Translate

Thursday, February 27, 2014

ሀይለመድህን አበራ፦ የታፈነ ብሶተኛ ወይንስ የሚያደርገውን የማያውቅ የአእምሮ በሽተኛ?

አሰፋ (ከዳላስ)

መንግስትና የመንግስት ደጋፊዎች ነን ባዮች ማምታታቱን ትተው አንዱን መምረጥ አለባቸው

Ethiopian Airlines pilot Hailemeden Abera Tegegnየሰሞኑ ትኩስ ዜና በሆነው የረዳት አብራሪ ሀይለመድህን አበራ የሚያበረውን አውሮፕላን ጠልፎ ስዊዘርላንድ ማሳረፉን በተመለከተ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው:: በተለይ የኢትዮጵያው አገዛዝ እና እሱን አውቀውም ይሁን ሳያውቁ ለመደገፍ የሚፈልጉ ሰዎች የሚስጡዋቸው መላምቶች የሚያስገርሙና እርስ በርሳቸው የሚጋጩ ናቸው:: ከነዚህ አስተያየቶች መካከል ሁለቱን ልጥቀስ:: በአንድ  በኩል ሀይለመድህን የአእምሮ ችግር አለበት ሲሉ በሌላ በኩል ደግሞ የሀገሪቱንም ሆነ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ስም ያጎደፈ በማለት ለመውቀስ ይዳዳቸዋል::

