Translate

Tuesday, February 25, 2014

ይድረስ ለፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ፡- በኢትዮጵያ ታሪክ ተወቃሾቹ የኦሮሞ ሕዝብና ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ብቻ ነውን እንዴ?!

በዲ/ን ኒቆዲሞስ ዕርቅ ይሁን  - nikodimos.wise7@gmail.com

‹‹ዕርቅና ሰላም የሕይወት ቅመም፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን እንደውለታ ቢስ ለሚቆጥሩ ወገኛ ሁሉ የሚሆን መልስ እነሆ!›› በሚል ርእስ የጻፉትን ጦማር እጅግ የማክበርዎና ኢትዮጵያዊው የምሆን ወንድምዎ ደጋግሜ አነብበኩት፡፡ ፕሮፌሰር በትክክል ተረድቼዎት ከሆነ እርስዎ በጽሑፍዎ ለማስተላለፍ የፈለጉት ዋንኛ መልእክትዎ፣ አንድም ‹‹ዕርቅንና ሰላም መስበክ›› ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ጠላት ወይም ውለታ ቢስ አድርገው ለሚቆጥሩ ወገኛ ሁሉ መልስ ይሆናል በሚል እነሆ ያሉት ጦማር እንደሆነ ነው፡፡
ፕሮፌሰር ለረጅም ዓመት ካካበቱት ዕውቀትዎ፣ በትምህርት ዓለም በሥራ፣ በምርምርና ጥናትዎ ከሕይወት ተሞክሮዎና ልምድዎ በመነሳትና እንዲሁም ዕድሜዎን ሙሉ ከመረመሯቸውና በአካዳሚያው ዓለም አንቱ ከተሰኙባቸው፣ ከበሬታን ካተረፉባቸውና ጥንታዊ የኾኑ መዛግብቶቻችንን በመመርመር እስካሁን ድረስ እያካፈሉን ስላለው ሰፊ የሆነ እውቀትዎ ከምስጋና ጋር ዝቅ ብዬ እጅ እነሳለሁ፡፡ ከገለታዬ አስከትዬ ግን በተለያዩ ድረ ገጾች ከሰሞኑን ባስነበቡን ጽሑፍዎ ማዘኔን ልገልጽልዎ እወዳለሁ፡፡

ይህ ጽሑፍዎ ከዕርቅና ሰላም ይልቅ ጠብንና ኹከትን፣ ከፍቅርና አንድነት ይልቅ መለያየትን የሚዘራ መስሎ ነው የታየኝ፡፡ መቼም ለእንደ እርስዎ ዓይነት ዘመኑን ሙሉ የኢትዮጵያን ጥንታዊ የሆኑ የሥነ ጽሑፍ ሀብቶች ሲመረምር ለነበረ ሊቅ/ምሁር ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን  ታሪከ ማስረዳት ‹‹ለቀባሪው አረዱት›› አሊያም ደግሞ ‹‹ልጅ ለአናቷ ምጥ አስተማረች›› እንዳይሆንብኝ እሠጋለሁ፡፡ ቢሆንም ግን ፕሮፌሰር በዚህ ጽሑፍዎ ለዕርቅና ሰላም ይሆናል ብለው ባቀረቧቸው መፍትሔዎች ዙሪያ ጥቂት ሙግቶችን እንዳቀርብልዎ አስገድዶኛል፡
በሙያዬ የታሪክ ተመራማሪ፣ የአርኮዮሊጂና የቅርስ ባለሙያ ነኝ፡፡ በመንፈሳዊ ሕይወት ረገድም ጥንታዊትና ሐዋርያዊት በምትሆን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ካሉ ሊቃውንት አባቶቼ እግር ስር ከማያልቀው ዕውቀት ምንጫቸው እጅግ በጥቂቱ ለመጥለቅ ሞክሬያለኹ፤ እስከ ሕይወት ፍጻሜዬም ከእነዚህ አባቶቼ የማያልቀውን ሰማያዊ ዕውቀታቸውንና ጥበባቸውን መጥለቄን እቀጥላለኹ ብዬ አስባለኹ፡፡ እናም ክቡር ፕሮፌሰር በአንዲት ቤ/ን ጥላ ስር መገኘታችንና ሁለታችንም የኢትዮጵያን ረጅም ዘመናት ታሪክ፣ የሕዝቦቿን ገናና ሥልጣኔ፣ መንፈሳዊና ቁሳዊ ቅርሶቿን ለመመርመር ምንተጋ ከመሆናችን የተነሣ በዚህ ጦማሬ ቋንቋ ለቋንቋ፣ አሳብ ለአሳብ እንግባባለን ብዬ እገምታለኹ፡፡
