል ማዋቀሩ፤በብሔረሰብ ማካለሉ ነው!!
ኢትዮጵያን በብሔረሰብ ሲዋቅር ወያኔ የመጀመሪያ አልነበረም። በ1928 ኢትዮጵያን የወረረው የጣሊያን፤ የሙሶሉኒ አወቃቀር በብሔረሰብ ላይ የተመሠረተ ነበር። “የጣልያን የምስራቅ አፍሪካ ግዛት! (Africa Orientale Italiana” ይለዋል። ከ19ኛው ምእተ አመት ጀምሮ ብዙ የጣሊያን “ሊቃውንት” ያጠኑት ጥናት ውጤት መሆኑ ነበር። የጥናታቸው ውጤት ኢትዮጵያን በጎሳ በመከፋፈል እርስ በርሳቸው ማናቆርና እነሱ ሲባሉ እኛ አርፈን መግዛት ነው የሚል ነበር። ታሪክ እንደሚነግረን፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዛኛው ተባብሮ፤ ዱር-ገደል ገብቶ ጣሊያንን አዋርዶ አባረረው። እንግሊዝም በሰሜን በኩል የትግራይ- ትግሪኝን፣ በምስራቅ በኩል የታላቂትዋን ሶማሌ መርዝ ቀበረች/ረጨች። ባጭሩ ይህ በብሔረሰብ መከፋፋል ከጠላቶቻችን የመጣ በመሆኑ ሞዴል አድርገን ልንቀበለው ከቶም አይገባም ለማለት ነው። ይህም ማለት ለአዲሱ፤ መጭው ክርምት፣ የሚሰራው ቤት በጠላቶቻችን ንድፍ ላይ የተመሠረት ሳይሆን በኢትዮጵያ እሴት፤ በኢትዮጵያ እውነት ላይ መሆን አለበት ለማለት ነው። መሠረቱ፤ ጣሪያ፤ ግርግዳው፤ ታዛው የኛው ይሁን ነው። ዞር-ዞር ብሎ የማየት እንጅ ታሪካዊ እሴት ሞልቶ የተረፈን አገር ነን። ከልቤ ነው የምልዎት!!
ደርግን “ከነጉዳንጉዱ”ብዬ ነበር የገለጽኩት። ለጊዜው ለተነሳሁበት ጉዳይ ሲባል ጉዳንጉዱን ልተወውና በጎ ጎኖቹ ሊባሉ ከሚችሉት ጥቂቱን ልጥቀስ። ከሁሉ ሁሌ ቁልጭ ብለው ከሚታዩኝ ውስጥ አብዮት አደባባይ ሰልፍ በተደረገ ቁጥር ከደርግ ሊቃናተ መንበሮች በስተቀኝ ፓትሪያርኩ አቡነ ተክለሐይማኖት፤ ከግራ ሐጂ ያሲን የክብር ቦታ ይዘው ተቀመጠው የማየው ነበር። በኢትዮጵያ ምድር የእምነት እኩልነት ለማየት ሲያልም ለነበረ እስልምና እንዲህ የክብር ቦታ አግኝቶ በአደባባይ ከማየት የተሻለ የሚያረካ ወቅት ይኖራል ብዬ አልገምትም። ከዚያም መስከርም 12ትን አረፋ፤ ታህሳስ 13ትን መውሊድ፣ ሰኔ 29ን ረመዳን ብሔራዊ በአል አድርጎ የደነገገዉ ደርግ ነበር።
የካቲቲ 25 ቀን 1967 የገጠር መሬት አዋጅና የትርፍ ቤቶችና የከተማ ቦታ አዋጅ ሌላው የሚጠቀስ ነበር። የነዚህ አዋጆች ትርጉም “መሬት ለአራሽ/ለባለቤቱ፣ የከተማ መኖሪያ ቤትን አናሳ ገቢ ያላቸው ጭምር ተከራይተው እንዲኖሩ ማድረግ ነበር። ደርግ ወያኔን ጉድፉን አጥርቶ፤መንገዱን ጠራርጎና ዘርግቶ ጠበቀው ልንል የምንችል ይመስለኛል። ወያኔን ከጥቂት ማሻሻል/በስተቀር “ግፋ በለው!” ብቻ ነበር የሚጠበቀው። ታዲያ ምን ሆነ?
ከዚያ የሆነውን እርስዎ ደጋግመው ከተናገሩት አንዱን ብቻ ወስጄ ለመግለጽ እንድሞክር ይፈቀድልኝል። ቃል-በቃል ባልጠቅስዎትም “መንግስታችን የኪራይ ሰብሳቢ መንግስት ሆነ!” አሉ። እኔም ልሁን ማንኛውም ተቃዋሚ ወይም መንግስትዎ አሸባሪ የሚላቸዉም ቢሆኑ ይህንን መንግስት ከዚህ፣ እርስዎ ከገለጹት በተሻለ ሊገልጡት የሚቻላቸው አይመስለኝም።
ለመሆኑ እኒህ ኪራይ ሰብሳቢዎቹ እነማን ናቸዉ? የሚያከራዩት ምንን/ማንን ነው? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ይመስለኛል። ብቻ የሚያከራዩት ቢኖር ነው አከራይተው ኪራይ የሚሰበስቡት። ይህ ደግሞ ራሱን በራሱ ገላጭ እውነት ነው። ከሆነ ደግሞ የሚያከራዩት ኢትዮጵያን ወይም የኢትዮጵያን መሬትና ቤት መሆኑ ነው። ተሳስቼም ከሆነ ልታረም ፈቃደኛ ነኝ። ልማት በሚባል ታላቅ አሳሳች ቃል ስር ዛሬ ብር ወይም ጉልበት ያለው የፈለገውን ያክል የገጠር መሬትና ቦታ ማግኘት እንደሚችል መንግስትዎ በአደባባይ የሚናገረውና አስፈጻሚ አዋጅም ያወጣለት ነው። በቅርቡ ያነበብኩት አንድ የአፍሪቃ የባለሚሊዮን ዶላር ሀብታሞች ዝርዝር ገርሞኝ ነበር። ባለሚሊዮን ዶላር ሀብታሞች ዝርዝር ውስጥ ኢትዮጵያዊያን የአንደኝነት ስፍራ ይዘዋል። አሁን አንደኝነታችን በረዥም ሩጫ ብቻ ሳይሆን በዶላር ጭምር መሆኑ ነዉ/ሆነ። እንደ ኢትዮጵያዊነቴ በዚህ ልኩራበት ወይስ ልፈርበት? ይህ ሁሉ የተቻለውን ‘በሕጉ’ መሠረት ባለመሬቶቹ ከመሬትና ቤት ንብረታቸው ተነቅለው ተጥለው ነው። የመሬት ላራሹ አዋጅ፣ መሬት ለኪራይ ሰብሳቢ በሚል አዋጅ የተተካ አይመስልዎትም? የእስልምና ተከታዮችም ከብዛታቸው የተነሳ ስማቸውን ልጠራ የማልችለውን ወህኒ ቤት ሞልተውታል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዘመነ መሳፍንት ተብሎ የተሰየመ አነሰም በዛ የመቶ አመት ታሪክ አለ። ይህም ማእከላዊ መንግስት የላላበት፤ የአካባቢ መሳፍንት የነገሱበት ዘመን ማለት ነው። ግዛቱን ለማስፋት፤ ወይም ጉልብቱን ለማሳየት፤ ወይም እኔ ካንተ በናቴም ባባቴም እበልጣለሁ በሚል ሰበብ አስባብ ጦርነት የሚከፋፈቱበት፤ ሚስኪኑ ኢትዮጵያዊ የሚያልቅበት ዘመን ነበር። ያንን ዘመን በር-ቀዳጅ የአድዋው ስሑል ሚካኤል ነበሩ።