እንግዲህ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ እነዚህ ሁለቱ ግምቶችና ወቀሳዎች በአንድ ግዜ እና በአንድ ላይ እውነት ሊሆኑ አይችሉም:: አንዱ እወነት ከሆነ ሌላው ሀሰት ይሆናል:: ይህም ማለት ሀይለመድህን የአእምሮ በሽተኛ ከሆነ የኢትዮጵያንም ሆነ የአየር መንገዱን መልካም ገፅታ በማቆሸሽ ሊወቀስ አይችልም:: ምክንያቱም አንድ ሰው የአእምሮ ህመም አለበት ከተባለ በአእምሮ ህመም ውስጥ ሆኖ ለሚፈፅመው ድርጊት ሀላፊነት ሊወስድ አይጠበቅም:: አመዛዝኖና አስቦ ያደረገው ስላልሆነ:: ድርጊቱ በሰውየው እንደተፈፀመ ተደርጎ አይታሰብም:: ምክንያቱም ከግለሰቡ ቁጥጥር ውጪ በሆነ ሀይል ተፅእኖ ስር ሆኖ ያደረገው የተከናወነ በመሆኑ:: በዚህም የተነሳ መልካም ነገር ቢሰራም ሊመሰገንና ሊሸለም እንደማይችል ሁሉ ክፉ ነገር ቢያደርግም ሊወቀስ እና ሊፈረድበት አይገባም:: ይህ ካልሆነ ግን የአእምሮ በሽተኛ የሚለውን ማንሳቱ ብዙም ትርጉም ሊኖረው አይችልም:: ስለዚህ መንግስትና የመንግስት ደጋፊዎች ነን ባዮች ማምታታቱን ትተው አንዱን መምረጥ አለባቸው::
ከላይ እንደገለፅኩት እውነት ሀይለመድህን የአእምሮ ችግር ወይንም የመንፈስ ጭንቀት ነበረበት ከተባለ ሊታዘንለት ይገባል እንጂ ሊወቀስ አይችልም:: ምናልባት ሊወቀስና ሊጠየቅ የሚገባው የአእምሮ ችግር ውስጥ ያለን ሰው አውሮፕላን ማብረርን የመሰለ ከፍተኛ የመንፈስ መረጋጋትን የሚጠይቅ ከባድ ስራ ውስጥ እንዲሰማራ ያደረገው ክፍል ይመስለኛል:: ለነገሩ ሀይለመድህን የሰራው ስራ በአእምሮ ጭንቀት ውስጥ ያለ ሰው ያደርገዋል ብሎ ማሰብ ፍፁም ይከብዳል:: አውሮፕላንን ያህል ነገር ከ200 በላይ ተሳፋሪ ጭኖ ያውም በሁለት የጦር ጄት አውሮፕላኖች እንደተከበበ አውቆ በተረጋጋ ሁኔታ በሰላም የሚፈልገው ቦታ ማሳረፍ መቻል አንድ የአእምሮ ችግር ካለበት ሰው የሚጠበቅ ድርጊት አይመስለኝም:: ይልቁንስ የሰከነ አስተሳሰብ ያለው እንዲሁም የሚያደርገውን ጠንቅቆ የሚያውቅ ሰው የፈፀመው ተግባር እንጂ የአእምሮ መረበሽ ውስጥ ያለ ሰው ድርጊት ያለመሆኑን አእምሮ ያለው የሚረዳው ነው::
ሌላው ከዚሁ ከአእምሮ ህመም መላምት ጋር ተያይዞ መነሳት ያለበት ጥያቄ በርግጥ ልጁ የአእምሮ መታወክ ከነበረበት ለዚህ የአእምሮ ችግር ያበቃው ምክንያት ምንድነው የሚለው ነው:: እስካሁን ባለው መረጃ “የአእምሮ ህመም” የሚለው ጉዳይ በመጀመሪያ መነሳት የጀመረው እህቱ ሰጠችው ከተባለው “መግለጫ” በኋላ ነው:: እህቱ ተናገረች የተባለውን እንኳን ብንቀበል እሷ የተናገረችው ወንድሟ ከአጎቱ ሞት በኋላ መረጋጋት እንደማይታይበት፤ የሚከታተሉኝ “ሰዎች” አሉ ብሎ እንደሚያስብና በዚህም ምክንያት ጭንቀትና መረበሽ ይታይበት እንደነበር ገልፃለች:: ኮምፒውተሩን (ላፕቶፑን) ሲከፍት እንኳን ስለሚጠራጠር ካሜራውን ይሸፍን ነበር ብላለች:: ከቤተሰቡም ጋር የነበረው ግንኙነት እየቀነሰ መጥቶ ብቸኝነትን ማዘውተር እንደጀመረም አስረድታለች ነው የተባለው:: ይህ የሚያያሳየው በአንድ ወይንም በሌላ መልኩ “የአእምሮ ህመሙ” ከአጎቱ ሞት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ነው::
በሌላ በኩል እስካሁን የታወቀውን በአጎቱ ሞት ዙሪያ ያሉትን እውነታ ስንመለከት “ሞተው ተገኙ” ከሚል በስተቀር ብዙም የታወቀ ነገር እንደሌለ እንረዳለን:: ስለዚህ የአጎቱ ሞት ለአዕመሮ ችግር በሚዳርግ መልኩ ያስጨንቀው ከነበረ ለምን ይህንን ያህል አስጨነቀው የሚለው መመለስ አለበት:: ለአጎቱ ካለው ቅርበት የተነሳ እሳቸውን በማጣቱ ጥልቅ ሀዘን ስለተሰማው አእምሮውን ረብሾት ይሆናል ብሎ ማሰብ ስህተት ላይሆን ይችላል:: በሌላ በኩል ደግሞ ስላሟሟታቸው የሚያውቀው ወይንም የሚጠረጥረው ነገር (ምስጢር) ስላለ በዚህም የተነሳ  ለራሱም ደህንነት ስጋት ውስጥ የከተተው ነገር በመኖሩ እንዲህ አይነቱ ድርጊት ውስጥ ሊገባ እንደቻለ መገመትም ተገቢ ይመስለኛል::
በእኔ አስተያየት ከመጀመሪያው ይልቅ ሁለተኛው ግምት ለእውነቱ ይቀርባል እላለሁ:: በሁለት ምክንያቶች:: በመጀመሪያ የአጎቱ ሞት ምክንያት ባለመታወቁ:: በሁለተኛ ደረጃ ልጁ አውሮፕላኑን ከማሳረፉ በፊት ከበረራ ደህንነት ተቆጣጣሪዎች  (Air Traffic controllers) ጋር ባደረገው የመልክት ልውውጥ ወቅት እንዲፈፀምለት የጠየቃቸው ሁለት ነገሮች ናቸው:: እነዚህም የስዊዘርላንድ መንግስት ጥገኝነት እንዲሰጠውና ለኢትዮጵያ መንግስት ተላልፎ እንደማይሰጥ ማረጋገጫ እንዲሰጠው የሚጠይቁ ነበሩ:: እንግዲህ ይህ ልጅ የአእምሮ ችግር አለበት ከተባለ ይህም የአእምሮ ችግር  ከአጎቱ ሞት ጋር የተያያዘ ነው ከተባለ አውሮፕላን መጥለፍን ምን አመጣው? ጥገኝነት መጠየቅስ ለምን አስፈለገ? እርሱ በውስጡ የያዘው ምስጢርና ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተያያዘ ስጋት ከሌለበት ለኢትዮጵያ መንግስት አሳልፋችሁ እንዳትሰጡኝ ማለትን ለምን መረጠ? እርስ በርሱ የተምታታ አንድምታ የሚሰጡት ወገኖች እነዚህን እና የመሳሰሉትን ሁሉ ጥያቄዎች መመለስ ይጠበቅባቸዋል::
ለማንኛውም ወጣቱ ረዳት አብራሪ ሀይለመድህን አበራ አውሮጵላን መጥለፍን ያህል ከባድ ድርጊት ውስጥ እንዲገባ ያስገደደውን ትክክለኛውንና የመጨረሻውን ምክንያት የምናረጋግጠው ከሱ ከራሱ አንደበት ስንሰማ ብቻ ነው:: አሁን ያለበት ሀገር ደግሞ ነፃ ሆኖ ሊናገር የሚያስችለው አጋጣሚ ስለሚፈጥርለት እውነታውን የምናውቅበት ግዜ እሩቅ አይሆንም::  እስከዚያ ድረስ ግን ስለልጁ አላማና ለዚህ ድርጊት ስለገፋፉት ምክንያቶች የሚሰነዘሩ ማናቸውም መላምቶች ተቀባይነታቸው ሊለካ የሚችለው ልጁ ራሱ ከፈፀመው ድርጊትና ከአንደበቱ ከተሰማው ቃል አንፃር እንጂ ከእኛ ፍላጎት ተነስተን መሆን የለበትም:: እንደኔ እንደኔ ግን ማንም የመሰለውን የማለት መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ የአእምሮ በሽተኛ ነው የሚለው ግምት እስካሁን ከታወቁት ጭብጦች ጋር ይጋጫል::
The writer can be reached at asefaabb@yahoo.com

No comments:

Post a Comment