ፕሮፌሰር ‹‹ዕርቅና ሰላም ለሕይወት ቅመም›› ብለው የጻፉት ጽሑፍዎ እንደሚመስለኝ መነሻ ያደረገው ባለፈው ሰሞን በአሜሪካ ሚቺጋን ስቴት የሚኖረው ወጣቱ የፖለቲካ ተንታኝ ጀዋር መሐመድ፣ አንዳንድ በውጭ አገርና በኢትዮጵያ ያሉ የኦሮሞ ልሂቃንና የብሔረሰቡ ተወላጆች ዘንድ ዳግመኛ እንደ አዲስ በሰፊው መከራከሪያ ሆኖ በዘለቀው የኦሮሞ ታሪክ ትንታኔ፣ የሕዝቡ የነጻነት ጥያቄ፣ የኢትዮጵያ ቤ/ን ለአቢሲኒያ/ለነፍጠኛ ገዢዎች ቅኝ ግዛት ዘመቻ ዋንኛዋ አጋር ነበረች በሚሉትና በመሳሰሉት ታሪካዊና ፖለቲካዊ ትኩሳቶች ዙሪያ ሲንሸራሸሩ የነበሩና አሁንም ያሉ አሳቦች ይመስሉኛል፡፡
እርስዎም በዚህ ክርክር መነሻነት ተስበው ይመስለኛል ለዕርቅና ለሰላም መፍትሔ ይሆናል ባሉት ጽሑፍዎ የኦሮሞ ሕዝብ አውዳሚ፣ አረመኔና ጨካኝ እንደሆነ የነገሩን፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ሕዝብ ‹‹ጋዳ›› የሚለው ሥርዓት አንዳንዶች እንደሚሉት አፍሪካ በቀል የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ሣይሆን ሕግ አልባ፣ በጭፍን የሚጓዝ የማፊያዎች ጥርቅም እንደሆነም አስረግጠው ነገሩን፡፡ እነ ጃዋርና ተከታዮቻቸውም በሸሪያ ሕግ ሊገዙንና ሊዳኙን እያቆበቆቡ ያሉ ጠባብ ብሔርተኞች፣ የኢትዮጵዊነት/የአንድነት መንፈስ ነቀርሳና የሰይጣን መልእክተኛ ናቸው ሲሉም ፈረጇቸው፡፡
አስከትለውም የኦሮሞ ሕዝብና ኢትዮጵውያን ሙስሊሞችም አባቶቻቸው በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ቅርስና ሥልጣኔ ላይ ላደረሱት ውድመትና ጥፋት ይቅርታ መጠየቅ እንደሚገባቸው ለማሳሰብ ሞከሩ፡፡
ስለ ኦሮሞ ሕዝብ ጭካኔና አረመኔነትም ከአገር ውስጥ ካሉ ጸሐፊዎች እስከ ውጭ አገር የታሪክ ጸሐፊዎችና ተመራማሪዎች ድረስ የመሰከሩት ስለሆነ፣ ‹‹ጩኸቴን ቀሙኝ›› አሊያም ‹‹ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮኻል›› እንዲሉ ካልሆነ በስተቀር ኦሮሞዎች በኢትዮጵያና በክርስቲያኑ ሕዝብ ላይ ላደረሱት አሰቃቂ ግፍና በደል፣ እንዲሁም ወደ አንድነትና ኅብረት እንዲመጡ ላደረጓቸው ንጉሥ ምኒልክ በሀውልታቸው ስር የይቅርታ ጉንጉን አበባ በማኖር ዕርቀ ሰላም እንዲያወርዱና ለባለውለታቸው ለምድራቸው/ለአፈራቸው ልጅ ለጎበና ዳጬም ሀውልት እንዲያቆሙላቸው ምክርዎን ለግሰዋል፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸውን ያህል ታላቅ ምሁርና ላለፉት በርካታ ዓመታት የኢትዮጵያን ታሪክ የመረመሩ ሰው እንዴት የኦሮሞ ሕዝብንና ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ብቻ ነጥለው በአገሪቱ ላይ ለደረሰው ውድመትና ጥፋት ተወቃሽና ይቅርታ ጠያቂዎች እንዳደረጓቸው ሊገባኝ አልቻለም፡፡ መቼም ፕሮፌሰር ኢትዮጵያ በምትባል ግዛት ይኖሩ የነበሩ የተለያዩ ሕዝቦች በተለያዩ ዘመናት ባደረጉት ጦርነትና የግዛት ማስፋፋት ወረራ የየበኩላቸውን ጥፋትና ውድመት እንዳደረሱ ይስቱታል ብዬ አልገምትም፡፡
ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ታሪካችን ዘመን፣ በታሪክ ምሁራን ዘንድ ‹‹ዘመነ መሳፍንት›› ተብሎ በሚጠራው ዘመን በአማራነት ስም የሚጠሩ ገዢዎች፣ መሳፍንትና መኳንንት፣ የጎንደሩ በወሎ፣ የጎጃሙ በሸዋ፣ በትግራይ የእንደርታው፣ በአጋሜ፣ የአድዋው በአክሱም፣ በኦሮሞው ግዛትም የአርሲ፣ የባሌ፣ የሸዋና ወለጋ እያለ እርስ በርሱ እንዳልተላለቀና የአገሪቱን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ቀውሶች እንዳልዳረጉ ለምን የኦሮሞን ሕዝብ ብቻ ነጥለው ወራሪ፣ አውዳሚና ብቻ አድርገው እንደሳሉት በእጅጉ ግራ የሚያጋባ ብቻ ሳይሆን የሚያስተዛዝብም ጭምር ነው፡፡
ፕሮፌሰር በእንዲህ ዓይነት የአንድ ወገን ብቻ የታሪክ አተያይና ትንታኔና እንዲሁም ፍረጃ ዕርቅንና ሰላምን ማውረድ ይቻላል ብለው አስበው ከሆነ ይህንን ጽሑፍ እንካችሁ ያሉት ትክክል አይመስለኝም፡፡ በእኔ እሳቤ በአብዛኛው በአገራችን ታሪክ አንድን ብሔር ወይም ሕዝብ ሆን ብሎ ለማጥፋት ወይም ለመፍጀት የተደረጉ ዘመቻዎች ነበሩ ብዬ ለመውሰድ እቸገራለኹ፡፡ አብዛኛው የታሪካችን ገጽ የሚሳየን ገዢዎች ለሥልጣን፣ በገብርልኝ አልገብርህም ሰበብ የኢኮኖሚ ጥቅምንና የፖለቲካ የበላይነትን ለመውሰድ በነበረ ውድድርና ፍጥጫ በተደረጉ ጦርነቶችና ወረራዎች ብዙዎች ምስኪኖች አምነውበትም ሆነ ሳያምኑበት ጭዳ እንደሆኑ ነው የማስበው፡፡
በተመሳሳይም በአገራችን በአብዛኛው በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል ተደረጉ ጦርነቶች ውስጥም ቢሆን ሃይማኖት መሳሪያ ወይም ሽፋን እንጂ ሃይማኖትን ሰበብ አድርገው በተነሱ ተፋላሚዎች የተደረጉት ጦርነቶች ዋና ምክንያት አልነበረም፡፡ ሃይማኖት ሽፋን ነው፡፡ ጠቡና መሠረታዊው ቅራኔ የክርስትና እና የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑትን የኅብረተሰብ ክፍሎች እንመራሃለን ወይም እናስተዳድርሃለን በሚሉት ገዢ መደቦች የሚነሳ የሥልጣንና የኢኮኖሚ ጥቅም ጥያቄ ነበር፣ ነውም፡፡
