ከኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ
የካቲት 15 ቀን 2006 ዓ/ም ( February 22, 2014 )
I. መግቢያ:
የካቲት 3 ቀን 2006 ዓ/ም የወያኔ/ኢሕአዴግ ሊቀ-መንበርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ለአገር-ውስጥ ጋዘጤኞች በሰጡት መግለጫ ላይ የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይን በተመለከተ ለቀረበላቸው ጥያቄ በድፍረት የሰጡት ምላሽ የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴን ብቻ አይደለም መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በእጅጉ ያሳዘነና ያሳፈረ ሆኖ አግኝተነዋል። በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እግር የተተኩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የተረከቡት የመንግሥት ሥልጣንን ብቻ ሣይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ከበሬታ-አልባነትንም በሚመስል መልክ ነው ይህንን በጣም የተምታታ፤ በተቃርኖዎች የተሞላና በእጅጉ ኃላፊነት-የጎደለው ጋዜጣዊ-መግለጫ የሰጡት።
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ባደረገው ያላሰለሰ ክትትል የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥት ከሱዳን መንግሥት ጋር የሕዝብን መሠረታዊ-ሉዓላዊነት በሚዳፈርና ዘለቄታዊ ጥቅሙን ለባዕድ አሣልፎ በሚሰጥ ሁኔታ እየሸረበ ያለውን ደባና እየፈጸመ ያለውን አሣፋሪ ድርጊት በተገቢ ጥናትና በጠራ-መረጃ ላይ ተመሥርቶ በተከታታይ ባወጣቸው መግለጫዎች እንዲሁም በልዩ-ልዩ መገናኛ-ብዙኃን አማካይነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ለወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎችና ልዩ-ልዩ ተቋማት፤ ለሱዳን መንግሥትና ለዓለም-አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር ሲያሳውቅ መቆየቱ ይታወቃል። የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ግን አሁንም በዚህ የአገር ድንበርን በሚያክል ከባድ ጉዳይ ላይ ከዋናው ባለ-ጉዳይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ የጀመሩትን እኩይ ተግባር እየገፉበት አንደሆነ ከራሣችው አንደበት እየሰማን ነው።
II. የመግለጫው ዓላማ፤
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ በሚከተሉት ምክንያቶች ከላይ የተጠቀሰውን የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ንግግር በተመለከተ ይህንን መግለጫ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል።
ሀ). ከማንኛውም አገርና መንግሥት መሪ በተለይም የውጭ ግንኙንትን በተመለከተ የሚሰነዘር አስተያየትም ሆነ የሚሰጥ መግለጫ የአገር አቋም ተደርጎ የሚወሰድና በዋቢነትም የመጠቀስ መዘዝን ያዘለ በመሆኑ በዝምታ ሊታለፍም ሆነ ‘አጉል-መዘላበድ’ ተደርጎ ችላ ሊባል የሚችል ጉዳይ ባለመሆኑ፤
ለ). በዚህ የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ እየፈጸመ ባለው በአገር-ክህደት የሚያስጠይቅ፤ ሕዝብን የናቀ የድፍረት አርምጃና ሕገ-ወጥ ድርጊት አገራችን ኢትዮጵያ አንጡራ መሬቷ ለባዕድ አሣልፎ እየተሰጠ መሆኑ ምንም ዓይነት ተቀባይነትም ሆነ አግባብነት የሌለው ብቻ ሣይሆን የማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጉዳይና ሁሉም በግልጥ ሊረዳው የሚገባ መሆኑን ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ መግልጫዎች የሰጠነበት ቢሆንም አሁንም በድጋሜ ማሳሰቡ አስፈላጊ ስለሆነ፤
ሐ). አፄ ቴዎድሮስ፤ ንጉሥ ተክለ-ኃይማኖትና አፄ ዮሐንስን የመሳሰሉ ታላላቅ መሪዎች እየታገሉና ክቡር መስዋዕትነት እየከፈሉ አስከብረውት የቆየውንና በአካባቢው ሕዝብ የመረረ ተጋድሎ ታፍሮና ተጠብቆ የኖረውን የሱዳን ወሰን በድብቅ ስምምነት ለባዕድ አሣልፎ ለመስጠት የሚደረግ ሕገ-ወጥ ውል ውሎ-አድሮ የሚያስከትለው መዘዝ በቀላሉ የማይታይ ከመሆኑም በላይ፤ ይህንን በመሰለ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጀርባ በተፈጸመ ውል ድንበር ለማካለል የሚወሰድ እርምጃ ሁለቱን እህትማማች አገሮች ወደ-አይቀሬ ጦርነት የሚወስድና ይህም ኢትዮጵያና ሱዳን በመልካም ጉርብትና መርኅ ተከባብረው እንዳይኖሩ፤ የውስጥ ሰላማቸውንና እድገታቸውን ወደሚያደናቅፍ ያላስፈላጊ ችግር ውስጥ ከማስገባት አልፎ ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ ጠንቅ እንደሚሆን ሁሉም ሊያውቀው ስለሚገባ፤
መ). የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች በሱዳን በኩል ያለውን የአገር ወሰን በተመለከተ በድብቅ የሚያደርጉትን የክህደት ተግባር በወቅቱ ማጋለጥና ማክሸፍ ተገቢና የማንኛውም ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታ እንደሆነ በተደጋጋሚ የሚያሳስበውና የሚታገለው፤ ይህ ሕገ-ወጥ እርምጃ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ድንበሮቻችን እንዲደፈሩና አገራችን ኢትዮጵያ አንጡራ መሬቶቿን በተመሣሣይ ሁኔታ እንድታጣ በር-ከፋች ማስረጃ ሊሆን እንዳይችል ለማድረግም ጭምር ስለሆነ፤
ሠ). ይህንን ድብቅ ሴራ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በትክክል እንዲያውቀውና በተለይም የአገሩን ዳር-ድንበር የማስከበር ኃላፊነት ያለበት የአገሪቱ የመከላከያ ኃይልና የአገር-ደኅንነት ክፍል አባላት የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች አሳፋሪ በሆነ መልኩ በተሳሳተ መረጃ ላይ ተመሥርተው የአገራቸውን አንጡራ መሬት ለባዕድ አሳልፈው ለመስጠት የሚያደርጉትን የአገር-ክህደት ተግባር በትክክል ተረድተው ከሕዝባቸው ጎን አንዲቆሙና የአገራቸውን ዘለቄታዊ-ጥቅም የማስከበር መሠረታዊ የሙያ፤ የተቋምና የዜግነት ግዴታቸውን አንዲወጡ ማሳሰቡ አስፈላጊ በመሆኑ፤
ረ). በአገራችን የሥርዓት-ለውጥ እንዲኖር የሚታገሉ ድርጅቶች ለዚህ ዓብይ አገራዊ ጉዳይ የተባበረ ምላሽ ለመስጠት የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በአገራዊ አንድነት መንፈስና በተቀናበረ ሁኔታ እንዲሆን ለማሳሰብ፤…ነው።
III. ጭብጦች፤
ሀ.) በአቶ ኃይለማርያም ደሳልኝ / ኢሕአዴግ በኩል፤