ከዚያ ያለው እንደገና የማእከላዊ መንግስት መመስረት፤ ወይም ግዛት ማስፋት ዘመን ነበር። የዚህ አይነት ብሔራዊ መንግስት የመመስረት ሂደት (The Formation of National State) የሰው ልጅ ታሪክ ወጥ አካል ነዉ። ከነክፋቱ!! የአሁንዋ/የዛሬይቱ ኢትዮጵያም የዚያ ወጤት ነች። አሁን ከ120 አመት በላይ ሆኖታል። በዚህም የተነሳ ዛሬ ኢትዮጵያ በሚባለው አገር ታይቶ ተስምቶ የማይታውቅ የብሔረሰብ አነባበሮ ተፈጥሯል። በዚህም 120 አመታት ውስጥ መጋባት፤ መገባባት፣ መግባባትና መዋለድ ብቻ ሳይሆን አብሮ የመኖርና የመቻቻል ስነ ልቦና (Psychological make up) ተፈጥሯል።
ይህንን የኢህአዴግ የክልል መንግስት፣ የታሪክና የማህበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት ነገ ሲተነትኑት፤ ዘመን መሳፍንት ዳግማዊ የሚሉት ይመስለኛል። በአገር ደረጃ ወደፊት መራመድ ራሱ ከባድ መሆኑን ይሔው የምታዩት ነው። 200 አመት ወደ ኋላ ለመውሰድ መሞከር ግን የጤና አይመስለኝም። ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ ዩጎዝላቪያ ይባል የነበረው አገር ህዝብ አይነት አይደለም። ያ ሕዝብና መንግስት እንደዚያ የተፈረካከሰው የዛሬ 500 አመት በፊት የሆነ የታሪክ በደል በማንዠጉና አላምጦ ባለመዋጡ ነበር። ቱርክም፤ ሊባኖስም፤ ሶሪያም፤ ኢራቅም አይደለም:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ቂም በቀል ፤የነበረ ያልነበረ የሚያመንዥግ ህዝብ አይደለም። አላምጦ ውጦ የታሪኩ አካል አድርጎ ወደፊት የሚራመድ ታላቅ “ይቅር ለግዜር!!” ተባባይ ህዝብ ነው። የታላላቅ እምነቶቹም ሆነ የባሕላዊ እምነቶቹ መሠረቱ ይሔው ነው።
የእስልምና እምነት በአላት በደርግ ዘመን ወደ ብሔራዊው በአልነት መሸጋገራቸውን አንስቼ ነበር። አሁን በኢሕአዴግ ዘመን ደግሞ ምን እንደደረሰባቸውና በመድረስ ላይ እንዳሉ የሚያዉቁትና መላው አለምም የሚያዉቀው ስለሆነ ዝርዘሩ ውስጥ አለገባም። አንድ ነገር ብቻ ላስታውስዎት እወዳለሁ። ጠቅላይ ሚኒስቴር የነበሩት የመለስ ዜናውን “የመጨረሻ ኑዛዜ” ያንብቡ። ኑዛዜ ያልኩት ከማረፋቸው አንድ ይሁን ሁለት ወር በፊት ያደርጉት የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ስብሰባ ቃለ ጉባዔ ነው። ይህንን ሚስጥራዊ ቃለ ጉባዔ ያነበብኩት ድሕረ ገጾች ላይ ተለጥፎ ነበር። ማመን ነበር ያቃተኝ!! ወይም አንድ ሰው “የመጨረሻው ደውል” እንደተደወለለት ሲያውቅ፤ “እውነቱን ተናግሬ ልሙት!” ያሰኘዋል ይሉናል። በዚያ ስበስባ ላይ የአቶ መለስ አስተያየት ከማውቃቸውና ከሚታውቁበት መለስ ለየት ያሉ ነበር። እውነት ብቻ ሳይሆን የሚስጥር እውነት ነበር። ይህ እውነት የመጀመሪያቸውም የመጨረሻቸውም ነበር ብዬ እገምታለሁ።