እናም የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ ሂደት ውስጥ የኦሮሞ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያም ሆነ የዓለም ሕዝብ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በበጎም ሆነ በክፉ ጎኑ የሚነሳበት ታሪክ ያለው ሕዝብ እንደሆነ ነው የማምነው፡፡ ፕሮፌሰር የኦሮሞ ሕዝብን ብቻ ነጥለው አውዳሚና የጥፋት ልጅ እንደሆነ በጻፉበት ብዕራቸውና ለዚህም መከራከሪያቸው ከጠቀሷቸው የአገር ውስጥና የውጭ አገር ጸሐፍት መካከል ለምን እነዚሁ ጸሐፊዎች በአንጻሩ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ የደረሰውን በደልና ግፍ በተመለከተ የተዉትን ምስክርነታቸውን ለመጥቀስ/ለመጻፍ እንዳልደፈሩ ግን ግልጽ አይደለም፡፡
እስቲ ለአብነት ያህል አፅሜ ጊዮርጊስ የተባሉ ጸሐፊ ‹‹የኦሮሞ ታሪክ›› በሚል በተዉልን የታሪክ ማስታወሻቸው ዐፄ ምኒልክና ሠራዊታቸው በኦሮሚያና በደቡብ የአገራችን ክፍሎች ባደረጉት የማቅናት ዘመቻ ወቅት በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ስለደረሰው በደልና ግፍ የከተቡትን በጥቂቱ እንመልከት፡፡
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ኦሮሞ ሁሉ ተገዛ፣ በአማራ ሕግና ሥርዓት ሔደ፣ ካህናቱ አንድ ኦሮሞ አስተምረው አላጠመቁም፡፡ ይልቅስ ተፊተኛው ቂም የበለጠ ቂም በልቡ አኑረውበት መሬቱን በቀላድ ወሰዱበት፡፡ አንድ ቀላድ የቅስና አንድ ቀላድ የአወዳሽ እያሉ በዚሁ ስብከት ንጉሡን አሳመኑ፡፡ ስለ መንግሥት ያሰቡ መስለው ለንጉሡም አንድ ቀላድ፣ ለወታደር አንድ ቀላድ … መሬቱን ተካፍለው ኦሮሞን እንደ ባሪያ አድርገው ይገዙታል እንጂ የክርስቶስን መንገድ አላሳዩትም፡፡ እነርሱም የእግዝሔርን መንገድ በሚገባ አልተማሩም፣ አስተማሪም ቢመጣም ይከለክላሉ …፡፡
ፕሮፌሰር ጌታቸው የኦሮሞ ወራሪ ኃይል በአማራውና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤ/ን ላይ ያደረሰውን ግፍና በደል ዘርዝረው የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባዋል ባሉበት ብዕራቸው ለምን ይህንም የኦሮሞ ሕዝብን በደል ወይም የታሪካችንን ሌላውን ገጽ ቦታ አንዳልሰጡት፣ ሊያነሡት ወይም ሊነግሩን እንዳልደፈሩ ግልጽ አይደለም፡፡ ፕሮፌሰሩ መልእክቴ በኢትዮጵያ ምድር ዕርቅና ሰላም ለማውረድ ነው ካሉን ዘንድ ሚዛናዊ በመሆን አንዱን ብቻ ሳይሆን ሌላውንም የታሪካችንን ገጽ ሊያሳዩን በተገባቸው ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የአንድ ወገን ብቻ የሆነ የታሪክ ትንታኔና ዕይታ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ወዴየትኛው የጥፋት መንገድ ይዞን እንደነጎደ በተግባርም ጭምር ዐይተነዋል፡፡