1ኛ) አቶ ኃይለማርያም በዚህ መግለጫቸው ከእሳቸው በፊት የነበሩት የወያኔ/ኢሕአዴግ ጠቅላይ-ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ግንቦት 13 ቀን 2000 ዓም የሕዝብ-ተወካዮች ምክር-ቤት ፊት ቀርበው ምንም ዓይነት ታሪካዊ ማረጋገጫ ሳይኖራቸውና ያለ-አንዳች ሃፍረት ያሉትን በመድገም ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ እስከ ደርግ የነበሩት የኢትዮጵያ መንግሥታት ሁሉም የሻለቃ ግዌንን መሥመር እንደተቀበሉና እንደተስማሙ፤
2ኛ) የእሳቸውም መንግሥት ወያኔ/ኢሕአዴግ ይህንኑ የግዌን የወሰን ክለላ መሥመር እንደሚቀበል፤ በተግባር የመተርጎም ግዴታ እንዳለባቸውና ለዚህም ዝግጁ መሆናቸውን፤
3ኛ) ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በሚደረገው ሂደት አንድም የተፈናቀለ ኢትዮጵያዊ እንደሌለና ወደፊትም ሊኖር እንደማይችል፤
4ኛ) የሱዳንን ታጋሽነት በማወደስና የኢትዮጵያን ‘የተስፋፊነት’ አቋም በማውገዝ፤ ሃቁን በመካድና ታሪክን በማጣመም አሁን ሱዳን ይገባኛል የምትለውና የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥትም ለማስረከብ የተዘጋጀው መሬት ቀደም-ሲል በሱዳን ይዞታ ሥር የነበረና የቀድሞው የግብፅ ፕሬዝደንት ሆስኒ ሙባራክ ኢትዮጵያን በሚጎበኙበት ወቅት በተካሄደው የግድያ ሙከራ ሳቢያ በኢትዮጵያና በሱዳን መኻል የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ ‘ሱዳኖች የለቀቁትን መሬት ኢትዮጵውያን ገበሬዎች አልፈው ሲያርሱት የነበረውን’ አንደሆነ፤
5ኛ) በሁለቱ አገሮች መኻል ያሉ ልዩ-ልዩ የጋራ ጉዳዮችን በተመለከተ ከሁለቱም አገሮች የተሰየሙ ኮሚቴዎች በቋሚነት እየተገናኙ ምክክር ከማድረግና ውሎችን ከመዋዋል ውጪ በአሁኑ ጊዜ የተከለለ መሬት እንደሌለ፤
6ኛ) ይህንን ኢትዮጵያ ለሱዳን መሬት አሳልፋ ሰጠች የሚለው ‘አሉባልታ’ በአገሪቱ በየአምስት ዓመት የሚደረገውን የምርጫ ወቅት እየጠበቀ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል በወያኔ/ኢሕአዴግ ላይ የሚነዛ ወሬ እንደሆነ፤…
የእሣቸውንና የመንግሥታቸውን አቋም ሲያሣውቁ፤ በአጠቃላይ የአቶ ኃይለማርያም ደሳልኝ መግለጫ ይዘት ከአሁን በፊት አቶ መለስ ታሪክን በመከለስና ሃቁን በማድበስብስ የተናገሩትን በአዲስ መልክ በመድገም የኢትዮጵያን አንጡራ መሬት ለሱዳን አሣልፎ ለመስጠት የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ያላቸውን አቋምና እምነት፤ ይህንንም በተግባር ለመተርጎም የደረሱበትን ውሳኔ ይፋ ያደረገና በኢትዮጵያ ላይ ምስክርነት የሰጠ ሆኖ አግኝተነዋል።
ለ.) በኢትዮጵያ ሕዝብ በኩል፤
1ኛ) የአውሮጳ ቅኝ-ገዥዎች ያለ-አፍሪቃውያን ተሣትፎና ይሁንታ የአፍሪቃን ምድር እንዳሻችው ሲቀራመቱ በነበረበት ወቅት ሱዳንን ከግብፅ ጨምራ ትገዛ የነበረችው ቅኝ-ገዠዋ እንግሊዝ የኢትዮ-ሱዳን ድንበርን በተመለከተ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት ከነበሩት ብልኁ መሪ አፄ ምኒልክ ጋር ድርድርና ውል ማድረጋቸው የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።
አፄ ምኒልክም ሆኑ ሌሎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች ከእነዚህ አውሮጳውያን ጋር ውል ሲዋዋሉና ሲደራደሩ በእነዚህ ባዕዳን የተውተበተቡ ብዙ ሴራዎችን እያከሸፉና የአገራቸውን ጥቅም ለአፍታም አሣልፈው ሳይሰጡ፤ አገራዊ ኃላፊነታቸውንና የመሪነት ግዴታዎቻቸውን በሚገባ የሚወጡ እንደነበር በኩራት የሚዘከር ነው።