አቶ መለስ ያሉት ቢጨመቅ “ይህንን የእስልምና እምነት ችግር የቀየስነውና የፈጠርነው እኛው (መንግስት) ስለሆንን ከዚህ በኋላ ይወገድ!” የሚል ይሆናል። የተቃወመ ሰው ቢኖር አንድ ዶክተር ሽፈራው ተክለ ማርያም የሚባሉ ነበሩ። የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ መደገፍ ብቻ ሳይሆን ድርጊቱን አውግዘውና ይህንን ወሳኔ አድምቀው፤ አክርረው ደግፈዋል። ያም ሆኖ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዛሬም አክራሪ ይሁን አሸባሪ (ልዩነት አልገባኝም፤ የገባውም ሰውም አላገኘሁም) በሚል እንደታጎሩ፤ያልታጎሩትም “ማነህ ባለ ሳምንት!”ን በመጠባበቅ እንደተሳቀቁ ናቸውና እባክዎን የአቶ መለሰን ኑዛዜ ስራ ላይ ያዉሉት። ከዚያ የተሻለ መፍትሔ የለምም!!
ይህንን ደብዳቤ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለሰ ዜናዊ አንዴ ከተናገሩት ጠቅሼ ማጠቃለል ፈለግሁ። መለስ፤ በሆነ አጋጣሚ (ረስቸዋለሁ) “በሩም መስኮቱም ከተዘጋ ህዝቡ ግድግዳውን ሰብሮም ቢሆን ይወጣል” ነበር ያሉት። ቃለ በቃል መጥቀሴ ሳይሆን መንፈሱ ይሔው ነበር። ዛሬ በመላው ኢትዮጵያ የሚታየው ቃል በቃል ይሔው መሆኑ የሚያከራክር አይመስለኝም። በምድር ላይ የሚታየው ማስረጃ ይሔው ነው። በሰነዶች ላይ የሚታየው ይሔው ነው። ተቃዋሚዎች፣ መንግስት ግን አክራሪ ወይም አሸባሪ የሚላቸውም፣ የሚናገሩት ይህንኑ ነው። አገርና አለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አካላትም የሚሉት ይህንኑ ነው። እርስዎም በተደጋጋሚ በሚያደርጉት ንግግር የሚሉት መንፈሱ ሲነጠር ይሕንኑ ይመስላል።
ይህ ሁሉ ሲሰባሰብ አንድ እውነት የሚያሳይ ይመስለኛል። ይህንን ኢሕአፈግ “ልማት፣ እድገት” ያለውን ሕዝቡ አልተቀበለውም። ይህንን ኢሕአዴግ መቶ-ከመቶ(100%) ድምጽ አግኝቼ ምርጫ አሸንፌያለሁ ያለው ውሸት መሆኑ ነው። ውሸትም ባይሆን ትላንት መቶ-ከመቶ (100%) የደገፈ በማግስቱ መቶ-ለመቶ ፈንቅሎ አይነሳበትም ነበራ! ወደ ህዝቡ መግቢያ ሽፋን እንዲሆኑ የተፈጠሩት ለምሳሌም እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ድርጅት የተባለውን ሽፋን መስጠት ቀርቶ ራሳቸው የሚሸፈኑበት ያጡ መሆናቸውም እውነት ነው። “አባይ ማደሪያ የለው ግንድ ያገላብጣል”ን አስታወሰኝ። እዚህ ያላነሳሁትን ሌሎች ማስረጃዎች ሰብሰብ አድርገን ብናበራያቸው ይህ ኢሕአዴግ ያመጣው ስርአት አልሰራም ማለት ነው። “ለማንም አልበጀ!” ሆኗል እንደማለት ነው። አድሮ ከዋለ ደግሞ ካደረሰው በላይ ዘላቂና ጠላቂ ጉዳት ያመጣል የሚል ብርቱ ፍርሐት አለኝ።