በሌላም በኩል እስቲ እስካሁንም ድረስ ሳስበው ግርም የሚለኝን ከዚሁ ካነሳሁት ርእሰ ጉዳይ ጋር የሚያያዝ አንድ ገጠመኜን እዚህ ላይ ጨምሬ ለማንሳት እወዳለኹ፡፡ ታሪኩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪ በነበርንበት ሰዓት የኾነ ነው፡፡ በዩኒቨርስቲው ካሉ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ዘንድ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ጥላ ስር አብረን ያለን ጓደኛዬ በአንድ ወቅት ‹‹ራእይ ማርያም›› ከሚል የጸሎት መጽሐፍ ኮፒ የተደረገ ጽሑፍ ከአንድ ከሌላ ኦሮሞ ብሔር ተወላጅ ጓደኛው ጋር ይዞ በመምጣት እንዲህ አለኝ፡፡
‹‹ይቅርታ፣ ከልቤ አዝናለሁ … በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በጌታችንና በመድኃኒታችን ክቡር ደም ፈሳሽነት/ቤዛነት ሁላችንም በአንድ መንፈስ፣ ሰማያዊ ዜጋ ሆነን የእግዚአብሔርን መንግሥት እንወርሳለን ብላ በምታስተምር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሕዝቦችን የሚለያይና የሚከፋፍል መጽሐፍ መኖሩን እስከዛሬ አላውቅም ነበር፡፡›› በጓደኛዬ ንግግር ውስጥ እልክና ብርቱ የሆነ አንዳንች የቁጭት መንፈስ ነበር የሚነበብበት፡፡ ‹‹… ለመሆኑ ይህን መጽሐፍ አይተኸው ወይም አንብበኸው ታውቃለህ በማለት ‹‹የራእይ ማርያም›› መጽሐፍን አንድ ገጽ ኮፒ እንዳነበው በእጄ ሰጠኝ፡፡ እንዲህ ይላል፡-
… ከስር እስከ ጫፍ፣ ከጫፍ እስከ ስር ድረስ በአምስት ሺሕ ዓመት የማይደረስበት ትልቅ ገደል አሳየኝ፡፡ ያንዱ ነፍስ በአንዱ ላይ ሲወድቅ ዐየኹ፡፡ እኔም ምንድናቸው ብዬ ልጄን (ለስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ኢየሱስን መኾኑን ልብ ይሏል) ጠየቅኹት፡፡ እርሱም እንዲህ ሲል መለሰላት፡- … አራስ፣ መርገም፣ ደንቆሮ፣ ‹‹እስላም››፣ ‹‹ጋላ››፣ ‹‹ሻንቅላ››፣ ‹‹ፈላሻ›› ጋር የተኙ፣ ፈረስ፣ አህያ፣ ግመል በግብረ ስጋ የሚገናኙ፣ ወንዱም ግብረ ሰዶም ወገሞራ የሚዳረጉ… እነዚህ ሁሉ ኩነኔያቸው ይህ ነው አለኝ …፡፡
በጊዜው ይህን ጉድ ካነበብኩ በኋላ እንዲህ ዓይነቱን ክፋትና እርግማን የሞላበት መጽሐፍ ቤተ ክርስቲያኒቱንና እውነተኞቹን የወንጌል መምህራን የሆኑትን አባቶቻችንን እንደማይወክል ባውቅም ይህ የጸሎት መጽሐፍ ተብዬ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ታትሟልና በጊዜው የመከራከሪያ አሳብም ሆነ የምሰጠው ምላሽ አልነበረኝም፡፡ ግና ስለ ስለዚሁ የጸሎት መጽሐፍ የኩነኔ ፍርድ ጥቂት ነገሮችን ለማለት ያህል፤ መቼም ሌላ ስምና መልክ እስካልተሰጠው ድረስ በመንፈሳዊው ዓለም አስተምህሮ/ሕግ ካልተፈቀደልንና የእኛ ከሆነችው ሴትም ኾነ ወንድ ውጭ መሔድ ዝሙት ነው፡፡