በአንድ ወቅት አፄ ዮሐንስ አራተኛ “ምጥዋን ለጣሊያኖች አልሰጠኋቸውም፤ እንግሊዞች ናቸው የሰጧቸው፤ ምጥዋ የኢትዮጵያ ነው። እኔ በአግባቡ የኢትዮጵያ የሆነውን ማንኛውንም ግዛት የመተው ፍላጎትም ሆነ ሥልጣኑም የለኝም’’ ሲሉ እንዳረጋገጡት ሁሉ፤ በአገር-ወዳድነታቸው የታወቁት የኢትዮጵያ መሪዎች ከፈጣሪ በታች ጠያቂ የሌለባቸውና ምንም ነገር ለማድረግ ሙሉ-ሥልጣን የነበራቸው ቢሆንም አንኳ የሕዝብንና የአገርን ጥቅም አሣልፈው ያልሰጡ ብቻ ሣይሆን ጥንት የኢትዮጵያ ግዛቶች የነበሩና በልዩ-ልዩ ምክንያቶች ከኢትዮጵያ ይዞታ ውጪ የሆኑትን ለማስመልስ ያለ-መታከት የሚጥሩ፤ በዚህ ጥረትም ሕይዎታቸውን መስዋዕት ያደርጉ እንደነበር ይታወቃል።
አገራችን ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ያላትን ወሰን በተመለከተ አፄ ምኒልክ ከእንግሊዝ መንግሥት ጋር የተዋዋሉት ያ ውል ግን አሁን የኢሕአዴግ መሪዎች የሚሉትንና አጣምመው የሚያቀርቡትን ሻለቃ ግዌን የተባለ የእንግሊዝ መኮንን ያለ-ኢትዮጵያ ተሣትፎና እውቅና፤ በራሱ ፈቃድና ዓይን-ባወጣ አድሎዓዊነትብቻውንአሰመርኩት የሚለውን መስመር ፈጽሞ የሚመለክት እንዳልሆነ በተገቢ ግልጥ መሆን ይኖርበታል። ‘የግዌን መስመር’ የተባለውን ይህ የተናጠል ውሳኔ አንድም የኢትዮጵያ መንግሥት ሆነ መሪ እንኳን ሊገዛበት ሕጋዊ እውቅና የሰጠበትም ሆነ ትክክል ነው ብሎ አምኖ የተቀበለበት ጊዜ የለም። እንግዲህ የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች በግልጥ እያምታቱ ያሉት አፄ ምኒልክ አገራቸው ኢትዮጵያ በሱዳን በኩል ያለውን ድንበሯን በተመለከተ ከእንግሊዝ ጋር ያድረጉትን ስምምነትና ከዚያ በኋላ ግዌን ከላይ በተጠቀሰው ሁኔታ ብቻውን አካልያለሁ የሚለውንና በኢትዮጵያ በኩል ምናልባት ከአቶ መለስና ከምትካቸው ከአቶ ኃይለማርያም የተዛባና ሃቁን ያወናገረ ምስክርነት በስተቀር ምንም ዓይነት ሕጋዊ-ተቀባይነትም ሆነ አስገዳጅነት የሌለውን የአንድ-ወገን ውሳኔ ነው።
‘የግዌን መስመር’ የተባለውን ቅድመ-ወያኔ/ኢሕአዴግ የነበሩ የኢትዮጵያ መንግሥታት መቸውንም ያልተቀበሉት፤ ኢትዮጵያም ልታከብረውና መቀበል ልትገደድበት የማትችል በመሆኑ፤ ይህንን በተለየ መልኩ ለማቅረብ የሚከጅሉ መሠረታዊ በሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊና አገራዊ ጥቅም ላይ ከሚዘምቱ ባዕዳን ተለይተው ሊታዩ የማይችሉና በአገር-ክህደት ተግባር የሚያስጠይቃቸው እንደሆነ ለሁሉም ግልጥ መሆን ይኖርበታል።
2ኛ) አቶ ኃይለማርያም በዚህ መግለጫቸው የተረኩት ሌላው በጣም አስገራሚና መሠረተ-ቢስ አባባል ደግሞ በኢትዮጵያና በሱዳን መኻል እ.አ.አ. በ1996 ዓም በተፈጠረው ግጭት ሣቢያ ሱዳኖች የለቀቁትን መሬት ኢትዮጵያውያን ድንበር ዘልለው ሲያርሱ እንደነበርና ይህ መሬት የሱዳን በመሆኑ ሊመለስላቸው እንደሚገባ መንግሥታቸው እንደሚያምንበት፤ ይህንንም ተቀብሎ በተግባር ከመፈጸም ወደ-ኋላ እንደማይል የሚለው ህቶት ነው።
ሃቁን ገልብጦ ለመረዳት ካልተፈለገ በስተቀር እውነታው ግን የዚህ ተቃራኒ መሆኑ ግልጥ ነው። በመጀመሪያ በኢትዮጵያ የተያዘ የሱዳን መሬት የለም። እንደሚታወቀው በአፄ ኃይለ-ሥላሴ መንግሥትም ቢሆን ኢትዮጵያ በሱዳን ወሰኗ በኩል ጎላ-ብለው የሚታዩ የጦር-ሠፈሮች አልነበሯትም። በደርግ ጊዜም ቢሆን በዋናነት የውስጥ ተቃዋሚዎችን ለመፋለም ካልሆነ በስተቀር ለድንበር ጥበቃ የሚበቃ ሠራዊት በዚህ የአገሪቱ መሥመር አልነበረም። ድንበሩ ተከብሮ የኖረውና በሱዳኖች በኩል ይደረጉ የነበሩ አንዳንድ ድንበር-ዘለል መተናኮሶችን ሲከላከልና ሲያከሽፍ የኖረው የአካባቢው አገር-ወዳድ ሕዝብ እንደነበር ይታወቃል። በደርግ ጊዜም በተለይ በጎንደር ክፍለ-አገር ባለው ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑበት አካባቢ ከሕዝቡ በተጨማሪ የኢዴኅ (ኢዲዩ)፤ የኢሕአፓ፤ የአገር-ወዳድ ድርጅት፤ የከፋኝ አርበኞች ድርጅት፤ ወዘተ ታጣቂዎች ይንቀሳቀሱ ስለነበር፤ አሁን የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ‘ቀድሞ የሱዳን ይዞታ የነበረና በኋላ ግን የኢትዮጵያ አራሾች የያዙት መሬት’ ብለው በድፍረት የሚናገሩት ከኢትዮጵያውያን ይዞታና ቁጥጥር-ውጭ ያልነበረ ነው። ደርግ እየተሸነፈ ወያኔ/ኢሕአዴግ ወደ አዲስ አበባ ሲያመራ ቀደም-ሲል ሕዝባቸውን እያስተባበሩ ድንበራቸውን ያስከብሩ የነበሩ የአካባቢው መሪዎች በሞት እየተለዩና ድንበር-ጠባቂዎችም የተለመደ የድንበር-ማስከበር ሥራቸውን መሥራት ያልቻሉበት ጊዜ ስለነበር፤ እንዲሁም በአካባቢው ይንቀሳቀሱ የነበሩ ኢትዮጵያዊ ታጣቂ-ኃይሎች በልዩ-ልዩ ምክንያቶች በአካባቢው ያልነበሩበት ሁኔታ በመከሰቱ፤ ሱዳኖች ይህንን የተፈጠረ ክፍተት ተጠቅመው ድንበር እያለፉ የኢትዮጵያን መሬት መያዝና ጦር ማስፈራቸው ይታወቃል። እግር-በእግርም የሱዳን ገበሬዎችና ሃብታሞች ይህንኑ በሕገ-ወጥ መንገድና በጉልበት የተያዘ የኢትዮጵያ መሬት ማረስና ማሳረስ፤ ጫካውንም እንደፈለጉ ማውደምና መዝረፋቸው ግልጥ ነው። የአካባቢው ሕዝብ ይህንን የሱዳን ድፍረት ለመቋቋም ለአዲሶቹ ገዥዎች (ለወያኔ/ኢሕአዴግ) አቤቱታ በማቅረብ ጭምር የሚችለውን ሁሉ ከማድረግ አልተቆጠበም።
“ማን ይናገር የነበረ፤ ማን ያርዳ የቀበረ” አንዲሉ ነውና ምናልባትም ይህንን ጉዳይ በትክክል ግልጥ ለማድረግ በወቅቱ የአዲሱ መንግሥት የመከላከያ-ሚኒስትር የነበሩት አቶ ስዬ አብርሃ ግንቦት 23 ቀን 2000 ዓ/ም በወጣው ‘አዲስ ነገር’ ጋዜጣ ላይ ያሠፈሩትን ሃቅ በዋቢነት መጥቀሱ አስፈላጊ ነው። አቶ ስዬ የተባለውን የጽሑፍ ምስክርነት የሰጡት ግንቦት 13 ቀን 2000 ዓ/ም አቶ መለስ የሱዳንን የድንበር ጉዳይ በተመለከተ ሕዝብ-ተወካዮች ምክር-ቤት ፊት ቀርበው ለሰጡት የተዛባ ዘገባ ምላሽ ነው። አቶ ስዬ በዚህ ጽሑፋቸው ግልጥ ያደረጉት ነገር የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች የኢትዮጵያን መሬት ለሱዳን አሣልፎ ለመስጠት በማስረጃነት ሊጠቀሙበት የሚሹትና እንደ-ምክንያት የሚያቀርቡት አንዱ ይህ አሁን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የደገሙትና ቀደም-ሲል አቶ መለስ ሃቁን ገልብጠው ያቀረቡት ለሱዳን ለመስጠት የወሰኑት ‘ቀደም-ሲል በሱዳን ይዞታ ሥር የነበረውንና በኋላ በግብፅ መሪ ላይ በተሰነዘረው የግድያ ሙከራ ሣቢያ ኢትዮጵያና ሱዳን መኻል የነበረው ግጭት በፈጠረው ክፍተት ኢትዮጵያውያን ድንበር ተሻግረው ያርሱት የነበረውንና ድሮም የሱዳን ይዞታ የነበረውን ነው’ የሚለውን የፈጠራ ትረካ ነው። አቶ ስዬ ስለዚሁ ጉዳይ በዚህ ጽሑፋቸው ያቀረቡትን በሰፊው እንጠቅሳለን።