እንደኔ እንደኔ መፍትሔው፤ መውጫው ችግሩን በድፍረት ፊት ለፊት መጋፈጥ ነው። አውቃለሁ! መጋፈጡ እንዲህ ቀላል አይመስለኝም! ድፍረቱም ብልሐቱም ላይኖር ይችላል። ያም ሆኖ ግን አማራጩ፤ ማለትም አድሮ ውሎ ጊዜ ይፈተዋል በሚል የሚሰጥ የመተንፈሻ ጊዜ መግዣ ምክንያት መደርደር የሚጸጽት አማራጭ ይፈጥራል።
ትላንትና ያደመጥኩትን አንድ ነገር ልጨምር ፈለግሁ:- ከሶቪየት ህብረት ዘመን ጀምሮ ሩሲያን የሚያውቁ፤ አሁን ጡረታ ላይ የሚገኙ ጋዜጠኛ አን ጋረለስ (Anne Garreles) ሰሞኑን Public Broadcasting System (PBS) በተባለ ራዲዮ ጣቢያ Fresh Air በሚባል ፕሮግራም ላይ ረዘም ያለ ቃለ መጠይቅ አድርገው ነበር። ለቃለ መጠይቁ ዋንኛ ምክንያት የፑቲን አገር “Putin Country” የሚል መጽሐፍ ደርሰው ስለነበር ነው።
ቭላድሚር ፑቲን የሩሲያ የአሁኑ ፕሬዚዳንት ናቸው። ጋረልስ በዚህ ምልልስ በዚያ አገር፣ በሩሲያ፣ ውስጥ የሚታየውን የፖለቲካና ሁሉ ዘርፍ አቀፍ ንቅዘት ይዘርዝራሉ። የፑቲንን ጨምሮ! “ይህ ሁሉ ጉድ እያለ ሕዝቡ ፑቲንን እንዴት ያያል?” ለሚለው በሰጡት መልስ “ዛሬ በአለም ላይ ከሚገኙት መሪዎች ሁሉ በመላው የሀገሪቱ ህዝብ በጣም ተወዳጅነት ያለው መሪ ቢኖር ፑቲን ናቸዉ”አሉ። ምክንያቱን ሲጠይቁ “ከሳቸው በፊት የነበረው ፕሬዝዳንት፣ ቦሪስ የልሲን፣ ሰካራም ከመሆኑም ሌላዘራፊም ነበር። ዝርፊያው እንደቀጠለ ሆኑ ፑቲን በአገራችን፤ በሩሲያዊነታችን እንድንኮራ፣ እንድንኩራራ፣ አፋችንን ሞልተን ሩሲውያን ነን ለመለት አበቃን!” የሚል መልስ ሰጡ። ቃለ ምልልሱን ከጠቀስኩት ጣቢያ ማድመጥ የሚችሉ ይመስለኛል።
ለኛም የምንኮራባት፤ በጠፍ ጨረቃ ጥለን የማንፈጥጥባት፤ እንደወጣን የማምንቀረርባት፤ ለመመለስ የምንናፍቃት ኢትዮጵያን እንዲያስቡ፤ እንዲያልሙ፣ ወደዚያ የሚወስደውን መንገድ በሙሉ መስራት ባይችሉ እንኳን ጠረግ ጠረግ እንዲያደርጉ ከልብ እመኛለሁ። እመኝሎታለሁም!
ብርታት፤ ብልሐት እመኝላችኋለሁ! ለአገሬም የተሻለውን፤ የሚበጀውን፤ የሚያምረውን፣ የሚዘልቀውን የሚያዘልቀንን እመኝላታለሁ!
ኢትዮጵያ በሕዝቦችዋ ትብብር በነጻነትዋ ለዘለዓለም ትኑር!
ከአክብሮት ጋር

No comments:

Post a Comment