‹‹ከጋላ›› ወይም ‹‹ከሻንቅላ›› ‹‹ከእስላም›› ወይም ‹‹ከፈላሻ›› ጋር ስለተኛን ወይም ስለዘሞትን የተለየ ነገር ሊሆንም ሊደርስም አይችልም፣ በአምስት ሺሕ ዘመንን በሚያስኬድ ገደል ውስጥም ልንጣልም አንችልም፡፡ ደግሞስ ምን ዓይነት ሕሊና ያለው ሰው ነው ሰውንና እንሰሳን በእኩል ሚዛን አስቀምጦ ፈረስም ተገናኘህ ‹‹ሻንቅላ›› ወይም ‹‹ፈላሻ›› ምንም ልዩነት የለውም ያው ነው በሚል የሚጽፍ፡፡
አንድን ጎሳና ብሔር ለይቶ ከእነርሱ ጋር ከተኛህ እንዲህ ዓይነት ቅጣት ይደርስብሃል/ያገኝሃል ብሎ እንዲህ ዓይነቱን መርገምን፣ ጥላቻንና ክፋትን የተሸከመ ድርሳን ቅድስት፣ ንፅሕትና ርትዕት በኾነች በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም አሳትሞ በማቅረብ፣ ‹‹ፈላሻነቱንም›› ኾነ ‹‹ሻንቅላነቱን›› ወዶና ፈቅዶ ባላመጣው ሰው ሕሊና ውስጥ የጥላቻ መርዝ እንዲረጭና ልቦናው ክፉኛ እንዲቆስል ምክንያት ኾኗል፡፡
ይህ ትናንትና እንደ ዘበትና ቀልድ ያየነውና በጊዜው በይቅርታ መፍትሔ ያላበጀንለት ነገር ይኸው ዛሬ ከታሪካችን ማኅደር እየተመዠረጠ የብዙዎችን ቁስል እያመረቀዘ ቤተ ክርስቲያኒቱንም ኾነ ተከታዮቿን በጥላቻ ዓይን እንዲታዩ ምክንያት ከኾነ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ እነዚህና ሌሎች መሰል ታሪኮችን ዕድሉ ያጋጠመን ሁሉ ደጋግመን ሰምተናቸዋል፡፡ መፍትሔው ምን ይሁን፣ ምን መላ እንፍጠር ከማለት ይልቅ ያለፈ ታሪክን ማንሳት ምን ይጠቅማል በሚል በማድበስበስ የተውናቸው ክስተቶች እያመረቀዙ በመካከላችን መፈራራትንና ጥላቻን አነገሡብን/አባባሱብን እንጂ መፍትሔ አልሆኑንም፡፡
ብዙዎቻችንን እያከራከረን ስላለው የትናንትና ታሪካችን ርእሰ ጉዳይ ስንመለስም አንድ ማስተዋል ያለብን ነገር ያለ ይመስለኛል፤ ይኸውም አብዛኛው የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ በጦርነትና በወረራ፣ በገብር አልገብርም፣ በልግዛህ አልገዛም በተደረገ ግብግብና ጭፍጨፋ በደም የቀላ ታሪክ ነው ያለን መሆኑን፡፡
አንዱ የገዢ መደብ ሌላውን፣ ክርስቲያኑ ሙስሊሙን፣ ሙስሊሙ ክርስቲያኑን ያጠቃበት የጨፈጨፈበት በርካታ ዘመናቶች የታሪካችን አካል ኾነው አብረውን አሉ፡፡ አንዱ አገር የሌላውን አገር በጦርነት በመግጠም ሀብት ንብረቱን በመዝረፍ፣ መሬቱን በመቀማት፣ በምርኮና በባርነት በማጋዝ ያሳለፍናቸው የታሪካችን ቁስሎች በፍቅር ዘይት ለስልሰውና በዕርቀ ሰላም ፈውስ አግኝተው መፍትሔ ካላገኘን አንድ ብሔርን/ሕዝብን ወይም ሃይማኖትን ብቻ ነጥሎ እንደ ጥፋተኛና አውዳሚ አድርጎ ማቅረብ ወደምንናፍቀው የዕርቅና የሰላም ምንገድ ያመጣናል ብዬ አላስብም፡፡