“የሱዳን መንግሥት ይህንን የጥበቃ ኬላዎች ያለመኖር ሁኔታ በመጠቀም ሠራዊቱን ወደዚህ ቀጠና ማስገባቱን ቀጠለ። ሱዳናውያን አራሾች የሠራዊታቸውን ኮቴ እየተከተሉ መጠጋት ጀመሩ። ባለቤት የሌለው መሬት አገኘን ብለው ደኑን ማጥፋት፤ የእርሻ መሬቱን እንዳሻቸው መያዝ ቀጠሉ። ይባስ ብለው በእርሻ ሥራ መቋቋም የጀመሩትን ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች መተናኮልና መጋፋት ጀመሩ። ሁኔታው አየባሰበት በመሄዱ ውሱን የመከላከያ ኃይል በዚሁ አካባቢ በማስፈር ቀስ በቀስ ይህንኑ ማጠናከር ጀመርን። ሠራዊቱ ይህን በአራሾች ላይ የሚደርሰውን በደል እና በዓይናችን ፊት የሚደርሰውን ውድመት መቃወም ጀመረ። በአካባቢው የተመደበው የመከላከያ ሠራዊታችን አዛዥ የጽሑፍ መልእክቱን አስይዞ አቻው ወደሆነው የሱዳን ጦር አዛዥ አንድ የመላክተኛ ጓድ ይልካል። የተላከው ጓድ የተደረገለት አቀባበል የወዳጅ ሠራዊት አቀባበል አልነበረም። ኑ ብለው ተቀብለው ትጥቃችውን አስፈትተው አረዷቸው። ይህ ድፍረትና ጭካኔ እንደተፈጸመ ሠራዊታችን አይምሬ የአጸፋ እርምጃ ወስዶ በአካባቢው የነበረው ጦር እንደወጣ ቀረ። እኔ በኃላፊነት እስከነበርኩበት ጊዜ ድረስ ሱዳኖች ወደዚህ እካባቢ ተተኪ ሠራዊት አላኩም። አቶ መለስ ሠራዊታችን በ1995/1996 አካባቢ የወሰደው ማጥቃት ብሎ የገለጸው ይህንኑ የአጸፋ እርምጃ ነው። ይህንን አካባቢ ሠራዊታችን በወሰደው የአጸፋ እርምጃ ምክንያት በእጃችን የገባ የእኛ ያልሆነ መሬት አድርጎ ማቅረቡ ግን ትክክል አይደለም። የሱዳን ወታደሮች እና እነርሱን ተከትለው የመጡት የሱዳን አራሾች ወደዚህ ቀጠና የመጠጋታቸው ታሪክ ከፍ ብሎ ከገለጽኩት የነገሮች አንድነት ጋር የተያያዘ ነውና ድንበር ሳይካለል በፊት እንደዚህ ብሎ ፍርድ መስጠት አይገባውም ነበር። አስቀድሞ በኢትዮጵያ ላይ እየመሰከረ ነው።”
ሲሉ ስለሁኔታው ምስክርነታቸውንና ትዝብታቸውን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ አሳውቀዋል።
3ኛ) የወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥት ለሰባት ዓመታት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሣይሆን እራሱ ከሚቆጣጥረው ፓርላማ ጀርባ በድብቅ ያቋቋማቸው ‘የኢትዮጵያና የሱዳን የጋራ ድንበር ኮሚሽን’ እና ‘የኢትዮጵያና የሱዳን የፖለቲካ ኮሚቴ’ የሚባሉ ሁለት ልዩ አካሎች መኖራቸውን ይፋ ያደረገው ይህን ድብቅ ሥራውን ማጋለጥ ከተቻለ በኋላ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ከሱዳን ጋር በእነዚህ ድብቅ አካሎች አማካይነት በየጊዜው ስለሚደራደራቸው ኢትዮጵያን የሚጎዱ ውሎችና ስለሚፈጽማቸው የሕዝብን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ተግባራት ማወቅ የቻለው በመንግሥት ስም ከተቀመጠው አካል ሣይሆን ጋፍኛ ከሱዳን መንግሥት ባለሥልጣናትና ከእነሱው መገናኛ-ብዙኃን ነው። የዚህ ድብቅ ሴራ ተጠቃሚ የሆኑት ሱዳኖች ከለጋስ የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች በየጊዜው ስለተቸሯቸው የኢትዮጵያ መሬቶች የምስራቹን ለሕዝባቸው ቢያበስሩና በአንፃሩ ከሕዝብ ጀርባ ተደብቀው አገርን የሚጎዳ የክህደት ተግባር ላይ የተሰማሩት የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች መሰሪ ሥራቸው እንዳይታወቅ ለመደበቅ ቢሞክሩ፤ ያ ደግሞ ሳያስቡት ይፋ ሲሆን ምንም ተቀባይነትም ይሁን ታሪካዊ እውነታ የሌላቸው የሃሰት ማስረጃዎችን ለመደርደር ቢማስኑ ላያስገርም ይችላል። የሚያስገርመውና የሚያሳዝነው ግን የባዕዳንን ተደጋጋሚ የቀጥታ ወረራዎች ጭምር ተቋቁማና ብዙ መስዋዕትነት ተከፍሎ ተከብራ የኖረች ኢትዮጵያ አገራችን እንመራታለን በሚሉ በራሧ ልጆች ችሮታ ድንበሯ መደፈሩና አንጡራ መሬቷን እንድታጣ መደረጉ ነው።