ደግሞስ አማራው ከኦሮሞው፣ ኦሮሞው ከትግሬ፣ ወላይታው፣ ከጉራጌው፣ ሐረሪው፣ ከአፋር በደም፣ በአጥንት በተዛመደ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖትና በጋራ ታሪክ  በተሳሰረ ሕዝብ መካከል ብሔርና ጎሳ ለይይቶ መወቃቀሱ ጥቅሙ ምንድን ነው፡፡ ትርፉስ ለማን ነው?! በእርግጥም ለእውነተኛው ዕርቀ ሰላም ቀናውን መንገድ ካላመቻቸን ላለፉት ሃያ ዓመታት ታሪክንና ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው እየተካሔዱ ያሉ የቂም በቀል ዘመቻዎች ፍፃሜያቸው እጅግ አስፈሪና አሳፋሪ እንደኾኑ ነው የታዘብነው፡፡
በሃይማኖትና በብሔርተኝነት ስም በአዲስ አበባና በሌሎች ክልል ከተሞች ቦግ እልም እያለ ያለውና ተዳፈኖ ያለው የረመጥ እሳት ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ ከወዲሁ መፍትሔ ካላበጀንለት (ያው እስከ ዛሬ ድረስ በአርባ ጉጉ፣ በበደኖ፣ በአርሲ ነገሌ፣ በወተር፣ በቤሻንጉል ጉሙዝ፣ በጅማ … የደረሰው አሰቃቂ እልቂት፣ ጥፋትና ውድመት ሳይዘነጋ) ይህ ዓለም ሁሉ የሚያደንቀውና የምንኮራበት፣ በቋፍ ያለው ለዘመናት አብረን በፍቅርና በወዳጅነት የቆየንበት አኩሪ ታሪካችን በነበር ልናወሳ የምንገደድባቸው ጊዜያቶች ሩቅ ሊኾኑ እንደማይችሉ በርካታ ማሳያዎችን መጥቀስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡
ያለፈው ሰሞን የእነ ጃዋር መሐመድና የኦሮሞ ወንድሞቻችን ኦሮሞነትን ከኢትዮጵያዊነት ነጥለው ያቀረቡበት ትርክትና የትናንትና ክፉ የታሪክ ጠባሳችን፣ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ላይ ያላቸውና እያንጸባረቁት ያለው ቁጣ፣ ቅያሜና ዛቻ የነገይቱ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱስ ዕጣ ፈንታ ምን ሊሆን ይችላል ብለን እንድንጠይቅ፣ እንድንሰጋ ያስገድደናል ብዬ ለማለት እደፍራለኹ፡፡
አገሪቱን እያሥተዳደረ ያለው መንግሥትም ለጉዳዩ መፍትሔ ከመስጠት ይልቅ ያለ ቅጥ ያራገበው የብሔር ፖለቲካ ወላፈኑ እራሱንም ጭምር እየለበለበው እንደሆነ እያየን ነው፡፡ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› በሚል ግትርነትና ዕድሜዬን ያራዝምልኛል በሚል እንዲሁ በአገም ጠቀም የተወው የጎሰኝነት/የዘረኝነት ጉዳይ ነገ መዘዙ ከየት እስከ የት ሊመዘዝ እንደሚችል መገመት የሚያዳግት አይመስለኝም፡፡ ትናንትና በሆነው በሚያኮራው ታሪካችን ተከባብረንና ተዋደን፣ አሳፋሪና ክፉ ጠባሳ የተዉብንን የታሪካችንን ምዕራፍ ደግሞ በይቅርታ ዘግተን በፍቅርና በመቀባበል መኖር ካልተቻለን የሚጠብቀን ዕድል ጥላቻ፣ መከፋፋት፣ ጠላትነት፣ መለያየት … ብቻ ነው ሚሆነው፡፡
ይህ እንዳይሆንብን፣ ይህ ክፉ ነገር እንዳይደርስብን ቆም ብለን ማሰብ ያለብን ጊዜ ላይ ያለን ይመስለኛል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር ጌታቸው ያሉ የዕድሜ ባለፀጋዎችና ምሁራን፣ የታሪክ ተመራማሪ ምሁራኖቻችንና የፖለቲካ መሪዎችም ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ወደ ፍቅር፣ ሰላምና አንድነት የሚመጡበትን ቀና የሆነ መንገድ በማመቻቸት አገሪቷን ከተደቀነባትና ካዣንበባት ጥፋት ሊታደጓት የትውልዱንም ልብ በፍቅር ዘይት አልስልሰው ለይቅርታ/ለዕርቀ ሰላም ሊያዘጋጁት ጊዜው አሁን ይመስለኛል፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ የሃይማኖት አባቶችና መሪዎች ከእኔ ይበልጥ ከእኔ ይበልጥ የፉክክር መንፈስ ወጥተው ለአገርና ለሕዝብ የሚሆን የዕርቀ ሰላም መልእክት ይዘውልን ሊመጡ ይገባቸዋል፡፡
ነገሥታትን/መንግሥታትንና ክፉ መሪዎችን በመገሠጽ፣ በሕዝቦች መካከል ፍቅርንና ሰላምን፣ በአገራችንም ብሔራዊ ዕርቅን በማስፈን ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውንና መንፈሳዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ጊዜው አሁን ነው፡፡ አሊያ ግን ዕርቅንና ሰላምን ያወርዳሉ ያልናቸው አባቶቻችንም እርስ በርሳቸው ተለያይተውና ተወጋግዘው፣ ለነገ ህልውናችን በሚል ሰበብ የፖለቲከኞችን ጉያ የሚመርጡ ከሆኑ፣ ከእውነትና ከፍትሕ ጎን ለመቆም መንፈሳዊ ድፍረትና ወኔ ከተለያቸው እንዴት ባለ መንገድ ነው ፍቅርንና ዕርቅን ሰብከው አገሪቱንም ሆነ ትውልዱን ከጥፋትና ከሞት መንገድ ሊታደጉት የሚችሉት?!
በታሪካችን ለኾኑት ስህተቶች በግልፅ ይቅርታ ተጠያይቀን ዕርቅ ማውድ ካልቻልን አስቸጋሪ ነው፡፡ የሚሻለው መነጋገርና መግባባት ነው፡፡ እንደ እውነቱም ከኾነ ትናንትና ለኾነው በደል እውቅና መስጠት ሳይቻል ዕርቅ ዕርቅ የሚለው ነገር ከጉንጭ አልፋ ወሬነት የሚያልፍ ፋይዳ ይኖረዋል ብዬ አላስብም፡፡ ዛሬ እንደገና ከበርካታ ዓመታትም በኋላ ተመልሶ እነ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ እነ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የምኒልክ ጦር በአያቶቻችን ላይ ያደረሰውን በደል አንረሳውም ወደሚል አዙሪት መልሶ እየከተታቸው ያለው ይኸው በይቅርታ ያልተወራረደው ታሪካችን ጥሎብን የሔደው ክፉ አበሳና ጠባሳ ይመስለኛል፡፡
እናም እንደ ፕ/ር ጌታቸው ያሉ ምሁራንና የዕድሜ ባለጠጋዎች የአንድ ወገን ታሪክን ብቻ በማጉላት ሳይሆን ሚዛናዊነት ባለው መልኩ ታሪካችንን በማቅረብ የሁላችንም የጋራ ቤታችን በሆነች ኢትዮጵያችን ተስማምተን፣ ተዋደን፣ ተፋቀርንና ተከባብረን የምንኖርባት አገር እንድትኖረን የታላቁን የሰላምና የይቅርታ አባት የኔልሰን ማንዴላን ዓይነት ሚና በመጫወት የትውልድ ባለውለታ ይሆኑ ዘንድ በእኔና በትውልዴ ስም አደራ እላለሁ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ!!

No comments:

Post a Comment