እንደ ሱዳን ባለ-ሥልጣኖች ቀጥተኛ ዘገባ ከሆነ ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን ድንበር ለመካለል ከወያኔ/ኢሕአዴግ መንግሥት ጋር መስማማታቸውን ብቻ ሣይሆን ቋሚ የወሰን ምልክቶችን ለማስቀመጥ ቀኖች መቆረጣቸው፤ ተግባራዊ ለማድረግ ከሚጠይቀው ወጪ ሱዳን ሁለት-ሦስተኛውን ለመሸፈን ፈቃደኛና ዝግጁ መሆኗን፤ እንዲያውም ሥራው ከወዲሁ መጀመሩን ጭምር ያስረዳል። ይህ እውነታ ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተለያዩ መንገዶች ሲታወቅ ብቻ በአብዛኛው ጉዳዩን ለማስተባበል ሲባል አልፎ-አልፎ በወያኔ/ኢሕአዴግ የውጭ-ጉዳይ መሥሪያ ቤት የሚሰጡ መግለጫዎችና አሁን አቶ ኃይለማርያም ከሚናገሯቸው የተምታቱ ንግግሮች መረዳት የሚቻለው ቢያንስ በሱዳን በኩል የሚቀርቡ ዘገባዎችን ሃሰትነት በአስተማማኝ የሚያረጋግጡ አይደሉም። አንዲያውም እውነታውን ይበልጥ የሚያጋልጡ ሆነው ይገኛሉ።
4ኛ) ከአሁን በፊት ኮሚቴአችን ባወጣቸው መግለጫዎች እንዳሳወቀው ሁሉ፤ አቶ መለስ ግንቦት 13 ቀን 2000 ዓ ም ፓርላማ ቀርበው ‘አንድም የተፈናቀለ ኢትዮጵያዊ የለም’ ብለው በድፍረት ሲናገሩ ልክ ከአንድ ወር በፊት (በሚያዝያ 13 ቀን) ድንበር ተሻግሮ በመጣ የሱዳን ጦር በቋራ ወረዳ ውስጥ ነፍስ-ገበያ ከተባለ የእርሻ ሥፍራ 34 ኢትዮጵያውያን ቤት ንብረታቸው ተቃጥሎና ተዘርፎ እነሱም ታግተው ወደ ሱዳን ተወስደው መታሰራቸው እንኳ ጥቂትም የወገናዊነት መቆርቆር ቀርቶ ሰብዓዊ ስሜት አልታየባቸውም። ይበልጥ ስሜታቸውን የነካውና የከነከናቸው ሱዳኖች ያሳዩት ታጋሽነት (ያውም የኢትዮጵያን መሬት ለመውሰድ) እንደሆነ በአንደበታቸው ገልጠውታል። በጣልያን ወራሪዎች የተፈጸመው ልዩ ሁኔታ እንዳለ ሆኖ፤ ምናልባትም እነ-ልዑል ዓለማየሁ ቴዎድሮስን አፍኖ ከአገራቸው ከኢትዮጵያ ወደ-እንግሊዝ ከወሰደው በናፒር የተመራው የእንግሊዝ የባዕድ ጦር ወዲህ ኢትዮጵያዊ ዜጎች በባዕድ ወራሪ ጦር ከአገራቸው ታፍነው ወደ-ባዕድ አገር ተወስደው የታሠሩት በዘመነ-ወያኔ/ኢሕአዴግ ብቻ ነው።
አሁንም ኢትዮጵያውያን አርሶ-አደሮች ከዘመን-ዘመን ከኢትዮጵያ ይዞታና ቀጥተኛ ቁጥጥር ውጭ ሆኖ ከማያውቀው እርሻቸው እየተፈናቀሉና እየተነቀሉ መሆናቸው፤ ሱዳኖች በወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ሥልጣንና ችሮታ ተሰጥቶናል በሚሏቸው ሥፍራዎች ቁጥጥራቸውን ለማጠናከር እየተጣደፉ እንደሆነ የዓይን ምስክሮች እያረጋገጡት ያለ ጉዳይ መሆኑ ሊታውቅ ይገባል።
5ኛ) ስለ-አገር ድንበር ጉዳይ በማንኛውም ጊዜ ማንሳትና የሚከሰቱ ስጋቶችን መግለጥ የማንኛውም ኢትዮጵያዊ የዜግነት ግዴታና የፖለቲካ ድርጅቶችም መሠረታዊ ኃላፊነት መሆኑን የዘነጉት አቶ ኃይለማርያም፤ ይህንን የድንበር ጉዳይ የሚያነሱ ወገኖችን (በተለይም የፖለቲካ ድርጅቶችን) ‘ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል የምርጫ ጊዜ ሲቃረብ እየተጠበቀ የሚቀርብ’ ተራ የፖለቲካ አጀንዳ አድርገው ለማሣየት ዳድተዋል። ጉዳዩን በዚህ መልክ ለማቅርብ የፈለጉበት ምክንያት ግልጥ ነው። አንድም የጉዳዩን ክብደት አቅልሎ ለማሳየትና ሕዝብን ለማደናገር ሲሆን፤ በዋናነት ግን አሁንም በተለይ ጉዳዩ በአግባቡ ያሳሰባቸውና ሕዝብን ሊያነሳሱብን ይችላሉ ብለው የሚሰጉባቸውን ድርጅቶች ከወዲሁ ለማሸማቀቅ በማሰብ ነው። የሚገርመው ግን በአንድ አፋቸው ከሱዳን ጋር ያለውን ድብቅ ድርድር ላለፉት አሥራ-ሦስት ዓመታት ሁለት ኮሚቴዎችን አቋቁመውና በየጊዜው እየተገናኙ ሥራቸውን እየሠሩ እንደሆነ እራሣቸው እየተናገሩ፤ እዚያው-በዚያው ይህንን እነሱ እያደረግን ነው የሚሉትንና ያልካዱትን ከሕዝብ የተደበቀ ሥራ ‘ሕዝብ እያወቀው ይሠራ፤ የምታደርጉት የአገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚጻረርና ሕገ-ወጥ ነው’ የሚሉ ወገኖችን ኃላፊነት-የተሞላበት አቤቱታ አምስት ዓመት ጠብቆ ከሚደረግና ውጤቱ አስቀድሞ ከተወሰነ የምርጫ ጨዋታ ጋር ለማያያዝ መሞከር ቢያንስ ተኣማኒነትም ሆነ ተቀባይነት የለውም።
IV. ማጠቃለያ:
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ አሁንም ለወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ያለው መልእክት አንድ ነው። የኢትዮጵያን ሕዝብ ንቃችሁ ከሱዳን መንግሥት ጋር በድብቅ የምታደርጉት ማንኛውም ውል ሕገ-ወጥ እንደሆነ፤ የአገርን ብሔራዊ ጥቅም አሣልፎ የሚሰጥና እናንተንም በአገር-ክኅደት ተግባር የሚያስጠይቅ ከፍተኛ ወንጀል መሆኑን ከወዲሁ ያስታውቃል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ባልመከረበት፤ ባላወቀውና ባላመነበት ድርድር የሚደረግን ውሳኔ በለከት-የለሽ ዕብሪትና በተራ-ማምታታት ተግባራዊ ለማድረግ መሞከር አገርን ለባሰ አደጋ ማጋለጥ እንደሆነና ለውስጥም ሆነ ለአካባቢ አለመረጋጋት ምንጭ እንደሚሆን ልትገነዘቡት ይገባል። ስለሆነም በአገርና በሕዝብ ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት በመገንዘብ፤ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጠውን ስምምነት ከመተግበር እንድትቆጠቡ እናሳስባለን።
የአገር-መከላከያ ክፍሎችና አባላት ለዚህ ዓብይ አገራዊ ጉዳይ የሚገባውን ክብደት ሰጥታችሁ ባዕዳን ድንበር ገፍተውና ተሻግረው በሕዝባችሁ ላይ ለሚደርስ ብሶትና ሰቆቃ የሚኖርባችሁን ሙያዊና የዜግነት ግዴታ ለመወጣት ብሔራዊ ኃላፊነት አለባችሁ።
ለሥርዓት ለውጥ የቆማችሁና የምትታገሉ አገር-ወዳድና ዴሞክራት ድርጅቶች የአገር ድንበር ጉዳይ በቀላሉ የሚታይም ይሁን ለጊዚያዊ የፖለቲካ ፍጆታ የሚመነዘር ሣይሆን መሠረታዊ የብሔራዊ ክብርና የጋራ ኅልውና መርኅ ነውና ተባብራችሁና ሕዝባዊ ኃይላችሁን አስተባብራችሁ ይህን እኩይ ሴራ ለማክሸፍ የጋራ እንቅስቃሴዎቻችሁን እንድታጎለብቱ እናሳስባለን።
ከአሁን በፊት በተደጋጋሚ አንዳስገነዘብነው ሁሉ ይህ ጉዳይ ለወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ወይም ለተወሰኑ ክፍሎች የሚተው ሣይሆን የሁሉም የጋራ አገራዊ ጉዳይ በመሆኑ፤ ዞሮ-ዞሮ የዚህ አሣፋሪ ድርጊት ዕዳ ከፋዩ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመኻልህ ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከትም፣ የጎሣ፣ የሐይማኖትም ይሁን የአካባቢ ልዩነት ሳታሣይ ወዳጅ ቀርቶ ጠላት በመሰከረልህ የተለመደ የአገር መውደድና የአንድነት መንፈስ የጋራ ድምፅህን እንድታሰማና በጋራ እንድትቆም ወገናዊ ጥሪያችንን በአክብሮት አናቀርባለን።
በኢትዮጵያ ላይ የሚሸረብ ደባ ይከሽፋል!
የኢትዮጵያ ዳር-ድንበር በሕዝቧ ኅብረትና አንድነት ተረጋግጦ ይቀጥላል!!
ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ለዘለዓለም ትኑር!!!
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ
No comments:
Post a Comment